38. ንጉሴ ተፈራ / ዶክተር/ Negussie Tefera
50 አመት በትጋት
ተወዳጅ ሚድያ እና
ኮሚኒኬሽን ለሀገር ውለታ የዋሉ ሰዎችን ታሪክ በዚህ የዊኪፒዲያ ገጽ ሲያወጣ እንደነበር ይታወቃል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ታሪካቸውን
የምንዘክርላቸው ሰው ዶክተር ንጉሴ ተፈራ ናቸው፡፡ ዶክተር በሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ በሀገራችን ሊዘነጋ የማይቻል ውለታ
የዋሉ ሲሆን የዘንድሮ የ2013 የበጎ ሰው እጩም ናቸው፡፡ ዶክተር ንጉሴ የህይወት የትምህርትና የስራ ተሞክሯቸው ለብዙዎች
አስተማሪ በመሆኑ እንደሚከተለው ታሪካቸውን እናቀርባለን፡፡
ብላቴናው- አንባቢ
ዶክተር የካቲት 12
ቀን 1940 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ነበር የተወለዱት፡፡ አብዛኛውን የልጅነት ዘመናቸውን ልዩ ስሙ አዲሱ ገበያ በሚባለው ሰፈር ነበር ያደጉት፡፡ ገና በልጅነት
የቄስ ትምህርት ሩፋኤል አጠገብ ከሚገኙ መምህር ዘንድ ተምረዋል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም ቁስቋም በሚባል ተማሪ ቤት ተምረዋል፡፡ አባታቸው በአንድ ወቅት ወታደር ከዚያም በጥብቅና ስራ የሚተዳደሩ ሰው
ነበሩ፡፡ እና አባት ተፈራ እምሩ በየጊዜው ጋዜጣ ይገዙ ነበር፡፡ በተለይ አዲስ ዘመን የሁል ጊዜም ምርጫቸው ነበር፡፡ በጊዜው
ገና ታዳጊ የነበሩት ብላቴናው ንጉሴ ከአባታቸው ጋዜጣ እየተቀበሉ ያነቡ ነበር፡፡ እናታቸው የላም ወተት ስለነበራቸው
እናታቸውንም በመርዳት ትልቅ እገዛ አድርገው ነበር፡፡ ብላቴናው ንጉሴ
እናቱም መጽሀፍ እንዲገዙለት ያደርግ ነበር፡፡ የንባብ ፍላጎቱንም በዚህ አጋጣሚ አሳደገ፡፡ ታዳጊው ንጉሴ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተፈሪ መኮንን ሲማር በክርክር
ክበብ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርግ ነበር፡፡
ትምህርት
ዶክተር ንጉሴ
የጋዜጠኝነት ትምህርት በመላው አፍሪካ የኮምዩኒኬሽን ማሰልጠኛ ተቋም(AACC) ናይሮቢ፣ ኬኒያ (እ.ኤ.አ. 1972)
አጠናቀዋል፡፡
ፖለቲካል ሳይንስና
ሥነ-መንግሥት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ (1966 ዓ.ም.) የተማሩ ሲሆን
ሁለተኛ ዲግሪያቸውንም በሚዲያና በጋዜጠኝነት ሙያ (M.Ed) በእንግሊዝ አገር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌልስ ኮሌጅ ኦፍ
ካርዲፍ (እ.ኤ.አ. በ1986) አጠናቀዋል፡፡
3ኛ ዲግሪያቸውንም
በ Development Communication በእንግሊዝ አገር ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ዌልስ (እ.ኤ.አ. 1989) ለማግኘት ችለዋል፡፡
• በሚዲያ
ኮሚንኬሽንና ሊደርሺኘ የተለየ ሥልጠና (ስፔሻላይዝድ ትሬይኒንግ) የወሰዱባቸው፡−
o በአሜሪካን አገር
በስምንት ስቴቶች የተደረገ የ5 ሳምንት ጥናታዊ ኘሮግራም (United States Government Cultural and
Educational Exchange Program December
1989 – January 1990)
o ኮርኔል
ዩኒቨርሲቲ፣ ኒውዮርክ፣ አሜሪካ (እ.ኤ.አ. በ1989)
o ጆን ሆኘኪንስ
ዩኒቨርሲቲ፣ ቦልቲሞር፣ አሜሪካ (እ.ኤ.አ. በ1990)
o በተባበሩት
መንግሥታት የሥነ-ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤት (UNFPA) የተዘጋጀ በPopulation Communication Strategy
Development ናይሮቢ ማስ ሚዲያ ኢኒስቲትዩት ኬኒያ(እ.ኤ.አ. 1993)
o ኢንዶኔዥያ የሥነ
ሕዝብ ኮምንኬሽን ጥናት ኢንስቲትዮት (BKKBN) ጃካርታ (እ.ኤ.አ. 1994)
o ኢንተርናሽናል
ሊደርሺኘ ትሬኒንግ ማዕከል፣ ሳንታ ክሩዝ፣ ካሊፎርኒያ፣ አሜሪካ (እ.ኤ.አ. በ1997)
o ሀጋይ አድቫንስድ
ሊደርሺፕ ኢንስቲትዩት ሃዋይ፣ አሜሪካ (እ.ኤ.አ.2002)
o ዩኒቨርሲቲ ኦፍ
ኒውዮርክ፣ ኒው ዮርክ ሲቲ አሜሪካ (እ.ኤ.አ. 2004)
o ዩኒቨርሲቲ ኦፍ
ሳውዘርን ካሊፎርኒያ (Anneberg School of Communication) ሎስ አንጀለስ፣ ካሊፎርኒያ፣ አሜሪካ (እ.ኤ.አ.
2ዐ15)
o በአውሮፓ፣
በአሜሪካ፣ በካናዳ፣ በአፍሪካ፣ በአውስትራሊያና በላቲን አሜሪካ በሚገኙ በርካታ አገሮች የተለያዩ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን የመካፈል፣
ጥናታዊ ጽሑፎችን የማቅረብና ትምህርታዊ ጉብኝት የማድረግ እድል ገጥሟቸዋል፡፡
1.
የሥራ አገልግሎትና ልምድ
1.1 የሚዲያና
የሥነ - ጽሑፍ ሥራ ባለሙያና አስተባባሪ − ሳውዘርን ባፕቲስት ኮንቬንሽን ሚዲያ አገልግሎት (1962−1968) ሳውዘርን ባኘቲስት ኮንቬንሽን ሚዲያ አገልግሎት በነበሩበት ወቅት ሁለት
መጽሐፍትን ጽፈዋል፣ የተልዕኮ ትምህርት የተዘጋጁ 5 መጽሐፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ ተርጉመዋል፡፡
1.2 ብሥራተ-
ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ (RVOG) (1964-1968) #የፍሬ- ነገሮች ማህደር; እና #የእሁድ ምሽት ልዩ ኘሮግራም፡ አዘጋጅ
ሆነው (ከ3 አመት በላይ በፍሪላንሰርነት) ሰርተዋል፡፡
o በብሥራተ-ወንጌል
ሬድዮ ጣቢያ የፕሮግራም አዘጋጅ በነበሩበት ወቅት በእውቅ ፕሮግራም አዘጋጅነት፣ ከወቅቱ የፖስታና ቴሌኮምንኬሽን ሚኒስትርና
የመካነ- ኢየሱስ ቤተ-ክርስቲያን ኘሬዚዳንት ከነበሩት ከክቡር አቶ አማኑኤል አብርሃም እጅ ልዩ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
o በ1966 እና
1967 ዓ.ም. ላይ በብሥራተ- ወንጌል ሬዲዮ ጣቢያ ባቀረቧቸው የተለያዩ አለም አቀፍ የፖለቲካ ትንተናዎች የተነሳ በወቅቱ
የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት የነበሩት መንግሥቱ ኃይለማርያም ጠርተው አነጋግረዋቸዋል፡፡ ይህንንም ተከትሎ በመንግሥት ጥሪና ውሳኔ ወደ
ኢትዮጵያ ሬድዮ ተዛውረው በፖለቲካ ተንታኝነት (Political Commentator) እንዲሰሩ ተመድበዋል፡፡
1.3 በኢትዮጵያ
ሬዲዮ ከ1968 ዓ.ም. እስከ 1972 ዓ.ም. ድረስ ያገለገሉ ሲሆን በተለይ በምርመራ ጋዜጠኝነት ሙያ ሰፊ የሆኑ ሀገራዊ
ሥራዎችን አከናውነዋል፡፡ ከምናየውና ከምንሰማው÷ በተሰኘው ኘሮግራማቸው ቀርበው በሕዝብ ዘንድ እንዲታወቁ ካደረጓቸው ሥራዎቻቸው
መካከል የሞዝቮልድ ኩባንያ፣ የሲንጀር ኩባንያ፣ የብሔራዊ ሃብት ልማት ሚኒስቴር ታሪክ፣ አስታዋሽ ያጡት የኢትዮጵያ ታሪካዊ
ቦታዎች ከባሕር ዳር እስከ አክሱም፣ የብሔራዊ ባንክና የውጭ ምንዛሪ ማሸሽ ታሪክ፣ ሃላይደጊና የአፋር ሰፈራ ጉዳይ የተደበቀው
ሚስጥር፣ የአዲስ አበባ ስቴድየም ገጽታና ጠቀሜታ፣ አዋሽ ሸለቆና የውሎ አበል ታሪክ፣ የደንና ዱር አራዊት ባለሥልጣንና
ተቆጣጣሪ ያጣው የሀብት ብክነት የሚመለከቱ በምርመራ ጋዜጠኝነት ውጤት ከተገኘባቸውና በመንግሥት እርምጃ ከተወሰደባቸው ሥራዎች
ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ በሃላይደጊ በአፋር ሰፊራ ጉዳይ ላይ ያቀረቡትን ሪፖርት
ለማጣራት ሚኒስትሮቻቸውን ይዘው ቦታው ድረስ ሄደዋል፡፡
1.4 የምርት
ዘመቻና የማዕከላዊ ኘላን ጠቅላይ መምሪያ (ከ1971-1981)
o በመጀመሪያ
በፖለቲካና ማስታወቂያ ጉዳይ በብሔራዊ ቋንቋዎች በመንግሥት ሚዲያ የሚቀርቡ ልማት ነክ ኘሮግራሞች ማስተባበሪያ ኃላፊ፣
o ከዛም የዘመቻ
መምሪያው የማስታወቂያና የሕዝብ ግኑኘነት ጉዳይ ኃላፊ፣
o የማዕከላዊ ኘላን
ጠቅላላ መምሪያ ወይም ዘመቻ መምሪያ በሚባለው የማስታወቂያና የሕዝብ ግኑኝነት ኃላፊ ሆነው በሚያገለግሉበት ወቅት የሀገሪቱ
ኘሬዚዳንት በ1973 ዓ.ም. አቋቁመውት በነበረው የጸረ ምዝበራና ብኩንነት ብሔራዊ ኮሚሽን ከመደበኛ ሥራቸው በተጨማሪ አባልና
የቅስቀሳና ኘሮፖጋንዳ ኮሚቴው ደግሞ ዋና አስተባባሪ እንዲሆኑ በፕሬዚዳንቱ በስማቸው በተጻፈ ደብዳቤ ተመድበው ሰርተዋል፡፡
ከዚሁ ጋር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የተዘጋጀውና ለአንድ ወር ለቆየው የመጀመሪያው ብሔራዊ የጸረ ምዝበራና ብኩንነት አውደ
ጥናትና ኤግዚቢሽን በማዘጋጀት ቁልፍ ሚና ተጫውተዋል፡፡ በወቅቱም ምዝበራና ብኩንነትን የሚመለከቱ በሬዲዮና በቴሌቪዥን የቀረቡና
እንዲሁም በጋዜጦች የታተሙ ከሃያ አምስት የሚበልጡ ጥናታዊ ጽሑፎችን አዘጋጅተው አቅርበዋል፡፡
o #የምርት ዘመቻ;
የሚል መጽሔት በመጀመር ከአራት ዓመት በላይ አዘጋጅ ሆነው ሠርተዋል፡፡
o ዘመቻ መምሪያ
የአስር አመቱን መሪ እቅድ ባዘጋጀበት ወቅት የልማት ኘላን ዝግጅት ታሪክ በኢትዮጵያ የሚለውን እንዲያዘጋጅ የተቋቋመው ኮሚቴ
ሰብሳቢ ሆነው ሠርተዋል፡፡
o ስለአስር ዓመቱ
መሪ እቅድ ጥናታዊ ጽሑፍ አዘጋጅተው በኢትዮጵያ ኘሬስ መምሪያ ሥር ይታተም በነበረው #የካቲት መጽሔት; ላይ ታትሞ ወጥቷል፡፡
1.5 በጠቅላይ
ሚኒስትር ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይ፣ የፍትህና ማስታወቂያ ቢሮ ኃላፊ (1981−1985
ዓ.ም.)
በጠቅላይ ሚኒስትር
ጽ/ቤት በቢሮ ኃላፊነት ይሰሩ በነበረበት ወቅት ካከናወኗቸው ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡−
o ዶ/ር ነጋሶ
ጊዳዳ የማስታወቂያ ሚኒስትር በነበሩበት ጊዜ የማስታወቂያ ሚኒስቴርንና በሥሩ የሚገኙትን የሚዲያ ተቋማት መዋቅርና ተግባርና
ኃላፊነት እንዲያጠና የተቋቋመው የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ባቀረቡት በጥናት የተደገፈ አስተያየት የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ
ተቋም ተቋቁሞ በመጀመሪያ በዲኘሎማ ከዛም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሥር ሆኖ እስከ ማስተርስ ዲግሪ ለማስተማር እንዲቻል
የታቀደው ዛሬ ተግባራዊ ለመሆን በቅቷል፡፡
o አገራችን የሥነ
ሕዝብ ፖሊሲ የሚያስፈልጋት ስለመሆኑ በደርግ ጊዜ በጉዳዩ ላይ ከነበራቸው ተሳትፎ በመነሳት ለነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር ማስታወሻ
በማቅረብና ከተባበሩት መንግሥታት የሥነ -ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤት
የኢትዮጵያ ቢሮ ኃላፊዎችም ጋር ተከታታይ ውይይት እንዲደረግ ለማድረግ ፖሊሲው እንዲወጣና የብሔራዊ ሥነ- ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤት
እንዲቋቋም ምክንያት ሆነዋል፡፡
1.6 የብሔራዊ
ሥነ- ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤት ኃላፊ (1985−1993) −
የሀገሪቱን ብሄራዊ የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ፖሊሲ እንዲያጠና በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተቋቋመው ኮሚቴ ሰብሳቢ በመሆን ከማገልገል ባሻገር
ፖሊሲው ከጸደቀ በኋላ ደግሞ የጽ/ቤቱ ኃላፊ በመሆን ለዘጠኝ ዓመት ሰርተዋል፡፡ በየክልሉ የሥነ- ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤቶች
እንዲቋቋሙና ከመቶ የሚበልጡ ባለሙያዎች ከሁሉም ክልል እንዲመረጡ
ተደርገው በተለያዩ አገሮች በሥነ -ሕዝብና ልማት ጉዳይ በትምህርታዊ ጉብኝትና በተለያዩ አጫጭርና ረዥም ጊዜ ሥልጠናዎች
እንዲያገኙ ተደርገዋል፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ
ብዙሃን የሥነ ሕዝብን ጉዳይ ለሕዝቡ ተገቢውን መረጃና ትምህርት መስጠት የሚያስችለውን የመጀመሪያው የኢትዮጵያ የሥነ- ሕዝብ
የአድቮኬሲና የኮምንኬሽን ስትራተጂ በሳቸው አስተባባሪነትና ሰብሳቢነት ተሰርቶ እንዲወጣና በሥራ ላይ እንዲውል አድርገዋል፡፡
1.7 ፖኘሌሽን
ሚዲያ ሴንተር (ፒ.ኤም.ሲ.) አለም አቀፍ ተቋም (እ.ኤ.አ. 2000-2019 መጨረሻ ድረስ) ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ በብሔራዊ ሥነ
ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤት የነበራቸውን ሥራ በፈቃዳቸው ከለቀቁ በኋላ በኢትዮጵያ ውስጥ በሚዲያ ሥራው የሚታወቀውና እስከ አሁንም
ድረስ ሰፊ የሚዲያ ሥራ እየሰራ የሚገኘው ፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር አለም አቀፍ ድርጅት በኢትዮጵያ እንዲቋቋም በማድረግና
የመጀመሪያውም የኢትዮጵያ ተጠሪ በመሆን ለሃያ አመት አገልግለዋል፡፡
o (ፒ.ኤም.ሲ.)
የኢትዮጵያ ቢሮ ከማቋቋም ባሻገር በካርቱም የሱዳንን የፒ.ኤም.ሲ. ቢሮ በማቋቋምና በማደራጀት እንዲሁም ለስዋዚላንድ የጤና
ጥበቃ ሚኒስቴር የኤች.አይ.ቪ. ኤድስ መከላከል የኮሚኒኬሽን ስትራቴጂ በማዘጋጀትና ሌሎችንም የአፍሪካ ቢሮዎች በማገዝ ቁልፍ
ሚና ተጫውተዋል፡፡
o ከ1993-2009
ዓ.ም. በእሳቸው አመራር በኢትዮጵያ በአይነታቸው የመጀመሪያ የሆኑ ጥናትንና ምርምርን መሠረት አድርገው የተሰሩ ዘጠኝ አዝናኝና
አስተማሪ ድራማዎች ተሰርተው ቀርበዋል፡፡ ከቀን ቅኝት ጀምሮ
የተሰሩት በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በውጭ አገሮችም ብዙ ተጽፎባቸዋል፡፡
o ሃሣቡን
ከማመንጨት አንስቶ የኢትዮጵያን ወጣትና አንጋፋ ደራሲያን በማስተባበርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ታዋቂ ምሁራንን በማሳተፍና
ሃሣባቸውን በማጋራት አስራ አራት በሀገራችን እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ መጻሕፍት እንዲጻፉ አድርገዋል፡፡ በመጽሃፍቱ
ቀርበው የነበሩት ምርጥና ልብ ሰቃይ ታሪኮች በኢትዮጵያ ሬዲዮ በኤፍ ኤምና በክልል ራድዮ ጣቢያዎች እንዲሁም በትምህርት መገናኛ
ሬድዮ ጣቢያዎች ጭምር በተደጋጋሚ እንዲሰሙ ተደርገዋል፡፡ በሬድዮ የተተረኩትን ታሪኮች ከሃያ ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ
እንዳደመጣቸው ተገምቷል፡፡
o በኋላም በተለያዩ
አለም አቀፍ ድርጅቶች ጥያቄ መሠረት በአማርኛ ከተጻፉት መጽሐፍት ታሪኮችን በመምረጥ በማስተርጎምና ተባባሪ አዘጋጅ በመሆን
ሁለት የእንግሊዝኛ መጻሕፍት ተዘጋጅተው እንዲወጡ አድርገዋል፡፡
o ፒ.ኤም.ሲ.
እንዲዘጋጅ ያደረገው የሳቅ ጀንበር የተሰኘና በኤች. አይ. ቪ. ኤድስ መከላከል ላይ ያተኮረ አዝናኝና አስተማሪ የመድረክ ድራማ
በሀገር ፍቅር ቲያትር ከስድስት ወራት በላይ ከመታየቱ ባሻገር በስምንት ክልሎች በመዘዋወር ሊታይ ችሏል፡፡
o በ1995−2ዐ11 ዓ.ም. ድረስ ከሶስት ሺ አምስት መቶ በላይ ጋዜጠኞች፣ ኘሮግራም አዘጋጆች፣
ደራሲያን፣ ተዋንያን፣ የወጣቶችና የሴቶች ማሕበራት መሪዎች፣ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሕግ አስፈጻሚ አካላትን፣ የጤና ኤክስቴንሽን
ኘሮግራም አስተባባሪዎችንና የተመረጡ የሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ዳይሬክተሮችን፣ የትምህርት መገናኛ ኘሮግራም አዘጋጆችን በልዩ
ልዩ የሀገራችን ዋና ዋና ማህበራዊ ጉዳዮችና በሚዲያና ኮምንኬሽን ክህሎት አሰልጥነዋል፡፡
o በታወቁ አለም
አቀፍ ድርጅቶች ማለትም በፓካርድ ፋውንዴሽን፣ ዩኤስ ኤይድ፣ ሲዲሲ (ዩ.ኤስ.ኤ.)፣ በዩኒሴፍ፣ በዩኤንኤፍፒኤ፣ በዩኤን ዊሜን፣
በኖርዊጅያን መንግሥት፣ በኖርዌይ እና በአሜሪካን ሕጻናት አድን ድርጅት፣ በጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና በዓለም ባንክ ድጋፍ የተካሄዱ
ልዩ ልዩ የሚዲያና ኮሚንኬሽን ኘሮግራሞችን በኃላፊነት መርተዋል፡፡
ዶ/ር ንጉሤ
የፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ያከናወኗቸው ሥራዎች ስኬታማ መሆናቸውን በማረጋገጥ፡−
o ጆን ሆኘኪንስ
ዩኒቨርሲቲ፣ ዩኤስ ኤይድ፣ ስታንፎርድ ዩኒቨርሲቲ፣ ኒውዮርክ የሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤትና
ሌሎችም በፒ.ኤም.ሲ. ልምዶችና የሥራ ውጤት ላይ የተለያዩ ጽሁፎችን አሳትመው አሠራጭተዋል፡፡
o በአሜሪከን አገር
በታተሙ ስድስት መጻሕፍት ውስጥ የፒ.ኤም.ሲ. ሥራዎች በምሳሌነት በሰፊው ተጠቅሰዋል፡፡ ስለፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር ኢትዮጵያ
የሥራ ውጤት በቢ.ቢ.ሲ.፣ በካናዳ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን፣ በቮይስ ኦፍ አሜሪካና በሌሎችም ውይይት ተካሄዶባቸዋል፡፡ አሜሪካ
በሚታተሙት የወርልድ ኮሚኒኬሽን መጽሔት፣ በሐርፐር መጽሔትና ዩኤስኤይድ ባሳተመው ከአፍሪካ የተመረጡ አስር የሚዲያ ሥራዎች
ውጤት ታሪክ ውስጥ የፖኘሌሽን ሚዲያ ሥራ አንዱ ሆኖ ተጠቅሷል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ፖኘሌሽን ሚዲያ ስለአከናወናቸው ሥራዎች
ውጤት የኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣና ዘ ኢኮኖሚስት መጽሔት ላይም ታትመው ወጥተዋል፡፡ በሀገር ውስጥ ስለፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር
ሥራዎችና ውጤቶች በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮ፣ በኢትዮጵያ ሔራልድ፣ በአዲስ ዘመንና በሌሎችም ከመቶ በላይ የሚሆኑ ቃለ
መጠይቆች፣ ሀተታዎችና ልዩ ልዩ ዘገባዎች ተጽፈው ቀርበዋል፡፡
o በጤና ጥበቃ
ሚኒስቴር አስተባባሪነት የሴቶች፣ የሕጻናትና የወጣቶች ሚኒስቴርና የእርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ተካተውበት በተደረገ ግምገማ
በተለይ ኤች.አይ.ቪ. ኤድስን በመከላከል ረገድ በፖኘሌሽን ሚዲያ
ሴንተር ተሰርተው የቀረቡት ተከታታይ ድራማዎች የትኛውም የሚዲያ ተቋማት ከሰሩት ሁሉ በላይ መሆኑን ባዘጋጀው ሪፖርት
አረጋግጦአል፡፡
o ቢ.ቢ.ሲ፣
ዩ.ኤስ.ኤድስ፣ የአሜሪካን ሕጻናት አድን ድርጅት፣ የኖርዊጅያን ኤምባሲ፣ ዩኒሴፍም በተናጠል ባስጠኗቸው ጥናቶች የፖኘሌሽን
ሚዲያ ሴንተር የሬድዮ ድራማዎች ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውን አረጋግጠዋል፡፡
o ዶ/ር ንጉሤ
ተፈራ በመሩት የፒ.ኤም.ሲ. ኢትዮጵያ የሚዲያ ሥራ ውጤቶች ላይ በሀገር ውስጥ አምስት ከኢትዮጵያ ውጭ ሶስት የማስተርስ ዲግሪ
ሥራዎች ቀርበውበታል፡፡
o ዶ/ር ንጉሤ
ተፈራ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በተለይም የሴት ልጅ ግርዛትን በመዋጋት አኳያ ያደረጉት የተቀዳጅ የሚዲያ ዘመቻ ስኬታማ
እንቅስቃሴ እውቅና በማግኘቱ በእንግሊዝ መንግሥት ድጋፍ በአፍሪካ በሴት ልጅ ግርዛት ላይ የሚደረገውን ዘመቻ እንዲያስተባብር
በተቋቋመውና አስር አባላት በነበሩት የአፍሪካ ቦርድ ውስጥ አንዱ አባል በመሆን ተመርጠው አገልግለዋል፡፡
o በፒ.ኤም.ሲ.
በኃላፊነት ይሰሩ በነበረበት ወቅት በተጨማሪ በሃዋይ ዩ.ኤስ.ኤ.ና በሲንጋፖር ከየሀገሩ ተመርጠው ለሚመጡ የተቋማት መሪዎች
ስልጠና የሚሰጠው የሐጋይ አድቫንስድ ሊደርሺኘ ኢንስቲትዩት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ የፋክልቲ አባል በመሆን እየተመላለሱ ስልጠና
በመስጠት አገልግለዋል፡፡ ድርጅቱ ለፋክልቲ አባልነት ለሚበቁት የሚሰጠውን “Leader and Trainer” የሚለውን ኦፊሻል መጠሪያ ተቀብለዋል፡፡
2. መጻሕፍትና
ጥናታዊ ጽሑፎች ዝግጅት
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ
በርካታ ጋዜጠኛችና የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ተማሪዎች የሚጠቀሙባቸውን የሚከተሉትን ሶስት መጽሐፍት አዘጋጅተዋል፡−
1.
Innovative Media and Communication Strategy for Development: Ethiopia’s
Experience
2.
Communication for Social Development: An Overview and the Ethiopian Experience
3. The
Ethiopian Media Profile
የተሰኙ ሶስት
መጻሕፍትን ጽፈዋል፡፡
4. በአሜሪካን
አገር በታተመና በአለም አቀፍ ደረጃ ስማቸው በሚታወቅ የሚዲያ፣ የኮሚኒኬሽን እና የኢንተርቴይንመንት ኤድዩኬሽን ምሁራን
በአዘጋጅነት በተሳተፉባቸው አራት መጽሐፍት ውስጥ አንዳንድ ምዕራፍ በመጻፍ በco-author�ነት ተሳትፈዋል፡፡ የጽሑፎቹ ርዕሶችና መጻሕፍቱ የሚከተሉት ናቸው፡፡
4.1.
“Organizing a Comprehensive National Plan for Entertainment-Education in
Ethiopia” in Singhal, A. etal (2004) Entertainment-Education and Social Change
– History, Research, and Practice.
Publishers, Lawrence Erlbaum Associate, New Jersey and London (page
177-189).
4.2. “The
Successful Application of a Comprehensive Behaviour Change Communication
Program in Ethiopia and Implications for Communication Projects Elsewhere” in
UNFPA and PMC (2011) Using the Media to Achieve Reproductive Health and Gender
Equity Published by UNFPA and Population Media Center P.O.Box 547, Shelburne,
Vermont, 05482, USA (page 81-87)
4.3.
“Communication, Lessons Learned from Decades of Media Outreach” in Lauren B.
Frank, Paul Falzone (2021) Entertainment-Education Behind the Scenes: Case
Studies for Theory and Practice
Published by Palgrave MacMillan, Cham.
Portland State University, Portland Peripheral Vision International,
Brooklin, USA (page 23-38)
4.4.
"Then and Now: Ethiopia's Progress and Challenges in Implimenting the
Beijing Declaration and Platform for Action" in the book, The Journey to
Gender Equality: Mapping the Implimentation of the Beijing Declaration and Plan
of Action. Published by University of Peace, UN Mandated Graduate Level School
in Costa Rica, June 2021.
5. በልዩ ልዩ
የሚዲያና ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ላይ በሀገር ውስጥና ከኢትዮጵያ ውጭም በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡ ሥልጠና ሰጥተዋል፡፡
6.
በተጨማሪም በተባባሪ አዘጋጅነት (Co-editor) በመሆን፡−
6.1. Blood Price
6.2. Ditched in the Jungle
የተሰኙ ሁለት
በኢትዮጵያ ማኀበራዊና ልማዳዊ እውነተኛ ታሪኮች ላይ የተመሰረቱ መጻሕፍትን ከአማርኛ ወደ እንግሊዘኛ ተተርጉመው እንዲታተሙ
አድርገዋል፡፡
7. የፒ.ኤም.ሲ.
ኢትዮጵያን የሥራ ልምድና ውጤት የሚመለከቱ ጥናታዊ ጽሑፎችን ከሃያ በሚበልጡ አለም አቀፍ መድረኮች ላይ ከነዚህም ውስጥ በቢል
ጌትስ ፋውንዴሽን፣ በጆን ሆኘኪንስ ዩኒቨርሲቲ፣ ግሎባል አለም አቀፍ ሄልዝ ኮንፍራንስ፣ ዓለም አቀፍ የሶሻልና የቢሄቪየር
ኮሚኒኬሽን ኮንፍራንስ፣ የአሜሪካን ኢንተርናሽናል የቢዝነስ ኮሚንኬሽን ማህበር አመታዊ ኮንፍራንስ፣ የአሜሪካ ፐብሊክ ሄልዝ
ማኀበር አመታዊ ኮንፍራንስ በሌሎችም ስብሰባዎች ላይ አቅርበዋል፡፡
2. ሕዝባዊ ተሳትፎ/ የበጎ ፈቃድ አገልግሎትና አማካሪነት
o ኢትዮጵያ ሬዲዮ
ይሰሩ በነበረበት ወቅት የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር መጀመሪያ ምክትል በኋላም ዋና ኘሬዜዳንት በመሆን በጠቅላላው ለአምስት
ዓመታት አገልግለዋል፡፡ (1969−1974 ዓ.ም.)
o የወርልድ ቪዥን
ኢትዮጵያ አማካሪ ቦርድ አባል (1985−1996 እ.ኤ.አ.) እና እንዲሁም የአማካሪ ካውንስል
ሊቀመንበር በመሆን (እ.ኤ.አ. ከ2013−2021) ድረስ አገልግለዋል፡፡
o በአፍሪካ
አንድነት ድርጅት ሥር የተቋቋመው የአፍሪካ ፖኘሌሽን ካውንስል ተቀዳሚ ም/ኘሬዚዳንትና በኋላም በኘሬዚዳንትነት ለሶስት ዓመት
አገልግለዋል፡፡
o እ.ኤ.አ.
ከ2ዐዐ7-2ዐዐ9 በየአመቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ በዋሽንግተን ዲ.ሲ. የሚዘጋጀው “Annual International
Conference on Global Health” አማካሪ (Advisor) በመሆን ለሶስት ዓመታት አገልግለዋል፡፡
o በተባበሩት
መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ጉዳይ ጽ/ቤት (UNFPA) በተቋቋመውና በፖካርድ ፋውንዴሽን ይደገፍ የነበረውና የታዳጊ ሀገሮችን የሥነ
ሕዝብ ኘሮግራም ለማጠናከር የተቋቋመው “South-South Leadership Initiative” ቦርድ አባል ሆነው ለአራት
ዓመት አገልግለዋል፡፡
o በሎስ አንጀለስ
ካሊፎርኒያ የሚገኘው የEarl Babbie Research Center, Chapman University የቦርድ አባል በመሆን
ከአምስት ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡
o ዶ/ር ንጉሤ
ተፈራ ከሚታወሱባቸው የበጎ ፈቃደኝነት አገልግሎት አንዱ የብርሃን ባንክ የተመሰረተው በሳቸው አስተባባሪነት በእሳቸው ቢሮ
የነበረ መሆኑ ነው፡፡ ይህን ባንኩ ለ1ዐኛ አመቱ የምስረታ በዓል ባወጣው መጽሔት ላይ አረጋግጧል፡፡
o ዶ/ር ንጉሤ
(ከጥቅምት 2ዐ13ዓ.ም. ጀምሮ) የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሀን ካውንስል እንባ ጠባቂ (Ombudsman) ሆነው በመመረጥ
በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
o ዶ/ር ንጉሤ
በአሁኑ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ የሚገኘው የፖኘሌሽን ኢንስቲትዩት ከፍተኛ አማካሪ (Senior Fellow) እንደሆኑ ተጠይቀው
በፈቃደኝነት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
o ዶ/ር ንጉሤ
ከዚህም ባሻገር በተለያዩ ተቋማት አብያተ ክርስቲያናትን ጨምሮ በአባልነትና በኃላፊነት የፈቃደኝነት አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡
4. ሽልማቶች
1. ዘመቻ መምሪያ
በነበሩበት ጊዜ በሕዝብ ግኑኝነት አገልግሎት ላሳዩት ውጤት የጎልድ ሜርኩሪ ልዩ ሰርተሪኬት ተሸልመዋል፡፡
2. ዋሽንግተን ዲሲ በሚገኘው በፖኘሌሽን ኢንስቲትዮት ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ
የኢንተርቴይንመንት ኤድዩኬሽን ስልት በመጠቀም በስነተዋልዶ ጤና
ዙሪያ ላሳዩት ከፍተኛ የሥራ ውጤት እውቅናና አክብሮት ለመግለጽ (May 27, 2009) በርካታ የክብር እንግዶችና የአለም
አቀፍ ድርጅት ተጠሪዎች በተገኙበት በዋሺንግተን ዲሲ ልዩ ስብሰባ አዘጋጅቷል፡፡
3. የግሎባል ሚዲያ አዋርድ 2011 (እ.ኤ.አ.) ተቀብለዋል (Global
Media Awards for Excellence in Population Reporting)
4. የ2012 (እ.ኤ.አ.) ዓመት የአፍሪካ ቸርማንስ አዋርድ ላሳዩት ስኬታማ
የኮሚኒኬሽን ሥራና አመራር ተሰጥቶአቸዋል (The Africa Chairman’s Award for Excellence in
Reproductive Health Communication Strategy Development)
5. በ
Leadership Transformation Ministries - The 2012 Cushite Leadership Award for
Demonstrating an Extraordinary Leadership Excellence አዋርድ ተሰጥቶአቸዋል፡፡
6. ሜዳልያ − ለሃያ አምስት ዓመት ለሥነ ሕዝብ ፖሊሲ መውጣትና ተግባራዊነት ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦ
የተሰጠ ሜዳልያ በኢትዮጵያ የኘላንና ልማት ኮሚሽንና በተባበሩት መንግሥታት የሥነ ሕዝብ ፈንድ ጽ/ቤት (UNFPA) በጋራ
ተሰጥቷቸዋል፡፡
7. የፖኘሌሽን
ሚዲያ ሴንተር ዓለም አቀፍ ቦርድ − ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ በኢትዮጵያ ሚዲያን በስልታዊ አመራር
በመጠቀም የሥነ ተዋልዶ ጤናን በማስፋፋት ላደረጉት የላቀ አስተዋጽኦና አመራር −
ከፍተኛ እውቅና የሚሰጠውን የቦርዱ ውሳኔ እንዲተለለፍ አድርጓል፡፡ ለዚህም የተዘጋጀውን አዋርድ ከፒ.ኤም.ሲ. ኘሬዚዳንት
ተቀብለዋል፡፡
8. በ2ዐ13
ዓ.ም. በሬዲዮ ጋዜጠኝነት በተለይም በምርመራ ጋዜጠኝነት ባከናወኑትና እንዲሁም የኢትዮጵያ ሚዲያ ሥራ ውጤታማ በሆነ መንገድ
መርተው ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽኦ ለአንድ ጋዜጠኛ የሚሰጠውንና ከፍተኛ የሆነውን የእድሜ ዘመን አገልግሎት ሽልማት ከኢትዮጵያ
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ተቀብለዋል፡፡
9. ሌሎችም በርካታ
የተሳትፎና የምስጋና የምስክር ወረቀቶችን ተቀብለዋል፡፡
5. በጋዜጠኝነትና
በሚዲያ ዙሪያ ስላከናወኑት የተዘጋጁ ልዩ ልዩ ኘሮግራሞች
• የሸገር ሬድዮ
ጣቢያ በሕይወት ታሪካቸውና በሰሯቸው የሚዲያ ሥራዎች ላይ ያተኮሩ ለአራት ሳምታት የቆየ ልዩ የውይይት ፕሮግራም አዘጋጅቷል፡፡
• የኢትዮጵያ
ሬድዮና ኤፍ ኤም 97 በአንድነት በዶ/ር ንጉሤ የጋዜጠኝነትና የሚዲያ ሥራ ላይ ያተኮረና ለሁለት ሰዓት የቆየ ሰፊ ዘገባ የያዘ
ውይይት አዘጋጅተዋል፡፡
• በኢሳት ቴሌቪዥን
በህይወታቸውና በሚዲያ አገልግሎታቸው ዙሪያ ያተኮረና (ሐምሌና ነሐሴ 2ዐ13) ለ4 ሣምንታት የቆየ የአንድ አንድ ሰዓት
ኘሮግራም ተዘጋጅቶ ቀርቧል፡፡
• በአዲስ ቲቪ፣
በጂኤምኤም ቲቪ፣ በሪቨር ቲቪ፣ በኢቫንጀሊካል ቲቪ፣ በኤልሻዳይ ቲቪ ኔትወርክ እና በሌሎችም የሕይወት ታሪካቸውንና
አገልግሎታቸውን የሚመለከቱ ተከታታይ ኘሮግራሞች ተዘጋጅተዋል፡፡
• በተለያየ ጊዜ
በሌሎችም የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲሁም በአዲስ ዘመንና ሄራልድ ጋዜጦች በሕይወት ታሪካቸውና በተለይም በሚዲያ ሥራ
ስላሳዩት የላቀ አስተዋጽኦ ቃለ-መጠይቆችና ሰፊ ዘገባዎች ቀርበዋል፡፡
6. በአሁኑ ጊዜ
ዶ/ር ንጉሤ ተፈራ፣
ዛሬም ጋዜጠኝነትንና የሚጠይቀውን ሥነ-ምግባር፣ ሚዲያን እንዴት ለሰላምና ለልማት መጠቀም ይቻላል በሚሉትና እጅግ ለሀገርና
ሕዝብ ጠቃሚ በሆኑ የተለያዩ አርዕስት ጉዳዮች ላይ በየጊዜው በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፣ በዋልታ ቴሌቪዥን ፣ በፋና ቴሌቪዥን፣
በአማራ ቴሌቪዥን፣ በGMM ቴሌቪዥን፣ በኢሳት ቴሌቪዥን፣ በኤልሻዳይ ቴሌቪዥን፣ በቀድሞ LTV እና በሌሎችም የመገናኛ ብዙሀን
ተከታታይና ትምህርታዊ ውይይቶችን በማድረግ ግልጽና አስተማሪ የሆኑ ጥናታዊ ጽሁፎችን ያቀርባሉ፣ ሥልጠናም ይሰጣሉ፡፡
ዳንኤል አያሌው፣ በአሁኑ ሰአት ከእነ መላ ቤተሰቡ መኖሪያውን በጀርመን
ሀገር ያደረገ የሚድያ እና የቴአትር ባለሙያ ነው፡፡ ዶክተር ንጉሴን ዳንኤል ሲገልጻቸው የሰው ነገር የሚገባቸው ይላቸዋል፡፡
‹‹…ዶክተር ንጉሴ ቢቆርጠኝ ይገባዋል፡፡ ፖፕሌሽን ሚድያ በሰራሁባቸው አመታት እንደ ዶክተር ንጉሴ አይነት ቀለል ብሎ የሚገኝ
ሰው አላየሁም፡፡ ጥሩ የስራ መሪ ናቸው፡፡ ‹‹የቀን ቅኝት››
ተከታታይ የሬድዮ ድራማን ስንሰራ የዶክተር ንጉሴ ተፈራ ሚና ትልቅ ነበር፡፡›› ሲል ዳንኤል ትዝታውን አወጋን፡፡
ዳንኤል አያሌው፣
ዶክተር ንጉሴን ሲገለጻቸው ጥሩ የስራ መሪ ይላቸዋል፡፡ እንደ አንዳንድ አለቃ የሚቆጡ ሳይሆኑ እንደ አባት አይተው ማበረታቻ
የሚሰጡ ናቸው በማለት የዶክተር ንጉሴ ሰብእና ለስራ የሚመች መሆኑን ይመሰክራል፡፡ ዳንኤል የድራማ ክፍለ-ትምህርት ኃላፊ
እንደመሆኑ ይህ ማቴሪያል ያስፈልገኛል ብሎ ከጠየቀ ዶክተር ንጉሴ
ለማሟላት ጊዜ አይወስድባቸውም ነበር፡፡ ይህ የአንድ መሪ ትልቁ ጠንካራ ጎን ነው፡፡
‹‹ ሆዴን ቢቆርጠኝ
ዶክተር ንጉሴን ይገባቸዋል፡፡ እንዲህ አይነት አለቃ ስለነበረኝ እኮራለሁ፡፡
ዶክተር ንጉሴ ስብሰባ ሲመሩ በቂ ዝግጅት ያደርጋሉ፡፡
እናም እኩል ለማውራት ሲቸግረን አስተውላለሁ፡፡ ግን እውቀት ለማስጨበጥ ደግሞ ወደኋላ የማይሉ በጎ ሰው ናቸው፡፡
አንዳንዴ በመኪና ቤት ሲያደርሱን አስታውሳለሁ፡፡ በቃ ስራህን
ወደህ እንድትሰራው የሚያደርጉ ሰው ናቸው፡፡›› ሲል ዳንኤል ምስክርነቱን ሰጥቷል፡፡
አባይነሽ ብሩ ዶክተር ንጉሴን ከ1970ዎቹ ጀምራ ታውቃቸዋለች፡፡ ‹‹
እርሱማ ትልቅ ሰው ነው›› ስትል በአድናቆት ሀሳብ መስጠቷን ጀመረች፡፡
በጋዜጠኛ አባይነሽ እይታ ዶክተር ንጉሴ ከበፊት ጀምሮ
ጥናታዊ ስራዎችን መስራት ላይ የተካኑ ነበሩ፡፡ ‹‹
ዶክተር ንጉሴ በራሱ ተማምኖ ይሰራ ስለነበር ሁላችንም ልዩ አክብሮት እንሰጠው ነበር፡፡ ብዙ ጊዜ እርሱንቨ ከማውራታችን በፊት እንጠነቀቅ ነበር፡፡ ምክንያቱም
ዶክተር ንጉሴ በንባብ የዳበረ ሰብእና የነበረው ሰው ስለነበር
ወደ እርሱ ከመሄዳችን በፊት በቂ መሰናዶ ማድረግ ይጠበቅብን ነበር፡፡
ጋዜጠኛ አባይነሽ እንደምትናገረው ‹‹ዶክተር ንጉሴ በአብዛኛው ጥልቅ
ትንታኔ የሚጠይቁ ስራዎች ይሰራ ስለነበር ሁላችንም ከእርሱ ለመማር ታላቅ ጥረት እናደርግ ነበር፡፡›› ብላለች፡፡
ዶክተር ንጉሴ ጋር
አብራ መስራቷ ብዙ ነገር እንዳስተማራት የምትናገረው
አባይነሽ ሰውን የሚያበረታታ ቀና ሰው ነው ስትልም
ትናገራለች፡፡ ‹‹ ዶክተር ንጉሴ ጋር በእዚህ 15 አመት ውስጥ አብረን በርካታ ስልጠናዎችን ሰጥተናል፡፡ በብዙ ጉዳዮች
የሚያበረታታኝ መጽሀፍ ማሳተም አለብሽ እያለ ሞራሌን የሚገነባ ሰው ነው፡፡ እና ዶክተር ንጉሴ ብዙ አልተነገረለትም፡፡ በተለይ
ከስነ-ህዝብ ጋር በተያያዘ ያበረከተው ሚና መጪው ትውልድ ሊያውቀው ይገባል እላለሁ፡፡ ›› ስትል የሚድያ ባለሙያ
አባይነሽ ሀሳቧን ሰጥታለች፡፡
ጋዜጠኛ ላእከማሪያም ደምሴ በኢትዮጵያ ሬድዮ በእንግሊዝኛው ክፍል ሲሰራ
የኖረ ነው፡፡ ዶክተር ንጉሴ ተፈራን ሲያውቅ ከ40 አመት በላይ ይሆነዋል፡፡
‹‹ ንጉሴ የምርመራ
ጋዜጠኝነት ሀገራችን ውስጥ በንቃት ካስተዋወቁ ሰዎች ምናልባት ቀዳሚው ሊሆን ይችላል ወይም ነው፡፡ በርካታ አድማጮች ደብዳቤ ይልኩ ነበር፡፡ ደብዳቤውም በማዳበሪያ
እየተደረገ ይቀመጥ ነበር፡፡ አንዳንድ ሰዎች ደግሞ ሰነዶችን
ያመጡለት ነበር፡፡ እነዚህ ሰነዶች ያኔ ለእርሱ በማቀበል ነበር
ትውውቃችን የተመሰረተው፡፡ አንዴ ከተዋወቅን በኋላ ግን ዶክተር ንጉሴን ቀና ሰው ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ በጣም ለስራው ቅድሚያ የሚሰጥ
ነው፡፡ ትዝ የሚለኝ ሰርጉ በዲአፍሪክ ሆቴል ነበር፡፡ ወንጌል አማኝ ስለነበር መዝሙር እና የመጽሀፍ ቅዱስ ትምህርት እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ወዲያው
ደግሞ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማህበር ምክትል ሊቀመንበር በመሆን ያገለግል ጀመር፡፡ ›› ሲል ትዝታውን አውግቶናል፡፡
ቤተሰባዊ ሁኔታ
ዶክተር ንጉሴ
በ1968 የዛሬ 45 አመት ከወይዘሮ ጸሀይ ካሳ ጋር ጋብቻ የመሰረቱ ሲሆነው 3 ልጆችን እንዲሁም 2 የልጅ ልጀችን ማፍራት
ችለዋል፡፡
መዝጊያ፣ ዶክተር
ንጉሴ በሀገራችን በሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ዘርፍ የጠለቀ እውቀት
ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ በተግባር የሚድያ ስራ ውስጥ ገብተው አቅማቸውን የፈተሹ ናቸው፡፡ ይህን አቅማቸውን ሲፈትሹ
ለአድማጭ አንድ ቁምነገር አክለዋል፡፡ በጥናት ላይ የተመሰረተ የጋዜጠኝነት ስራ ሲሰራ ምን ያህል ዘመን አይሽሬ እንደሚሆን
ኣሳይተዋል፡፡ ዶክተር ንጉሴ ከ40 አመት በፊት በኢትዮጵያ ሬድዮ ሳሉ ይሰሩት የነበረውን መሰናዶ ልብ ብለን ስናጤን
ጋዜጠኝነትን ለሚማሩ ሁሉ ጥሩ ማሳያ የሚሆን ነው፡፡ ዶክተሩን
ለዚህ ስኬት ያበቃቸው ሁለት ነገር ይመስለናል፡፡ አንደኛ አንባቢ በመሆናቸው እና በመደበኛ ትምህርት በደንብ በመማራቸው ነው፡፡
ጥሩ አሳቢም ናቸው፡፡ ሀሳብ ሲያፈልቁና ነገሮች ከፍሬ ሲያበቁ ብዙዎች ያውቋቸዋል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት እንደ
ዶክተር ንጉሴ አይነት ብስለትን የተላበሱ ሰዎች በየዩኒቨርሲቲው እየተጋበዙ ልምዳቸውን ሊያካፍሉ ይገባል፡፡ ታሪካቸው በሚገባ
ሊሰነድ በመጽሀፍም ታትሞ ሊወጣ ይገባል፡፡ ዶክተር ንጉሴ ይህ የዊኪፒዲያ ጽሁፍ ሲሰናዳ የ73 አመት ልደታቸውን አክብረዋል፡፡
ከ23 አመታቸው ጀምሮ እግዚአብሄር አቅፎ እና ደግፎ ለዚህ እንዳበቃቸው ማመን ያስፈልጋል፡፡ አእምሮን ብሩህ የሚያደርግ ፈጣሪ
ብቻ ነው፡፡ ዶክተር ንጉሴም በተካኑበት ሙያ ሀገራቸውን ያለ አንዳች ስስት ሲያገለግሉ ነበር፡፡ አሁንም አይደክማቸውም፡፡
እንዲህ አይነት ብሩህ እና ብርቱ ኢትዮጵያዊ የበጎ ሰው የ2013 እጩ መሆናቸው ሁላችንንም የሚያስደስት ነው፡፡ ነሀሴ 30
2013 በሚደገረው ስነ-ስርአት ዶክተር ንጉሴ ከሌሎች እጩዎች ጋር ይቀርባሉ፡፡ እኛም መልካሙን ተመኘን ፡፡ / ይህ ከዶክተር ንጉሴ ተፈራ የተገኘን ጽሁፍ መሰረት አድርጎ የተሰራ አጭር
ግለ-ታሪክ በየጊዜው አስፋላጊው ማሻሻያ የሚደረግበት ሲሆን የቃለ-መጠይቅ ፤ የምርምርና የአርትኦት ስራው በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ
የተከናወነ ነው፡፡ ./
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ