44. ዬሐንስ አያሌው      -     Yohannes(Johnny) Ayalew

ዮሀንስ አያሌው  ካናዳ ከመሄዱ ቀደም ብሎ ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሳለ ጥሩ መሰናዶዎችን አየር ላይ በማዋል ስመ-ጥር ለመሆን የቻለ ነው፡፡ በዜና እና በመዝናኛው ዘርፍም የራሱን አስተዋጽኦ ያበረከተ ነው፡፡ ቶሮንቶ ካናዳ ከሄደም በኋላ ይህን የጋዜጠኝነት አቅሙን ለበጎ በማዋል እየተጠቀመበት / እየጠቀመበት ይገኛል፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ሰዎች ባህር ማዶ ሆነው የሚያደርጉትን ሚና ለማጤን የዮሀንስን ታሪክ እንካችሁ ብሎናል፡፡   

         ልጅነት

ዮሐንስ አያሌው ቢሻው በ1969 ነበር የተወለደው፡፡  ብዙዎች የሚያውቁት ጆኒ አያሌው በሚለው ስሙ ሲሆን  በቶሮንቶ ካናዳ የሚኖር ጋዜጠኛ ፣ የጤና እና ማሕበራዊ አገልግሎቶች (Health and Social Services) ባለሙያ ነው፡፡

       ልጅነት  

ዮሐንስ አያሌው ተወልዶ ያደገው በመሐል አዲስ አበባ ካዛንቺስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሲሆን እናቱ ወ/ሮ አንጓች ዮሐንስን እርጉዝ ሆነው በላንድሮቨር መኪና ከሥራ ሲመለሱ ከመኪና ይወድቃሉ ፤ ሆኖም ፅንሱም ሆነ እናት አልተጎዱም ። ከቀናትም በኋላ ዮሐንስ ተወለደ፡፡ ወር በገባ በአራተኛው ቀን ለወንጌላዊው ዮሐንስ የተሰየመ ቀን በመሆኑ ይህንን ከአደጋ የተረፉበትን ቀን ለመዘከር እናቱ “ዮሐንስ” የሚለውን ስም አወጡለት ።ከመንፈሰ ጠንካራ እናት እና ፅኑ የንባብ ልማድ ከነበራቸው አባቱ አቶ አያሌው ቢሻው ጋር በማደጉ የንባብ ፍቅርን አጎልብቷል፡፡

    ኳስ ይወድ ነበር

ዮሐንስ ኣብዛኛውን የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው በእግር ኳስ ነው ። ህይወት ማለት ኳስ መጫወት  ብቻ እስኪመስለው ድረስ ኳስ ይወድ ነበር ።

የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በምሥራቅ ጎህ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ሲጀምር ህይወቱ በመምህራኑ እና በትምህርት ቤቱ መቀረፅ ጀመረ፡፡ በሚያገኛቸው ሽልማቶች እየተበረታታ የሚፈልገውን ነገር ከማግኘት ምንም የሚያግደው እንደሌለም ተማረ፡፡

በሕይወት እርምጃዎቹ ሁሉ የታላላቆቹን ምክር በመስማት በፈተናዎች የላቀ ውጤት በማምጣት የትምህርት ፍላጎቱ ወዳደገበት ወደ ቦሌ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ገባ።

እናቱ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሊያስመዘግቡት ሲሄዱ  በመጠንና በዕውቀት እንደውቅያኖስ የሰፋውን ግቢ ሲያይ እጅጉን እንዳስደነቀው መቼም አይረሳውም፡፡

ዮሐንስ የመጀመሪያውን ዲግሪ በትምሕርት አስተዳደር (Educational Management) ያገኘ ሲሆን በዚህ ዘርፈ- ብዙ መስክ ሳይኮሎጂ ፣ ፔዳጎጂ ፣ ሶሺዮ ኢኮኖሚክስ እና ካልቸራል ሳይንሶችን ተምሮበታል፡፡ ወደ ካናዳ እስከመጣበት ጊዜ ድረስም በጆርናሊዝም እና በማስ ኮሚኒኬሽን ማስተር ዲግሪውን እየተማረ ነበር፡፡ 

ዮሐንስ እንደተመረቀ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኙ የግል ትምህርት ቤቶች እና በኮሌጅ ላይ በአስተማሪነት አገልግሏል፡፡

አስገራሚው ነገር በመምህርነት ሙያው ላይ እያለ በተመሳሳይ ቀን ሶስት የተለያዩ ስራ ቦታዎች ፤ አንደኛ የኮሌጅ የእንግሊዝኛ አስተማሪ እንዲሆን፣ ሁለተኛ በሚኒስቴር መስሪያ ቤት የፈተና ኤክስፐርት እንዲሆን፣ ሶስተኛ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ሪፖርተር እንዲሆን ለተወዳደረባቸው ስራዎች መመረጡ ነበር ።  ዮሐንስ የወደፊት ጥሪው በጋዜጠኝነት መስክ እንደሆነ በማሰብ የኢቲቪን ሥራ ተቀብሏል፡፡  በኢቲቪ በነበረበት ወቅት ዜና አቅራቢ ሪፖርተር፣ የወጣቶችና መዝናኛ ፕሮግራሞች ፕሮዲዩሰር በመሆንም አገልግሏል፡፡ በኢትዮጵያ ቲቪ ከ1994-1998 አ.ም እ ኤአ ደግሞ ከ2001-2005  ለ 4 አመታት የሰራው ዮሀንስ አያሌው ኢቲቪ ጥሩ ጊዜ ማሳለፉን ይናገራል፡፡

በኢቲቪ በስራ ባሳለፈው ጊዜ ውስጥም ዮሐንስ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ሪፖርት ያደርግ ነበር፡፡ ከእነዚህም ለመጥቀስ ያህል የፓርላማ  እንዲሁም፣ አለማቀፍ ስብሰባዎችን፣ የመዝናኛ ዝግጅቶችን፣ አፍሪካ ጆርናል እንዲሁም የሀገሪቱን የዕለት ከዕለት ሁነቶችን በዜና ይዘግብ ነበር፡፡ ከዚህም በላይ የሀገር ውስጥ ከፍተኛ መሪዎችንና አርዓያ ሊሆኑ የሚችሉ ግለሰቦችን ቃለ መጠይቅም አድርጓል፡፡ በዚህም ሳይወሰን አለማቀፍ ዕውቅና ያላቸውን ግለሰቦች እንደ ኦፕራ ዊንፍሬን ፣ የተ.መ.ድ ዋና ጸሐፊ የነበሩትን ኮፊ አናንን ፣ የቀድሞ የሊቢያውን መሪ ሙአመር አልጋዳፊን ፣ ግራሚ አዋርድ አሸናፊ ተዋናይት ኤማ ቶምሰንን ፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሲውዲናዊቷ ኤሚሊያ ተሾመን ፣ ተዋናይ ዳኒ ግሎቨርን እና የሬጌ አቀንቃኙ ሾን ፖልን እንዲሁም በርካታ ሌሎች ታዋቂ ግለሰቦችን ቃለመጠይቅ ለማድረግ ዕድሉን አግኝቷል፡፡

ዮሐንስ በ120 የመዝናኛ ፕሮግራም ‹‹ሾው ቢዝ›› የተሰኘ ተወዳጅ ዝግጅት ያቀርብም ነበር፡፡ ዮሐንስ በሙያው እንዲያድግና ትክክለኛውን አቅጣጫ እንዲይዝ እገዛ ያደረጉለት የሥራ ባልደረቦቹን እገዛ ምንጊዜም ቢሆን አይረሳም፡፡ በዙሪያው የነበሩትን አርአያ የሆኑትን ሁሉ ከልቡም ያመሰግናል፡፡

በ2007 እ.ኤ.አ ወይም በ2000 አ.ም ወደ ካናዳ ከመጣ በኋላ CHIN Multicultural Radio ውስጥ ለኢትዮጵያዊያን ማኅበር ከታዋቂው ጋዜጠኛ ከዳግማዊ ታሪኩ ጋር በመሆን የአንድ ሰዓት ክፍለ ጊዜ ያለው የማህበረሰብ ራዲዮ ፕሮግራም ይመራ ነበር፡፡

ዮሐንስ ፣ በአሁኑ ወቅት አስፈላጊ መረጃዎችን ከቶሮንቶ ለመላው ካናዳ የሚያሠራጭ ሲሆን በኢትዮ ፊደል የዌብሳይት ቴሌቪዥን አማካኝነት ስለ ኢሚግሬሽን ፣ አዲስ መጪዎች በካናዳ እንዲቋቋሙ የሚረዱ መረጃዎችን ፣ ሲቪክ ትምህርቶችን ፣ በቋሚነት ያሰራጫል፡፡ በኢትዮ ፊደል ዌብሳይቱ እና ዩቲዩብ ቻናሉ ላይ ጤና ነክ ጉዳዮችና መዝናኛ ፕሮግራሞችም ይካተታሉ፡፡

በኢትዮ ፊደል በጣም ብዙ እንግዶችን ለቃለመጠይቅ ያቀረበ ሲሆን ተሸላሚ ደራሲዎች ፣ የኮሙኒቲ አንቀሳቃሾች ፣ እናም ወደ ካናዳ የመጡ ታዋቂ ከያኒያንን ከድምፃውያን ማሕሙድ አሕመድ ፣ ነፃነት መለሰ ፣ ጸሐዬ ዮሐንስ ፣ ቴዎድሮስ ታደሰ ፣ ሚካኤል በላይነህ ፣ ቴዎድሮስ ካሳሁን ፣ አበባ ደሳለኝ ፣ ፋንታሁን ሸዋንቆጨው ፣ ጃህ ሉድ እና ሌሎችም ፤ ሠዓሊ ያሬድ ንጉሱ ከኮሜዲያን ክበበው ገዳ ፣ ነፃነት ወርቅነህ ፣ መስከረም በቀለ ፣ ፍልፍሉንና ሌሎችንም ያቀረበ ሲሆን በጠቅላላው በኢትዮ ፊደል ዩቱብ ቻናል እና ዌብሳይት ላይ ከ250 ሥርጭቶችን እና በሺህ የሚቆጠሩ ዜናዎችን አቀናብሮ አስተላልፏል፡፡፡

ዮሐንስ በኢትዮ ፊደል ላይ በእንግድነት ካቀረባቸው እንግዶች መሀል የቀድሞው የካናዳ የኢሚግሬሽን ሚኒስትር አቶ አህመድ ሁሴን ፣ የቶሮንቶ ከንቲባ ጆን ቶሪ ፣ የቀድሞው የካናዳ መከላከያ ሚኒስትር ጄሰን ኬኒ ፣ የቀድሞው የቶሮንቶ ከንቲባ የነበሩትና በሞት የተለዩት ራብ ፎርድ ፣ የቀድሞው የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪም ካምቤል እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

በተጨማሪም እንደ ኩሶ ኢንተርናሽናል(Cuso International) ካሉ ዓለማኣቀፍ ድርጅቶች ጋር የዲያስፖራ ወገኖችን የበጎ ፍቃድ ተሳትፎ በተመለከተ አብሮ ሰርቷል።











ዕውቅናና ሽልማቶች

የኢትዮ ፊደል ዳት ካም(Ethiofiedel.com) ድህረ ገጽ ዳይሬክተርና አዘጋጅ የሆነው ዮሐንስ አያሌው በራዲዮ ፣ በቴሌቪዥን ፣ በኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ ዘርፍ በተሻለ አመለካከት ፣ አቀራረብና አመራረጥ የክብር ሽልማት ከ Canadian Ethnic Media Council ምርጥ የበይነ መረብ ሚዲያ (Social Media) ሽልማት በ 2017 እ.ኤ.አ ከኦንታሪዮ ገዥ እጅ ተበርክቶለታል፡፡

በሺህ የሚቆጠሩ በካናዳ የሚኖሩ የኮሙዩኒቲውን አባላት በተለያዩ መንገዶች በበጎ ፈቃደኝነት በመርዳት ላበረከተው አስተዋጽኦም ከተለያዩ የኮሙኒቲ ድርጅቶች እና ከፓርላማ አባላት ምስክር ወረቀት ተበርክቶለታል፡፡

የበጎፈቃድ ሠራተኞች እና የኮሙኒቲ ግንባታን በተመለከተ ባደረገው አስተዋፆ በ Huffington Post ጋዜጣ የ2013 እ.ኤ.አ ምርጥ የ ካናዳ ማህበረሰብ ገንቢዎች ውስጥ ተካቷል ፡፡

https://www.huffingtonpost.ca/.../best-community-builders...

ማሕበራዊ ግልጋሎቶች ሙያ

ወደ ካናዳ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ ዮሐንስ በማህበረሰቡ ውስጥና በጤና ዘርፎች ግልጋሎት ሰጥቷል፡፡ ካናዳ በደረሰ በአጭር ጊዜም በኢትዮጵያ ማህበር በቶሮንቶ የበጎፈቃድ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ፤ በዛውም የኤች አይቪ ኤድስ ትምህርትና መከላከል አስተባባሪ በመሆንም አገልግሏል፡፡ በዚህ መርሀ ግብርም ኤች አይ ቪ ኤድስን በተመለከተ እጅግ ብዙ ስልጠናዎችን ሰጥቷል፡፡

በኢትዮጵያ ባህላዊ የቡና አቀራረብ “ቡና ጠጡ” በሚል የግብዣ ጥሪ ላይም የውይይት መድረክ በመፍጠር የኮሙኒቲው አባላት እንዲነጋገሩ በማስተባበርና የኤች አይ ቪ ጫናን በተለይም የአዕምሮ ጤንነትን ፣ የወጣቶችን እና የሴቶችን አቅም ለማጎልበት መደረግ ስለሚገባቸው ነጥቦች ተሳታፊዎቹን አወያይቶ አመርቂ ውጤትን አስገኝቷል፡፡

በተጨማሪም “እችላለሁ” የሚል ዘመቻ በመጀመር በካናዳ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ኤች አይ ቪ ኤድስን እና በፆታ ላይ ያተኮረ ጥቃትን በተመለከተ የማንቂያ ደወልን አስተጋብቷል፡፡

አፓ (APA.org) የተባለ ሌላ የኤድስ አገልግሎት ድርጅት ውስጥ በሰራባቸው በርካታ አመታት ላይ 5000 ያህል የበጎፈቃድ ሠራተኞችን በመመልመል በሺህዎች የሚቆጠሩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰዓታት አሰጥቷቸዋል፡፡

አዲስ ለሚመጡ ወጣቶች እና አለማቀፍ ስልጠና ያገኙ ባለሙያዎችን ወደ ካናዳ የስራ ሲስተም ውስጥ  እንዲገቡ የአቅሙን ረድቷል፡፡

ዮሐንስ በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች የቦርድ አባል ፣ አማካሪ ቡድን እና የፈንዲንግ ፍቃድ ኮሚቴ እና ኮሙኒቲን ያማከለ የጤና ምርምር ውስጥ በቦርድ አባልነትም አገልግሏል፡፡

ዮሐንስ ጋዜጠኝነት "አወንታዊ ታሪኮችን በማቅረብ ይህንን ዓለም የተሻለ ለማድረግ የሚያስችል ዘለአለማዊ ተፈላጊነት ያለው ሙያ ነው" ይላል፡፡

ለዚህም ነው በኢትዮ ፊደል ዳት ካም አዳዲስ ታሪኮችን እና ቪዲዮዎችን  ያለማሰለስ የሚጽፈውና የሚያቀርበው፡፡ በአሁኑም ሰዐት በዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዋተር ሉ(University of Waterloo) ካናዳ በሕዝብ ጤና ሳይንስ (Public Health) ማስተርሱን ተምሯል ፡፡

የእግዚአብሔር ፀጋ እና የሌሎች እገዛ በሄደበት እንደሚከተለው የሚናገረው ዮሐንስ እዚህ እንዲደርስ ለረዱት ለቤተሰቦቹና ለስራ ባልደረቦቹ የከበረ ምስጋና ይሰጣል፡፡

መዝጊያ : ሰው ከሀገር ቤት ወጥቶም የሀገሩን ስም በበጎ ያስጠራል፡፡ ሀገሩ ጎበዝ የሆነ ባህር ሲሻገርም ብርታቱን ጨምሮ ያሳያል፡፡ ዮሀንስ በቶሮንቶ ሀገራቸውን ካስተዋወቁ ፤ በሚድያው አርፍ ከደከሙት አንዱ ነው፡፡ ካናዳ ቶሮንቶ ውስጥ ባበረከተው ሚና ሽልማት ማግኘት ችሏል፡፡ ይህ ጥረቱ ተጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል፡፡ በተለይ በማህበረሰብ አገልግሎት  ሳይታክት እየሰራ እንደሆነ ታሪኩ ድንቅ ምስክር ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች በጥረት እናምናለን፡፡ ሰው የትም ሆኖ ኢትዮጵያ የሚለውን ታላቅ ስም በበጎ መልኩ ማስጠራት እንደሚችል ጥሩ ግንዛቤ ወስደናል፡፡ ለዚህ ደግሞ ዮሀንስ አያሌው ታሪኩ በአዲሱ ትውልድ እንዲታወቅ ፈልገን እነሆ እወቁት ብለናል፡፡  

ዮሐንስ(ጆኒ) አያሌውን በ ዩቲዩብ ፣ ፌስ ቡክ ፣ ትዊተር እና ሊንክድኢን ሊከተሉት ይችላሉ።





















 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች