47‹‹በግብርና ትምህርት ክፍል ብመደብም ጋዜጠኛ እንደምሆን እርግጠኛ ነበርኩ፡፡››

    ትዕግስት በጋሻው ተሊላ-  Tigist Begashaw Telila

            ትእግስት በታዛ ፕሮግራሟ ትታወቃለች፡፡ 90 ደቂቃ የቲቪና የሬድዮ  መሰናዶ አድማጭ ተመልካች በሚገባ ያውቃታል፡፡ ጎበዝ ኤዲተርም ሆና 90 ደቂቃ ሲጀመር የማይረሳ አሻራዋን አኑራለች፡፡ በቲቪና በሬድዮ በየጊዜው ብትቀርብም ያልታየ አቅም የተቸረች በመሆኑ ታሪኳ ተሰንዶ እንዲቀመጥ አድርገናል፡፡ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን ባለፉት 2 ወራት 100 በላይ የመዝኛኛ የጥበብ እና  የመረጃ ሰዎችን ግለታሪክ ሲያወጣ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ ወደ ትእግስት በጋሻው እናልፋለን፡፡

        ትውልድ  ልጅነት እና ትምህርት

ጋዜጠኛ ትዕግስት በጋሻው  ሚያዝያ 25 1977 . ከመምህር አባቷ አቶ በጋሻው ተሊላ እና ከእናቷ / የሺመቤት ከተማ በአዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስፍራው ጨርቆስ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ  ነው የተወለደችው፡፡

ሁለት ወንድም እና ሁለት እህት ያላት ሲሆን ለቤታቸው ሦስተኛ ልጅ ናት፤ከልጅነቷ ጀምሮ ማንበብ ፣መፃፍ እና ሠዎች ፊት ቀርቦ ንግግር ማድረግን ትወድ ነበር ፤የአማርኛ መምህሮቿም ይህንኑ ይነግሯት ነበር፡፡

ለዛሬ መሰረቷም የአማርኛ መምህሮ ይሰጧት የነበረው አስተያየት ሲሆን አባቷም ማንበብን እንደትወድ ያበረታቷት  የነበረ  ሲሆን የተለያዩ የተረት መፅሀፍትን በተለይ ‹‹እንቅልፍ ለምኔ››የተሰኘውን መፅሀፍ በተደጋጋሚ እንዳነበቡላት ታስታውሳለች፡፡

ትዕግስት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፈለገ-ዮርዳኖስና በጠመንጃ ያዥ ትምህርት ቤቶች   የተማረች ሲሆን ገና  በዚሁ ትምህርት ቤት እየተማረችም የሰንደቅ ዓላማ መስቀል እና ማውረድ ስነስርዓት ላይ ትረካዎችን፣ማሳሰቢያዎችን፣ልብወለዶችን እንድታነብ ትመረጥ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ነበር የሚድያ ፍላጎት  ያደረባት፡፡

በኢትዮጵያ ቤተሰብ መምሪያ ውስጥም የተለያዩ የኪነ- ጥበብ ስራዎች ላይ ትሳተፍ የነበረ ሲሆን  በብሩህ የጋዜጠኞች አማተር ክበብ ወስጥም ታቅፋ የተለያዩ ስልጠናዎችን በመውሰድ የጋዜጠኝነት ችሎታዋን ማዳበር የጀመረችው ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነበር፡፡

በኢትዮጵያ ራዲዮም የቅዳሜ መዝናኛ ላይ ከጓደኞቿ ጋር በመሆን  በዳንኤል አያሌው እና  በሌሎች የመዝናኛ ባልደረቦች አማካይነት ጭውውቶችን፣ግጥሞችን እና ድራማዎችን በማቅረብ ትሳተፍም ነበር፤በተጨማሪም በለገዳዲ ራዲዮ ላይም ተከታታይ የራዲዮ ድራማን ትሰራ ነበር፡፡ በተለይ ትእግስት በአንድ ወቅት ለቅዳሜ መዝናኛ የጻፈችው መጣጥፍ ላይ አበረታች አስተያየት በመሰጠቱ ትልቅ ሞራል እንደሆናት ትናገራለች፡፡ ይህንንም ሀሳብ የሰጣት ዳንኤል አያሌው መሆኑን በዚህም ትልቁ ባለውለታዋ  እንደሆነ ታስባለች፡፡

ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ማለትም ዘጠነኛ እና አስረኛ ክፍል ትምህርቷን በንፋስ ስልክ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና የአስራ አንድ እና የአስራ ሁለተኛ ክፍል ትምህርቷን  ደግሞ በአብዮት ቅርስ ትምህርት ቤት  ተምራለች፡፡

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲም  ልማረው እችለዋለሁ ብላ ባልጠበቀችው ትምህርት በግብርና ትምህርት ክፍል ስር የሆነውን የእንስሳት የዱር ህይወት እና የግጦሽ መሬት ሳይንስን ተምራለች፤በእርግጠኛነት ግን ይህንን ትምህርቷን እንደጨረሰች ጋዜጠኛ እንደምትሆን ትናገር ነበር፡፡

በኋላም  ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሰቲ   በስነ ልቡና ትምህርት በዲግሪ ደረጃ መማር ችላለች፡:

     የጋዜጠኝነት  ጅማሮ

      ‹‹ሁል ጊዜ አዲስ ነገር መፍጠር ፈልጋለሁ፤ጉዞዬን አልጨረስኩም፡፡››

የተለያዩ ሚዲያዎችን ታዳምጥ የነበረችው ትዕግስት በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ‹‹ኳንተም ሰርክል››በተሰኘ ተማሪዎች በነፃነት የሚሰባሰቡበት እና የሚነጋገሩበት ላይ በመቅረብ ሃሳቧን ስታካፍል ድምጽዋ  እንደ አነጋገሯ እንደሚያምር ይነግሯት ነበር፡፡ኳንተም ሰርክል የተለያዩ ጠቃሚ እሳቤዎች የሚፈልቁበት እና ትእግስትም ጠቃሚ እውቀት የቃረመችበት ስብስብ ነበር፡፡

ወርሃ መስከረም መጨረሻ  ፋና ኤፍ ኤም አዲሱ ስርጭት ሰራተኞችን ለመቅጠር ባወጣው ማስታወቂያ ተወዳድራ ከሚፈለጉት አስር ሰዎች ውስጥ ሳትካተት በተጠባባቂነት ተያዘች፤የወጣትነት ንዴት እና አለመረጋጋት ተከትሎ ወደ አንድ ግብርና ላይ ወዳተኮረ ተቋም ዘንድ  ተወዳድራ ወደ ዋግ ህምራ ተመደበች፡፡ ይህ ደግሞ በቤተሰቧ ፈቃድን ሳያገኝ ቀረ   ቤተሰቦቿ ለጋዜጠኝነት ያላትን ፍቅር ስለሚያውቁ ታግሳ  ፋና የመግባቱ ነገር  ላይ ትኩረት እንድትሰጥ  ምክር ለገሷት፡፡በዚህ መሃል ከፋና ተደወለላት፡፡

ፋና ኤፍ ኤፍ ላይ ከመጋቢት ወር 1999 ጀምሮ በስምንት መቶ አርባ አምስት ብር ተቀጠረች፡፡

ፋና ተቀጥራ በቆየችባቸው ስድስት ዓመታት ከጀማሪ ሪፖርተርነት እስከ ኤዲተርነት ያለ እረፍት ገጠመኝ እና ማስታወሻ፣ቡና ጠጡ፣ፍቅር ትዳር ቤተሰብ  የቀጥታ የስልክ ውይይት፣ዜና መጽሄት፣ዘጠና እና መቶ ሃያ ደቂቃን  ጨምሮ  የተለያዩ ፕሮግራሞችን መስራት ችላለች፡፡

ትዕግስት ሰዎችን በማድመጥ፣ያላቸውን ችሎታ እንዲያወጡ በማድረግ እና በጥሩ የመምራት ችሎታዋም ትጠቀሳለች፡፡

ትእግስት ጥሩ የመምራት ክህሎት አላት የሚባለው በተለይ 2003 ጀምሮ አየር ላይ የዋለው 90 ደቂቃ አርታኢ በነበረች ጊዜ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት 90 ደቂቃ ፎርማት በአቀራረቡ ሳቢ ስለነበር ይህ በሳምንት 5 ቀን የሚተላለፍን መሰናዶ ከሌሎች ባልደረቦች ጋር በመሆን መከታተል ነበረባት፡፡ ትእግስት ሰውን ለማሰራት  የሚቀል መልካም ሰብእና እንዳላት አብረዋት የሰሩ ሁሉ ይመሰክራሉ፡፡ የአማርኛ ክህሎቷ ወይም ቋንቋን የማቃናት ችሎታዋ ቀድሞ የዳበረ ስለነበር የሚመጡ 90 ደቂቃ ጉዳዮችን  በወጉ ለማድረግ ችሎታው እና ፍላጎቱ ነበራት፡፡

2003.  ከዛሬ 10 አመት በፊት 90 ደቂቃ ለአድማጭ አዲስ ብቻ ሳይሆን አቀራረቡም ለየት ያለ ስለነበር በጣቢያው ሃላፊዎች ዘንድም ትኩረት ያገኘ ነበር፡፡ ትእግስትም እንደ ስራ መሪ ከአርታኢነት ባሻገር  ራሷ በቀጥታ ስርጭት 90 ደቂቃን በመምራት  የዳበሩ መረጃዎችን ለአድማጭ በማቀበል የሚድያ ሰው ሃላፊነቷን በሚገባ ተወጥታለች፡፡ ትእግስት ያሰራቻቸው  ወደ 4 የሚሆኑ ሰዎች ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ እንዳስረዱት  ትእግስት እንደ ስሟ ትእግስትን የታደለችና የስራ ሞራል የማምጣት አቅም ያላት ሰው ናት ሲሉ ሀሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡

 ትእግስት 6 አመት የስራ ልምድ ካገኘች በኋላ የራስን ስራ መፍጠር ወደሚለው እሳቤ ነው የገባችው፡፡ በጋዜጠኝነት የበለጠ ማደግ የምትችለው በዚህ መልኩ እንደሆነ ስላሰበች በጉዳዪ ላይ ጊዜ ሰጥታ ማሰብ ጀመረች፡፡

ሁል ጊዜ አዲስ ነገር መፍጠር አለብኝ እያለች ለራሷ ትነግረው ነበር፡፡ ይህም ሀሳብ የቅርብ ባልደረባዋና ጓደኛዋ እጸገነት ላአቀ ጋር ስለነበር ጉዞ በዚህ መልክ ተጀመረ፡፡

ጉዞው 2005 . ላይ ከአዲካ ጋር 97.1 ማለፊያ በተሰኘ ፕሮግራም ተጀመረ፡፡

 ማለፊያ አድማጭን እያዝናና ብሎም እያስተማረ ቆየ፡፡ ትእግስት እና እጸገነትም  የአድማጭን ስሜት  በተሻለ መልኩ ለማርካት  ይደክሙ ነበር፡፡ ጥረታቸውም ይታይ ነበር፡፡

ትዕግስት እና እፀገነት በጋራ በመሆን 97.1 ከነበራቸው በጣም ጥሩ የሚባል የስድስት ወራት ቆይታ በኋላ ታዛ የተሰኘ በብዙ አድማጮች የተወደደ የራዲዮ ፕሮግራምን በፋና ኤፍ ኤም 98.1 ጀመሩ፡፡

ታዛ ሁለት ጓደኛማች ሴቶች ስለ ህይወት ቁጭ ብለው የሚያወሩበት ያልተገደበ አዝናኝ እና ቁምነገር የሚያስጨብጥ ፣በኑሮ ዘዬ ማህበረሰቡን በድግግሞሽ ለውጦ እራሳቸውን ለመለወጥ አልሞ የተጀመረ ፕሮግራም ነው፡፡ ታዛ ሀሙስ አርብ ቅዳሜ የሚቀርብ መሰናዶ ሲሆን በተለይ ሰዎች በማህበራዊ ህይወታቸው የሚያልፉበትን መንገድ ፍንትው አድርጎ የማሳየት አላማ ያለው መሰናዶ ነው፡፡ ታዲያ የፕሮግራሙ ባለቤቶች ይህንን መሰናዶ የበለጠ ማራኪ ለማድረግ ታላቅ ጥረት ስለሚያደርጉ አድማጭ የሚሳተፍበት መሰናዶ ለመሆን ችሏል፡፡ ትእግስት እና እጸነነት ይህን መሰናዶ ከጀመሩ 8 አመት እየሞላቸው ሲሆን በእነዚህ አመታት የተሻለ አማራጭ የሬድዮ ፕሮግራም ለመስራት የተቻላቸውን አድርገዋል፡፡ በበቂ ዝግጅት የሚሰሩ በመሆኑም ዛሬ ታዛ ተደማጭ ከሆኑ ፕሮግራሞች አንዱ ለመሆን ችሏል፡፡

በተጨማሪም በፋና ሬዲዮ ዘጠና እና መቶ ሀያ ደቂቃን በፍሪላንሰርነት እንዲሁም በቴሌቭዥኑም  በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡  ትእግስት 90 ደቂቃን ሲመሰረት አንስቶ የምታውቀው በመሆኑ ዛሬ ስትመራ ከበቂ ልምድና እውቀት ጋር ነው፡፡ ብዙ ጀማሪ የሚድያ ሰዎች የትእግስትን አርአያ በመከተል ሙያቸውን በሚገባ ማዳበር ችለዋል፡፡

ከልጅነቷ ጀምሮ ትሳተፍበት በነበረው የመድረክ መምራት ስራም የተለያዩ ትላልቅ የተባሉ መድረኮችን መምራት ችላለች፡፡ ትእግስት መድረክ ስትመራ በቂ የሆነ ዝግጅት ስለምታደርግ ይዋጣላት ሲሉ መድረክ ስትመራ የተመለከቱ ምስክርነት ይሰጣሉ፡፡

 ትእግስት በመሞከር ታምናለች፡፡ ለምን ወደ ፊልም አለም አልገባም በሚልም ኮንደሚኒየሙ እና ባቢሎን በተሰኙ ፊልሞች ላይም ተሳትፋለች፡፡

WHO ጋር በጋራ በመሆን የተለያዩ ሞጁሎችን በመስራት የጊዜ አጠቃቀምን በእጅጉ ተምራበታለች፡፡

በደቡብ አፍሪካም የኦሞ ማስታወቂያ ሲሰራ ተወዳድራ በራስ መተማመን እና ድምፅን በተገቢው በመጠቀም አንደኛ በመውጣት ነበር የሄደችው፤በደቡብ አፍሪካ በተቀረጸው በዚህም ስራዋ 45 ደቂቃ ማስታወቂያን ለመስራት የሚወስደውን ሰዓት ሁሉም ባለሙያ በሙያው የሚያደርገውን የራሱን ሃላፊነት መመልከቷ በእጅጉ እንዳስተማራት ትናገራለች፡፡ ትእግስት ባላገሩ አይድል የተጀመረ ሰሞን 2004 ግድም የፕሮግራም መሪ በመሆን 4 አመት ሰርታለች፡፡ ለአንድ አመት ያህል ደግሞ ጥበብ በፋና በተሰኘው ፕሮግራም ላይ ሙያዊ የሆነ አስተዋጽኦዋን አክላለች፡፡

                   ቤተሰባዊ ሕይወት

     ‹‹ሕይወት የሂደት ውጤት ነው፡፡››

ትዕግስት ትዳር የመሰረተች ሲሆን  2 ልጆች እናትም ነች፡፡

አሁን የደረሰችበት ሁሉ የሕይወት ሂደት ነው በማለትም ትናገራለች፤ከልጅነቷ ጅምሮ ያለፈችባቸው መንገዶችም እያስተማሯት እና ቅርፅ እያስያዟት እርሷን እየሰሯት እንደመጡ ነው የምትመሰክረው፡፡

ትዕግስት ለወደፊትም ያለፈችባቸውን መንገዶችም በመፅሀፍ ለመፃፍ ፍላጎትም አላት፡፡

መዝጊያ ÷ ትእግስት ለሚድያ ስራ ነው የተፈጠርኩት ብላ ስለምታምን ሙያዋን ወዳው ነው የምትሰራው፡፡ ሁለገብ በመሆን ስለምትሰራም ይህም ትልቅ ርካታን ይሰጣታል፡፡ በዚህ ሙያ በቆየችባቸው  አመታት ሁሉ ነገር አልጋ በአልጋ ነው ባይባልም ሁሉንም በትእግስት አልፋ ለራሷ  የምታምንበትን እያደረገች ኖራለች፡፡  ሚድያ የማይሞላ ቋት ነው የምትለው ትእግስት በጥረት የምታምን በመሆኑ ይህ ታላቅ ጥረቷ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡  ‹‹…የምፈልገውን በቃ አግኝቻለሁ›› ብላ የማትቆመው ትእግስት ሁሌም በጥረት ላይ ነች፡፡ ፍለጋዉ አያልቅም እንደማለት፡፡ በሳምንት 3 ቀን በሬድዮ አየር ላይ ስትገባ ለአድማጭ አንድ ቁምነገር ጣል እንደምታደረግ ታስባለች፡፡ ይህም ትልቅ ርካታን ይፈጥርላታል፡፡ አድማጭ በሬድዮ ገብቶ መተንፈሻ ላይ የውስጡን ሲናገር እርሷና ጓደኛዋ በፈጠሩት መድረኩ መሆኑን ስታስብ እንኳንም ታዛ ተጀመረ ትላለች፡፡

  ትእግስት ፣ሰውን  በማበረታታት የምታምን በመሆኑ  ሰዎች ሁልጊዜ ምክርን ይጠይቋታል፡፡ ትእግስት በሬድዮ አቅራቢነት ብቻ አትወሰንም ወሳኝ የሆኑ አለም አቀፍ እና ሀገራዊ ስብሰባዎችን ስትመራ የሚድያ ሰብእናዋን ታስከብራለች፡፡ በእነዚህ የመድረክ ስራዎቿ ብዙዎች ታላቅ ከበሬታን ይቸሯታል፡፡ ትእግስት በዚህ ብቻ አትወሰንም ትልቅ በሆነው የሀገራችን የማስታወቂያ ኢንዱስትሪ ላይ የራሷን አሻራ እያኖረች ነው፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ትእግስት በስራ አለም በቆየችባቸው 14 አመታት የባከነ ጊዜ የላትም፡፡  ጊዜዋ ስላልባከነም አንድ ቁምነገር ማከናወን የቻለች ብርቱ ሴት ልንላት እንችላለን ፡፡ ገና በልጅነት አንድ ተብሎ የተጀመረው የሚድያ ስራ ዛሬ ትእግስት አንድ ትልቅ ነገር አስተምሯታል፡፡ ይህም ሰው ካሰበበት የህልሙን መኖር እንደሚችል፡፡ በአንድ በኩል ቤተሰብ እየመራች እንደ እናት አደራዋን እየተወጣች በሙያዋም ወደፊት አያለች ነው፡፡  አዲሱ ትውልድ ይህን የትእግስትን ታሪክ ሲያነብ አንድ ነገር ይማራል፡፡ በአዳዲስ ተሞክሮዎች ማለፍ ሰውን በብዙ መልኩ እንደሚለውጠው፡፡ ታሪኳን በዚህ መልኩ እንድናቀርበው ስንሻ አንድ  አሻራ ማኖሯን ግምት ውስጥ በማስገባት ነው፡፡ ትእግስት ከዚህ በላይ ጨምራ ትመጣለች-መልካም እድል/ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሀምሌ 19 2013 በዊኪፒዲያ ላይ የወጣ ሲሆን ተገቢው ማሻሻያም እየተደረገለት ወደ አንባቢ ይደርሳል፡፡  /






አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች