50. ትዕግሥት አለሙ ዱባለ TIGIST ALEMU DUBALE
ትእግስት አለሙ ጎበዝ ደራሲና ተዋናይት ናት፡፡ ተመልካች የመሰከረላት ተዋናይት፡፡
በሀገራችን ጥቂት ከሚባሉ የቴአትር ደራሲዎች ተጠቃሹዋ የሆነችው ትእግስት ለብዙዎች አርአያ የሚሆን የሙያ ተሞክሮ ስላላት ታሪኳን አቅርበነዋል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን
በመዝናኛ በመረጃ እና በኪነጥበብ ዘርፍ ያሉ ሰዎችን በኢንሳይክሎፒዲያ
መጽሀፍ አድርጎ የሚያወጣ ሲሆን ትእግስትም ከእነዚህ ተርታ ተመድባለች፡፡ ታሪኳም ከዚህ በታች በተቀመጠው መልኩ ተሰንዷል፡፡
ፍቅር
የነገሰበት ቤተሰብ
በተለያዩ የመድረክ፣ የሬድዮ ብሎም የቴሌቪዥን ስራዎቿ የምናውቃት ፀሀፌ ተውኔት ገጣሚ እና ተዋናይት ትዕግሥት አለሙ ዱባለ ትውልድዋ ናዝሬት ላይ ሲሆን እድገቷ ደግሞ
አዲስ አበባ አራት ኪሎ ነው።የልጅነት ግዜዋ ጣፋጭ እንደነበር ሁሌም ታስታውሳለች። በጣም ከሚዋደዱ ወላጆች ነው የተገኘችው፡፡ የመቶአለቃ አለሙ ዱባለ እና ወ/ሮ ውብአለም አየለ፤ እርስ በእርስ የሚዋደዱና የሚከባበሩ የአባቷን ታጋሽነት እና የእናቷን ሀይለኛነት አቻችለው በሚኖሩ ልጆቻቸውን በፍቅር ማሳደግ ምርጫቸው ካደረጉ ምርጥ ወላጆች እጅ ላይ ነበር ያደገችው። ፍቅርና ሰው ወዳድ ባህሪዋ የእድገቷ መሰረት ፍቅር መሆኑን ያሳብቃል። ቤተሰባቸው እርስ በእርስ እንዲዋደድ እና እንዲፋቀሩ ከማድረጋቸው በላይ ለሌሎች ሰዎች ለአብሮ አደጎች ለጎረቤቶች ለት/ቤት ጓደኞች ሁሉ በፍቅር እንዲኖሩ ሰፊ መሰረት የዘረጉና
በዚያ ደስ የሚል የፍቅር መንገድ እንዲጓዙ ያደረጉ የፍቅር ሞተሮች እንደነበሩ ልጆቻቸው ዛሬ ላይ ይመሰክሩላቸዋል። የዘሩት ፍቅር እጅግ ጥልቅ እና ጠንካራ መሰረት ያለው ስለነበረም በልጅነት እድሜያቸው በሞት ካጧቸው በኋላም እነርሱ ባሰመሩላቸው የፍቅር የመቻቻል እና የመከባበር ከሌሎች ጋር በመተሳሰብ
የመኖር መስመር ላይ እንዲራመዱ እንዳረጓቸው ትዕግስት ትናገራለች ።
ትምህርት
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በቅዱስ ማርቆስ (የዛሬው የጥበብ መንገድ) ትምህርት ቤት በመቀጠል መስከረም ሁለት ወይም በአታ ተብሎ በሚታወቀው ት/ቤት ተምራለች፡፡ ቀጥላም በኢትዮጵያ አንድነት ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን አጠናቅቃ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን በምንሊክ ት/ቤት ተማረች። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቲያትርና ስነ-ጥበብ ት/ቤት ደግሞ በ2000 ዓ.ም የመጀመሪያ ድግሪዋን ተቀብላለች። የግቢ ቆይታዬ እጅግ አውቃለሁ ብዬ
ገብቼ አለማወቄን አውቄ ፣የወጣሁበት ፣ብዙ የተማርኩበት ሙያዬን በትምህርት ያዳበርኩበት ግዜ ነበር ትላለች። በነሲብ የሚሰራውን ስራ ቅርፅ ያስያዘላት፣ የተንጋደደውን ያቃናላት፣ የተንጨረፈፈውን የከረከመላት፣የዕውቀት ግቢ እና የጥበብ ክፍል እንደነበረ ትመሰክራለች። ዝግጅት፣ ትወና ፣የተውኔት አፃፃፍ ዘዴ በተጠናና በእውቀት በታገዘ ስልት ችሎታዋን እንድትሞርድ መምህሮቿ እንዳገዟትና ለዚህም ውለታቸው ከአክብሮት ጋር ምስጋናን ታቀርባለች።
የትዕግሥት አለሙ የስራዋ ጅማሮ በሀይሉ ከበደ ርሆቦት ፕሮሞሽን ተፅፎ በተስፋዬ ገ/ማርያም የተዘጋጀው
የገና ስጦታ ነበር።
የትዕግሥትን ስራዎች በጥቂቱ ዘርዘር አድርገን ብንመለከት:-
መድረክ
ላይ በትወና ከተሳተፈችባቸው መሀከል ፍርሀት፣ሦስተኛው አይን፣የሚተኑ አበቦች፣ዳና፣የመጨረሻው ህልም፣የክፉ ቀን ደራሽ፣የከርቸሌው ዘፋኝ፣መንታ መርፌ ይገኙበታል። በመድረክ ድርሰት የሙሉ ሰዓት ቴአትር ማዶ ለማዶ ከነዝግጅቱ የእርስዋ ሲሆን በዋን አክት ፕሌይ ወይም ባለአንድ ገቢር
ደግሞ በማዘጋጃቤት ምሬት፣ሰላም ፣ጎመን በጤና እና ሽልማትን በፀሀፊነት የሰራቻቸው ናቸው።በሀገር ፍቅር አማት እና ምራትን፣ እስረኞቹና ግምገማ የፃፈች ሲሆን በራስ ቴአትር ነጭ እድል የእርስዋ ነበሩ። በቴሌቭዥን ድርሰቶች በቤቶች ድራማ ላይ ኔትወርክ፣ዕዝን፣ወሬ እና ኮብል የእርስዋ ስራዎች ናቸው። ከአፍሪካ እና ዘውገ ጋር ደግሞ አባት፣አብሮ አደግ እና ስጦታን ሰርታለች። የኢቲቪ 2 የመስኮት ድራማዎች ለቁጥር በሚያታክት መልኩ የቀረቡት የድርሰት ስራዎች የእርሷ ነበሩ።በፊልም ስራ ደግሞ
አንናገርም በትዕግሥት አለሙ ነው የተደረሰው።
አርቲስት ትዕግሥት አለሙ ከተሳተፈችባቸው የሬድዮ ድራማዎች መካከል በትወና የማዕበል ዋናተኞች እና የቀን ቅኝት ይታወሳሉ። በድርሰት በኢትዮጵያ ሬድዮ የቅዳሜ መዝናኛ ላይ ለቁጥር አዳጋች የሆኑ ስራዎችን አቅርባለች።በ96.3 እና በርሆቦት ፕሮሞሽንም ላይ ብዙ ስራዎችዋ ቀርበዋል።
በ2000ዓ.ም አነስተኛና ደስተኛ የበለፀገ ቤተሰብ በተሰኘ ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ አሸናፊም ነበረች።
የግጥምና ዜማ ስራዎች ላይ ፣ሀገራዊ መድረኮች ላይ፣ ከወቅታዊ ሁነቶች ጋር ያሉ ስራዎችም ላይ በብዛት የምትሳተፈው ትዕግሥት ለምሳሌ ከምድር ባቡር ጋር የባቡርን ምርቃት መጀመር ምክንያት በማድረግ
ባቡር የሚል የቪድዮ ክሊፕ ግጥም አዘጋጅታለች
ቪድዮውን ዳይሬክት በማድረግም ሰርታለች። ከጤና ጥበቃ ጋር የአተት በሽታ ላይ ግጥምና ዜማ እንዲሁም ቪድዮ ዳይሬክቲንግ ላይ ጤናችን በእጃችን በሚል ሰርታለች።
ከእሳትና ድንገተኛ አደጋዎች ጋርም የቲቪ ፕሮግራም መግቢያ አለኝታ ወይም ደራሽ በሚል ግጥምና ዜማ ከነዳይሬክቲንጉ ሰርታለች። በብዛት እንደዚህ አይነት ነገሮች ላይ ከመሳተፍዋም በላይ ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ የተፈጥሮ ሀብት አንባሳደር በመሆን ከኢትዮጵያ ዱር እንሰሳት ልማት ጥበቃ ባለስልጣን ጋር
በመተባበር በ8 የኢትዮጵያ ፓርኮች ላይ የተመረኮዘ ግጥም በ ባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ፣ሰሜን ተራሮች፣ ባሌ፣ ጋምቤላ ፣ሲንቅሌ ፣አዋሽ፣ አብጃታ ላይ ሰርታለች። እንደውም በአቢጃታ ውሀው ደርቆ በጣም አሳዛኝ ሁኔታ ገጥሞ ነበርና እነዚህ ላይ ግጥሞች ሰርታ ስሜትን ለመኮርኮር ሁሉም ግድ እንዲለው የሚያነሳሳ የግሏን አስተዋፅኦ በሞያዋ እና በተፈጥሮ ሀብት አንባሳደርነቷ ተወጥታለች ፤ውጤትም የታየበት ነበረና ከምትረካባቸው ስራዎችዋ መካከል ይገኝበታል።
ከባህልና ቱሪዝም ጋር በተደጋጋሚ ለመዘርዘር አዳጋች የሆኑ በርካታ ስራዎችን የሰራችው አርቲስት ትዕግስት አለሙ
‹‹ሴት ትችላለች›› በሚለው
ከሴቶችና ህፃናት ጋር በመሆን በኢሲኤ አቅርባለች ፤ የሀኪሞች ቀን ላይ ደግሞ ጳውሎስ ሆስፒታል ስፖንሰር ያደረገውና ጭብጡንም ብዙ ሰዎች ሰው ሲሞትባቸው ሀኪሞችን ያማርራሉ ግን ከእግዚአብሔር በታች ለሰዎች ባለውለታና ጥሩ ነገር ያላቸው ናቸው በሚል
የአንድ ሀኪምን ሚስት ወክላ የሰራችበት ግጥም ብዙዎችን ያስደሰተና የማይዘነጋ ነው።
አርቲስት ትዕግሥት አለሙ በርካታ የግጥምና ዜማ ስራዎችንም ለሙዚቀኞችም ሰጥታለች። የግጥምና ዜማ ስራ በጣም የምትወደው እና የምትረካበት ስራ መሆኑንም ትናገራለች። ትዕግስት በበርካታ የስነ-ፅሁፍ ስራዎች ላይ እንዲሁ ትሳተፋለች፡፡ ለአብነት በቅርቡ ፍቅርን ጨምሩ ሰላምን ፍጠሩ በሚል በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቲአትር ቆንጆ ስራ ሰርታ እርሷም ተመልካቹም ስሜታዊ ሆነው የታደሙበት የስነፅሁፍ ምሽት የሚዘነጋ አይደለም። የድሮ ፍቅራችንን መተሳሰብና መዋደዳችንን እንመልሰው የሚል አንደምታም ነበረው።
አርቲስት ትዕግሥት አለሙ በስራዎቿ ሁሉ ትረካለች፡፡ አብዝታም ትወዳቸዋለች ፡፡አብልጣ ግን በጣም የምትወዳቸው መዝሙር ፈንቴ ፅፎት ማንያዘዋል እንደሻው ያዘጋጀው ዳና የመድረክ ቲያትር እና ቴዎድሮስ ተ/አረጋይ ፅፎት ዳንኤል ሙሉነህ ያዘጋጀውን 3ኛውአይን የመድረክ ቲያትሮችን ነው። የሬድዮ ድራማዎችዋን ግን ከምንም አታወዳድራቸውም።
አርቲስት ትዕግሥት አለሙ በአሁኑ ሰዓት ሩብ ጉዳይ የተሰኘ ተውኔት ከተስፋ ኢንተርፕራይዝ ጋር በብሄራዊ ቴአትር እየሰራች ትገኛለች።
በቀጣይ ብዙ ለመስራት እቅድ ያላት አርቲስት ትዕግስት አለሙ በድርጅቷ ፋሬስ አማካኝነት የስነፅሁፍ ምሽቶችን፣የሬድዮ ፕሮግራሞችን፣በተለይ ደግሞ ሀገራዊ ይዘት ያላቸውን መድረኮች እንዲሁም ኢቨንቶችን የማዘጋጀት ዕቅዶች አሏት።
መዝጊያ ፤ ተዋናይትና ጸሀፌ-ተውኔት እንዲሁም
ገጣሚ ትእግስት አለሙ ለኪነጥበብ የተፈጠረች ናት፡፡ ለጥበብ ሁሉን ሁኝ ከተባለች ትሆናለች፡፡
ስነ-ጽሁፍና ቴአትር ውስጥ
አንድ ጊዜ ገብታ በዚያው ሰምጣ የቀረችው ትእግስት
ጥቂት ከሚባሉ የሀገራችን ሴት የቴአትር ጸሀፊዎች አንዷ ናት፡፡ በሀገራችን የቴአትር ታሪክ
ውስጥ ሴት የቴአትር ደራሲያን በጣት ቢቆጠሩ ነዉ፡፡ ከእነዚያ ውስጥ ትእግስት በሙሉ ሀይል ከሚሰሩት ውስጥ ትመደባለች፡፡ ትእግስት ጸሀፊ ብቻ አይደለችም ስትተውንም ልዩ ብቃት እንደምታሳይ ባለሙያዎች ይመሰክሩላታል፡፡
በሙያዋ ባሳለፈችባቸው አመታት አንድ ነገር
ለማበርከት ስትጥር የኖረችው ትእግስት ህልሙዋ እንደተሳካላት ብታምንም በዚህ ብቻ የምትቆም አይደለችም፡፡ ዛሬም መድረክ ላይ ክህሎቷን ታሳያለች፡፡ ብእር ከወረቀት አዋህዳ መጻፏንም ተያይዛዋለች፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች
ትእግስት ለዞህ ሀገር ኪነ-ጥበብ
ያበረከተችው አንድ ቁምነገር አለ ብለን በጽኑ ስላመንን ታሪኳ በአዲሱ ትውልድ
እንዲታወቅ አድርገናል፡፡ / ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሮብ ሀምሌ 14 2013 ዊኪፒዲያ ላይ ወጣ››/
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ