58.ታምሩ አለሙ ይረፉ  -TAMIRU ALEMU YEREFU

                  ይህቺን ለቅምሻ-በሬድዮ ፋና

 

ታምሩ አለሙ፣ በስፖርት ጋዜጠኝነቱ ይታወቃል፡፡  በተለይ ጣፋጭና ዘና የሚያደርጉ የመዝናኛ ጉዳዮችን ቅልል እና ቅልጥፍ ባለ መልኩ በማሰናዳት ይታወቃል፡፡ ሙያውን ከልጅነቱ ጀምሮ የሚወደው  ታምሩ ዛሬ  በሀገረ-አሜሪካ  ሆኖም  ‹‹ጋዜጠኝነት በደሜ ውስጥ ነው›› ይላል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከበፊት ጀምሮ እስከአሁን በመዝናኛ እና በመረጃ ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን እያስተዋወቀ እንደሆነ ይወቃል፡፡ አሻራ አኑረዋል ብላችሁ ያመናችሁባቸውን  ባለሙያዎች ጠቁሙን፡፡አሁን የታምሩ አለሙን ታሪክ ልናስነብብ ነው፡፡

                  ንብረት አንድ -ሬድዮ

   ታምሩ  አለሙ የኳስ ሜዳ ልጅ ነው፡፡   አዲስ ከተማ ኳስ  ሜዳ የኪነጥበብ ባለሙያዎችና የስፖርት ሰዎች ያፈለቀች አካባቢ ነች፡፡  ታምሩ አለሙም በዚህች ሰፈር ጥቅምት 6/1977 ዓ.ም ከአባቱ አቶ አለሙ ይረፉ እና ከእናቱ ከወ/ሮ ቀፀላ ፈጠነ  ነበር የተወለደው ፡፡ ከቤተሰቡ 3 ልጆች መካከል የቤቱ ሁለተኛ ልጅ የሆነው ታምሩ በልጅነቱ ፓይለት፣ ዶክተር፣ ሳይንቲስት፣ ኢንጂነር እነዚህን መሰል የብዙዎች የልጅነት ምኞቶች እሱ ዘንድ ቦታ አልነበራቸውም። "ስታድግ ምን መሆን ትፈልጋለህ?" የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ ሁለቴ ማሰብ አስፈልጎት አያውቅም። ከልጅነት እስከ እውቀት ህልምና ፍላጎቱ አንድ ብቻ ነበር፤ ጋዜጠኛ መሆን...ለዚያውም የሬዲዮ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ከአንደኛ እስከ ስምንተኛ ክፍል በተማረበት ቀስተደመና አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት አብሮ አደጎቹና የክፍል ጓደኞቹ የሚያስታውሱት ሚኒ ሚዲያ ላይ ሲሳተፍና ሲመራ ወይም ክፍል ውስጥ ለተማሪው መፅሀፍ ሲተርክ ነው። የመጀመሪያ ንብረቱ እንደ እኩዮቹ መጫወቻ አልነበረም ፤ ሬዲዮ እንጂ።ከትምህርት መልስ የሚተክዝባት፣ የሚዝናናባት ብሎም አብራው የምትዞር በባትሪ የምትሰራ አንዲት ሬዲዮ ነበረችው። በሬዲዮው ፕሮግራሞችን እየሰማና ጋዜጠኞችን እያስመሰለ የኳስሜዳ ሰፈር የእግርኳስ ውድድሮችን እየተከታተለ በትምህርትቤቱ ደግሞ በሚኒሚዲያ ለተማሪው እያቀረበ ለኢትዮጵያ ሬዲዮና ለሬዲዮ ፋና በተለይ ለልጆች ክፍለ- ጊዜ ፅሁፎችን እየላከ የልጅነት ጊዜውን አሳልፏል፡፡

                         ፍቅሩ አደገ 

 የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን 9ኛና 10ኛ ከፍል በተማረበት ከፍተኛ ሰባት ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም 11-12ኛ ክፍልን ባጠናቀቀበት አዲስ ከተማ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ይኸው ፍቅሩ አድጎ በሚኒሚዲያ የስፖርትና መዝናኛ መረጃዎችን ያቀርብ ነበር፡፡ በአካባቢው በሚገኙ  የስነ-ፅሁፍ ክበቦች በመሳተፍም፣ በት/ቤቶች የስነ ፅሁፍ ውድድር ላይ በማሸነፍ ችሎታውን ያዳብር ነበር፡፡ በመቀጠል በዲላ ዩኒቨርስቲ ቆይታው "መቅረዝ" በተባለው የግቢው የኪነጥበብ ማዕከል በፕሮግራም መሪነት እንዲሁም ፅሁፎችን በማቅረብ ተሳትፏል ፡፡በዚህ ወቅት ከመምህራንና ከአቻ ተማሪዎች ብዙ ልምድ ቀስሟል፡፡ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነ- ፅሁፍ ዘርፍ ተመርቆም ዲግሪውን ይዟል፡፡

             አለምነህ ዋሴን ፍለጋ

 ታምሩ ለስምንተኛ ክፍል ፈተና በሚዘጋጅበት ዓመት የልጅነት ህልሙን ለማሳካት  የወቅቱን ተወዳጅ የሬዲዮ ሰው ለመተዋወቅ ወደ ሬዲዮ ፋና ሄደ፡፡ አለምነህ ዋሴን ፍለጋ....እጁን ጨብጦ ፣ አድናቆቱን ገልፆ ፣ በአካል አይቶ ሙያዊ ምክር ሊቀበል ከትምህርት ቤት ቀርቶ ደብተሩን እንደያዘ ከነ ዩኒፎርሙ ጥቁር አንበሳ ድረስ በእግሩ ተጉዞ...በማለዳ ሬዲዮ ፋና ደጃፍ ደረሰ፡፡ ለዕለቱ ጥበቃ አለምነህ ዋሴን ፍለጋ እንደመጣ ነገረው፡፡ ጥበቃውም የግርምት ፈገግታ አሳየውና ከበሩ ርቆ እንዲጠብቀው አዘዘው፡፡ ሰዓቱ እየነጎደ ፀሀዩ እየበረታ መጣ:: ከረፋዱ አራት ሰዓት እስከ ዘጠኝ ሰዓት የጋዜጠኝነት አለሙን ፍለጋ አለምነህን ሲጠብቅ ቆየ ፡፡ጥበቃው አሁን ይመጣል በሚል የማላገጥ ተስፋ አውሎት የሳዳም ሁሴንና የፊደል ካስትሮ ወዳጅ ይመስለው የነበረውን አለምነህ ዋሴን ሳያገኝ ረሀብና ድካም ተሸክሞ ወደ ቤት ተመለሰ:: ከዚያ በኋላ ጥበቃውን ጥላቻ ወደ ጣቢያው አልሄደም፡፡ አለምነህን ከነ አድናቆቱ በሬዲዮ ሞገድ ብቻ መከታተል ግድ ሆነበት፡፡ ከአመታት በኋላ ሬዲዮ ፋና በጋዜጠኝነት ተቀጠረ። በቤጂንግ ኦሊምፒክ ልዩ የስፖርት ፕሮግራም ላይ አብሮ ለመስራት በቃ ለመጀመሪያ ጊዜ አለምነህ አጠገብ ተቀምጦ በቀጥታ ስርጭት ስሙን ሲጠራው እርሱን ፍለጋ ያሳለፈው ትዝ ብሎት እንባ ተናነቀው፡፡ በታምሩ አለሙ የጋዜጠኝነት ጉዞ አስተዋፅኦ ከነበራቸው ሰዎች መካከል አለምነህ ዋሴ አንዱና ዋነኛው ነው ።

               ታምሩና እለታዊው አዲስ ዘመን

   በኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኝነት ሙያ ከማይዘነጉ ተወዳጅ የአቀራረብ ለዛ ካላችው ቀደምት ሁለገብ ጋዜጠኞች አንዱ  ታምሩ ዓለሙ የጋዜጠኝነት መንገዱን አንድ ብሎ  የጀመረው  በህትመት ሚድያ ነበር፡፡ ከተመረቀ ከሁለት ወራት በኋላ የቀረበውን ፈተና አልፎ የመጀመሪያ ስራውን በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት አዲስ ዘመን ጋዜጣ የስፖርት ጋዜጠኛ በመሆን በሪፖርተርነት የስራውን አለም ተቀላቀለ፡፡ ከ1999-2000 በየቀኑ በሚወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ በስፖርት አምድ  ላይ በመፃፍ ለአንድ አመት አገለገለ። በቆይታውም ከተቋሙ አንጋፋ ጋዜጠኞች የአፃፃፍ ስልትና ቴክኒካዊ ጉዳዮችን እንደቀሰመ ይናገራል፡፡

               ይህቺን ለቅምሻ-በሬድዮ ፋና

 ታምሩ አለሙ ፣ከበርካታ ተወዳዳሪዎች መካከል በረዥም ፈተና የተሻለ ውጤት አምጥተው ከተመረጡ ጋዜጠኞች አንዱ ሆኖ በኢትዮጵያ ሚሊኒየም 2000 ዓ.ም ላይ ሬዲዮ ፋናን ተቀላቀለ። እስከ 2005 ዓ.ም ለአምስት አመታት በሬድዮ ፋና ከሪፖርተርነት እስከ ከፍተኛ አዘጋጅነት እና የስፖርት ክፍል መሪነት አገልግሏል፡፡ በአቀራረብ ለዛው በልዩ ተሰጥኦው የአድማጭ ተመልካችን ቀልብ መሳብም ችሏል፡፡ በተለይ በሬድዮ ፋና ቆይታው "ይህቺን ለቅምሻ" ፎርማት፣ የመዝናኛ ዝግጅቶች፣ ባለው ሁለገብ ዕውቀት በሚሰራቸው ዜና ትንታኔዎቹ ተወዳጅነትን ይበልጥ አግኝቷል፡፡ በጋዜጠኝነት ህይወቱም የሬዲዮ ፋና ቆይታውን ወርቃማ ጊዜያት ይለዋል፡፡

           ታምሩ--- በሌሎች መገናኛ ብዙሃን

ታምሩ አለሙ በ2005 ዓ.ም የራሱን የአየር ሰዓት በመውሰድ በዛሚ ኤፍ.ኤም የሀገር ውስጥ ስፖርት እንዲሁም ሸገር ኤፍ.ኤም በሸገር ስፖርት ፕሮግራም ላይ በተባባሪ አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡ በዚህ ወቅትም በደቡብ አፍሪካ በተካሄደውና ዋሊያዎቹ በተሳተፉበት የአፍሪካ ዋንጫ ላይ በቦታው በመገኘት ለአድማጮች ዘገባዎችን ሰርቷል፡፡ ከ2006 መጨረሻ-2007 ደግሞ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት(ኢቢሲ) ስፖርት ክፍል በቴሌቪዥንና በሬዲዮ የስፖርት ጋዜጠኝነት በመስራት ያለውን አቅምና ተፈላጊነት አሳድጓል፡፡ የስፖርት ዘገባዎች ይበልጥ እየዳበሩና እየተወደዱ በመጡበት በ2006 መጨረሻ ዓ.ም ላይ ብስራት ኤፍ.ኤምን በመቀላቀል ከጣቢያው የስፖርት ክፍል መስራቾች አንዱ በመሆን ሳቢና ተናፋቂ በሆነ አቀራረብ ስፖርትን በመተንተን በዘመናዊው የስፖርት አቀራረብ ላይ ትልቅ አስተዋፆ አበርክቷል፡፡ ከስፖርት ዘገባው  በተጨማሪ "ብስራት መዝናኛ" የተሰኘ የራሱን ሳምንታዊ መዝናኛ ፕሮግራም እያዘጋጀ በጣቢያው ለሁለት አመታት ቆይቶ ወደ አሜሪካ አቅንቷል፡፡ በሀገረ አሜሪካ ከስራ ጎን ለጎን መሴ ሪዞርት ለተሰኘው መሰናዶ የኢትዮጵያዊያንን ኑሮና አስደናቂ ታሪኮችን በማዘጋጀት ሰርቷል ፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ለታምሩ ጋዜጠኝነት በደሙ ውስጥ ያለ ሙያ እንጂ በቀላሉ የሚለቅ ነገር አለመሆኑ ነው። በግሉ የደረሱበትን ጫናዎች ተቋቁሞ ራሱን ለሙያው አሳልፎ በመስጠት የራሱን አሻራ አሳርፏል፡፡ አሁን መፅሃፍትን ፅፎ ለአንባቢያን ለማድረስ እየተጋ ይገኛል፡፡

 ታምሩ አለሙ ፣ከ15 በላይ ሀገራት ላይ በመሄድ በአለምአቀፍ እና አህጉር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ላይ ተገኝቶ በቀጥታ ስርጭት በመዘገብና በቅንብር መልክ በማዘጋጀት ይታወቃል ፡፡ ከእነዚህም መካከል ፡- ደቡብ አፍሪካ የአፍሪካ ዋንጫን፤ ኳታር፣ ቤልጂየምና አሜሪካ ላይ ዳይመንድ ሊግን፤ ዱባይ የአትሌቲክስ ውድድሮችን፤ ስፔን የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግን፤ አልጄሪያና ኮንጎ የአፍሪካ ዋንጫና የአለም ዋንጫ ማጣሪያዎችን በመዘገብ ለአድማጭ አቅርቧል። በዘገባዎቹ ለሀገር ውስጥ ስፖርት ትኩረት በመስጠት፣ ባለድርሻ አካላትን በማወያየት፣ አዳዲስ ስፖርተኞችን በማስተዋወቅ፣ የስፖርቱን ችግሮች በማጋለጥና የመፍትሄ ሀሳቦችን በመስጠት አስተዋፅኦ አበርክቷል። ከተለመደው የዘገባ ልምድ በመውጣትም የፈጠራ አቅሙን ተጠቅሞ ስራዎቹን አየር ላይ ይዞ በመምጣት መነጋገሪያ የሚሆኑና በአድማጭም ዘንድ የማይዘነጉ ስራዎችን ሰርቷል፡፡

ያገኛቸው ዕውቅና ና ሰርተፍኬት

  • ያለውን እውቅናና መልካም ስም ለበጎ አላማ በማዋል በግሉና ሌሎችን በማስተባበር   

   የተቸገሩ ሰዎችን በመርዳቱ፣ በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ በተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች

    በመሳተፍ የምስክር ወረቀት

    • ከኦሊምፒክ ኮሚቴ የለንደን ኦሊምፒክ የመፅሄት አዘጋጅ ሆኖ በመስራቱ የምስጋና     

       ሰርተፍኬት

     •ከአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሻምፒዮናዎችን በመዘገብ የምስጋና ሰርተፍኬት

     •ከፌደራል ስፖርት ኮሚሽን በጋዜጠኞች የአቅም ማጎልበት ስልጠናዎች በመሳተፍ   

         ሰርተፍኬት

• ከአዲስ አበባ እግርኳስ ፌዴሬሽን ለከተማው ስፖርት እድገት በማበርከት ሰርተፍኬት ከአዲስ ከተማ ክፍለከተማ ለክፍለከተማው ስፖርት አስተዋፅኦ በማድረግ የምስጋና ሰርተፍኬትና ዋንጫ

• ሀይስኩል በሚኒሚዲያ ሰርተፍኬቶች ፣ ከዲላ ዩኒቨርስቲ "መቅረዝ" የኪነጥበብ ማዕከል በአባልነትና በአመራርነት ሰርተፍኬት

• ከሬድዮ ፋና አጫጭር ኮርሶች ስልጠና ሰርተፍኬት

  ከሬድዮ ፋና የአመራርነት ስልጠና ሰርተፍኬት

• ከሬድዮ ፋና ከስፖርት ክፍሉ የተሻለ አፈፃፀም በማሳየት እድገትና የምስጋና ደብዳቤዎች

መዝጊያ: ታምሩ አለሙ የልጅነት ህልማቸውን ካገኙ እድለኞች አንዱ ነው፡፡ እድለኛ ብቻ ሳይሆን አቅሙን ሳይቆጥብ ከጽኑ የሙያ ፍቅር ጋር ለሀገሩ የተሻለ ነገር ለማቅረብ ሙከራ አድርጓል፡፡ በ14 አመት የሚድያ ቆይታ የራሱን ቀለም ለመፍጠር ሞክሮ ተሳክቶለታል፡፡ በተለይ ስፖርትን እንደመዝናኛ በመቁጠር አድማጭ አንባቢ የተከሸነ እና ያማረ መረጃ እንዲያገኝ በማድረጉ አድማጭ አንባቢ ሊዘነጋው አይችልም፡፡ ታምሩ በዚህ የሚያቆም ወይም የሚረካ ሳይሆን ከዚህ በላይ አቅሙን በመጨመር ለሙያው የተፈጠረ መሆኑን ያስመሰክራል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆችና የቦርድ አባላት የታምሩ ታሪክ እንዲሰነድ ከውሳኔ ላይ ስንደርስ የራሱን ቀለም ለመፍጠር ያደረገውን ጥረት በማየት ነው፡፡ ትናንት ታምሩ የአለምነህ አድናቂ ነበር፡፡ መጪው ትውልድ ደግሞ ከታምሩ አንዳች ቁምነገር ይቀስም ዘንድ ታምሩን ከታሪክ መዝገብ ላይ አኑረነዋል፡፡ ወደፊት አስተዋጽኦ ሲጨምር እንጨምራለን፡፡ እስከዚያው ዛሬ እሁድ ሰኔ 27 2013 ታምሩን እንካችሁ ብለናል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች