56. ዳንኤል አያሌው ካሳ-  Daniel Ayalew kassa 

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝናኛው ዘርፍ ያሉ ባለሙያዎችን አጭር ግለ-ታሪክ ባለፉት 2 ወራት እያወጣ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ አሁን ደግሞ 1982-1995  በመዝናኛ እና በሬድዮ ድራማ ዘርፍ የበኩሉን ድርሻ ስለተወጣው ስለ ዳንኤል አያሌው ካሳ እናቀርባለን፡፡ ሌሎች ባለሙያዎችንም በመጠቆም ተባበሩን፡፡ tewedajemedia@gmail.com 

                ትውልድ እና እድገት

ዳንኤል አያሌው ካሳ፣  መስከረም 19 ቀን 1957  ነበር የተወለደው፡፡  አባቱ አቶ አያሌው ካሳ እናቱ ወይዘሮ  ዘነበች ወልዴ  ይባላሉ፡፡ የተወለደውም በአዲስ አበባ ከተማ ነው፡፡

 ዳንኤል 7ወር ህጻን በነበረበት ጊዜ ነበር - አባቱን ያጣው :: በዚህም ምክንያት ከአባቱ ቤተሰቦች አንዷ ወይዘሮ ድንኳኔ ፋንታዬ ወስደው አሳድገውታል፡፡ አባቱን ባያገኝም - ባለሁለት እናት ሆኖ ነው ያደገው፡፡

      እንደማንኛውም የጊዜው ህጻናት በአካባቢው በሚገኝ የቄስ ትምህርት ቤት ነበር -በቅድሚያ ፊደል የቆጠረው ::ከቄስ ትምህርት ቤት በኋላ ከመኖሪያው ብዙ ሳይርቅ በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤት ነበር -መደበኛውን ትምህርት የጀመረው -እስከ 12 ክፍልም የቀጠለው ፡፡

                  ቴአትር ጥበባት

    1978 .  መጀመሪያም ላይ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት የቲያትር ጥበባት የትምህርት ክፍልን ተቀላቅሏል  ፡፡ በዚህ ክፍል ነበር ታላላቆቹን መምህራኑን ያገኘው  መንግስቱ ለማ፣ ተስፋዬ ገሰሰ፣ ደበበ ሰይፉን  እንዲሁም በወቅቱ ወጣት መምህራን የነበሩት ማንያዘዋል እንደሻው ፣በላይነህ አቡኔ፣ አቦነህ አሻግሬ ፍስሃ በላይ ይማም እንዲሁም የውጭ ሃገር አስተማሪዎችም ነበሩት  

በተማሪነት ዘመኑ በተለይ በትወና ላይ የተሳካለት እንደነበር የሚመሰክሩለት አሉ    የኪዩፒድ ቀስት   የሚባ አንድ በማህበረሳዊ ጥናት ላይ የተመረኮዘ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ህይወትን የተመለከተ ድራማ ላይ ከመሪ ተዋንያን አንዱ ነበር ፡፡    ፟፟   አባትየው  ፟፟    የስዊዲናዊው ኦገስት ስትሪንበሪ አዛማች ትርጉም ተውኔት ላይም የተጫወተው ይታወሳል ለተመልካች ባይቀርብም የኒኮላይ ጎጎል  ዋናው ተቆጣጣሪ  ትያትር ላይም ተጫውቷል  በዩኒቨርሲቲ የመጨረሻ ተርም ላይ የማክሲም ጎርኪ ፔቲ ቡርዥዋ ሌላው የተሳካ ትወና ያደረገበት ነበር::







               ኢትዮጵያ ሬድዮ

   1981 መጨረሻ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አጠናቆ በተከታዩ አመት መጀመሪያ ላይ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ኢትዮጵያ ሬድዮ ተቀጠረ ።በኢትዮጵያ ሬድዮ ስቱዲዮ ስልጠና ላይ

በሬዲዮ የመጀመሪያ ስድስት ወራት በታዋቂው ጋዜጠኛ ጌታቸው ሃይለማሪያም ስር በዜናና መዋእለ ዜና ዋና ክፍል ውስጥ መሰረታዊ የሬድዮ ጋዜጠኝነት ስልጠናና ልምምድ ለማድረግ ችሏል፡፡   ከዚህ ጊዜ በኋላም በተለያዩ ጊዜያት  በሬዲዮ ውስጥም ሆነ ውጪ የተለያዩ ስልጠናዎችን አግኝቷል፡፡ከሃገር ውጭም በጀርመን ድምጽ በኮሎኝ 10 ወራት በተግባር ልምምድ ጭምር ያደረገው ስልጠና በጣም ጠቃሚ እንደነበር ደጋግሞ ያነሳዋል::

  ዳንኤል ከጌታቸው ደስታ ጋር ዶቼ ቬሌ በቀጥታ ስርጭት 1986 ግድም የሰራ ሲሆን ይህም ምስል ከዚህ ጽሁፍ ጋር አብሮ ወጥቷል፡፡

       በኢትዮጵያ ሬድዮ የአማርኛ ፕሮግራም ክፍል 1982 አንስቶ ስራ ለቆ ወደ ፖፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር እስከገባበት 1995 ድረስ ከፕሮግራም አስፈጻሚነት አንስቶ የተለያዩ ፕሮግራሞችን ሲያዘጋጅና በኤዲተርነትም ሲመራ ነበር፡፡

   የተለያዩ የሙዚቃ ፕሮግራሞችን በየሳምንቱ አቀናብሯል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት

ሰኞ ምሽት ቆየት ያሉ የአማርኛ ሙዚቃዎች

ቅዳሜ ምሽት የውጭ ሙዚቃዎች

እሁድ ምሽት የሃገር ውስጥና የውጭ ለስላሳ ሙዚቃዎችና የዘፈን ምርጫ አዘጋጅም ነበር፡፡

     የወጣቶች ፕሮግራም አዘጋጅና ኤዲተርም ሆኖ አገልግሏል፡፡

 ዳንኤል የወጣቶች ፕሮግራም አመታዊ በአል ሲያከብር ከአዘጋጆቹና ከቴክኒክ ባለሙያዎቹ ጋር  በአንድ ላይ 1985 የተነሱትን ምስል ስንመለከት ያንን ዘመን ወደ ኋላ በትዝታ  እንድናይ የሚያደርገን ነው፡፡ ይህ ፎቶ 28 አመት ወደ ኋላ የሚወስደን ሲሆን በምስሉ ላይም የዛን ጊዜዎቹን  ስመጥሮች እናገኛለን፡፡ አስካለ ተስፋዬ፣ደረጀ ሀይሌ ብርሀኑ ገብረማሪያምና ዘውዱ ግርማ  በምስሉ ላይ ተቀምጠው የሚታዩ ሲሆኑ  ቆመው ያሉት ደግሞ ቴክኒሻን ሳህሉ በቀለ ተካ ወልደሀዋሪያት/ የቴክኒክ ሱፐር ቫይዘር እንዳልካቸው ፈቃደ ዮናስ ኪቲላና ባለታሪኩ ዳንኤል አያሌው ናቸው፡፡  በዚህ ምስል ላይ ያሉ በተለይ ባህር ማዶ ያሉትንና ሀገር ውስጥ ሆነው  የቀድሞ ትዝታ ሊያወጉን የሚችሉትን ብትጠቁሙን ደስታውን አንችለውም ፡፡

   ዳንኤል የኪነ- ጥበባት ምሽት ፕሮግራም ከመጀመሪያው እስከ ጣቢያው ስንብት ድረስ በፕሮግራሙ አዘጋጅነትና መሪነት የሰራበት ነው፡፡ የኪነ-ጥበባት ምሽት በጣቢያው ከቆዩ ፕሮግራሞች አንዱ ሲሆን በቀደመው ጊዜ ብዙ የሃገሪቱ ታላላቅ የጥበብ ሰዎች   የተሳተፉበት ተናፋቂ ፕሮግራም ነበር፡፡ ዳንኤልም ወደዚህ ፕሮግራም የመጣው ፈልጎ ነው፡፡ 1984 ዓም መጀመሪያ ላይ ፕሮግራሙን የመምራት ዕድል እንዳገኘ የመጀመርያ ተግባሩ የነበረው ከወቅቱ አዘጋጆች ጋር በመሆን ፕሮግራሙ በኪነጥበባት ጉዳዮች ዙርያ ብቻ እንዲያተኩር የሚያስችለውን አቅጣጫ ማመላከት ነበር  ፡፡ ታላላቅ የኪነጥበብ ሰዎች በተለይም ኢትዮጵያውያን ከያንያን  ይዘከሩበታል- ይደነቁበታል  በተቻለ መጠን ሁሉም አይነት ጥበባት ይስተናገዱበታል፤፡ ኪነጥበባዊ ሃገር አቀፍ ጉዳዮች ይሸፈናሉ፡፡

          ዳንኤል   በዚህም መሰረት ነበር ፕሮግራሙን ሲያዘጋጅና ሲመራ የነበረው  እጅግ የበዙ ባለሙያዎች የፕሮግራሙ እንግዳ ነበሩ -ደራሲያን አዘጋጆች ተዋንያን ሙዚቀኞች ሰአሊያን ኪነህንጻ ባለሞያ ወዘተርፈ አነጋግሯል፡፡ ስራቸውንም አስተዋውቋል፡፡ እንዲሁም ታላላቅ ኪነጥበብ ነክ እንቅስቃሴዎች በየተካሄዱበት እየተገኘ ዘግቧል -በፕሮግራሞቹ አቀናብሮአል :- ለመጠቃቀስ ያህል

የባህል ፖሊሲው ከቀረጻው አንስቶ እስከ ጸደቀበት ድረስ የስነጥበባትና የመገናኛ ብዙሃን የሽልማት ድርጅት በተከታታይ ከተካሄዱት ውይይቶች አንስቶ እስከ ሽልማቱ ድረስ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቋንቋ ጥናት ፋካልቲ አመታዊ ጉባኤ ዳሰሳ ፣የተለያዩ የግጥም ምሽቶች የሙዚቃ ኮንሰርቶች የስዕል ኤግዚቢሽኖች የትያትርና የመጻህፍት ምረቃዎችና የመሳሰሉት የፕሮግራሙ  ርዕሰ ጉዳዮች  ነበሩ

   ከዚህ ሌላ አስተዋጽኦ ያደረገበት  የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም ነበር እዚህም የፕሮግራሙ አዘጋጅና ኤዲተር ነበር

የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም የብዙ ወጣቶችን አይን የገለጠ ሲሆን የአጭር ልብወለድ ትረካ፣ መጣጥፎች (ወጥና ትርጉም)፣ግጥሞች፣ጭውውቶችና ድራማዎች የሚቀርቡበት አዝናኝ ፕሮግራም ነው ። 











            የቅዳሜ መዝናኛ

   የቅዳሜ መዝናኛ፣ በአድማጩም ዘንድ በጣም ተናፋቂ ነበር ለዚህ እንደማስረጃ ሊሆን የሚችል አንድ የበጎ ፈቃደኞች ኪዳን የተባለ የሽልማት ድርጅት የህዝብ ድምጽ አሰባስቦ የአመቱ ምርጦች ሽልማት 1994 . በዋቢሸበሌ ሆቴል ባካሄደበት ጊዜ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም የዓመቱ ምርጥ መዝናኛ ተብሎ ተመርጦ ነበር ።ከአዘጋጆቹ ጋር በመሆን ዋንጫውን የተቀበለው ዳንኤል ነበር።

          እርግጥ የቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም  የተሳታፊዎች ፕሮግራም ቢባል ስህተት አይሆንም   እጅግ ብዙዎች ያላቸውን ይዘው  ለመሳተፍ በየሳምንቱ ይቀርባሉ- በነጻ ትንሽም ቢሆን ክፍያ የነበረው ድራማው ነው - እሱም ቢሆን ከታክሲ የሚያልፍ አልነበረም

        የፕሮግራሙ አዘጋጆች የሚቀርቡ ዝግጅቶችን (ጽሁፎችን )የመምረጥ የመቅረጽና አቀናብሮ ለህዝብ የማድረስ ውክቢያ ውስጥ ነው ስራቸውን የሚያከናውኑት ለፕሮግራሙ ከሚደርሱት ዝግጅቶች ብዛት አንጻር ፈጣን ውሳኔዎች ይጠይቃሉ፡፡ በተለይም ዳንኤል ድራማው ላይ ዋና ትኩረቱን አድርጎ ነበር

         የሬዲዮ ድራማ ዝግጅት የሚጀምረው ለፕሮግራሙ የሚሆን ድራማ ከመምረጥ ነው ፡፡ከባዱና ጊዜ የሚወስደውም  ይህ እንደሆነ ዳንኤል ይገልጻል። በጣም የበዛ የተውኔት ጽሁፍ ይቀርባል ።ያልተመረጡትን  መመለስ አታካች ነበር ።የኤዲቶርያል ፖሊሲውም አንዱ መመዘኛ ነበር ።በጣም አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር ተውኔቶቹን ታይፕ ማድረግ/መተየብ/ አይቻልም ነበር

ከዚህ ጊዜ ቀጥሎ ተዋናይ መመደብ ይከተላል፡፡ ከዚያ በፊት ከነበረው በተለየ ሁኔታ በየድራማው ተዋናይ እየለዋወጡ ማቅረብ ተጀምሯል፡፡

          የተዋናይ መረጣ አንዱ ፈተና ነበር፡፡  እንደሚታወቀው የራዲዮ ድራማ ይደመጣል እንጂ አይታይም፡፡ ስለዚህም ድምጽ ወሳኝ ነው የአንዱ ድምጽ ከሌላው በጉልህ ተለይቶ የሚታወቅ መሆን አለበት ።ጥሩ ማንበብ የቻለ ሁሉ የራዲዮ ድራማ ተዋናይ አይሆንም፡፡

   ራድዮ ድራማ ለአድማጩ ሳቢ ካልሆነ ተከታታይ አያገኝም ብቻ ሳይሆን ሰዉ ሬድዮኑን ሊዘጋ ወይም ጣቢያ ሊለውጥ ይችላል፡፡ ስለዚህም ነው የአዘጋጁ ሃላፊነት ትልቅ የሚሆነው ።የድራማውን ዋና ጭብጥና እንዲሁም እያንዳንዱ ተዋናይ የሚጫወተውን ገጸ -ባህሪይ ጊዜ ወስዶ ማጥናት ባለመቻሉ የተነሳ   ቢያንስ አንድ ጊዜ ከቀረጻ በፊት በሚደረገው  ልምምድ  አዘጋጁ የመግለጽ የማብራራት ሃላፊነት አለበት እናም ካለእረፍት በየሳምንቱ በዚህ መንገድ ነበር ድራማ የሚዘጋጀው ቅዳሜ መዝናኛ ፕሮግራም በአንድ ክፍል ወይም እስከአራት ክፍል የሚደርሱ ድራማዎች ነበሩ የሚቀርቡበት ።ይህ በዚህ እንዳለ እሁድ ጠዋት የሬድዮ ፕሮግራም ላይም ያሉትን ረጅም ተከታታይ ድራማዎች በተደራቢነት እንዲያዘጋጅ ሆኗል፡፡

እዚህ ደግሞ በህዝብ ዘንድ ተወዳጅ የነበሩትን እንደ ጥንዶቹ ፣የማእበል ዋናተኞች የልደት ጧፍ የመሳሰሉት ይታወሳሉ።ዳንኤል ካዘጋጃቸው የሬድዮ ድራማዎች መካከል በአድማጭ ዘንድ የሚታወቀው  የልደት ጧፍ እንዲሁም የማእበል ዋናተኞች ይጠቀሳሉ፡፡

                          የቀን ቅኝት-አዘጋጅ                                                                       

ዳንኤል 1994  ዓም መጨረሻ ከኢትዮጵያ ራድዮ ተሰናብቶ የራድዮ ድራማን ይሁነኝ ብሎ ለህብረተሰብ ማስተማርያነት ሊያውል የተቋቋመው መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት Population Media Center የአማርኛ ራድዮ ድራማ አዘጋጅ ሆኖ ተቀጠረ  

    በጊዜው ባነሳው ጭብጥ ፣ባካሄደው ጥናት ፣በተሳታፊ ብዛት/ በርካታ ደራሲያንና ተዋንያን /አጥኚ ባለሙያ፣ ጸሃፊ ሁሉ ሳይቀር የተሟላለት መሰረቱን አሜሪካ ያደረገው መስርያ ቤት ለሃገራችንም ቢሆን የመጀመርያውን ረጂም ድራማ የቀን ቅኝትን ያስመረቀው በትልቅ ደረጃ ነበር፡፡                                                  

የቀን ቅኝት ድራማ በሳምንት 2 ጊዜ በኢትዮጵያ ራዲዮ እንዲሁም FM 97.1 ሌላ መግቢያ ተሰርቶለት ይተላለፍ ነበር፡፡ ይህም በአይነቱ አዲስ ነበር፡፡ የአድማጩም ከፍተኛ ሁኔታ መጨመር መስርያ ቤቱ ከሚደርሰው የደብዳቤ ጎርፍ መረዳት ይቻላል የሆነ ሆኖ   አዘጋጁ ዳንኤል አያሌው አንድ ዓመት ያህል ከሰራ በኋላ በግል ምክንያት ስራውን ለቆ ስዊድን ኑሮውን አድርጓል ዳንኤል በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን በስዊድን ጉተንበርግ ያደረገ ሲሆን ቤተሰባዊ ሁኔታውን  በተመለከተ ባለትዳር እና 2 ልጆች አባት ነው፡፡

                  ዳንኤል በሌሎች ሰዎች እይታ

ዳንኤል በቅዳሜ መዝናኛ እና በሬድዮ ድራማ አዘጋጅነቱ ብዙዎችን ያፈራ ያበቃ እንዲሁም   አንዳንድ የጥበብ ሰዎችም እንዲያድጉ ዋና ምክንያት ሆኗል፡፡ በአሁኑ ሰአት የራሷን ታዛ የተሰኘ የሬድዮ ፕሮግራም እየሰራች የምትገኘው ጋዜጠኛ ትእግስት በጋሻው ገና ታዳጊ በነበረች ጊዜ ቅዳሜ መዝናኛ ላይ ትሳተፍ በነበረበት ጊዜ ዳንኤል እንድትጽፍ ብሎም በሬድዮ ላይ ተሳትፎ እንድታደርግ ያበረታታት ነበር፡፡ ያኔ በቅዳሜ መዝናኛ ላይ ብዙ ወጣቶች ዳንኤል ጋር ጽሁፍ ይዘው ይመጡ ነበር፡፡ ታዲያ ዳንኤል ትእግስትና ጓደኞቿንም  አይዟችሁ አትፍሩ እያለ በማደፋፈር ጽሁፋቸውን አየር ላይ ያውል ነበር፡፡  በዚህም  ትእግስት የማልረሳው ታላቅ ባለውለታ ነው ስትል ምስጋናዋን ማቅረብ ትሻለች፡፡  ሌላዋ የዳንኤል አቅም ትልቅ ነው ስትል ሀሳብ የሰነዘረችው አርቲስት ሀረገወይን አሰፋ ናት፡፡ ሀረገወይን በቀን ቅኝት ተከታታይ የሬድዮ ድራማ ላይ ስትተውን የዳንኤልን ልዩ የዝግጅት ብቃት አይታለች፡፡ ያንን ሁሉ ሰው አስተባብሮ 2 አመት የቆየ ድራማን መስራት የዳንኤልን ልዩ ክህሎት ያሳያል ስትል ሀረገወይን ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡

                   ስለ ዳንኤል አያሌው-ሰአዳ መሀመድ ከተናገረችው…….

‹‹……….1990/91 በኢትዮጵያ ሬድዮ ቅዳሜ መዝናኛ  ድራማዎች በማቀርብበት ወቅት አዘጋጅ የነበረው ዳንኤል አያሌው ነበር። "ጥልልፎሽ፣ ያበቃ ህልም ያልተደፈነ ጉድጓድ፣ ሶስቱ መስኮቶች እና መክሊት " የተሰኙ የድራማ ስራዎችን አዘጋጅቷል። ዳንኤል ከአዘጋጅነቱም በላይ የድራማ ፅሁፎቼን ገምግሞ የሚያያቸውን ችግሮች እንዳሻሽል አስተያየቱን በመስጠት ያግዘኝ ነበር። በተለይ ድራማ ፅሁፎች ላይ የምጠቀማቸውን ረጃጅም ቃለ -ተውኔቶች በአጭርና ቀለል ባለ ቋንቋ እንድፅፍ ደጋግሞ ይነግረኝ ነበር። በተጨማሪም 30 ደቂቃ መተላለፍ ያለበትን ስክሪፕት መጥኜ  እየተቸገርኩ እስከ 40 ደቂቃ አደርሰው ስለነበር በአንድ ወቅት " ስክሪፕትና ዲያሎግን በሚፈለገው መጠን መጥነሽ ፃፊ እንጂ ሰአዳ! ሌላ ግዜ አትፅፌም እንዴ!" የሚል አስተያየት ሰጥቶኝ ነበር።  ይህ የዳንኤል አስተያየት ዛሬም ድረስ ድራማ ስፅፍ የስክሪፕት ርዝመትንና የዲያሎግ መመጠንን እንዳስብበት አድርጎኛል። ዳንኤል ስክሪፕት ከማቅናት አንስቶ የድራማ ርዕስ ለተውኔቱ ካልመጠነ ርዕሱን እንድቀይር ያደርግ ነበር። በአንድ ወቅት  አንድ የድራማ ፅሁፍ ሳስረክበው  ርዕሱን አይቶ እንድቀይረው ጠየቀኝ። በወቅቱ ምንም ርዕስ ሊመጣልኝ ስላልቻለ " ምንም ርዕስ አልመጣልኝም"  አልኩት። ወዲያው " መክሊት የሚለውን ርዕስ ልስጠው ይስማማሻል? " አለኝ። ተስማማሁ ድራማው ተቀርፆ ሲተላለፍ ርዕሱ መክሊት መሆኑ ተገቢ እንደሆነ ተረዳሁ።  ዳንኤል አያሌው ጀማሪ ፀሐፊ ሆኜ ያገኘሁት ጎበዝ አዘጋጅና መልካም መምህር ነበር።  ዳንኤልን በዚህ አጋጣሚ ማመስገን እፈልጋለሁ።     

መዝጊያ: ትናንት ለሀገራቸው የሰሩ ዛሬ መታወስ አለባቸው፡፡ በህይወት እያሉ ያበረከቱት በዝርዝር እየተነገረ ታሪክ ሊያወሳቸው ይገባል፡፡ ዳንኤል አያሌው 14 አመታት በቆየበት ሙያ አቅሙን ሳይቆጥብ ስራው እና ስራው ላይ ብቻ ትኩረት ሰጥቶ ደከመኝ ሳይል ሰርቷል፡፡ ለእርሱ ብዙ የሰራ ላይመስለው ይችላል፡፡ ነገር ግን 1980ዎቹና 1990ዎቹ በመዝናኛው ዘርፍ የተሳተፉ ሰዎችን ስናይ ዳንኤል የእነርሱ አቅም ሳይቆጠብ እንዲወጣ ማድረጉን እናስተውላለን፡፡ ብዙ የሰሩ ሰዎች  በሚረሱበት እና እከሌ ግን የት ነው ያለው? በሚባልበት ሀገር ዳንኤል አያሌውን ስናቀርብ  ስለሚገባው እና ስለሚችል ነው፡፡ የእናት ሀገር ፍቅሩ ታላቅ እንደሆነ የሚናገረው ዳንኤል ዛሬም የጥበብ ፍቅሩ ውስጡ እንዳለ ነው፡፡ ወቅትና ሁኔታዎች ሲመቻቹ የዳንኤልን የጥበብ ስራ  ማግኘታችን አይቀርም፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች የዳንኤልን ታሪክ  በዚህ መልኩ ስናወጣ መጪው ትውልድና አብረው የሰሩትም እንዲያውቁትና እንዲያከብሩት እንፈልጋለን፡፡ ዳንኤል ባለበት ስዊድን እንዲቀናውና ለጥበቡም አንድ ነገር እንዲያበረክት ምኞታችን ነው፡፡ / ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሰኔ 30 2013 የተጻፈ ሲሆን ጽሁፉም የተጠናከረው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሲሆን ዳንኤልም ከስዊድን ሆኖ ያለፈበትን ታሪክ ተናግሯል፡፡

57. ስሜነህ መኮንን ዘለቀ-SEMENEH MEKONNEN ZELEKE 

  እነማን ነበሩ?

ጠንቃቃው አርታኢ-ስሜነህ መኮንን ዘለቀ

ህይወቱ ካለፈ ዛሬ ሰኔ 28 2013 16 አመት አለፈው፡፡ በበሳል ጋዜጠኝነቱ ብዙዎች መስክረውለታል፡፡ የጀማሪ ጋዜጠኞችን ጽሁፍ በማቃናት መልካም ጅምር አሳይቷል ይባልለታል፡፡ ጋዜጠኛ እና አርታኢ ስሜነህ መኮንን ዘለቀ፡፡

ይህ ሰው 57 አመቱ ህይወቱ ቢያልፍም በዜና አጻጻፍ በአርትኦት ስራና በበሳል መምህርነቱ ለሀገር አንድ ትልቅ አሻራ ትቶ ያለፈ ነው፡፡ ‹‹የጋዜጠኝነት ሀሁ›› የተሰኘውን መጽሀፍ የጻፈና የአርትኦት ስራን በብቃት ያከናወነ ሲሆን ከእግሩ ስር የተማሩም ለስኬት በቅተዋል፡፡ በዚህ የዊኪፒዲያ ገጽ  ሊረሱ የማይገባቸው ሰዎችን እናስታውሳለን፡፡ ትልቅ አሻራ ያስቀመጡ  ጠንካራ ሰዎችን፤ ብዙ ሚድያ ያልዳሰሳቸው በህይወት የሌሉ ባለሙያዎችን እንዘክራለን፡፡ ዛሬ የምንሰራው ትናንት ታላላቆቻችን ባስቀመጡልን መስመር ወይም ቦታ ስለሆነ ስሜነህ መኮንንን ስናስታውስ ለሀገሩ ላበረከተው  ታላቅ ተግባር እውቅና እየሰጠን ነው፡፡ በህይወት ባይኖርም የሰራቸው ስራዎች ህያው እንደሆኑ ይኖራሉ፡፡ ይህ ሰው በህይወት ቢኖር 73 አመት አዛውንት ይሆን ነበር፡፡ ለዚህ ሰው እንደባህላችን አንቱታ እንደሚገባው እናምናለን፡፡ ነገር ለወጣቶች ቅርብ ለባልደረቦች ቀለል ብሎ የሚታይ በመሆኑና ጋዜጠኛ እና የጥበብ ሰው አንቱ አይባልም የሚለውን መርህ አንግበን ስሜነህን እንደቅርብ ሰዋችን አንተ እያልን ታሪኩን እናቀርባለን፡፡  በህይወት የሌሉ ነገር ግን ለሀገራቸው  አሻራ አኑረዋል ብላችሁ ያመናችሁባቸውን ባለሙያዎች ጠቁሙን፡፡ tewedajemedia@gmail.com፡፡ ለመሆኑ ስሜነህ መኮንን ዘለቀ ማነው?

        ትውልድ እና ልጅነት 

 እናቱ ወይዘሮ አመለወርቅ በዛብህ ሲባሉ አባቱ ደግሞ አቶ መኮንን ዘለቀ ይባላሉ፡፡ የተወለደውም ጥር 19 1940 ነበር፡፡ የልጅነት ጊዜውን ገዳም ሰፈር ወይም በተለምዶ ጣሊያን ሰፈር በሚባለው አካባቢ ያሳለፈ ሲሆን ያደገውም ከእናቱ  ጋር ነው፡፡ የአንደኛ እና 2 ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞው የተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ያጠናቀቀ ሲሆን  በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም 1 አመት ያህል ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡

                 ወደ ሚድያ እና ጽሁፍ አለም

ስሜነህ ገና በወጣትነቱ ለተረትና ምሳሌ ብሎም ለስነ-ቃሎች የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ የንባብ ፍቅሩም የጀመረው ገና በወጣትነቱ ነበር፡፡ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱ እየተከታተለም ማታ ማታ የተፈሪ መኮንን ተማሪ ቤት ውስጥ 8 እና 9 ክፍል ተማሪዎችን አማርኛ እና ሂሳብ ያስተምር ነበር፡፡ በመቀጠልም በኮሎኔል ሙላቱ አማካይነት የክቡር ዘበኛ የሬድዮ መገናኛ ውስጥ በመቀላቀል በትርጉም ስራ ሲያገለግል ቆይቷል፡፡ 21  አመቱ ማለትም ከመስከረም 21 1961 ጀምሮ 2 አመታት በሬድዮ መገናኛ ውስጥ በትጋት የተሰጠውን ሃላፊነት በብቃት ሲወጣ ነበር፡፡

1963-1967 4 አመታት በኢትዮጵያ ሬድዮ ተቀጥሮ በተርጓሚነት በሬድዮ መምሪያ ውስጥ ያገለገለ ሲሆን 1967-1969 ባሉት ጊዜያትም በአማርኛ ዜና ምክትል አዘጋጅነት  አገልግሏል፡፡

በዚህ የስራ ቆይታውም በሀንጋሪ የጋዜጠኝነት ስልጠና ወስዶ ዲፕሎማ ለማግኘት ችሏል፡፡

ከሀንጋሪ መልስ ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በመዘዋወር  በረዳትና በአዘጋጅነት 1969-1977 8 አመታት  ያለ አንዳች እረፍት ሙያውን በመውደድ እና ለሙያው አስፈላጊውን መስዋእትነት በመክፈል አገልግሏል፡፡ 1977 ወደ ፕሬስ መምሪያ ተዘዋውሮ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን 1977-1986 ድረስ አገልግሏል፡፡

          ኢዜአ

በመጨሻም ወደ ኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ተመልሶ የብሮድካስት ሞኒተሪንግ ዴስክ ዋና አዘጋጅ በመሆን ለጋዜጠኝነት ሙያ መጎልበት የድርሻውን ሚና ስለመወጣቱ በስፋት ይነገርለታል፡፡ በተለይ ደግሞ የጋዜጠኝነት ሀሁ የተሰኘውን መጽሀፍ በጥሩ መልኩ ያዘጋጀና የአርትኦት ስራውንም በአርኪ ሁኔታ ያከናወነ የሙያው አባት ነው፡፡ይህ መጽሀፍ 1993 ለኢዜአ 60 አመት ክብረ-በአል የታተመ ሲሆን ዛሬ ድረስ ብዙዎች በሙያቸው ላይ ለማደግ የእውቀት ክህሎት የሚያገኙበት የስሜነህ የድካም ፍሬ የታየበት የህትመት ውጤት ነው፡፡ 

        መገናኛ ብዙሀን ማሰልጠኛ

ስሜነህ በሚድያ ስራ በጊዜው 30 አመት በላይ ልምድ ያካበተ በመሆኑና በስራውም በብዙዎች የተደነቀ ስለነበር በመገናኛ ብዙሀን ኢኒስቲትዩት እንዲያስተምር ተደርጎ ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እውቀቱን ለአንድም ጊዜ ሳይሰስት ማካፈሉን  ያስተማራቸው የሚናገሩት ነገር ነው፡፡ ከማስማሩም ባሻገር በርካታ ጋዜጠኝነት ለማሳደግ የሚረዱ የጥናት ወረቀቶችን ለማቅረብ ችሏል፡፡

         ልዩ ክህሎትን የተላበሰ  አርታኢ-  

አቶ ተሾመ ብርሀኑ ከማል፤ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ላይ መጣጥፍ አቅራቢ በነበሩ ጊዜ ስሜነህ የጋዜጣዋ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ ስሜነህ በአቶ ተሾመ አባባል ለወጣት ጀማሪ ጋዜጠኞች እድል የሚሰጥ ንፉግ ያልሆነ ሰው ነው፡፡ በስሜነህ አበረታች ቃላት ሞራላቸው በሚገባ ተገንብቶ ጥሩ ጋዜጠኛ የሆኑ በርካታዎች ናቸው፡፡ አቶ ተሾመ ብርሀኑ የበርካታ መጽሀፎች ደራሲና በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ 2000 በላይ ጽሁፍ የታተመላቸው ሰው ሲሆኑ የስሜነህ ጽሁፍን የማቃናት ችሎታ ሁል ጊዜም ግርም ይላቸዋል፡፡ በጊዜው በስሜነህ ስር ይሰሩ የነበሩ ጋዜጠኞች ስሜነህ ጽሁፋቸውን ቢያይላቸው እና ተገቢ አርትኦት ቢሰራላቸው ይመርጡ እንደነበር አቶ ተሾመ ይናገራሉ፡፡

          ለማዳመጥ የተፈጠረ-የማይኮፈስ 

 ስሜነህ ወጣት የሆኑ የሚድያ ሰዎችን በእርጋታ የማስረዳት ልዩ ክህሎትን የተላበሰ ብቻ ሳይሆን ለማዳመጥም የታደለ ሰው ስለነበር ይህ ክህሎቱ ጥሩ ዋና አዘጋጅ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

ስሜነህ ለአንድ ጋዜጠኛ እስቲ በዚህ ርእሰ-ጉዳይ ጻፍ ብሎ ሀሳብ ለመስጠት የሚችል ሰው ነበር፡፡ ታዲያ ይህን ሁሉ ሲያደርግ  ራሱን እንደዋና አዘጋጅ ወይም አለቃ ሳይኮፍስ በትህትና መስጠት ያለበትን ሀሳብ ይለግሳል፡፡  ከታናናሾቹም ጋር ወርዶ ቡና ለመጠጣት የሚቀለውና የማይከብድ መልካም ሰው መሆኑን አብረውት የሰሩት  ይህን ባህሪይ ወይም ሰብእና እንደ መልካም ጎን ይይዙለታል፡፡

በየካቲት መጽሄት ላይ በዋና አዘጋጅነት ለአመታት የሰሩት አቶ ጸጋዬ ሀይሉ ተፈራም የስሜነህን በሳል የሚድያ ሰውነት ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡  ስሜነህ ለህትመት ሚድያ የተፈጠረ ነው ሲሉም በሀገራችም የዜና እና የህትመት ስራ  ታሪክ ውስጥ የራሱን ትልቅ አሻራ ያኖረ መሆኑን በሙሉ አንደበታቸው ይመሰክራሉ፡፡ አብሬው በሰራሁበት ዘመናት ከሰው ተግባቢ፤ ደግ እና ጥሞና ሰጥቶ የሚያዳምጥ ሰው መሆኑን ግንዛቤ አግኝቻለሁ ብለዋል አቶ ጸጋዬ ፡፡

         አጎቴን እወዳለሁ 

የስሜነህ መኮንን የእህት ልጅ ወይዘሮ ሸዋን ግዥውዳምጤ ደግሞ ለአጎቴ ለስሜነህ  የተለየ አክብሮትነ ፍቅር አለኝ በማለት 16 አመት በፊት በአጸደ ስጋ ስለተለየው ጋዜጠኛ ማስረዳታቸውን  ይቀጥላሉ፡፡ ያኔ ጣሊያን ሰፈር ስሜነህ ያሳለፋቸው የወጣትነት ዘመናት አይረሴ ነበሩ ሲሉ ወይዘሮ ሸዋንግዥው 40 አመት ወደ ኋላ ተጉዘው ዘመኑን በትዝታ መነጽር ለማየት ይፈልጋሉ፡፡ ለትንሹ ለትልቁ ደግ የነበረው አጎቴ ስሜነህ 16 አመት ሙት አመት መታሰቢያው በዚህ መልኩ መዘከሩ ለቤተሰቡ ትልቅ የማስታወሻ አጋጣሚ ነው በማለት ይህ አጭር ታሪኩ መቅረቡን አድንቀዋል፡፡ ስሜነህ ላበረከተው ታላቅ ውለታ መንግስትም ተገቢውን ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

          በዜናዎቹ ላይ ህይወት የሚዘራ 

አቶ ይልማ ሀብተማሪያም ‹‹…ስሜነህን 1990 ጀምሮ አውቀዋለሁ›› ይላሉ፡፡ ስሜነህ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የአዲስ አበባ ዜና ዴስክ ሃላፊ በነበረ ጊዜ አቶ ይልማ ሪፖርተር ነበሩ፡፡ ታዲያ ስሜነህ በጊዜው ሪፖርተሮቹ እነ ይልማ ይሰሯቸው ለነበሩ ዜናዎች በእንዴት ያለ መልኩ ህይወት ይዘራባቸው እንደነበር ይታወስ ነበር፡፡ በኤዲቲንግ ከፍተኛ ክህሎት የነበረው ስሜነህ እምነት የጣለበትን ጋዜጠኛ አምኖ በማሰማራት እያበቃ ያሰራ እንደነበር አቶ ይልማ ያስታውሳሉ፡፡

‹‹….. እምነት ጥሎ ወደ መስክ ካሰማራቸው ጋዜጠኞች መካከል አንዱ እኔ ራሴ ነኝ ›› ሲሉ አቶ ይልማ ራሳቸው ያስተዋሉት የስሜነህ ልዩ ክህሎት ላይ ሃሳብ ይሰነዝራሉ፡፡

ስሜነህ መኮንን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎትን  የእውነት ኢዜአ እንዲሆን ካስቻሉት በጣት ከሚቆጠሩ ጋዜጠኞች አንዱ እንደነበር ብዙዎች አፋቸውን ሞልተው ይናገራሉ፡፡ ስሜነህ ወደ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ በተዛወረበትም ጊዜ ለጋዜጣዋ ህይወት የሰጠ ሰው  እንደነበር በቅርብ አብረውት የሰሩት ያስረዳሉ፡፡

ታደሰ ሙሉነህ፤ ዳሪዮስ ሙዲና  ጥላሁን በላይ የስሜነህ የቅርብ ጓደኞች የነበሩ ሲሆን 3ቱም በአሁን ሰአት በህይወት የሌሉ ናቸው፡፡ ከስራ ሲመጣ በእረፍት ቀናት ሳይቀር ብዙ መስራት ልምድ ያደረገው ስሜነህ የንባብ ክህሎቱ የዳበረ ነበር፡፡

            ቤተሰባዊ ህይወት 

ስሜነህ መኮንን 1968 ከወይዘሮ አልማዝ ሙላቱ ጋር ጋብቻን መስርቶ 2 ሴቶችንና አንድ ወንድ ልጅ ያፈራ ሲሆን ስማቸውም ሶስና ስሜነህ ዘላለም ስሜነህ እና ሰላም ስሜነህ ይባላሉ፡፡

            ሚድያዎች ስሜነህ ዘክሩት-በተለይ ኢዜኤ እና ፕሬስ 

 ገና ብዙ ሊሰራ ሲችል 57 አመቱ ሰኔ 28 1997  ላይ ለህልፈት የተዳረገው ስሜነህ የኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ላይ አንድ ትልቁ ጡብ ያስቀመጠ ተብሎ ሊወሳለት የሚገባ ሰው ነው፡፡ በተለይ 1970ዎቹ  መጀመሪያ አንስቶ እስከ 90ዎቹ ድረስ በሀገሪቱ ለመጣው የዘመናዊ ጋዜጠኝነት ለውጥ የስሜነህ እጅ አለበት፡፡ ስሜነህ መኮንን የዛሬ 16 አመት ሰኔ 28 ነበር ህይወቱ ያለፈው ፡፡

        የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ

መዝጊያ: ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን እንደስሜነህ አይነት ደማቅ አሻራ አኑረው ነገር ግን በህይወት የሌሉ ከዋክብት ሰዎችን  በዚህ ዊኪፒዲያ የመዘከር መርሀ-ግብር አለው፡፡ ሀገር ያደገችው በቀደሙት ታላላቆች እና አሁን ባሉት ጀግኖች ነውና የሁሉንም ታሪክ እንደየሚናው ልክ እየነቀስን የሀገር ኩራቶችን መድረኩ ላይ እናመጣለን፡፡ መጪው ትውልድም እንዲያውቃቸው እናደርጋለን፡፡ ከእነዚህ የሀገር ኩራቶች አንዱ ስሜነህ ነው፡፡ ስሜነህን የኢትዮጵያ ሬድዮ ሰዎች የኢዜአ  ሃላፊዎች የፕሬስ ድርጅት ሰዎች እንዲያስታውሱት እናሳስባለን፡፡ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ ነውና የቀደሙ የሀገር ባለውለታዎችን በዚህ መልኩ እየዘከርን ነውና የስሜነህን የመሰሉ ታሪኮች የሚድያ ሽፋን ቢያገኙ ስንል ሀሳብ እንለግሳለን፡፡ ስሜነህ የሚጠበቅበትን ሰርቷል፡፡ እኛም የመዘከር ሚናችን እነሆ ተወጥተናል፡፡ ሁሉም በየፊናው አንድ ነገር ካቀበለ ኢትዮጵያ ማለት ይህች ናት፡፡ የእኛም አላማ ይህ ብቻ ነው፡፡

ምስጋና: ይህን የስሜነህን ታሪክ እንድንሰራ የመጀመሪያውን ሀሳብ ለሰጠችን ለወይዘሮ አመለወርቅ ወልደኪዳን ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ በመቀጠል የስሜነህ መኮንንን የቅርብ ሰዎች ስልክ በመስጠት ለተባበረን የኢዜአው ደሳለው ጥላሁን፡፡ እንዲሁም ለሰናይት ወልደኪዳን አጠቃላይ ለአቶ ስሜነህ መኮንን ቤተሰቦች ላቅ ያለ ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ ምስጋና ለሶስና ስሜነህ ለዘላለም ስሜነህ እና ለሰላም ስሜነህ እንዲሁም ለአቶ ስሜነህ ባለቤት ለወይዘሮ አልማዝ ሙላቱ ማቅረብ እንፈልጋለን፡       / ይህ ጽሁፍ ከመነሻው ጀምሮ የተጻፈው እና የተጠናከረው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ሲሆን የጥንቅር ቀኑም ዛሬ እሁድ ሰኔ 27 2013 ከሌሊቱ 7 ሰአት ነው፡፡

 








 

 

 

 

 

 

 

 

 

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች