57. ስሜነህ መኮንን ዘለቀ-SEMENEH MEKONNEN ZELEKE
እነማን
ነበሩ?
ጠንቃቃው አርታኢ-ስሜነህ መኮንን ዘለቀ
ህይወቱ ካለፈ ዛሬ ሰኔ 28 2013 16 አመት አለፈው፡፡ በበሳል ጋዜጠኝነቱ ብዙዎች መስክረውለታል፡፡ የጀማሪ ጋዜጠኞችን ጽሁፍ በማቃናት መልካም ጅምር አሳይቷል ይባልለታል፡፡ ጋዜጠኛ እና አርታኢ ስሜነህ መኮንን ዘለቀ፡፡
ይህ ሰው በ57 አመቱ ህይወቱ ቢያልፍም በዜና አጻጻፍ ፣ በአርትኦት ስራና በበሳል መምህርነቱ ለሀገር አንድ ትልቅ አሻራ ትቶ ያለፈ ነው፡፡ ‹‹የጋዜጠኝነት ሀሁ›› የተሰኘውን መጽሀፍ የጻፈና የአርትኦት ስራን በብቃት ያከናወነ ሲሆን ከእግሩ ስር የተማሩም ለስኬት በቅተዋል፡፡ በዚህ የዊኪፒዲያ ገጽ
ሊረሱ የማይገባቸው ሰዎችን እናስታውሳለን፡፡ ትልቅ አሻራ ያስቀመጡ
ጠንካራ ሰዎችን፤ ብዙ ሚድያ ያልዳሰሳቸው በህይወት የሌሉ ባለሙያዎችን እንዘክራለን፡፡ ዛሬ የምንሰራው ትናንት ታላላቆቻችን ባስቀመጡልን መስመር ወይም ቦታ ስለሆነ ስሜነህ መኮንንን ስናስታውስ ለሀገሩ ላበረከተው
ታላቅ ተግባር እውቅና እየሰጠን ነው፡፡ በህይወት ባይኖርም የሰራቸው ስራዎች ህያው እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡ ይህ ሰው በህይወት ቢኖር የ73 አመት አዛውንት ይሆን ነበር፡፡ ለዚህ ሰው እንደባህላችን አንቱታ እንደሚገባው እናምናለን፡፡ ነገር ለወጣቶች ቅርብ ፤ ለባልደረቦች ቀለል ብሎ የሚታይ በመሆኑና ጋዜጠኛ እና የጥበብ ሰው አንቱ አይባልም የሚለውን መርህ አንግበን ስሜነህን እንደቅርብ ሰዋችን አንተ እያልን ታሪኩን እናቀርባለን፡፡
በህይወት የሌሉ ነገር ግን ለሀገራቸው
አሻራ አኑረዋል ብላችሁ ያመናችሁባቸውን ባለሙያዎች ጠቁሙን፡፡ በtewedajemedia@gmail.com፡፡ ለመሆኑ ስሜነህ መኮንን ዘለቀ ማነው?
ትውልድ
እና ልጅነት
እናቱ
ወይዘሮ አመለወርቅ በዛብህ ሲባሉ አባቱ ደግሞ አቶ መኮንን ዘለቀ ይባላሉ፡፡ የተወለደውም ጥር 19 1940 ነበር፡፡ የልጅነት ጊዜውን ገዳም ሰፈር ወይም በተለምዶ ጣሊያን ሰፈር በሚባለው አካባቢ ያሳለፈ ሲሆን ያደገውም ከእናቱ
ጋር ነው፡፡ የአንደኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞው የተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ያጠናቀቀ ሲሆን
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም ለ 1 አመት ያህል ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡
ወደ ሚድያ እና ጽሁፍ አለም
ስሜነህ ገና በወጣትነቱ ለተረትና ምሳሌ ብሎም ለስነ-ቃሎች የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ የንባብ ፍቅሩም የጀመረው ገና በወጣትነቱ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ እየተከታተለም ማታ ማታ የተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ውስጥ የ8ኛ እና የ9ኛ ክፍል ተማሪዎችን አማርኛ እና ሂሳብ ያስተምር ነበር፡፡ በመቀጠልም በኮሎኔል ሙላቱ አማካይነት የክቡር ዘበኛ የሬድዮ መገናኛ ውስጥ በመቀላቀል በትርጉም ስራ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ በ21
አመቱ ማለትም ከመስከረም 21 1961 ጀምሮ ለ2 አመታት በሬድዮ መገናኛ ውስጥ በትጋት የተሰጠውን ሃላፊነት በብቃት ሲወጣ ነበር፡፡
ከ1963-1967 ለ 4 አመታት በኢትዮጵያ ሬድዮ ተቀጥሮ በተርጓሚነት በሬድዮ መምሪያ ውስጥ ያገለገለ ሲሆን ከ1967-1969 ባሉት ጊዜያትም በአማርኛ ዜና ምክትል አዘጋጅነት
አገልግሏል፡፡
በዚህ የስራ ቆይታውም በሀንጋሪ የጋዜጠኝነት ስልጠና ወስዶ ዲፕሎማ ለማግኘት ችሏል፡፡
ከሀንጋሪ መልስ ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመዘዋወር
በረዳትና በአዘጋጅነት ከ1969-1977 ለ 8 አመታት
ያለ አንዳች እረፍት ሙያውን በመውደድ እና ለሙያው አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፈል አገልግሏል፡፡ በ1977 ወደ ፕሬስ መምሪያ ተዘዋውሮ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ከ1977-1986 ድረስ አገልግሏል፡፡
ኢዜአ
በመጨሻም ፤ ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተመልሶ የብሮድካስት ሞኒተሪንግ ዴስክ ዋና አዘጋጅ በመሆን ለጋዜጠኝነት ሙያ መጎልበት የድርሻውን ሚና ስለመወጣቱ በስፋት ይነገርለታል፡፡ በተለይ ደግሞ የጋዜጠኝነት ሀሁ የተሰኘውን መጽሀፍ በጥሩ መልኩ ያዘጋጀና የአርትኦት ስራውንም በአርኪ ሁኔታ ያከናወነ የሙያው አባት ነው፡፡ይህ መጽሀፍ በ1993 ለኢዜአ 60ኛ አመት ክብረ-በአል የታተመ ሲሆን ዛሬ ድረስ ብዙዎች በሙያቸው ላይ ለማደግ የእውቀት ክህሎት የሚያገኙበት የስሜነህ የድካም ፍሬ የታየበት የህትመት ውጤት ነው፡፡
መገናኛ
ብዙሀን ማሰልጠኛ
ስሜነህ በሚድያ ስራ በጊዜው ከ30 አመት በላይ ልምድ ያካበተ በመሆኑና በስራውም በብዙዎች የተደነቀ ስለነበር በመገናኛ ብዙሀን ኢኒስቲትዩት እንዲያስተምር ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እውቀቱን ለአንድም ጊዜ ሳይሰስት ማካፈሉን
ያስተማራቸው የሚናገሩት ነገር ነው፡፡ ከማስማሩም ባሻገር በርካታ ጋዜጠኝነት ለማሳደግ የሚረዱ የጥናት ወረቀቶችን ለማቅረብ ችሏል፡፡
ልዩ
ክህሎትን የተላበሰ
አርታኢ-
አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማል፤ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ መጣጥፍ አቅራቢ በነበሩ ጊዜ ስሜነህ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ ስሜነህ በአቶ ተሾመ አባባል ለወጣት ጀማሪ ጋዜጠኞች እድል የሚሰጥ ንፉግ ያልሆነ ሰው ነው፡፡ በስሜነህ አበረታች ቃላት ሞራላቸው በሚገባ ተገንብቶ ጥሩ ጋዜጠኛ የሆኑ በርካታዎች ናቸው፡፡ አቶ ተሾመ ብርሀኑ የበርካታ መጽሀፎች ደራሲና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ከ2000 በላይ ጽሁፍ የታተመላቸው ሰው ሲሆኑ የስሜነህ ጽሁፍን የማቃናት ችሎታ ሁል ጊዜም ግርም ይላቸዋል፡፡ በጊዜው በስሜነህ ስር ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ስሜነህ ጽሁፋቸውን ቢያይላቸው እና ተገቢ አርትኦት ቢሰራላቸው ይመርጡ እንደነበር አቶ ተሾመ ይናገራሉ፡፡
ለማዳመጥ
የተፈጠረ-የማይኮፈስ
ስሜነህ
ወጣት የሆኑ የሚድያ ሰዎችን በእርጋታ የማስረዳት ልዩ ክህሎትን የተላበሰ ብቻ ሳይሆን ለማዳመጥም የታደለ ሰው ስለነበር ይህ ክህሎቱ ጥሩ ዋና አዘጋጅ እንዲሆን አስችሎታል፡፡
ስሜነህ ለአንድ ጋዜጠኛ እስቲ በዚህ ርእሰ-ጉዳይ ጻፍ ብሎ ሀሳብ ለመስጠት የሚችል ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ሲያደርግ
ራሱን እንደዋና አዘጋጅ ወይም አለቃ ሳይኮፍስ በትህትና መስጠት ያለበትን ሀሳብ ይለግሳል፡፡
ከታናናሾቹም ጋር ወርዶ ቡና ለመጠጣት የሚቀለውና የማይከብድ መልካም ሰው መሆኑን አብረውት የሰሩት
ይህን ባህሪይ ወይም ሰብእና እንደ መልካም ጎን ይይዙለታል፡፡
በየካቲት መጽሄት ላይ በዋና አዘጋጅነት ለአመታት የሰሩት አቶ ጸጋዬ ሀይሉ ተፈራም የስሜነህን በሳል የሚድያ ሰውነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡
ስሜነህ ለህትመት ሚድያ የተፈጠረ ነው ሲሉም በሀገራችም የዜና እና የህትመት ስራ
ታሪክ ውስጥ የራሱን ትልቅ አሻራ ያኖረ መሆኑን በሙሉ አንደበታቸው ይመሰክራሉ፡፡ አብሬው በሰራሁበት ዘመናት ከሰው ተግባቢ፤ ደግ እና ጥሞና ሰጥቶ የሚያዳምጥ ሰው መሆኑን ግንዛቤ አግኝቻለሁ ብለዋል አቶ ጸጋዬ ፡፡
አጎቴን
እወዳለሁ
የስሜነህ መኮንን የእህት ልጅ ወይዘሮ ሸዋን ግዥውዳምጤ ደግሞ ለአጎቴ ለስሜነህ
የተለየ አክብሮትነ ፍቅር አለኝ በማለት ከ 16 አመት በፊት በአጸደ ስጋ ስለተለየው ጋዜጠኛ ማስረዳታቸውን
ይቀጥላሉ፡፡ ያኔ ጣሊያን ሰፈር ስሜነህ ያሳለፋቸው የወጣትነት ዘመናት አይረሴ ነበሩ ሲሉ ወይዘሮ ሸዋንግዥው 40 አመት ወደ ኋላ ተጉዘው ዘመኑን በትዝታ መነጽር ለማየት ይፈልጋሉ፡፡ ለትንሹ ለትልቁ ደግ የነበረው አጎቴ ስሜነህ የ16ኛ አመት ሙት አመት መታሰቢያው በዚህ መልኩ መዘከሩ ለቤተሰቡ ትልቅ የማስታወሻ አጋጣሚ ነው በማለት ይህ አጭር ታሪኩ መቅረቡን አድንቀዋል፡፡ ስሜነህ ላበረከተው ታላቅ ውለታ መንግስትም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡
በዜናዎቹ
ላይ ህይወት የሚዘራ
አቶ ይልማ ሀብተማሪያም ‹‹…ስሜነህን ከ1990 ጀምሮ አውቀዋለሁ›› ይላሉ፡፡ ስሜነህ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአዲስ አበባ ዜና ዴስክ ሃላፊ በነበረ ጊዜ አቶ ይልማ ሪፖርተር ነበሩ፡፡ ታዲያ ስሜነህ በጊዜው ሪፖርተሮቹ እነ ይልማ ይሰሯቸው ለነበሩ ዜናዎች በእንዴት ያለ መልኩ ህይወት ይዘራባቸው እንደነበር ይታወስ ነበር፡፡ በኤዲቲንግ ከፍተኛ ክህሎት የነበረው ስሜነህ እምነት የጣለበትን ጋዜጠኛ አምኖ በማሰማራት እያበቃ ያሰራ እንደነበር አቶ ይልማ ያስታውሳሉ፡፡
‹‹….. እምነት ጥሎ ወደ መስክ ካሰማራቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እኔ ራሴ ነኝ ›› ሲሉ አቶ ይልማ ራሳቸው ያስተዋሉት የስሜነህ ልዩ ክህሎት ላይ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡
ስሜነህ መኮንን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን
የእውነት ኢዜአ እንዲሆን ካስቻሉት በጣት ከሚቆጠሩ ጋዜጠኞች አንዱ እንደነበር ብዙዎች አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡ ስሜነህ ወደ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በተዛወረበትም ጊዜ ለጋዜጣዋ ህይወት የሰጠ ሰው
እንደነበር በቅርብ አብረውት የሰሩት ያስረዳሉ፡፡
ታደሰ ሙሉነህ፤ ዳሪዮስ ሙዲና
ጥላሁን በላይ የስሜነህ የቅርብ ጓደኞች የነበሩ ሲሆን 3ቱም በአሁን ሰአት በህይወት የሌሉ ናቸው፡፡ ከስራ ሲመጣ በእረፍት ቀናት ሳይቀር ብዙ መስራት ልምድ ያደረገው ስሜነህ የንባብ ክህሎቱ የዳበረ ነበር፡፡
ቤተሰባዊ ህይወት
ስሜነህ መኮንን በ1968 ከወይዘሮ አልማዝ ሙላቱ ጋር ጋብቻን መስርቶ 2 ሴቶችንና አንድ ወንድ ልጅ ያፈራ ሲሆን ስማቸውም ሶስና ስሜነህ ፤ ዘላለም ስሜነህ እና ሰላም ስሜነህ ይባላሉ፡፡
ሚድያዎች ስሜነህ ዘክሩት-በተለይ ኢዜኤ እና ፕሬስ
ገና
ብዙ ሊሰራ ሲችል በ57 አመቱ ሰኔ 28 1997 ላይ
ለህልፈት የተዳረገው ስሜነህ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ላይ አንድ ትልቁ ጡብ ያስቀመጠ ተብሎ ሊወሳለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ በተለይ ከ1970ዎቹ
መጀመሪያ አንስቶ እስከ 90ዎቹ ድረስ በሀገሪቱ ለመጣው የዘመናዊ ጋዜጠኝነት ለውጥ የስሜነህ እጅ አለበት፡፡ ስሜነህ መኮንን የዛሬ 16 አመት ሰኔ 28 ነበር ህይወቱ ያለፈው ፡፡
የኋላው
ከሌለ የለም የፊቱ
መዝጊያ: ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደስሜነህ አይነት ደማቅ አሻራ አኑረው ነገር ግን በህይወት የሌሉ ከዋክብት ሰዎችን
በዚህ ዊኪፒዲያ የመዘከር መርሀ-ግብር አለው፡፡ ሀገር ያደገችው በቀደሙት ታላላቆች እና አሁን ባሉት ጀግኖች ነውና የሁሉንም ታሪክ እንደየሚናው ልክ እየነቀስን የሀገር ኩራቶችን መድረኩ ላይ እናመጣለን፡፡ መጪው ትውልድም እንዲያውቃቸው እናደርጋለን፡፡ ከእነዚህ የሀገር ኩራቶች አንዱ ስሜነህ ነው፡፡ ስሜነህን የኢትዮጵያ ሬድዮ ሰዎች ፤ የኢዜአ
ሃላፊዎች ፤ የፕሬስ ድርጅት ሰዎች እንዲያስታውሱት እናሳስባለን፡፡ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ነውና የቀደሙ የሀገር ባለውለታዎችን በዚህ መልኩ እየዘከርን ነውና የስሜነህን የመሰሉ ታሪኮች የሚድያ ሽፋን ቢያገኙ ስንል ሀሳብ እንለግሳለን፡፡ ስሜነህ የሚጠበቅበትን ሰርቷል፡፡ እኛም የመዘከር ሚናችን እነሆ ተወጥተናል፡፡ ሁሉም በየፊናው አንድ ነገር ካቀበለ ኢትዮጵያ ማለት ይህች ናት፡፡ የእኛም አላማ ይህ ብቻ ነው፡፡
ምስጋና: ይህን የስሜነህን ታሪክ እንድንሰራ የመጀመሪያውን ሀሳብ ለሰጠችን ለወይዘሮ አመለወርቅ ወልደኪዳን ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ በመቀጠል የስሜነህ መኮንንን የቅርብ ሰዎች ስልክ በመስጠት ለተባበረን የኢዜአው ደሳለው ጥላሁን፡፡ እንዲሁም ለሰናይት ወልደኪዳን አጠቃላይ ለአቶ ስሜነህ መኮንን ቤተሰቦች ላቅ ያለ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ ምስጋና ለሶስና ስሜነህ ፤ ለዘላለም ስሜነህ እና ለሰላም ስሜነህ እንዲሁም ለአቶ ስሜነህ ባለቤት ለወይዘሮ አልማዝ ሙላቱ ማቅረብ እንፈልጋለን፡
/ ይህ ጽሁፍ ከመነሻው ጀምሮ የተጻፈው እና የተጠናከረው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሲሆን የጥንቅር ቀኑም ዛሬ እሁድ ሰኔ 27 2013 ከሌሊቱ 7 ሰአት ነው፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ