59. ጋሽ ሰለሞን ገብረስላሴ   Solomon  gebreselassie  ከልጆች አለም

ምንግዜም የማይዘነጉ -ዛሬም ትዝታ አላቸው

 ጋሽ ሰለሞን ገብረስላሴ ዛሬ የ79 አመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከልጆች አለም ላይ የሰሩ የትናንት አበባዎች ዛሬ በሰፊው ያመሰግኗቸዋል፡፡ ለመሆኑ ጋሽ ሰሌ አሉ? ወደየት ይሆኑ? ሲሉ ይጠይቃሉ፡፡ ተወዳጅ ሚደያ እና ኮሚኒኬሽን ዛሬ አቶ ሰለሞን ቤት ሊወስዳችሁ ነው፡፡ ታሪካቸው አስተማሪ በመሆኑ እነሆ አንቡት፡፡ እንደ ጋሽ ሰለሞን አይነት ሊዘመርለት የሚገባ የተዘነጋ በህይወት ያለ ሰው ካወቃችሁ ባካችሁ ጠቁሙን፡፡ 

     7 አመት ልጅ ሳሉ

ጋሽ ሰለሞን ገብረስላሴ  የተወለዱት እዚሁ አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ ‹‹ቅድስተማሪያም›› በሚባል ስፍራ  ነበር  ፡፡ ጊዜውም በሀምሌ 1934 ፡፡ጋሽ ሰለሞን ገብረስላሴ ገና የ 7 አመት ልጅ ሳሉ ቦንብ በመፈንዳቱ 2 እጃቸውንና አንድ አይናቸውን  በአደጋው ምክንያት ካጡ በኋላ በአሰላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን መከታተል ችለዋል፡፡ አደጋው በምን አይነት መንገድ እንደደረሰባቸው አቶ ሰለሞን ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች ተናግረው ነበር፡፡

         ነገሪቱዋ ምንድነች?

 ጋሽ ሰለሞን በልጅነታቸው አንድ ለየት ያለ ነገር  ሲመለከቱ ስለ ነገርየው ለማወቅ ታላቅ ጉጉት ያድርባቸዋል ፡፡ ሚያዝያ 23 1941 ነበር ሁኔታው የተፈጸመው፡፡ በጊዜው  የ7 አመት ልጅ የነበሩት ጋሽ ሰለሞን ከአጎታቸው ጋር ወደ ጊዮርጊስ ቤተክርስቲያን  ያቀናሉ፡፡ ታዲያ በዚያ እለት ህጻን ሰለሞን አንዲት ድቡልቡል ነገር ይመለከታል፡፡ ይህች ድቡልቡል ነገር መኪና ውስጥ የነበረች ሲሆን ነገሪቱዋ ምንድነች? ብሎ እንደለመደው መጠየቅ ይጀምራል፡፡  ከመጠየቅ አልፎም ያቺን  ድቡልቡል ነገር በእጁ መያዝ ጀመረ፡፡ ከመያዝ አልፎም እያገላበጠ ማየት ሲጀምር ወዲያው የፈንጂ ድምጽ ተሰማ ፡፡  ህጻኑ ሰለሞን እጅ ላይ ቦንቡ ፈነዳ፡፡ የእጅ ቦንብ ነበር፡፡ ጋሽ ሰለሞን 72 አመት ወደ ኋላ ተጉዘው ሲያስቡት ያኔ የሰሙትን የድምጽ ጩኸት ዛሬ ድረስ አይዘነጉትም፡፡ ወዲያው ህጻኑ ሰለሞን ወደቀ፡፡ከሰአት ማሰሪያው በታች ያለው እጁ ሙሉ ለሙሉ ተቀንጥሶ ሲወድቅ አንደኛው እጁም ከፍተኛ ጉዳት ደረሰበት፡፡ በዚህ ምክንያት ህጻኑ ሰለሞን 2 እጆቹንና አንድ አይኑን ሊያጣ ቻለ፡፡ ወዲያው ቤተሰቦች ተረባርበው ወደ ሀኪም ቤት ወሰዱት፡፡ ወቅቱ ጣሊያን ሀገራችን ለቆ ከወጣ 8 አመት በኋላ መሆኑ ነው፡፡

       ለእናት ምን ተብሎ ይነገር?

 በጊዜው ህጻኑ ሰለሞን፣ በምኒሊክ ሆስፒታል ለ 2ወራት ፣ሲታከም ነበር፡፡ ይህ ልጅ 2 እጆቹን አጥቶ ከዛሬ ነገ ይሞታል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡ በጊዜው የአቶ ሰለሞን ወላጅ እና አሰላ ነበሩ፡፡ በ7 አመቱ ልጃቸው ላይ ስለደረሰው ከባድ አደጋ የሚያውቁት ነገር አልነበረም፡፡ ታዲያ ለሰለሞን እናት ለወይዘሮ የሺ ምን ብለው  ይንገሯት? በጣም ፈታኝ ሁኔታ ነበር፡፡ ለእናት ምን ተብሎ ይነገር? ለ3ወር ከልጃቸው ርቀው የነበሩት ወይዘሮ  የሺ የልጃቸው ናፍቆት አላስችል ብሏቸው አዲስ አበባ ደረሱ፡፡ ነገር ግን የልጃቸው አይን እና እጅ በቦንብ መጥፋቱ በፍጹም አልተነገራቸውም፡፡ ብቻ ለ 3 ወር የተለዩት ህጻን ሰለሞን ናፍቆአቸው በጉጉት በአይናቸው ይፈልጉታል፡፡ ሰለሞን ግን አጠገባቸው ነበር፡፡  ‹‹….ውይ ይሄ ልጅ ሲያሳዝን ብለው ከንፈር ከመጠጡ በኋላ አሁንም 9 ወር የተሸከሙትን ልጅ መፈለግ ያዙ፡፡ ታዳጊው ሰለሞንም ‹‹ምነው እናቴ በዝምታ ተዋጠች? ምነው  ዘጋቺኝ?.›› ሲል ሰለሞን በሃዘን  ውስጡ ተላወሰ፡፡ ህጻኑ ሰለሞን ቤት ውስጥ ተኝቶ ቁስል በቁስል ነው፡፡  አለባበሱም እንደነገሩ ነበር፡፡ ወይዘሮ የሺም ወዲያው ብድግ ብላ ስትሄድ ሰለሞን ከመጀመሪያው በባሰ መልኩ ሆድ ባሰው፡፡ ፣‹‹እንዴት እናቴ ሰለሞን ብላ አትጠራኝም?.›› ብሎ በጣም ተከፋ፡፡  እናቱም ‹‹ልጄ የት አለ ?››ብላ የቤቱን ሰዎች ጠየቀች፡፡ ‹‹አሁን ነበር እዚህ ምናልባት ተልኮ ከሆነ ››  የሚል ምላሽ ነበር የተሰጣት፡፡ እናት ግን ጉዷን አላወቀችም፡፡  በመጨረሻ ግን ቁርጡ ሰአት ሲደርስ ሰለሞን  ተጠራ፡፡  ጋሽ ሰለሞን እናታቸው ላይ ያዩትን ታላቅ የመደንገጥ ስሜት  ዛሬ 79 አመት ሞልቷቸው እንኳን በፍጹም አይዘነጉትም፡፡ በትዝታ ተጉዘው ሲነግሩንም.‹‹….. እናቴ  በሀምሌ 1941 ይህን የልጇን አደጋ ባየች ሰአት መሬት ላይ እየወደቀች ማልቀስ ጀመረች፡፡ ተይ ብትባል ማንንም የማትሰማ ሆነች፡፡ ለ 2ወር ልጄን ብለየው ይህ አይነት አደጋ ይድረስበት!? ብላ በጣም አዘነች፡፡ አሰላ ይዤው ካልሄድኩም አለች፡፡ ሰዎች ግን አይሆንም አሏት፡፡ አስተምረዋለው ብላ በአቋሟ ጸናች፡፡ እጆቹ ከባድ አደጋ  ደርሶባቸው እንዴት አድርጎ ሊጽፍ ነው የምታስተምሪው ብለው ምክር ሊለግሷት የሞከሩ ነበሩ ፡፡ ፣‹‹ልጄን ትቼው ባልሄድ ኖሮ አደጋ አይደርስበትም፡፡ ስለዚህ አሰላ ይዤው እሄዳለሁ›› ብላ በ1942 ግድም ጉዞ ወደ አሰላ ሆነ፡፡፡›› በማለት ጋሽ ሰለሞን በእናታቸው አድሮ የነበረውን ስሜት ተርከውልናል፡፡

                 ሰለሞንን ማን ይቻለው? 

              ጋሽ ሰለሞን የአንደኛ ክፍል ትምህርታቸውን  በአሰላ እንደጀመሩ የተማሪ ቤቱ መምህር የትምህርት ፍላጎታቸውን ልብ ብሎ አጤነ፡፡ ነገር ግን ‹‹ይህ ልጅ በእጆቹ ላይ በደረሰ የአካል ጉዳት ምክንያት አይጽፍም ምን እናድርገው?›› የሚል ጥያቄ ከመምህራኖቹ ዘንድ ይነሳ ነበር፡፡ በዚህ ሰአት ታላቅ የመማር ጉጉት አድሮበት የነበረው ትንሹ ሰለሞን ጉንጮቹ ላይ የእንባ ዘለላዎች መፍሰስ ጀመሩ፡፡  በዚህ ሁኔታ መምህራኖቹ የሰለሞንን ጽኑ የመማር ፍላጎት አጢነው  ወደ 2ኛ ክፍል አስገቡት፡፡ ይህ ለታዳጊው ልጅ መልካም የምስራች ነበር፡፡ ከጎበዝ ተማሪዎች ጋር አንድ ላይ በመሆን በትምህርቱ ላይ መበርታት ጀመረ፡፡  አንዳንድ ጊዜ የክፍል ጓደኞቹ ይጽፉለታል፡፡  ብዙውን ጊዜ በማዳመጥ እውቀትን ይቀስም የነበረው ብላቴናው ሰለሞን ትምህርት የሚገባው ልበ-ብርሀን ልጅ ሆነ፡፡ መምህራኖቹም ማበረታታቸውን ቀጠሉበት፡፡ ሰለሞንም በረታ፡፡ 3ኛ ክፍል ገባ፡፡ የተሻለ ውጤትም አመጣ፡፡ ወደ 4ኛ ክፍልም ተዛወረ፡፡  ከዚያ በኋላ ሰለሞንን ማን ይቻለው?  በየጊዜው የመምህራንን የከረሜላ ስጦታ ከእጁ ማስገባት ጀመረ፡፡ ይህ ይበልጥ አበረታታው፡፡  በተለይ 4ኛ ወጥቶ ሽልማት ሲቀበል  ልጅ ሰለሞን ከዚህ በላይ አጥንቼ መሸለም አለብኝ ብሎ በቀጣዩ ክፍለ-ጊዜ አንደኛ ወጥቶ ከተማሪ ቤቱ ጎበዝ ተማሪዎች አንዱ ሆነ፡፡ በቀጣዮቹ አመታትም ሰለሞን ተሸላሚ በመሆን ዘለቀ፡፡  ሰለሞን ምንም እንኳን እጁን በአደጋ ቢያጣም አሰላ የነበሩት ፈረንጅ ዶክተሮች ግን በአንድ ዘዴ መጻፍ የሚችልበትን ብልሀት ቀይሰውለት ነበር፡፡ ይህም እንደ ሰአት ማሰሪያ የሆነ ላስቲክ ነበር፡፡ በሰአቱና በሰለሞን እጅ መካከል እርሳስ ወይም ብእር / እስክሪቢቶ ይገባል፡፡ከዚያ በኋላ በዚህ መንገድ ሰለሞን መጻፍ ጀመረ፡፡ በዚህ ተበረታትቶ  ደብተር ተገዝቶለት ቀኑን ሙሉ ሲጽፍ ዋለ፡፡  እና አንድ ቀን እናቱ ልጇ ቆይቶ የመጣ ጊዜ ቆየህ ምነው ልጄ ስትለው ‹‹ …. እናቴ የቆየሁት ስጽፍ ነው›› የሚል ምላሽ ሰጣት ፡፡ እናትም የምን ጽሁፍ?! ስትል በመገረም ተሞልታ ጠየቀች፡፡  ፈጣኑ ሰለሞን ወዲያው የጻፈውን አሳያት፡፡እናት ማመን ሲያቅታት ደብተሩን አውጥቶ እዚያው ጻፈና ‹‹እማ አየሽው ?.›› አላት፡፡ እናት በደስታ ተሞልታ አለቀሰች፡፡ ፈጣሪዋን አመሰገነች፡፡  ‹‹ተመስገን እንኳን  ልጄን አሰላ ይዤው መጣሁ ፡›› ስትል በውሳኔዋ ተደሰተች፡፡ ሰለሞን ከ4ኛ ክፍል አንስቶ ኮከበ-ጽባህ መምህራን ማሰልጠኛ እስከሚገባ ድረስ በዚህ አይነት መንገድ ሲጽፍ ኖረ፡፡

              ቁንጥጥ አደረገኝ

በአንድ ወቅት ጋሽ ሰለሞን  በምኒሊክ ተማሪ ቤት እየተማሩ ሳሉ ጃንሆይ ቀድሞ እንደሚያደርጉት ተማሪዎችን ለመጎብኘት መጡ፡፡  በዚህ ጊዜ ጋሽ ሰለሞን የእግዚአብሄርን ድንቅ ስራ ማንሳት ይሻሉ፡፡ ጊዜው በ1949 ነበር፡፡  ጃንሆይ ሲመጡ ያው በወቅቱ ግርግር መፍጠር የተለመደ ነበር፡፡ ለእነ ሰለሞን ራት ተሰጣቸው፡፡

  ጋሽ ሰለሞን ትዝታቸውን ሲያወጉ፦ 

   ነጭ መሀረብ አውጥተው እንባዬን ጠረጉልኝ፡፡

‹‹……ጃንሆይ ሲጎበኙ ልክ  ለልጆቹ ብርቱካን ሰጥተው  ሲመለሱ ወደ እኔ ሲቃረቡ የክፍል ጓደኛዬ ህመም በሚፈጥር መልኩ ቁንጥጥ አደረገኝ፡፡  እኔም በዚህ ምክንያት ብድግ ስል ጃንሆይም  ምን ነበር ? አሉኝ እኔም ጃንሆይ እጄ እንዲሰራልኝ ፈልጋለሁ አልኩ ፡፡ ከዚያ በፊት እጅ ስለመሰራት የማውቀው ነገር አልነበረም፡፡  ጃንሆይም የጠየቅኩትን ጥያቄ ካደመጡ በኋላ አንዱን ወታደር ጠርተው  ስሙ ጻፈው ብለው ትእዛዝ ሰጡ፡፡ ወታደሩም ስሜን ጻፈው፡፡ አባ ሀናም ወዲያው መጡ፡፡ ለእርሳቸውም ዝክ ዝክ አድርጌ ታሪኬን ነገርኳቸው፡፡ አባ ሀና ግን ለደቂቃዎች ከሰሙኝ በኋላ አጥጋቢ ምላሽ አልሰጡኝም ነበር፡፡ በአባ ሀና አባባል ደግሞ ዳግም ማልቀስ ጀመርኩ፡፡ወዲያው የምኒልክ ተማሪ ቤት ሞግዚቶች  መጡ፡፡ በጣም አጽናኑኝ፡፡  አንድም ምክርም ለገሱኝ፡፡ ጃንሆይ በዚህ በመኪና ሲያልፉ ለጥ ብለህ እጅ ንሳ ሲሉ መከሩኝ፡፡ እኔ ግን አንድም ቀን ለጥ ብዬ እጅ ሳልነሳ ቀረሁ፡፡ ደግሞ በሌላ ቀን ተማሪ ቤት በሚዘጋበት ጊዜ ወደ ሀምሌ 13 ግድም  ተማሪዎች ስለሚሸለሙ አንድም ተማሪ ቤተ-መንግስት እንዳይቀር ተብሎ ሁላችንም ወደዚያው አቀናን፡፡ ተሸላሚ ሲጠራ የእኔ ስም ተጠራ፡፡ በጊዜው የትምህርት ሚኒስትር ከፍተኛ ሃላፊ የነበሩት አቶ ከበደ ሚካኤል ነበሩ፡፡ ፣‹‹ሰለሞን ገብረስላሴ! ሲሉ ደግሞ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ተጣሩ፡፡ ከዚያም ወደመድረኩ ሄጄ፡ ለጥ ብዬ እጅ ነሳሁ፡፡ ነገር ግን ሽልማቱን በምኔ ልቀበል? ሳልቀበል ወደ መቀመጫዬ ተመለስኩ፡፡ በዚህ ጊዜ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል እና ጃንሆይ  በእኔ ጉዳይ ተነጋግረው ኖሯል፡፡ ከእኔ በኋላ የተጠራው ልጅ የራሱንም የእኔንም ሽልማት ይዞ ተመለሰ፡፡ከዚያ በ1949 አመተ ምህረት ቤተ-መንግስት እንድትመጣ ተባልኩ፡፡  ጉዞ ወደ ቤተ-መንግስት ተደረገ፡፡  ቀኑ ሰኞ ነበር፡፡ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ሰኞ ቤተ- መንግስት  ጠብቀኝ ባሉኝ መሰረት እዚያው ጠበቅኳቸው፡፡ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል የጠሯችሁ ተማሪዎች እናንተ ናችሁ ተብሎ አሳላፊው ማስገባት ሊጀምር ሲል የእያንዳንዱን ተማሪ አለባበስ ልብ ብሎ ያጤን ነበር፡፡  ብዙው ተማሪ ሱፍ የለበሰ ነበር፡፡ እኔ  ግን አንድ ካኪ ለብሼ ነበር፡፡ አንተ ቁም ተብዬ ጥበቃው እንዳልገባ አደረገኝ፡፡  ወዲያው የተለመደው እንባዬን ማውረድ ጀመርኩ፡፡ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ከልጆቹ መሀል እኔ አለመኖሬን ሲመለከቱ ወዲያው በሩ ጋር መጡ እና ና አሉኝ፡፡ እምባዬ ከአይኔ መፍሰሱን ሲመለከቱ  ከኪሳቸው ነጭ መሀረብ አውጥተው እንባዬን ጠረጉልኝ፡፡ አይዞህ አታልቅስ ሲሉኝም አጽናኑኝ፡፡ ይዘውኝም ጃንሆይ ጋር ገባን፡፡ ክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ጃንሆይ እና እኔ ጽህፈት ቤት ውስጥ ቀረን፡፡ ጃንሆይ ከወራት በፊት ምኒልክ ተማሪ ቤት መጥተው እኔን ማነጋገራቸውን በደንብ አስታወሱ፡፡ እንዴት አደጋው እንደደረሰ በዝርዝር አስረዳሁ፡፡  ጃንሆይ 2 እጆቼን አጥቼ ጎበዝ መሆኔ በጣም አስገርሟቸው፡ አንተ ታዲያ እንዴት ተሸላሚ ተማሪ መሆን ቻልክ? ብለው  ውስጣቸው የተብላላውን ጥያቄ ጠየቁ ንጉሱ፡፡ እኔም  ጎበዝ የመሆኔ ትልቁ ሚስጥር በርትቼ ማጥናቴ እንደሆነ ተናገርኩ፡፡ በዚህ ጊዜ ጃንሆይ  ይህ ልጅ ጀርመን ሀገር ሄዶ ሰው ሰራሽ እጅ ሊሰራለት ይገባል በማለት ለክቡር አቶ ከበደ ሚካኤል ትእዛዝ ሰጡ፡፡እኔም እጅ ነስቼ ወጣሁ፡፡ ጀርመን ሀገር የሚለው ነገር ተወስኖ የነበረ ቢሆንም እርሱ ቀረና አንድ ጣሊያን ባለሙያ ጋር ሰው ሰራሽ እጅ እንዲሰራልኝ ተደረገ፡፡ 

   የልጆች ፕሮግራም -1959

አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ከ1951-1959 በአሰላ እና በአርበኞች ተማሪ ቤት በመምህርነት አገልግለዋል፡፡  በታህሳስ 1959 አንድ የምስራች ድምጽ  ሬድዮ የሚሰራ ጓደኛቸው አንድ ስራ እንዳለ ይነግራቸዋል፡፡  ይህም በየምስራች ድምጽ ሬድዮ የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅ እንደሚፈለግ  ያስረዳቸዋል፡፡ አቶ ሰለሞን ግን ብዙም ቁብ አልሰጡት፡፡ መምህርነትን በጣም ይወዱ ስለነበር የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅ የሚለው ነገር ብዙም አልተዋጠላቸውም ነበር፡፡ ጓደኛቸው እንዲያመለክቱ ጉትጎታ ቢያደርግም አቶ ሰለሞን ግን  በጊዜው ይህን ማድረግ አልቻሉም፡፡ በሂደት ግን ጓደኛቸው አመልክቶላቸው በ1959 አ.ም የልጆች ፕሮግራምን ማዘጋጀት ጀመሩ፡፡ አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ፣ፈተናውን  ተፈትነው እንዳለፉ ወዲያውኑ የልጆች ፕሮግራም ማዘጋጀት የጀመሩበትን አጋጣሚ ዛሬ ድረስ አይዘነጉትም፡፡ ከእርሳቸው በፊት አንድ ባለሙያ የልጆች ፕሮግራም ለማዘጋጀት ተቀጥሮ የነበረ ቢሆንም ብዙም ሳይቆይ ነበር አቶ ሰለሞን የተተኩት፡፡

በጊዜው አቶ ሰለሞን በሉትራን ቤተ-ክርስቲያን የሰንበት ተማሪ ቤት መምህር ነበሩ፡፡ እና በዚያን ጊዜ የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅ ተብለው ሲመደቡ ሰንበት ተማሪ ቤት የሚማሩ ልጆችን በማሰባሰብ ወደ ስቱዲዮ በመውሰድ የልጆች ፕሮግራምን ታህሳስ 15 1959 አንድ ብለው መጀመራቸውን ይናገራሉ፡፡ ያኔ በጭውውት መልክ  የተለያዩ መሰናዶዎች  ይቀርቡ ነበር፡፡ አቶ ሰለሞን ከ1959-1966 ድረስ  የልጆች ፕሮግራምን በየምስራች ድምጽ ስር ሆነው የሰሩ ሲሆን በርካታ ልጆችም በእነዚህ 7 አመታት ስቱዲዮ ድረስ እየመጡ ይቀረጹ ነበር፡፡ ታዲያ  ጋሽ ሰለሞን ለብዙ አመታት የልጆች ፕሮግራም አዘጋጅ ሆነው ለበርካታዎች መታነጽ ምክንያት ሆነዋል፡፡  በ1967 የምስራች ድምጽን  ደርግ  ሲወርሰውና አንዳንድ ባለሙያዎች ከስራ ሲሰናበቱ አቶ ሰለሞን ግን እንዲቀጥሉ ተደረገ፡፡ ከዚያም የልጆች ፕሮግራም በኢትዮጵያ ሬድዮ ስር ሆኖ በርካታ ልጆችን የሚመለከቱ መሰናዶዎችን አየር ላይ ሲያውል ቆይቷል፡፡   በጊዜው የምስራች ድምጽ የሚሰሩት ሳይሆኑ በሌላ አዲስ ድምጽ እና ልጆች እንዲሰራ በመፈለጉ አቶ ሰለሞንም ይህን ማድረግ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡   መጀመሪያ አካባቢ  አቶ ሰለሞን የልጆች ፕሮግራምን ሲጀምሩ ስለ መታዘዝ እንዲሁም አባትና እናትን ስለማክበር ያቀርቡ ነበር፡፡ እንዲህ አይነቱ መሰናዶ የልጆችን ስነ-ምግባር በማነጽ በኩል የራሱ ሚና ነበረው፡፡ እግዚአብሄርን ስለመፍራት ሁሉ በርካታ መሰናዶዎች ይቀርቡ ነበር፡፡  በተጨማሪም ትምህርትን ስለመውደድ  በተማሩት ስራ ሀገርን ስለማገልገል ሀገርን ስለመውደድ ሁሉ በልጆች አለም መሰናዶ ውስጥ ለአመታት ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ አቶ ሰለሞን   ለአመታት በልጆች ፕሮግራም  ላይ እንደመስራታቸው መግቢያ ላይ የሚሉትን ዛሬ ድረስ አይዘነጉትም ….

‹‹…….. ሰላም እንደምን ሰነበታችሁ የፕሮግራማችን አድማጮች…… እንግዲህ የፕሮግራማችን አድማጮች ስል ይህ ፕሮግራም የማነው?  የፕሮግራሙ ባለቤቶች እናንተ ልጆች ናችሁ፡፡ ስለዚህ እንደምን ሰነበታችሁ ልጆች? ደህና ናችሁ አይደል? ባለፈው ሳምንት በዚህ ፕሮግራም ተገናኝተን ነበር፡፡ ዛሬ ደግሞ እግዚአብሄር ፈቅዶልን ዳግም ለመገናኘት በቅተናል፡፡ ደስ ይላል አይደለም፡፡ እኔ በበኩሌ በጣም ደስ ብሎኛል፡፡  እናንተስ ደስ ብሎናል አላችሁ አይደል?  አዎን  ባለፈው ሳምንት የተማርነው ስለምን እንደነበር ታስታውሳላችሁ፡?   ምን ነበር እስቲ? በእናንተ ፋንታ እኔ መልሱን ልንገራችሁ፡፡ ባለፈው ሳምንት መታዘዝ  ጠቃሚ ነገር እንደሆነ ተነጋግረን ነበር፡፡ ለማን መታዘዝ? ለወላጅ ፣ ለአስተማሪ ለሁሉም ታላላቆች መታዘዝ ጠቃሚ መሆኑን ተምረን ነበር፡፡ ዛሬም እንግዲህ ከዚህ ሀሳብ ጋር የተያያዙ ጥያቄዎችን እየጠየቅኳችሁ አብራችሁን ትዘልቃላችሁ፡፡ ተዘጋጁ ከዚያ በፊት ግን አንድ መዝሙር አሰማችኋለሁ፡፡ መዝሙሩን እያደመጣችሁ ለሚቀጥለው ፕሮግራም ተዘጋጁ እሺ፡፡›› በማለት ከልጆች አለምን  ያስተዋውቁ ነበር፡፡

    ልጆች ላይም አንድ በጎ ተጽእኖ ማሳረፍ 

 የልጆች ፕሮግራም በየሳምንቱ ቅዳሜ ከጠዋቱ አንድ ሰአት ከ10 ደቂቃ ጀምሮ የሚቀርብ ፕሮግራም ሲሆን  ከልጆች አለም የሚለውንም ስያሜ ያገኘው  ደርግ ብስራተ ወንጌልን ከወረሰው በኋላ  በደርግ ጊዜ ነበር፡፡ ጋሽ ሰለሞን አብረዋቸው የሰሩ ልጆችን በፍጹም አይዘነጓቸውም፡፡ እንደ ልጆቼ ነበር የማያቸው ሲሉ  ለልጆቹ ያላቸውን ፍቅር ይገልጻሉ፡፡ አቶ ሰለሞን ከ40 አመት በላይ ከልጆች አለምን ሲያዘጋጁ ለትውልድ አንድ ትልቅ መሰረት እያስቀመጡ እንደሆነ ያስባሉ፡፡ ከሬድዮ አድማጮች ባሻገር ከእርሳቸው ጋ ሆነው ፕሮግራሙን የሚሰሩት ልጆች ላይም አንድ በጎ ተጽእኖ ማሳረፋቸውን ይናገራሉ፡፡ ብዙዎቹ ከእርሳቸው ጋር ሆነው ከልጆች አለምን ሲያሰናዱ የነበሩ ታዳጊዎች ዛሬ ትልቅ ቦታ ደርሰው ሀገራቸውን ለማስጠራት ችለዋል፡፡ አቶ ሰለሞን በዚህ ጉዳይ በቃላት ሊገልጹት የማይችሉት የመንፈስ ርካታ ይሰማቸዋል፡፡ በተለይ ያኔ የዘሩትን ዘር ዛሬ ማጨዳቸው ታላቅ ደስታን ያመጣላቸዋል፡፡  በአሁኑ ሰአት  አውሮፓ ስዊዘርላንድ የምትገኘው ሉሊት ታፈሰ ከወንድሟ ጋር ሆና ከልጆች አለም የሚለውን መግቢያ ድምጽ ያነበበች ናት፡፡ ሉሊት ስለ ጋሽ ሰለሞን ተናግራ አትጠግብም፡፡ በልጅነት እድሜያችን የወደፊቱን የህይወት መሰረት ጥሩ አድርገው ያስቀመጡልን  ደግ አባት ናቸው ስትልም ያላትን ጥልቅ አክብሮት ትገልጻለች፡፡ በአሁኑ ሰአት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትምህርት ሙያ በከፍተኛ የስራ ሃላፊነት  እያገለገለች የምትገኘው  ሉሊት ታፈሰ የትምህርት ፍቅር ውስጡዋ  እንዲሰርጽ ያደረጉትን ጋሽ ሰለሞንን ማመስገን ትፈልጋለች፡፡ ቅድስት በላይም እንዲሁ ከልጆች አለም ላይ ስትሰራ  ቆይታ በኋላ በኢትዮጵያ ሬድዮ እና ቲቪ እስከ ዳይሬክተር የስራ መደብ ለመድረስ የቻለች ሰው ነች፡፡ ቅድስት ብትሆን ያኔ በልጅነት እነ ጋሽ ሰለሞን ብስኩት እና ሻይ እየጋበዙ ከልጆች አለም ላይ ሲያሰሯት  የነበረውን ጣፋጭ  ጊዜ ፍጹም ልትዘነጋው አትችልም፡፡ ጋሽ ሰለሞን ልጆችን የሚወዱ እና በምላሹም ልጆች የሚወዷቸው  ደግ አባት እንደሆኑ በብዙዎች ተመስክሮላቸዋል፡፡  ጋሽ ሰለሞን 40 አመታት ለሚጠጋ ጊዜ ልጆችን በሬድዮ ሲያዝናኑ ብሎም ሲያስተምሩ የቆዩ በፍጹም የማይዘነጉ ታላቅ ባለውለታ ናቸው፡፡ ጋሽ ሰለሞን 40 አመት ወደ ኋላ ተመልሰው  ይህን የከልጆች አለም  ትዝታ ሲያወጉን እጃቸው ላይ የድሮ ፎቶዎችን በመያዝ ነው፡፡ ህጻናቱ በቀረጻ ላይ ሳሉ የሚያሳዩ ከ 14 በላይ ምስሎችን ይህን የእርሳቸውን የዊኪፒዲያ ታሪክ ላሰናዳው ሰው የሰጡት ሲሆን ይህም የሚያሳየው ከከልጆች አለም ጋር ያላቸውን  የትዝታ ቁርኝት ምን ያህል የጠበቀ መሆኑን ነው፡፡ ጋሽ ሰለሞን ጋር የሰሩ ብዙ ልጆች ዛሬ በሚድያ እና በኪነ-ጥበቡ መስክ ተሰማርተው እናት ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡  ከእነዚህ መካከል አስካለ ተስፋዮ / ኢትዮጵያ  ሬድዮ / ብርሀኑ ገብረማሪያም ፤ የአሀዱ  ሬድዮ ዋና የሰራ መሪ  ጥበቡ በለጠ ፤ የቁምነገር መጽሄት መስራች ታምራት ሀይሉ ፤ ዳዊት ንጉሱ ፤ ነጻነት ሰለሞን ፤ ፍሬዘውድ ተሾመ እንዲሁም ተገኝ ጃለታ ይገኙበት ነበር፡፡ 

 ጋሽ ሰለሞን የልጆችን ሚድያ ወግ በያዘ መልኩ በማደራጀት ሚናቸው የጎላ ብቻ ሳይሆን ቀጣይነት እንዲሁም ተከታታይነት ያለው ትውልድ የማይዘነጋው ውለታ የዋሉ ናቸው፡፡ በልጅነት የገጠማቸው አደጋ አንዳችም ጊዜ ሳይበግራቸው ለትውልድ የሚጠቅም ታላቅ ስራ ሲሰሩ ኖረዋል፡፡ ጋሽ ሰለሞን ይህን ያለፉበትን የህይወት መንገድ በመጽሀፍ ሰድሮ የማስቀመጥ ህልም አላቸው፡፡ ያለፉበት መንገድ ለብዙዎች  አስተማሪ በመሆኑ የመጽሀፉ መዘጋጀትና ታትሞ ለንባብ መብቃት ፋይዳው ትልቅ መሆኑ አይቀርም፡፡ ጋሽ  ሰለሞን አፍንጮ በር ግድም ከሚገኘው ቤታቸው ሆነው ለ 80 ደቂቃ ከዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ጋር ሲጨዋወቱ  በትዝታ ወደ ኋላ ምስጥ ብሎ የመሄድ አዝማሚያ በስፋት ይስተዋልባቸዋል፡፡ ዛሬ 79 አመታቸው ላይ ሆነው ደስታ ሰውነታቸውን ይወረዋል፡፡ በዚህ ምድር ስኖር ፈጣሪ ለፈጠረኝ በጎ አላማ  አንድ ትልቅ ነገር አበርክቻለሁ ብለው ያስባሉ፡፡

መዝጊያ፦   ጋሽ ሰለሞን የልጆች ፕሮግራምን በጥሩ መልኩ እንዲሰራበማድረጋቸው  ትውልድ የሚሻገር  በጎ ነገር ዛሬ መመልከት ችለናል፡፡ ያኔ ሳይደክማቸው ልጆች ላይ በመስራታቸው ፍሬውን ለማየት ቀንቷቸዋል፡፡ እግዚአብሄር ለሁሉ ነገር አላማ አለው የሚሉት ጋሽ  ሰለሞን አብዛኛውን  ጊዜ በመገናኛ ብዙሀን አበርክቷቸው ሲወሳ አይታይም፡፡ እርሳቸው ልታይና ልታወቅ በሚል ሳይሞሉ ስራቸውን በብርታት ሲያከናውኑ የቆዩ ነበሩ፡፡ መቼም የሰራ ሰው አንድ ቀን መውጣቱ አይቀርምና ጋሽ ሰለሞንን በዚህ የዊኪፒዲያ  ገጽ ለመሰነድ ሞክረናል፡፡ ትውልድ እኒህን ደግ ሰው ይወቃቸው ያክብራቸው ስንል ይህ አጭር ጽሁፍ እንካችሁ ብለናል፡፡   /ይህ ጽሁፍ ተሰናድቶ ፖስት የተደገረው ሰኔ 23 2013 ሲሆን  ጽሁፉን አጠናክሮ ያሰናዳው ደግሞ እዝራ እጅጉ ነው/

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች