41. ተስፋዬ ኃይሌ ስንቄ-TESFAYE HAILE SINKE 

በጎ አሳቢው  ኢትዮጵያዊ -ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ስንቄ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከዚህ ቀደም በጥበብ፤በመዝናኛ እና በመረጃ  ዘርፍ ላይ ተሰማርተው ሀገራቸውን ያገለገሉ ሰዎችን ታሪክ በዊኪፒዲያ ሲያወጣ ነበር፡፡ አሁን  ደግሞ በበጎ አድራጎት ፤ በጤና እና ማህበራዊ አገልግሎት ሀገራቸውን የረዱ ምርጥ ኢትዮጵያውያንን እንዘክራለን፡፡ እነዚህ ሰዎች በባህር ማዶም በሀገር ውስጥም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ከቀናት በፊት ህይወታቸው ያለፈው ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ስንቄ በዛሬው እለት ነሀሴ 8 2013 የቀብር ስነ-ስርአታቸው በምድረ-አሜሪካ ይፈጸማል፡፡ ላለፉት 49 አመታት በባህር ማዶ የኖሩት ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ስንቄ በአሜሪካ የኢትዮጵያ ኮምዩኒቲ እንዲመሰረት ትልቁን ድርሻ ያበረከቱ ናቸው፡፡ በዚህም ታላላቅ ሽልማቶችን ለመሸለም የበቁ ናቸው፡፡ ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ስንቄ ማናቸው?   

          የፈረንሳይ ለጋሲዮኑ ልጅ ተስፋዬ

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ከእናቱ ከክብርት ወ/ሮ ሙሉነሽ ገሠሠ እና ከአባቱ ከክቡር ደጃዝማች ኃይሌ ሥንቄ በወሎ ክፍለ ሐገር በደሴ ከተማ እንደ ሐገራችን አቆጣጠር በ 1942 ዓ.ም ተወለደ። ልክ ሁለት ዓመትም ሲሞላው ከደሴ ወደ አባቱ ወደ ክቡር ደጃዝማች ኃይሌ ስንቄ እና አሳዳጊ እናቱ ክብርት ወ/ሮ አድማስወርቅ መኮንን መኖሪያ በመምጣት ከ1944 ዓ.ም ጀምሮ ከቀሩት ወንድም እና እህቶቹ ጋር በአዲስ አበባ ከተማ በቀበና አቦ (በፈረንሳይ ሌጋሲዮን) ሰፈር አደገ።

በዚያም በክቡር ደጃዝማች ኃይሌ ሥንቄና በባለቤታቸው ክብርት ወ/ሮ አድማስ ወርቅ መኮንን ይዞታ ስር በልዩ እንክብካቤ የልጅነት እድገቱን በመልካም ሥነ- ምግባር እየተኮተኮተ እና እየታነጸ አደገ። ልጅ ተስፋዬ ለቀሪው ዘመኑ ሁሉ በሔደበት እና በተሰማራበት ባለፈባቸው እና በተላለፈባቸው የሕይወት  ጎዳናዎች ላይ ሁሉ ሥንቅ እንዲሆነው እና አሻራውንም ማስቀመጥ ይችል ዘንድ ያስቻለውን የመልካምነት፣ የትሁትነት፣ የቅንነት፣ ለተቸገረ የመድረስ፣ የአዛኝነት፣ የአስታራቂነት፣ ፍቅርን የመጋራትም ሆነ የማጋራትን ምስጢር የተረዳው ገና በለጋነት እድሜው ነበር።

         ለጋሱ ልጅ

ታላቅነትን፣ ለጋሽነትን፣ ግብረገባዊነትን፣ ሥርዓትን፣ ግብር ማብላትን፣ ሠው ወዳድነትን፣ ከተከበሩት ወላጆቹ ገሃድ ሕይወት እያየ እየተለማመደ እየቀዳና እየተማረ የማደግ የእድል በር በሰፊው የተከፈተለት ልዑል እግዚአብሔር የረዳውና ያገዘው ብላቴና ነበር።

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ በዘመኑ በሐገራችን ይተገበር እንደነበረው ሁሉ እርሱም ከወንድሞቹና ከእህቶቹ ጋር በመሆን የግል መምህር  ተቀጥሮላቸው የአማርኛ ትምህርቱን በመማር ዳዊትንም ደግሟል።

በመቀጠልም ልጅ ተሥፋዬ ኃይሌ እአአ ከ1960 – 1972 ዓ.ም የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንንና፣ በደጃዝማች ወንድይራድ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ  እና፣ በልዑል አስፋው ወሰን ኮምፕርሄንሲቭ ትምህርት ቤቶች ተምሯል።

ከዚያም ከፍተኛ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ሰሜን አሜሪካ በ1972 ዓ.ም ተጉዞ መጀመሪያም በዊስኮሲን ስቴትና በኒዮርክ ከተማ ጥቂት ቆይቶ ካደረገ በኋላ በሮችስተር ኒዮርክ ኑሮውን አደረገ።

             ኑሮ በአሜሪካ

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ የከፍተኛ ትምህርቱን በ State university of New York(SUNY) @ Brockport በመከታተል በ 1977 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን በ ፖለቲካል ሳይንስ (Political Science)  እንዲሁም የሁለተኛ ዲግሪውን በ 1979 ዓ.ም በ እርባን ፕላኒንግና በፐብሊክ አድምኒስትሬሽን (Urban planning and public administration) ተመርቋል፡፡

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ በሥራውም መስክ ከ 1973 ዓ.ም ጀምሮ በ United Parcel Service (UPS) መስሪያ ቤት በተለያዩ የአገልግሎት መስኮች በማኔጀርነት ሲሠራ ቆይቶ ከ 35 ዓመታት አገልግሎት በኋላ ጡረታ ወጥቷል፡፡

   ቤተሰብ 

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ፣ ከወ/ሮ ሠላማዊት ሠለሞን ጋር ጁላይ 8 ቀን 1984 ዓ.ም በዋሽንገተን ዲሲ ተጋቡ። ትዳራቸውም ለ37 ዓመታት የዘለቀ በፍቅር እና በመተሳሰብ ላይ የተመሰረተና ጸንቶም የቆመ ጋብቻ ነበር። ከዚህም ትዳር ወይዘሪት ኤልሻዳይ ወይዘሪት አብሳራ (ጊጊ) እና  ልጅ ታዲያስ ተስፋዬ የተባሉትን ሦስት ልጆች አፍርተዋል። 

ልጆቻቸውንም በደንብ እና በስነ-ስርዓት እንዲሁም በፈሪሃ እግዚአብሔር ኮትኩተው እና አንጸው አሳድገዋል። ልጅ ተስፋዬ ኃይሌና ባለቤቱ ወ/ሮ ሠላማዊት ሠለሞን በልጆቻቸው ላይ ያፈሰሱት ድካምም ሆነ የዘሩት ፍሬ አፍርቶላቸው ሶስቱም ልጆች ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአንደኛና የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ተቀብለው በተለያየ የሙያ መስክ በሥራ ላይ ተሰማርተው ማየት የውድ አባታቸው ደስታ ነበር።

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ለውድ ባለቤቱ ለ ወ/ሮ ሠላምዊት ሠለሞን እና ዓይቶ ለማይጠግባቸው ልጆቹ የነበረው ፍቅር ከፍተኛ ነበር። ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ሰፊ ልብ የነበረው፣ ሰውን መርዳት የሚያስደስተው፣ መጫወትን የሚያዘወትር ፈገግታም ከገጹ ላይ በጭራሽ ተለይቶት የማያውቅ፣ የቁምነገር ማህደር፣ ሰውን አክባሪ ሰው ነበር።

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ መልካም ባል፣ አባት፣ ወንድም፣ እንዲሁም ጓደኛ ነበረ፡፡ ዘመድ ወዳጅ፣ ጓደኛን አሰባሳቢ፣ የቤተሰብ አውራ በመሆን ወዳጅነትን፣ መረዳዳትን ባጠቃላይ ፍቅር እንዲሰፍን እልፍ ያለ ጥረትና ትጋትን ለማበርከት ደከመኝ ሰለቸኝ የማይል በጎ ሰው ነበር። ልጅ ተስፋዬ የቀደሙትን የወላጆቹን የአሳዳጊዎቹን እራዕይ በትውልድ ፊት ያስቀመጡትን የማዕዘን ድንጋይ ያልዘነጋ ይልቁንም ሕይወቱን፣ ጊዜውን፣ ሃብቱን፣ እውቀቱን፣ ጉልበቱን፣ ባጠቃላይ ያልተሸራረፈ ሙሉ ማንነቱን ማበርከትን ደስታው እና ጥሪውም ያደረገ ሰው ነበር።

        ሽልማት 

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ፣ በተለያዩ የሐገራችን እና የዜጎቿ ጉዳይ ውስጥ የተሻለ ነገን ለማምጣት በሚተገበረው ጥረት ውስጥ የነበረው ጉልህ ማሕበራዊ ተሳትፎና እና ያገኛቸውም ሽልማቶች ዝርዝር እንደሚከተለው ይነበባል።

• የማሕበረ ግዩራን ዘረ ኢትዮጵያ SEED (Society of Ethiopia Established in Diaspora) ከ1993 ዓ.ም ጀምሮ መስራች አባልና የመጀመሪያ ተሸላሚ

• በሮችስተር ኒዮርክ የመንክረ ኃይላ ኪዳነ ምህረት የኢትዮጵያ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን  ከ 1999 ዓ.ም ጀምሮ መሥራች አባል

• በሮችስተር ኒዮርክ የኢትዮጵያውያን ማህበረሰብ ማሕበር ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ መስራችና አባል

• በሮቸስተር ኒዮርክ የኧርባን ሊግ ከ1970 ዓ.ም ጀምሮ አባል እና የ1981 ዓ.ም የሊጉ ተሸላሚ

• የዓባይ ሕዳሴ ግድብ እና በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 የማእከላዊ እና ምዕራባዊ ኒዮርክ የእርዳታ ስብሰባ አስተባባሪ በመሆን ከኢትዮጵያ ኤምባሲ የተሳትፎ እውቅናና ምስጋናም አገኝቷል፡፡

• የፊታውራሪ ስንቄና የእማሆይ ፈለቀች አያኔ የቤተሰብ ማህበር መስራችና ዋና ሰብሳቢ በመሆን እስከመጨረሻዋ እስትንፋሱ ድረስ አገልግሏል።

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ከላይ በተዘረዘሩት እና በሌሎችም ዘርፎች ሁሉ ውጤትን ለማስገኘት ያልተገደበ ጥረቱን የሰጠ ለሐገርና ለወገን ያለውን ከልብ የመነጨ ተቆርቋሪነት ያለማሰለስ ተግብሯል።

            ስለ ልጅ ተስፋዬ ስንቄ ሌሎች ምን ይላሉ?

አቶ ጁሴፔ ኬፔኔ ፣ልጅ ተስፋዬ ኃይሌን ለአመታት ያውቁታል፡፡እናት ሀገሩን ኢትዮጵያን ከልቡ የሚወድ ትህትና የተላበሰ ደግ ሰው ሲሉ ይገልጹታል፡፡

‹‹….. ልጅ ተስፋዬ አሜሪካን ሀገር ከመጣበት ሰአት አንስቶ ኢትዮጵያውያንን ሲረዳ የኖረ ለገንዘቡም ሆነ ለጊዜው ሳይሳሳ መላ ነገሩን የሰጠ ሰው ነው›› ሲሉ ይገልጹታል፡፡

አቶ ጁሴፔ እንደሚገልጹት ልጅ ተስፋዬ ሰውን ትንሽ ትልቅ ሳይል እኩል የሚያይ በጎነትን የተላበሰ ሰው ነው፡፡  ማህበራዊ ሚድያ ከመፈጠሩ በፊት ራሱ ማህበራዊ ሚድያ ሆኖ ሰዎችን ሲያገናኝ የነበረ ቀና አሳቢ መሆኑን አቶ ጁሴፔ ይመሰክራል፡፡ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ታላቅ ከበሬታን የተጎናጸፈው ልጅ ተስፋዮ ቤቱ ሰዎችን በማሰባሰብ ግብዣ በማድረግ ይታወቃል፡፡ ይህም ትልቅ ደስታ የሚፈጥርለትና የሚያረካው ነገር ነበር፡፡  ሰዎች እርቅ ሲፈጽሙ ፤ ሲፋቀሩ ልጅ ተስፋዬ ደስ ይለዋል፡፡   ሰላምን ማምጣት ከምንም በላይ ያስደስተዋል፡፡

ወይዘሮ ቤተልሄም ገድሉ የእናቷ ወንድም ስለሆነው ስለ ልጅ ተስፋዬ ስትናገር ‹‹ ጋሽዬ አሜሪካን ሀገር ከገባን ቀን አንስቶ ልዩ ክብካቤ ሲያደርግልን የነበረ ድንቅ አጎታችን ነው ስትል ይህን ሰው ማጣት ትልቅ ሀዘን መሆኑን ቤተሰቧን ወክላ ተናግራለች፡፡

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ስንቄ  የአያቶቹን ታሪክ እና የቤተሰብ ማህበሩን በወጉ በመምራት  ትልቅ ኃላፊነቱን የተወጣ ሰው ነበር፡፡  ልጅ ተስፋዬ ለእህት ለወንድሞቹ ትልቅ አክብሮትና ፍቅር ያለው ሲሆን ከልጅ ጋር እንደልጅ ከ አዋቂ ጋር እንደ አዋቂ በመሆን ሰውን ደስ ለማሰኘት የሚጥር ሰው ነው፡፡ ከምንም በላይ ኢትዮጵያዊ አንድነት ላይ የጸና አቋም ያለው  ልጅ ተስፋዮ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረጉ ሀገርን በሚለውጡ ፕሮጀክቶች ላይ ቀዳሚ ተሰላፊ ነው፡፡ 

           ፕሮፌሰር መላኩ ላቀው

ፕሮፌሰር መላኩ ላቀው በስታክቶን ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ወይም የኢኮኖሚክስ መምህር በመሆን ያገለገሉ ናቸው፡፡ ልጅ ተስፋዮ ሀይሌን ከ40 አመት  በፊት እንደሚያውቁት ይናገራሉ፡፡ ልጅ ተስፋዬ ሀይሌ የአሜሪካንን ምድር ከ49 አመት በፊት የረገጠ እንደመሆን የሀገሪቱን ጓዳ ደህና አድርገው ከሚያውቁት መካከል አንዱ ነው ይላሉ ፕሮፌሰር፡፡ ከዚህ አንጻር ልጅ ተስፋዬ ሀይሌ የከተማችን የሮችስተር ከንቲባ ነው እያልን እንጠራዋለን ሲሉ ፕሮፌሰር ልጅ ተስፋዬ በኢትዮጵያውያን ማህበረሰቦች ዘንድ የነበረውን ክብር ያወሳሉ፡፡ ከዛሬ 29 አመት በፊት ሲድ የተሰኘውን ሰዎችን የሚያከብር  የእውቅና ሰጪ ተቋም  ከመሰሩቱት ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አንዱ የሆነው ልጅ ተስፋዮ ይህ ተቋም ሰውን የማክበር ትልቅ ግብ እንዲኖረው ያደረገ መሆኑን ፕሮፌሰር  ይመሰክራሉ፡፡

 ልጅ ተስፋዬ እና ጓደኞቹ ይህን ሲድ የተሰኘ ድርጅት በይፋ እውን ካደረጉት በኋላ እና ለሰዎች እውቅና መስጠት ከጀመሩ አንስቶ ሌሎች እውቅና ሰጪ ድርጅቶችም ይህንኑ በመከተል መጀመራቸውን ፕሮፌሰር መላኩ ይናገራሉ፡፡ይህም የእነ ልጅ ተስፋዬ ሀሳብ  ቀናኢነትን የተሞላ መሆኑን ያሳያል ይላሉ፡፡

 ፕሮፌሰር መላኩ ልጅ ተስፋዮን ሲገልጹት እርሱማ መስተዋት ነው ይሉታል፡፡  ‹‹…ለጓደኞቹ ተገን ነው፡፡ በተለይ ሰው ለመርዳት የፈጠነ ነው፡፡ ለገንዘቡ ሳያስብ መስጠትን ዋና መርሁ ያደረገ ደግ ሰው ነው፡፡ በዚህ መልካም ባህሪው ደግሞ ብዙ ሰው ይወደዋል፡፡  አንድን ሰው ሄዶ ስሙን ጠርቶ ወንድሜ እወድሀለሁ በማለት የፍቅርን ስሜት ሰው ላይ የሚያጋባ ሰው ነው፡፡›› በማለት ፕሮፌሰር መላኩ ልጅ ተስፋዮን ገልጸውታል፡፡

 ልጅ ተስፋዮ ሰርግ ሀዘን ላይ ቀድሞ በመገኘት በሰዎች ላይ የሚደርስ ደስታ እና ሀዘን ላይ በመካፈል ኢትዮጵያዊ ባህሉን ያንጸባረቀ ሀገር ወዳድ መሆኑን እነ ፕሮፌሰር መላኩ  ይመሰክራሉ፡፡

        ኢንጂነር አክሊሉ ደምሴ 

  ኢንጂነር አክሊሉ ደምሴ  ደግሞ በኦሀዮ ክፍለ ግዛት የሚኖሩ ሲሆኑ ከዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ጋር ባደረጉት ቆይታ ልጅ ተስፋዮ ገና በወጣትነቱ አሜሪካንን የሚያውቅ በመሆኑ የሀገሩን ዜጎች በብዙ ጎኑ ለመርዳት የቻለ ሰው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ ልጅ ተስፋዮ በሮችስተር ከተማ ያለችው የኪዳነ-ምህረት ቤተ-ክርስቲያን እንድትመሰረት ትልቁን ሚና የተጫወተ ነው፡፡ በዚህም በርካታ ኦርቶዶክስ ክርስቶያኖች እናመሰግነዋለን ሲሉ ኢንጂነር አክሊሉ ስለዚህ ታላቅ ሰው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

  ኢንጂነር አክሊሉ እንደነገሩን ከሆነ ልጅ ተስፋዮ በሮችስተር ከንቲባም የተወደደ እና በተግባሩም የተመሰገነ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜም የሮችስተር ከንቲባ ልጅ ተስፋዬ ቤት ለግብዣ ይመጣ እንደነበር ኢንጂነር አክሊሉ ያስታውሳል፡፡ ይህ የሚያሳየው ልጅ ተስፋዮ በአሜሪካኖች ዘንድ የነበረውን ተቀባይነት ነው፡፡

     ኢንጂነር ሻውል በየነ

ሻውል በየነ በፈረንጆቹ በ1981 ምድረ- አሜሪካን ረገጡ፡፡ ያኔ ሲመጡ ካወቁት ደግ ኢትዮጵያውያን አንዱ ልጅ ተስፋዮ ነበር፡፡

‹‹ ገና  አሜሪካን እንደደረስኩ አንድ ለሰዎች መልካም የሚያስብ ሰው አለ ብለው ልጅ ተስፋዬን አስተዋወቁኝ፡፡ ልጅ ተስፋዬ የእውነትም ሲቀርቡት ደስ የሚል መንፈሱ የተረጋጋ ሰው ነበር፡፡ ያኔ የመጣሁ ሰሞን ለህይወቴ የሚያስፈልገኝን  ምክር የለገሰኝ ትልቅ ባለውለታዬ በመሆኑ ሁሌ አመሰግነዋለሁ፡፡ምን መሆን እንዳለብኝ ፤ ምን መስራት እና መማር እንዳለብኝም ተገቢውን ምክር ለግሶኛል፡፡›› ሲሉ ኢንጂነር ሻውል ስለልጅ ተስፋዬ አጫውተውናል፡፡

 ኢንጂነር ሻውል በየነ ከልጅ ተስፋዮ የሚወዱለት ባህሪይ ላመነበት ጉዳይ እስከመጨረሻው የሚጓዝ መሆኑ ነው፡፡ ልጅ ተስፋዮ አንድ ጉዳይ ጉዳት ያመጣል ብሎ ካመነ ትልቅ ክርክር ይገጥማል፡፡ መጨረሻም ላይ አስረድቶ ሀሳብ የማስቀየር አቅም እንዳለው ብዙዎች ይመሰክሩለታል፡፡

‹‹ ሙዚቃ ሳቅ ጨዋታ የሚወደው ልጅ ተስፋዮ በሰው ላይ ክፉ ነገር ማድረግ አይወድም፡፡ ሰው ሲጠቃ ማየት አይወድም፡፡ ብቻ እርሱ ከትንሽ ትልቁ ጋር ፍቅር በመሆን ያምናል፡፡›› በማለት ኢንጂነር ሻውል በየነ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

      ፍሬህይወት ገብረህይወት

   ፍሬህይወት ገብረህይወት መኖሪያዋን ያደረገችው አዲስ አበባ ሲሆን አጎቷ ልጅ ተስፋዬ ቅን ለሰው አሳቢ መሆኑንም ተናግራለች፡፡ ልጅ ተስፋዬ ህይወቱ ከማለፉ ጥቂት ቀናት ቀደም ብሎ በስልክ አናግሯት እንደነበርም አስታውሳለች፡፡ ህልፈቱን ስትሰማ ትልቅ ዱብ እዳ ነው የሆነባት፡፡ ለመላ ቤተሰቡም መጽናናትን ተመኝታለች፡፡

  ህልፈት 

ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ በደረሰበት የጤና እክል በጤና ባለሙያዎች ሲረዳ ቆይቷል። ውድ ባለቤቱና ልጆቹ እንዲሁም መላው ቤተሰቡ የፍቅር እንክብካቤ ሳያጓድሉበት ድንገታዊ በሆነ ሁኔታ ኦገስት (August) 7 ቀን 2021 ዓ.ም እኩለ ሌሊት ላይ ባለቤቱና ልጁ ባሉበት ከዚህ ዓለም በአካል ተለይቷል። ልጅ ተስፋዬ ኃይሌ በአካል ቢለየንም የዘራው የደከመበትና ያፈራው የመልካምነትና የፍቅር ዘር በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ ታትመው ስለሚኖሩ ዘወትር ሲወሱና ሲታሰቡ ይኖራሉ።   

         የቤተሰብ  መልእክት

ክቡራትና ክቡራን  በልጅ ተስፋዬ ኃይሌ ሕልፈተ ሕይወት ምክንያት ዛሬ በዚህ የመጨረሻ መሰነባበቻ ዝግጅት ለልጅ ተስፋዬ ኃይሌ   ክብራችሁን እና ፍቅራችሁን ለመግለጽ ከቅርብም ይሁን ከሩቅ ከአራቱም አቅጣጫ አገር አቋርጣችሁ ለመጣችሁ የተወደዳችሁ እና የተከበራችሁ ቤተሰቦቻችን፣ ወዳጅ ዘመድና ውድ ጓደኞች በሙሉ በዚህ ፈታኝ እና አሰቸጋሪ የሐዘን ግዜ ከጎናችን በመቆም የሐዘናችን ተካፋይ በመሆን ፍቅራችሁን በተለያየ ሁኔታ ለገለጻችሁልን እና ላጽናናችሁን ሁሉ በውድ ባለቤቱ በወ/ሮ ሠላማዊት ሠለሞን፣ በልጆቹ በወይዘሪት ኤልሻዳይ፣ በወይዘሪት አብስራ (ጊጊ) እንዲሁም በልጅ ታዲዮስ ተሥፋዬ እና በመላው ቤተሰቡ ሥም ጥልቅና ልባዊ የሆነ ምስጋናችንን እናቀርባለን ።

 እግዚአብሔር ያክብርልን። ልዑል እግዚአብሔር የልጅ ተስፋዬን ነፍስ በአጸደ ገነት ያሳርፍልን።

ከልጅ ተስ ፋዬ ኃይሌ ቤተሰቦች በሙሉ።

መዝጊያ ፤ ኢትዮጵያን በአሜሪካ ሀገራቸውን የሚጠቅም በጎ ነገር ይሰራሉ፡፡ የባህር ማዶ ትምህርት ተምረው ሀገራቸውን ለማገዝ በብዙ መልኩ ይጥራሉ፡፡  አንዳንድ ጊዜ አኩሪ የሆነውን ኢትዮጵያዊ ጨዋነት ይዘው በዚህ ባህል አሜሪካ ውስጥ ኑሮን ይመሰርታሉ፡፡ ልጅ ተስፋዮ አሜሪካንን ከ49 አመት ሲያውቃት ይህንን እውቀቱን ሰው ለመርዳት አዋለው፡፡ ሲድን ሲመሰርቱ ዋናው ግባቸው ሰው በህይወቱ እያለ ይመስገን የሚል ነበር፡፡ እና ይህንን ሀሳብ ላለፉት 29 አመት ሲተገብሩ ነበር፡፡ በዚህም ልጅ ተስፋዮ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ ነፍስ ይማር

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች