39. ታምራት አሰፋ  ዓለማየሁ-TAMRAT ASSEFA ALEMAYEHU

      ሁለገቡ ታምራት አሰፋ

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለሙያዎች ህይወታቸው ካለፈ በኋላ እንዳይዘነጉ የመሰነድ ስራዎችን እያከናወነ ይገነኛል፡፡ ከዛሬ 40 አመት በፊት በሬድዮ ብዙዎችን ሲያዝናና እውቀት ሲያስጨብጥ የነበረው ታምራት አሰፋ  መጪው ታህሳስ 9 2014 ሲመጣ ድፍን 20 አመት ይሞላዋል፡፡በእነዚህ 20 አመታት ስለ ታምራት ምን ያህል እንደተነገረ ያወቀ ይመስክር፡፡ ይህ ሰው አቅሙን ሳይቆጥብ ፈጣሪ በሰጠው ድንቅ ክህሎት በትጋት ሲያገለግል ነበር፡፡ ታምራት አሰፋ ከብዙ በጥቂቱ ታሪኩ እንደሚከተለው ይቀርባል፡፡

       የሽሮ ሜዳው ታምራት 

ጋዜጠኛ  ታምራት አሰፋ የተወለደው ፣ የካቲት 03 ቀን 1945 ዓ ም በአዲስ አበባ ከተማ በእንጦጦ ሽሮ ሜዳ አካባቢ በቀድሞ ስሙ ራስ ደስታ ሰፈር ፣ ሃይለ መለኮት መንገድ (የዛሬው ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 04) ነበር ፡፡

አባቱ የቀድሞው የንጉሰ ነገስቱ ክብር ዘበኛ ባልደረባ የነበሩት የመቶ አለቃ አሰፋ ዓለማየሁ ሲሆኑ እናቱ ደግሞ ወ/ሮ ክብነሽ አበባው ይባላሉ፡፡ ጋዜጠኛ  ታምራት ከነኝሁ ወላጆቹ ከተወለዱት አምስት ወንድሞቹና ሶስት እህቶቹ ጋር አብሮ በማደግ እስከ ዕለተ- ሞቱ ድረስ ቤተሰባዊ ህይወቱን ሲመራ ቆይቷል፡፡

የትምህርት ህይወቱን የጀመረው በአምስት ዓመቱ በሰፈሩ ውስጥ በነበረው የቄስ ትምህርት ቤት ሲሆን ለሁለት ዓመት ፊደል ከቆጠረና ዳዊት ከደገመ በኋላ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል በአምሀ ደስታ ትምህርት ቤት የተማረ ሲሆን የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ ከ7ኛ እስከ 12ኛ ክፍል በቀድሞው አስፋወሰን አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ (ምስራቅ አጠቃላይ) ት/ቤት ተምሯል ፣ ከዚያም በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም የመምህርነት ስልጠናውን አጠናቅቆ ከ1969 እስከ 1971 ዓም በወላይታ ሶዶ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በመምህርነት አገልግሏል ፡፡

               የጥበብ ዝንባሌ 

ጋዜጠኛ ታምራት አሰፋ፣ በወጣትነት ዕድሜው ከ5ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ይማር በነበረበት ወቅት በትርፍ ጊዜው በሰፈሩ ውስጥ በተቋቋመው የሕዝባዊ ኑሮ ዕድገት የአንጦጦ ዕድገት ጣብያ በወጣቶች አደረጃጀት ውስጥ የዕድገት ፋና ክለብ ( C- club) አባልና መሪ  በመሆን በወጣቶቹ እንቅስቃሴ በተለይ በሙዚቃ፣ በቴያትርና በስፖርት እንቅስቃሴዎች ንቁ ተሳታፊ ነበር ። በተለይም የምድር ጦር የሙዚቃ ክፍል ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በሙዚቃ ሞያ ሲያሰለጥን አቶ ታምራትም የዚሁ ዕድል ተጠቃሚ በመሆን ሳክስፎን በሚባል የሙዚቃ መሳሪያ በመሰልጠንና የሙዚቃ ቡድን አባል በመሆን ተሳትፏል ፡፡

           ታሪክ ተጠብቆ እንዲቆይ

አቶ ታምራት ፣ በ1971 በኢትዮጵያ ሬዲዮ ጣቢያ ሲቀጠር ሥራ የጀመረው በድምጽ ላይብረሪያንነት ሙያ ሲሆን በክፍሉ ውስጥ የተከማቹትን ንግግርና ሙዚቃ የተቀዳባቸውን ቴፖች መመዝገቢያ ካታሎግ በማዘጋጀትና ኦሪጅናል ቴፕ ከላይብረሪው ሳይወጣ በኮፒ የሚሰራበትን ሁኔታ ከበላይ አለቆቹ ጋር በመነጋገር ታሪክ ተጠብቆ እንዲቆይ የራሱን ከፍተኛ ሚና ተወጥቷል ፡፡

በላይብረሪያንነት ሥራው ምክንያት ከፕሮግራም አዘጋጆች ጋር በፈጠረው የስራ ግንኙነት መነሻ የፕሮግራም አዘገጃጀትን ተግባር ከአንጋፋዎቹ ከነአቶ ታደሰ ሙሉነህ መማርና መለማመድ በመቻሉና በፈቃደኛነት አብሯቸው በመስራት ያሳየውን የሥራ ፍላጎትና ቅልጥፍናውን ተገንዝበው በሰጡት ምስክርነት  ወደዚሁ ክፍል በመዛወር  የሥራ ፍላጎቱን ለማሳካት ችሏል ፡፡

በሬዲዮ ጣቢያው የመዝናኛ ፕሮግራሞችን አጠናክሮ ለመስራት በተደረገው እንቅስቃሴ

ንቁና ግንባር ቀደም  ተሳታፊ በመሆን በተለይም ፣

የእሁድ ጠዋት መዝናኛ ፕሮግራምን ፣

    በየመስሪያ ቤቱ እንዲካሄድ ያዘጋጁትን “ እርስዎም ይሞክሩት “ በመባል ይታወቅ

     የነበረውን  የጥያቄና መልስ ፕሮግራምን ፣

    የቅዳሜ ምሽት የባህር ማዶ ምርጥ ሙዚቃ ፕሮግራምን ፣

  የተማሪዎች የጥያቄና መልስ ፕሮግራምን ፣

ከቅርብ የስራ ጓዶቹ (እነ ታደሰ ሙሉነህ ፣ ንጉሴ አክሊሉ ፣ አባይነሽ ብሩ ፣ መዓዛ ብሩ፣ አሊ አብዶ ሂጅራ፣ ) ጋር በማዘጋጀት በሕዝብ ዘንድ ታላቅ ተወዳጅነትን ያተረፈና በተጨማሪም በዋና ዋና በዓላት በቀጥታ ስርጭት (LIVE ) ፕሮግራሞችን ያለአንዳች ችግር በመስራት ለዛሬዎቹ የኤፍ ኤም (FM) ፕሮግራም አዘጋጆች ፋና ወጊ በመሆን በሥራ ባልደረቦቹም ሆነ በአድማጮቹ አድናቆትንና ታዋቂነትን ያገኘ፣ ባጠቃላይ ለ23 ዓመታት  በሬዲዮ ጋዜጠኝነት አገልግሎት የሰጠ አንጋፋና ተወዳጅ ጋዜጠኛ  ነበር ፡፡

 ለሥራው በነበረው ከፍተኛ ፍቅርና ለአድማጮቹም በነበረው ልዩ ክብር ታሞ በነበረበት ጊዜ ሳይቀር በሰው ድጋፍና እርዳታ እየታገዘ ፕሮግራሙን ያካሂድና ይመራ  እንደነበረ ከቤተሰቦቹና የዓይን ምስክርነት ከሰጡ ሰዎች መገንዘብ ይቻላል ፡፡

ጋዜጠኛ  ታምራት  ለኪነ- ጥበብ ካለው ከፍተኛ ፍቅር የተነሳ በኢትዮጵያ የስነ- ጥበባትና የመገናኛ ብዙሀን የሽልማት ድርጅት የቦርድ አባል በመሆን ሙያዊ አገልግሎቱን አበርክቷል ፡፡

             ታምራት በሌሎች አንደበት 

ታምራት አሰፋ ጋር አብረውት የሰሩ ሁሉ ያሳይ የነበረውን ልዩ ትጋት ያደንቃሉ፡፡ ከታምራት አሰፋ ጋር ከ1974 ጀምሮ እንደሚተዋወቅ የሚናገረው ጋዜጠኛ በልሁ ተረፈ የታምራት አሰፋን ሁለገብ እውቀት ሁልጊዜም ያደንቅ ነበር፡፡ በተለይ በእሁድ ጠዋት ፕሮግራምና በእሁድ ከሰአት የዝክረ-ሰንበት መሰናዶ ታምራት አሰፋ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን ፕሮግራሙን በአድማጭ ዘንድ ተወዳጅ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ያኔ በየተማሪ ቤቱ እየሄዱ የጥያቄና መልስ ውድድር ሲያደርጉ  ታምራት አሰፋ ጥያቄዎችን በማውጣትና መድረኩን በጥሩ ሁኔታ በመምራት ሚናው ትልቅ እንደነበር በልሁ ያስታውሳል፡፡

‹‹….. ታምራት ቅን ሰው ነው፡፡ ለሙያው ቅድሚያ የሚሰጥ ጠንካራ ባለሙያ ነበር›› ሲል ጋዜጠኛ በልሁ ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡  ከሰው ጋር በቀላሉ የሚግባባው ታምራት በተለይ  የኢትዮጵያ ሬድዮ የድምጽ ላይብረሪ ውስጥ ይሰራ በነበረበት ጊዜ ንግግሮችና ዜማዎች በወጉ ተሰንደው እንዲቀመጡ ማድረጉ በብዙዎች ያስመሰግነዋል፡፡

‹‹ … ታምራት ሀሳብ ስትሰጠው ያለ አንዳች ማመንታት የሚቀበል ሰው ነው፡፡ ለስራው እስከጠቀመው ድረስ የሚሰጠውን   አስተያየት ተቀብሎ ማሻሻያ ያደርጋል፡፡ በዚህ ባህሪውም ብዙዎች አድናቆታቸውን ይቸሩታል ›› ሲል በልሁ ሀሳቡን ሰንዝሯል፡፡

ተራኪ እና ጋዜጠኛ ደጀኔ ጥላሁን በበኩሉ ከታምራት ጋር በ1980ዎቹ ግድም በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም ላይ አብሮ መስራቱን ይናገራል፡፡ በደጀኔ እይታ ታምራት በ1950ዎቹ በ1960ዎቹ ወጥተው የነበሩ ሙዚቃዎችን  ጥንቅቅ አድርጎ ያውቃቸዋል፡፡ ከድምጽ ላይብረሪያንነት ወደ ሚድያ ሰውነት ሲሸጋገር ያኔ ድምጽ ላይብረሪ ሳለ ያከማቸው እውቀቱና ልምዱ በጣም ጠቅሞት ነበር፡፡

ደጀኔ የታምራትን ሁለገብ የሆነ ክህሎት ያደንቃል፡፡ ታምራት ለመዝናኛው ኢንዱስትሪ የተፈጠረ መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ በተለይ የቀጥታ ላይቭ የመድረክ ስራዎችን ሲሰራ ማንም አያክለውም፡፡ ደጀኔም ይህን የታምራት የመድረክ አያያዝ ብቃት ያደንቃል፡፡

              ከወንድሙ ከአቶ በድሉ አሰፋ የተሰጠ አስተያየት ፣

“ ታምራት ከኔ ቀጥሎ የተወለደ ታናሽ ወንድሜ ሲሆን የተወለድነው በተከታታይ፣ በአንድ ዓመት ተኩል የዕድሜ ልዩነት ስለነበረ ዕድገታችንና ግንኙነታችን እንደወንድማማች ብቻ ሳይሆን እንደቅርብ ጓደኛ ነበር ፣ ከታምራት የህይወት ተሞክሮዎችና የሞያ ጥረቶች በምሳሌነት ከሚጠቀሱት ጥቁቶቹ ፣

- ለመላው ቤተሰቡ በአጠቃላይና ለአባታችን ደግሞ በተለይ ልዩ ፍቅር ነበረው ፣ ጨዋታ አዋቂና ተወዳጅ በመሆኑ እርሱ ባለበት ጊዜ ሁሉ ቤቱ ይደምቅና ደስታው ይበዛ ነበር፣

- በአንድ ወቅት በቤተሰብ ሠርግ ላይ ምግብ ቀርቦ ብሉ ሲባል አባታችን ስላልነበረ ታዳጊው ወጣት ታምራት አባቴ ካልመጣ አልበላም ብሎ የተለየበትንና በሌላ ጊዜ ደግሞ ለበዓል የቀረበ መጠጥን አባታችን ካልመጣ አይከፈትም በማለት ቤተሰባዊ ፍቅሩን ይገልጽ የነበረበትን ሁኔታ አስታውሳለሁ ፣

- ለሥራው የነበረው ልዩ ፍቅር፣ ለዝግጅቱ ማማርና ተቀባይነት ያደርግ የነበረው ጥንቃቄ በጣም የተለየና ለሌሎችም አስተማሪ ሊሆን የሚችልና በሙሉ ዕውቀት ላይ በመመስረት ይዘጋጅ የነበረ ነው ፣ የሙዚቃ ፕሮግራም ሲያዘጋጅ በቅድሚያ ስለ ሙዚቃዎቹ ጥናት በማድረግ፣ የተጫዋቾቹን ማንነት፣ የሙዚቃዎቹን ይዘት፣ በሙዚቃዎቹ ውስጥ ያሉትን መሳሪያዎች፣ ወዘተ ከተለያዩ ማጣቀሻዎች እያነበበ ለአድማጮቹ የተሙዋላ ፕሮግራም ያቀርብ ነበር፣

- ታምራት ዘፈን የመዝፈን ፣ የሙዚቃ መሳሪያ የመጫወት ፣ በስፖርት የመሳተፍ ፣ ቀልዶችን የማቅረብ ፣ ጽሁፎችን የማዘጋጀት ፣ ሀሳቡን በግልጽና በድፍረት የማቅረብ ፣ ለጉዋደኞቹና ለሥራ ባልደረቦቹ አቅሙና ችሎታው በፈቀደ መጠን ድጋፍና እገዛ በማድረግ የታወቀ ፣ ወዘተ ሁለ-ገብ ዕውቀት የነበረው በመሆኑ ሥራው የተሙዋላ ፣ እርሱ በሚገኝበት ቦታ ሁሉ ስብስቡ የሚደምቅ፣ የሚያስቀናና የሚናፈቅ ነበር ።

- ከአድማጮቹ በየጊዜው የሚላኩለትን በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ የፖስታ መልዕክቶችን ያለመሰልቸት በማንበብና በመመዝገብ ለቀጣዩ የፕሮግራም ዝግጅት በግብዓትነት በመጠቀም አድማጮቹን የሚያሳትፍና የፕሮግራሙ የጋራ ባለቤት እንዲሆኑ ያስቻለ ጋዜጠኛ ነበር ፣

- በእሁድ ጠዋት የመዝናኛ ፕሮግራሙ ላይ ወጣትና ጀማሪ ድምፃውያንን በመጋበዝና ለህዝብ በማስተዋወቅ ዛሬ ታዋቂ ድምፃውያን እንዲሆኑ ታላቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ነው ፣

- በደርግ የመጨረሻዎቹ ዘመን ለስልጠና ወደ አውሮፓ ተልኮ በነበረበት ወቅት በዚያው እንዲጠፋ ቢመከርም ሀገሬን አልክድም በማለት የተመለሰና ለሀገሩ ያለውን ታማኝነት በተግባር ያስመሰከረ የጋዜጠኝነት ሞያውን እስከህይወቱ መጨረሻ ድረስ አክብሮና አስከብሮ የቆየ ነበር፣

የአቶ ታምራት ባለቤት ወ/ሮ መብራት ስብሀቱ የምትባል ወጣት የባንክ ባለሞያ ነበረች ፣ የትዳር ህይወታቸውን በሚገባ ሳያጣጥሙ ባጭሩ በመቀጨታቸው ሀዘኑ ምንጊዜም በውስጣችን ይኖራል ።

         ዝናሽ ማሞ- ስለ ታምራት አሰፋ

 ታምራት አሰፋ ሞት  ቀደመው እንጂ ብዙ የመስራት አቅምና ተነሳሽነትን የነበረው ታታሪ ጠንካራና ደፋር ጋዜጠኛ  ነበር

አብሬው በሰራሁባቸው አመታት ስራውን ቀለልና ዘና እድርጎ የመስራት ዘይቤውን እወድለት ነበር::

የማዝናናት ባህርይን የተላበሰሙዚቃን በመምረጥ የተካነ፤ ተራሩጦ  ለመስራት ያልደከመ ነበር::

የቅዳሜ ምሽት ምርጥ ሙዚቃም በብዙ አድማጮች ጆሮ ውስጥ የተቀረፀ  እስከሚመስል  ድረስ ተወዳጅ ነበር::

          እሸቱ ገለቱ ስለ ታምራት

‹‹ ታምራትን ሳውቀው 28 አመት ይሆነኛል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተመርቄ በ1985 መጀመሪያ አካባቢ ኢትዮጵያ ሬድዮን ካላመዱኝ ቀዳሚ ሰዎች አንዱ ነው፡፡ ያኔ ላያቸው ከምጓጓቸው ጋዜጠኞች አንዱ ታምራት አሰፋ ነበር፡፡ ታምራት አሰፋን ገና ተማሪ ሳለሁ የሬድዮ አድማጭ በነበርኩበት ጊዜ አድናቂው ነበርኩ፡፡ እና ገና ስተዋወቀው  የነበረውን ሞገስ አልረሳውም፡፡ ቁመቱ ረጅም ነው፡፡ ብቻ የሚገርም ሰብእና የነበረው ነበር፡፡ ሰው ሲያወራ በትህትና የተሞላ ነበር፡፡በተጨማሪም ኢትዮጵያዊ ስነ-ምግባርን የተላበሰ ሰው እንደነበር ገና ስተዋወቀው አስተውዬ ነበር፡፡መስክ ለመጀመሪያ ጊዜ ስወጣ ያኔ ስለ ፊልድ ጋዜጠኝነት በቂ እውቀት እንዳገኝ የረዳኝ ታምራት አሰፋ ነበር፡፡ ያኔ ከትግርኛ ዝግጅት ክፍል ነጋ ተገኝም አብሮን ነበር፡፡ እና ታምራት አሰፋ የመስክ ዘገባ ስሰራ በቂ ስልጠና  የሰጠኝ ሰው ነው፡፡ ያኔ መስክ የሄድነው ወሎ ነበር፡፡ ታዲያ ያኔ ታምራታ በዘፈን የማውቃትን ወሎን በሚገባ እንዳስጎበኘኝ አስታውሳለሁ፡፡ በስልክ ስለሚሰራ ዘገባም በቂ ትምህርት ሰጥቶኛል፡፡ በኋላም  ዘነበ ወርቅ በሚገኘው ኢትዮጵያ ሬድዮ ግቢ ውስጥ ጎረቤት ሆነን አንድ ላይ ኖረናል፡፡ በዚህም አጋጣሚ ጥብቅ የሆነ ቤተሰባዊ ቅርበት አዳብረን ነበር፡፡ ከታናሽ ወንድሞ ብርሀኑ አሰፋ / ኢትዮጵያ ሬድዮ በቴክኒክ ክፍል 10 አመት የሰራ . ጋርም በጣም እንግባባ ነበር፡፡ በየወሩ ቤት ለቤት እንጎበኛኝ ነበር፡፡ ትዝ ከሚሉኝ መካከል ልባርጋቸው ሽፈራው   አንዱ ጎረቤቴ ነበር፡፡ ሁለተኛው ልጄ እዮብ እሸቱን  ታምራት አጎትህ ነኝ ይለው ነበር፡፡  ልጄን ተማሪ ቤት ስሸኘው በቀዳሚነት ታምራትን አሳይቼ ነው፡፡ የዚህን ያህል ቤተሰባዊ ቅርርባችን የጠነከረ ነበር፡፡ ልጄ ኢዮብ በተኮለተፈ  አንደበት ጋሽ ታሜ  ብሎ ነበር የሚጠራው፡፡

ታምራት ስራውን በጣም ከመውደዱ የተነሳ ቤቱ ሁሉ ይሰራ እንደነበር አስታውሳለሁ፡፡ ታምራት የመዝኛኛ ፕሮግራም እንደመስራቱ ለቃላት አገባቡ ለአረፍተ-ነገር አመራረጡ እጅግ የሚጨነቅ ነበር፡፡ይህ ለአድማጭ ያለውን አክብሮት ያሳያል፡፡ የቃላት ምርጫ መሰረታዊ እንደሆነ የሚያምን ሰው ነው፡፡ ስቱዲዮ ከመግባቱ ቀደም ብሎ ቤቱ የሚያነበውን ስክሪፕት በደንብ ይለማመዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ሀሳቡ ውስጡ ሰርጾ መግባቱን ሲያረጋግጥ ወደ ስቱዲዮ ይገባል፡፡ ዛሬ ያሉት የሬድዮ ጋዜጠኞች ከእርሱ አንድ ነገር ሊማሩ ይገባቸዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

የታምራት ሰርግ በ1986 ግድም ነበር፡፡ ቦታውም በሀገር ፍቅር ቴአትር ነበር፡፡ የሀገራችን አሉ የሚባሉ የሙዚቃ ሰዎች ነበሩ፡፡ እነ አለማየሁ እሸቴ ፤ ጥላሁን ገሰሰ ሁሉ ታድመው ነበር፡፡ ጥላሁን በታምራት ሰርግ እለት አንድ ዜማ ተጫውቶ መሄዱን አስታውሳለሁ፡፡ የቴአትር ሰዎችም ነበሩ፡፡ ትልቁ ነገር ታምራት ለሰው ያለው አክብሮት  ትልቅ ነበር፡፡ በጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ  በተለይ ስለመዝናኛው ስናወራ ታምራት አሰፋን እንዲህ እንደዋዛ የምንዘነጋው አይሆንም፡፡ ታምራት ብሉይ የሆኑ የድሮ ፊልሞችንም ማየት ይወድ ነበር፡፡ ይህ ሰው ዛሬ ህይወቱ ቢያልፍም በዚህ መልኩ መታወሱ ታሪክ ተቀብሮ እንደማይቀር የሚነግረን ነው፡፡  

ጋዜጠኛ ታምራት አሰፋ  ባደረበት ህመም ሳቢያ በህክምና ሲረዳ ቆይቶ ታህሳስ 8 ቀን 1994 ዓ ም በተወለደ በ 49 ዓመቱ ከዚህ ዓለም በሞት በመለየቱ ስርዓተ ቀብሩ በማግስቱ ታህሳስ 9 ቀን 1994 ዓ ም ቤተ ሰቦቹ፣ የሥራ ባልደረቦቹ፣ ወዳጅ ዘመድና አድናቂዎቹ በተገኙበት በቀጨኔ ደብረ ሰላም መድሀኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል ።

መዝጊያ ፤ ታምራት ለሀገራችን የመዝናኛ ኢንዱስትሪ አንድ ጡብ ያኖረ ታላቅ ሰው ነው፡፡  እሁድ ጠዋት ፕሮግራም የብዙዎች የመዝናኛ አማራጭ በነበረበት በዚያን ዘመን ታምራት አድማጭን የሚመጥን መሰናዶ አየር ላይ በማዋል የበኩሉን አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ በተለይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሬድዮ አርካይቭ በካታሎግ እንዲደራጅ ብዙ የደከመ ነው፡፡ ዛሬ እንደልባችን አርካይቭ መጠቀም የቻልነው  ታምራት እና ባልደረቦቹ ታሪኩን ሳይጠፋ ስላስቀመጡልን ነው፡፡ ይህ እንደትልቅ ሚና የሚቆጠር ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ  አዘጋጆች ሰዎች ላኖሩት  ለሁሉም ትልቅ አሻራ እውቅና ይሰጣል፡፡ ታምራት ባለፉት 20 አመት በሚድያው ላይ ባይኖርም ያበረከተው አንድ ውለታ ግን እርሱ ቢያልፍም  ታሪኩ ግን ዛሬ ሊዘከር በቅቷል፡፡ ታምራት አሰፋ በራሱ ወርቃማ ዘመን የራሱን አድናቂዎች ያፈራ የዘመኑ ዝነኛ ነበር፡፡ በየተማሪ ቤቱ ዝክረ-ሰንበትን  ሲያወዳድር በ1986 የዛሬ 27 አመት የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ  ተመልክቷል፡፡ በተለይ በኮከበጽባህር ተማሪ ቤት የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ የ9ኛ ክፍል ተማሪ ሳለ ተወዳዳሪ ሆኖ ታምራትን ቀርቦ ለማነጋገር እድሉን አግኝቶ ነበር፡፡ ታምራት ፈገግታ የሚያዘወትር ቀለል ያለ ሰው ነበር፡፡ ይህ ሰው የድምጹ ተፈጥሯ ለዛ ፤ ሁሉ ነገሩ ለሚድያ እንደተፈጠረ መመስከር ይቻላል፡፡ ገና በ49 አመቱ ህይወቱ ያለፈው ታምራት ቢኖር ብዙ ሊሰራ እንደሚችል ይታመናል፡፡  በሚድያው አለም በ23 አመት ውስጥ ብዙ ሰርቶ  ስሙን በበጎ ጎኑ ለማስጠራት ችሏል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ከ20 ፤ ከ30 ፤ ከ40 አመት በፊት ለሀገር ሰርተው  ህይወታቸው ያለፈ ነገር ግን የተዘነጉ ብዙ አሉ፡፡ እነዚህን ማስታወስ የሁላችንም ፋንታ ነው፡፡ ሀገር ማለት በአጋጣሚ ሳይሰሩ የታወቁ ሰዎች መኖሪያ ሳትሆን  የሰሩ ሰዎች ደረታቸውን ነፍተው በኩራት የሚኖሩባት ጎጆ ነች፡፡ ይህን የታምራትን ታሪክ ለመጪው ትውልድ ስናቆይ መጪው ትውልድ እነማን ነበሩ? ለሚለው በቂ መልስ እንዲያገኝ ነው፡፡ / የዚህ ግለ-ታሪክ ሙሉ ዝግጀት በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተከናወነ ሲሆን የታምራት አሰፋ ታሪክ በዚህ መልኩ እንዲቀርብ የረዱንን .1 ዝናሽ ማሞን 2. አቶ ብርሀኑ አሰፋን  3 አቶ በድሉ አሰፋን ማመስገን እንወዳለን፡፡ ይህ በ1060 ቃላት ተሰንዶ የቀረበ ታሪክ ዛሬ ቅዳሜ ነሀሴ 8 2013 በተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የፌስቡክ ገጽና በዊኪፒዲያ ላይ ወጣ፡፡ አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው  ይወጣል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች