60. አንድነት አማረ አስረሱ - ANDINET AMARE
ASERESU
ኢትዮጲስ እና . አንድነት ልጆች ላይ መስራት-ትውልድን መገንባት
ከ20 አመታት በዘለቀ
የጋዜጠኝነት ሙያ የበርካታ ህጻናትን ቤት አንኳኩታለች፡፡ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትንም በፍቅር ገዝታለች ፡፡ የህፃናት ድምፅ በመሆን
ብዙዎችን አነጋግራለች፡፡ ዛሬም ህይወቷ ከልጆች ጋር የተቆራኘ ነው፡፡ እጅግ የምትወደውን ስራ እየሰራች በመሆኑ ሁሌም አምላኳን
ታመሰግነዋለች ፡፡ በኢቢኤስ ቴሌቪዠን የሚተላለፈው ኢትዮጲስ እንዲሁም
በቅርቡ በዲኤስ ቲቪ አቦል ላይ መተላለፍ የጀመረው ‹‹ቲቲሎ.››
የተሰኙ የልጆች ፕሮግራም ባለቤት እና የፕሮግራሙ ዋና አዘጋጅ ናት፡፡ አንድነት አማረ፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ልክ አንድነት አይነት በጎ አሻራ ለሀገር ያኖሩ ሰዎችን ታሪክ ስለሚፈልግ ብትጠቁሙን ደስ ይለናል፡፡ tewedajemedia@gmail መገኛችን ነው፡፡ ለመሆኑ የዛሬዋ ባለታሪክ አንድነት አማረ ማናት?
ትውልድና እድገት
በአዲስ አበባ ልደታ
በሚባለው ሰፈር ሀምሌ 19 ቀን 1971 ዓ.ም ከአባቷ ኢንጂነር አማረ አስረሱ ከእናቷ ወ/ሮ ሙሉ አርአያ ተወለደች፡፡ አባቷን በልጅነት እድሜዋ በማጣቷ
ምክንያት ልጆችን የማሳደግ እጣ ፈንታ በእናቷ ላይ ወደቀ። ጥንካሬን እና የውሳኔ ሰው መሆንን ከእናቷ ተምራለች። ተውልዳ ባደገችበት
አካባቢ የመዋእለ -ህፃናት ትምህርቷን በልደታ መካነ- ኢየሱስ ፊደል እና ኤ ቢሲ ዲን ቆጠረች ፡፡ ከ አንድ እስከ ስድስተኛ ክፍል
በአብዲሳ አጋ ትምህርት ቤት ሰባትን ተስፋ ኮከብ ስምንትን ጆኔፍ ኬኔዲ
ተምራለች ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በሽመልስ ሃብቴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ ተከታትላለች ፡፡ የመጀመሪያ
ዲግሪዋንም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጲያ ቋንዎች እና ስነ-ፅሁፍ
በማታው ክፍለ- ጊዜ ተምራ በመጨረስ ተመርቃለች፡፡
የስነ-ፅሁፍ ዝንባሌ
የስነ-ፅሁፍ ዝንባሌ
የነበራት ከልጅነቷ ጀምሮ ነው፡፡ በተለይ የስድስተኛ ክፍል ተማሪ እያለች ካነበበቻቸው መፅሃፍቶች ላይ ፅፋ ይዛ በመሄድ ለተማሪዎች
ሰልፍ ላይ ታቀርብላቸው ነበር፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በምትማርበት ትምህርት ቤት ውስጥ ንቁ የሚኒ ሚዲያ ተሳታፊም ነበረች
፡፡ በተለይ ተረቶችና አስደናቂ ታሪኮች ስለሚመስጧት በ ቤተ መፅሃፍትና ቤተ- መዛግብት /ወመዘክር / በመገኘት መፅሀፍትን ታነብ
ነበር ፡፡ በጳውሎስ ኞኞ አማተር የጋዜጠኞች ማህበር ወስጥ አባል በመሆንም የስነ-ፅሁፍ ፍቅርና ዝንባሌዋን ለማሳደግ ጥረት አድርጋለች ፡፡
የጋዜጠኝነት ህይወት
ኢትዮጵያ ሬድዮና ቴሌቪዥን
በኢትዮጵያ ሬድዮ በከልጆች
አለም ፕሮግራም ላይ ለልጆች የሚሆኑ ፕሮግራሞች እንዲሁም ድራማዎችን በመስራት ትሳተፍ ነበር፡፡ በጊዜው እትዬ ቅድስት ተስፋዬ አስካል
ተስፋዬ የመሰሉ ታላላቅ ሰዎች ነበሩ፡፡ አንድነት እና የእድሜ እኩዮቿ
በልጆች ፕሮግራም ላይ ይሳተፉ ነበር፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በማታው ክፍለጊዜ በመመዝገብ በኢትዮጲያ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ
የመጀመሪያ ዲግሪዋን መማር ጀመረች ፡፡ በዚህ መሃል የኢትዮጲያ ቴሌቪዥን
የልጆች ፕሮግራም ላይ ባወጣው ክፍት የስራ ቦታ በመወዳደር ከአባባ ተስፋዬ ጋር መስራት ጀመረች ፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዠን ቆይታዋም
የተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ለልጆች የሚመጥኑ ፕሮግራሞችን በመስራት ሙያዊ ግዴታዋን ተወጥታለች ፡፡
ፊልሞችን በመተርጎም
የተለያዩ አዝናኝና አስተማሪ ፕሮግራሞችን ሰርታለች፡ ፡ በኢትዮጲያ ቴሌቪዥን ቆይታዋም ‹‹ሳይንስና አካባቢ›› እንዲሁም በዜና ክፍል ፕሮግራም በመስራትና ዜናዎችን
በመዘገብ ለ 5 አመታት አገልግላለች ፡፡ በቴሌቪዥን ቆይታዋም በልጆች ፕሮግራም ላይ በወቅቱ ተወዳጅ በነበረችው ‹‹ቼሪ.›› ስም ከኮሜዲያን አስረስ በቀለ ጋር በመተባበር የመጀመሪያዋን የተረት መፅሃፍ
ፅፋ አሳትማለች፡፡ ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ከወጣች በኋላም በግሏ ለመስራት
ብዙ ጥረት አድርጋለች፡፡ ሁለት ፖፔቶችን በማሰራት ከቀድሞ የስራ ባልደረባዋ ራሄል አሰፋ (ማሾ)
ጋር የልጆቸ ፕሮግራሞችን ለማዘጋጀት እቅዶችን ያወጡ እንዲሁም ልምምዶችን ያደርጉ ነበር ፡፡ በመሃሉ ራሄል ወደ ውጭ
ሃገር በመሄዷ ምክንያት ብቻዋን መስራት ትጀምራለች ፡፡ አንዷን ፓፔት ባለቤቷ ሃብታሙ ቦጋለ ፣ ‹‹ኢትዮጲስ›› ብሎ ስያሜ አውጥቶላት ወደ ስራ ገባች፡፡ ታላቁ ሩጫ በሚያዘጋጀው የልጆች
የሩጫ ውድድር በመገኘት ለልጆች አዝናኝ መሰናዶ አቅርባለች ፡፡ በእሸት
የህጻናት እና ወጣቶች ማህበር በመገኘት ቅዳሜ ቅዳሜ በእረፍት ጊዜያቸው ለልጆች አስተማሪ ተረቶችን ፕሮግራሞችን ታቀርብ ነበር ፡፡
በወቅቱ ይህን እድል የፈጠረላትን እና የድርጅቱ ስራ አስኪያጅ የነበረውን ጓደኛዋን ዳዊት ንጉሡን ማመስገን ትፈልጋለች ።
በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ሴንተር ፎር ኮሚኒኬሽን
በጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ
ሴንተር ፎር ኮሚኒኬሽን ፕሮግራም (ጄ.ኤች.ዩ ሲሲፒ) ውስጥ ተቀጥራ ‹‹ቤተኛ›› የተሰኘ የሬዲዮ ፕሮግራም ታዘጋጅ ነበር ፡፡ በዚህም
ሃዋሳ ድረስ በመሄድ ከቫይረሱ ጋር አብረው የሚኖሩ ባለታሪኮችን አነጋግራለች ፡፡ ለቫይረሱ የተጋለጡባቸውን ምክንያቶች በዝርዝር እንዲነግሯት በማድረግም ለአድማጮች
አቅርባለች ፡፡ በዚህ የሬዲዮ ፕሮግራም በተለይ ህጻናት ሴቶች ላይ
የሚፈጠረውን ከፍተኛ ተጽዕኖ ለመቀነስ የማስተማሪያና ግንዛቤ ማስጨበጫ
ፕሮግራሞችን ሰርታለች፡፡ በድርጅቱም ለአራት አመታት ያህል ቆይታ አድርጋለች፡፡
አማራጭ ሚዲያ እና ኢንተርቴይመንት
ከድሮ ጀምሮ ህልሟ ልጆች
የሚወዱትና የሚማሩበት ፕሮግራም መስራት ነበር ፡፡ ኢ.ቢ.ኤስ ቴሌቪዥን
ኢትዮጵያ ውስጥ ሲጀምር የድርጅቱን ስራ አስኪያጅ አቶ አማን አምደፂዮንን በአካል በማግኘት የልጆች ፕሮግራም የመስራት ፍላጎቷን በማስረዳት
ፍቃድ ታገኛለች፡፡ ከስራ ባልደረባዋ እና የስዕል ባለሞያ ከሆነው ሳምሶን መረሳ ጋር በመሆን አማራጭ ሚዲያና ኢንተርቴይመንት
ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅትን አቋቁማ ስራ ጀመረች። በኢትዮጲያ ብሮድካስት ህግ በልጆች ፕሮግራም ላይ ምንም አይነት ማስታወቂያ
ማስተላለፍ አይቻልም ፡፡ ይህ ደግሞ ፕሮግራሙ ምንም አይነት ገቢ
ማምጣት የማይችል በመሆኑ ብዙ ፈተናዎችን ያለፈች ቢሆንም የኢቢኤስ ቴሌቪዥን ስርጭት ከጀመረበት ጊዜ ጀምሮ አንድም ቀን ሳይቋረጥ ልጆች ከለጋ እድሜያቸው ጀምሮ ሃገራቸውን ባህላቸውንና ማንነታቸውን
ሳይለቁ እንዲያድጉ ታላቅ አስተዋጽኦ አበርክታለች፡፡
ኢትዮጲስ በኢቢኤስ ቴሌቪዥን
ለ 11 አመታት ሳይቋረጥ ቅዳሜና በድጋሚ እሮብ እየተላለፈ የሚገኝ ፕሮግራም ነው፡፡ ባቋቋመችው ድርጅት ውስጥ አስራ ሶስት ቋሚ
ሰራተኞች ተቀጥረው እንዲሰሩ እድሉን ከፍታለች። ገቢ ለማግኘትም ልደቶችን ታከብራለች። በእምቢልታ ሲኒማ የልጆች ቲያትር፣ ሰርከስ
፣ተረቶች እና የተለያዩ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት በየሳምንቱ እሁድ እንዲቀርብ
አድርጋለች። በዚህም ከሃያ በላይ ሰራተኞች በጊዜያዊነት እንዲሰሩ እድሉን ፈጥራለች። በዚህ አጋጣሚ መናገር የምትፈልገው ጥሪ ባደረጉላት
የመንግስት ትምህርት ቤቶች በመገኘትከትምህርት ቤቱም ሆነ ከተማሪዎች ምንም አይነት ክፍያ ሳትጠይቅ ወጪዎችን በማውጣት የመዝናኛ እና የማስተማሪያ ፕሮግራሞችን በማቅረብ ማህበራዊ ግዴታዋን
እየተወጣች ትገኛለች ። የገንዘብ አቅም ለሌላቸው ቤተሰቦችም ልደት በነፃ አክብራለች። ኢትዮጲስ ፕሮግራም እስካሁን
የቆየው በኢ.ቢ.ኤስ ድጋፍ በመሆኑ የኢቢኤስ ሰራተኞች እና ማኔጅመንቱን
ማመስገን ትፈልጋለች ፡፡ የእነርሱ ቅንነት እና ትብብር ባይታከልበት ኖሮ ፕሮግራሙ ይህን ያህል ጊዜ መቆየት አይችልም ነበር ብላ
ታምናለች፡፡
በተጨማሪ ፣ በቅርቡ
በዲኤስ ቲቪ አቦል ቻናል ላይ በተሻለ ጥራት ፣‹‹ቲቲሎ.›› የተሰኘ
የልጆች ፕሮግራም ማሰራጨት ጀምራለች፡፡ ይህ ፕሮግራም 25 ደቂቃ ፍጆታ ያለው ነው፡፡ ‹‹ቲቲሎ›› የተባለችው ፓፔት የህጻን ባህሪይ
የተላበሰች ስትሆን የኢትዮጲስ ጓደኛ ነች፡፡ በዲኤስ ቲቪ አቦል ላይ ቲቲሎ የልጆች ፕሮግራም ልጆች በነጻነት ሃሳባቸውን እንዲገልጹ የሚረዳቸው የሚዝናኑበት ፕሮግራም
ነው፡፡ ዲኤስ ቲቪ የዚህን ፕሮግራም የአየር ሰዓት ክፍያውን በመሸፈኑ
ምክንያት ፕሮግራሙ በተሻለ ጥራትና ይዘት በመተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡
በተጨማሪ ተዝቆ ከማያልቀው
ስነ-ቃላችን ላይ ጨልፋ 3 የህጻናት ተረቶችን አሳትማለች ፡፡ በሃገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በሚባል ደረጃ በሃብታሙ ቦጋለ ተደርሶ
በረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ የተዘጋጀውን ‹‹ጠቢቡ ቡቻቻ.›› እና
የኢትዮጲስ እንቆቅልሾች የተሰኘ መልቲ ሚዲያ ቲያትር ተዘጋጅቶ ለህዝብ እንዲቀርብ ግንባር ቀደም ሚና ተጫውታለች፡፡
በሁሉም የሃገሪቱ ክፍሎች
በመሄድ ከ50 በላይ የንባብ ፌስቲቫሎችን በማዘጋጀት ህጻናትን በማዝናናት እንዲያነቡ ቅስቀሳ አድርጋለች። በዚህ አጋጣሚ በዚህ ጉዳይ
አብሯት በመስራት ላይ ያለውን ይትባረክ ዋለልኝን (ባቢሽን) ማመስገን
ትፈልጋለች ።ከሀገር ውጪም በዱባይ በመገኘት በዱባይ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ቤተሰቦች እና ልጆች ጋር በዓልን አክብራለች ፡፡ በቅርቡ
የአመቱ የሂሳብ ሰው ማነው? በሚል የውድድር ፕሮግራም ጀምራለች፡፡ ተማሪዎች በሂሳብ ትምህርት የተሻለ ውጤት እንዲያመጡ የሚያግዝ
ፕሮግራም ሲሆን ለውጡንም በግልፅ በማሳየት ወላጆች ምስክርነት ሰጥተዋታል ፡፡
በኮቪዱ ምክንያት ስራዎችን
እንደልብ ተንቀሳቅሶ ማዘጋጀት ከባድ በሆነበት ጊዜ ፕሮግራሙ እንዳይቋረጥ ከፍተኛ ትግል በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡ ለዚህም የስራ
ባደረባዋ እና በስራ አስኪያጅነት በማገልገል ላይ ያለውን ሳምሶን መረሳ እንዲሁም የትዳር አጋሯ ሃብታሙ ቦጋለ ከጀርባዋ ሆነው ከፍተኛ
አስተዋጽኦ በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም አጋጣሚ የድርጅቷን ሰራተኞች በቂ ክፍያ ሳይከፈላቸው በደስታ የሚሰሩትን ፣ ወላጆች
እና የስራ አጋሮቿ የሆኑት ወንድም እና እህቷን ጓደኞቿን ጨምሮ ቤተሰቦቿን ሁሉ ሁሌም አጠገቧ ሆነው ለስራው መቀጠል የበኩላቸውን
አስተዋጽኦ እያደረጉ ስለሆነ ማመስገን ትፈልጋለች፡፡
የቤተሰብ ሁኔታ
የትዳር አጋሯ የግጥምና ዜማ ደራሲ ሃብታሙ ቦጋለ ነው፡፡ ጋዜጠኛና የስነልቦና ባለሞያ በመሆኑ
ከጎኗ ሆኖ የልጆች ሙዚቃዎችን በማዘጋጀት ሃሳቦችን በመስጠት እና ልዩ አማካሪ በመሆን ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያደረገ ይገኛል፡፡ ህይወትን
ቀለል አድርጎ የሚመለከት ተጫዋች እና ቀልደኛ ባል አምላኳ ስላደላት
ደስተኛ ናት። በትዳር 17 አመታትን ያሳለፉ ሲሆን የአራት አመት ወንድ ልጅም አላቸው ፡፡
የእውቅና ሸልማቶች እና የምስክር ወረቀቶች
ኢትዮጲስን የሚወዷት የተለያዩ የመንግስት ትምህርት ቤቶች ለልጆቹ አዝናኝና
አስተማሪ ዝግጅቶችን በማቅረብ የተለያዩ የምስክር ወረቀቶችን ተቀብላለች፡፡ ለኢትዮጵያ ህጻናት በሚለው ዘርፍ ላበረከተችው አስተዋጽኦ
ካገኘቻቸው ሽልማቶች ውስጥም በተባበሩት መንግስታት ‹‹ መሪ መሆን እችላሁ›› በሚል ባዘጋጀው የሴቶች የሩጫ ውድድር ላይ ‹‹ የእኔ አርአያ›› በ2009 ‹‹ my icon women›› በሚል የክብር ስም ተሰጥቷቸው በሩጫው ላይ የተሳተፈችበት አንዱ ነው፡፡ በ
2010 ደግሞ የአመቱ በጎ ሰው በሚል የእውቅና ሽልማት ላይ ለሃገር ለወገን በጎ በማሰብ ትውልድ ላይ የሰሩ ግለሰቦች በሚል እጩ ተሸላሚ ሆና በመቅረብ እውቅና ተሰጥቷታል፡፡
ማጠቃለያ: አንድነት አማረ በልጆች ሚድያ ላይ ከ20 አመት በላይ ስትቆይ ታላቅ
ርካታ ይሰማታል፡፡ አንድነት ፈታኝ በሆነው የልጆች ስነ-ጽሁፍ እና
ሚድያ ላይ ስትሰራ ፈተናዎች ተደራርበው ቢመጡባትም ያለመችውን ከማሳካት ወደኋላ አላለችም፡፡ የዛሬ አበባዎች የነገ ፍሬዎች የነገይቱን ኢትዮጵያ የሚረከቡ ስለሆኑ ልጆች
ላይ መስራት መሰረታዊ መሆኑን ስለምታምን ያለ እረፍት ልጆች ላይ አሻራዋን እያሳረፈች ትገኛለች፡፡ ነገ የምናገኛትን ኢትዮጵያን ጠብቀው የሚያኖሯት የዛሬ ልጆች ናቸው ብላ የምታምነው
አንድነት ዛሬ ልጆችን በበጎ ምግባር አንጾ ማሳደጉ ላይ በርትታለች፡፡ ይህ ጥንካሬዋ ደግሞ በየጊዜው እያደገ ፍሬ እያፈራ ስለመጣ
ኢትዮጵያም አንድነትን በበጎ ስራዋ ታነሳታለች፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አሰናጆች ለሀገር አንድ አሻራ ያስቀመጡ ሰዎችን ስንሰንድ ልክ እንደ አንድነት ብዙ ለፍተው እንዲገኙ እንፈልጋለን፡፡ አንድነት ዛሬ
የሰራችው ስራ በመጪዎቹ ትውልዶች እንዲመሰገን እና እንዲታወቅ ይህን ታሪኳን ለትውልድ እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ዛሬ ሰኔ 20
2013 ሲሆን ታታሪዋ አንድነት አሁንም ለመስራት ሳትቆጠብ አቅሟን እያሳየች ትገኛለች፡፡ በዚህም እናመሰግናታለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ