42. ሙሉጌታ ሉሌ ደስታ- MULUGETA LULE DESTA
ያልተዘመረለት ጋሽ ሙሉጌታ ሉሌ ክፍል አንድ
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን ዛሬ ወደ ሙሉጌታ ሉሌ ታሪክ ዘልቋል፡፡ ያልተዳሰሱ
ታሪኮች ይነካሉ፡፡ በቅርቡ በምናሳትመው የኢትዮጵያ ኢንሳይክሎፒዲያ መጽሀፍ ውስጥ የሙሉጌታ ሉሌ ታሪክ ተካቷል፡፡ የፖለቲካ ተንታኝ፤ ብርቱ
አንባቢ የነበረው ሙሉጌታ ሉሌ 50 አመት በዘለቀ የጋዜጠኝነት ህይወቱ ለእናት ሀገሩ ብዙ ሰርቷል፡፡ ውብ በሆኑት
መጣጥፎቹ የኢትዮጵያን አንድነት በትጋት ሰብኳል፡፡ ታዲያ ሙሉጌታ
በ75 አመቱ ህይወቱ ቢያልፍም ታሪኩ ግን ወደ ቀጣዩ ትውልድ ይሻገራል፡፡ እርሱ ግን ማነው? ክፍል አንድን ይከታተሉ፡፡
የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ
ተወዳጁ ጋዜጠኛ
ጸሀፊና የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ ደስታ ሀምሌ 3 1933
ነበር የተወለደው፡፡፡፡አባቱ ሉሌ ደስታ ሲባሉ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ ወርቅነሽ ጎሹ ይባላሉ፡፡ የተወለደበትም ስፍራ ግንደ በረት ይባላል፡፡አባትና እናቱ
ግንደበረት በንግድ ስራ ይተዳደሩ ነበር፡፡አቶ ሙሉጌታ የቤተሰቡ የመጨረሻ ልጅ ሲሆን ታላቆቹ ውርስ አረፍ ሉሌ ፣ ተፈራ
ሉሌ፣ስንሻው ሉሌ፣ይታይሽ ሉሌ ሲሆኑ ሁሉም ቀደም ብለው ከዚህ አለም በሞት የተለዩ ናቸው፡፡
የዶክተር ነጋሶ መምህር
አቶ ሙሉጌታ በሸዋ
ጠቅላይ ግዛት፣ አምቦ ከተማ ማእረገ -ህይወት ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ትምህርት ቤት አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ፣
በደብረብርሀን ኃይለማሪያም ማሞ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ቤት ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡በመቀጠልም ናዝሬት በሚገኙት የባይብል
አካዳሚዎች በመግባት ዘላቂ መሰረት የሆነውን እውቀት ወስዷል፡፡
ከቀዳማዊ ኃይለስላሴ ዩኒቨርሲቲ ለ 4 አመታት በፖለቲካል ሳይንስ ኤንድ ገቨርመንት ከፍተኛ ትምህርቱን መከታተል ችሏል፡፡
አቶ ሙሉጌታ ወደ ስራው አለም የዘለቀው እዚያው በሰለጠነበት ባይብል
አካዳሚ የታሪክ እና የአማርኛ መምህር በመሆን ነበር፡፡ከ1955-1956 ድረስ ባደረገው ቆይታም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ታዋቂ
የሆኑትን እንደ ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ፣ ዶክተር ላጲሶ ጌ ዲሌቦ ፣ አቶ ሌንጮ ለታንና የመሳሰሉትን ማስተማሩ ተዘግቦለታል፡፡
ፐርሶኔሉ ሙሉጌታ ሉሌ-ወደ አዲስ ዘመን
በ1957 አ.ም በኢትዮጵያ መብራትና ኤሌክትሪክ ኃይል ባለስልጣን ውስጥ
በፐርሶኔልነት ተቀጠረ፡፡ከ1958 አ.ም ጀምሮ ደግሞ በየምስራች ድምጽ የሬድዮ ጣቢያ ላይ መስራት ጀምሯል፡፡ የአለም አቀፍ
ሉትራን ፌዴሬሽን ንብረት በሆነውና ኋላም መንግስት በወረሰው የብስራተ-ወንጌል የሬድዮ ጣቢያ ውስጥ ለ 2 አመታት በፕሮግራም
አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡ ስራውንና ብእሩን በልዩ አድናቆት የተመለከቱት የስራ ባልደረቦቹና አለቆቹ ጳውሎስ ኞኞ እና ብርሀኑ ዘሪሁን ወደ ማስታወቂያ ሚኒስቴር መጥቶ
እንዲሰራ አግባብተውታል፡፡
በዚህም መሰረት፣
አቶ ሙሉጌታ በ1960 ግድም፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ተቀጠረ፡፡ለበርካታ አመታት፣ አቶ ሙሉጌታን በወዳጅነት የሚያውቁት አቶ
አሰፋ ጫቦ እንደተናገሩት ፤ አቶ ሙሉጌታ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይቀጠር እንጂ በተለያዩ በወቅቱ ይታተሙ ለነበሩ የህትመት
ውጤቶች ጽሁፍ ያበረክት እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ዘርፈ- ብዙ ጋዜጠኛ የነበረው ሙሉጌታ ሉሌ እንደ ሄራልድ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ
፣የኢትዮጵያ ድምጽ ፣ መነንና አዲስ ሪፖርተር በመሳሰሉ ጋዜጦች ላይ በአማርኛና በእንግሊዝኛ በርካታ ጽሁፎችን ለንባብ
አብቅቷል፡፡ አንዳንዶቹም ላይ በረዳት አዘጋጅነት ሰርቷል፡፡በ1967 ግድምም የዛሬይቱ ኢትዮጵያ ተባባሪ ዋና አዘጋጅ ሆኖ
መስራቱን የመነን መጽሄት ዋና አዘጋጅ ሆኖ መሾሙን ከራሱ የስራ ፋይል ለመረዳት ተችሏል፡፡
ሙሉጌታና የዚያድ ባሬ ወረራ
አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣
በ1968 ወደ ኤርትራ በልዩ የግዳጅ ስራ ሄዶ ‹‹ ኢትዮጵያ›› የሚል መጠሪያ የተሰጣት ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ ተመደበ፡፡ በጊዜው በሪፖርተርነት ስራ
መደብ አብሮት መስራቱን ጋዜጠኛ ክፍሌ ሙላት ይናገራል፡፡ በምስራቁ በኩል የተቃጣውን ወረራ ለመመከት የሚያስችል ልዩ የፕሮፖጋንዳ እና የስነ-ጽሁፍ ክፍል
በማስፈለጉበማስታወቂያ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ ሬድዮ ጋር ልዩ መምሪያ ሲቋቋም መምሪያውን በስራ ኃላፊነት እንዲመራ የታጨው ሙሉጌታ
ሉሌ ነበር፡፡ በዚህም መሰረት መንግስት በ1970 መጀመሪያ ላይ አቶ ሙሉጌታ ከአስመራ ወደ አዲስ አበባ ተመልሶ መላውን
የኢትዮጵያ ህዝብ የሚያንቀሳቅስ የፕሮፖጋንዳና የስነ-ጽሁፍ ስራ እንዲመራ አድርጓል፡፡አሉ የተባሉ ከየመምሪያው የተውጣጡ
ባለሙያዎችን በበቂ ሁኔታ በመምራት ግዳጁን ተወጥቷል፡፡ አቶ ክፍሌ ሙላት እንደሚናገረው በጊዜው ኢትዮጵያ ሶማሊያ ላይ
ላደረገችው ድል የሙሉጌታ ሚና ከፍተኛ መሆኑን ይናገራል፡፡
ይህ መሆኑን
በትክክል የሚያስታውሱት አቶ አሰፋ ጫቦ ሙሉጌታ ሉሌ ፤ የሶማሊያና የኤርትራን የፖለቲካ ታሪክ በሚገባ አንብቦና ተንትኖ የሚያውቅ ባለሙያ ነው ብለው ነበር፡፡ በዚህ
የጠለቀ እውቀቱ ምክንያትም የመንግስት ባለስልጣናትንም በማማከር ትልቅ ስራ ሲሰራ እንደነበር አቶ አሰፋ ጫቦ ያስረዳሉ፡፡አቶ
አሰፋ እንደሚናገሩት፣ አቶ ሙሉጌታ ከራሱ ሀገር አልፎ
የአውሮፓና የአሜሪካ የፖለቲካ ትንታኔዎች ላይም
የጠለቀ ንባብ ያለው ሰው መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ይህንን እውቀቱን ዘልቆ ለመረዳት የሚጽፋቸውን ጽሁፎች ማንበብ ብቻ
ይበቃል፡፡ሙሉጌታ ይህን መጽሀፍ አንብበሀል ? ያንንስ ተመልክተኸዋል?እያለ አዲስ አበባ ተቀምጦ አሜሪካ ያለን ሰው የሚፈትን
ነው ሲሉ አቶ አሰፋ ጫቦ ሀሳባቸውን ሰጥተው ነበር በህይወት በነበሩበት ጊዜ፡፡
እንጨት እንጨት ይላል ማነው የጻፈው ?
በኤርትራም፣ የቀይ
ኮከብ ዘመቻ ሲጀመር ፤ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ በበአሉ ግርማ የተመራውን የጋዜጠኞች ቡድን በምክትልነት እየመራ ስራውን በብቃት
ያከናውን ነበር፡፡አቶ ሙሉጌታ በርካታ ባለሙያዎችን አፍርቷል፡፡እስከ 1975 አ.ም ድረስ በኢትዮጵያ ሬድዮ በስራ መሪነት
ያገለገለ ሰው ነበር፡፡ አቶ ሙሉጌታ ፣በፖለቲካ እና በቅስቀሳ ስራዎች ብቻ ሳይወሰን ተወዳጅ የሆኑ ማህበራዊና የመዝናኛ
ዝግጅቶችንም በመስራት ጽሁፎችንም በማበርከት ይታወቃል፡፡የቪኦኤው ጋዜጠኛ
አዲሱ አበበ ስለዚሁ ሲገልጽ ‹‹…. አቶ ሙሉጌታ አንዳንዴ ለእሁድ ጠዋት ፕሮግራም የሚሆን ጽሁፍ ይሰጠናል፡፡ ይሄ
ጽሁፍ እንጨት እንጨት ይላል ማነው የጻፈው ? እያለ ይቀልድብን ነበር፡፡ ከዚያ ጽሁፉን ከወሰደ በኋላ ደላልዞ እንደገና የመጻፍ
ያህል አስተካክሎ ይሰጠናል፡፡›› ብሎ ነበር፡፡ አዲሱ እንደሚያስታውሰው ሙሉጌታ ልክ መጽሄት ላይ በብእር ስም እንደሚጽፈው ሁሉ በሬድዮም መጣጥፎችን
ሲያበረክት የራሱ የብእር ስሞች ነበሩት፡፡ ያኔ በተለይ በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ በየሳምንቱ የማይቀር ጽሁፍ ነበረው፡፡ ጋዜጠኛ አባይነሽ በ1970ዎቹ
መጀመሪያ ላይ ሬድዮ ላይ ስትሰራ አቶ ሙሉጌታ አለቃዋ እንደነበር ታስታውሳለች፡፡ በተለይ ፕሮግራም አየር ላይ ከዋለ በኋላ
ገንቢ አስተያየት በመስጠቱ ታስታውሰዋለች፡፡
ኣገር ቢቀማም ብእሩን ያልተቀማ
አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምሪያ ኃላፊ በመሆን ከ1976-1983 ድረስ አገልግሏል፡፡ በዚህ ቆይታውም፣ በስሩ አዲስ ዘመን ፤
ኢትዮጵያን ሄራልድ፣የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣በሪሳ / በኦሮሞኛ የሚታተምና ‹‹አልአለም››/ በአረብኛ የሚታተም./ የተባሉ የህትመት
ውጤቶችን መርቶ አስተዳድሯል፡፡ማስተዳደር ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያን ሄራልድ፣
ለአዲስ ዘመንና ለዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጽሁፎችን ሲያበረክት ርእሰ-አንቀጽ ሳይቅር ጽፎ እየሰጠ አጋርነቱን ሲወጣ
ነበር፡፡ቀደም ሲል በመነን ያደርግ እንደነበረው እንደ የካቲት
በመሳሰሉ መጽሄቶችም ላይ ቋሚ አምደኛ ነበር፡፡
የመንግስት ለውጥ
እስከተካሄደበት እስከ 1983 ድረስ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ፣ እንደ ብዙዎቹ ሀገር ወዳድ ኢትዮጵያውያን ለአመታት ካገለገለበት
መስሪያ ቤት ተፈናቅሏል፡፡ከስራው ይፈናቀል እንጂ ከሙያው ያልተፈናቀለ በመሆኑ ገና በለውጡ የመጀመሪያው አመት በ1984 ከሙያ
ባልደረቦቹ ጋር አንድ ላይ በመሆን ‹‹ጦቢያ›› መጽሄትን አቋቁሞ
ይበልጥ ገናና የሆነበት ብእሩን ለአንባቢ ለማሳየት ችሏል፡፡
እነጸጋዬ
ገብረመድህን አርአያ የተባሉት ስመ-ጥር የብእር ጀነራሎች የተወለዱትም ከዚሁ ጊዜ አንስቶ ነበር፡፡ጋሽ ሙሉጌታ ተርቡ ፣ ስንሻው
ተገኝ ፣ ስልቁ የመሳሰሉ ሌሎች የብእር ስሞችም አሉት፡፡ የነጻውን ፕሬስ ጫና እንዲሁም የእነ ጸጋዬ ገብረመድህንን አርአያ
የሰላ ሂስ መቋቋም ያልቻለው መንግስት ማሳደዱን ቀጠለበት፡፡ አቶ ሙሉጌታ ሉሌንም በክስና እስራት ያጣድፍ ጀመር፡፡ አቶ ሙሉጌታ
ሉሌ ላይ ከ15 በላይ ክሶች የተመሰረቱበት ሲሆን ለተደጋጋሚ ጊዜያትም ለመታሰር የበቃ ነው፡፡በደህንነት ሰዎች በመኪና ተድጦ
ህይወቱ እንዲያልፍ ቢሞከርም ሊተርፍ ችሏል፡፡ ቢሮውም በእሳት የጋየበት ጋዜጠኛ ነው፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ ኣገር ቢቀማም ብእሩን ያልተቀማ ታላቅ ጀግና ነበር፡፡
ወዳጆቹ እንደሚናገሩት በተለይ በግድያ ሙከራነቱ ስለሚጠረጠረው
የመኪና አደጋ በተአምር ተርፎ ሆስፒታል ተኝቶ
ነበር፡፡ ሆስፒታል ድረስ እየተከታተሉ ያስቸገሩትን የደህንነት አባላት ለመሸሽ ህክምናውን በመኖሪያ ቤቱ ተኝቶ በወዳጅ ሀኪሞች
ለመከታተል የተገደደበት ሁኔታ ሁሉ ነበር፡፡ ታዲያ በዚህ የህመም ወቅት አቶ ሙሉጌታ ‹‹…. እንኳንም እጄን አልቆረጡት ፡፡
ብእር የምይዝበት እጄ እስካለ ድረስ ተርፌአለሁ፡፡›› እያለ ወዳጅ ዘመዶቹን ያጽናና ነበር፡፡ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ነጻ
ጋዜጠኞች ማህበር መስራች አባል ሲሆን እነ አቶ
አቶ ከፋለ
ማሞ ፕሬዚዳንት በነበሩ ጊዜ ምክትል በመሆን አገልግሏል፡፡ እንደ ሲፒጄ ካሉ አለምአቀፍ የጋዜጠኞች መብት ተሟጋች
ድርጅቶች ጋርም በመተባበር ለሙያ ልጆቹና አጋሮቹ መብት ጥብቅና ሲቆም የኖረ ባለውለታ ነው፡፡ በባህር ማዶ የሚኖሩ የነጻው
ፕሬስ ጋዜጠኞች መልካም ስም ከመቃብር በላይ ዘላለማዊ ሆኖ ይኖራል ሲሉ ሙሉጌታ ሉሌ ለአዲሱ የፕሬስ ትውልድ ፈር ቀዳጅ ነው
ብለዋል፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ በአንደበቱ እውነትን ከልቡ የመሰከረ በሳላ ብእሩ ሀቅን የፈነጠቀ ለኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ምሳሌ ሆኖ
ያለፈ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ነው ሲሉም አክብሮታቸውን ገልጸውለታል፡፡
ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ
፣ ወደ ህንድ ሀገር በመመላለስ የተለያዩ ኮርሶችንም ወስዷል፡፡
ከህንድ የመገናኛ ብዙሀን ባልደረቦችና ከኢንዲያን ዴይሊ ጋዜጠኞች ጋርም ሰርቷል፡፡ በሶቭየት ህብረት እንደ ፕራቭዳና ትሩድ
ከመሰሉ ጋዜጦች በተጨማሪም ከቺኮዝሎቫኪያ ፣ሀንጋሪ፤ምስራቅ
ጀርመን ፤ ከቡልጋሪ እና ኩባ ሀገር ጋዜጦች ጋር የልምድና የስራ ልውውጥ በማድረግ ተሳትፏል፡፡
በኢትዮጵያ ሬድዮ
ውስጥ ለ 5 አመታት ይህም ከ1970-1975 ባሉት ጊዜያት ያገለገለ ሲሆን በጊዜውም የነበሩ ጋዜጠኞች አቶ ሙሉጌታን አይዘነጉትም፡፡ በኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
ደግሞ 10 አመት ለሚሆን ጊዜ አገልግሏል፡፡ በንጉሰ -ነገስቱ ዘመን በአሜሪካ ኤምባሲ ይዘጋጅ በነበረው ‹‹ እድገት ››
በተሰኘው ህትመት ላይም በጽሁፍ አቅራቢነት ተሳትፏል፡፡ በአሜሪካን ሀገር ህግ እንዴት እንደሚወጣ የሚል መጽሀፍ ተርጉሞ አሰናድቷል፡፡በውጭ
ጉዳይ ሚኒስቴር አማካሪ በመሆን በተለይም የኬንያ ፣ ጅቡቲ ፣ ሱዳን፤ግብጽና ሶማሊያ ጉዳዮችን በሚመለከት በተደረጉ ሰፋፊ
የጥናትና የፖሊሲ ምርምሮች ላይ ተሳትፏል፡፡በስቴት ዲፓርትመንት ለመገናኛ ብዙሀን መሪዎች በሚሰጠው ጉብኝት አማካይነት በ1995
በአሜሪካ የሚገኙ ዋና ዋና የመገናኛ ብዙሀንን የህዝብ ግንኙነት ተቋማትን ጎብኝቷል፡፡
አርአያ ሊሆን የሚችል ሰው
አቶ ሙሉጌታ ሉሌ
ሞገስ ያለው ነው፡፡ሆይ ሆይታ እምብዛም አይጥመውም፡፡ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌም በህይወት በነበሩ ጊዜ ይህንኑ ነው ያሉት ፡፡
ሙሉጌታ ረጋ ያለ ነው፡፡ነገርን ግራና ቀኝ ማስተዋል ይችላል፡፡እውነትን
ለመፈለግ ብዙ ይጥራል፡፡እውነትንም ለመናገር ወደ ኋላ አይልም፡፡አርቆ ያያል፡፡ሙሉጌታ ሰበር ዜና ወይም ትኩስ ዜና የሚጥመው
ሰው አይደለም፡፡እርሱ የሚያተኩረው ትምህርት ሰጪና ጠለቅ ያሉ ነገሮች ላይ ነው፡፡በሰውነቱ ታጋሽ፣ ነገሮችን በትእግስት ማለፍ
የሚችል ሰው ነው፡፡ አርአያ ሊሆን የሚችል ሰው ነው፡፡ራሱ አውቃለሁ ብሎ ከሚያውቀው በላይ የሚያውቅ ሰው ነው፡፡ ትሁትም
ነው፡፡ቢያውቅ እንኳን እንደማያውቅ ሆኖ ይጠይቃል፡፡የዘመናችንን ፖለቲካ እና ታሪክ ያውቀዋል፡፡ እስከመጨረሻው ለአገሩ
ለኢትዮጵያ ያስብም ነበር፡፡አጫጭር ድርሰት አያውቅም፡፡ምክንያቱም ብዙ ያነባል፡፡ስለሆነም ብዙ ያውቃል፡፡ብዙ የሚያውቀው ነገር
ስላለ ደግሞ ያንን ተናግሮ ማቆም ያቅተዋል፡፡ያም የእውቀቱን ምልክት ያሳያል፡፡ንባብ አፍቃሪነቱ ሚድያ ላይ ከገባ በኋላ የመጣ
ሳይሆን ገና በልጅነት የጀመረ ነው፡፡ ገና የ10ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ የሼክስፒርን መጻህፍት እነ ሀምሌት፤ማክቤዝ ፤ ኦቴሎ
የመሳሰሉትን በቃሉ ይወጣቸው ነበር፡፡ጽህፈት ይሆንለታል፡፡ እንዲያውም ካናዳዊው መምህር ይህን ሌላ ሰው ጽፎልህ ይሆናል እንጂ
እንደምን አንተ ልትሆን ትችላለህ?፡፡ብሎ ያንገራግር እንደነበር በጨዋታ ማንሳቱ ተሰምቷል፡፡ ወደፊት ትልቅ ጸሀፊ ትሆናለህ
ብሎኝም ያውቃል እያለ ይቀልድ ነበር፡፡ከትህትናውና ይሉኝታው ብዛት አንተ ለምንድን ነው ስለራስህ የማትጽፈው? ተብሎ ሲጠየቅ
እሺም እምቢም ሳይል በፈገግታ ይሸኛል፡፡ስለ ግለ-ታሪኩ እንኳን ቃለ-መጠይቅ ሲጠየቅ ማውራት የማይፈቅድ ሌላው ግን ሲተነትን
ለሰአታት ቢቀመጥ የማይታክተው ሰው ነው፡፡ ልጻፍ ብሎማ ሲነሳ ፍጥነቱ በብዙዎች ለመደነቅ የቻለ ነው፡፡
ጋሽ ሙሉጌታ፣
ከአገር ከወጣ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ጦቢያን ከዚያም የልሳነ-ህዝብን መጽሄት ላይ ተሳትፎውን የቀጠለ ቢሆንም ሁለቱም ከህትመት
ውጭ እንዲሆኑ በመደረጋቸው ለተወሰነ ጊዜ የጽሁፍ አምሮቱን ተወጥቷል፡፡ አልፎ አልፎ በድረ-ገጾች ላይ ቢጽፍም ከወረቀት
እንደሚገጥመው አያረካውም፡፡ ወደ ኋላ ላይ ከተወሰኑ ጋዜጠኞች ጋር የጀመረው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትወርክ/ኢቲኤን/ ላይ ከህልሙ የቻለውን ያህልም ቢሆን ፈጽሞ አልፏል፡፡ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ስራ አስኪያጅ ሆኖ
በመስራችነት ጭምር አቅሙን ያሳየ ነበር፡፡
ከቅርብ የስራ
ባልደረቦቹና ወዳጆቹ መካከል አለምጸሀይ ወዳጆ ጠዋት ጠዋት ሁሌም ሙሉጌታ በስራ ተወጥሮ ፤አቀርቅሮ እንደምታገኘው ትናገራለች፡፡
ጋሽ ሙሉጌታ ሁሌም አጎንብሶ ወይ ሲያነብ አሊያ ሲጽፍ ነው የማየው ብላለች፡፡ እንደእርሱ ያለመታከት ሲያነብ የኖረ ሰው አይቼ
አላውቅምም፡፡›› ብላለች ፡፡
አቶ ከበደ አኒሳ፣
ለአዲስ ኦብዘርቨር እንደተናገሩት‹‹…. ሙሉጌታ የትውልድ ጋዜጠኛ ነው፡ሲሉ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት መምሪያ ኃላፊ የነበሩት
አቶ መርእድ በቀለም የአቶ ሙሉጌታ ህልፈት ሀገሪቱ ትልቅ ሰው እንዳጣች የሚነግረን ነው ብለው ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡ የኢትዮጵያ
ድምጽ ፣ ኢትዮጵያ/ አስመራ/ ፣ አዲስ ዘመን ፣ኢትዮጵያን ሄራልድ፣ የዛሬይቱ ኢትዮጵያ፣ መነን የካቲት ፤አሻራውን የተወባቸው
የህትመት ውጤቶች ነበሩ፡፡ በተጨማሪም የምስራች ድምጽ ፣ አለም አቀፍና ብሄራዊ የሬድዮ ጣቢያዎች፣እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
፣ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ኔትወርክ ፣በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሳተላይት ቲቪ ሬድዮ ኢሳት ላይ ትልቅ ተሳትፎ
አድርጓል፡፡በ1984አ.ም ደግሞ በዮሀንስ ሙሉጌታ ስም ‹‹አጥፍቶ
መጥፋትን›› ለማሳተም ችሏል፡፡
ልጅ በልቶ የሚጠግብ አይመስለውም
ዮሀንስ ሙሉጌታ፣ የሙሉጌታ ሉሌ የመጀመሪያ ልጅ ሲሆን እንደ አባት መልካም
አባት መሆኑን በሙሉ አንደበቱ ይመሰክራል፡፡ ዮሀንስ እንደሚናገረው በአቶ ሙሉጌታ ቤት ብዙ ልጆች ያድጉ ነበር፡፡ ይህም አቶ
ሙሉጌታ ለልጅ ያለውን ፍቅር የሚያሳይ ነበር፡፡ ዮሀንስ፣ ስለ አቶ ሙሉጌታ ሲያነሳ በጠዋት ትምህርት ቤት ሲወስዳቸው የነበረውን
ትዝታ ፍጹም አይዘነጋውም፡፡ ያኔ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ በስራው ላይ ረጅም ጊዜ ያጠፋ ስለነበር ልጆቹን የሚያገኝበት ጊዜ ጠዋት ላይ
ነበር፡፡
ዮሀንስ ፣ስለ አባቱ
ሲያነሳ ሩህሩህነቱ ይታወሰዋል፡፡ አንድ ልጅ በልቶ የሚጠግብ የማይመስለው ሙሉጌታ ልጆች ትምህርታቸው ላይ ልዩ ትኩረት
እንዲያደርጉ ይፈልጋል፡፡ ለትምህርት የቱንም ያህል ወጪ አውጣ ከተባለ ሙሉጌታ ጋር አልችልም የሚል መልስ አይሰጥም፡፡ ዮሀንስ
ይህን ሲያጤን አባቱ ስለ ነገ የሚያስብ አርቆ አሳቢ መሆኑን ያምናል፡፡ ልጆቹ በሙሉ በግል ተማሪ ቤት እንዲማሩ ነበር
ያደረገው፡፡
የእናት ፍቅር እና ንባብ
ሙሉጌታ
ሉሌ፣ ለእናቱ የተለየ ፍቅር ነበረው፡፡ ለእናቱ ምንም ሁን ቢባል
ይሆናል፡፡ አቅሙ በፈቀደ መጠንም እናቱን ረድቷል፡፡ ወይዘሮ ወርቅነሽ ጎሹ፣ ሙሉጌታን በጥንቃቄ እና በስስት ነበር
ያሳደጉት፡፡ ታዲያ በስተእርጅናቸው ጊዜ ህመም ያጠቃቸው ስለነበር እናቱን በማስታመም ሙሉጌታ ትልቅ አደራውን ተወጥቷል፡፡
በየሆስፒታሉ እናቱን እያዞረ የተሻለ ህክምና እንዲያገኙም ጥረት
አድርጓል፡፡ ይህም ልባዊ ርካታ የሚሰጠው ነገር ነበር፡፡
ዮሀንስ ሙሉጌታ
ከአባቱ ባህሪይ የቱን ታደንቃለህ ሲባል ለስራ ያለው ትጋት ድንቅ ይለዋል ፡፡‹‹….. ቀን መስሪያ ቤት ሲሰራ ውሎ ደግሞ ቤት
ይመጣና ቢሮ የጀመረውን ስራ ይቀጥለዋል፡፡ ምንም አይደክመውም፡፡
አንዳንድ ጊዜ እየሰራ የሚያድርበት ጊዜ አለ፡፡ መኝታ ቤት አልጋ ለማንጠፍ ስገባ ከ 5 የሚበልጡ ለመነበብ የተጀመሩ መጽሀፍትን
እናገኛለን፡፡ የሚገርመኝ ነገር አንዱ መጽሀፍ ከአንዱ አይምታታም
ወይ? ብዮ የምጠይቅበት ጊዜ አለ፡፡ እርሱ ግን አንዳቸውም አይጠፉትም፡፡ መጽሀፍት ለእርሱ እንደ አንድ ትልቅ ሀብት እንደማለት ነው፡፡ በዚህ ላይ ደግሞ አንድ ሀሳብ ሲመጣለት ባገኘው ነገር
ላይ ይጽፋል፡፡ ሶፍት ካገኘ ከአእምሮው የፈለቀውን ሀሳብ ሶፍቱ ላይ ያሰፍራል፡፡ ይህም የቆየ ልማዱ ነው፡፡ ደግሞ ከተቀመጠ
የሚጽፈው ነገር አያጣም፡፡. በአንድ በኩል እያነበበ ደግሞ በሌላ ሬድዮ ያዳምጣል፡፡ ያኔ በልጅነት ትዝ እንደሚለኝ ቤታችን
በሬድዮ ድምጽ የተሞላ ነበር››፡ ብሏል ዮሀንስ፡፡
ዮሀንስ፣ እንደ
አባቱ ጎበዝ አንባቢ እንዳልሆነ ያስባል፡፡ ነገር ግን የሙሉጌታ የሁልጊዜ ምኞቱ ልጆቹ አንባቢ እንዲሆኑ ነው፡፡ በፊት ዮሀንስ
የስነ-ጽሁፍ ዝንባሌ ነበረው፡፡ ነገር ግን በሂደት ወደ ሌላ ሙያ ገባ፡፡ ሙሉጌታ ከቤተሰብ ጋር ያለው ቁርኝት ቀላል
አይደለም፡፡ ሶፋ ላይ ሆኖ እግሩ ይታሽለታል፡፡ ከዚያ ትንሽ ከተጫወተ በኋላ ወደ መኝታ ቤት ይገባል፡፡ መኝታ ቤት ገባ ማለት
ትልቅ ስራ ሊሰራ ነው ማለት ነው፡፡ ይህንን ልማዱን የሚያውቁት የቤተሰቡ አባላት ከስራው ጋር አገናኝተውት ዘወር ይላሉ፡፡
ታዲያ ሙሉጌታ መኝታ ቤት ገብቶ ረጅም ሰአት ከሰራ በኋላ የሚተኛው ለአጭር ሰአት ነው፡፡ ወዲያው ደግሞ ስራ መግባት ስላለበት
ማልዶ ይነሳል፡፡
ውለታ መላሾች
እጃቸውን ዘረጉ
ዮሀንስ ፣ ሙሉጌታ
ሉሌ ከስራ የተሰናበተበትን ወቅት ሲያስታውስ ሙሉጌታ ራሱ ከስራ
እንደሚሰናበት ያውቅ እንደነበር ይናገራል፡፡ከሙሉጌታ በፊት በደርግ ዘመን የነበሩ የሚድያ የስራ መሪዎች ከስራቸው እንዲሰናበቱ
ተደርጎ ስለነበር ሙሉጌታም አንድ ቀን ይህም ለእኔ አይቀርም እያለ ቀኑን ይጠባበቅ ነበር፡፡
በሀምሌ 1983
ሙሉጌታ ከስራ ሲሰናበት ገቢ ሁሉ ቆመ፡፡ በጊዜው ቤተሰቡን የመመገብ ታላቅ አደራ በእርሱ ላይ የወደቀ ነበር፡፡ ሙሉጌታ በጊዜው
ፍጹም እንዳልተረበሸ ዮሀንስ ያስታውሳል፡፡
ሙሉጌታ ቀድሞ ውለታ
የዋለላቸው ሰዎች አሁን ደግሞ እርሱ ስራ ባጣበት ጊዜ ደረሱለት፡፡ በፊት ሙሉጌታ ለሰው ችግር መድረስ ፤ ሰውን ማገዝ ተክኖበት
ነበር፡፡ በ1983 የቤተሰቡ ገቢ በታጣበት ጊዜ ውለታ መላሾች
እጃቸውን ዘረጉ፡፡ አንዱ ጤፍ ሲያመጣ ሌላው ደግሞ የቤት ውስጥ መሰረታዊ ነገሮችን ያሟላል፡፡ ‹‹ ……ከበፊት ጀምሮ የቤቱን
አስቤዛ የማደርገው እኔ ነበርኩ፡፡ ምን ጎደለ? ፤ ይህ ይጨመር? ሙሉጌታ / አባቴ/ የሚያውቀው ነገር የለም፡፡ እኔ ነኝ
የጓዳው ነገር ውስጥ የምገባው፡፡ አስቤዛ ማድረግ ፤ የቤት ኪራይ፣ ውሀና መብራት መክፈል የመሳሰሉት ኃላፊነቶች የእኔ ነበሩ፡፡
በዚህ ሰአት አንዱ ዘመድ የአንዱን ወር የቤት ኪራይ ይከፍላል፡፡ አንዱ ደግሞ እህል ይሰፍራል፡፡ እናም ስራ ባጣበት ጊዜ ቤቱ
ውስጥ አንድም የጎደለ ነገር አልነበረም፡፡›› በማለት ዮሀንስ ትዝታውን ያወጋል፡፡
ምን ልንሰራ እንችላለን?
ሙሉጌታ ሉሌ
በ1983 ክረምት ላይ የስራ ስንብት ከደረሰው በኋላ ብዙም የሞራል ጉዳት አልደረሰበትም፡፡ በጊዜው የ50 አመት ጎልማሳ የነበረው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ
ሉሌ ደስታ ገና የመስራት ህዝብን የማስተማር ጉልበት አለኝ ብሎ ያምን ስለነበር ሊሰራ የሚችል ነገር እንዳለ ያምን ነበር፡፡
ከቅርብ ሰዎቹ ጋር በየጊዜው በመገናኘትና መጽሀፍን በጥልቀት በማንበብ ጊዜውን ያሳልፍ የነበረው ሙሉጌታ መንፈሰ -ጠንካራነቱን
አሳይቶ ነበር፡፡ አቶ ሙሉጌታ ብቻ ሳይሆን ቁጥራቸው 52 የሚጠጋ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የስራ መሪዎች ከስራ ተሰናብተው
ስለነበር ሁሉም በየፊናው ምን ልንሰራ እንችላለን? በሚል ቆም ብለው ማሰብ ጀምረው ነበር፡፡ ሙሉጌታም ከአሳቢዎቹ ጎራ
ይመደባል፡፡
ሙሉጌታና ሌሎች ባለሙያዎች አንድ ላይ ሆነው በ1984 ዓ.ም አጥቢያ ኮከብ የህትመትና የማስታወቂያ
ስራ ድርጅትን 15 በመሆን በማቋቋም ስራ ጀምረዋል፡፡ በዚህ ሰአት ከስራ ተሰናብተው የነበሩት ባለሙያዎች አንድ ነገር
ለሀገራቸው ሊያበረክቱ እንደሚችሉ ያመኑ ነበሩ፡፡
በወቅቱ
የነበረው የእነ ሙሉጌታ ስብስብም እውቀትን መሰረት ያደረገ እና
ያማከለ እንደነበረ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
ስብስቡን የጀመሩት
እና ሃሳቡን ያነሱት አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ፣ አቶ ወሌ ጉርሙ ነበሩ፡፡
በወቅቱም የድርጅቱ ባለአክሲዮን
የነበሩት ወሌ ጉርሙ ፤ እምሩ ወርቁ ፣ ጎሹ ሞገስ ፣ ኤሊያስ ብሩ ፣ አልማዝ ደጀኔ፤ ሙሉጌታ ሉሌ ፤ ታደሰ
ጉርሙ፤በላይ ፈለቀ ፤ ሀይሉ ወልደጻድቅ፤ ደርበው ተመስገን
ከብዙሀኑ በጥቂቱ የሚጠቀሱ አባላት ናቸው፡፡ በወቅቱም አቶ ኃይሉ ወልደፃዲቅ እንደነገሩን በአባልነት 15000
የኢትዮጵያ ብር በማዋጣት የሼር ባለድርሻ ነበሩ፡፡ ሌሎቹም የሚችሉትን ያህል በማዋጣት ጦቢያ መጽሄትን እውን ለማድረግ
ችለዋል፡፡ ጦቢያ መጽሄት በሚያዝያ 1984 የመጀመሪያ እትሟን ለአንባቢ አቀረበች፡፡
የድርጅቱ አባላትም አላማቸውን ከግቡ ለማድረስ መፅሄት ማዘጋጀት ፣
የቴሌቪዥን እና የሬዲዮ ማስታወቂያዎችን መስራት ፣ መፅሀፍ ማሳተም፣ የትርጉም ስራዎችን መስራት ጀመሩ፡፡
በወቅቱም በቢሮነት
ሲገለገሉበት የነበረው የአቶ ሙሉጌታ ሉሌ መኖሪያ ጊቢን ነበር፡፡ ቦታውም ፓስተር ጳውሎስ አካባቢ ነበር፡፡
መፅሄት የማዘጋጀት
ስራውን ከሌሎች ስራዎች በላይ በትኩረት ይሰሩ ነበር፡፡
እነዚህ በ1960ዎቹና በ1970ዎቹ በሀገሪቱ ሚድያዎች ላይ ቁልፍ ሚና
ሲወጡ የነበሩ ጠንካራ ባለሙያዎች ጦቢያን ለመጀመር በጊዜው የተፈቀደው የፕሬስ ነጻነት ህትመት እንዲያወጡ ይፈቅድላቸው ስለነበር
አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው ፈቃድ ሰጪው አካል ጋር መሄዳቸው አልቀረም፡፡ ፍቃድ አውጥተው የሳንሱር ህጉ እና የማሳተም ሂደቱን ለማስጀመር አቶ ዲማ
ነገዎ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ኃላፊ ጋር በመሄድ የማሳተም እና ስራ የመጀመር ፍቃዱን ማግኘት ችለዋል፡፡ በጊዜው የመጀመሪያዋን
የመጽሄቱን የጽሁፍ ቅንብር የሰራው ብራና ኤሌክትሮ አሳታሚ ነበር፡፡
አቶ ሙሉጌታና ጓደኞቹ የሳንሱር ሂደቱንም አልፈው ለመጀመሪያ ጊዜ
5000 መፅሄቶችን ጦቢያ በሚል ስያሜ አሳተሙ፡፡ ነገር ግን ገበያ ላይ በብዛት መሸጥ አልቻለም፡፡
በዚህ ጊዜም
የነበረው ፈተና አንድ የወቅቱን መንግስት የሚደግፍ ጋዜጠኛ
በጦቢያ ላይ የስም ማጥፋት ዘመቻ መጀመሩ ነበር፡፡ ጋዜጠኛውም
‹‹…ጦቢያ ማለት ጦሩ ቢዋጋ ያሸንፍ ነበረ ማለት ነው
ብሎ የራሱን ትርጉም ሰጠ፡፡ እርሱ ለክፉ ያሰበው ሴራ በተቃራኒው
ሆነ፡፡ ይህን ወሬ በማውራቱ የጦቢያ መጽሄት ህትመት ብዙ አንባቢያንን ማግኘት ቻለ፡፡
በዚህም ምክንያት
ሁለተኛ ህትመት በቶሎ እንዲታተም ተደርጎ በቶሎ ለገበያ ቀረበ፡፡
በወቅቱም የጦቢያ መጽሄት ዳግም ህትመትን አስመልክቶ የ30 ሰከንድ ማስታወቂያ በሬድዮ ተላለፈ፡፡ በዚህም ምክንያት ብዙ አንባቢያንን መሳብ ቻሉ፡፡ በሁለተኛ
ህትመቱም 60000/ስልሳ ሺህ ቅጂ ታትሞ በመላው ኢትዮጵያ መሰራጨት ቻለ፡፡
በወቅቱም የሽያጭ
ሃላፊ የነበሩት ኃይሉ ወልደፃዲቅ ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ እንደነገሩት በወቅቱ የነበራቸው የሽያጭ ገቢም 1 ሚሊዬን ገደማ ደርሶ
ነበር፡፡ የወቅቱ የመፅሄቱ የመሸጫ ዋጋም 3 ብር ብቻ ነበር
በመቀጠልም
የማስታወቂያ ስራውን የመስራቱን ሂደት ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫቸው አድርገው ከ አክ ፓክ የማስታወቂያ ድርጅት ጋር በመሆን
የማስታወቂያ ስራዎችን በስፋት መስራት ጀመሩ፡፡
በአምስት ኪሎ
አካባቢ የራሳቸውን ስቱዲዮ ማቋቋም ቻሉ፡፡ በዚህም ብዙ ማስታወቂያዎችን መስራት እና ማስተላለፍ ጀመሩ፡፡
በተጨማሪነትም
፣ዶክመንተሪዎችን መስራት ጀምረው ከፍተኛ ተቀባይነትን ማግኘት ችለው ነበር፡፡ ከነዚህ ውስጥ ‹‹እምቡጥ ፅጌረዳ››
የሚለው ዶክመንተሪ ተጠቃሽ መሆን የሚችል ነው፡፡
በተጨማሪነትም
በአዲስ አበባ በሚገኙ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚሰራጭ ኩኩሉ መፅሄት በስፋት ተዘጋጅቶ በ90000 ብር በጀት መታተም
ጀመረ፡፡
ይህ ለእነ ሙሉጌታ
ሉሌ ሞራል የሚገነባ ነገር ነበር፡፡ የመጀመሪያዋ የጦቢያ የፊት ሽፋን የፕሬስ ነጻነት ለኢትዮጵያ የሚል እሳቤን የያዘች
ነበረች፡፡ በመጀመሪያዋ የጦቢያ እትም ሙሉጌታ ሉሌ ዮሀንስ ሙሉጌታ በሚል የብእር ስም ምን ነካን! የሚል አንድ መጣጥፍ አቅርቦ
ነበር፡፡ ይህ መጣጥፍ ብዙ ሀሳቦችን የሚነካካ ሲሆን በተለይ ሙሉጌታ የሚያነባቸውን መጽሀፎች እየጠቃቀሰ እንዲሁም ቃለ-መጠይቅ
ያደረገላቸውን ሰዎች እያነሳሳ በዛ የተባ ብእሩ ሀሳቡን ኩልል እያደረገ ያወርዳል፡፡ ሙሉጌታ በዚህ ጽሁፉ ወረድ ብሎ እንዲህ
ይላል‹‹……ስለ ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ የተጻፉት መጽሀፍት በአብዛኛው በውጭ ደራሲያን ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ መጽሀፍት የህዝቡን
የአንድነት ስሜት፤የእንግዳ ተቀባይነት ሁኔታ በክፉ ቀን ህዝቡ የብሄረሰብና የእምነት ልዩነት ሳይኖርበት የሚያሳየው አንድነትና
ለአገር መቆርቆር ዛሬ ምን ያህል እንጥፍጣፊ ቀርቶታል? አብረን የምንጠይቀው ነው፡፡›› ሲል ሙሉጌታ ሉሌ በመጀመሪያዋ የጦቢያ
እትም ላይ መጣጥፉን አቅርቦ ነበር፡፡
አቶ ደርበው ተመስገን ከጦቢያ ባለአክሲዮኖች አንዱ ነበሩ፡፡ አቶ ሙሉጌታ
ጋር ትውውቃቸው በ1970ዎቹ አጋማሽ ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምሪያ ሃላፊ ሳለ ነበር፡፡ አቶ ደርበው ተመስገን፣
የበለጠ ከሙሉጌታ ጋር ትውውቃቸው የጠነከረው ጦቢያ ከተጀመረች በኋላ ነበር፡፡ አቶ ደርበው የሙሉጌታን ችሎታ ሲገልጹ ቢሰራ ቢሰራ የማይደክመው ነው ሲሉ
ይገልጹታል፡፡ በተለይ ርእሰ-አንቀጽ አቶ ደርበውና ሙሉጌታ በየተራ እየገቡ ይጽፉ ነበር፡፡ አቶ ደርበው ተመስገን፣ ሙሉጌታን
በልዩ ምልከታውና በበሳል ጸሀፊነቱ ያደንቁታል፡፡ ተገቢውን ምንጭ በመጥቀስ ምርጥ መጣጥፍ ሲጽፍ አንባቢን ያጠግባል ሲሉም ነጥሮ
የወጣ ጸሀፊ መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡ ‹‹ እኔ ሙሉጌታ የሚገርመኝ
አንዴ ቁጭ ብሎ ከጻፈ ቶሎ ይጨርሳል፡፡ አንድ ስህተት ልፈልግ ቢባል አይገኝም፡፡ የአረፍተ -ነገር አወቃቀሩ እራሱ የተደራጀ
ነው፡፡ እኛ አልፎ አልፎ ለማረም ብንፈልግ እንኳን አዳጋች
ይሆንብናል፡፡ አሜሪካን እስከሚሄድ ድረስ ለ5 አመታት በ2ቱ የብእር ስሞቹ በርትቶ ይጽፍ ነበር፡፡ አሜሪካን ሀገር ከሄደ በኋላ
ደግሞ አንዳንዴ በፋክስ ከዚያ ደግሞ በኢንተርኔት ጽሁፉን ይልክ ነበር፡፡ ሙሉጌታ ለዛ ያለው ቀልዱ ሁል ጊዜም ይስበን ነበር፡፡
በጣም የምናከብረው ወንድማችን ነበር ›› ሲሉ አቶ ደርበው ሀሳባቸውን አጠናቀዋል፡፡
አቶ አጥናፍሰገድ
ይልማም ሙሉጌታን ሲያውቁት 50 አመት በላይ ይሆናል፡፡ ሙሉጌታ ዜና ላይ የማነፍነፍ ችሎታው የሚደንቅ እንደነበር አቶ አጥናፍ
መስክረዋል፡፡
ትህትናው ትሁት ያደርግሀል
ጦቢያ ሲጀመር የመጽሄቱ ዋና አዘጋጅ ሙሉጌታ ሉሌ ሲሆን ምክትል ዋና
አዘጋጅ ደግሞ አቶ እምሩ ወርቁ ነበሩ፡፡ በዋናነት ሙሉጌታ ውጭ ሀገር እስከሄደበት ቀን ድረስ ከ1984-1988 ለ 5 አመታት
ጸጋዬ ገብረመድህን አርአያ በሚለው ስሙና በሌሎቹም ጽሁፎችን በመጻፍ ከአንባቢ ጋር ትውውቅ ፈጥሯል፡፡ በአሁኑ ሰአት ካናዳ
የሚገኘው ጋዜጠኛ አንተነህ መርእድ እምሩ ፤ ሙሉጌታ ሉሌን የሚያውቀው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የስራ መሪ ሳለ ነበር፡፡ ያኔ
አቶ አንተነህ በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ድርጅት ያገለግል ነበር፡፡ ጊዜውም 1981 ነበር፡፡ በ1984 ጦቢያ በተመሰረተች
ሰሞን የተለያዩ መጣጥፎችን በማቅረብ ከአቶ ሙሉጌታ ጋር መተዋወቁን ይናገራል፡፡ በ1986 ደግሞ የጦቢያ ዝግጅት ክፍልን
ሲቀላቀል ሙሉጌታ ሉሌን በቅርበት የማወቅ እድሉን አገኘ፡፡
አቶ አንተነህ ትዝታውን ሲያወጋ ‹‹…..ጦቢያን ስቀላቀል አቶ ሙሉጌታን
በቅርቡ ለማወቅ እረድቶኛል። በመሆኑም አቶ ሙሉጌታ አለቃዬ፣ አስተማሪዬ፣ የእስር ባልደረባዬ፣ ታላቅ ወንድምና መከታ አድርጌ
የማየው በመሆኑ ስለእሱ ዘርዝሬ ለማስረዳት ቦታ እና ጊዜ የሚበቃኝ አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን ጠቅለል ባለ መልኩ አቶ ሙሉጌታን
ለመግለጽ ከሁለመናው በስብዕናውና በሙያው ላይ ብቻ ባተኩር የተሻለ ይሆናል።›› ሲል ካናዳ ሆኖ ሀሳቡን ለግሶናል፡፡
በአቶ አንተነህ
እይታ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ መሬት የረገጠ ስብዕና ያለው ሰው ነው። በሙያው፣ በማህበራዊ ህይወቱ፣
በዕድሜው፣ በዕውቀቱ ከፍ ያለ ደረጃ ላይ ያለ ሰው ሆኖ ሁሉንም ሰው ከልጅ እስከአዋቂ፣ ካልተማረው እስከተጠበበው፣ ከሃብታም
እስከድሃ፣ ከባለስልጣን እስከ ተራሰው በትህትና ቀርቦ የሚያዳምጥ፣ የሚያነጋግርና የሚረዳ፤ በችግራቸውም ቀድሞ የሚገኝ ሰው
ነው። አቶ አንተነህ ስለ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሲያስታውስ እነዚያ ምሁራዊ እይታን የተላበሱ ጽሁፎቹ ይታወሱታል፡፡ አቶ አንተነህ
እንደሚያስታውሰው ሙሉጌታ ጽሁፍ ሲጽፍ ፍጥነት አለው፡፡ ሁልጊዜም ደግሞ ሰዎች ሲናገሩ ፤ መጽሀፍ ሲያነብ ፤ ሬድዮ ሲያዳምጥ
ማስታወሻ ስለሚይዝ ሀሳብ አይቸግረውም፡፡ ለሚናገረው ሀሳብ ማዳበሪያ ከፈለገም ያነበባቸው መጽሀፎችን ስለማይረሳ ጠቃሚ
ምሳሌዎችን እና ጥቅሶችን በተዋበ መልኩ ጽሁፉ ውስጥ ያካትታቸዋል፡፡
አቶ ሙሉጌታ ሉሌ
ጽሁፉ ላይ ለሚሰጠው ሙያዊ አስተያየት በሩ ክፍት ነው፡፡ አቶ አንተነህ
ስለ ሙሉጌታ ጽሁፎች ሲያወሳ ይህን አጫወተን‹‹…መቼም ጦቢያ ላይ የጸጋዬ ገብረመድህን አርአያ ጽሁፍ ተጠባቂ ነው፡፡ እና ሙሉጌታ ሲጽፍ ማብቂያ የለውም፡፡ በኤፎር
ወረቀት እስከ 20 ገጽ አነስ ካለ ደግሞ 16 ገጽ ይጽፍና በቃህ ብለን የጻፈውን ተረክበን እናስተይበዋለን፡፡ ከተተየበ በኋላ
አንዳንድ እርማቶችን አድርገን እንሰጠዋለን፡፡ እርሱ ደግሞ እኛ የጨመርነውን ይዞ ዳግም ተጨማሪ ማሻሻያ አክሎበት ምርጥ ጽሁፍ
ይዞ ብቅ ይላል፡፡ ይህ የሙሉጌታ ሉሌ ድንቅ ብቃቱ ነው፡፡›› ሲል አቶ አንተነህ የሙሉጌታ ጽሁፎች አንባቢ ዘንድ የሚደርሱበትን
መንገድ አመላክቷል፡፡
አቶ አንተነህ አሁንም ሃሳቡን ቀጠለ ‹‹….አቶ ሙሉጌታ ጋር በእግር
መንገድ ከጀመርክ ከፈልግከው ቦታ በሰዓቱ መድረስ አትችልም። የማያቆመው፣ የማያነጋግረው፣ የማይቀልደው ሰው የለም። ከቅድስት ማርያም የጦቢያ ቢሮ እስከፒያሳ በእግር ጉዞ ብዙ ሰዓት
ሊወስድብህ ስለሚችል ወይ ጋሽሙሉጌታን ተሰናብተህ ተለየው ያለዚያም ቻለው። ሁሉም ሰው እኩል ዋጋ አለው ለጋሽ ሙሉጌታ።
ትህትናው የበለጠ ትሁት እንድትሆን ያስገድድሃል። ቢሮው የሚመጣ የሰው አይነት ብዙ ነው። ከትልልቅ ሰው እስከ ጎዳና የሚተዳደር
ተራ ግለሰብ ይመጣል። በግል ንጽህናውና በአለባበሱ ጋሽሙሉጌታን
የሚያህል ጠንቃቃና ጽዱ አላየሁም።›› በማለት አጫውቶናል፡፡
አቶ ሙሉጌታን ልዩ
የሚያደርገው ከሃያ ዓመት በፊት እንኳ ያነበበውን ነገር ሳያዛባ መጽሃፍ ሳይገልጥ አስታውሶ በአስረጂነት መጻፍ መቻሉ ነው።
በኢትዮጵያ ታሪክ በተጻፈውም ባልተጻፈውም ላይ ያለው እውቀቱ ሰፊ ነበር። የእርሱን ጽሁፍ እንዲያርሙ፣ ሃሳብ እንዲሰጡ፣
እንዲተቹ ያለተአብዮ የሚፈልግና ጊዜ ካላስገደደው ከእጁ ካልተነጠቀ ደጋግሞ ኤዲት ባደረገው ቁጥር ስራው ላይ የበለጠ ውበት
የሚሰጥ ትጉሀ ሰው ነበር።
አቶ ሙሉጌታ በጦቢያ
መጽሄት ምክንያት ተደጋጋሚ እስር ገጥሞታል፡፡ በተለይ አቶ
አንተነህ ከጋዜጠኛ ሙሉጌታ ጋር በ1987 ለ1 ወር መታሰሩን ያስታውሳል፡፡ ያኔ በእድሜ ወጣት የሆኑ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞች
በወህኒ ስለነበሩ ጋሽ ሙሉጌታን ቀርበው ሲያነጋግሩት በጣም ቀለል የሚልና በትህትና የተሞላ አንባቢ ሰው መሆኑን
መስክረዋል፡፡ ያኔ ሙሉጌታ ስኳርና የልብ በሽታ ስለነበረበት ምንም ማድረግ ስለማይችል ለወህኒ ተዳረገ፡፡ ሙሉጌታ ብቻውን ሳይሆን ሌሎች የጦቢያ ባልደረቦችም እስር ይገጥማቸው
ነበር፡፡ በዚህ ሰአት ታዲያ ለታሳሪዎች ዋስ በመፈለግ ፣ እንዲሁም የታሳሪዎችን ቤተሰቦች በማጽናናት ሙሉጌታ የአባትነቱን ሚና
ይወጣ ነበር፡፡ አቶ አንተነህ በዚህ ጉዳይ ሀሳቡን ሲያብራራ‹‹ …. ጋሽ ሙሉጌታ እኔ ታስሬ በነበረበት ሰአት የአንተነህ
መርእድን ባለቤት ጠይቋት እያለ አጋርነቱን ያሳይ ነበር፡፡ እኔ ከእስር ከወጣሁ በኋላ ይህን ታላቅ በጎነት ማድረጉን ሰዎች
ነገሩኝ፡፡ እንዲህ አይነት ሰው በቀላሉ አይገኝም፡፡ አቶ ሙሉጌታ ከሀገር ቤት ከወጣ በኋላ እስር በሚገጥም ሰአት ትልቅ ክፍተት
መፈጠሩን ሁላችንም አስተውለናል›› ሲል አቶ አንተነህ ነግሮናል፡፡
ቪዛ ሰጡት
አቶ ሙሉጌታ ሉሌ
በጦቢያ መጽሄት ላይ ለ 4 አመት ከ8ወር ከሰራ በኋላ ወደ ባህርማዶ በተደረገለት ግብዣ ሲያቀና ጊዜውም ህዳር 1989 ነበር፡፡
ያን እለት በኮሞሮስ ደሴት የደረሰ የአውሮፕላን አደጋ ነበር፡፡
ታዲያ እነ ዮሀንስ ሙሉጌታ እና ሁሉም ቤተሰቦች ተደናግጠው ነበር፡፡ እርግጥ ሙሉጌታ ያኔ በሳኡዲ አየር መንገድ ነበር ጉዞውን
ያደረገው፡፡ቢሆንም ቤተሰቡ እንዲሁ ሰግቶ ተደናግጦ እንደነበር ልጁ
ዮሀንስ ሙሉጌታ አጫውቶናል፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ ወደ
ባህርማዶ ሲያቀና ለ1 ወር እንደሚቆይ ነበር፡፡ በጊዜው ግብዣ
ያደረገለት ዮሀንስ አበበ የሚባል ጓደኛው ነበር፡፡ በሂደት ግን የቅርብ ዘመዶች ጋር በማቅናት ኑሮውን በምድረ- አሜሪካ
መመስረት ችሏል፡፡ አቶ ሙሉጌታ ያኔ ወደ አሜሪካ ለመሄድ
በተነሳበት ጊዜ ቪዛ ለማግኘት ወደ አሜሪካ ኤምባሲ በገባ እለት ቪዛ ሊሰጠው እንደማይችል እርግጠኛ ነበር፡፡ ነገር ግን ቪዛውን
ሲያገኝ ለእነ ዮሀንስ በመገረም ተሞልቶ ነበር ያጫወታቸው፡፡ሙሉጌታ ሉሌ አሜሪካ ከማቅናቱ በፊት በርካታ ክሶች ተመስርተውበት
ነበር፡፡ ልጁ ዮሀንስ ፣አንዳንድ ጊዜ ዋስ የሚሆንበት ጊዜ ነበር፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ የዮሀንስ ጓደኞች ዋስ ይሆኑት ነበር፡፡
ስለሆነም በአንድ በኩል የአቶ ሙሉጌታ ወደ ባህር ማዶ ማቅናት በጎ ነገር ነው የሚሉ ነበሩ ፡፡ ሙሉጌታ ደግሞ ከሀገሩ ርቆ
የመኖር ምንም አይነት ፍላጎት አልነበረውም፡፡ ልጁ ዮሀንስ እንደሚያስታውሰው ሙሉጌታ ከእስር ሲወጣም ሆነ ወደ እስር ሲገባ
እንዲህ አደረጉኝ እንዲህ ደረሰብኝ ብሎ የማውራት እና ምሬት የማሰማት ልምድ አልነበረውም፡፡ ምንም እንዳልተደረገ በማሰብ ሰውም እንዳይጨነቅ በማሰብ ነበር የጋዜጠኝነቱንና የተንታኝነቱን ስራ
ሲያከናውን የነበረው፡፡
ሙሉጌታ፣ አሜሪካ
ከሄደ በኋላ የቅርብ ሰዎቹ መልካም አቀባበል አድርገውለታል፡፡ ባህር ማዶ ከደረሰ በኋላ በአንድ መስሪያ ቤት ውስጥ
የትራንስፖርት ክፍል ሀላፊ ሆኖ አገልግሏል፡፡ አቶ ሙሉጌታ
ከጦቢያ መስራቾች አንዱ ስለነበር በየአመቱ የትርፍ ክፍያ ሲፈጸም ልጁ ዮሀንስ ሙሉ ውክልና ስለነበረው ሙሉጌታ በሚፈለገው መንገድ ገንዘቡ ይወጣ ነበር፡፡ ነገር ግን ብሩ ወደ
ሙሉጌታ ኪስ የሚገባበት አንድም ጊዜ እንዳልነበር ልጁ ዮሀንስ ያስታውሳል፡፡ ጋዜጠኛ ሙሉጌታም ሆነ ሌሎቹ የጦቢያ መስራቾች ከጦቢያ ትርፍ ለማግኘት ሳይሆን ሀገር
ለማገልገል የሚል ራእይ በመሰነቃቸው ነበር ወደ ስራው የገቡት፡፡ ሙሉጌታም ጽሁፍ ሲጽፍም ሆነ የሚድያ ስራን ሲያከናውን ገንዘብ
የማካበት ህልም ኖሮት አያውቅም፡፡
ኢትዮጵያውያንን የማሰባሰብ ክህሎት የታደለ
ዶክተር ገብርዬ
ወልደሩፋኤል፣ በአሜሪካን ሀገር የታወቁ ሀኪም ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ወይዘሮ ትእግስት ንጋቱ ደግሞ የሙሉጌታ የአክስት ልጅ
ናቸው፡፡ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ ወደ አሜሪካ ሲያቀና በመጀመሪያዎቹ ቀናት ያረፈው እነ ወይዘሮ ትእግስት ጋር ነበር፡፡ ዶክተር
ገብርዬ እንደሚያስታውሱት ሙሉጌታ አሜሪካ እንደመጣ የልብ ቀዶ ጥገና ማድረጉን ይናገራሉ፡፡ ያኔ ሙሉጌታ በጆን ሆፕኪንስ
ሆስፒታል ህክምና ወስዶ ነበር፡፡ ከዚያም የልብ ቀዶ ጥገና አድርጎ ለተወሰኑ ጊዜያት ዶክተር ገብርዬ ቤት እረፍት አደረገ፡፡
ከዚያ በኋላ ነው ከህመሙ ሲያገግም ስራ ወደመፈለግ የሄደው፡፡
ዶክተር ገብርዬ እንዳጫወቱን ሙሉጌታ ዘመድ ወዳድና ኢትዮጵያውያንን የማሰባሰብ ልዩ ክህሎት የታደለ በጎ ሰብእና
የተላበሰ ሰው መሆኑን ይመሰክራሉ፡፡
ዶክተር ገብርዬ
ሙሉጌታን ሲገልጹት ‹‹ ….. በጣም አዋቂ ከሚባሉት ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በሚጽፋቸው ጽሁፎች ሁልጊዜም እንዳስደመመን
ነው፡፡በስነ-ምግባርም የሚመሰገን ታላቅ ሰው ነው፡፡ሰው መርዳት ይወዳል፡፡ በአሜሪካ ያለ ዘመድ አዝማድ ሁሉ እርሱን ነው እንደ
ታላቅ ወንድም የሚቆጥረው፡፡ እኔ በሙያዮ ሀኪም ስለሆንኩ የልብ ህክምናውን በሚያደርግበት ሰአት በቅርበት እከታተለው
ነበር፡፡እናም የጽሁፍ ስራዎችን ሲሰራ አየው ነበር፡፡ አይደክመውም ፡፡ በአንድ በኩል አሜሪካ ሀገር ቀን ይሰራል ማታ ሲሆን
ደግሞ ጊዜ ወስዶ ይጽፋል፡፡ እንግዲህ በአመት ለጦቢያ 20 ጽሁፍ ቢልክ ጠቅላላ አሜሪካ ሆኖ ከ150 በላይ መጣጥፎችን
ለአንባቢያን አበርክቷል፡፡ ይህ ድንቅ ክህሎቱን የሚመሰክር ነው፡፡
ሙሉጌታ ደግሞ ሲጽፍ መሰረዝ እና መደለዝ የሚባል ነገር ፍጹም አያውቅም፡፡ ታዲያ እኔ የእርሱን ጽሁፍ ሳየው በጣም
እገረም ነበር፡፡ እንዴት አይነት ድንቅ ችሎታ ይሆን ያለው? ጽሁፎቹም ለኢትዮጵያ አንድነት እንድንተጋ የሚያደርጉ ነበሩ፡፡ ከሙሉጌታ ጋር ሁልጊዜም ስለ
ሀገር እናወራ ነበር፡፡ እናም ኢትዮጵያ አግኝታ መልሳ ካጣቻቸው ድንቅ ስጦታዎች አንዱ ሙሉጌታ ይመስለኛል ›› ሲሉ ዶክተር
ገብርዬ አሜሪካን ሀገር ሆነው ትዝታቸውን አጫውተውናል፡፡
ገንዘብ ሳይከፈለው ማገልገል
ሲሳይ አጌና የኢሳት
ባልደረባና ቀደም ሲል ኢትኦጵ የተሰኘውን ጋዜጣ ያሳትም የነበረ በሳል ጋዜጠኛ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት በአሜሪካ ሀገር የሚገኘው
ሲሳይ አቶ ሙሉጌታን ሉሌን ገና ጦቢያ ሲመሰረት ጀምሮ በተለይ በሚጽፏቸው ጽሁፎች በሚገባ ያውቃቸው ነበር፡፡ ሲሳይ አቶ
ሙሉጌታን በጥልቅ ትንታኔ አሰጣጣቸው እጅግ አድርጎ
ያደንቃቸዋል፡፡ በተለይ ሲሳይ ነጻ ጋዜጣ ላይ ይሰራ በነበረበት ጊዜ አቶ ሙሉጌታ የኢትዮጵያ ነጻ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት
ስለነበር በቅርበት አቶ ሙሉጌታን የማወቅ እድሉን እንዳገኘ ያስረዳል፡፡
ሲሳይ አጌና፣
በስደት ወደ አሜሪካ ካቀና በኋላ ኢሳትን ተቀላቅሎ ካገኛቸው ሰዎች መካከል አንዱ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ
አንዱ ነበር፡፡በዚህ አጋጣሚ ሲሳይ ከሙሉጌታ ጋር ይበልጥ የመተዋወቅ እድሉን አገኘ፡፡ አቶ ሙሉጌታ ሲሳይ እንደተመለከተው
በኢትዮጵያ ጉዳይ ከሚሰራ ማንኛውም ድርጅት ጋር ይተባበራል፡፡ ኢሳት ሲመሰረትም በትርፍ ጊዜው አንዳችም ገንዘብ ሳይከፈለው
ያገለግል ነበር፡፡ በተጨማሪም፣ ደግሞ አሜሪካና አውስትራሊያ ለሚታተሙ የህትመት ውጤቶች ጽሁፎችን በማበርከት ሚናውን ያለ
አንዳች ስስት ይወጣ ነበር፡፡
ሲሳይ እንዲህ
ይላል‹‹…. አቶ ሙሉጌታ እስከመጨረሻው ህልፈታቸው ድረስ ሲተጉ ነበር፡፡ እንደእሁድ ህይወታቸው ሊያልፍ አርብ እለት ሲጽፉ
ነበር፡፡ እኒህ ሰው አብሬያቸው ስሰራ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር በሁሉም ጉዳይ እውቀት ያላቸው መሆኑን ነው፡፡ በታሪክ ፤
በፖለቲካ ትንተና የእርሳቸውን ያህል የሰራ ቢኖር ምናልባት በጣት ቢቆጠር ነው፡፡ አቶ ሙሉጌታ መጽሀፍ ያነባሉ፡፡ የኢትዮጵያንም
ጉዳይ በቅርበት ይከታተላሉ፡፡ በእውቀት ላይ የተመሰረት አስተያየት ለመስጠት ያስቻላቸውም ይህ ቅርበታቸው ነው፡፡ ›› በማለት
ሲሳይ የአቶ ሙሉጌታን ክህሎት በማድነቅ ሀሳቡን ሰጥቶናል፡፡ ክፍል 3እና የመጨረሻው ይቀጥላል፡፡
ግፍን አይቶ
የማይቀበለው ሙሉጌታ
አቶ አያልነህ እጅጉ፣ ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌን የሚያውቁት ከ 48 አመት
በፊት ነው፡፡ በተለይ በስደት ላይ በነበሩበት ወቅት ሁለቱ
ጓደኛሞች በየቀኑ ይደዋወሉ ነበር፡፡ አቶ አያልነህ እጅጉ፣ በአንድ የሰርግ ስነ-ስርአት ላይ ነበር ሙሉጌታን የማወቅ
እድሉን ያገኙት፡፡ከ1965 ግድም አንስቶ አቶ አያልነህ እጅጉ
ሙሉጌታን ሲያውቁት በብስራተ ወንጌል ሬድዮ ላይ ይሰራ ነበር፡፡ የበለጠ ደግሞ ሁለቱ ቅርርባቸው እየጠነከረ የመጣው ሙሉጌታ
የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት የስራ መሪ ሳለ ከ1975 አ.ም አንስቶ ነበር፡፡ያኔ በየቀኑ ይገናኙ ነበር፡፡ አቶ አያልነህ ሙሉጌታን እንደመምህር፤ እንደ ጓደኛና አባት ይቆጥሩታል፡፡
አቶ አያልነህ እጅጉ ስለ ሙሉጌታ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ : ‹‹
ለሚደርስብኝ ችግር ሁሉ ቀድሞ የሚደርሰው ሙሉጌታ ነው፡፡ ለእኔም
የቅርቤ ሰው ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ሲሰራ ጠዋት ሻይ ላይ የሚያገኛቸው ሰዎች ነበሩ፡፡ እና እኔንም በዛ ስብስብ
ውስጥ እንድገባ ያበረታታኝ ነበር፡፡ መረጃ እና ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ለማወቅ ከፈለግህ ና እኛ ጋር ይለኝ እንደነበር
አልዘነጋውም፡፡ ያኔ የሙሉጌታ አብዛኛው የጨዋታው ርእስ ስለ ሀገር ነው፡፡ እጅግ በርካታ ሰዎች ቢሮው ይደውሉለታል፡፡ በጸሀፊዋ
በኩልም ብዙ መልእክቶች ይመጡለት ነበር፡፡ ሙሉጌታ፣ ለራሱ ሳይሆን ለሀገሩ የሚኖር ሰው ነው፡፡ ብዙውን ጊዜ የሚደርሱ
አስተዳደራዊ በደሎች ያንገበግቡታል፡፡ ሊፈቱ የሚችሉበትን ብልሀት ይቀይሳል፡፡ ለእኔ ብሎ ሀብት ለማካበት አንዳችም ቀን አስቦ
አያውቅም፡፡አንዱ ትልቁ የሙሉጌታ ህልም የኢትዮጵያ አንድነት ተጠብቆ መቆየት አለበት የሚል ነው፡፡ በዚህ ላይ አንድም ቀን
ሀሳቡ ተቀይሮ አያውቅም፡፡ በነገራችን ላይ ጋሽ ሙሉጌታ ጋዜጠኛ እና የፖለቲካ ተንታኝ ብቻ ሳይሆን የደህንነት እውቀቱ ራሱ
ይደንቀኝ ነበር፡፡ ትዝ የሚለኝ በሱማሌ የድንበር ጉዳይ ላይ ሚና ከነበራቸው ሰዎች አንዱ ነበር፡፡ በሶማሌ ጉዳይ ማስታወቂያ
ሚኒስቴርን እየወከለ የሚገኝ ሰው ስለነበር እውቀቱን ያለስስት በማካፈልና ከሌሎችም በመቀበል ለሀገሩ በትጋት የሰራ ጠንካራ
ባለሙያ ነው፡፡ ሙሉጌታ፣ ለኢትዮጵያ የሰሩ ሰዎችን ሰብእና ጠንቅቆ የሚያውቅ ለሀገር የከፈሉትንም መስዋእትነት የተረዳ ታላቅ
ሰው ነው፡፡በእኔና በሙሉጌታ መካከል ከ15 አመት በላይ ልዩነት አለ፡፡ እንደ ታላቅ ወንድም ነው የምቆጥረው፡፡ ከእርሱ ጋር
መሆን ፈታ ያደርገኛል፡፡ ደግሞ ሚሊተሪ ውስጥ ያሉ ሰዎች የቅርብ
ሰዎቹ ናቸው፡፡ በቀላሉ ሰውን የማቅረብ ባህሪይ ስለነበረው ብዙዎቹ ይወዱት ነበር፡፡ ከመኮንን እስከ ጀነራል ድረስ የሙሉጌታ
ወዳጆች ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ታዲያ ስለውትድርና እነርሱ ከሚያውቁት በላይ ያስረዳቸው ነበር፡፡ይህም ሁለገብ የሆነ የእውቀት
አድማሱን ያሳየናል፡፡ ቀልድ ሲቀልድ ይችልበታል፡፡ ግን ቀልዶ ብቻ አይቀርም ፡፡ ወዲያውኑ ወደ ቁምነገሩ ይገባና ስለ ታሪክ
ፖለቲካ ማውሳቱን ይቀጥላል፡፡አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ሆደ- ቡቡ ይሆናል፡፡ በሰው ልጅ ላይ የሚደርስን ግፍና መከራ አይቶ
አያልፍም፡፡ ከልብ ያዝናል፡፡›› ሲሉ አቶ አያልነህ ነግረውናል፡፡
አቶ አያልነህ
እንደሚያስታውሱት፣ ሙሉጌታ ለልጆቹ ትልቅ ፍቅር አለው፡፡ ተንከባክቦም ነው ያሳደጋቸው፡፡ በተለይ ለልጅ ልጆቹ ስም የሚያወጣው
እርሱ ነበር፡፡ለ19 አመታት ልጆቹንም ሆነ የልጅ ልጆቹን የማየት እድል ስላልነበረው ስም የማውጣቱን ተግባር በሚገባ ተወጥቶ
ነበር፡፡ የኪስ ቦርሳው በሙሉ በልጅ ልጆቹ ፎቶግራፍ የተሞላ ነበር፡፡
ሙሉጌታ ለሰው ነው የኖረው
ወይዘሮ ስርጉት
ገብረእግዚአብሄር የሙሉጌታ ሉሌ የቀድሞ ባለቤትናቸው፡፡ ሁለቱ ትውውቃቸው በአንጋፋው ጋዜጠኛ እና ደራሲ በጳውሎስ ኞኞ መኖሪያ
ቤት ነበር፡፡ ወይዘሮ ስርጉት የጋሽ ጳውሎስ የቅርብ ዘመድ ነበሩና
በጳውሎስ ቤት የማህበር ድግስ ተደርጎ እዚያ ይታደማሉ፡፡በዚያን ጊዜ ነበር አቶ ሙሉጌታ ወይዘሪት ስርጉትን
ያያት፡፡ሙሉጌታ ሉሌ ና ጳውሎስ ኞኞ ደግሞ የወንድም ያህል የሚቀራረቡ ሰዎች ነበሩ፡፡በዚያ አጋጣሚ ትውውቁ ተጀመረ፡፡
ደብረዘይት በተደረገ ጉዞም ላይ ለትዳር እንደሚፈልጋት አቶ ሙሉጌታ ጠየቀ፡፡ጊዜውም በ1970 መሆኑ ነው፡፡በቤተሰብ ሽምግልና
ተልኮ ጋብቻ ተመሰረተ፡፡ ሚዚዮች የነበሩት አቶ መርስኤሀዘን አበበ ፤ አቶ ማእረጉ በዛብህ፤ ፕሮፌሰር ንጉሴ አየለ እንዲሁም
አቶ አጥናፍሰገድ ይልማ ይነሳሉ፡፡
ወይዘሮ ስርጉት
ባለቤታቸውን ሲገልጹ:‹‹…. በጣም ደግ ነው፡፡ እንዲህ ነው የምለው ቃላት የለኝም፡፡ ሁልጊዜም መልካም አሳቢ ነው፡፡ ኤዶም
ከዚያ ተወለደች፡፡ ኤዶም በመልክም በባህሪም ሙሉጌታ ማለት ነች፡፡ ሙሉጌታ ለሰው ነው የኖረው፡፡ ኤዶምም ደግነትን ከአባቷ
የወረሰች ይመስለኛል፡፡ ሙሉጌታ መጻፍ ይወዳል፡፡ ሌሊቱን ሁሉ
ሲያነብና ሲጽፍ እንቅልፍ ሳይወስደው የሚነጋበት ጊዜ ነበር፡፡ሲያመሽ ደግሞ ቡና ይጠጣል፡፡መጀመሪያ አካባቢ ገና ልጅ ስለነበርኩ
ይህ ትጋቱ ያስገርመኝ ነበር፡፡ የገብስ ቆሎ አጠገቡ ይቀመጥለትና እርሷን እየቆረጠመ ንባቡን ያካሂድ ነበር፡፡ለሙሉጌታ ሰው ሁሉ
እኩል ነው፡፡ ደሀ ሀብታም አይልም፡፡ ሲያወራኝ ስሜቴን ጠብቆ ያደምጠኛል፡፡ በመሃላችን 12 አመት ልዩነት አለ፡፡ እና የተጋባን ሰሞን የሚድያ ሰዎች ቤታችን ለምሳ ይመጡ እንደነበር
አስታውሳለሁ፡፡ አቶ ወንድወሰን አለሙ፤ ከበደ አኒሳ ቤት ለምሳ ይመጡ እንደነበር አልዘነጋውም፡፡ በጣም የቅርብ ወዳጆቹ አቶ
አጥናፍሰገድ ይልማ፣ እንዲሁም አቶ መርስኤ ሀዘን አበበ እርጉዝ በነበርኩ ጊዜ ይጠይቁን ከነበሩት መሃል አንዱ ናቸው፡፡ ጋሽ
ጳውሎስ ኞኞም ይመጣ ነበር፡፡ የእኔ ቤተሰቦች ወንድም እህቶቼ
በተለይ አባቴ ሁሉም ይወዱት ያከብሩት ነበር፡፡ሙሉጌታ ለሁሉ ቅርብ ነው፡፡ የልብስ ቁምሳጥኑ ለሁሉ ክፍት ነው፡፡ መጀመሪያ
አካባቢ ጓደኞቹ ሸሚዙን አውጥተው ሲለብሱ ግር ብሎኝ ነበር፡፡ ይህ ግን
መቀራረብ ያመጣው ነበር፡፡ ከበረዳቸው ካፖርቱን ለብሰው ይሄዳሉ፡፡ የእርሱን ጓዳ እንደጓዳቸው ነበር የሚያዩት፡፡ይህን ያህል መልካም ሰው
መሆኑን ለመናገር ፈልጌ ነው፡፡ የሙሉጌታ መጽሀፍ መደርደሪያ በጣም ብዙ መጽሀፍትን የያዘና በጣምም ትልቅ ነው፡፡ያንን ሁሉ
የመቀበል ችሎታው ያኔ አሰብ ሳደርገው ግርም ይለኛል፡፡ስለሁሉ ነገር ያውቃል፡፡ ግርም ይለኝ ነበር፡፡ ሙሉጌታ ሁሌጊዜ ጊዜ
በስራ ጉዳይ ላይ ይመክረኝ ነበር፡፡ ስራ እንድሰራ ዘወትር ይጎተጉተኝ ነበር፡፡ ጎትጉቶ ስራ እንድገባ ያደረገኝ ሙሉጌታ ነው፡፡
መስራት አእምሮን እንደሚያበስል ይነግረኝ ነበር፡፡ ፕላኒንግ ኮሚሽን 35 አመት ሰርቼ ነው የወጣሁት፡፡ ደግሞ ልክ እንደእርሱ
መጽሀፍ እንዳነብ ይመክረኝ ነበር፡፡ እኔም የሰጠኝን ምክር ተቀብዬ አነብ ነበር፡፡ ይህም አሁን ላለው ህይወቴ ትልቅ የመሰረት
ድንጋይ አስቀምጦልኛል፡፡አሜሪካም ሳለ በስልክ እንደዋወል ነበር፡፡ ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚችልበት አጋጣሚ ስላልነበር ሁሉ
ነገር በስልክ ነበር፡፡ሙሉጌታ ለእኔ በጣም የሚመች፣ ክፉ ነገር እንኳን አንድም ቀን ተናግሮኝ የማያውቅ ሰው ነው፡፡ ሊሞት
ትንሽ ቀናት ሲቀሩት ራሱ በስልክ እናወራ ነበር፡፡›› በማለት ወይዘሮ ስርጉት ስለባለቤታቸው ስለ ሙሉጌታ ሉሌ ተናግረዋል፡፡
የሙሉጌታ ሉሌ
ጽሁፎች፣ ትንቢታዊ ጽሁፎች ነበሩ፡፡ ስለ ኤርትራ ፤ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት የሚጽፋቸው ነገሮች ሁሉ ዛሬ ላይ እየሆኑ ነው፡፡
ወይዘሮ ስርጉትም ከዚህ አንጻር የአቶ ሙሉጌታን ጽሁፍ ሲያነቡ ነገን የመተንበይ አቅም ያላቸው ሆነው አግኝተዋቸዋል፡፡ ጋዜጠኛ
ሙሉጌታ፣ ያኔ እንዲህ ይሆናል ብሎ የተናገራቸው ነገሮች ሆነዋል፡፡ይህ እንግዲህ የጸሀፊውን ሩቅ የማየት ድንቅ ብቃት የሚያሳየን
ነው፡፡ ‹‹….ባለቤቴ ለሀገሩ ሲል እስከሞት ድረስ በብእሩ ታግሏል›› ሲሉ ወይዘሮ ስርጉት ሀሳባቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ በብሄር
ያልተከፋፈለች ኢትዮጵያን ሙሉጌታ ምንጊዜም ይናፍቃል፡፡
አንዳንድ ነገሮች ስለሙሉጌታ ሉሌ
ሙሉጌታ ሽሮ ነፍሱ
ነች፡፡ ታዲያ ከሽሮው ጎን ቃሪያ ከኖረ ደስታውን አይችለውም፡፡ ለመጠጥ ብዙም ግድ የለውም፡፡ ልብስ ላይ ግን ልዩ ምልከታ
አለው፡፡ ሽቅርቅር ከሚባሉት ተርታ ይመደባል፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ሱፍ መልበስ ደስ ይለዋል፡፡ ቅዳሜና እሁድ ሲሆን ደግሞ ጃኬቱን አድርጎ ሲታይ ውበት ያላብሰዋል፡፡ ሙሉጌታ 2 ቁምሳጥን ሙሉ
ልብስ አለው፡፡ አለባበስን ማሳመር መሰረታዊ እንደሆነ ሙሉጌታ ያምናል፡፡ ለእግርኳስ የተለየ ፍቅር አለው፡፡ ጥሩ ለተጫወተ ብቻ
ይደግፋል፡፡ የዚህ ቡድን ደጋፊ ተብሎ መነሳት አይሻም፡፡ ሙሉጌታ
ለሰው ደግ ነገር ያደርጋል፡፡ ከተቀየመ ግን መመለሻ የለውም፡፡ ቶሎ ያዝናል፡፡ ይህንን ባህሪ የቅርብ ሰዎቹ እንደደካማ ጎን
ይመለከቱታል፡፡ ሙሉጌታ ጦቢያ በነበረ ጊዜ የዛሬ 29 አመት በወር የሚከፈለው 500 ብር
ነበር፡፡ ነገር ግን ከድርጅቱ ባለቤቶች አንዱ ስለነበር ለገንዘብ ብዙም ደንታ አልነበረውም፡፡ እርሱ ብቻ ሳይሆን ሌሎቹ በስራው
ውስጥ ይሳተፉ የነበሩ ባለቤቶችም ደሞዛቸው ከ 500ብር
አይበልጥም ነበር፡፡ ሙሉጌታ የሚነዳት መኪና ማርቼዲስ ነበረች፡፡ ይህቺን መኪና እየነዳ ነበር አደጋ የደረሰበት፡፡ ነገር ግን
ከአደጋው በቶሎ አገግሞ ወደ ስራው ተመልሷል፡፡ ጊዜውም
1986 ነበር፡፡
እንዴት ሞተ ሳይሆን እንዴት ኖረ?!
ኤዶም ሙሉጌታ ሉሌ፣ የሙሉጌታ ሉሌ 3ኛ ልጅ ነች፡፡ ኤዶም በልጅነቷ እንደ አባቷ ደራሲ ወይም ጋዜጠኛ የመሆን ህልም ሰንቃ
ነበር፡፡ ኤዶም ስለ አባቷ ትዝ ሲላት በልጅነቷ ቤታቸው
የሚከፈተው የቢቢሲ ሬድዮ አይዘነጋትም፡፡ በተጨማሪም አባት ሙሉጌታ ራሱን ከወረቀቶች ጋር አቆራኝቶ የነበረበት ጊዜ
አይረሳትም፡፡ እንደ አባት ደግሞ ፍቅር የሆነ አባት እንዳላት ታስባለች፡፡
ሙሉጌታ ሉሌ በ1989 ኢትዮጵያን ለቀው ሲወጡ ኤዶም ገና የ2ኛ ደረጃ ተማሪ ቤት ውስጥ ነበረች፡፡ በጣም የምትወደው
አባቷ ወደ አሜሪካ መሄዱን ስታስብ ይመለሳል የሚል ግምት ይዛ ነበር፡፡ ነገር ግን አልሆነም፡፡ ኤዶምና ሙሉጌታ ይደዋወላሉ፡፡
ሙሉጌታ ትንሹዋን ኤዶምን ይመክራል፡፡ ሰዎችን በምንም ደረጃ ቢሆን እንዳትቀየሚያቸው ይቅርታ ማድረግ አለብሽ እያለ ይቅርታ
ለህሊና የሚሰጠውን ርካታ ይነግራት ነበር፡፡ በፍጹም አኩራፊ እንዳትሆኚ እያለም ትልቅ የሚለውን ምክር ይለግሳት ነበር፡፡
በተጨማሪም፣ ሙያዋን ወዳው ትሰራ ዘንድ አባታዊ ምክሩን ከመስጠት ወደኋላ ብሎ አያውቅም፡፡
ኤዶም አባቷን ናፍቃ
ነበር፡፡ በመስከረም 2008 የ75 አመቱን ባከበረበት ሰሞን ህይወቱ ማለፉ ሲነገር አዲስ አበባ ላሉት ቤተሰቦቹ እጅግ
የሚያሳዝን ነበር፡፡ በተለይም ደግሞ ባለቤቱና ልጆቹ ለ19 አመት አይተውት ስለማያውቁ ህልፈቱን መቀበል አዳጋች ሁኖባቸው
ነበር፡፡ ያኔ ሙሉጌታ ድንገት ነበር ቲቪ እያየ ለህልፈት የተዳረገው፡፡ ይህ ዜና በተለይ ለልጅ ኤዶም እጅግ የሚቆጭ ብቻ
ሳይሆን ባህር ማዶ ሄዳ ለመቅበር አለመቻሏ ሀዘን ውስጥ የጨመራት ጉዳይ ነበር፡፡ በሚኖርበት አሜሪካ የቀብር ስነ-ስርአቱ እጅግ በደመቀ መልኩ የተከናወነ
ሲሆን ታላላቆችም ታድመው ነበር፡፡ ኤዶም ይህን ስነ-ስርአት በአካል ተገኝታ ለማየት እና ውስጣዊ ሀዘኗን ለመወጣት ባትችልም
በቪድዮ ሙሉ ስነ-ስርአቱን መመልከት ችላለች፡፡ ህይወቱ ባለፈ በ6ኛ ወሩ በየካቲት 2008 በኢሳት አስተባባሪነት የማስታወሻ
ፕሮግራም ተዘጋጅቶለት ነበር፡፡ በዚህ መሰናዶ ላይ ለመታደም ኤዶም ፈልጋ ነገር ግን ሳይቻላት ቀርቷል፡፡ በዚህም ታላቅ ቁጭት
ውስጥ ገባች፡፡
ኤዶም ይህን ቁጭቷን ለመወጣት አንድ ነገር ማድረግ አለብኝ ስትል ሀሳብ
አደረገች፡፡ የአባቷ 1ኛ አመት ሙት አመት በታሰበበት እለት
በመስከረም 2009 ሰው ስንፈልግ ባጀን በሚል ርእስ የሙሉጌታን ስብስብ መጣጥፎች ለማሳተም ችላለች፡፡ ይህ መጽሀፍ 344 ገጾች
ያሉትና 31 የሙሉጌታን መጣጥፎች እንዲሁም አንድ ከራሱ ከሙሉጌታ ጋር የተደረገ ቃለ-መጠይቅን ያካተተ መድብል ነው፡፡ ኤዶም
ይህን መጽሀፍ አሳትማ በማስመረቋ ታላቅ የመንፈስ ርካታ ይሰማታል፡፡በተለይ ደግሞ መጽሀፉ በአንባቢያን ዘንድ የተደረገለት
አቀባበል ሙሉጌታ ምን ያህል ተወዳጅነቱ የሚዘልቅ ባለሙያ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ በመቀጠልም ‹‹በእዳ የተያዘ ህዝብ››
የሚለውን መጽሀፍ ኤዶም አሳትማለች፡፡ ኤዶም አባቷ የሚኮራበት
ታላቅ ሰው መሆኑን በጽናት ታምናለች፡፡ ታላላቅ ምሁራን ሳይቀሩ የመሰከሩለት ነውም ትላለች፡፡ ለዚህም ፕሮፌሰር መስፍን
ወልደማሪያም የሰጡትን አስተያየት ማንሳት ትፈልጋለች፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ በወገን ናፍቆት በጸና ታመመ ሲሉ ፕሮፌሰር ሀሳብ
መስጠታቸውን ቀጠሉ፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ፣ በአሜሪካ ደህና ኑሮ እየኖረ
ኢትዮጵያን መርሳት አቃተው ሲሉ ምሁሩ ሀሳባቸው ቀጠሉ፡፡ ፕሮፊሰር መስፍን ቀጠሉ‹‹…ሙሉጌታ በጭቆና እየኖሩ ያሉትን ወገኖቹን
እያሰበ ተጨነቀ፡፡ ጋዜጠኞችን በተለይ እያሰበ ተጨነቀ፡፡በአሜሪካ ያገኘው ነጻነት በኢትዮጵያ ያጣውን ነጻነት ሊተካለት
አልቻለም፡፡ ነፍሱ የተጠማችው የኢትዮጵያን ነጻነት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ነጻነት እንደተጠማች እያለቀሰች አረገች›› ሲሉ ፕሮፌሰር መስፍን ሙሉጌታ የሞተ ሰሞን
ሀሳባቸውን ሰጥተው ነበር፡፡
የሙሉጌታ ሉሌ ወዳጅ
የነበሩት አቶ አሰፋ ጫቦ ደግሞ የሙሉጌታ ሉሌን የተዋጣለት ጸሀፊ መሆን መስክረዋል፡፡ አቶ አሰፋ እንዳሉት ሙሉጌታ
የሚያምነውንና የሚያውቀውን ብቻ ይጽፋል፡፡ እምነቱ ደግሞ ጥልቀት ካለው ባህር የሚቀዳ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡ ለአሰፋ ጫቦ
ሙሉጌታ ሉሌ ዘመናይ ሰው ነው፡፡ ስልጡንም ጭምር፡፡
አቶ አሰፋ ጫቦ
በ2015 በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ እንደጻፉት እንዲህ አሉ‹‹…. የማይሞት ሰው ሞተ ይባላል፡፡አባባል ነው! ሰው ብቻ ሳይሆን
ፍጥረት ሁሉ ይሞታል፡፡ይተካልም! የሙሉጌታ ሞት በስደት ባይሆን ጥሩ ነበር፡፡ ያ ደግሞ የሀገራችን አካልና አምሳል ገላጭ ባህር
ሆኗል፡፡ዋናው ነገር እንዴት ሞተ ሳይሆን እንዴት ኖረ ተብሎ ነው መጠየቅ ያለበት ሙሉጌታ አንገቱን ቀና አድርጎ ያመነበትን
በግልም በአደባባይም ፤ ተናግሮም ጽፎም ያለፈ ጀግና ነው›› በማለት አቶ አሰፋ ሀሳባቸውን ቋጭተው ነበር፡፡
ሉሌ ሙሉጌታ፣
ለአባቱ ታላቅ ክብር አለው፡፡ የአባቱ የንባብ ፍቅር ለብዙ
ወጣቶች አርአያ እንደሚሆን ያስባል፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ የብዙዎች አባት መሆኑንም ሉሌ ይመሰክራል፡፡ በተለይ ጦቢያ ላይ ይወጡ
የነበሩት መጣጥፎች የአስተሳሰብ አድማስ የማስፋት አቅም እንዳላቸው ይናገራል፡፡ አሁን የኣባቱ ታሪክ በዊኪፒዲያ በዝርዝር ጥናት መቅረቡ ትልቅ ርካታን
እንደፈጠረለት ሉሌ ነግሮናል፡፡ ኢትዮጵያ ልክ እንደ ሙሉጌታ አይነት ለእናት ሀገር ፍቅር የደከሙ ብዙዎች ባለውለታዎች
እንዳሏትና የእነርሱም ታሪክ ትውልድን እንደሚያንጽ ሉሌ ይናገራል፡፡
ሙሉጌታ ከሞት አትርፎኛል
አቶ ጫኔ ደበበ፣
የ81 አመት አዛውንት ናቸው፡፡ ከሙሉጌታ ጋር በእናቱ በወይዘሮ ወርቅነሽ ጎሹ በኩል የአንድ አያት ልጆች ነን
ይላሉ፡፡
‹‹ ሄሎ ጋሽ ጫኔ እንዴት ነዎት?››
‹‹ አቤት ማን ልበል?››
‹‹ የሙሉጌታ ሉሌን ታሪክ እየሰራን ነበር፡፡ እና አንድ የተለየ ታሪክ
እንዲነግሩን ነበር››
‹‹ ጓደኞቹን ብትጠይቁ አይሻልም?››
‹‹ አብረውት የሰሩትን ጠይቀናል፤ እንዲያው ከቅርብ ዘመድ አዲስ ነገር
ከተገኘ ብለን ነው››
‹‹ መልካም ቆየት ብላችሁ ደውሉ››
‹‹ እናመሰግናለን አቶ ጫኔ››
አቶ ጫኔ የ3 ልጆች
አባት ናቸው ፡፡ ስለሙሉጌታ አውርተው የሚጠግቡ አይነት አይደሉም፡፡ በስልክ ሲያወሩን ደግነቱን ለመግለጽ ቃላት
አነሳቸው፡፡ ሙሉጌታ ህይወቴን ከሞት ያዳነ ወንድሜ ነው ሲሉ
ታሪክ ማጫወት ጀመሩ፡፡ ያኔ በደርግ ዘመን አንዱ ታሳሪ ሌላው አሳሪ የሚሆንበት ጊዜ ነበር፡፡ በተለይ አቶ ጫኔ በሚሰሩበት
ሜታአቦ ፋብሪካ ውስጥ የሰራተኛ ማህበር ውስጥ ትልቅ ብጥብጥ ይነሳል፡፡በጊዜው ግትር የነበሩት አቶ ጫኔ ከሰራተኛ ማህበሩ
መሪዎች ጋር በሀሳብ ሊግባቡ አልቻሉም፡፡ በዚህ ሰአት ወስደው አሰሯቸው፡፡
ማሰር ብቻ ሳይሆን የሞት ፍርድ
ተበየነባቸው፡፡ በዚህ ሰአት ቤተሰቡ ታላቅ ጭንቀት ውስጥ ገባ፡፡ ያኔ የደህንነት ዋና ኃላፊ የነበረው ኮሎኔል
ተስፋዬ ወልደስላሴ የሞት ፍርድ የተበየነበትን ደብዳቤ እስቲ አምጡ ብሎ ይህ ሰው ሊሞት አይገባውም፡፡ እንዲያውም ፍቱት ሲል
ትእዛዝ ሰጠ፡፡ አቶ ጫኔም ተፈቱ፡፡ አቶ ጫኔ ይህ ትልቅ ከሞት የማምለጥ አጋጣሚ በጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ አማካይነት መደረጉን
አወቁ፡፡ ደብዳቤው እንዲቀር በማድረጉ በኩልም ሙሉጌታ ትልቅ ስራ የሰራ መሆኑን ተገነዘቡ፡፡ ከ40 አመት በፊት የ40 አመት ጎልማሳ
እያሉ የተቀጠለላቸው እድሜ ዛሬ 80ን አሳይቷቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ በሙሉጌታ እንዲሁም በእግዚአብሄር ርዳታ የሆነ ነበር፡፡
ሁለት አርቲክል አሁኑኑ አድርስ
“እኔም በጣም
የሚደንቀኝ ችሎታው ይላል ሰሎሞን ክፍሌ። ቀድሞ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን
የቪኦኤ እውቅ ጋዜጠኛ የነበረው ሰሎሞን ክፍሌ ጋሽ
ሙሉጌታ እንደፎቶግራፍ ያየውን ያነበበውን የሰማውን ቀርጾ ማስቀረት የሚችል የተለየ ጭንቅላት አለው ብሎ ነግሮናል። ሀሳቡንም
እንዲሁ አንዴ ፎቶ ያነሳዋል መሰለኝ ወረቀት ላይ ቁጭ ሲያደርገው ወዲያው ነው። ለምሳሌ አንድ ጊዜ በመኪና ረጅም መንገድ እየተጓዝን ነበርን። ያኔ
ከወጣም በኋላ ጦቢያ መጽሔት ላይ ይሠራ በነበረበት ጊዜ ነው። እና ለካ እሱ ሁለት አርቲክል አሁኑኑ አድርስ ተብሎ ኖሯል።
መኪና ውስጥ ሆኖ ከጎኔ ተቀምጦ ይሞነጫጭራል። ኧረ ጎሹ ለጦቢያ መጽሔት አድርስ ያለኝ ሁለት አርቲክል አለ እያለ አንድ ጊዜ
መሞነጫጨር ጀመረ። በኋላ ገረመኝ ከዲሲ ተነስተን ቦልቲሞር እስክንደርስ አንደኛው አልቋል አለኝ። ፔንሲልቪኒያ ስንደርስ
ሁለተኛውን ጨርሶታል። በል አሁን እዚህ እንውረድና ጽሁፎቹን እንላክላቸው ሲለኝ በጣም በጣም ደነቀኝ። ያንን ሲያደርግ ከኪሱ
የሚያወጣቸው የሚያመሳክራቸው ምንም ነገር የለም። ብዙ ሰዎችን
ብዙ ቀኖችን ዓመተ ምህረቶችን ነው የሚጠቅሰው። እና እነዚያን አርቲክሎች ሌላ ጊዜ በትክክል አንብቤያቸዋለሁ። ጥልቅ ናቸው።
ይህ ሁል ጊዜም ይገርመኛል።” ብሏል ሰለሞን ክፍሌ።
ባህርይው ከሥራው
ውጭ ሌላው የሚያስደንቀኝ ደግሞ ይሄ ትልቅ ሰው ነው፣ ይሄ ትንሽ ሰው ነው የሚለው ነገር አልነበረውም። ከሁሉም ጋር ቁጭ ብሎ
በማንኛውም ርዕስ ላይ ይወያያል። እኔ ብቻ አውቃለሁ የሚል አይደለም። ለማስረዳት የሚያደርገው ጥረት ይገርመኛል።
በመጨረሻዎቹ ጊዜያት
ከበውት ከሚውሉ አድናቂዎቹ ወጣቶች አንዱ የሆነው ተስፋዬ ተሰማ ይህንኑ የሰሎሞን አባባል አረጋግጧል። “ እኛ ወደሱ ከፍ
እያልን ሳይሆን እሱ ወደኛ ዝቅ ብሎ እየመጣ ነው ፣ ምክንያቱም
ጋሽ ሙሉጌታ ውሎው ትንሽ ትልቅ ብሎ የሚለይ አይደለም ብሏል። ደግ ሰው ፣ጋባዥ ትሁትና ተጫዋች ነው።
ሰሎሞን ክፍሌ
እንደሚለው ጋሽ ሙሉጌታ የአንድ ሰው ጭንቅላት ብቻ የተሸከመ
አይመስለኝም፡፡ የብዙ ሰው ጭንቅላት የተሸከመ ነው የሚመስለኝ፡፡ የዛሬ 30 ዓመት የተለያየኸውን ሰው ስትጠይቀው እስከ እነ
አባቱ እስከነ ቅድመ አያቱ ይነግርሃል። እዚህ አገር ቆይቶ ቢሆን ኖሮ እንደኛ የሶሻል ሴኩሪቲውን ቁጥር የጫማ ቁጥሩን ሁሉ
ሳይነግረን አይቀርም ብሎ ቀልዷል።
በሀዘኑ እጅግ
ከተነኩት አንዱ የሆነው ሰሎሞን “ጋሽ ሙሉጌታ ለአገሩ አፈር አለመብቃቱ ያሳዝነኛል፡፡ ወደመጨረሻው ላይ ዓይኑን አሞት ኧረ
ታውሬ አይኔ ከሚታወር ለአገሬ አብቁኝ ቢፈልጉ ይግደሉኝ ይል ነበር። እሱ ሁሌም አብሮኝ ኖሮ ይረብሸኛል።”
“ሐውልቴ የሚሠራው ጠላቶቼ ከሚወረውሩብኝ ድንጋይ ብዛት ነው”
በመረበሹስ ላይ
ታማኝ በየነም አለበት። አባቴና ልጄ በሚባባሉት ታማኝና ሙሉጌታ ሉሌ መካከል ከ1988 ጀምሮ የሰነበተ ፍቅር መኖሩን ታማኝ
ተናግሯል። እንዲያውም ያኔ ጋሽ ሙሉጌታን ለመጀመሪያ ጊዜ ያየሁበት ነው እንጂ በጽሑፍ ከረታኝ ቆይቷል። ጋሽ ሙሉጌታን በጦቢያው
ፀጋዬ ገ/መድህን ነው ይበልጥ የማውቀው። ከዚያም ውጭ አንባቢነቱን ስለማውቅና አክብሮትና ፍቅሬም ገደብ ስላልነበረው እሱን
የምተዋወቅበትን ቀን እናፍቅ ነበር። መጽሐፍ እጅግ እንደሚወድ እስማ ስለነበር አንድ ቀን በዚያውም ትንሽ ፈገግ አደርገው
እንደሁ ብዬ ከለንደን ጠረጴዛ የሚያክል ግዙፍ መጽሐፍ ይዤለት ወደ ኢትዮጵያ ቤቱ ድረስ ልጠይቀው ሄድኩ። ጊዜው የአድዋ በዓልም
አካባቢና ጋሽ ሙሉጌታ በግጭቱ ጉዳት ደርሶበት የነበረበት እለት ነበር። እና ገና ከመነሻው ሳውቀው ተጎድቶ ነው። ከዚያ በኋላ
ይበልጥ ያየሁትና የተዋወቅሁት ደግሞ እዚህ ነው። እዚህም በደህና ነገር ሳይሆን የአባቴን ሞት ሊያረዳኝ ቤቴ ድረስ መጥቶ ነው
ያወቅሁት። እና ከዚያ በብዙ እየተቀራረብን መጣን። “የሚቆጣኝ ይህን በል ያን አትበል” የሚለኝ ሰው ነበር። “ይሄን ደግሞ
በየወቅቱ እየወጣህ እኔ ትንሽ ሰው ነኝ የምትለውን ነገር ተው!”
ይለኛል።
ደግሞ ሌላ ጊዜ
በማደርገው ነገር ሰዳቢዎቼ በዝተው በጣም ሳዝን ይመጣብኛል። በተለይ በአንድ ወቅት የተናገረኝ ነገር መቼም አልዘነጋውም “ ስማ
ታማኝ አንድ የፈረንሳይ ፈላስፋ ምን ይል ነበረ መሰለህ፣ ካለ በኋላ… እና ግን ምን ያደርጋል ጋሽ ሙሉጌታ ቀርቶብናል…. ብሏል።
ታማኝ የሚያዝነው
በሁለት ነገር ነው። አንድም ጋሽ ሙሉጌታ ስለራሱ መጽሐፍ ሳይጽፍ በመሄዱ እና ትልቁና ዋነኛው ደግሞ ለአገሩ አፈር ሊበቃ አለመቻሉ
ነው። ምክንያቱም ጋሽ ሙሉጌታ ስለአገሩ የነበረውን ፍቅርና ተመልሶ የማየት ጉጉት ያውቃል። ጋሽ ሙሉጌታን ለመጨረሻ ጊዜ
የተሰናበተው ኢሳት ቢሮ ውስጥ አቀርቅሮ ሲጽፍ ነበር። ሁሌም “ማንበብ ምን ያደርጋል? ቁምነገሩ መጻፍ ነው እያለ..” የቀልዱን
ያበሽቀው እንደ ነበር ይታወቃል።
18 ዓመታት አሜሪካ
ከመጣ ጀምሮ እንደ አባት ወንድም መካሪና ጥሩ ወዳጄም ነበር። ኢትዮጵያን በልዩ ሁኔታ ከሚያፈቅሯትም ልዩ ሰዎች እንደ አንዱ
አድርጌ የማየው ሰው ነው። ታላላቅ ሰዎች ቢያልፉም ሥራዎቻቸው አያልፍም እንደሚባለው የጋሽ ሙሉጌታ ሥራዎች የሚያልፉ
አለመሆናቸው የሚያጽናና ነው። ወጣቶቹን የኢሳት ጋዜጠኞችን
በአርአያነትና በሙያ በመግራት ያደረገው አስተዋጽኦም ቀላል የሚባል አይደለም። እንደ ኢሳት ባልደረባ በትንታኔዎቹ
ኢንሳይክሎፒዲክ በሆነ እውቀቱ ሚሊዮኖቹን አስተምሯል። ብሏል።
የመጨረሻዋ የሙሉጌታ ጽሁፍ -ሰኔ 2007
ጋዜጠኛ እና
የፖለቲካ ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ፣ ጦቢያ መጽሄት ከተዘጋች ከ1997አ.ም ወዲህ በቋሚነት አንድ የህትመት ውጤት ላይ ባይጽፍም
ለአንዳንድ ድረ-ገጾች ጽሁፍ ማበርከቱ አልቀረም፡፡ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ ለመጨረሻ ጊዜ በሰኔ 2007 ጽፎታል የተባለው መጣጥፍ
አሻራ በተባለው መጽሄት ላይ የወጣ ነበር፡፡ አሻራ፣ በሳምሶን አስፋው እና በአቢይ አፈወርቅ የሚዘጋጅ መጽሄት ሲሆን አቶ
ሙሉጌታ ሉሌ በዚህ መጽሄት ላይ ጽፎ ነበር፡፡‹‹ ጠፍአት አገርነ›› ትናንት ማታ ጨረቃዋንም አዋልደናል በሚል ርእስ ሙሉጌታ
በጻፈው ጽሁፍ በርካታ ቁምነገሮችን አመላክቷል፡፡ ሙሉጌታ ሉሌ
በዚህ ጽሁፉ መቋጫ ላይ ሀሳቡን ሰብሰብ አድርጎ ሲቋጭ
እንዲህ አለ‹‹…… ሁላችንም ዛሬ ያለብን ኃላፊነት በዘረኞች ላይ የሚካሄደውን የአርበኝነት ትግል ወያኔዎች ወደ ትግራይ ህዝብ
የህልውና ተጋድሎ እንዳይለውጡት ነው፡፡ የትግራይን ህዝብ ከኢትዮጵያ ህብረተሰብነትና አካልነት ያስወጣ ማነው? አጥንታችን
አጥንቱ ፣ስጋችን ስጋው አይደለምን?›› በማለት ጽፎ ነበር፡
የሙሉጌታ ንግግሮች
ኢትዮጵያ ውስጥ
ጀግና የሚከበርበት አጋጣሚ የለም፡፡ የሚከበርበት ብቻ
አይደለም፡፡ የሚታወቅበት እድልም የለም፡፡ይሄም የብዙዎቻችን
የእግር እሳት ነው፡፡
ሁላችሁም እዚህ
የምትገኙ በ3ኛው ትውልድ ላይ የምትገኙ ናችሁ፡፡ ዛሬ እዚህ አዳራሽ ውስጥ ያላችሁትን በ3 ትውልድ እመድባችኋለሁ፡፡
የመጀመሪያው 33 አመት ከ3ወር ከ3ቀን ያላችሁት ናችሁ፡፡ ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ 66 አመት ለ6ወር ከ6ቀን የሆናችሁ
ናችሁ፡፡ከዚያ በላይ ደግሞ እንደእኔ ያላችሁ በሌላ ትውልድ ዘመን ውስጥ የምትኖሩ ናችሁ፡፡ ጦቢያ ላይ ስጽፍ በነበረበት ጊዜ
ትውልድን ስራገም ነበር፡፡ባለፈው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም እንዳለው ጀግና ትውልድ ገዳይ ሀገር ብሏል፡፡ ራስ አበበን በላይ ዘለቀን
የገደለ ትውልድ ብሏል፡፡ ያኔ ጀግናውን የማያከብር
ትውልድ ብዬ ስራገም ነበር፡፡ ያሁኑ ዘመን ትውልድ ትግል ከድሮዎቹ በጣም የተለየ ነው፡፡ የድሮዎቹ ኢትዮጵያውያን ሀገራቸውን
ከጠላት ለማዳን ይከላከሉ ነበር፡፡ ይህንን ትውልድ በጣም እናደንቀዋለን፡፡ ይሄ ትውልድ አዲስ አይነት ጦርነት ውስጥ ነው
የገባው፡፡ስለዚህ ማነው የሚረገመው ማነው የማይረገመው? መጠየቅ አለበት፡፡ሁላችንም ዛሬ እየተጋፈጥነው ያለ ጠላት የውስጥ ጠላት
ነው፡፡ ይህ ጠላት ኢትዮጵያን ከውስጥ ሊያጠፋ የተነሳ ክፉ ጠላት
ነው፡፡ ይህ ጠላት የኢትዮጵያን ክብር የናደ ክብሯንም የናደ ስለሆነ በዚህ ወቅት እንሙት ብለው ደማቸውን የገበሩትን እናገኛለን፡፡ደማቸውን የገበሩት
ኢትዮጵያን ለማዳን ነው፡፡ ሰልፉ የጀግና ነው ድሉ የእግዚአብሄር ነው፡፡ ህይወታቸውን በሰልፉ ውስጥ
ያስገቡ ሰዎችን ሳስብ የእኔ ሚና ምንድነው እያልኩ ጠይቃለሁ፡፡
ይህንን ትውልድ ስራገም የነበረበትን ቋንቋ ቀይሬ ይቅርታ ጠይቃለሁ፡፡ ሀገሪቱ አዳዲስ ጀግኖችን እያፈራች ስለሆነ አሁንም ሰልፉ
የጀግና ነው ድሉ የእግዚአብሄር ነው፡፡
ፍጻሜ
ሙሉጌታ መስከረም
23 2008 በ75 አመቱ ህይወቱ አለፈ፡፡ የአቶ ዮሀንስ ሙሉጌታ፣ የአቶ ሉሌ ሙሉጌታ ፤ የኤዶም ሙሉጌታ አባት በሁሉ
እንደተወደደ አሸለበ፡፡ የ 6 ልጆች አያት የሆነው ሙሉጌታ በአጸደ ስጋ ቢለይም ተግባሩ ጽሁፎቹ ይኖራሉ-እስካኖርናቸው ድረስ፡፡
መዝጊያ፣ ጋሽ
ሙሉጌታን እንዴት እንደምንወደው በዚህ ጽሁፍ አሳይተናል፡፡ እርሱ ሀገሩን ይወድ ነበር፡፡ እኛ ደግሞ እርሱን እንወደዋለን፡፡
ጋሽ ሙሉጌታ ምን ያህል በሳል ጸሀፊ እንደነበር ጽሁፉን ያነበቡት
ብቻ ያውቁታል፡፡ ሙሉጌታን አንቱ ብንለው ለክብር አንተ ብንለው ለፍቅር፡፡ ይከበራል፡፡ ይወደዳል፡፡ 75 አመት እስኪሞላው
ድረስ እውቀቱን ሳይሰስት ለግሷል፡፡ 75 አመቱ ድረስ ብእርና ወረቀትን እያዋደደ እውቀት ሲሰድልን ኖሯል፡፡ ያነበበውን ጨምቆ
እየነገረን ከብዙ ልፋት አድኖናል፡፡ በዚህ ኢትዮጵያ ልታመሰግነው ይገባል፡፡ በ1983 የመንግስት ለውጥ በተደረገ ጊዜና
በ1984 የነጻ ፕሬስ በይፋ ሲፈቀድ ቀድመው ከገቡት መሀል ሙሉጌታ እና ጓደኞቹ ነበሩ፡፡ ሳይፈራ መንግስት ሲተች ብዙ መከራ
ቀመሰ፡፡ ታሰረ-ተንገላታ፡፡ ሙሉጌታ አሁንም ዘረኝነትን ተዋጋ፡፡ ኢትዮጵያ አስቀደመ፡፡ አንድነት ግድ ነው ሲል ብእሩን
አነሳ፡፡ አሁንም መመስገን ሲገባው የቀድሞው መንግስት ክንድ ተሰነዘረበት፡፡ እርሱን ግን ማንም ከእውቀት የሚነጥለው
አልነበረም፡፡ እውቀቱን እንደያዘ ወህኒ ገባ፡፡ ደግሞ ተፈታ፡፡ ጋሽ ሙሉጌታ በኢትዮጵያ ተስፋ አይቆርጥም፡፡ አንባቢን በማክበር
በምንም ችግር ውስጥ ቢያልፍ ድምጹን አጥፍቶ ይጽፋል፡፡ ድምጹን አጥፍቶ ያነባል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ሙሉጌታ
ሉሌ ያልተዘመረለት ጀግና ነው፡፡ በጋዜጠኝነት በቆየበት ዘመን ሀገሩ ጠርታ የክብር ሽልማት መስጠት ሲገባት ጭራሽ ባለህበት ቆይ
ብላ ሲሞትም ለሀገሩ እንዳይበቃ አደረገች፡፡ የደከመላትን የማታውቀው ኢትዮጵያ ላልሰራላት ሽልማት እያቀረበች ታይታ ወዳዶችን
እያሞገሰች የምትቀጥለው እስከመቼ ይሆን? እንደ ሙሉጌታ ሉሌ አይነት ሰዎች ታሪካቸው ወጥቶ ለአዲሱ ትውልድ የማይቀርበውስ ለምንድነው? በምርምር የተደገፈ የባለታሪኮችን ዋና ሚና የያዘ ግለ-ታሪክ በስፋት
የምናየው መቼ ነው? እኛ የዚህ ዊኪፒዲያ አሰናጆች መንገዱን
ጀምረናል፡፡ ሙሉጌታ ሉሌን ለማክበር ለማወደስ ስንል ግለ-ታሪኩን በመጽሀፍ ፤ በመጽሄት ፤ በፌስ ቡክ፤ በሬድዮ፣ በቲቪ፤
በዊኪፒዲያ ፤ በኦድዮ ሲዲ ፤ በሁሉም አይነት መንገዶች ለማሳወቅ ጥረቱን ጀምረናል፡፡ በዚህ ሁሉ መንገድ ጋሼን ካሳወቅነው
ከዚህ በላይ ሀሴት ከወደየትም አይገኝም፡፡ / የዚህ ጽሁፍ
የምርምር ፤ የቃለ-መጠይቅእና የጽሁፍ ስራ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን ይህም ጽሁፍ በየጊዜው አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በተወዳጅ ሚድያ
የፌስቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ላይ ይወጣል፡፡ ይህን ስራ በዚህ
መልኩ እንድንሰራ ብርታት የሰጡን 5 ቁልፍ ሰዎችን ማመስገን እንሻለን 1.ስለሺ ሽብሩ 2 . ሲሳይ አጌና 3 ኤዶም ሙሉጌታ 4 ዮሀንስ ሙሉጌታ
እና 5. ዶክተር ገብርዮ ወልደሩፋኤል / ይህ ጽሁፍ ዛሬ ሀሙስ ነሀሴ 6 2013 ዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ