37. አንተነህ መርዕድ እምሩ Anteneh Merid Emeru

 የጦቢያ ዋና አዘጋጅ አንተነህ መርእድ

 ተወዳጅ  ሚድያ ታሪኩን የሚያቀርብላችሁ ሰው ጋዜጠኛ አንተነህ መርእድ እምሩ ይባላል፡፡ በጦቢያ መጽሄት እና ጋዜጣ ላይ በዋና አዘጋጅነት ያገለገለ ነው፡፡ በአሁኑ ሰአት መኖሪያውን በካናዳ ያደረገው አንተነህ ከእነ አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፤ አቶ ጎሹ ሞገስና ከመሳሰሉት በሳል ሰዎች ጋር የሰራ ባለሙያ ነው፡፡ ባለበት ካናዳ 2 መጽሀፎችን የጻፈ ሲሆን አንዱን ለህትመት አብቅቶታል፡፡ባለትዳርና የ2 ልጆች አባት የሆነው  የ63 አመቱ አንተነህ መርእድ ልቡ ያለው ኢትዮጵያ ነው፡፡ ያለፈበት መንገድ ለብዙዎች እንደሚያስተምር ታምኖ እነሆ ታሪኩ በዚህ መልኩ ተሰናዳ፡፡

               የባህር ዳሩ -አንተነህ 

አንተነህ መርዕድ እምሩ  ጠረፍ ጠባቂ ፖሊስ ከሆነው መርዕድ እምሩ ንጉሴና ከእናቱ ሂሩት አበራ ጀንበር ዛሬ ህዳሴ ግድብ በሚገነባበት ዳንጉር ተረግዞ  ቻግኒ ከተማ በ1950አ.ም  ዓ ም ተወለደ። የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በዲንካራ ቢጀምርም እናቱ በሞት ስለተለየችው ታላቅ ወንድሟ አቶ አያሌው አበራ ጋር በዳንግላና በግምጃቤት ኑሮን ቀጠለ። የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱንም በባህርዳር አጼ ሰርጸ ድንግል መላክ ሰገድ የተከታተለ ሲሆን ገና ዘጠነኛ ክፍልን የጀመረው አብዮቱ በተቀጣጠለ ዘመን በ1966አ.ም በመሆኑ የተማሪዎች እንቅስቃሴ እስከ 1969 ዓ ም ድረስ በመቀጠሉና ደጋግሞ ትምህርት የሚቋረጥ በመሆኑ ትኩረት ሰጥቶ ተምሯል ለማለት አያስደፍርም። እንዲያውም ዘጠነኛና አስራ አንደኛ ክፍልን የአንድ ሴሚስተር ትምህርት ብቻ እየተማረ በነጻ (ፍሪ ፕሮሞሽን) ስላለፈ እርሱና ጓደኞቹ በአካዳሚው ተገቢ እውቀት አልቀሰሙም።

                   ጫካ ገባ

በዚህ የለውጥ ጊዜ፣ ገና የአስራ አንደኛ ክፍል ተማሪ እያለ እንደአብዛኛው ወጣት ስርዓቱን በመቃወም በ1968 ዓ ም ጀምሮ ኢህአፓ ውስጥ በመሳተፍ ለትምህርትና ለሌላም የወጣትነት እድገት የሚያበቁ ሁኔታዎችን ወደጎን ትቶ ውስብስቡ የአገር ጉዳይ ላይ እንደእኩዮቹ ተቀላቀለ። በ1970 ዓ. ም ለስድስት ወራት መምህር ሆኖ ቢሰራም በፖለቲካው ምክንያት ሊታሰር እንደሚፈለግ ሲያውቅ የካቲት ወር ላይ በትግሉ ለመቀጠል ጫካ ገባ። ከ2ዓመት መንከራተት በኋላ ሚያዝያ 19 ቀን 1972 ዓ ም በዳንግላ አካባቢ ሲንቀሳቀስ በገበሬዎች ተከበበ።

          በተአምር ተረፈ

የሚድያ ባለሙያ አንተነህ  41 አመት ወደ ኋላ ተጉዞ  ትዝታውን ሲያወጋን እንዲህ አለ፡፡‹‹…..ራሴን ለመከላከል የያዝኩት አንድ ግዙፍ የእጅ ፈንጅ ስለነበር እታገልላቸዋለሁ ብዬ የወጣሁላቸውን ገበሬዎች ገድዬ ከማመልጥ ራሴን መስዋዕት ለማድረግ ወሰንኩና ፈንጂውን በራሴ ላይ ጣልኩ። ብያዝም የሚጠብቀኝ ተሰቃይቶና ጓደኞቼንና ድርጅቴን አጋልጦ መሞት ነበርና። በራሴ ላይ ያፈነዳሁት ፈንጂ በአየር ላይ ወርውሮ ከከበቡኝ ሰዎች ጀርባ ሲጥለኝ እግሬና ሆዴ ላይ ከደረሰብኝ መጠነኛ መቁሰል ውጭ ከፍተኛ ጉዳት ሳይደርስብኝ መቅረቱ አሁንም ድረስ አይገባኝም። ከሞቱ ያተረፈኝ አምላክ ሁለተኛ እድል ሰጥቶኝ አሁን ድረስ አለሁ። ህይወቴ የተረፈው ከፈንጂው ብቻ አልነበረም። የተያዝሁት ደርግ ከአሁን በኋላ መግደል ይቁም ብሎ የወሰነ ሰሞን መሆኑ ነው እንጂ ከወራት በፊት የተያዙ ባልደረቦቻችን ሁሉም ተገድለዋል።›› ሲል በተአምር የተረፈበትን አጋጣሚ እየተገረመ ያስታውሳል፡፡ እንዲህ አይነት እድል ፈጣሪ ካልሰጠ ማንም ሊቸር አይችልም ብሎም ያስባል፡፡

                              ዩኒቨርሲቲ እና ኢዜአ መግባት 

አዲሱን ህይወቱን በባህርዳርና በደብረ- ማርቆስ እስር ቤት  ለ3 ዓመት የሚጠጋ ጊዜ  ካሳለፈ በኋላ በቅጡ ያላጠናቀቀውን ትምህርት ለመማር ባህርዳር ተመልሶ  የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ተከታትሎ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ጥናት ተመርቆ በ ህዳር 1981 ዓ ም በኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋዜጠኛ ሆኖ ስራ ጀመረ። የዜና አገልግሎት ስራ ከክፍለሃገርና ከአዲስ አበባ ዜናዎችን እያጠናቀሩ ማቅረብና ለተለያዩ ሚድያዎች ማሰራጨት በመሆኑ ከዜና አገልግሎት የቀሰመው ዜና በመስራት ላይ የተወሰነ ነበር። በደርግ ጊዜ የሚሰራውም ዜና በፖለቲካው የሚፈለገው ለፕሮፓጋንዳ የሚመች፣ የህዝቡንም እውነተኛ ህይወት የሚያንጸባርቅ አለመሆኑ ግልጽ ነበርና የዛን ጊዜ የነበሩ ጋዜጠኞች ብዙም በስራቸው ደስተኛ ሳይሆኑ ተጠንቅቀው ይሰሩ ነበር፡፡ አንተነህም በተመሳሳይ ሁኔታ ሶስቱን ዓመት በዚህ መልክ እንዳሳለፈ ይናገራል፡፡

               ቡና ላኪዋ ኤርትራ

 <<…በ1983 ዓ. ም ኢህአዴግ ስልጣኑን ሲቆጣጠር የመጀመርያው የጥቃት ኢላማ የሆነው ሚድያው ስለነበር ለዘመናት ልምድ ያካበቱ በሳል ጋዜጠኞችን በማባረር ከጫካ የመጡ አባሎቹንና ይሰሩልኛል ያላቸውን ይዞ በመቀጠሉ አሁንም ሚድያው ለገዢው አካል ፍጹም አገልጋይ ከመሆኑም አልፎ በሳል ጋዜጠኞቹን በማጣት ተዳክሞ ስለነበር የቀረነው ተገቢ ልምድ የምቀስምበት ተስፋችን የጨለመ ነበር።የጠበቅነው አገራዊ ለውጥ ቀርቶ ኢህአዴግ የያዘው መንገድ ስላላማረኝና ስራዬም ላይ ይሄው ሁኔታ መታየቱ ስላልቀረ በተደጋጋሚ በሰራኋቸው ዜናዎች ላይ አለቆቼ ደስተኛ አልነበሩም። በተለይ ኤርትራ አንድ እግር ቡና ሳታበቅል የቡና ኤክስፖርተር መሆኗ በታወቀበት ጊዜ ይህንኑ አግባብ ያልሆነ የኤርትራና የኢትዮጵያ ግንኙነት በቡና ነጋዴዎች ላይ ያመጣውን ችግርና ኢትዮጵያም ያጣችውን ጥቅም በመረጃ አስደግፌ ያቀረብሁት ዜና፣ ተቃዋሚዎች ባደረጉት ሰልፍ ላይ የቀረቡ ጥያቄዎችን ያካተትሁበት ዜናዎች አየር ላይ ከዋሉ በኋላ ለህትመት እንዳይበቁ እየታገዱ እኔም ለግምገማ እየቀረብሁ ማስጠንቀቂያ ሲሰጠኝ በጊዜው በርካታ የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ስራ ስለጀመሩ እዚህ የማይወጡ ዜናዎችንና መጣጥፎችን ስሜን በመደበቅ ለአሌፍ፣ ለደወል፣ ለጦብያ፣ ለመስታወትና ለሉባር አስተዋጾ ማድረጉን ቀጠልሁበት። የተቃዋሚ ፖለቲካ ድርጅቶችም አማራጭ ሃይሎችና መአህድ ጋዜጦቻቸውን ሲጀምሩ ዜናዎችንና የፖለቲካ መጣጥፎችን በማቅረብ፣ የሰው ሃይላቸውንም በማጠናከር አግዝ ነበር። ይህ አስተዋጾየም በነሃሴ 1986 ዓ ም ከዜና አገልግሎት ስታገድ ጦቢያን ለመቀላቀል አስችሎኛል።›› በማለት የሚድያ ባለሙያ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ወደ ጦቢያ ያደረገውን ሽግግር ይነግረናል፡፡

                ጦቢያ ወርቃማ ጊዜ 

 የሚድያ ሰው አንተነህ የጋዜጠኝነት ሙያን ጦቢያ ላይ ጀመረ ቢባል ማጋነን አይሆንም። በመጀመርያ ደረጃ የጦቢያ ባልደረቦች አቶ ሙሉጌታ ሉሌ፣ አቶ ጎሹ ሞገስ፣ አቶ ደርበው ተመስገን፣ አቶ ሃይሉ ወልደጻድቅ፣ አቶ ሙሉጌታ ወልደሚካኤል፣ አቶ ኤልያስ ብሩ፣ አቶ ከበበው ገበየሁ፣ አቶ ታዬ በላቸውን የመሳሰሉ እውቅና በሳል ሰዎች ጋር መስራት እያንዳንዷ ቀን ትምህርት ስለነበረች ብቻ ሳይሆን ወደ ጦቢያ የሚጎርፈው ዜና፣ መጣጥፍና መረጃ በጣም ብዙ ከመሆኑም በላይ በአካል የሚያገኛቸው ሰዎችም አገሪቱ ውስጥ አሉ የተባሉ አዋቂዎችንና ባለታሪኮችን በመሆኑ በህይወቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ የተማረበት ወርቃማ ጊዜ ነበር። በሳምንት ሃሙስ የሚወጣው ጦቢያ ጋዜጣና በወር የሚታተመው መጽሄት በአገር ውስጥና በውጭ እየተሰራጨ ለዚያም የሚጎርፈው ምላሽ ብዙ በመሆኑ ከቢሮ አልፎ ቤታቸው ሳይቀር ሲጽፉ፣ ኤዲት ሲያደርጉ፣ መረጃ ለማግኘት ሲሯሯጡና ስልክ ሲደውሉ ስለሚውሉ ከቤተሰብ ጋር የሚያሳልፉት ጊዜ እንኳ አልነበረም።

 አቶ አንተነህ 5 አመት ስለሰራበት የጦቢያ ትዝታ ሲያወራ በርካታ ገጠመኞችን ማስተናገዱን ይናገራል፡፡ 27 አመት መለስ ብሎ  ከህሊና ማህደሩ እየመዘዘ ያጫውተን ጀመር‹‹…..  ከዚያም በላይ በስራችን ደስተኛ ያልሆነው ስርዓቱ የሚፈጥራቸውን መሰናክሎች እያለፉ የሌባና ፖሊስ ጨዋታ ይመስል እየተሹለከለክን መረጃዎችን የምናገኝበት ሁኔታ አደጋው ለቤተሰቦቻችንና ለወዳጆቻችን ሰቀቀን ቢሆንም ለእኛ ጀብድ ከዚያም አልፎ ለአገር የምንከፍለው መስዋዕት አድርገን እንቆጥረው ነበር።የምንሰራቸው ዜናዎች በመረጃ የተደገፉና ሚዛናዊ እንዲሆኑ ብዙ የምንደክም ስለነበር በዜናዎቻችን ላይ ክስ መመስረትና መርታት ለስርዓቱ አስቸጋሪ ነበር። እኛም የታጠረልንን መሰናክል ለመዝለል የምናደርገው ጥንቃቄ መረጃውን ከምናጠናቅርበት የበለጠ ጊዜና ጉልበት ይወስድብናል። ያም ሆኖ ማዋከቡ ማስፈራራቱ በአካል፣ በቃል፣ በቤተሰብ፣ በጓደኛ፣ በፖሊስ ጣቢያና በፍርድ ቤት ያለማቋረጥ የሚቀጥል በመሆኑ አደጋ እየሸተተንም ቢሆን ያለማቋረጥ እንሮጣለን። በየጊዜው ፖሊስ ጣቢያ ተጠርቶ ቃል መቀበልና ማስፈራራት ስላልሰራ የእስር ዘመቻው በሰፊው ቀጠለ።

የአቶ ሙሉጌታን የተባ ብዕር ለማስቆም በህይወቱ አደጋ እስከማድረስ የሄደው ስርዓት በ1996 ዓ ም በዘመቻ ጋዜጠኞችን ለማዋከብ አቶ ሙሉጌታን፣ ታዬ በላቸውንና እኔን ከበርካታ ወጣት የነጻ ፕሬስ አባላት ጋር ማዕከላዊ ወረወረን። እስሩን በደርግ ጊዜም የለመድሁት በመሆኑ ባይደንቀኝም ቀደም ብዬ ቀርቤ ከማላውቃቸው ወጣት ጋዜጠኞች ጋር ያስተዋወቀኝ፣ የአቶ ሙሉጌታን ስብዕና እኔ ብቻ ሳልሆን ብዙ ወጣት ጋዜጠኞች በቅርብ ያዩበት በመሆኑ ከእስር ስንወጣ የነጻ ፕሬስ አባላት በትብብር እንድንሰራና እንድንደራጅ መሰረት የጣልንበትን አጋጣሚ ፈጠረልን። ከአንድ ወር እስር በኋላ ስንፈታ ስራችንን የበለጠ ከሌሎች የፕሬስ አባላት ጋር በትብብር መስራቱን ቀጥልንበት።›› በማለት በዛን ጊዜ የነበሩ የነጻፕሬስ ጋዜጠኞች ይከፍሉት የነበረውን ዋጋ አስረድቷል፡፡

       ‹‹ጦቢያ እና ተቃዋሚዎችን ሰልልልን››

አሁንም አቶ አንተነህ መተረኩን ቀጠለ፡፡‹‹…..በአቶ ከፋለ ማሞ ሊቀመንበርነትና በአቶ ሙሉጌታ ምክትልነት የተጀመረው የነጻ ፕሬስ ማህበር ከዓለም አቀፍ ጋዜጠኞች ማህበርና ከሌሎችም ድጋፍ የምናገኝበትና የመንግስትን ጫና የምናጋልጥበት ጠንካራ መድረክ ሆነ። እንደገና በ1997ዓ ም የእስሩ ዘመቻ ማእበሉ ቀጠለና ከጦብያ እኔ፣ አቶ ጎሹ ሞገስ፣ አቶ ታዬ በላቸው ቆይቶም እኛን ተክቶ አዘጋጅ የሆነው አቶ አረጋ ወልደቂርቆስ ከበርካታ ጋዜጠኞች ጋር ወደ ማዕከላዊ ተወረወርን። በዚህ በሁለተኛው እስር ላይ ማዕከላዊ እያለሁ አንድ ቀን ቢሮ ተጠራሁና ቀድሞ ዜና አገልግሎት አብሮኝ ይሰራ የነበረና ወደ ደህንነት የገባ ጋዜጠኛ ጠበቀኝ። በግልጽ ከደህንነት ጋር እንድሰራና ጦብያንና ተቃዋሚዎችን እንድሰልል ልመና አይሉት ትዕዛዝ ሰጠኝ። በዚህ በጣም ተበሳጭቼ ለአቶ ጎሹ ስነግረው “መናደዱን አቁምና ነገ ዛሬ እያልክ እሺም እምቢም ሳትል በጉዳዩ ተኛበት እንጂ አትጋፈጥ” በሚል ምክር አጽናናኝ። ከሁለት ወር ተኩል እስር በኋላ በተፈጠረው ዓለም አቀፍ ግፊት ተፈታን። ደህንነቱ ጋዜጠኛም ከመንገድ በመኪና ወስዶ ዋቢ ሸበሌ ሆቴል ከአለቆቹ አጋፈጠኝ። በተለያየ ጊዜ እየወሰዱ ማባበልም፣ ማስፈራራትም ስለቀጠለ ላስብበት እያልሁ ሞጋች የሆነ ጊዜ የሚወስድም ጥያቄ እያቀረብሁ ቆየሁና ሶስተኛ ዙር እስር በ1998 ዓም እንደገና ታሰርን፣ ቢሮአችንም ተቃጠለ ተባለ። በዚህኛው እስር ከማዕከላዊ አልፎ ወህኒም ወረድንና ከሰባት ወር በላይ ታስረን ሃምሌ 24 ቀን 1990 ዓ. ም ተፈታን። ከደህንነቶች መሸዋወድ የማይሰራበት ደረጃ በመድረሱ ካልተባበርኳቸው ህይወቴም አደጋ ላይ መሆኑ፣ ጦብያ ውስጥ አቶ ሙሉጌታ ሳለ የነበረው መተባበርና የስራ መንፈስም ጠፍቶ ስለአገኘሁት ከአገር መውጣትና ህይወቴን ማትረፍ እንዳለብኝ ሲገባኝ በሞያሌ ለመውጣት ወሰንሁ። በዚህ ሁኔታ እያለሁ አቶ ከፋለ ማሞ ከአውሮፓ ሆኖ አሩሻ ታንዛንያ  ለሚካሄደው ዓለም ዓቀፍ የጋዜጠኞች ስብሰባ ግብዣ ስለላከልኝ ጥቅምት 1991 ዓ .ም አገሬንና ቤተሰቤን ጥዬ ተሰደድሁ። ›› በማለት ከ22 አመት በፊት ከሀገር የወጣበትን አጋጣሚ በዝርዝር ነግሮናል፡፡

         ስደት

 አቶ አንተነህ ፣አሩሻ ታንዛንያ የሚካሄደው የጋዜጠኞች ስብሰባ ሲጠናቀቅ ናይሮቢ ኬንያ በስደተኝነት ለአንድ ዓመት ቆየና ከነቤተሰቡ የካቲት 1992 ዓ. ም ካናዳ ገባ። ሳይማር ያስተማረውን የአገሬን ህዝብ ማገልገል በምችልበት አፍላ የጉልምስና ዘመኑ ላልደከመበት ህብረተሰብ ጉልበቱንና እውቀቱን ሊገብር ተገደደ። በተሰደደበት ካናዳ በጋዜጠኝነቱ የመቀጠል እድሉ ጠባብ በመሆኑ ዮርክ ዩኒቨርስቲ ገብቶ የጤና ሳይንስ በማጥናት ተመርቆ  ላለፉት አስራ ሰባት ዓመታት የጤና ባለሙያ ሆኖ ይሰራል 

 የሚድያ ሰው አንተነህ ከ1980 -1991 ለ11 አመት በሚድያ ስራ ላይ  ሲቆይ ለሙያው የተለየ ፍቅር አሳድሮ ነበር፡፡ምንም እንኳ ከአገር ቢርቅ ህዝቡን በጨለማ የሚገዛንና እርሱንም ለስደት ያበቃውን ስርዓት በሚያውቀው ሙያ ጊዜና አጋጣሚ በገኘ ቁጥር ለመታገል አቅሙ የፈቀደለትን ያህል አድርጓል። በተለይ ትምህርቱን ከጨረሰ  በኋላ ህዝቡን ለትግል የሚያነሳሱ፣ ስርዓቱንም የሚያጋልጡ መጣጥፎችን በሬድዮ፣ በድረ-ገጾች በተከታታይ በማቅረብ አስተዋጽዖ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ኢሳት ከተቋቋመም በኋላ በቶሮንቶ የኢሳት አስተባባሪ በመሆን ለበርካታ ዓመታት ሙያዊ እገዛ ቸሯል፡፡ ጋዜጠኝነት የሚወደው ሙያ ነው። ሙሉ ጊዜውን ሰጥቶ ለአገሩ አስተዋጽዖ እንዳያደርግ ስርዓቱ ቢያደናቅፈውም በሚቀረው ጊዜ ከአሁን በኋላ የሚችለውን አደርጋለሁ  ብሎ ያስባል።

              ዜና አገልግሎት

የሚድያ ባለሙያ አንተነህ በሀገር ቤት ሚድያው ላይ በቆየባቸው 11 አመታት በአቅሙ ያኖረውን አሻራ ወይም የለወጠውን ነገር እንዲያስቀምጥ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች በጠየቅነው መሰረት ይህን አከል አድርጎልናል፡፡

‹‹ ….ዜና አገልግሎት ውስጥ አዲስ ከመሆኔም በላይ ብዙ ለውጦችን ለማምጣት የማያስችል የነበረ ቢሆንም ኢህአዴግ ስልጣን ከያዘ በኋላ ዜና አዘጋገባችንን ትንሽ ለቀቅ ያለና የግል ጋዜጦች ዜና አቀራረብም ጋር መነጻጸር ስለመጣ ሚዛናዊ ዜና ለመስራት ሞክረናል። የህወሃት ሰዎች መደላደልና ማፈን መጀመራቸው ብቻ ሳይሆን ውስጣችን የነበሩት አድርባይነት የሚያጠቃቸው ጋዜጠኞች አንዳንዶቻችንን ማስጠቆር ጀምረው ነበር። አርብ በሚካሄድ ግምገማ “ይህን ለምን ሰራኸው? ለምን ይሄንስ አካተትኸው?” የሚሉትን አይነት ጥያቄዎች ማስተናገድና መወቀስ የተለመደ ሆነ። ከላይ እንደገለጽሁት በኤርትራ ቡና ንግድ ላይ እና በተቃዋሚዎች ሰልፍ በሰራሁት ዜና በግምገማ ሊረቱኝ ባይችሉም በትዕዛዝ ለህትመት እንዳይበቁ አድርገዋል። እነዚህ ሁሉ ተደማምረው ነው ያልተፈለግሁት። ትልቁ እድል የግል ጋዜጦችና መጽሄቶች ላይ ዜናዬን በተለያየ መልክ ማውጣት የምችል መሆኑ ጠቅሞኛል።›› ሲል ሚናውን አጠር አድርጎ ነግሮናል፡፡

               ጦቢያ

ጦቢያ ስመጣ ዋናው ልምዴና አቅሜ ዜና መስራት ላይ ስለሆነ በርካታ ዜናዎችን አፈላልጌ ሚዛናዊ በሆነ መንገድ ለመስራት እድሉን አግኝቻለሁ። በተለይ በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ ባለስልጣናትና ህወሃት ይሰሩት የነበረውን ወንጀል የሚያጋልጡ መረጃዎችን የሚተባበሩኝ ቁልፍ ሰዎች ስለነበሩ ለማጋለጥ ድርጅቱንም ጠቅልለን ባናድነውም ከብዙ ዘረፋ ለጊዜው ታድገነዋል። በተለይ ዛሬ በህይወት የሌለው የህግ ባለሙያው ካሳሁን አድማሱ በአገር ሃብት ተቆርቋሪነቱ ያካፍለኝ የነበሩ መረጃዎች ከባድ በመሆናቸው ባንኩ ማስተባበል ወይንም መክሰስ አይቻለውም ነበር። በኢትዮጵያ መብራት ሃይል የሚፈጸመውን ደባም ከስሩ እናጋልጥ ነበር። በመንግስት ሃይሎች በሩ ላይ በግፍ የተገደለው የህግ ባለሙያና ጋዜጠኛ ተስፋዬ ታደሰ በግልም ጓደኛዬ ስለነበረ በኪራይ ቤቶችና በተለያዩ መስሪያቤቶች ያሉትን ገበና የሚያጋልጡ ዜናዎችን ይሰጠን ስለነበር ትልቅ ባለውለታዮ ነው። ተስፋዬ ታደሰ መስታወት መጽሄትና ሉባር ጋዜጣን ሲያትም ዜና አገልግሎት ሆኜ አግዘው ስለነበር የራሱን ጋዜጣና መጽሄት ሲያቆም ሰፊ ምንጩን ለግሶኛል።

ጦቢያ ዜና ስንሰራ ትልቁ ድጋፍ የሆነን እየታሰርን ምንጮቻችንን የማናጋልጥ መሆናችንን ህብረተሰቡ ከተገነዘበ በኋላ የተፈጠረው መተማመን ራሱ እየፈለገን ዜና ይሰጠን ስለነበር ድካማችንን አቅልሎልናል። የመንግስት ባለስልጣናትንም “ይህ መረጃ ደርሶናል ሚዛናዊ ለማድረግ የእናንተን ምላሽ እንፈልጋለን” እያልን መጠየቃችን በሚፈሩንና በሚጠሉን ዘንድ እንኳ መከበርን የሰጠን መሆኑን ደጋግመው ነግረውናል። ሲቻላቸውም የራሳቸውን ምላሽ በድፍረት የሰጡን ጥቂት አይደሉም። በተለይ በመንግስት ጫና ያልነበረባቸው የውጭ ድርጅቶች፣ አንዳንድ ምሁራን፣ አልፎ አልፎ አንዳንድ መስሪያቤቶች ለመንግስት ሚድያ ከመስጠት ለእኛ ያደሉ ነበር።

ሌላው ትዝታዬ በፖለቲካ ድርጅቶች በኩል ያለው ነው። ብዙዎች የፖለቲካ ድርጅቶች መሬት ወርደው ህዝብ ከማደራጀት በሁለትና በሶስት ወር የተቃውሞ መግለጫ በማውጣት መኖራቸውን የሚያሳውቁበት ሁኔታ ስላለ ለዜናነት የማይመጥነውን መግለጫዎቻቸውን ስለማናስተናግድ ቅሬታቸው ከፍተኛ ነበር። በሌላ በኩል ድርጅቶች የእነሱን አቋም የሚጻረር ወይንም የተለየ ሃሳብ ካስተናገድንም ስድቡ ማስፈራራቱ ከፍተኛ ነበር። ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና ኦነግን አስመልክቶ በሰጡን ተከታታይ መጣጥፍ በጊዜው አዘጋጅ ስለነበርሁ “እንገድልሃለን” ማስጠንቀቂያ ይደወልልኝ እንደነበር አስታውሳለሁ።

በምዕራቡ አለም ኑሮ ለማቃናት ወከባ ስለሆነ ተረጋግቼ ለመጻፍ እድል ባላገኝም ከማነባቸው ይጠቅማሉ ያልኳቸውን ሁለት መጽሃፍት ተርጉሜ አንዱ “የተቆጡ አንበሶች” የሚል ታሪካዊ ልብ ወለድ በ2008 ዓ ም ካናዳ አሳትሜያለሁ። ለአገር ውስጥ አንባብያን ስላላቀረብሁ ስመጣ አሳትመው ይሆናል። ሌላው መጽሃፍ አልቆ ለህትመት ይደርሳል ብዬ እየጠበቅሁ ነው። እግዚአብሄር እድሜ ከሰጠኝ እጽፋልሁ የሚል እምነትና ተስፋ አለኝ።

 ቤተሰባዊ ሁኔታ

አቶ አንተነህ መርእድ ለዛሬ 35 አመት በፊት ከባለቤቱ ከወይዘሮ አልማዝወርቅ ክብረት መንገሻ ጋር ትዳር መስርቶ ሰላም አንተነህ እና ብሩክ አንተነህ የተባሉ ልጆችን አፍርቷል፡፡ሶስተኛዋ ልጁ የወንድሙ ልጅ የአምላክ ጥበብ የሺጥላ ከአምስት አመት በፊት ካናዳ አምጥቷት እርሱ ጋር ሆና የኒቨርስቲ ትማራለች። ስለሆነም አንድ ወንድና ሁለት ሴት ልጆች አሉት ማለት ነው።

መዝጊያ፣ የሚድያ ሰው አንተነህ መርእድ እምሩ እናት ሀገሩን በማገልገል የሚያምን፣ ይህንኑ በተግባር እውን ለማድረግ ሲጥር የኖረ ባለሙያ ነው፡፡ገና 20ዎቹ ውስጥ በደርግ ዘመን ታስሮ/ኢህአፓ ሆኖ./ በነበረበት ጊዜ አንድ እምነት ነበረው ኢትዮጵያ ውለታዋ ከፍ ያለ ስለሆነ ከፍ እንድትል የአቅሙን ማቀበል ይሻ ነበር፡፡ የወጣትነት ህልም ይከበራልና ይህን አልሞ ጫካ እስከመግባት ደርሷል፡፡ ይህንን ህልሙን በቆየባቸው የጋዜጠኝነት አመታት በከፊም ቢሆን አሳክቷል፡፡  እርሱ ከፊል ቢያሳካ ሌላው ከፊል እውን ቢያደረግ ነገር ከተቀየረ ያ ራሱ ቀላል አይባልም፡፡ አንተነህ፣ በ2 ሚድያዎች ላይ ተቀጥሮ ሲሰራ ብዙ ነገሮችን ታዝቧል፡፡ ለሀገር የሚደክሙ ቀን ተሌት ሲለፉ አይቷል፡፡ ለራስ ጥቅም የሚኖሩ ደግሞ የሌሎችን ያለ አንዳችይሉኝታ ሲወስዱ ተመልክቷል፡፡ ሃላፊነት የጎደላቸው  የመንግስት ሃላፊዎች ህዝብን ሲያሰቃዩ አብሮ ስቃዩን ቀምሷል፡፡በጋዜጠኝነት ፍጹም የሚባል ነጻ ወይም ትክክለኛ ይህ ነው ባይባልም በራሱ መንገድ ሚዛናዊ ለመሆን መጣሩን ከታሪኩ እንረዳለን፡፡ የሚድያ ባለሙያ አንተነህ፣ ሀገር ቤት ሆኖ ቢጽፍ ምንኛ ደስ  ባለው! ሀገር ቤት ሆኖ አንድ አሻራ ቢያኖር ሀሴቱ ምን ያህል ከፍ ይል ነበር፡፡ አንድ ነፍሱን ለመዳን ግን ተሰደደ፡፡ ሀገር ቤት ሳለ ብዙም  በገንዘብ እና በማቴሪያል መርካት አይቻልም፡፡ አሪኪ ባልሆነው የጋዜጠኝነት  ሙያ ሲሰራ ሀገሩ ይህን ለፍተሀል ይህን ተቀበል ባትለውም ሀገሩን እንደ ሀገር ሊርቃትና ሊወቅሳት አይወድም፡፡ እናት በምጥ ከወለደች ትፈልጋለች፡፡ ይህ ተፈጥሯዊ ነው፡፡ እናት አስከፍታም ጥላ አትጥልም፡፡ ዛሬ አንተነህ በምድረ- ካናዳ የራሱን መሰረታዊ ፍላጎት አሟልቶ ፤ ቤት መኪና የሚባሉት መሰረታዊ  ፍላጎቶች ኖረውት ስለሁሉ ማመስገኑን አላቆመም፡፡  የማያውቃት፣ ያልወለደችው፣ ካናዳ አቅፋ ደግፋ ስታኖረው ፣ አምጣ የወለደች እናት ፣ወላድ ናትና ልጄ ና ማለቷ አልቀረም፡፡ አንተነህ ፣ ሰው ድሎት ስላለው ርካታ ያገኛል ብሎ አያምንም፡፡ እርግጥ ነው ድሎት ቢመጣ  ማንም አይጠላም፡፡ ብቻውን ግን ምሉእ አያደርግም፡፡ ድሎት ይምጣ ግን ብቻውን አይምጣ፡፡ ሰው በሰው ሀገር ሆኖ የራሱንም ሀገር ሲረዳ እና ለሁሉ ሲተርፍ ደስ ይላል፡፡ የሚድያ ሰው አንተነህ ተምሮ ስራ አለው፡፡ ቤተሰቡን ይመራል፡፡ አሁንም ግን ያልማል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም ከውስጡ ገብታ አለህልኝ የምትለው ይመስለዋል፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች በባህር ማዶ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን በየጊዜው በስልክ ፣በቴሌግራም፣ በኤሜይል፤ በዋትስ አፕ ስናነጋግር እንዲነቁ እንፈልጋለን፡፡ ታሪካቸው እንዲዘከር የምንሻውም በኢትዮጵያ የትናንት ፤ የዛሬ እና የነገ እድገት ላይ ድርሻ ስላላቸው ነው፡፡ የሚድያ ሰው አንተነህ ሀገር ቤት መጥቶ አንድ ቁምነገር መስራቱ አይቀርም፡፡ እስከዛሬ የሰራቸው ለእርሱ ጅምር  ናቸው፡፡ ጅምሮችም ቢሆኑ መሰረት ያላቸው ናቸው፡፡  የሚድያ ሰው አንተነህ በኢትዮጵያ የነጻ ፕሬስ ጋዜጠኝነት ላይ፣ የበኩሉን አሻራ ማኖሩ አልቀረም፡፡  ከዛሬ 40 አመት በፊት ከሞት ተርፎ ነበር፡፡ ዛሬ አለ፡፡ ተመስገን! ይህን የምስጋና ቀን በእናት ሀገሩ ፤ የሀገሩን አየር እያሸተተ  ማክበር ይፈልጋል፡፡ ይህ ደግሞ በቅርቡ እንዲሆን እየተመኘን ለአቶ አንተነህ መርእድ ከእነ መላ ቤተሰቡ  ሰናይ ሰናዩን ብቻ እንመኛለን፡፡/  ይህን የአቶ አንተነህ መርእድን ታሪክ እንድንሰራ ለዊኪፒዲያ ቦርድ የጠቆመውን የኢሳቱን ሲሳይ አጌናን ማመስገን እንወዳለን፡፡ ይህ  ጽሁፍ በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ የተጻፈ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበት በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡/

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች