49. ያሬድ ቁምቢ ሰንበቶ -YARED KUMBI SENBETO    

ያሬድ ቁምቢ ሰንበቶ በዋዜማ ሬድዮ ላይ በእውቀት ከሚሰሩ ብርቱ ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም በፋና ሬድዮ አቅሙን ያሳየው ያሬድ ማነው? በምን አይነት መንገድ አለፈ? ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በመዝኛኛ በመረጃ እና በጥበብ ዘርፍ ያሉ ሰዎች ታሪካቸው ሊሰነድ እንደሚገባ ያምናል፡፡ የያሬድ ታሪክ እነሆ፡፡

  ልጅነት እና ትምህርት

ጋዜጠኛ ያሬድ ቁምቢ ከእናቱ / ሙሉ ለማ እና አባቱ አቶ ቁምቢ ሰንበቶ በወርሃ ነሐሴ 5 ቀን 1978 ነበር የተወለደው፡፡

ሁለት ወንድም እና አንድ እህት ያሉት ሲሆን ተወልዶ ያደገውም በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ ጎላ ሰፈር እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

እድሜው ለትምህርት ሲደርስም  ጎላ ሚካኤል ቅጥር ግቢ ውስጥ በሚገኘው አቦይ ቄሺ እና ጳውሎስ የቄስ ትምህርት ቤት አሳልፏል፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በዘርዓይ ድረስ እና ለገሀር አካባቢ በሚገኘው እድገት በህብረት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት 1986 እስከ 1993 . ድረስ ተከታትሏል፡፡ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በጥቁር አንበሳ እና አዲስ ከተማ መሰናዶ አጠናቋል፡፡

የከፍተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ 1998 . በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል በሬዲዮ የትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

በህንድ ሀገር እውቅና ባለው ጃዋህራል ነህሩ ዩኒቨርሲቲ ‹‹Indian mass communication institute››በጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን በመማር ዲፕሎማንም ማግኘት ችሏል፡፡

            የጋዜጠኝነት ጅማሮ

ከልጅነቱ ጀምሮ ለጋዜጠኝነት እና ለስነ ጽሁፍ በነበረው ፍቅር ምክንያት በዙሪያው ያሉ ታላላቆቹ የወደፊት ሙያህ ይህ ነው ሲሉ በእርግጠኝነት ይናገሩለት ነበር፡፡

ገና በልጅነቱ አጫጭር ልብ- ወለዶችን እና ግጥሞችን በመፃፍ በዙሪያው ላሉት ያነብላቸው ነበር፤ጋዜጦችም የሚገዙ ሰዎች ካለበት አስጠርተው ድምጹን ከፍ አድርጎ እንዲያነብላቸው ያደርጉ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ራዲዮ የህፃናት ፕሮግራም ላይ ደብዳቤዎች እና ግጥሞችን በመላክ ደግሞ ተሳትፎውን አሳደገ፡፡

97.1 ራዲዮ ጣቢያ ላይ የብዕር ትሩፋት የሥነ-ጽሁፍ ዝግጅት ላይ የሥነ-ፅሁፍ ስራዎቹን በማቅረብ ለመጀመሪያ ጊዜ 1996 . ራዲዮ ስቱዲዮ ጋር ተዋወቀ፡፡

በአዲስ ከተማ ትምህርት ቤት የሚኒ-ሚዲያ ዝግጅቶችን በአቅራቢነት እና በአወያይነት በመሳተፍ የራዲዮ ህይወትን ይበልጥ እንዲተዋወቀው ሆኗል፤በዚሁ ወቅት ለመጀመሪያ በሚባል መልኩ የቴሌቭዥን ሚኒ -ሚዲያ በጋራ በመጀመር ተማሪዎች በፕላዝማ እንዲከታተሏቸው በማድረግ የጋዜጠኝነት አድማሱን ወደ ቴሌቭዥን ማሸጋገር እንደሚቻል የተማረበት ነው፡፡

ይሁንና ለራዲዮ የነበረው ፍቅር ቴሌቭዥን ማሸነፍ አልቻለም፤ለመጀመሪያ ጊዜም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቀን መርሃ -ግብር የጋዜጠኝነት እና ኮሚዩኒኬሽን ትምህርት ክፍል ትምህርትን መስጠት ሲጀምር ከመጀመሪያዎቹ ተማሪዎች አንዱ በመሆኑ ይኮራል፤በቆይታውም በራዲዮ ዘርፍ ተመርቋል፡፡

በትምህርት ቆይታው የመጨረሻ ዓመት ላይ እንደሚደረገው ኢንተርንሺፕ አንጋፋው ጋዜጠኛ ልባርጋቸው ሽፈራው በመሠረተው ዴልታ መልቲሚዲያ መሠረታዊ የጋዜጠኝነት ሥራ ጀመረ፡፡

ስራውን ወደደው፡፡ ጋዜጠኛ ልባርጋቸው ሽፈራው ጋር ከትምህርቱ ጎን ለጎን የኢንተርንሺፒ (የመስክ ልምምድ) ጊዜው ቢያበቃም በወር አንድ ሺህ ብር እየተከፈለው ሊሰራ ችሏል፤በዚህም በራዲዮ እኛም በቤታችን የተሰኘ ትኩረቱን ኤች አይ ኤድስ ላይ ያደረገ በኤፍ ኤም 97.1 እንዲሁም የህብረት ስራ ድምፅ የተሰኘ በኢትዮጵያ ራዲዮ ላይ ከጳውሎስ አለማየሁ እና ከመላኩ ታደሰ ጋር መሥራትን ጀመረ፡፡

በዚህ ብቻ ሳያበቃ በሰሜን አሜሪካ በሚተላለፈው የታማኝ በየነ ቻናል ዶክመንተሪ እና ዘገባዎችን በመስራት በራዲዮ እና ቴሌቭዥን ጋዜጠኝነቱ ቀጥሏል፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተምሮ ከተመረቀ በኋላም በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን በራዲዮ አዘጋጅነት ለአንድ ዓመት ያህል፣በልደታ ክፍለ- ከተማ ‹‹ነጋሪ.›› የተሰኘ ጋዜጣና መጽሄት በከፍተኛ አዘጋጅነት ለስምንት ወራት ያህል በመስራት አገልግሏል፡፡

በአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን የአንድ ዓመት ቆይታው ስለ ፍቅር እንወያይ፣የህትመት ዳሰሳ  እንዲሁም የተለያዩ ፍርማቶችን በመቅረፅ ሰርቷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በአዲስ ቲቪ ተወዳጅ የነበረውን እውቅ ሠዎች በእንግድነት የሚጋበዙበት መሰናዶ ሃሳቡን ከማመንጨት አንስቶ ተቋሙን እስከለቀቀበት ጊዜ ድረስ ሰርቷል፡፡

ረዥም ጊዜን ያገለገለበትን ፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን ወርሃ ሚያዝያ 2004 . ተቀላቅሎ በራዲዮ ውይይት፣ሀኪም በፋና፣ቢዝነስ በቅዳሜ መዝናኛ 60 ደቂቃ እና 120 ደቂቃን በመምራት፣በአውድ ዓመት እና በልዩ ዝግጅቶች ወቅት በቀጥታ ስርጭት ጋዜጠኛ ያሬድ ቁምቢ የማይታጣ ነበር፡፡

90 ደቂቃ እጅግ ለዛ ያላቸው ሌሎች ሠዎች ባላዩበት እና ባላስተዋሉበት መልኩ ፊቸር ዜና በመስራት፣የጠጠረን ዜና እንዲደመጥ በማድረግ  በፊቸር ስራው እውቅናን ማግኘት ችሎም ነበር፡፡

በውጭ ትንታኔ 90 ደቂቃ እና ቅዳሜ 30 ደቂቃ ዓለም ዓቀፍ ጉዳይ ላይ ያኮሩ ትንታኔዎችንም ይሰራ ነበር፡፡

በራዲዮ ፋና ላይ ምርጥ ደብዳቤ፣ራዲዮ ቱር፣ገስት ዲጄ፣ቡና ጠጡ በተሰኙ ፕሮግራሞች ላይም ሰርቷል፡፡

  ያሬድ የማይገባበት የለም ይባላል፡፡

የፋና የኢንተርኔት ስርጭት እንዲህ ሳይሆን ከስቱዲዮ በዜና አቅራቢ በሚቀርብበት ወቅት የመጀመሪያው ሊባል የሚችል የቴሌቭዥን የመስክ ዘገባ በመስራት ቀዳሚ ነው፡፡

የካቲት 2009 . ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የለቀቀው ወደ ሰሜን አሜሪካ በመጓዙ ቢሆንም ከጋዜጠኝቱ ጋር አልተለያየም፤በስደት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞች በተመሰረተው ዋዜማ ሬዲዮ ላይ ተሳትፎ ያደርጋል፡፡

መዝጊያ ያሬድ ቁምቢ በስራ አለም በቆየባቸው 15 አመታት ሙያውን የበለጠ ለማዳበር ትልቅ ሙከራ አድርጓል፡፡ ከልጅነት ይዞት የመጣው ሙያ በመሆኑ በየወቅቱ በትምህርት እና ጥረትን በማከል ሊያዳብረው ችሏል፡፡ ያሬድ በሙያው አንድ አሻራ ለማኖር የበኩሉን ጥረት በማድረግ ላይ ሲሆን ከዚህ በበለጠ መልኩ እድሎች ከተመቻቹ በጋዜጠኝነት ዘርፍ አንድ ቁምነገር ማከናወኑ አይቀርም፡፡ የበሳል ጋዜጠኞች ስብስብ በሆነው በዋዜም ሬድዮ ላይ አንድ ትልቅ ጥረት እያደረገ ያለው ያሬድ ነገ ደግሞ በተጨማሪ ጥረት እናገኘዋለን፡፡


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች