46.ካሣ አያሌው
ካሣ -KASSA AYALEW KASSA
የተጓዥ ነቃሹ ካሳ
ካሳ አያሌው
ካሳ ፣በተጓዥ ነቃሽ ፕሮግራሙ ስም ያተረፈ ጋዜጠኛ ነው፡፡
ለሙያው የተፈጠረ ነው፡፡ ሙያውን ያከብራል-ይወዳልም፡፡ 18 አመት በቆየበት ሙያ ላይ ዛሬም በጽኑ እምነት
ያገለግላል፡፡ በሬድዮ ጋዜጠኝነት፤ በድርሰት ስራ እንዲሁም
በፊልም ሁለገብ እውቀትና ክህሎቱን እያሳየ ያለው ካሳ አያሌው
ማነው? ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በጥበብ ፤ በመረጃ እና
በመዝናኛ ዘርፍ ታሪካቸውን በጥራዝ መልክ በኢንሳይክሎፒዲያ
ከሚሰራላቸው አሻራ ያኖሩ መሀል ካሳ ይጠቀሳል፡፡ ካሳን እነሆ አንብቡት፡፡
የትውልድ ታሪኩና የስሙ መጠሪያ ግንኙነት
ካሣ አያሌው ካሣ
ተወልዶ ያደገው አዲስ አበባ ከተማ ልዩ ስሙ‹‹ ሽሮ ሜዳ ››ተብሎ የሚጠራው ሰፈር ነው። አባቱ አቶ አያሌው ካሣ እና እናቱ
ወ/ሮ በላይነሽ ተ/ወልድ በጋብቻ ከተጣመሩ አንስቶ ቤታቸው የልጅ ፍሬ ማግኘት ሳይችል ረጅም ዓመታትን ቆይቷል። በዚህ ምክንያት
እናቱ መካን እንደሆኑ ታምኖ የአብራካቸውን ክፋይ እንደማያገኙ እርግጠኛ ሆነዋል።
ነገር ግን የወላጆቹ
እርግጠኛ የሆኑበት ጉዳይ ከአምላክ ዘንድ ከተፈቀደው የሚገናኝ ሆኖ እስከ መጨረሻው አልዘለቀም። ልክ እንደ ካህኑ ዘካርያስና
ኤልሳቤት የልጅ ፍሬን ማየት ተስፋ በመነመነበት ትዳር ውስጥ ያልተጠበቀውና ያልታሰበው ተስፋ ባልተጠበቀና ባልታሰበ ቸጊዜ ከተፍ
አለ። «መካን» ተብለው የተቆጠሩትና እርሳቸውም ይህንኑ አምነው የተቀበሉት ወ/ሮ በላይነሽ ተ/ወልድ በሆዳቸው ፅንስ ቋጠሩ።
እርግዝናቸው እውን ሆኖ የቤቱን ተስፋ አንሰራራው። በዘጠነኛ ወራቸው የካቲት 8/ 1974ዓ.ም ለእኝህ እናቱ የመጀመሪያም
የመጨረሻም የሆነው ልጃቸው ካሣ አያሌውን ተገላገሉ።
የካሣ መጠሪያ ከዚህ
አወላለዱ ጋር የተያያዘ ታሪክ እንዳለው ይነገራል። «አባቴ በንጉሡ ዘመን ከመሳፍንቱ ወገን የነበረ ከበርቴ ነበር። ደርግ ወደ
ስልጣን ሲመጣ ያለ የሌለ ሃብት ንብረቱን ወርሶ የድህነት ህይወት ውስጥ ጥሎታል። በዚህ ሳቢያ ክፉኛ ተበሳጭቶ ለጤና ችግር
ተዳርጎ ቆይቷል። በዚህ ላይ በኋለኛ ዘመኑ ካገባት ባለቤቱ ልጅ ባለመውለዱም የከፋ ሀዘን ገብቶት ነበር። በዚህ ሁኔታ ውስጥ
እያለ ነው እንግዲህ እኔ ልወለድ የቻልኩት። የኔን መወለድ ከአምላክ የተሰጠው የመጨረሻ ዘመኑ ስጦታ እንደሆነ አምኖ ባጣውና
በተቀማው ሁሉ ምትክ ፈጣሪው እንደ ካሰው አስቦ «ካሣ» ብሎ
ጠራኝ» ሲል ካሣ የአወላለዱና የስም መጠሪያው ግንኙነትን ያስረዳል።
አባቱ አቶ አያሌው
ለልጃቸው ይህንን ስም ያወጡበት ተጨማሪ ምክንያትም አላቸው። እርሳቸው አባታቸውን ገና ህፃን ሳሉ ሳይጠግቧቸው በሞት
በመነጠቃቸው ቋሚ መታሰቢያ ኖሯቸው ትውልድን እንዲሻገሩ ይፈልጉ ስለነበር የአባታቸውን ስም የልጃቸው መጠሪያ ለማድረግ
በቅተዋል። በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች የተነሳ ለአባቱ የመጨረሻ ለእናቱ ደግሞ ብቸኛ ሆኖ ሳይታሰብ በቤታቸው የተከሰተው
የአብራካቸው ክፋይ የሆነው ልጃቸው ካሣ አያሌው ካሣ ተብሎ ሊጠራ በቅቷል።
በዕድገትና ትምህርት፤ ከራስ መክሊት ጋር መገናኘት
ካሣ ገና የአራት
ዓመት ህፃን ልጅ ሳለ በወቅቱ የትምህርት ገበታን መቋደስ የሚጀመርበት የቄስ ትምህርት ቤት ተልኮ ፊደል መቁጠር ጀምሯል። በዚህ
ቆይታው ከፊደል ቆጠራ እስከ ዳዊት ንባብ በአግባቡ ለመማር በቅቷል። በኋላም በጊዜው «እንጦጦ አምባ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ
ደረጃ ት/ቤት» ተብሎ ይጠራ የነበረው ት/ቤት በመዝለቅ ዘመናዊ ትምህርቱን አንድ ብሎ ጀምሯል።
ካሣ በዚህ ት/ቤት
ሳለ ነበር ውስጡ ከነበረው የህይወት መክሊቱ ጋር የተገናኘው። የሦስተኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ በት/ቤታችን የሚገኘውን ሚኒ ሚዲያ
የምቀላቀልበት ዕድል ተፈጠረ። ይህ ዕድል የተገኘው በክፍሌ ውስጥ ተማሪዎች ፊት ቆሜ ጋዜጣ ሳነብ ድንገት ክፍላችን በተገኙት
የት/ቤታችን ም/ርዕሰ መምህር አማካኝነት ነው። ስማቸው መምህር ግርማ ይገዙ ይባላል። አነባበቤን አይተው ስለወደዱት እርሳቸው
ይመሩት የነበረውን የሚኒ ሚዲያ ክበብ እንድቀላቀል አደረጉ። በዚህ ክበብ ውስጥ ሆኜ በትምህርት ቤቱ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮሩ
ዜናዎችን እየዘገብኩ ዘወትር ማለዳ የኢትዮጵያ ህዝብ መዝሙር እየተዘመረ ሰንደቅ ዓላማ በሚሰቀልበት የተማሪዎች ሰልፍ ላይ ማንበብ
ጀመርኩ» በማለት ካሣ የጋዜጠኝነት ህይወት መስመሩ አንድ ብሎ የተጀመረበትን ሁኔታ ያስታውሳል።
ባልተፈጠረበት
ህይወት እራሱን ፍለጋ የባዘነበት ዓመታት
ካሣ አያሌው ካሣ
የዘጠነኛ ክፍል ትምህርቱን በ«እንጦጦ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት /ቲ ኤም ኤስ/» ከጀመረ አንስቶ ሙሉ ትኩረቱን የቀለም
ትምህርቱ ላይ አድርጎ ቆይቷል። በዚህ ቆይታው ከማህበራዊ ሳይንስ ይልቅ የተፈጥሮ ሳይንስን ምርጫው አድርጎ ትምህርቱን
ተከታትሏል። የአስራ ሁለተኛ ክፍል መልቀቂያ አገር ዓቀፍ ፈተና ሲወስድም እንደ ተለመደው ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገብ ወደ
ከፍተኛ ትምህርት የሚሸጋገርበት ዕድል አግኝቷል።
በወቅቱ የከፍተኛ
ትምህርት ምደባ የሚሰጠው በዕጣ ስለነበር ካሣ በዚህ አመዳደብ መሰረት የኢንጂነሪንግ ትምህርት እንዲማር የአዳማ ቴክኒክ ኮሌጅን
እንዲቀላቀል ምደባ ወጥቶለታል። ምደባውን ተከትሎ ወደ አዳማ በማቅናት የቴክኖሎጂ ትምህርቱን መከታተል ቢጀምርም ቅሉ ሁኔታው
ምቾት እንዳሳጣውና እንዳሎደደው ካሣ ይናገራል።
ካሣ በአዳማ
የጠበቀው ትምህርት ከውስጥ ብቃቱና ክህሎቱ በእጅጉ የተራራቀ ሆኖ በመገኘቱ ስልጠናውን ሳይወደው መቅረቱን ይናገራል። «በውስጤ
ለቴክኖሎጂ ዕውቀት ስልጠና የሚመች አንዳችም ብቃት አልነበረም። የተግባር ተኮር ስልጠና በሚካሄድበት ቤተ ሙከራ /ላቦራቶሪ./
ውስጥም ይሁን እንደ ኢንጂነሪንግ ንድፍ ሃሳብ ያሉ ትምህርቶችን በለመድኩት ስኬት ማከናወን ከባድ ሆኖብኛል። ይህም ክፉኛ
ፍርሀትና ጭንቀት በውስጤ እንዲፈጠር አድርጎ የከፍተኛ ትምህርት ክትትሌን እንድጠላው አስገድዶኛል» በማለት የገጠመውን ፈተና
ያወሳል።
ካሣ በአዳማ
የትምህርት ቆይታው የገጠመውን የስሜት ፈተና ተቋቁሞ መዝለቅ የቻለው ለዘጠኝ ወራት ብቻ ነው። የመጀመሪያ ዓመት ሁለተኛ መንፈቀ
-ዓመት ስልጠናው አጋማሽ ላይ ሲደርስ ሁሉ ነገር ከአቅሙ በላይ ሆኖ ለህመም ዳረገው። በዚህ ምክንያትም ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ
ከቴክኖሎጂ ትምህርት ስልጠና በመለያየት የአዳማ ቴክኒክ ኮሌጅ ጊቢን ለቆ ወደ እናቱ ቤት ተመለሰ።
ከተፈጥሮ ክህሎቱ
ደግሞ በመገናኘት ፤ ወደ ስኬት ያመራትበ አዲስ ትምህርት
ካሣ አያሌው ካሣ
ከአዳማ ትምህርቱ በተቆራረጠ አንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የተፈጠረ አንድ አጋጣሚ ዘንግቶት ወደቆየው የውስጥ ፍላጎቱና ክህሎቱ
የሚመለስበት ዕድል መፈጠሩን ያስታውሳል። አጋጣሚው የተፈጠረው «ሰባራ ባቡር» ተብሎ የሚጠራው ሰፈር የሚገኘው የቅዱስ ዮሐንስ
ቤተ ክርስቲያንን ተሳልሞ ወደ ጊዮርጊስ በእግሩ እያመራ ሳለ ነው። በዚህ አጋጣሚ አቡነ ጴጥሮስ አደባባይ አካባቢ ሊደርስ ጥቂት
ሲቀረው የቀድሞው የኢትዮጵያ ሬዲዮ ጊቢ የነበረው ግንብ ላይ አንድ ማስታወቂያ ተለጥፎ ያነባል።
ማስታወቂያው
«የመገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት በመጪው አዲስ ዓመት ለመጀመሪያ ጊዜ የግል አመልካቾችን ተቀብሎ በማታው ትምህርት
ዘርፍ ለማሰልጠን ይፈልጋል» የሚል ነበር። ካሣ ማስታወቂያውን አንብቦ ሲያበቃ ውስጡ በተፈጠረ ግፊት ወደ ኢንስቲቲዩቱ ጊቢ ዘው
ብሎ ይገባና የስልጠናው ማመልከቻን በሃያ ብር ገዝቶ ይወጣል። በማመልከቻ ቅፁ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች እንደሚያሟላ
በማረጋገጡም ልቡ በደስታ ተሞልቶ ጠፍቶ የቆየው የመማር ስሜቱ እንደ አዲስ ማበብ ይጀምራል፡፡
በእርግጥም ካሣ
ኢንስቲቲዩቱ ያወጣውን መስፈርት ማሟላት በመቻሉ በ1994ዓ.ም በአድቫንስ ስታንዲንግ ዲፕሎማ ደረጃ የጋዜጠኝነት ትምህርት
መከታተል የሚጀምርበት አዲስ ዕድል አግኝቷል። በዚህ «የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት» ተብሎ በሚጠራው ተቋም
የጀመረው የጋዜጠኝነት ስልጠና አቅምና ችሎታውን እንዲያረጋግጥ ያስቻለው ገና በመጀመሪያው ጊዜ ነበር። ስልጠናውን የሚሰጡት
መምህራን ሳይቀሩ እጅግ የሚደመሙበት ውጤት በማስመዝገብ ካሣ ለጋዜጠኝነት የተፈጠረ መሆኑን አረጋግጧል። ስልጠና ከሰጡት
መምህራን መካከል እንደ ዶ/ር ገ/መድህን ስምዖን፤ ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻ፤ ረዳት ፕሮፌሰር አማኑኤል አብዲሳና አቶ
ስለሺ ተሰማ ያሉ አስተማሪዎቹም ይህንን ብቃቱን ያረጋግጣሉ። ካሣ የጋዜጠኝነት ስልጠናው የሚወስደውን ሦስት ዓመታት ጊዜ አጠናቆ
በድምር ውጤቱ 3.92 በማስመዝገብ እጅግ በከፍተኛ ማዕረግ ለመመረቅ በቅቷል። በዚያው ትምህርቱን ቀጥሎ ከአ.አ.ዩ. በተመሳሳይ
የሙያ ዘርፍ ስልጠናውን አካሂዶ በተመሳሳይ በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ የባችለር ዲግሪውንም ተጎናፅፏል።
ከስልጠና ጎን ለጎን
በስራ ስምሪት፤ ተጨማሪ ስኬት
ካሣ አያሌው ተወልዶ
ባደገበት ሰፈር ከአንጋፋው ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር ጋር የቅርብ ጉርብትና ያላቸው ከመሆኑ ባሻገር የቤተሰብ ያህል የተቀራረበ
ወዳጅነት እንደነበራቸው ይናገራል። «ጎርፍነህ ብዙ አይናገርም። በዝምታ ነገሮችን ይከታተላል። ማድረግ የሚገባውንም አድርጎ
ያሳያል እንጂ አስቀድሞ አይፎክርም» ሲል የጎርፍነህ ይመር ሰብዕናን ይገልፃል።
ጎርፍነህ የወንድሙ
ያህል የሚያውቀው ካሣን የጋዜጠኝነት ትምህርት ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአንክሮ ውጤቱን ሲከታተል ቆይቷል። በትምህርቱ
እያስመዘገበ ካለው ስኬት ጎን ለጎን ተግባራዊ ዕውቀቱም እንዲዳብር በማሰብ ልምዱን ከማጋራት ቦዝኖ አያውቅም። የጎርፍነህ
አስተዋፅዖ በዚህ ብቻ የተወሰነም አይደለም። ካሣ ጋዜጠኝነትን ከቀለም ስልጠና ባሻገር በተግባር ሊማር የሚችልበትን ቦታ
ሲያፈላልግ ቆይቶ ዕድሉን በማግኘቱ ፈጥኖ ወደ ጋዜጠኝነት ስራ እንዲሰማራ ጥርጊያ መንገዱን አመቻችቶለታል።
ካሣ በጎርፍነህ
አማካኝነት ያገኘውን የስራ ዕድል ያገኘው ትምህርቱን በጀመረበት የመጀመሪያ ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር። በዚያ ወቅት «አዲስ
ብሮድ ካስቲንግ ኩባንያ /ABC/ » ተብሎ የሚጠራ አንድ ድርጅት ተመስርቶ የጋዜጣ ህትመት ለመጀመር በቅቷል። ድርጅቱ «አዲስ
ዜና» የተባለ ጋዜጣ ማሳተም ከመጀመሩ ጥቂት ወራት በፊት ሰራተኞቹን ሲያደራጅ አንድ ክፍተት ይገጥመዋል። ይህንን ክፍተቱን
የሚያሟላ የትርፍ ጊዜ ሙያተኛ በመፈለጉ የጋዜጣው ዋና አዘጋጅ የነበረው አቶ መለስካቸው አምሃ የልጅነት ጓደኛው የሆነው
ጎርፍነህ ይመርን ያማክረዋል። ጎርፍነህም ካሣን ክፍተቱን የሚያሟላ ትክክለኛ ሙያተኛ እንደሆነ አምኖ ለዚህ ስራ እጩ አድርጎ
ያቀርበዋል።
«ድርጅቱ ከዚያ
ቀደም በተለያየ ስፍራ ጋዜጠኝነት ይሰሩ የነበሩ ሙያተኞችን አሰባስቦ በኬኒያና በኖርዌይ አገራት ስልጠና እንዲወሰዱ አድርጎ
ነበር። በስልጠናው ተሳትፈው የተመለሱት ሙያተኞች ‹አዲስ ዜና› የተባለው ጋዜጣ ላይ የተለያዩ ዐምዶችን ተከፋፍለው የሙከራ ስራ
ይጀምራሉ። ያኔ ታዲያ የስፖርት ዘጋቢ በመካከላቸው ባለመገኘቱ መለስካቸው ይህንን ክፍተት የሚሞላ ጋዜጠኛ ያገኝ ዘንድ ጉዳዩን
ለጎርፍነህ ያማክረዋል። ጎርፍነህም እኔን ለዚሁ ስራ እጩ አድርጎ ወደ ድርጅቱ ይልከኝና በጋዜጣው የስፖርት ዐምድ ላይ አንድ
ብዬ የጋዜጠኝነት ሙያን ለህዝብ አገልግሎት የማውልበት ዕድል ሊፈጠር በቅቷል» በማለት አጋጣሚውን ካሣ ያስረዳል።
ጎርፍነህ ይመር
፤ ካሣ ከተመደበበት ስራ ጋር እስኪወዳጅ ድረስ ተፈላጊውን እገዛ
ሲያደርግለት እንደቆየ ካሣ ይናገራል። በተጨማሪም መለስካቸው አምሃ፤ ካሣ የሚያሰናዳቸው ፅሑፎችን ከማረም ባሻገር ስህተቱን ቁጭ
አድርጎ በማስተማርና አቅሙን በማሳደግ ረገድ ላቅ ያለ ሚና ተጫውቷል። ከዚህም አልፎ ካሣ ከስፖርት ዐምድ በተጨማሪ በማህበራዊ
ዐምድና በዜና ስራ ላይ እንዲሰማራ በማድረግ አቅሙን እንዲያጎለብት ምቹ ሁኔታን ፈጥሮለታል።
ካሣ በአዲስ ብሮድ
ካስቲንግ ኩባንያ የነበረው ጊዜ ከስልጠናው በተጓዳኝ ጋዜጠኝነትን በተግባር ዕውቀት እየቀሰመ ከፍ ያለ ልምድ እንዲያጎለብት
አስችሎታል። ምንም እንኳን ድርጅቱ በሁለተኛ ዙር መልምሎ በውጪ አገር አሰልጥኖ ለስራ ባበቃቸው መደበኛ ሰራተኞቹ መካከል
የስፖርት ዘጋቢ ማግኘት ቢችልም፤ ካሣን ግን ሊያሰናብተው አልወደደም። ይልቁንም የስፖርት ዐምዱን በቋሚነት የምትይዝ ሰራተኛ
መገኘቷን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመቁጠር ካሣ በተለይም በጠንካራ ጉዳዮች ላይ ዘገባ በመስራት የጋዜጠኝነት አቅምና ችሎታውን
ይበልጥ እንዲያጠናክር ተጨማሪ ዕድል ሊፈጥርለት በቅቷል።
«በ‹አዲስ ዜና›
ጋዜጣ ላይ የስፖርት ዘጋቢ ሆኜ ስራዬን ብጀምርም ከዚያ ይልቅ ነፍሴ ይበልጥ ለጠንካራ የጋዜጠኝነት ዘገባ የተሰጠች እንደነበር
ሁሉም ይረዳሉ። ለዚህም ነው ለዜናና ለማህበራዊ ዐምድ የሚሆኑ ዘገባዎችን እንድሰራ ዕድሉን ያመቻቹልኝ። ከድርጅቱ ጋር
ትምህርቴን እስካጠናቅቅ ድረስ በቆየሁባቸው ሁለት ዓመታት ከፍ ያለ የጋዚጠኝነት ልምድ ለመቅሰም በመቻሌ ቀጣዩ የስራ ዘመኔን
አቅልሎልኛል። ይህም ብቻ ሳይሆን በትርፍ ሰዓት ሰራተኛ አከፋፈል ስኬሉ መሰረት ይከፍለኝ የነበረው ገንዘብም የስልጠና ህይወቴን
ያለ ችግር እንድገፋ አስችሎኛል» ሲል ካሣ ይናገራል።
ካሣ በአዲስ ብሮድ
ካስቲንግ ኩባንያ ከድርጅቱ ባልደረቦች ጋር የነበረው ግንኙነት ምን ያህል በፍቅር፤ መግባባትና መተጋገዝ የደረጀ እንደ ነበር
አይዘነጋውም። ከድርጅቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ክፍሉ ታደሰ አንስቶ ዋናና ምክትል አዘጋጆቹ መለስካቸው አምሃና ፋሲል የኔ
አለም፤ አዳነች አበራ፤ ጥበቡ በለጠ፤ ራሄል ዘውዱን የመሳሰሉ ሙያተኞች ጋር የነበረው ቅርርብና በዚህ ቅርርቡ ሙያተኞቹ ለስራ
ስኬቱ ማማር የተጫወቱት ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ይመሰክራል።
ነቃሹ ጋዜጠኛ ካሣ
አያሌው ካሣ
ካሣ የአሁኑ «ፋና
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትን» የተቀላቀለው በነሐሴ ወር 1996ዓ.ም ነው። ሬዲዮ ፋና ከነበረው አገር ዓቀፍ ስርጭት በተጨማሪ
በመካከለኛ ሞገድ 1080 ለአዲስ አበባና ዙሪያዋ ላሉ የሚደርስ አዲስ ስርጭት ሲጀምር ይህንን የስርጭት ዘርፍ ተቀላቅሎ ስራውን
ጀምሯል። በፋና ሬዲዮ መካከለኛ ሞገድ በተጀመረው ስርጭት ውስጥ «አራዳ ነቃሽ» የተባለ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢ ለመሆን
በቅቷል።
«አራዳ ነቃሽ»
በምርመራ ጋዜጠኝነት መርሆ የሚመራ በሙስና፤ መልካም አስተዳደርና ብሉሽ አሰራር ላይ ትኩረቱን አድርጎ የሚሰናዳ ዝግጅት ነው።
መሰናዶው በየሳምንቱ ረቡዕ የሚተላለፍ ሲሆን በእያንዳንዱ ዝግጅት በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሙሉ መረጃን በማሟላት ተሰናድቶ
የሚያቅርብ ነው። በዚህ ምክንያት ስራው እጅግ አድካሚ ቢሆንም ካሣ በየሳምንቱ የተሟላ ዝግጅትን ለብቻው አሰናድቶ ማቅረብ ግን
አልተሳነውም።
«አንድን ርዕሰ
ጉዳይ ማስረጃ አጠናክረህና የሚመለከታቸው ባለድርሻዎችን ሁሉ በጉዳዩ ላይ አነጋግረህ እውነትን ገሀድ ለማውጣት ጠንካራ ትግል
ይጠይቃል። የምትሰራው ስራ ሌቦችና በዳዮችን የሚያጋልጥ፤ የተገፉና የተበደሉን እሮሮ ለህዝብ ጆሮ የሚያደርስ በመሆኑ ለአደጋ
የሚያጋልጥ መሆኑ መዘንጋት የለበትም። በዚያ ላይ መረጃ ፍለጋ ስትንከራተት በር ከሚክፍትልህ ይልቅ ዘግቶ የሚሰወርብህ ይበዛል።
ይህንን ሁሉ ተጋፍጠህ በየሳምንቱ አንድ የተሟላ ማስረጃ ይዞ የተቀናበረ ዝግጅት ለአየር ማቅረብ ምን ያህል አድካሚና ፈታኝ እንደሆነ
ማሰብ አያስቸግርም» ሲል ካሣ ያሰናዳው የነበረው ዝግጅት አድካሚነትን ይገልፃል።
«አራዳ ነቃሽ»
ለህዝብ በእጅጉ የቀረበ የተበዳዮች ልሳን መሆን የቻለ ዝግጅት በመሆኑ በአጭር ጊዜ ተደማጭነትና ተወዳጅነት ለማግኘት
አልተቸገረም። በዚህ መሰናዶ ከእህል በረንዳ እስከ አዲስ አበባ ትራንስፖርት፤ ከግል የትምህርት ሴክተር እስከ ቀበሊና ክፍለ
-ከተማ አገልግሎት አሰጣጥ ያልተነቀሰና ችግሩ ፈርጦ አደባባይ ያሎጣ ጉዳይ አይገኝም። ይህም ለአዘጋጁ ብቻ ሳይሆን ለጣቢያውም
ጭምር ከፍ ያለ ተዓማኒነት እንዲያገኝ ተጨማሪ አቅም ሆኖታል።
ካሣ ፈታኙን
የ«አራዳ ነቃሽ» ዝግጅት ከማሰናዳት ጎን ለጎን የዚሁ የመካከለኛ ሞገድ ስርጭት ዜናን የመምራት ኃላፊነት ለመውሰድ የበቃው
በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ነው። ይህም የሬዲዮ አዘጋጅ ከመሆን ባሻገር የሚዲያ አመራር አቅሙን እንዲያዳብር ዕድል ፈጥሮለታል።
ሬዲዮ ፋና የመካከለኛ
ሞገድ ስርጭቱን እንደ ተሞክሮ በመውሰድ የኤፍ ኤም ስርጭት ለመጀመር መሰናዶ ሲጀምርም ካሣ ከጣቢያው መስራቾች አንዱ ለመሆን
በቅቷል። ፋና ኤፍ ኤም 98.1 የፎርማትና የዝግጅት ቅርፆችን በሚያወጣበት ጊዜ ከአመራሮቹ ጋር በመሆን የመመስረቱ ተግባር ላይ
ተሰማርቷል። ይህንኑ ተከትሎ ጣቢያው ተመስርቶ ለስርጭት ሲበቃም የአዲስ አበባ ፋና ኤፍ ኤም 98.1 ኃላፊ በመሆን ተጨማሪ
የአመራርነት ድርሻን ለማግኘት ችሏል።
ፋና ኤፍ ኤም
98.1 ሲመሰረት የተሰጠውን ኃላፊነት በአንድ በኩል እየተወጣ፤ በሌላ ጎኑ ደግሞ ቀድሞ ይሰራ የነበረው የ«አራዳ ነቃሽ»
ዝግጅት የይዘትና የፎርማት ለውጥ አድርጎ «ተጓዥ ነቃሽ» በተባለ ስያሜ ስርጭት በመጀመሩ የዚህ ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢነት
ሚናውን ተረክቦ በምርመራ ጋዜጠኝነት ዘርፍ የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ቀጥሏል። «ተጓዥ ነቃሽ» ከቀድሞው ዝግጅት የሚለየው
አድማጮች በቀጥታ ስልክ መስመር የሚሳተፉበት ዕድል በማመቻቸቱ ነው። ይህም ዝግጅቱ ከፍ ያለ ጥንቃቄ በተሞላበት አኳኋን
እንዲከናወን በማድረግ ለአዘጋጁ ተጨማሪ ኃላፊነትን እንዲወጣ ያስገድደዋል። ካሳ ይህንን ዝግጅትም በብቃት በመወጣት አድማጮች
ለዝግጅቱ፤ አዘጋጁና ጣቢያው ያላቸው ፍቅር ከፍ እንዲል አስችሏል።
ካሣ «በፋና ብሮድ
ካስቲንግ ኮርፖሬት በድምሩ 8 ዓመታትን አገልግያለሁ። በዚህ የስራ ዘመኔ እጅግ ፈታኝ በሆነው የምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ
ተሰማርቼ በመቆየቴ ለህይወትና ለእውነት የቀረበ የዳጎሰ ልምድ ለማካበት አስችሎኛል። በዚህ የፋና ቆይታዬ አብዛኛው ጊዜዬን
ያሳለፍኩት በተለያየ የአመራርነት ደረጃ ላይ መሆኑ ደግሞ ለሚዲያ ስራ ማስተባበርና መምራት የሚያስችል ብቃት እንዳዳብር
አስችሎኛል። በአጭር ቃል ፋና እንደ አዲስ አፍርሶ የገነባኝ ተቋም ነው» በማለት በድርጅቱ የነበረው ጊዜን ያስረዳል።
በ«ተጓዥ ነቃሽ»
መሰናዶ ከአዲስ አበባና የፊንፊኔ ዙሪያ ከተሞች የመሬት አስተዳደር ችግርና ሙሰኝነት አንስቶ እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፤
ከተለያዩ የአገልግሎት ተቋማት አንስቶ እስከ መሰረተ ልማት አቅራቢ ድርጅቶች፤ ያልተፈተሹ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሳንካዎች
የሉም። አብዛኞቹ ዝግጅቶችም ለመንግስት ስራ ማሻሻያ የሚውል በቂ ማስረጃ በመስጠት የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ ነው።
ከነቃሽ ጋዜጠኝነት
ወደ ጣቢያ መስራችነት
ካሣ በጋዜጠኝነት
ያካበተው ልምድና አቅምን ወደ ላቀ ደረጃ መሸጋገሩን ያረጋገጠበት ስራ የሰራው በአሐዱ ሬዲዮ 94.3 ጣቢያ ምስረታ ወቅት መሆኑ
ይነገራል። ጣቢያው ወደ ምስረታ ሲገባ ከተቀላቀሉት ቀደምት ሙያተኞች አንዱ ነበር። በዋና አዘጋጅነት የስራ መደብ የተቀጠረ
ሲሆን፤ ከተመደበበት ስራ ባሻገር የጣቢያውን ቅርፅና ይዘት በመወሰኑ ተግባር ላይ ግንባር ቀደሙን ሚና እንደተጫወተ በወቅቱ
አብረውት የሰሩ ባልደረቦቹ ይመሰክራሉ።
አሐዱ ሬዲዮ 94.3
የራሱ የሆነ የተለየ ቀለምና ቅርፅ ይዞ በዘርፉ ተወዳዳሪ ጣቢያ ሆኖ እንዲመሰረት ካሣ ከፍ ያለ ሚና ተጫውቷል። አሁን በጣቢያው
ላይ የሚሰሙ አብዛኛዎቹ ዝግጅቶችን ከስያሜ አንስቶ ቅርፅና ይዘታቸውን ጭምር በሙያ ፈጠራ ታግዞ ዕውን አድርጓቸዋል። የዚህ
ጣቢያ ልዩ ለዛ የሆነው አድማጮቹን የሚጠራበት «ቤተሰቦች» የሚለው ቃልም የእርሱ ፈጠራ ውጤት መሆኑ ይነገራል።
ካሣ በአሐዱ
የነበረውን አስተዋፅዖና ቆይታ በተመለከተ ሲናገር «ጣቢያው ምስረታውን ሲጀምር ተቀላቀልኩት። ከዚያም በአዲስ አበባ ከተማ ያሉ
ተደማጭ የኤፍ ኤም ጣቢያዎችን እንደ መነሻ በመውሰድ ጥንካሬና ድክመታቸውን በአጭር የጥናት ዳሰሳ ለመመልከት ሞከርኩ። ይህንን
ታሳቢ በማድረግ አሐዱ እንዴት ያለ የተለየ ቀለምና ለዛ ይዞ ሊወጣ እንደሚችል ጊዜ ወስጄ ማጥናት ጀመርኩ። የጥናት ውጤቱን
ከጣቢያው ባለቤትና ከመስራች ባልደረቦቼ ጋር በጋር ምክክር አዳብረን አሐዱ አሁን ያለውን ለዛና ቅርፅ ይዞ እንዲወጣ ለማስቻል
በቃን። ይህ ስራ እንዲሳካ ከፍ ያለ አስተዋፅዖ ያበረከቱት የጣቢያው ባለቤትና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ እሸቱ በላይ ናቸው።
ሙያዊ አቅማችንን እንድንወጣ ያልተገደበ ነፃነት ከመስጠት አንስቶ የሚያስፈልገንን ሁሉ በፍጥነት በማሟላትና እጅግ ገንቢ ሃሳብ
በመስጠት ያሰብነውን በአጭር ጊዜ እንድናሳካ ደግፈውናል።» ይላል።
ከአሐዱ ሬዲዮ
በኋላም ካሣ አፍሪ ሄልዝ ቴሌቪዥንን በዋና ዳይሬክተርነት በመምራት በስምንት ወራት ቆይታው አዳዲስ የፕሮግራም ፎርማትና
ይዘቶችን በመቅረፅ ጣቢያው በተለየ መንገድ ተሻሽሎ ወደ ስርጭት እንዲገባ አስችሏል።
ሥነ ፅሑፍና ካሣ
ካሣ አያሌው ካሣ
በቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማ ፅሑፍ ዝግጅት በ«ዳና ድራማ» ላይ በአማካሪነትና በደራሲነት ተሳትፏል። በተጨማሪም «ተልዕኮ
ምፅዓት፤ አቫንቲ/ወደ ጥቁሩ ገዳምና ወያኔው» የተባሉ ሦስት መፅሐፎችን አሳትሞ ለንባብ አብቅቷል። «ተልዕኮ ምፅዓት» በአባይ
ወንዝ ጉዳይ ላይ አትኩሮ የተፃፈ ረጅም ልቦለድ ነው። «አቫንቲ/ወደ ጥቁሩ ገዳም» የተሰኘው ስራው ደግሞ በአሜሪካናዊው ታዋቂ
ደራሲ የተፃፈውን <<The Quest>> የተሰኘ በኢትዮጵያ ጥንተ ጥንት ታሪክ ላይ ያተኮረ መፅሐፍ በአዛማጅ
ትርጉም ስልት ተርጉሞ ለንባብ ያበቃበት ሲሆን፤ «ወያኔው» በተባለ መፅሐፉ የህወሓት የ60ዎቹ ትግልን በትግሉ መስራች አባይ
ፀሐየ ታሪክ ላይ ተመስርቶ የገመገመበትና የአሁኑን ትውልድ ከ60ዎቹ ፖለቲካ አንፃር የቃኘበት ዳጎስ ያለ መፅሐፍ ነው።
ካሣ በቅርቡ
«ጉራንጉር» የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልምን ለዕይታ ለማብቃት ከፕሮዲውሰሮች ጋር ውል ፈፅሟል። በራሱ ታሪክ ላይ ያተኮረ
«ጠፍ ጨረቃ» የሚሰኝ ወጥ ረጅም ልቦለድ መፅሐፍም ለማሳተም ዝግጅት ላይ ይገኛል።
ቤተሰባዊ ህይወት
ካሣ
በ2005ዓ.ም ላይ ከፍቅረኛው ሊና ኑር አሕመድ ጋር በጋብቻ የተሳሰረ ሲሆን ቀዳማዊትና ለዕልና የተባሉ
ሁለት ሴት ልጆችን ወልዷል። በትዳር ህይወቱ እጅግ የተሳካለት እንደሆነ በቅርበት የሚያውቁት ጓደኞቹ ይመሰክራሉ። ከስራ ውጪ
ያለ ሰዓቱን ሁሉ ከቤተሰቦቹ ጋር ማሳለፍ እንደሚያስደስተው ሁሉም ይመሰክሩለታል።
ካሣ ራሱም ዋነኛ
ይህይወት ፍልስፍናውን ሲገልፅ «በህይወትህ የተረጋጋ፤ ፍፁም ሰላማዊና እውነተኛ ፍቅርን የተላበሰ ቤተሰብ ከመመስረት የሚበልጥ
ስኬት ከየትም አይገኝም። ቤተሰብ የትውልድ መቀጠያና የአገር መመስረቻ እርካብ ስለሆነ» ይላል።
መዝጊያ : ካሳ
አያሌው ካሳ በተጓዥ ነቃሽ ፕሮግራሙ ስም ያተረፈ ጋዜጠኛ ነው፡፡ ለሙያው የተፈጠረ ነው፡፡ ሙያውን ያከብራል-ይወዳልም፡፡ 18
አመት በቆየበት ሙያ ላይ ዛሬም በጽኑ እምነት ያገለግላል፡፡ በሰራባቸው ሚድያዎች የራሱን አሻራ ለማኖር ሲል ሌት ተቀን
ለፍቷል፡፡ ከባድ በሚባለውና ፈታኝነትን በተላበሰው የምርመራ
ጋዜጠኝነት ዘርፍ ላይ ካሳ የበኩሉን ድርሻ ተወጥቷል፡፡ የቅርብ አለቆቹና ባልደረቦቹ ብቃቱን በሙሉ አንደበታቸው እስኪመሰክሩ
ድረስ ካሳ የጋዜጠኝነት አቅሙን አጎልብቶ ያሳየ ነው፡፡ ለምርመራ
ጋዜጠኝነት የሚያስፈልገውን በራስ መተማመን ከድፍረት ጋር አዳብሎ የተላበሰው ካሳ በስራው ላይ ብቻ በማተኮሩ ይታወቃል፡፡
ያነባል፡፡ ይጽፋል፡፡ ትርጉም ይሰራል፡፡ እንደመሪ ሆኖ ደግሞ ፎርማት ይቀርጻል፡፡ የተቀረጸው ፎርማት ተግባራዊ መሆኑን
ይከታተላል፡፡ በዚህ አይነቱ የጋዜጠኝነት ይትባህል ነው ያለፈው፡፡
በሄደባቸውም ቦታዎች መልካም ስም ለማትረፍ የቻለ ሰው
ነው፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ፤ ካሳ በኢትዮጵያ ባለፉት 20 አመታት ጋዜጠኝነት ላይ ተሰማርተው አንዳች ለውጥ ለማምጣት ከቻሉት አንዱ ነው፡፡
ሁልጊዜም ታሪክን የመናገር ባህላችን ደከም ስለሚል እንጂ ካሳን ጨምሮ ለሙያው ማደግ ላይ ታች ሲሉ የኖሩ ግን ያልተነገረላቸው
ብቁዎች ብዙ አሉ፡፡ የኢትዮጵያ የሚድያ ታሪክ ሲነሳ ካሳ ይነሳል፡፡ አንድ ስራ ከተወደደ እና ለውጥ ካመጣ ስራው መቼም በግኡዝ
አካል ሊሰራ አይችልም፡፡ የጉዳይ ፈጣሪ ሰው እንጂ ጉዳይ በራሱ አልመጣም፡፡ አይመጣም፡፡ ስለሆነም ካሳ ለአዲሱ ትውልድ የሚያስተምረው
5 ነገሮችን ነው 1ኛ መክሊትን ፈልጎ ማግኘት 2ኛ የበለጠ በሚችሉት ስራ ላይ መሰማራት 3ኛ በመደበኛ ትምህርት ጎብዞ መገኘት
4 ሁለ-ገብ ሆኖ በሚድያ እና በስነ-ጽሁፍ ብሎም በፊልም መሰማራት
5ኛ መሪነት መላበስ ብዙ መጥቀስ ቢቻልም ካሳ ከዚህ
በላይ ይሰራል እንጂ በዚህ አይገደብም፡፡ ፋና ኤፍኤም 98.1 ሲመሰረት ዋና ኤዲተር የነበረው ካሳ ቆየት ብሎ ዋና አዘጋጅ
በመሆን አቅሙን ያሳየ ነው፡፡ ከተጓዥ ነቃሽ በተጨማሪ ዳሰሳን ሲሰራ የነበረው ካሳ የማስተማር አቅምም የማማከር ክህሎትንም
የታደለ ነው፡፡ አትሮንስ የተሰኘውንም በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ ያተኮረ መሰናዶ አየር ላይ ሲያውል ነበር፡፡ ካሳ ፤ በአሁኑ
ሰአት የአሀዱ ሬድዮ የዋና ስራ አስፈጻሚው አማካሪ በመሆን እያገለገለ ሲሆን
መልካም የስራ እድል እንዲገጥመው እንመኛለን/ ይህ ጽሁፍ ከካሳ አያሌው ካሳ በተገኘ መረጃ ላይ ተመስርቶ የተጻፈ
ሲሆን ካሳ ዊኪፒዲያ ላይ እንዲወጣ በመጠቆምና ይህን የማሳረጊያ ጽሁፍ ከእነ መጠነኛ አርትኦቱ የሰራው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ
ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ አርብ ሀምሌ 23 2013 ዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ