55.  ፀሐይ ተፈረደኝ

 

ትውልድ እና እድገት እንዲሁም ትምህርት፡-

 

ፀሐይ ተፈረደኝ /እየሱስ ከእናትዋ / በዛጌጥ ቦጋለ እና ከአባትዋ አቶ አበበ ፀጋዬ መጋቢት 5/1946 / በምእራብ ሸዋ ሆለታ ከተማ ውስጥ ተወለደች፡፡ ፀሐይ በወራት እድሜ እያለች እናትና አባትዋ በተከታታይ ስለአረፉ በአያትዋ አቶ ቦጋለ /ሚካኤል አማካኝነት ወደ አዲስ አበባ መጥታ መርካቶ (ተክለሀይማኖት) አካባቢ ይኖሩ በነበሩት ቀለሟ ገብረጻዲቅ በሚባሉት አክስትዋ ቤት አደገች፡፡ በጊዜው ትምህር ትዋን የጀመረችው በቄስ ትምህርት ሲሆን በመቀ ጠልም ንጉስ ወልደጊዮርጊስ ይባል በነበረው ከዚያም ተስፋ ኮከብ፤ደጃዝማች ባልቻ አባነፍሶ ይባሉ በነበሩት ትምህርት ቤቶች እስከ ስምንተኛ ክፍል ተማረች፡፡ 1963 / መርካቶ መኪና ተራ ልዑል መኮንን ይባል በነበረው ትምህርት ቤት ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን መከታ ተል ጀመረች፡፡ ነገር ግን በጊዜው መሬት ላራሹ በሚል በነበረው ትግል ምክንያት ትምህ ርቷን መከታተል አልቻለችም ነበር፡፡  የመሬት ላራሹን ተከትሎ የተከሰተው አመጽ በጊዜው ከፖሊስ ድብደባ በተጨማሪ በቤተሰብ ጥሩ የሆነ ምላሽ የማይሰጥበት ነበር፡፡ በጊዜው የፀሐይ ተፈረደኝ አሳዳጊ የሆኑት አቶ ተፈረደኝ /እየሱስ ባለእርስታና ባለሀብት ሰለነበሩ የነበረውን አመጽ አይቀበሉትም ነበር፡፡ ስለዚህም እናንት የዛሬ ልጆች የምትበሉትን የምትረግሙ ናችሁ ይሉ ነበር፡፡ ይሄን አይነቱ ስሜት የፀሐይ ቤተሰቦች ብቻ ሳይሆኑ በጊዜው የነበሩት የብዞዎቹ ሰዎችም ነበር፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ በዚህ ምክንያት ግራ በተጋባችበት ወቅት ነበር የመከላከያ ሚኒስቴር 1963-64 / ለመጀመሪያ ጊዜ ሴት ወታ ደሮችን አወዳድሮ ለመቅጠር እንደ ሚፈልግ የሚገልጽ ማስታወቂያ በትምህርት ቤታቸው ግድ ግዳ ላይ የለጠፈው፡፡ በየእለቱ በፖሊስ ከመደብደብስ ይሄ ይሻላል በማለት ፀሐይ ተፈረደኝ  በውትድርና ሙያ አገርዋን ለማገልገል ወስና ተቀጠረች፡፡

ውትድርና፡-

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በምድር ጦር የቅጥር ስነስርአት በተሟላበት ሁኔታ ከተቀጠሩት 62/ሴት ወታደሮች ውስጥ አንዷ ፀሐይ ተፈረደኝ ነች፡፡ የውትድርና ስልጠናው በሆለታ ጦር ትምህርት ቤት ይባል በነበረው የተካሄደ ሲሆን ይህም የመኮንኖች ማሰልጠኛ የነበረ ነው፡፡ ተራ ወታደሮች ለስልጠና የሚገቡት ፍቼ ከሚገኘው የውትድርና ማሰልጠኛ ሲሆን ሴት ወታደር ግን ሲቀጠር የመጀመሪያው በመሆኑና ለጥንቃቄ ሲባል ለሴት ወታ ደሮች ሲፈቀድ የመጀመሪያ ጊዜ ነበር፡፡ የሴት ውትድርና ቅጥር የተፈለገው የሴት ሰራዊትን በአገሪቱ ለመ መስረት ስለነበር 62/ ቅጥር የሴት ወታደሮች ውስጥ 13/የሚሆኑ ጎበዝ ሰልጣኞች ለብቻቸው ተጨማሪ ትምህርት እንዲወስዱ ሲመረጡ አንዱዋ ፀሐይ ተፈረደኝ ነበረች፡፡ ይህን በተጨማሪ የተሰጠውን የውትድርና ትምህርት እንድታስተምር እና ምሳሌ እንድትሆን እስራኤላዊት ሻምበል ተመድባ ነበር፡፡ እስራኤላዊቷ ሻምበል ሁልጊዜ አንድ ነገር ትናገር ነበር፡፡

‹‹እናንተ እኮ አገር ስላላችሁ አገራችሁን ልታገለግሉ በመመረጣችሁ እድለኞች ናችሁ፡፡ እኛ ግን አገር ስለሌለን አገር ለማግኘት ነው ወታደር የሆንነው ትል ነበር››

ይህች ሻምበል ኮርሱን ሰጥታ እንደጨረሰች በአገርዋ ሰላምን ለማስከበር ሲባል በአለም ዙሪያ ያሉት እስራኤላውያን ተጠርተው ወደሀገራቸው ከሄዱት አንዷ ነበረች፡፡ ይህች ሻምበል በውጊያ ላይ ግዳጅዋን በመወጣት ላይ እያለች ሕይ ወትዋ አልፎአል፡፡ በውትድርና ስልጠና ወቅት አንድ ወታደር ሊያውቀው የሚገባውን ሁሉ ተኩስን ጨምሮ ፀሐይ በሚገባ የሰለጠነች እና በመተ ግበሩም በኩል ጎበዝ ነበረች፡፡ ስልጠናው ለአንድ አመት እስከ(1965) ድረስ የቆየ ሲሆን የአስተ ዳደር ትምህርትንም ያካተተ ነበር፡፡ በምረቃ ወቅትም ፀሐይ 7 ክፍል ተማሪ ሆና የጻፈችውን የቲአትር ድርሰት በማውጣት ሰልጣኞችን በቲአትር አሰልጥና ለህዝብ ለማ ቅረብ በቅታለች፡፡ በጊዜው ሴት ወታደሮቹ ከወንድ ጋር አብሮ የመሆን ፈቃድ ስላል ነበራቸው ከሴት ወታደሮቹ መካከል ሶስቱ እንደወንድ ሆነው ቲአትሩን እንዲጫወቱ ሲደረጉ አንዱዋ ወንድ ፀሐይ ተፈረደኝ ነበረች፡፡ ይህ ቲአትር በሆለታ በጦር ትምህርት ቤቱ በሚገኘው አስናቀ አዳራሽ ውስጥ ከሰራዊቱ ጀምሮ በከተማዋ ውስጥ ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በማሳየት በተገኘው ገንዘብ የሴት ወታደሮቹ የምረቃ ስነስርአት ሊከናወን ችሎአል፡፡ በዚያን ጊዜ የኢትዮጵያ ንጉስ የነበሩት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ከመኮንኖች በታች የሆኑ ወታደሮችን አይመርቁም ነበር፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ እና ጉዋደኞችዋ ግን በራሳቸው በንጉሱ ፈቃድ ማለትም ተጠይቀው እመርቃቸ ዋለሁ በማለታቸው ከእሳቸው እጅ ሰርተፊ ኬታቸውን ለመቀበል በቅተዋል፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ /ስላሴ ንጉሰ ነገስት ኢትዮጵያ በተለያየ ምክንያት ወደ ሆለታ ጦር ትምህርት ቤት ይመጡ የነበረ ሲሆን ሴት ወታደሮች እየጨፈሩ እሳቸውን መቀበልና መሸኘት አንዱ በደስታ የሚከ ውኑት ነገር ነበር፡፡ ፀሐይ ሰልፈኛውን ወይንም ጨፋሪውን እየመራች

(ጠቅል ምን አለ ጠቅል ምን አለ አገሬን ለሰው አልሰጥም አለ)

የሚለውን ዜማ እያወረደች መጨፈርና ማስጨፈር ትወድ ነበር፡፡

ንጉሱም በጦር ትምህርት ቤቱ በጠቅላላው ላለው ወታደር ትልቅ አገል ግልና ቁርጥ ስጋ እንዲሁም ጠጅ አስከትለው ነበር ወደ ሆለታ የሚያመሩት፡፡ ፀሐይ በውትድርና ስልጠና ላይ በነበረችበት ጊዜ ብዙ የማይረሱ ትውስታዎች አሉአት፡፡ ለውትድርና ልምምድ ሙሉ ወታደራዊ ልብስ ለብሶ እና መሳሪያ ታጥቆ ወደገጠሩ መውጣት የተለመደ ነበር፡፡ ከልምምድ ስፍራው ሲደርሱ መመሳሰል የሚባል ነገር አለ፡፡ ጭቃ ተለቅልቆ እና ቅጠል ለብሶ ጉቶ ወይንም ከፍ ያለች ኮረብታ መምሰል አንዱ ነው፡፡ እንደዚህ ያሉት ልምምዶቸ ከጠላት ጋር ሲዋጉ እስከምን ድረስ መሄድ እንደሚገባ ከሚያሳዩት መካከል ናቸው፡፡ ታዲያ ወደልምምዱ ሲኬድ በኮዳ ውሀ ካልሆነ በስተቀር ምግብ አይያዝም፡፡ ስለዚህም መራብ አይቀርም፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ ይህን ስታስ ታውስ አንድ አጋጣሚን አትረሳም፡፡ እንዲህ ብላለች፡፡

ከአዲስ አበባ ወደ ሆለታ ሲኬድ በሚገኘው ወልመራ በሚባለው አካባቢ በአንድ ወቅት የሴት ወታደሮቹ (እነ ፀሐይ) ከልምምድ ሲመለሱ አንድ አባወራና እመወራ ገበሬዎች ኩታ ቸውን አገልድመው አትለፉን እባካችሁ ግቡ ብለው በኦሮምኛ ይናገራሉ፡፡ የወታደሮቹ አስተማሪም እሺ ብሎ ወደግቢያቸው ሴት ወታደሮቹ እንዲገቡ አደረገ፡፡ በረዥሙ ከአጠና እንጨት የተሰራ ገበታን ከበባ አድርገው ተቀመጡ፡፡ በገበታው ላይ የባሀር ዛፍ ቅጠል ተጎዝጉዞ በላዩ ላይ ጉበት የመሰለ መልክ ያለው ወፍራም ትኩስ እንጀራ በድርብ ሆኖ ወደ አምስት ቦታ ተዘረጋ፡፡ ፡፡ ወጡ በድስት ተሞልቶ ቀረበ፡፡ በትላልቁ የተከተፈ ስጋ ቀይ ወጥ ነበር፡፡ ለልምምድ ተረኛ የነበረው አንድ የመቶ ሲሆን የሴት ወታደሮቹም ቁጥር 31/ሰላሳ አንድ ነበር፡፡ ሰላሳ አንድ የሴት ወታደሮች አንዳቸው ከአንዳቸው ሳይተያዩ አጎንብሰው ነበር ያንን ምግብ የተመገቡት፡፡ ማወራረጃውም እርጎ በሚጥሚጣ ነበር፡፡ ለዚያ ሁሉ የሴት ወታደር እርጎው በመጠጫው እየተደረገ ተዳረሰ፡፡ ይህንን የጋባዦቹን ለውትድርና ሙያ ያላቸውን ክብርና እንደሰው ደግነት እንዲሁም የዋህነት ፀሐይ እንደማ ትረሳው ገልጻለች፡፡

 

ከምረቃው በሁዋላ ሁሉም ወደየጦርክፍሎቹ ተበትነው የጽህፈት ስራእንዲሰሩ ተመደቡ፡ከተወሰኑ አመታት በሁዋላ ፀሐይ ተፈረደኝ በነበራት ንቁ ተሳትፎ እና በፈተና ውጤት ተመርጣ በውትድርና በሰራዊቱ ውስጥ በአገልግሎት ላይ ላሉ የሰራዊቱ አባላት ማስተማሪያ እንዲሆን የአስተዳደርና የጽህፈት ስራ ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ሲቋቋም ፀሐይ ተመድባ የጽህፈት ስራ ትምህርት ክፍሉ ኃላፊና አሰልጣኝ በመሆን 1970-1974 አገልግላለች፡፡ ከሰራዊቱ ከመሰና በትዋ በፊት የአስር እልቅና ማእረግ አግኝታለች፡፡

ኢህአዲግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በሁዋላ ሰራዊቱ ካለምንም ደመወዝ ወይንም ጡረታ በመበተኑ ከችግር ላይ ወድቆ ነበር፡፡ 1984/ዓም ለቀድሞው ሰራዊት የጡረታ ክፍያ እንዲ ሰጠው ሲወሰንለት ፀሐይ ተፈረደኝ የባለሌላ ማእረግ ጡረታ ክፍል ምክትል ኃላፊ በመሆን ተመድባ ሰርታለች፡፡ ፀሐይ ከዚህ ጋር በተያያዘ አንድ ገጠመኝ አላት፡፡

ጡረታ የሚገባው የክብር ዘበኛ አባል የሆነ በማእረግ የሀምሳ አለቃ የነበረ ሰው ጡረታውን ለማስወሰን የሚረዳ መረጃ ይጠፋል፡፡ ከአንድ ወር በላይ በየስፍራው ቢፈለግ ሊገኝ አልቻለም፡፡ በሁዋላም አንድ ቀን በምሳ ሰአት ፀሐይ ብቻዋን ቁጭ ብላ ስራዋን ስትሰራ ወደ ቢሮዋ ይገባል፡፡ እስዋም በማዘን ይህን ሰው ምን ልርዳው እያለች ስትጨነቅ ከደረት ኪሱ ስቦ በቁመናው የታጠፈ ወረቀት ጠረጴዛዋ ለይ ያስቀምጣል፡፡ ምንድነው ብላ ገለጥ ስታደርገው የቅጥር ፎርሙ ከነፎቶግራፉ ነው፡፡ ከየት አመጣኸው ብላ ስትጠይቀው ሲጋራ ልገዛ ከሱቅ ቆሜ ባለሱቁ ለስኩዋር መጠቅለያ ሊቀደው ሲል ኡኡ ብዬ አስጣልኩት እና ይዤ መጣሁ አለ፡፡ በዚህ ታሪክ በማዘን ከዚያ በሁዋላ ለሚመጡ ባለጉዳዮች መረጃ ሲጠፋ የት ድረስ መፈለግ እንደሚገባቸው ፀሐይ ታስረዳቸው ነበር፡፡

 

ጋዜጠኝነት፡-

ፀሐይ ተፈረደኝ የውትድርና ስልጠናውን ጨርሳ ከተመረቀች በሁዋላ በምድር ጦር በጽህፈት ስራ ላይ ተመደባ እየሰራች ባለበት ወቅት ለጦር ኃይሎች ሬድዮ ጋዜጠኝነት ሴቶች ይፈለጋሉ ሲባል ተመርጣ ለውድድር ቀረበች፡፡ ፀሐይ ውድድሩን ሶስተኛ በመውጣት ለስልጠና ወደማስታ ወቂያ ሚኒስቴር ተላከች፡፡ በጊዜው  እነ ጌታቸው /ማር ያም፤ታደሰ ሙሉነህ፤ልኡል ሰገድ ኩምሳ፤ እና ሌሎችም እውቅ የጋዜጠኝነት ባለሙያ ዎች ለሶስት ወር የጋዜጠኝነትን ሙያ ሰለጠነች፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ ከዚያ በሁዋላ ሙያውን በተመለከተ የወሰደቻቸውን ትምህርቶች ከዚያ ስልጠና ጋር ስታመዛዝነው ለስልጠናው ከፍ ያለ ዋጋ ትሰጣለች፡፡ ስልጠናውን ከወሰደች በሁዋላ ከጽህፈት ስራ ጋር በተደራቢነት በጋዜጠኝነት ስራ አገልግ ላለች፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ 1978 / ጀምሮ ከሰራዊቱ በህክምና ቦርድ ተሰናብታ ሲቪል ሆና ነበር፡፡ በመሆኑም የጦር ኃይሎች ሬድዮ ጋዜጠኛ በመሆን ሙሉ በሙሉ መስራት የጀመረችው 1978 / ጀምሮ ሲሆን እስከ 1983// ማለትም ኢህአዲግ አገሪቱን እስከተቆጣጠረበት ጊዜ ድረስ አገልግላለች፡፡ የጦር ኃይሎች ራዲዮ በሳምንት ሁለት ቀን ማለትም ረቡእና እሁድ ይተላለፍ የነበረ ሲሆን በተለይም የረቡእ እለት ፕሮግራሙ አዘጋጅ በመሆን ነበር የሰራችው፡፡  በዚህ የጋዜጠኝነት ዘመንዋ ህብረተሰቡ ስለውትድርናው አገልግሎት እና ወታደሩ በማህበራዊ ሕይወቱ ዙሪያ ምን ያገኛል ወይንም ምን ይጎድ ልበታል የሚለውን በተቻለ መጠን ህብረተቡ እንዲያውቅ ጥራለች፡፡ ወታደሩ ዳር ድንበሩን በመጠበቁ ሌላው ህብረተሰብ በሰላም እየኖረ መሆኑን መልእክት ስታስ ተላልፍ ነበር፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ በጦር ኃይሎች ሬድዮ በምሳሌነት ሊነሱ ይገባል የተባሉ አርበኞችን ታሪክ በመተረክ ከአድማጭ ጆሮ እንዲደርሱ አድርጋለች፡፡ የእነ በላይ ዘለቀ፤ባልቻ አባነፍሶ ታሪኮች መጽሐፈ ሲራክ ይባል በነበረ ሰው የተጻፉ ሲሆን ተራኪዋ ፀሐይ ተፈረደኝ ነበረች፡፡

 

   ኢትዮጵያ ሬድዮ፡-

 

የጦር ኃይሎች ሬድዮ ጋዜጠኛ የነበረችው ፀሐይ ተፈረደኝ ኢህአዴግ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በሁዋላ በተለያዩ ሙያዎች በመከላከያ ሚኒስቴር የሰራች ሲሆን ውሎ አድሮ ግን ከነሙሉ ዶክመንትዋ ወደ ኢትዮጵያ ሬድዮ እንድት ዛወር ተደረገ፡፡

ፀሐይ ተፈረደኝ በኢትዮጵያ ሬድዮ ውስጥ ከሰራቻቸው ስራዎች ዋና ዋናዎቹ ኢትዮጵያን እንቃኛት ፤በሕይወት ዙሪያ ፤የሴቶች ፕሮግራም የተሰኙት ነበሩ፡፡ በተጨማሪም ካነበብነው፤ጠይቁን እንመልሳለን፤መወያየት መልካም፤የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም፤ የሚባሉት ፕሮግራ ሞችም ከምትሰራቸው ፕሮግራሞች መካከል ነበሩ፡፡ በቀጥታ ስርጭትም ትሰራ ነበር፡፡  የጋ ዜጠኝነት ስራው እንደዛሬው የዘመነ ሳይሆን ድምጽ የተቀረጸበት የቴጵ ክር በስለት እየተቆረጠ በስፕላሽ እየተጣበቀ ስለነበር ኤዲቲንግ የሚባለውን ስራ ከባድ ያደርገው ነበር፡፡

 

ፀሐይ ኢትዮጵያን እንቃኛትን ከጋዜጠኛ አስፋው ገረመውና ጋዜጠኛ ወንድሙ ከበደ ጋር በመሆን  ከመመስረት ጀምሮ በሕይወት ዙሪያን መጠሪያውን እንዲያገኝ እስከማድረግ እና ስራውን እስከመጀመር ጥረት አድርጋ ተሳክቶላታል፡፡ ፀሐይ ኢትዮጵያን እንቃኛትን ስትሰራ በቀጠታ ባህሉን የምታስተዋውቅለትን ህረተሰብ መጨረሻ ድረስ ወርዳ አብራ ውላ እስከማደር በመድረስ ታሪኩን፤ባህሉን፤ልማዱን፤ተፈጥሮንወዘተ የቻለችውን ያህል ለህዝብዋ አስተዋ ውቃለች፤በሬድዮ አስጎብኝታለች፡፡ ፀሐይ በማህበራዊው ዘርፍ ህጻን ሽማግሌ፤ወንድ ሴት ሳትል በገጠር በከተማው ሁሉ በጤና ፤በሰላም ፤በእድገት እንዲኖሩ የሚያስችለውን በመጠቆም የበኩ ልዋን  ጥራለች፡፡ እንደጋዜ ጠኛ ለህብረተሰቡ ሚዛናዊ መረጃን በማቅረብ ፤ሴቶች መብታቸው ተከብሮ እንዲኖሩ፤ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲወገዱ ህጻናት ካለእድሜ አቸው እንዳይዳሩ ፤ጠለፋ፤አስገድዶ መድፈር የመሳሰሉት ሁሉ እንዲወገዱ የቻለችውን ያህል በምሳሌ እያስደገፈች፤ሁነቶችን እየዘገበች ትምህርታዊ መልእክቶችን አስተላልፋለች፡፡ ፀሐይ ኤዲተር በመሆን ብዙ ፕሮግራሞችን ትመለከት እንዲሁም ታርም ነበር፡፡ በዚህም ፕሮግራሞ ቻቸውን እንድታይላቸው የሚያቀርቡላትን ባለሙያዎች ስራ ጠንቅቃ በመመልከት ወይንም በማድመጥ የህብረተሰቡን አቅጣጫ የሚያስቱ መልእክቶች እንዳይተላለፉ እርማትን ታደርግ ነበር፡፡ ለአዘጋጆቹም ምክርን ትለግስ ነበር፡፡

የመስክ ጉዞ፡-

ፀሐይ በጋዜጠኝነት ስራዋ መስክ ተጉዋዥም ነበረች፡፡ የፀሐይን የመስክ ጉዞ ልዩ የሚያደርገው ህዝብ በሚጉዋጉዋ ዝባቸው አውቶቡሶች በመጠቀም ቅርብ ነው እሩቅ ነው ወይንም ይመቻል አይመችም ፤ደጋ ነው ቆላ ሳትል በድፍረት ህብረተሰቡን ካለበት ክልል ፤ዞን፤ወረዳ ድረስ በመዝለቅ በየቤቱም ጭምር እየተገኘች አኑዋኑዋ ራቸውን እየተመ ለከተች ስራዋን ያከናወነች መሆንዋ ነው፡፡ በአገሪቱ ዙሪያ ማለትም በሰሜን በሱሉልታ በኩል ወጥቶ ጎጃም፤ጎንደር፤ማይጨው፤አድዋ፤አዲግራት፤አክሱም፤መቀሌወዘተ ድረስ ተዘዋውራ ስለህብረተሰቡ ስለ ጤና፤ትምህርት፤ልማድ፤ባህልወዘተ ዘግባለች፡፡ በዚሁ መልክ ወደ ደቡብም ዝዋይ ፤ሻሸመኔ፤ሐዋሳ፤ ይርጋለም፤ዲላ፤እንዲሁም ጅማ ቦንጋ፤ሚዛን፤ማሻወዘተ በቤንሻንጉል አሶሳ፤ማኦ ኮሞ፤በርታ፤ ሽናሻወዘተ ኮንሶ አርባምንጭ፤ወላይታ፤..ወዘተ ምናልባትም ከጥቂት ቦታዎች በስተቀር በኢትዮጵያ በርካታ አካባቢዎችን ተዙዋዙራ ለህዝብ አስተዋውቃለች፡፡ ደብረብርሀን፤አልዩ አምባ፤አምቦ፤ወዘተ የመሳሰሉትን ሁሉ ተመልክታለች፡፡ ፀሐይ ወደመስክ ስትሄድ በቤትዋ ውስጥ ያሉትን ልጆችዋን ለባለቤትዋ በመተው ነበር፡፡ ባለቤትዋም በዚህ ጉዳይ ተቃውሞ አሰምቶ ስለማያውቅ ሊመሰገን ይገባዋል ብላለች ፀሐይ፡፡ የመጀመሪያ ልጅዋ ትነበብ ብርሀኔ በልጅነት አእምሮዋ የበሰለች ጨዋ ልጅ ስለነበረች ምንም እንኩዋን እድሜዋ ኃላፊነት ለመሸከም ባይፈቅድም እስዋ ግን ወንድም እህቶችዋን ስርአት በማስያዝ ሳይጎዳዱ እናታቸውን እንዲጠብቁ በማድረጉ ረገድ ውለታዋ አለብኝ ትላለች ፀሐይ ተፈረደኝ፡፡

ትምህርት፡-

ፀሐይ ተፈረደኝ በልጅነት የትምህርት ዘመንዋ የአገር አቀፉ የሚኒስትሪ ፈተና ይስጥ የነበረው 6ኛና ስምንተኛ ክፍል ነበር፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ ወደ ውትድርና ስትገባ ትምህርትዋን ያቋረጠችው 9 ክፍል ነበር፡፡ ከዚያም በምሽት ትምህ ርትዋን ለማ ሻሻል በወሰደችው እርምጃ ስራዋን እየሰራች፤ልጅ እየወለደች፤ልጆችዋን እያሳደገች እስከ 12 ክፍል ድረስ ተማረች፡፡ ከዚያም በን ግድ ስራ ኮሌጅ የቢሮ አመራ ርና የሴክረታሪነት ሙያን ለሁለት አመት ተምራ በሰርተፊኬት ተመረቀች፡፡ በዚሁ የትምህርት ደረጃ ላይ እያለች ነበር በኢትዮጵያ ሬድዮ የጋዜጠ ኝነት ስራዋን የጀመረችው፡፡ በስራዋ ላይም ኤዲተርም ስለነ በረች አንድ ጋዜጠኛ ሊተላለፍ የማይችል ብላ ያገደችውን አንድ ፕሮግራም ይሰጣታል፡፡ ፕሮግራሙን ስታደም ጠው የማይሆን በመሆኑ ሊተላለፍ እንደማይ ችል ነግራው ትመልስለታለች፡፡ የእሱም መልስ እጅግ ሞራል የሚነካ ነበር፡፡

‹‹እኔማ እንኩዋንስ መሐይም ህጻን ልጅም ቢያዘኝ እሺ ነው የምለው›› አለና ሰርቶ ያመጣውን ክር ወሰደ፡፡ ፀሐይ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ እንቅልፍ አጣች፡፡ እውነቱን ነው፡፡ እሱ ከዲግሪም በላይ ማስተርስ አለው፡፡ እኔ 12/ ክፍል ተማሪ ነኝ፡፡ ግን በስራዬ ተመርጬ ተሸሜአለሁ፡፡ ስራዬ ንም በሚገባ እየሰራሁ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁኔታው አይገናኝም፡፡ መማር አለብኝ የሚለው ሀሳብ የመጣላት በዚህ ሰው ንግግር መሆኑን ፀሐይ ትናገራለች፡፡ ታዲያ የዚህን ሰው ንግግር ዛሬ ታመሰግናለች፡፡ ለመወሰን ረድቶኛል ትላለች፡፡ ይህንኑ ሀዘንዋን በዚያን ጊዜ በቅርብዋ ለነ በረችው አስተባባሪ ሰሎሜ ደስታ ታማክራለች፡፡ እስዋም ትማሪያለሻ….መገናኛ ብዙሀን ኢንስቲ ትዩት ገብተሸ ትማሪያለሽ የሚል ተስፋ እንደሰጠቻትና ይህንንም ለስብሰባ አቅርባ መወያያ እንደሆነ ነግራኛለች ብላለች ፡፡ መወያያ የሆነበትም ምክንያት ፀሐይ የልጆች እናት ነች፡፡ እን ዴት አድርጋ ትማራለች ከሚል ነበር፡፡ ከዚያ በሁዋላ መማር እንደምትፈልግ ተጠይቃ ፍላጎት እንዳላት በመናገርዋ በውድድር አልፋ ለመማር በመገናኛ ብዙሀን ማሰልጠኛ ኢንስ ቲትዩት 1990/የቀን ትምህርት እድል አገኘች፡፡ ተቋርጦ የነበረውንና እንዴት አድርጋ እንደ ምትቀጥ ለው ግራ ያጋባትን ትምህርት እንድትማር ለረዳቻት ሰሎሜ ደስታ የከበረ ምስጋና አላት፡፡

 

ፀሐይ ትምህርቱን በምትማርበት ወቅት ልጆችዋ ወደ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ የደረሱ ስለነበሩ በማስጠናቱ በኩል ይተባበሩአት እንደነበር አትረሳውም፡፡ በተለይም ሶስተኛው ልጅዋ አንተነህ ብርሀኔ የቤት ስራ በመስራት እና በማስጠናት በኩል በጣም ይረዳት ስለነበር ታመሰግነዋለች፡፡ፀሐይ የዲፕሎማ ትምህርትዋን በጥሩ ውጤት በማእረግ አጠናቀቀች፡፡

ፀሐይ አሁንም ዲፕሎማ ያገኘችበት ትምህርት ቤት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስር ሆኖ ምሽት የዲግሪ ትምህርት ስለጀመረ ዲግሪዋን .. (2008) ያዘች፡፡ በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1998/ መጀመሪያ ላይ ከጡረታ እድ ሜዋ አስቀድማ ጡረታዋን አስ ከብራ ስራ ከለቀቀች በሁዋላ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪዋን በኮሚዩኒኬሽንና ጆርና ሊዝም .. (2015) ለመያዝ በቅታለች፡፡ ፀሐይ ማንኛውም ሰው መማር አለበት የሚል እምነት ስለነበራት ሀብ ታምና ገንዘብ የተረፋት ባትሆንም ያላትን እያጋራች ከልጆችዋ ውጭ ብዙዎች እንዲማሩ እና ለወግ ማእረግ  እንዲበቁ አድርጋለች፡፡ ለዚህም እግዚአብሔርን ታመሰግናለች፡፡ 

ቤተሰብ፡-

ፀሐይ ተፈረደኝ 1966// ከአቶ ብርሀኔ /መስቀል ጋር ጋብቻ ፈጽማለች፡፡ የመጀመሪያ ልጅ (ትነበብ ብርሀኔን)1969/ ሁለተኛ ልጅ (አዳነ ብርሀኔን) 1971 ሶስተኛ ልጅ (አንተነህብርሀኔን) 1973 አራተኛ ልጅ (ምእራፍ ብርሀኔን) 1975 አምስተኛ ልጅ አዲስ አለም ብርሀኔን 1982 / ወልዳ ከባለቤትዋ ጋር በጥሩ ሁኔታ አሳድገው ለወግ ማእረግ አብቅ ተዋል፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ እና ባለቤትዋ አቶ ብርሀኔ ስድስተኛ ልጅ ሀና ጥበቡን አስተምረው በጥሩ ሁኔታ አሳድገው ለማእረግ አብቅተዋል፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ ቤተሰብን መስርታ በዚህ መልክ ልጆችዋን ያፈራች፤በውትድርና ፤በጋዜጠኝነት ስራዋ ላይ ይቅር ወይንም ይዋል ይደር የማይባል ስራን በመስራት፤በማህበራዊ ኑሮዋ መድረስ ላለባት ጉዳይ ሁሉ በተቻለ መጠን የበኩልዋን ለመወጣት ጥረት ያደ ረገች ስለሆነች በእስዋ እምነት የዚህ ሁሉ ምንጩ በውትድርና የቆየችበት ስነስርአት ሊሆን እንደሚችል ግምት አላት፡፡ በውትድርናው ሕይወት አንድ ሰው ምንም አይነት ችግር ቢገጥ መው ያንን ችግር ሳያስወግድ አስቀድሞ ይቅርታ መጠየቅ ወይንም ላደርገው አልችልም ማለት አይፈቀድለትም፡፡ አባባሉም ‹‹እባብ ቢጠመጠ ምብህ እንኩዋን ችግሩን ሳትፈታ አስጥሉኝ ብለህ መጮህ የለብህም›› የሚል ነው፡፡ ስለዚህም ፀሐይ ይህንን መመሪያ እስከአሁንም የምጠቀምበት ይመስለኛል ባይ ነች፡፡

ፀሐይ ተፈረደኝ በስራዋ ጸባይ ምክንያት በኑሮዋ ያጎደለችው ነገር የለም ለማለት አትደፍርም፡፡ ስራዋን ከመውደድዋ የተነሳ እንዲሁም ልጆችዋን ለማሳደግ ስራዋን ማክበር እንዳለባት ታምን ስለነበር ፀሐይ መስክ ስትወጣ 15/ቀን እስከ 20 ቀን ሊደርስ የሚችል ቆይታ ይኖራት ነበር፡፡ ቤተሰብዋ በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ለማወቅ የምታደርገው ጥረት እንደዛሬው ሞባይል የመሳሰለው መገናኛ ያልነበረ በመሆኑ እጅግ አስቸጋሪ ነበር፡፡ በከተማም ውስጥ ብትኖር የሬድዮ ጣብያው ስርጭቱን እስኪጨርስ እስከ ምሽት አምስት ሰአት ቆይቶ ከሌሊቱ 6-7 ሰአት ድረስ ልጆች ከተኙ በሁዋላ ወደቤት መግባት ወይንም የጠዋት ተረኛ ከሆኑ ከሌሊቱ 10/ሰአት ልጆች ከእንቅልፋቸው ሳይነሱ መውጣት ግዴታዋ ነበር፡፡ ይህ ለብዙ ቀናት ይታይ የነበረ እውነታ ነው፡፡ እንደ ትንሳኤ ፤ገና፤ዘመን መለወጫ ባሉት አመት በአላት ጊዜም ከበአላቱ ቀደም ብሎ የሚሰሩ ስራዎችን ከመስራ ትና ከማማከር ጀምሮ በእለቱ ለመስተንግዶው ወይ እስከቀኑ ሰባት እና ስምንት ሰአት አለበለዚያም ከስምንት እና ዘጠኝ ሰአት ጀምሮ እስከ ምሽት አምስት ሰአት ቆይቶ እንደተለመደው ሌሊት መግ ባት የማይቀር ሀቅ ነው ብላለች ፀሐይ ተፈረደኝ፡፡ ስለዚህም ባለቤትዋ (ነፍሳቸውን ይማር) እና ልጆችዋ እንደ ሌሎች እናቶች በስፋት ሳያገኙዋት ያደጉ መሆናቸውን ታምናለች፡፡ ሆኖም ግን በማንኛውም አስፈላጊ ነገር ሁሉ ቀድማ የምትገኝ ፤ትምህርታቸውን ጤናቸውን፤አኑዋኑዋራቸውን፤የወደፊት አቅጣጫቸውን መስመር በማስያዝ እራሳቸውን በበቂ ቦታ ላይ እንዲያገኙ በማድረጉ ረገድ ያላሰለሰ ጥረት አድርጋለች፡፡ በተለይም የጋዜጠኝነት ሙያው ብዙ ነገር እንድታውቅ ስለረዳት ከዚያ ልምድ በመውሰድ በልጆችዋ ላይ ምንም እንከን ሳይፈጠር ትምህርታቸውን እያጠናቀቁ ወደ ስራው አለም እንዲሁም ወደ ትዳር እንዲዘልቁ ለማድረግ እድሉን አግኝታለች፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ ዛሬ የስድስት ልጆች እናትና የስምንት የልጅ ልጆች አያት ነች፡፡

ልዩ ልዩ፡-

ፀሐይ በተለያዩ መስኮች (በጤና፤በማህበራዊወዘተ) የሚሰጡ በርካታ ስልጠናዎችን ተሳት ፋለች፡፡ ከቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ትረስት ጋር በትራኮማ እና በተለያዩ የጤና ጉዳዮች ትምህርታዊ መልእክቶችን ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ፀሐይ መስሪያ ቤትዋ ከተቀበላቸው የተለያዩ በጎ አድራጎት ድርጅቶች( የኢትዮጵያ የህግ ባለሙያ ሴቶች ማህበር፤የጎዳና ተዳዳሪ ህጻናት ወዳጆች ማህበርወዘተ) ጋር በመሆን ስለህብረተሰቡ ያለውን በጎና ክፉ ጎን በጥልቀት ዘግባለች፡፡ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች እንዲወ ገዱም ትምህርታዊ መልእክቶችን በማስተላለፍ የበኩልዋን አስተ ዋጽኦ አድርጋለች፡፡ ፀሐይ ተፈረደኝ በማህበራዊ ፕሮግራሞችዋ አስተ ማሪነት ያላቸውን መል እክቶች በትረካ እና ጭውውት መልክ በብእር ስም ስትጽፍ እና ስታስተላልፍ ቆይታለች፡፡ ወላጅ ያጡ እና በችግር የወደቁ ሕጻናት አሳዳጊ አግኝተው እንዲያድጉ አስተዋጽኦ አድርጋለች፡፡

 

ከጡረታ በሁዋላ፡-

ፀሐይ ተፈረደኝ ከኢትዮጵያ ራድዮ ከተሰናበተች በሁዋላ ከተለያዩ ድርጅቶች ጋር የመገናኛ ብዙሀንን ስራ ስትሰራ ቆይታለች፡፡ ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስም በስነተዋልዶ ጤና ዙሪያ በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር ተቀጥራ በጋዜጣ እና በሬድዮ ዘገባ በማቅረብ ላይ ነች፡፡ በዚህ ስራ የሬድዮ ብቻ ሳይሆን የጋዜጣም ጋዜጠኛ ነች፡፡ ይህ ጽሁፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ድረስ ከአጋፔ የቲአትርና ፕሮሞሽን ጋርም በመተባበር በወጣቶች ላይ ትኩረቱን ያደረገ በዋግህምራ ዞን የሚተላለፍ የሬድዮ ስራ ዋና አዘጋጅ በመሆን ፕሮግራሙን በማዘጋትና ጭውውትም በመጸፍ ለአማራ ክልል ሬድዮ እየሰራች ትገኛለች፡፡  

ተሳትፎ፡-

የኢትዮጵያ ሴት ጋዜጠኞች ማህበር (EMWA) ቦርድ ፕሬዝዳንት በመሆን

የኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር (YWCA) ቦርድ አባል በመሆን ተሳትፋለች፡፡

ሽልማት፡-

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በተከበረው የአለም አቀፍ የሬድዮ ቀን በአል 2012 / ተሸላሚ ከነበሩት የመጀመሪያ ምርጥ ጋዜጠኞች አንዷ ፀሐይ ተፈረደኝ ነበረች፡፡ በሽልማቱ ወቅት ከቀረበው ምስክ ርነት የሚከተለው ይገኛበታል፡፡

‹‹………ህዝቡ ውስጥ ውላ እያደረች፣ የህዝቡን ባህል እያስተዋወቀቸ፣ የህዝብ ድምፅ ለመሆን የበቃች አንጋፋ ጋዜጠኛ- ፀሐይ ተፈረደኝ  ………ፀሐይ እንደሪፖርተር-መረጃ ሰርሳሪ፣ እንደፕሮዲውሰር ማራኪ ፕሮግራም ቀማሪ፣ እንደኤዲተር መንገድ መሪ፣እንደጉዞ ዘጋቢ አገር ዟሪ፣ እንደሴት ደግሞ  ፅናት አስተማሪ ናት፡፡››››የሚል ነበር፡፡

ባህርይ፡-

     ፀሐይ ተፈረደኝ ስራ ወዳድነትን፤ግልጽነትን፤ቅንነትን ፤በሰዎች መካከል አድሎ እንዳይኖር ባጠቃላይም ‹‹ሰው ሁሉ እኩል ሰው ነው›› የሚል እምነት አላት፡፡

     ፀሐይ ተፈረደኝ የማይቻል ነገር የለም የምትል ናት፡፡

     ፀሐይ ተፈረደኝ ከሚገባት፤በትክክለኛው መንገድ ከምታገኘው ነገር ውጪ ምንም ከማንም መፈለግ አይገባኝም የሚል እምነት አላት፡፡ 

     ፀሐይ ተፈረደኝ እውሸትን የምትኮንን እውነትን የምትደግፍ ናት፡፡

እግዚአብሔርን መፍራት አገርን መውደድ ከምንም ነገር ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል ባይ ነች፡፡







 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች