45. ዝናሽ ማሞ አብዲ-Zinash Mamo Abdie

                                     

ዝናሽ ማሞ ፣ በኢትዮጵያ ሬድዮ በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ከ1979 ጀምሮ በመስራት ትታወቃለች፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ ለ 16 አመት ያገለገለችው ዝናሽ ከእነ ታደሰ ሙሉነህ ፤ ታምራት አሰፋ ጋር በትጋት የሰራች ሲሆን ከ20 አመት በፊት ከእነ ቤተሰቦችዋ ወደ ምድረ አሜሪካ አቅንታለች፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የጥበብ ፤ የመረጃ እና የመዝናኛ ሰዎችን ታሪክ እያሰባሰበ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ዝናሽ ማሞ አብዲም በወርቃማው የጋዜጠኝነት ዘመን ያለፈች በመሆኑ ታሪኳን እነሆ ፡፡

            ልደት

እምብዛም ልደት መከበር ባልተለመደበት በዚያን ዘመን ከተወለደች ከአንድ አመቷ ጀምሮ እስከ 16 አመቷ ድረስ ቤተሰቦቿ የልደት በዐልዋን እያከበሩላት ያደገችው ዝናሽ ማሞ አብዲበአዲስ አበባ ከተማ ግንቦት 21 ቀን 1954 አ.ም መወለድዋን ለማስታወስ አልተቸገረችም:

ትውልዷም እድገቷም ጠብመንጃ ያዥ ወይም በቅሎ ቤትበሚባለው አካባቢ ነበር::እናትና   አባቷ  ወ/ሮ ሽብሬ ወ/ሃናና አቶ ማሞ አብዲ  ይባላሉ:

አቶ ማሞ ከመጀመርያ ትዳራቸው ልጅ የነበራቸው ቢሆንም ከወ/ሮ ሽብሬ ጋር ግን የጋራ ልጅ የሆነችላቸው ይህች ህፃን ነበረች:: ከማህፀን እንደወጣች እንኳን ተወለድሽ በሚል ልዩ ፍቅር ተቀብለው በስስት ያሳደጓት ብቸኛና ብርቅዬ ልጃቸው ሆነች:: ሆኖም ግን ወሬ አይደበቅ ሆነና እነዚህ ቤተሰቦቿ ወላጆቿ አለመሆናቸውን በሹክሹክታ ወሬው ተናፍሶ ተናፍሶ ከረፈደ ወደ ጆሮዋ ገባ ::

አክስቴ ብላ ስትጠራት የኖረችው የእናቷ እህት ወ/ሮ በሻዱ ቦኩ ወላጅ እናቷ መሆኗን መስማት  ጀመረች:: አስተዳደግዋ እንደ እህት ልጅ ሳይሆን እንደ ልጅ ስለነበር በወቅቱ ዱብ እዳ እንደሚባለው አይነት አስደንጋጭ  ስሜት ነበር: የፈጠረባት:: ደግነቱ አድጋ  ተምራ ትዳር ይዛ  ባለችበት እድሜ በመሆኑ አመዛዝና ተገቢ የመሰላትን ውሳኔ ለመወሰን አልተቸገረችም:: ካሳደጓት ቤተሰቦቿም ሆነ ወላጅዋ ከሆነችው ከአክስቷ በኩል ይህንን ለእርሷ ለመንገር  የደፈረም አልነበረም::በአጠቃላይ ምንም ፍንጭ አይታይም ነበር::

ስለዚህ ጥያቄውን በማንሳት ከህፃንነት አንስተው አሳድገው ለወግ ማዕረግ ያበቋትን የቤተሰቦቿን ደስታና ተስፋ ማጨለም ስሜታቸውንም መጉዳት አይገባም በሚለው ውሳኔዋላይ ፀናች:::ስለዚህ ሁሉንም በነበረበት መንገድ ማስቀጠሉ ለእርሷ አማራጭ የሌለውመፍትሄ ሆነ:: ምንም እንዳልሰማች ና እንዳላወቀች በመሆን ከቤተሰቦቿ ጋር እንደቀድሞው በታማኝነት ምንም የልጅነት ፍቅሯንና ሃላፊነቷን ሳታጎድል እርሷም የቤተሰቦቿን ፍቅር ሳታጣ ቀጠለች:

በመጨረሻም አምስት የልጅ ልጆችን አይተውና አሳድገው ሁለቱን ለወግ ማእረግ አብቅተው የህይወት ዘመናቸውን ደስ ተሰኝተው ዘላለማዊ ፍቅራቸውን በዚህችው በምትወዳቸው ልጃቸውና በልጅ ልጆቻቸው ልቦና ውስጥ ተክለው አክስቴ ስላት የኖርኩት እናቴም ጭምር ሁሉም ወደ ማይቀሩበት ወደ ዘላለም ማረፊያቸው ተሸኝተዋል::በመጨረሻም የአንድ ልጅነት ዘመኔ አብቅቶ የአክስቴ ልጆች በማለት የማውቃቸውን ሁለት ወንድሞችና ሦስት እህቶች አግኝቻለሁ:;

ሁሉንም ቤተሰቦቼን ነፍሳቸውን ይማር ምንጊዜም እወዳቸዋለሁ ብላለች

ህፃንነት

በተለይ በህፃንነት እድሜዋ በጣም ታምማ መላ ቤተሰቡ ተስፋ ቆርጦ ዛሬ ነገ ትሞታለች ተብሎ የሞቷን ቀን የሚጠባበቁበት አንድ ወቅት ነበር:: አባቷ አቶ ማሞ አብዲ ግን‹‹…. ልጄ አትሞትም ሆስፒታልም አላስተኛም፡፡ መድሀኒቱን ብቻ እዘዙልኝ በቤቴ አስታምማታለሁ›› በማለት ቤት ውስጥ ራሳቸው እያበሰሉና እየመገቡ መድሃኒት በአግባቡ እየሰጡ ለማስታመም በቆራጥነት ከፍተኛ ሀላፊነትን ወሰዱ:: የቅርብ ወዳጅ የነበሩት ሀኪም ለገስ ቸርነትን ቤት ድረስ እየመጡ በየቀኑ የታዘዘውን መርፌ እንዲወጉላቸው ጠየቁ::ሀኪም ለገሰ ቸርነትም በነበራቸው ቅን ልቦና ሙሉ ትብብር አደረጉ::የአምላክ በጎ ፈቃድም ሆኖ ድካምና ጥረታቸው ተሳክቶ ይህች ህፃን ወደ ሙሉ ጤንነቷ ተመለሰችላቸው:: ትናንት አበቃላት ሞተች የተባለችው የዚህ ባለታሪክ ለአቶ ለገሰ ቸርነት ነፍስ ይማር በማለት ከፍተኛ አክብሮት እንዳላት ገልፃለች፤፤

እድገት

የአለምን ወሬ በተመለከተም አባቷ እንደጀርመንና የአሜሪካንን ሬድዬ በመከታተል ትኩስ ዜና አያመልጣቸውም ነበር፤፤ ዛሬ በአለም ዙርያ ምን ወሬ አለ እስኪ ሄደን ከአቶ ማሞ ጋር እንጫወት ብለው ወደ ቤታችው ለሚመጡት ለጎረቤቶቻቸውና ለጓደኞቻቸው የዜና ምንጭ እንደነበሩም ገልፃለች:: አባቷ ሳይማሩ የትምህርት ጥቅም የገባቸው ከተማሩት የበለጠ ብሩህ አእምሮ የነበራቸው ስለነበሩ ጓደኞቻቸው ‹‹….አንተ እኮ ትንሽ ብትማር ኖሮ ማንም አይችልህም ነበር›› እያሉ የሚያደንቋቸው ሰው ነበሩ  :: <<…. እኔንም በርትቼ እንድማር ሴትነቴ እንዳይገድበኝ ማንኛውንም ስራ ከአባቴ ጎን በመሆን እንድሞክርና እንድሰራ በማደፋፈር በእችላለሁና በራስ በመተማመን መንፈስ አሳድገውኛል ::>> ስትል ዝናሽ ትናገራለች፡፡ ‹‹……..እናትና አባቴ ጠንካራና ታታሪ ሰራተኞች ስንፍናን የሚጠየፉ ስለነበሩ ድፍረትን ጉብዝናን ጥንካሬና ታታሪነትን አውርሰውኛል::ስራን ለነገ ማሳደር ወይም በኋላ ማለት የእኔ አይደለም አንድን ነገር ካሰብኩ መፈፀም ከጀመርኩም መጨረስ ግዴታዬ ነው :: በስራ መሸነፍ ሰላም ስለማይሰጠኝ ስራን ለመፈፀም እልከኛ ነኝ ::በግልፅነት እውነትን በመናገርና ስህተትን በመቀበል በጣም አምናለሁ::>> ትላለች ዝናሽ ፡፡ ውሸትን በጣም ትፀየፋለች፡፡ እውነቱን ተናግሮ የመሸበት ማደር በጣም የሚስማማት አባባል ነው፡፡

የትምህርት አለም

 ዝናሽ ማሞ ፣መጀመሪያ በቄስ ትምህርት ቤት ከፊደል እስከ መልእክተ -ዮሀንስ ተምራ  ፊደላትን ከለየች በኋላ በበቅሎ ቤት አካባቢ በነበረው አስቀድሞ ኤስ አይ ኤም የልጃገረዶች ክርስቲያን አካዳሚ ተብሎ ይታወቅ በነበረው ጂሲኤ የልጃገረዶች ት/ቤት ከ አንደኛ እስከ ስድስተኛ ቀጥሎም ይኸው ት/ቤት የፀጋ ክርስቲያን አካዳሚ በመባል ስሙ ተቀይሮ ወንዶችም አብረው መማር በጀመሩበት ት/ቤት ከሰባተኛ እስከ አስረኛበመጨረሻም በጊዜው የነበረው የኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት ት/ቤቱን ወደ መንግስት ንብረትነት በማዘዋወር የአብዬት ቅርስ ተብሎ ከሰየመው በኋላ አስራ አንደኛና አስራ ሁለተኛ ክፍልን እዚያው ተምራለች:: በመልካም መንፈሳዊ ስነ-ምግባር እግዚአብሔርን በመፍራት ታላላቆችን በማክበር አገርን በመውደድ በቀለሙም በኩል ጥሩ ውጤት በማምጣት ጎበዝ ከሚባሉት ተማሪዎች ተርታ በመመደብ በመምህሮቿ እንደተመሰገነች አስራ ሁለቱንም አመት በአንድ ትምህርት ቤት አጠናቃለች::በክረምት ወቅት ጊዜዋን በጨዋታ ብቻ እንዳታሳልፍ ለሚቀጥለው የትምህርት አመትም እንዲረዳት ተብሎ ቅዱስ ያሬድና የእውቀት ምንጭ የሚባሉ የህዝብ ትምህርት ቤቶችም ተምራ ነበር::በልጅነቷ በነበራት ግጥም የመግጠም ችሎታ በክፍል ውስጥ ግጥሟ ተመርጦ የምታነብበት ጊዜ እንደነበርም አልዘነጋችውም :: በተማረችበት መንፈሳዊ ት/ቤትም በገና በአል ጊዜ የጌታችን የእየሱስ ክርስቶስን የልደት በአልን አስመልክቶ በሚዘጋጁ የመድረክ ትያትሮችም ላይ ትሳተፍ ነበር::በት/ቤቱ ቻፕል ውስጥ ባለው የመዘምራን ኩዋየር ውስጥም አባል በመሆን ትዘምር ነበር:: ማታ ማታም ለቤተሰቦቿ መፅሀፍ ቅዱስ አንብቢልን እየተባለች ፊት ለፊታቸው ቆማ ታነብ ነበር:: ይህ ሁሉ በራስ የመተማመን አቅምን እንደፈጠረላት ትገምታለች::












ዩኒቨርሲቲ '

ወደ ከፍተኛ የትምህርት እርከን ስናመራ ደግሞ አራት ኪሎ በሚገኘው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይንስ ፋክልቲ ትምህርቷን የቀጠለችው የልጅነት ጓደኛዋ የነበረውን የአሁኑን ባለቤቷን አግብታ የአንድ ልጅ እናት ከሆነች በኋላ ነበር: ::በትዳር ምክንያት ትምህርቷ ተቋረጠ ብለው ቤተሰቦቿ እንዳያዝኑ ህፃኗን ለቤተሰቦቿና ለባለቤቷ ትታ ዶርም ገባች:: በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በሂሳብ (maths)ሜጀርና በፊዚክስ (physics) ማይነር ለሁለት አመት ተኩል ያህል ከተማረች በኋላ የመጀመሪያ ምርጫዋ ምህንድስና ሁለተኛው መድሀኒት ቅመማ ወይም ፋርማሲ የነበረ በመሆኑና ያም ባለመሳካቱ ሁለተኛ ልጇንም በዚያን ወቅት ስለወለደች ልቦናዋ ወደ ስራ ፍለጋ ዞረ :: በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ በአንድ ዶርምና በአንድ ዲፓርትመንት አብራት ትማር የነበረችው ጓደኛዋ የሺ ተካ ነበረች አይኖቿን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር እንድታደርግ ያበረታታቻት ::በወቅቱ የሺ ተካ የኢትዬጵያ ቴሌቪዥን የህብረ- ትርኢት አዘጋጅ ሆና ትሰራ ነበር:: ወዲያውኑ የኢትዮጵያ ሬድዮም የስራ ማስታወቂያ አወጣ፡፡፡እርስዋም ማስታወቂያውን አይታ በመወዳደር የፅሁፍና የድምፅ ፈተና ውን አልፋ የመጀመሪያ ስራዋ የሆነውን የሬድዬ ጋዜጠኝነቱ አለም በ22 አመት እድሜዋ ተቀላቀለች::

የጋዜጠኝነቱ  ጅማሬ

1976 ሰኔ ወር ላይ ነበር በፕሮግራም አስፈፃሚና አቀነባባሪነት በአቡነ ጴጥሮስ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ግቢ ውስጥ ስራውን የጀመረችው::ብዙ ታዋቂዎችንና የአገር ባለውለታዎችን ላፈራው የአቡነ ጴጥሮስ ቢሮና ስቱድዮ ትልቅ ክብርና ልዩ ትዝታ አላት፡፡

በወቅቱ አቶ ሀይሉ ወ/ፃድቅ (ጋሽ ሀይሉ)የፕሮግራም ክፍል ሀላፊ ነፍሳቸውን ይማርውና አቶ ታደሰ ሙሉነህ (ጋሽ ታዴ) የሬድዬ ጣብያው ምክትል የመምሪያ ሀላፊ እንዲሁም አቶ ሞገስ ታፈሰ የመምሪያ ሀላፊ ነበሩ ::

ዝናሽ  ስለ ቀድሞ መስሪያ ቤቷ ትዝታ ስታወራ ‹‹… የመጀመርያ ቢሯችን እንደሰማሁት ከሆነ የንጉሴ አክሊሉ  ቢሮ ነበረች:: በዚያች ቢሮ ውስጥ አብረን የገባነው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የማስ ሚድያ  ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት ረዳት ፕሮፌሰር ከሆነው አማኑኤል አብዲሳና ሙሉጌታ ዘውዴ ጋር ነበር :: በኋላ ደግሞ ብሩክት መላኩ ና ሰገዱ ጉዋዴ ተተክተው አብረን ሰርተናል:

ከጎናችን በነበረው ቢሮ ደግሞ አቶ ማሞ ውድነህ ነበሩ::>> ትላለች፡፡

ዝናሽ ሀሳቧን ስትቀጥል ….. ‹‹…….ስራ ከመጀመራችን በፊት ነፍሳቸውን ይማረውና ወ/ሮ አለምሰገድ ህሩይ  ከወ/ሮ አሰለፈች ይበርታና  ከቴክኒክ ባለሙያ ከነበረው ከካህሳይ ጋር  በመሆን መሰረታዊ የጋዜጠኝነት መርህን የፕሮግራም  አሰራርና  አቀራረፅን አነባበብና ኤዲት ማድረግን  አስተምረውናል:: ከዚያም የማን ድምፅ ለምን አይነት ፕሮግራም እንደሚመጥን ለመለየት  በስልጠናው ወቅት የተደረጉ የድምፅ ቀረፃዎችን መሰረት በማድረግ ለዜና  ለፕሮግራም ለትረካ እያሉ የሁላችንንም ድምፆች ከገመገሙ  በኋላ  የእኔ  ድምፅ  ለዜና ሳይሆን ለፕሮግራም እንደሚሆን ተነግሮኝ  ወደ ፕሮግራም ክፍል ገባሁኝ::›› ብላለች፡፡

ዝናሽ ፤በህዳር ወር 1978 አ.ም  ደግሞ በማስታወቂያ ሚኒስቴርና በጀርመን ዲሞክራቲክ  ሪፐብሊክ ጋዜጠኞች ማህበር  የተዘጋጀውን የስድስት ሳምንት  የሬዲዮ ጋዜጠኝነት ኮርስ  እዚሁ አዲስ አበባ መጥተው ተከታትላለች፡፡

ሌላው ደግሞ ኬንያ ናይሮቢ በ1983 በህዳርወር መጨረሻ አኤአ December 1991 Goethe institute with Kenya institute of mass communication ባዘጋጀው የሬድዮ ድራማና የዶክመንታሪ ፕሮግራም አዘገጃጀት ላይ ተሳትፌ ስልጠናን ወስጃለሁ: በማለት አጀመማሯንና ጉዞዋን አስታውሳለች፤፤

                           የስራው አለም

ዝናሽ ፤መደበኛ ፕሮግራም ከመጀመሯ በፊት አዲስ እያለች  የየፕሮግራሙ አዘጋጆች እዲስ ድምፅ ሲፈልጉ እየመጡ ይህን አንብቢልን ሲሉ ታነብ ነበር:: በወጣቶች ፕሮግራም ሲተላለፍ የነበረው የቤዛዬ ግርማ ፅሁፍ ;

በቅዳሜ መዝናኛ ጭውውቶች ላይም ሰው ሲቸግር ድምጹዋን ታሰማ ነበር፡፡:አዲሱ አበበም ህግና ህብረተሠብን ሲሰራ በድምፅ የምታነበው ዝናሽ ነበረች ፤፤ካነበብነው በሚል ጠዋት ጠዋት የሚቀርብ ፅሁፍ ከጋዜጦች አምድ ተብሎ ከቀኑ ዜና ቀጥሎ የሚቀርብ ዝግጅት ከብዙዎቹ መሀል ጥቂቶቹ ናቸው:: ፕሮግራም ስትጀምር የመጀመርያው ፕሮግራሟ ከከተማ ነዋሪዎች ማህበር አካባቢ የሚባለው ነበር:: ሙሉጌታ ወ/ሚካኤል የቅርብ አለቃዬ ነበር :: የተለያዩ የከነማ አካባቢዎች በመሄድ የመዋእለ- ህፃናት ግንባታዎችን ወፍጮ ቤቶችና እንጀራ መጋገርያ ማእከሎችን በወቅቱ የተጀመሩ ብዙ ልማታዊ እንቅስቃሴዎችንና የሚታዩ ችግሮቿንም ለእርምትና ለመሻሻል በሚረዳ መልኩ ሰርታለች፤፤

          የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም

ዝናሽ ፣ 1979  አ.ም የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም አዘጋጆችን ተቀላቀለች ፡፡በዚህም ነፍሱን ይማረውና ከጋሽ ታደሰ ሙሉነህ ጋር አብሮ ስቱድዬ ገብቶ የቀጥታ ስርጭት  live የመስራት እድል አግኝታለች ::ጋሽ ታደሰ አዲስ አዘጋጅ ፕሮግራሙን ሲቀላቀል ስቱድዬ ይዞ ገብቶ ከአድማጩ ጋር የማስተዋወቅ መልካም የሆነ ልምድ ነበረውና ዝናሽንም አስተዋውቋት አስጀመራት፡፡ በዚህም የነበረውን የአቀራረብ ችሎታና  ጥንቅቅ ብሎ ሁሉን ነገር ቅደም ተከተል አስይዞ organized ሆኖ መስራትን ከርሱ ተምራለች ::

‹‹…… ነፍሱን ይማረውና ከታምራት አሰፋ(ታሜ )ጋር አብሮ የእሁድ ጠዋትን መስራት ደግም ልዩ ነበር፡፡ ከመቼው ሰአቱ አለቀ እስከምንል ድረስ አድማጮችን ብቻ ሳይሆን ስቱድዬ ያለነውን በሙሉ ዘና ፈታ የማድረግ ችሎታ እንደነበረው አስታውሳለሁ:: አባይነሽ ብሩም በዝግጅቶች ላይ የነበራትን የኤዲቲንግ ችሎታዋን ቅድመ- ጥንቃቄዋንና አቀራረብዋን አደንቃለሁ::ብሩክት መላኩ አምባዬ አማረ ሂሩት ሀይሉ ሽበሺ ፀጋዬ ከፍያለው አዘዘ ደጀኔ ጥላሁን እንዳልካቸው ፈቃደ ና አበበ ፈለቀ አብሬ ከሰራኋቸው ከብዙዎች መሀል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡የዘነጋኋቸውን ይቅርታ እጠይቃለሁ::ነፍሱን ይማረውና ከተስፋዬ ሀ/ገብርኤል ጋር በመሆንም ፈገግ እያስደረጉ ቁም ነገር የሚያስጨብጡ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችንና አጋጣሚዎችን በማንሳት እርስዎስ ይህ ቢያጋጥሞት ምን ይሰማዎት ይሆን እያልን ሳቢ በሆነ መልኩ ተራ በተራ የምንፅፈውና በመቀባበል የምናቀርበው ተወዳጅ ዝግጅት ነበረን::›› ስትል ዝናሽ 30 አመት ወደ ኋላ ተጉዛ ትዝታዋን ታወጋለች፡፡

ነፍሳቸውን ይማርና የቀድሞ የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ከነበሩት ክቡር የመቶ አለቃ ግርማ ወ/ጊዬርጊስ ጋር የልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ በነበሩበት ግዜ በልማቱ ዙርያ ቃለ ምልልስ የማድረግ እድልም አግኝታ ነበር:: ከሀይማኖት አባቶች አለቃ አያሌው ታምሩን እየሩሳሌም ስለሚገኙ የኢትዮጵያገደማት በተለይም ስለ ዴር ሱልጣን ገዳም እንዲሁም አቡነ ገብርኤልንና ሌሎችንም ከአርቲስቶች ደግሞ ከጀማሪ እስከ አንጋፋ ;የብዙዎች ጥያቄ ሆነው ምላሽ በሚሹ ጉዳዬች ዙርያ የህግ ባለሙያዎችን ;አነጋጋሪ የጤና ችግሮች ለሆኑት ደግሞ ለቆዳ ችግር ዶ/ር ጥበበ የማነ ብርሃንን ለአእምሮ መታወክ ዶ/ር አታላይ አለምን እያልን ብንዘረዘር ቁጥራቸው በርከት ያሉ የጤና ባለሙያዎችን አነጋግራለች፡፡ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ህዝብ ግንኙነት የነበረውን ይስሀቅ ሁሴን አባቦራንና:የቤተክህነቱን ካህሳይ ገ/እግዚእብሄርን ቀና ትብብር ልትዘነጋው አትችልም፡፡

ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል የሚያስብሉ ጆሮ ሳቢ ዝግጅቶችን ከባልደረቦቿ ጋር አቅርባለች:: ድራማዎችና ጭውውቶችን ከይዘታቸው ና መልእክታቸው አንስቶ እስከ ቀረፃ ባለው ሂደት ኤዲት በማድረግ ተሳትፎ ነበራት :: ሰለሞን አለሙ ፣ ሰራዊት ፍቅሬ ፣ ተስፋዬ ማሞ ፣ አብርሃም ወልዴ ና ሀይሉ ፀጋዬ ከእሁድ ፕሮግራም ተከታታይ ድራማ ፀሀፊዎች  ጥቂቶቹ ሲሆኑ  አብዬ ዘርጋው የታውቁበት ሸምጋይ ; ግዞና ባይከዳኝ  የሚታወሱበት  እማ ትርፌ  ; የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች እንዴት ወደ ልማት እንደተሰማሩ  ያሳይ የነበረው ወደ ሀብት ጉዞ ከብዙ ተከታታይ ድራማዎቻችን መሀል የሚጠቀሱ ሲሆን  የታገል ሰይፉ ሀምሳ አለቃ ገብሩም አይዘነጉም::"

‹‹…..ጠዋት ጠዋት ይተላለፍ በነበረ የማለዳ ፕሮግራም ላይ ከሰሎሜ ደስታ ፀሀይ ተፈረደኝ በህጉ መሰረት ና ሌሎችም ጋር የጤናችንን ፕሮግራም ነፍስዋን ይማረውና የጤናችን ፕሮግራም ሲነሳ ስምዋ ሳይነሳ መታለፍ ከሌለባት መንበረ መኮንንና በሴቶችና ህፃናት ዙርያ ብዙ ከሰራችው ከስርጉት አስፋው ጋር አብሬ የመስራት እድል እግኝቻለሁ::እንደዚሁም ከሙዚቃ ፕርግራሞች መሀል የእሁድ ምሽት ምርጥ ሙዚቃ ናየሀሙስ ምሽት የሙዚቃ ሰዎችና ስራዎቻቸውም የሚጠቀሱ ናቸው::በጣት የሚቆጠሩ ቢሆኑም የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎችን መስራቴንም አስታውሳለሁ፡፡›› ስትል ዝናሽ ትዝታዋን ታወጋለች፡፡

                             በኢትዮጵያ ሬድዬ ቆይታዋ

ሁልጊዜም የምታስታውሰው በአዘጋጆች መሀል የነበረውን አብሮ የመስራት መንፈስ team work ነው::ይህም አብረዋቸውይሰሩ የነበሩ የቴክኒክ ባለሙያዎችን ጭምር ያጠቃልላል::ነፍሳቸውን ይማረውና ተካ ወ/ሀዋርያት ሳህሉ በቀለ ፣አለማየሁ እንዲሁም ገበየሁ ኑሬሳ ብርሃኑ አሰፋ ፣ምስራቅ ፣መቅደስ ፣ፍሬህይወት ;ደበላ ቱቲ ና በሻህ ችሎታቸው የሚደነቅ ነበር:: ብርሀኑ እጅጉና ይበልጣልም አይረሱም ::በትራንስፓርት ክፍል የነበሩት እነ አፈወርቅ አለማየሁ ስዩም ሌሎቹም ...ትብብራቸው ን ዝናሽ አትዘነጋውም፡፡ ‹‹……የትራፊክ ክፍሏ ወርቅነሽ ና ብርሃኑየሙዚቃ ላይብረሪዎቹ ጌራ ገነት አበራሽፀሀፊዎቻችን እታጉ ና ሸዋዬ ... ስቱድዬ ለመግባት የስቱድዮ መግቢያ መታወቂያ ማሳየት ግድ ነበር: የስቱድዬ ፈቃድ ሰጪና የመቅርጫ መሳርያዎች ( ኡኸር )አደላዳይ የነበሩት አቶ ሙሉጌታ እኔ በነበርኩበት ዘመን የማይረሱ ናቸው፡፡›› ስትል ዝናሽ የጋዜጠኝነት ትዝታዋን አውርታለች፡፡ የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም እስከ 1986 ድረስ ሁለት የአየር ሰዐት ሲሆን ይህም ከ2-4 ነበር:: በሁዋላ ግን ከ1986 እስከ 1989 ደግሞ ከ2-5 ሰዐት በማራዘም የሶስት ሰዐት የአየር ሽፋን ተሰጥቶን ከ5-6 ሰዐት የፖሊስ ፕሮግራም ይረከበን ነበር፡፡ ከ1989 በኋላ ደግሞ 30 ደቂቃ ተቀንሶ እኛ 4:30 ላይ እናበቃና የመከላከያ ፕሮግራም ዝግጅቶቹን እስከ 5 ሰዐት ያቀርብ ነበር::

               ከእሁድ ጠዋት በተጨማሪ 

‹‹ እሁድ ከሰዐት በኋዋላ ዝክረ-ሰንበት በሚል ስያሜ ከ7-9 የሚተላለፍ ፕሮግራም ነበረን፡፡ እዛም ላይ ሰርቻለሁ፡፡

ከ9ሰአት በኋላ ለአበራ ማሞና ጥሩነህ ማሞ የዘፈን ምርጫ ፕሮግራም አስተላልፈን ነበር የምንወጣው ::

በዚህ የከሰዐት በኋላ ፕሮግራም ላይ ነበር በመስሪያ ቤቶችና በወረዳዎች መካከል ሲካሄድ የነበረው የእርስዎም ይሞክሩት ውድድር ይተላለፍ የነበረው::ውድድሩ ተቀርፆ እንዳበቃ ማታውኑ ቢሮ ተመልሰን ኤዲት አድርገን አስተካክለን ጨርሰንነበር ወደ ቤት የምንሄደው :: እኩለ- ለሊትም ቢሆን እንኳን ካላንዳች መሰላቸት ና ቅሬታ በፍቅርና በትጋት ልዩ በሆነ የትብብር መንፈስ የሰራንባቸውን አመታት መቼም አልዘነጋቸውም:: ቅዳሜና እሁድን በስራ ማሳለፍ ማልዶ መውጣትና አምሽቶ መስራት ያም ካልበቃ እቤት ወስዶ የሚፃፈውን መፃፍ የተላለፈውን እንደገና አድምጦ ለሚቀጥለው ቀን ግምገማና እቅድ መዘጋጀት የተለመደ የስራው ባህርይ ነበር

አመት በዐል ሲመጣ በዋዜማው የነበረው ሽር ጉድ ሁሉም የቀረፀውን ካመጣ በኋላ በየቢሮውና በየስቱድዮው የነበረው ደፋ ቀና የስቱድዬና የኤዲቲንግ መሳርያዎችን ቅድሚያ ለማግኘት የነበረው ሩጫ የበአል ማስታወቂያዎች የአቀራረብ ለዛ .የበአል ዝጅቶች የቀጥታና የዋዜማ ስርጭት ድምቀት ልዩ መአዛ ነበረው::ፕሮግራሞቻችን ከመደመጥ አልፈው በምናብ ወደ አድማጮች ህሊና ገብተው እንዲታዩአቸው ለማድረግ ከቃላት አመራረጥ እስከ አነባበብ የድምፅ ቅላፄ ድረስ የሚሰጠው ትኩረት የሚደነቅ ነበር ፤፤የቱን አንስቼ የቱን እንደምተወው ስለምቸገር የኢትዮጵያ ሬድዬ ትዝታው ብዙ ነው ብዬ ባልፈው ይሻላል::>> ትላለች ዝናሽ፡፡

‹‹……ጋዜጠኝነት የእውቀት ማዕከል ሲሆን ጋዜጠኛ መሆን ደግሞ መታደል ነው:: የህዝብ ጆሮና አፍ ሆኖ ማገልገል ትልቅ ሀላፊነት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ሀላፊነት በታማኝነት ለመወጣት ትምህርት ቤት እንዳለ ተማሪ ሁልግዜ ማንበብ ደጋግሞ ማንበብ ያላወቁትን መጠየቅና በጥንቃቄ ማድመጥንም ይጠይቃል :: ያገኙትን መረጃ ተአማኒነት ለማረጋገጥ ደግሞ ትንሽ ጥረት አክሎ ማስረጃዎችን ማገላበጥ የጉዳዩን ባለቤቶች አግኝቶ ከራሳቸው አንደበት መስማትና ፍርዱን ለአድማጭ ትቶ እንዳለ እውነቱን ማቅረብ የሙያው ስነምግባር የሚጠይቀው መሰረታዊ መመርያችን ነበር  :: በየሳምንቱ ከሚደርሱን በርካታ የአድማጭ ደብዳቤዎች መሀል በግል የሚላኩልን አድናቆቶችና ማበረታቻዎችም ብዙ ነበሩ::በየቀኑ ነው ወይ የሚፅፈው ብዬ እስክገረም ያደረሰኝን ዘቢብ ግርማ የተባለ ከብዙዎች አንዱን የብዕር ደንበኛዬን ግን ሳላነሳው አላልፍም፡፡ በሳምንት በትንሹ አራትና አምስት ደብዳቤዎች ይደርሱኝ ነበር::ሀሳቡን የሚገልፅበት የስነፅሁፍ ችሎታውና ልብ-ወለድ ትረካ የሚመስል አፃፃፉ እንዳስታውሰው አድርጎኛል::እሁድ ጠዋት ላይቭ እየሰራን ስቱድዬ ድረስ ከአድማጭ የተላከልን ኬክም የሚረሳ አይደለም ፤፤፡በስራው አለም በቆየሁባቸው አመታት አተኩሬ ስሰራባቸው በነበሩት የሕዝብ ጤና አጠባበቅ ዙርያ የመገናኛብዙሀን ሚና በጤና አጠባበቅ ትምህርት ስርጭት ዙርያ በሚል የተዘጋጁ ሴምናሮችን ወስጃለሁ:: ፖልዮ ኤድስና ወባን የመከላከልና የፀረ ትምባሆ የቅስቀሳ ፕሮግራምች ዙርያ ለነበረኝ ተሳትፎ በተለያዩ ግዜያት የምስክር ወረቀቶችን አግኝቻለሁ:: እሁድ ከሰአት በኋላ ተላልፎ በነበረው የሚኒስቴር መ/ቤቶች የእርስዎም ይምክሩት ውድድር ለነበረኝ ተሳትፎ የምስክር ወረቀት አግኝቻለሁ:: 1993 አ.ም እስከለቀቅሁበት ግዜ ድረስ በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም አዘጋጅና አቅራቢነት ኤዲተርነት እያንዳንዱን ዝግጅት አዳምጦ ኤዲት አድርጎ በአየር ላይ እስከሚውልበት ደረጃ ኅላፊነትን በመውሰድ የፕሮግራሙ አስተባባሪ በመሆን ሰርቻለሁ፡፡ በዚህም ከፕሮግራም አስፈፃሚነት እስከ ከፍተኛ የፕሮግራም አዘጋጅነት ደርሻለሁ:: ከአቶ ሞገስ ታፈሰ ጀምሮ አቶ ታደሰ ሙሉነህ አቶ ስዩም እስከ አቶ ፍቃደ የምሩ ድረስ ከነበሩ መምርያ ሀላፊዎች ና ስራ አስኪያጆች ጋር ስርቻለሁ አቶ ሀይሉ ወ/ፃድቅ ሙሉጌታ ወ/ሚካኤል ሰለሞን ደስታ አምባሳደር ሱሌይማን ደደፎ ከፍያለው አዘዘ ና ዋጋዬ በቀለን ጨምሮ ከሁሉም ጋር መልካም የሆነ የስራ ግንኙነት ነበረኝ፡፡ ለሁሉም ትልቅ አክብሮት አለኝ :: እንዲሁም መላው የኢትዮጵያ ሬድዬ ባልደረቦቼን ጭምር::›› ትላለች ዝናሽ ማሞ፡፡

 ዝናሽ አሁን ጊዜያዊ መኖሪያዋ አሜሪካን አገር ሲሆን በዩኒቨርስቲ  ቆይታዋ ምርጫዋ የነበረውና በወቅቱ ያላገኘችውን የመድሀኒት ቅመማን ተምሬ certified pharmacy technician በመሆን ውሎዋን ከመድሃኒቶች ጋር በማድረግ  በጤናው ዘርፍ ተሰማርታ በጥሩ ሁኔታ በመስራት ላይ ትገኛለች::

የምህንድስና ምኞቷን ደግሞ በልጆቿ አግኝታለች::

እንደማንኛውም ውጭ የሚኖር ኢትዮጵያዊ ለሀገሯ ፍቅር አላት፡፡  መቼ እንደሚሆን ባታውቀውም ህልምና ምኞቷ  ግን እንደእግዚአብሔር ፍቃድ ወደ ሀገር መመለስ ነው:: ለሀገሯ  ሰላምንና እድገትን ለህዝቦችዋም አብሮነትና ፍቅርን ለሙያውም  ስነ-ምግባሩ  የሚጠይቀውን ተአማኒነት  መሰረት  ያደረገ ከግል ጥቅምና  ዝና የራቀ  ሙያን አክብሮ የሚያስከብር ሙያተኛ እንዲበዛላት ትመኛለች::

ዝናሽ ፤ ከሀገር የወጣችው ባለቤትዋ በደረሰው የዲቪ ሎተሪ  አማካይነት ነበር፡፡ልጆቻችንን ለማስተማር ከነበርን ጉጉት የተነሳ ነው:: ወደ አሜሪካ ያቀናነው ትላለች፡፡

‹‹………. ዝናሽ ከባለቤቷ ከአቶ ተረፈ አሰፋ አርአያ ጋር ሰኔ 7 ቀን 1972 አ.ም በልጅነታችን ተጋብተን ፀደንያ ሳምራዊት ሮቤል ሜሮንና ረድኤት የተባሉ አምስት ልጆችን ወልደን የሰባት የልጅ ልጆች አያት ለመሆን በቅተናል::ለዚህም እግዚአብሔርን በጣም አድርጌ አመሰግናለሁ፤፤›› ስትል ሀሳቧን ትቋጫለች፡፡

        ኂሩት መለሰ  ስለ ዝናሽ ማሞ

ዝናሽ ማሞ የሕይወት ታሪኳን እጹብ ድንቅ በሆነው ማራኪ የስነ ጽሁፍ ችልታዋ አንድም ነገር ሳታስቀር በግልጽ ማንነቷንአሳውቃናለች።ስለ ራስዋ ብቻ ሳይሆን በሕይወትዋና በሙያዋ ትልቅ አስተዋጽኦ የነበራቸውን ሰዎችና የስራ ባልደረቦችዋን በዝርዝርአስታውሳናለች።በምናብ ለብዙ ዓመታት ወደ ኋላ መልሳ ከርስዋ ስራ ይልቅ የእነዚያን የኢትዮጵያ ራድዮ ጣቢያ ምሰሶ የነበሩ ሰዎችን አስተዋጽኦ አጉልታ ማቅረቧ ብቻ ማንነቷን ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።ዝናሽ ከባድ ሸክም በሆነው በራድዮ ጋዜጠኝነት ሞያየተመሰገነች ናት። በተፈጥሮ የታደለችው ወፍራም አስገምጋሚና ሳቢ ድምጿ ልዩ ውበቷ ነው።በሃያዎቹ መጀመሪያ እድሜ ላይ ሆናበኢትዮጵያ ራድዮ በጀመረችው የራድዮ ጋዜጠኝነት በተወዳጁ የእሁድ ጠዋት ፕሮግራም አዘጋጅነት ታዋቂነትን አትርፋለች።

ከአንጋፋዎቹና ተወዳጆቹ የራድዮ ጋዜጠኞች የቀሰመችው ልምድ፣ በተፈጥሮ የታደለቻቸው ብስለትዋ ፣በራስተማመንዋ፣ሃላፊነትንበአግባቡ የመወጣት ችሎታዋና ከምንም በላይ ስራ አክባሪነትዋ ለዚህ አብቅተዋታል ብዬ አምናለሁ።በእሁድ ፕሮግራም ብቻሳይሆን በአስተባባሪነትና በአዘጋጅነት በሰራችባቸው ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ በሚያተኩሩ ዝግጅቶችም ትታወቃለች፤ብዙምአስተዋጽኦ አድርጋለች።

የእኔና የዝናሽና ትውውቅ ብዙ ዓመታት አስቆጥሯል።በብልህዋ፣በቆራጥዋ፣ለእውነት በምትቆመው፣ የዓላማ ጽናቷ ተወዳዳሪበሌለው፣በጠንቃቃዋ እና ቁም ነገረኛዋ ጓደኛዬ ዝናሽ ሁሌም እኮራለሁ።ከዛም በላይ የምታሳሳኝ እህቴ ናት።ለኔ ምትክ የላትም።

አጽናኜ መካሪዬ፣የችግሬ ደራሽ፣ አሁን ለምገኝበት የስራ ደረጃ መሰረት የሆነችኝ እግዚአብሔር የባረካት ሰው ናት።ዝናሽየምትመራው መንገድ፣ሁሌም ጥሩ ቦታ ያደርሳል። የሰውን ችግር እንደራስዋ የምታይ፣ ችግር ሳይፈታ እንቅልፍ የማይወስዳት፣የማትታክት ፣ከራስዋ ይልቅ የሰውን ችግር የምታስቀድም፣ ለተጎዳ አብዝታ የምትጨነቅ፣የታመመ ጠያቂ ፣የተቸገረን በምትችለውሁሉ የምትረዳ……………………… ሌላም ሌላም ብዙ ብዙ በጎ ነገሮችን የምታደርግ ታላቅ ሰው ናት።ሁሉንም ዘርዝሬ አልጨርሰውምና፣በአጭሩ ዝናሽ የጥሩ ነገሮች ሁሉ ምሳሌ ናት፤ ብዬ ባጠቃልለው ነው የሚሻለው።በሌላ በኩል ዝናሽ የማታምንበትን ጉዳይ

በይሉኝታ የማትቀበል ፣በተገቢው ቦታ የምትገስጽና የምታርም ግልጽና ስህተትን የማታልፍ ሰው ናት።እርስዋና እኔ ከልጅነት አንስቶእስከዛሬ ያልተለያየን፤ከአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚጀምረው ትውውቃችን እስከ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የዘለቀ፣ በኢትዮጵያራድዮም የስራ ባልደረቦች የነበርን የቅርብ ጓደኛሞች ነን።ብዙም አልቆየሁም እንጂ እግዚአብሔር ፈቅዶ በምድረ አሜሪካ የመኖርእድል ባገኘሁበት ወቅትም ከአምስት ልጆችዋ በተጨማሪ እኔን እንደ ስድስተኛ ልጅ ተቀብላ አስተናግዳኛለች።ያኔ በባዕድ አገር

ስኖር የመጀመሪያዬ ባይሆንም ዝናሽ ማድረግ ከሚገባት በላይ ርቀት ሄዳ ቤተሰቦቿን በመጫን ደግፋኛለች። ውለታዋን

እግዜአብሔር ይክፈላት ከማለት ሌላ እኔ የምከፍለው አይደለም።በነገራችን ላይ ዝናሽ በአንድ ወቅት ኑሮዋን ለመደገፍ በአሜሪካን

በፋርማሲ ቴክኒሽያንነት ሙያዋ በሦስት ቦታዎች ትሰራ የነበረች ጠንካራ ሰውም ናት።

የምታፈቅራቸውን«እሜ»የምትላቸውን እናትዋን ወይዘሮ ሽብሬንና አባትዋን ጋሽ ማሞን አብዝታ የምታከብር እስከ መጨረሻየሕይወት ዘመናቸውም ተንከባክባ በክብር የሸኘችም ናት። እግዚአብሔር የሚወደውን የምታደርገው ዝናሽ በትዳርዋና በልጆችዋተባርካለች።ለትዳርዋም ብዙ መስዋዕትነት ከፍላለች። ልጆችዋንም ከባለቤትዋ ከአቶ ተረፈ አሰፋ ጋር የሚገባቸውን ፍቅር ሰጥታበትምሕርታቸው እንዲበረቱም የቅርብ ክትትል እያደረገች እየመከረችም አሳድጋለች፤ለክብርም አብቅታለች።እነርሱም አሁንበሚኖሩበት በአሜሪካን ከፍተኛ ትምህርታቸውን አጠናቀው በተለያየ የስራ መስክ ላይ ናቸው።አራቱ ቤተሰብ መስርተውወልደው

ከብደዋል።በጣም የምወዳት አሜሪካንን ያላመደችኝ የመጨረሻ ልጅዋ በስነጥበብ ሞያ ትልቅ ደረጃ ላይ የምትደርስ ባለሞያሆናለች።ይህ ሁሉ ዝናሽ ለትዳርዋ የከፈለችው መስዋዕትነት ውጤት ነው።ጎበዝዋ ተማሪና ብልህዋ ዝናሽ በትዳርና በልጆችምክንያት የዩኒቨርስቲ ትምሕርቷን አቋርጣ ስራ መያዟ የእግዚአብሔር ፈቃድ የነበረ ቢሆንም እንደ ሰው ሰውኛው በትምሕርትዋብትገፋ የት በደረሰች ብዬ ሁሌም እቆጫለሁ።ለምን ብትሉ ዝናሽ ላድርግ ካለች ማድረግ የማትችለው ነገር የለም ብዬ ስለማምንነው። ከዝናሽ ብዙ ተምሬያለሁ፤ አሁንም እየተማርኩ ነው፤ወደፊትም እድሜ ከሰጠን ከርስዋ ብዙ እማራለሁ።የሕይወት ታሪክዋ

አስተማሪ ስለሆነ በዝርዝር ጽፋ እንድታቀርበው ምኞቴ ነው።ይህን ምኞቴንም ነግሬያታለሁ። ፍቅር የሆነችውን የዝናሽን ቀሪየህይወት ዘመን እግዚአብሔርን አብዝቶ እንዲባርክላት እርስዋንም ቤተሰቦችዋንም ከክፉ ሁሉ እንዲጠብቅላት የዘወትር ጸሎቴነው። በዚህ አጋጣሚ የርስዋንና የሌሎችንም ብዙ ልምድ ያላቸውን ግን ያልተወራላቸውን አንጋፋ ጋዜጠኞች ታሪክ፣ለንብብ

ያበቃችሁትን የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አባላት ማመስገን እሻለሁ፡፡

 መዝጊያ: 41 አመት በትዳር አለም የቆየችው ዝናሽ ማሞ ጠንካራ ጋዜጠኛ ብቻ ሳትሆን ብርቱ እናት ናት፡፡ ልጆቿን አስተምራ ለቁምነገር ያበቃች ሲሆን ሁለቱ ልጆቿ ኬሚካል ኢንጂነሮች ሆነዋል፡፡ አንድ የጤና ባለሙያ አንድ ኢኮኖሚስትና የሂሳብ ባለሙያ እንዲሁም የስነ ጥበብ አርቲስት የሆኑ ልጆችን አፍርታለች፡፡ ይህ በራሱ ቆራጥ እናትነቷን ያሳያል፡፡ ዝናሽ ልጅን በአግባቡ ማሳደግ መሰረታዊ ነገር ነው ብላ ታምናለች፡፡ ከባለቤቷ ጋር አንድ ላይ ሆና ቤተሰቡን ደህና አድርጋ መርታለች፡፡ ዝናሽ ማሞ ጋዜጠኝነትን ወዳው ስትሰራ ኖራለች፡፡በተለይ ከ1977-1993 ባሉት ጊዜያት ከሁሉ ጋር በፍቅር በሰላም ሰርታለች፡፡ አይረሴ ድምጽ አላት፡፡ ከ1979 ጀምሮ እሁድ ጠዋት የሬድዮ መሰናዶን ያደመጠ አድማጭ ዝናሽን ሊዘነጋት አይችልም፡፡ ዝናሽ ከታደሰ ሙሉነህ፤ አዲሱ አበበ፤ ሀይሉ ወልደ ጻድቅን ከመሳሰሉ ብርቱ ባለሙያዎች ጋር የአቅሟን ያህል ሰርታለች፡፡ በሃላፊነት ደረጃም በመድረስ በአንጋፋው የኢትዮጵያ ሬድዮ ውስጥ ጉልህ ተጽእኖ ለመፍጠር ሞክራለች፡፡ አንድ አሻራ ያኖሩ ሰዎች እንደ ቀልድ ይዘነጋሉ፡፡ ዝናሽም ባህር ማዶ በመኖሯ የምትረሳ ቢመስልም ነገር ግን ቢያንስ ድምጹዋን የሰማ ሊረሳት አይችልም፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ዝናሽ ማሞ በወርቃማው ዘመን ያገለገለች በሳል ሰው ስትሆን በዘመኗ ስለነበሩት የሚድያ ሰዎች በበቂ ሁኔታ መመስከር የምትችል ነች፡፡ እናም ታሪኳ እንደሚያስተምር አምነን እነሆ አቅርበነዋል፡፡








አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች