36. አዲስ ገብረማርያም -ADDIS GEBREMARIAM

    (ውልደትና እድገት)

 አዲስ ገብረማሪያም በጠንካራ የሬድዮ ድራማ ደራሲነቱ ይታወቃል፡፡ ሁልጊዜም ራሱን ከመጻፍና ከንባብ ጋር ያቆራኘው አዲስ ገብረማሪያም በቀን ቅኝት የሬድዮ ድራማው አቅሙን ያሳየ ነው፡፡ አዲስ ገብረማሪያም ማነው? ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ባለፉት 2 ወራት የጥበብ ፤ የመዝናኛ እና የመረጃ ሰዎችን ግለታሪክ በአጭሩ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል፡፡ አሁንም የአዲስን እነሆ::

      አዲስ  ለአባቱ አቶ ገ/ማርያም  ቄንሶና ለእናቱ ሐረገወይን አጥናፌ ሶስተኛ ልጅ ነው። የተወለደው ሐረር ከተማ ልዩ ስሙ አደሬ ጢቆ የሚባል አካባቢ ነው። መምህር የነበሩት አባቱ የስራ ቦታቸው ከሐረር 300 ሜትር  ርቃ በምትገኘው ሀብሮ(ገለምሶ ) ነበር ፤፤

     አዲስ ሲያድግ ተርቧል ..ጠግቧል...የተጣፈ ሱሪ ለብሧል ..ዘንጧል ። ሠርቋል..የተሠረቀ መልሧል ..አልቅሧል ስቋል ።

      አዲስ..ትንሽ ትንሽ ኳስ ተጫውቷል ። ብዙ ሩጯ ሮጧል ። ሌባና ፓሊስ ..ድብብቆሽ ..ውጊያ..ቆሪኪና ብይ ደርድሮ መበላላት..ወንዝ ወርዶ መዋኘት በእንጨትና ኩሽኔታ መኪና ህፃንነቱ ያለፈባቸው ጨዋታዎች ነበሩ ። ከጓደኞቹ ጋር ቲኒ (በልስ) ቆርጦ ፣ የወፍ ቆሎ ፣ ዋንዛ ወሽመላ ቀጥፎ በልቷል ። ሆያ ሆዬ ጨፍሯል ። የእንቁጣጣሽ ሰእሎች ስሏል ። የፍቅር ግጥም ለራሡ ፣ ላፈቀሩ ጎደኞቹም ፅፎላቸዋል ። የቆርቆሮና የቀርከሃ (መቃ) ሙዚቃ ጓድ እያቋቋመ ሰፈሩን አዝናንቷል ።

        የልጅነት ጊዜያቶቹ ግን በጨዋታ ብቻ ያለፉ አልነበሩም ።የቤተ- መጽሐፍት ሃላፊ የነበሩት አባቱ ከሰበሰቧቸውን መፀሐፍት እያወጣ በንባብ የሚመሰጠው ታላቅ ወንድሙ ዮናስን ዳና መከተል ጀመረ።  አይኑን የማረከውን መፅሐፍ ፣ ቢገባውም ባይገባውም መግለጥ ጀመረ። በዚህ የተጀመረው ከመፀሐፍት ጋር ጓደኝነት በወንድሙ እገዛ ፣ አዳዲስ መፅሐፍት በሚገዙት አባቱ ማበረታቻ እየጎለመሠ፣ የጨዋታ ጊዜውን የማንበብ አመል እየተካው መጣ ።

    ትምህርት..እስከ ስምንት

  አዲስ ትምህርት የጀመረው ወ/ሮ የሺመቤት ት/ቤት ነው ። ክፍል ውስጥ መደበኛ የሚባል ተማሪ የነበረ ቢሆንም ፤ የሬድዮ ዜና ፣ ሙዚቃ ፣ አንብቦ ያገኛቸውን ለጓደኞቹ በማቅረብ ይለያል ። አንድ ተማሪ ያወጣለት "ፈላስፋው " የሚል ቅጥያ ስሙ እስከሚሆን ደርሶ..ሲጠራ ይዞር ነበር።

     አዲስ ቄስ ትምህርት ተምሯል ። የሡ ለየት የሚለው ወደ ቄስ ትምህርት የሄደው፣ ፊደል ለመቁጠር አልነበረም። ፈደል ቀድሞ የሺመቤት ቆጥሯል ። ወደ ቄስ ትምህርት ያመራው የክረምት እረፍት በዋዛ እንዳያሣልፍ በሚፈልጉት አባቱ አስገዳጅነት ነበር ። እዚያ ላይ የምንማርበት ቦታ ጠረን ፣ የመምሩ ግርፊያ ተጨማምሮ ፤ የቄስ ትምህርቱን ጊዜያት 'የማያስደስት ትዝታ ' አድርጎበታል ።

    እስከ ስድስተኛ ክፍል የነበረውን የየሺመቤት ት/ቤት ቆይታ በ6ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና አጠናቆ ፣ ወደ ራስ መኮንን ት/ቤት አቀና ።  መካከለኛ ተማሪነቱ የቀጠለ ቢሆንም ፤ የንባብ ፍላጎቱ እየጨመረ ፣ ፊልም የመመልከት አዲስ ጨመረ ። ሃጂ ቦምባ የተሠኘው ሲኒማ ቤት የተጀመረው ፊልም የማየት ልክፍት ገንዘብ ሠርቆ ፣ ከት/ቤት ፎርፌ እየመታ ቀጠለበት ። አቤት ያየኋቸው ፊልሞች ብዛት! ማዘር ኢንዲያ ..ሃቲ ሜሪ ሣቲ ..ዎክት ..ኩሊ..ማርድ..የሆሊውድ ቢባል..ክሊዎፓትራ..ኢንዲያና ጆንስ..ስፓርታከስ..ደርቲ ዶዝን..ኮናን ዘ ባርቤሪያን ..ዘ ድራንክን ማስተር የፊልም ማየት ልክፍቴን ሣስበው ይገርመኛል ። ሃጂ ቦንባ ፊልም ቤት የጠዋት (አንድ ፊልም)  ፣ የቀን (ሁለት ፊልም ) ፣ የማታ (አንድ ፈልም) ነበር ኘሮግራሙ ። ብታምኑም ባታምኑም የሦስቱንም ፕሮግራም ፊልሞች እመለከት ነበር ። ከጅብ እየተገናኘሁ ያመለጥኩባቸው ጊዜቶች ነበሩ ።

    ሰከንደራ ትምህርት..

      የ8ኛ ክፍል መልቀቂያ አልፌ ዘጠነኛ ክፍል የገባሁት ሐረር መድሃኒአለም አጠ/ሁለተኛ ደ/ት/ቤት ነበር ። ነገር ግን ወደ አስር እንዳለፍኩ ፣ አባቴ ተቀይሮ አስተዳዳሪ ወደ ሆነበት ሐረር ጁኒየር2ኛ ደረጃ ት/ቤት እንድቀየር አደረገ ። ለመከታተል አስቦ ያደረገው ቢሆንም መደበኛ ተማሪነቴ ፣ ልክፍተ-ሲኒማው ላይ የንባብ ፍላጎቴን አልቆ ፣ ድራማ የመስማት ጉጉቴን ጨምሮ መጣ ።

    ማትሪክ ወገመች!

     በእርግጥ ዪኒቨርሲቲ ለመግባት ለ12ኛ ከ/መልቀቂያ ፈተና ጠንክሬ ነበር ያጠናሁት፡፡ ማትሪክ ግን ወገመች! ለትምህርት ትልቅ ቦታ ያለው አባቱ ፣ ወዲያው ነበር አለማያ ዩኒቨርሲቲ ተመዝግቦ የማታ ትምህርት እንዲጀምር ያደረግኩት ። ማኔጅመንት ! ከቁጥርና ጋር እየተሟገተ ሁለተኛ አመት ላይ ቢደርስ ፤ የሐረር ከተማ ባህልና/ስፓርት ክፍል የተውኔት አፃፃፍና ትወና ለማሰልጠን ማስታወቂያ አወጣ ። ተመዘገበ ። ስልጠናውን መከታተል ጀመረ። የዩኒቨርሲቲው ትምህርትና ስልጠናው ክፍለ -ጊዜዎች ግን እየተጋጩ መጡ ። ቤተሠብ እየከፈለ ከሚያስተምረው ትምህርትና ከስልጠናው መምረጥ የግድ ነበር ። አዲስ ኪነትን መረጠ ። ሁለት ሊመረቅ ሁለት አመት የቀረውን ማኔጅመንት ትቶ ፣ ከስድስት ወር በኋል በትወናና ቴአትር አፃፃፍ ተመረቀ ።

  አማተር ክበብ ..ቴአትር ..ህይወት

     ከመሠል ጓደኞቹ ጋር 'ኢቲዮፒስ ' የተሠኘ የቴአትር ክበብ አቋቁሞ መንቀሣቀስ ጀመረ። ትልቅ የስራ ተስፋ ያለውን ማኔጅመንት ትቶ የስነጥበብ ለዚያውም የአማተርነትን መንገድ መምረጥ ፣ ትልቅ ድፍረትና እብደት ሊሠኝ የሚችል ነበር ።

       ብስራት በሚባል መሠል ክበብ ውስጥ ይንቀሣቀስ የነበረው መስፍን ጌታቸው ፤ ክበቦቹን የማዋሃድ ሃሣብ አመጣ ። ተዋሃድን ቀጠለና ቅርስ የተሠኘ ቴአትር አዘጋጅተን ከሃረር አልፎ እንደ ጅጀጋ .ጉርሡም ፣ ባቢሌ ፣ ድሬደዋ ፣ ጨለንቆ፣ ሂርና ፣ ደደር ፣ ጭሮ ፣ አዋሽ ፣ መተሃራ ፣ አዳማ ፣ ወንጂ፣ ቡሾፍቱ የመሣሠሉ ከተሞች ለሚገኙ ቴአትር አፍቃሪዎች በማቅረብ የጥበብ ደጅ እንድረግጥ ሆነ።

 ከትወና ወደተውኔት ..

       ሸገር በር የደረሠው ቡድን የጥበብ ወለላ ቀምሶ ያጣጣመው አማተር አርፎ ሐረር እንዴት ሊቀመጥ ። መስፍን ጌታቸው ለሣላይሽ የስ/ማ/ ኢንተርፕራይዝ ተውኔቱ እንዲሠራ ሲሠጥ ከሐረር ለትወና ከተመረጡት መሃል አዲስ አንዱ ሆነ።

          አንድ ቀን የፃፈውን የሬድዮ ድራማ ቴአትሩ ልምምድ ላይ ለሚሣተፉት ተመስገን አፈወርቅና ሱራፌል ወንድሙ እንዲያዩለት ሠጣቸው ። በወቅቱ ታዋቂ የነበሩት ሁለቱም የሰጡት ጥሩ አስተያየት ነበር ። አስተካክሎ የድሮው የሬድዮ ጣቢያ አቡነ ጴጥሮስ አመራ ። በወቅቱ የድራማ ክፍል ሃላፊ የነበረችው ቤዛዊት ግርማ ተቀበለችው ።አሁን በትክክል በማያስታውሠው ምክንያት ድርሠቱን ይዞ ተመለሠ።

በኢትዮጱያ የሚገኙ ከተሞች መተወን ተከተለ። ከነዚህ ጉዞዎች መልስ ሲያሻሽል የቆየውን ድራማ ይዞ ወደ አቡነ ጴጥሮስ ብቅ አለ። አሁን የተቀበለው ዳንኤል አያሌው ነበር ። ጥቂት የማስተካከያ አስተያየቶች ብቻ። በሁለተኛው ቀጠሮ ወደ አቡነ ጴጥሮስ ስመጣ ፣ የሬድዮ ድራማዬን ተዋንያን እያጠኑት ነበር ። ለእኔም አንድ ፓርት ተቀምጧል ! ቀጣዩ ቅዳሜ "የፍቅር ደውል " ለአድማጭ ቀረበ!

መፃፍ መኖር በሸገር !

ከሣላይሽ ጋር የሠራንበት ቴአትር ሲጠናቀቅ ወደ ሃረር ከመመለስ ውጭ ሃሳቡም አቅሙም አልነበረንም ። ሌሎቹ ጓደኞቻችን ሲመለሡ እኔና መስፍን በማናውቀው ግፊት ለመቅረት ወሠንን ። ሌላ ስራም ሆነ ገቢ ባይኖረንም፤ ሣሪስ ሃምሳ ስምንት የሚባል ሠፈር "መኖር " ጀመርን ።

       እኔም ፣ አርአያዬን የተከተለው መስፍንም የሬድዮ ድራማ እንፅፋለን ። እንተውናለን ። ቤተሠብ ይደጉመናል ። መልካም የሚባሉ አከራያችን ከነልጆቻቸው የእናት ያህል ነበሩ። ኑሮ ቀጠለ ። እንደጉድ ይፃፍ ጀመር። ቃየል..የትላንቱ ነገ..ሀውልት ..ማለፊያ..ሻማ..የመፀሐፍ ገፆች ለቅዳሜና እሁድ መዝናኛ በአዲስ ተፅፈው ከተተወኑ የሬድዮ ድራማ ጥቂቶቹ ናቸው ።

ቴአትር..ተከታታይ ድራማዎች ..

           በሬድዮ ድራማ የተፍታታው የአዲስ እጆቸ ፤ ትንሽም ፋታ ስላገኝ አንድ "ቃየል"የሚሠኝ የሬድዮ ድራማውን ወደ ተውኔት ቀየረው፤ አበበ ፈለቀ አዘጋጅቶት ለብሔራዊ ቴአትር መድረክ አበቃው ።

        የሬድዮ ድራማ ፀሐፊያን የሚፈልገው ፓፑሌሽን ሚዲያ ሴንተር ሴንተር ማስታወቂያ ያወጣል። አዲስ ለመመዝገብ ዳተኛ ነበር። መስፍን ግን ሲቪያቸውን ይዞ በመሄድ ተመዘገቡ ። ከተመረጡት ፀሐፍያን መካከል ሆኑ።

        ሴንተሩ አዲስ የአሠራር ስልት ነበር ይዞ ብቅ ያለው ። በጋራ የመፃፍ ዘዴ። መንገዱ ለብዙ ፀሐፊያን የማይመች ስለነበር ፤ ብዙዎቹ የስራው ጅማሮ ላይ ነበር እየተው የሄዱት ። አዲስ ፣ መስፍንና ዳንኤል አበበ ቀሩ ። የቀን ቅኝት ተፀነሠ -ተወለደ ። ፍሬው ያማረ ነበርና ማለዳ..መንታ መንገድ ..የረገፉ ፈትሎች ..የብርሃን አፅናፋት ..ሠቀቀን የሚሠኙ ተከታታይ ድራማዎችን ከጓደኞቹ ጋር በመሆን አዲስ ለ'አይነ ስጋ ' እንዲበቁ አድርጓል።

     '  ህልም እልም '..የዘመን ችግኞች ..ደቦ..ማለፊያ..ዘመን የሚሰኙት የሬድዮና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎች ውስጥ አዲስ የበኩሉን አበርክቷል ።

       አዲስ በሚችለው አቅም ፤ በሚፈቅድለት መንገድ ይፅፋል። ከሞከራቸውም ውጭ ለመምከርም ያስባል።

         አዲሰ በፍቅር ሃያልነት ያምናል ። በፍቅር ሰዎች ሲረቱ፤ በሮች ሲከፈቱ አይቷልና ። ከዚህ ውጭስ የህይወት መመሪያ ይባል የህይወት ፍልስፍና ከየት ሊያገኝ ኑሯል !

       አዲስ ፍለጋ ላይ ነው ። በሁሉም አቅጣጫ የሚደረግ ፍለጋ ። ይሄ ፍለጋ የሚያስገኝለትን ለሌላው ለመስጠት በቅንነት ቃል ይገባል ። ይሄ እንዲታወቅለትም ይፈልጋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች