34. ነጋሽ መሐመድ ይገዙ- NEGASH MOHAMMED YIGEZU
ኃላፊነት የሚሰማው ምርጥ ጋዜጠኛ
ነጋሽ መሐመድ ይገዙ ሐምሌ 16፣ 1958 አልዩ አምባ ተወለደ።ጋዜጠኛ እና አሰራጭ (ብሮድካስተር)
ነዉ።በ1981 ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተመረቀ።ከጥቂት ወራት በኋላ በ1982 ማስታወቂያ ሚንስቴር (በእጣ) ከዚያም ኢትዮጵያ ራዲዮ በአብዛኛዉ ሕዝብ
ዘንድ ዜና ፋይል ተብሎ በሚታወቀዉ የዜናና መዋዕለ ዜና ክፍል በነባር ፕሮግራም አዘጋጅነት ተቀጠረ።
በተማሪነት ዘመኑ
ምኞቱ አስተማሪ መሆን ነበር።ይሁንና ዕውቁ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም ከሚመራው ክፍል ሲመደብ፣የጋዜጠኝነት
ሙያ የሚጠይቀዉን ክሒል፣ ዕዉቀት፣ ሥርዓት፣ ኃላፊነትና ሥነ-ምግባር ለማሟላት ብዙ አላዳገተዉም። ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን
ከዚህ ቀደም ከ100 በላይ የሚጠጉ በጥበብ፤ በመረጃ እና
በመዝናኛ ዘርፍ ያሉ ሰዎችን ታሪክ ሲያቀርብ ነበር፡፡ አሁን ደግሞ የነጋሽ መሀመድን የህይወት እና የስራ ገጽ መግለጽ ልንጀምር
ነው፡፡
መሠረት - የንባብ ፍቅር
በዩኒቨርስቲ
ትምሕርቱ የወሰዳቸዉ የኦዶ ቪዥዋል፣ የምርምርና ዘገባ አፃፃፍ (Research and report writing)፣ትርጉም፣የድርሰት
አፃፃፍ (Composition) ሥነፅሁፍና ሌሎችም ኮርሶች ለፈጣን ስኬቱ እርሾ ሆነዉታል።
ይሁንና «ራዲዮ
ማድመጥ የጀመርኩበትን ጊዜ አላስታዉስም።በልጅነቴ እቤታችን ዉስጥ በክብር የሚቀመጡ ሶስት ነገሮች ነበሩ።» ይላል
ነጋሽ።«የእናቴ ጌጦች (በአብዛኛዉ የብር) የአባቴ አሮጌ ጠመንጃ (ምናልባት ምንሽር) እና 6 ባትሪ የሚጎርስ ትልቅ
ራዲዮ----» መፅሐፍ፣ ጋዜጣና መፅሔት ማንበብ፣ ወቅታዊ ጉዳይ መከታተል የጀመረዉ የ4ኛ ክፍል ተማሪ በነበረወቅ ነዉ።«ጋዜጠኛ
ባልሆንም፣ ጋዜጠኛ ከመሆኔ ከብዙ አመታት በፊት የጀመርኩና የወደድኳቸዉን ማንበብ፣ ማድመጥና ወቅታዊ ሐገራዊና ዓለም አቀፋዊ
ጉዳዮችን መከታተል አልተዉም ነበር» ይላል ነጋሽ።»
መፅሐፍት መርጦ
የማንበብ ችሎታና ፍላጎቱ፣ ቢቢሲን የመሳሰሉ ዓለም አቀፍ ማሰራጪያ ጣቢያዎችን ማድመጥ፣ News week እና Time የመሳሰሉ
መፅሄቶችንና ሌሎች ሊያገኛቸዉ የሚችላቸዉን ጋዜጦችና መፅሔቶችን ማንበቡ አቅጣጫ ጠቋሚ (ኮፕፓስ) ሆኖት፣ ሰፊና ጥልቁን
የጋዜጠኝነት ባሕርን በጥንቃቄ ግን በፍጥነት ወደ ትክክለኛዉ
መድረሻ ይቀዝፍ ገባ።
የመጀመሪያዉ የፋርስ
ባሕር ሰላጤ ጦርነት የፈነዳዉ ነጋሽ ሥራ በያዘበት ዓመት ነበር።1982።ወጣቱ ጋዜጠኛ ለሙያዉ፣በጣሙን ዜናን ለማጠናቀር፣
ላቀራረብና አነባበብ ቴክኒኩ፣ለዜና ፋይልም አዲስ ቢሆንም ቀድሞዉ ጣቢያዉን ከተቀየጡትና ረጅም ጊዜ ካገለገሉት የራዲዮ ጋዜጠኞች
እኩል፣ ካንዳዶቹም በበለጠ ጥራት፣ ዉበትና ጥልቀት ዘገባዎችን መተርጎም፣ ማጠናቀር፣ መተንተንና ማሰራጭት ችሏል።
የዜና ብልትን
የመለየት ልዩ ችሎታዉ፣ በሳል የቋንቋ ዕዉቀቱ፣ ድልብ የቃላት ሐብቱ፣ የአረፍተ ነገር አሰካክ ብልሐቱ፣ የሱና የሱ ብቻ የሆነዉ
የአነባበብ ቅላጼና ድምፁ ከመጠነኛ የዓረብኛ ዕዉቀቱ ጋር ተዳምረዉ በዚያ ዘመን ብዙዎች ከሚናፍቋቸው ጥቂት የራዲዮ ጋዜጠኞች
አንዱ ለመሆን በቅቷል።
የኢትዮጵያ ራዲዮን
እስከለቀቀበት እስከ 1992አ.ም ድረስ በነባር አዘጋጅነት፣ በከፍተኛ ሪፖርተርነት፣ በከፍተኛ አዘጋጅነት፣ በአንከርነት፣ በዜና
ክፍል የቡድን አስተባባሪነት፣ በዜና ክፍል ኃላፊነት፣ በአማርኛ ቋንቋ አስተባባሪነት አገልግሏል።
በ1992 የዶቼ ቬለ
(የጀርመን ራዲዮ) ባልደረባ ከሆነ በኋላም በዜና እና ዜና መፅሔት ተርጓሚነት፣ አዘጋጅነት፣አቅራቢነት፣በአርታኢ (ኤዲተርነት)
በወቅታዊ ጉዳዮች ከፍተኛ አዘጋጅነት፣ ፖለቲካዊ ጉዳዮች
ተንታኝነት፣ በተለያዩ ሳምንታዊ ዝግጅቶች አዘጋጅነት፣ በውይይት አዘጋጅና መሪነት፣ በማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች
አርታኢነት አገልግሏል።
«ማሕደረ ዜና»
የተባለውን ዝነኛ ሳምንታዊ ዝግጅት ራሱ ቀርፆት፣ ራሱ ጀምሮት እነሆ እስካሁን ከ20 ዓመታት በላይ እንደያዘው አለ።
ከ2011 ጀምሮ
የዶቼ ቬለ ምክትል ኃላፊ ሆኖ በማገልገል ላይ ነው።ከ1982 ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥና ኢትዮጵያ የምትካፈልባቸውን አካባቢያዊ፣
አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ታላላቅ ሁነቶችን፣ መድረኮችን፣ጉባኤዎችንና መግለጫዎችን በአካልም፣ ከሩቅም ሆኖ ዘግቧል።
በዚህም ምክንያት
ከ1980ቹ የመጀመሪያ አጋማሽ ጀምሮ ኢትዮጵያ ውስጥና ኢትዮጵያን የሚነኩ ትላልቅ ጉዳዮችን መገናኛ ዘዴዎች የዘገቡበት መንገድና
ታሪክ ሲወሳ የነጋሽ ተሳትፎ ካልተጠቀሰ ታሪኩ የተሟላ መሆኑ አጠራጣሪ ነዉ።
ነጋሽ- እንደ አሰልጣኝ
ነጋሽ መሐመድ ድንቅ
ጋዜጠኛ ወይም አርታኢ ብቻ አይደለም፤ ጋዜጠኞችን መልማይ፣ፈታኝ፣ አሰልጣኝ-ሙያውን አውራሽ ጭምር እንጂ።የራዲዮ የተለያዩ
ክፍሎች ኃላፊ ብቻ (አልነበረም) አይደለም፤ራዲዮ ጣቢያ መስራች፣ ፕሮግራሞ አፍላቂ (ፈጣሪ)፣ ቀራጭም ጭምር ነዉ።
በተለይ ኢትዮጵያ
ራዲዮ በነበረበት ወቅት ለኢትዮጵያ ራዲዮ እና ለራዲዮ ፋና በርካታ ፕሮግራሞችን ፈጥሯል፣ ቀርጿል።የኤፍ ኤም ስርጭትን
ለኢትዮጵያ ያስተዋወቀዉ የኢትዮጵያ ራዲዮ ነዉ።ለኢትዮጵያ ራዲዮ ለራሱ ያስተዋወቀዉ ግን እሱ ነዉ።ነጋሽ።
ዛሬ «ፋና
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት» የተባለው ጣቢያ ስም ሳይወጣለት ግን
በአማርኛና በኦሮሚኛ የሚያሰራጭ ራዲዮ ጣቢያ እንዲሆን በ1985 ግድም ሲወሰን፣የወደፊቱ የጣቢያዉ ኃላፊ አማካሪ፣ የአብዛኞቹ
ፕሮግራሞች ይዘት፣ ቅርፅና የስርጭት ጊዜ ሐሳብ አፍላቂና ተባባሪ ቀራጭም ነበር። ያኔ ከጣቢያው የስራ መሪ ከአቶ ሙሉጌታ ገሰሰ
ጋር አንድ ላይ በመሆን ፎርማት የመቅረጽ ስራዎችን ነጋሽ ያከናውን ነበር፡፡ የበለጠ ግን ጋዜጠኞች የማሰልጠኑን ተግባር ነጋሽ
ያከናውን ነበር፡፡ በተጨማሪም ፣ አቶ አማረ አረጋዊ በፖሊሲ ጉዳዮች ስልጠናዎችን ይሰጥ ነበር፡፡
የመጀመሪያዎቹ
የጣቢያዉ (የፋና) ጋዜጠኞችና በዚያው ሰሞን ሊመሰረት ታቅዶ
የነበረዉ የዛሬዉ ዋልታ ኢንፎርሜሽን ማእከል ጋዜጠኞች በተለይ
የዜና አሰባሰብ፣ አፃፃፍና አዘገጃጀት አሰልጣኝም ነበር።«ፍልሚያ» ትባል የነበረችው የቀድሞዉ የኢሕዲን (ልሳን) ጋዜጣ
«ማሕቶት» በሚል መጠሪያ ባዲስ ስምና መልክ ስትደራጅ የአደራጆቹ አማካሪ፣ የገፆችዋ አስተዳደር (ሌይ አውት) ሐሳብ ሰጪም
ነበር።
የኢትዮጵያ ራዲዮ
የሥነ-ምግባር መመሪያ Manwual (ታትሞ ይሆን?) ተባባሪ (ከአቶ ጥላሁን በላይ ጋር) አዘጋጅ (አስተባባሪ)፣ በተለይ
የማንዋሉ የዜና እና የወቅታዊ ምዕራፎች ደራሲ ነበር።ከ1983 ጀምሮ በየጊዜው የሚቀጠሩ የኢትዮጵያ ራዲዮ ጋዜጠኞች መልማይና
አሰልጣኝም ነበር።
ኢትዮጵያ ራዲዮና
ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጣምረው (ከመንግስት ቀጥታ ቁጥጥር ይወጣሉ ተብሎ ነበር) ድርጅት ሲሆኑ፣ የጣቢያዎቹ ጋዜጠኞች መዳቢ ኮሚቴ
(መጀመሪያ አባል) ኋላ ፀሐፊ ሆኖ ሰርቷል።የጋዜጠኞች ማሰልጠኛ ኮሌጅ ምስረታን ባጠናው በማስታወቂያ ሚንስትር በሚመራዉ ኮሚቴ
ዉስጥም የኢትዮጵያ ራዲዮ ኃላፊን በመተካት ላጭር ጊዜ ሰርቷል።
ዶቼ ቬለ ውስጥም
በተለይ ከ1998 ጀምሮ በተደረገው ለውጥ የጣቢያውን የሥርጭት ጊዜ፣ የዝግጅቶቹን ይዘቶችና አቀራረቦችን፣ ነባሮቹን ዝግጅቶች
በማሻሻል፣ አዳዲሶችን በመፍጠር፣ አዳዲስ ጋዜጠኞችን በመቅጠር፣ልዩ ዝግጅቶች በፕሮጀክት መልክ እንዲጠናቀሩ፣ ለየጋዜጠኛው
እንዲደለደሉና እንዲሰራጩ ሐሳብ በማፍለቅ፣ በማስተባበር እና ናሙና (የመጀመሪያ) ዝግጅቶችን በማቅረብ እየሰራ ነው።
ብዙ ነው።ብቻ
ከ1980ዎቹ ጀምሮ የኢትዮጵያ እና ስለኢትዮጵያ የሚዘግቡ መገናኛ ዘዴዎች በተለይም የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ ዘዴዎችና ጋዜጠኞች
ያሳዩት ለውጥ፣ እድገት ይባል ዉድቀት የነጋሽ መሐመድ ዕዉቀት ወፈርም፣ ቀጠንም ብሎ አለበት።
ልጅነት
ታላቅ እህቱ፣ «እናት አከል፣ አሳዳጊ፣ ተንከባካቢ፣ መካሪዬ----»የሚላት
የእናቱ ልጅ አይንሻ ሼሕ ሲራጅ ከታናናሾቹ አንዳቸውን ታቅፋ ወይም አዝላ ስታባብል የምታንጎራጎራቸዉን ዘፈኖች ወይም መዝሙሮች
ብዙ ጊዜ በተመስጦ ያዳምጣል።አንዳንዶቹን በኮልታፋ አንደበቱ እህቱን እየተሻማ ወይም ብቻውን ለማንጎራጎር ይመክራልም።
የሙዚቃ ፍቅሩ ያኔ
የጀመረ ይሆን? አናውቅም።ሙዚቃ ግን ይወዳል።አሁን ድረስ የትርፍ
ጊዜ ልምድ (ሆቢ) ቢጠየቅ በትክክል አያውቀዉም።ግን በትርፍ ጊዜዉ አንዳንዴ በስራዉም መሐል ያንጎራጉራል።ያነባል-ሙዚቃ
እያደመጠ።ወይም ጓሮዉን ይኮተኩታል-እያንጎራጎረ ወይም እያደመጠ።
በዚያ ጨቅላ ዕድሜው
ከእህቱ ከሚሰማቸዉ ዘፈን ወይም መዝሙሮች ምናልባት የብዙዎቹን ምንነት ጠይቆ ተመልሶለት ይሆናል።ያልረሳዉ ግን ይሕን ነዉ።
«ሐምሌ 16 ቀን
የመነጨው ምንጭ፣
ጥቁር ጤፍ አብቅሎ አፈራዉ ለነጭ---»
«ጥቁር
ጤፍ----ነጭ ይሆናል እንዴ?»
የመዝሙሩን ይዘት፣
የመልዕክቱን ምንና ለማንነት አስረዳችዉ።«አንተም እኮ የተወለድከዉ ሐምሌ 16 ነዉ---» አለችዉ እህቱ።1958፣ ሸዋ ጠቅላይ
ግዛት፣ በተጉለትና ቡልጋ አዉራጃ፣ አንኮበር ወረዳ፣ ከጥንታዊቱ የንግድ ከተማ አልዩ አምባ (ሳር አምባ ቀበሌ) ተወለደ።
ነጋሽ የሚለው ስም
የተሰጠውም በልደቱ ዕለት ምክንያት ነዉ።
የአንደኛ ደረጃ
ትምህርቱን እዚያዉ አልዩ አምባ ጀምሮ፣ሙሉ 3ኛ ክፍል እንዳጠናቀቀ እናትና አባቱ ተለያዩ።ከእናቱ ጋር ቀረ። 4ኛ ክፍል አዋሽ
ቀጠለ። አራተኛ ክፍል እያለ እናቱ የሚመኩበት ርስት ተወረሰ።መሬት ላራሹ።አባት የለም። ርስት የለም።ድሕነት ፣አባት ሲቀነስ
ስድስት አባላት ካሉት ከነነጋሽ ቤት አይኑን አፍጥጦ ገባ።
የዕድገት በሕብረት
ዘመቻ መታወጁም «የተማረ ወደገጠር ሒድ እየተባለ፣ ትምህርት ምን ያደርጋል » ለሚሉት ለነጋሽ አጎቶች ጥሩ ሰበብ ሆኖ ከሚወደው
ትምሕርት አቋርጦ ሱቅ ጠባቂ እንዲሆን «ተፈረደበት።» አርባ ቦርደዴ።
በሱቅ ጠባቂነት
የሠራባቸዉን ሶስት ዓመታት «የፖለቲካ ሴራን፣ መገዳደልና መካካድን፣ የማሕበራዊ ኑሮ ዉስብስብ ሚስጥርን፣ የሰዎችን ባሕሪ፣
የኑሮን ጣጣ----ያየሁበት፣ ብዙ ያነበብኩበት፣ሐላፊነት መሸከምን፣ ራስን መቻልን፣ የሕይወትን ጡቃንጡቅ የተማርኩበት፣ ዓለምን
በዕዉቀቴ ልክ የተረዳሁበት፣ የወደፊት የሕይወት አቅጣጫዬን የቀየስኩበት፣ የወሰንኩበትም ይለዋል።»
ከኢሕአፓ ፓምፕሌቶች
እስከ ፍቅር እስከመቃብር፣ የሶማሊያ መንግሥት ከሚበትነው ወረቀት እስከ ማክሲም ጎርኪ መፅሐፍት (ትርጉም)፣ ከአዲስ ዘመን/
የዛሬይቱ ኢትዮጵያ እስከ የማሞ ዉድነሕ ትርጉሞች፣ ከጎሕ መፅሔት እስከ ካድማስ ባሻገር---- ያነበበዉ ያኔ ነዉ።
የአብዮታዊት
ኢትዮጵያ ራዲዮ፣ ሞቃዲሾ ራዲዮ፣ የጀርመን ድምፅ፣ ካይሮ ራዲዮ፣ የኢዲዮ ራዲዮ፣ እንዱሩማን ራዲዮ ወዘተ ጣቢያዎችን ያለማቋረጥ
ይከታተል ነበር።
የሚሰራበት ሱቅ
ከከተማይቱ ትልቁ፣ ሥፍራዉ አማካይ፣ ትልቅ ራዲዮ (ቴፕ) ያለበት በመሆኑና በተለይ የጀርመን ራዲዮ ብቸኛዉ ገለልተኛ የዜና
ምንጭ በመሆኑ፣ የዚያች ትንሽ ከተማ አስተማሪዎች፣ የቀበሌ መሪዎች፣ የፖሊስና የጦር ሠራዊት አዛዦች፣ሽማግሌዎች ወዘተ የ11 ሰዓቱን ሥርጭት ለመከታተል እዚያ ሱቅ ይሰበሰቡ ነበር።
በአጭር ሞገድ
የሚሰራጨዉን መልዕክት ተሰብሳቢዎቹ እንዲያደምጡ የዚያን ትልቅ ራዲዮ
ጣቢያ መፈለጊያ (ሞጃ) እያሽከረከረ የማስተካከሉ ኃላፊነትና «ዕውቀት» የነጋሽ ነበር።
«እነዚያ ትላልቅ፣
የተማሩ፣ የብዙ ሰዉ አለቆች (አንዳዴ የሱቁ ባለቤት ጭምር) ትንሿ እጄ ላይ አፍጥጠዉ ሲጠብቁኝ ሳይ፣ ትልቅ ኩራትና ርካታ
ይሰማኝ ነበር» ይላል ነጋሽ። «ዜናዉ ወይም ትንታኔዉ ባይገባኝም
ከስርጭቱ በኋላ ተሰብሳቢዎቹ የሚያደርጓቸዉ ክርክሮችና የሚሰጡት ማብራሪያ ይማርከኝ፣ ብዙ ዕዉቀትም አገኝበት ነበር።»
መፅሐፍት፣ ጋዜጣና
ሌሎች የሚነበቡ ፅሁፎችን የሚያዉሱት በአብዛኛዉ ቦርደዴ የነበሩ አስተማሪዎች ነበሩ።
ነጋሽ ባለሱቅ ወይም
ባለ መቅሐዊ (ሻሒ ቤት) የመሆን ሰፊ እድል ነበረዉ። አልፈለገም።የተማረዉ እስከ 4ኛ ክፍል ብቻ ቢሆንም የስድስተኛ ክፍል
ሚኒስትሪን (የአንደኛ ደረጃ መልቀቂያ ፈተና) ተፈትኖ በአኩሪ ዉጤት አለፈ።ሥራዉን አቆመ።እንደገና ትምሕርት።
ትምሕርት ያቋረጠዉ
ለ3 ዓመት ቢሆንም፣ ከትምህርቱ ጊዜ ያባከነዉ ግን አንድ ዓመት ብቻ ነዉ።ሰባተኛ ክፍልን አዋሽ ጀመረ።ከወራት በኋላ ወደ
ናዝሬት ቀየረ።ሁለተኛ ደረጃንም እዚያዉ ናዝሬት አጠናቀቀ።1977።
የሁለተኛ ደረጃ
መልቀቂያ ፈተናን ከወሰደ በኋላ መሰረተ ትምሕርት ለማስተማር አዳአ አዉራጃ፣ ጨፌ ዶንሳ ወረዳ፣ ጠዴ ቀበሌ ገበሬ ማሕበር ዘምቷል።በልጅነቱ
አልዩአምባ በትናንሽ ዓይኑ ያየዉን የገበሬዎች ኑሮ በጉርምስናው እንደገና አየው።«ስለ ደገኛዉ የኦሮሞ ገበሬ ባሕል፣ ሥራና
አኗኗር በቅርብና ብዙ ያወቅሁበት ነው» ይላል።በ1978 አዲስ
አበባ ዩኒቨርስቲ ገባ።
ዳራና አጋጣሚ
አራተኛ
ክፍል።የስፖርት ነገር ብዙ አይሆንለትም።የዚያን ቀን የመጨረሻዉ ፔሬድ ነዉ። 5 ሰዓት ከ45 ግድም። የአዋሽ ፀሐይ
ገርራለች።የስፖርት አስተማሪዉ የነነጋሽ ክፍል ተማሪዎችን ይዘዉ ወደ ሜዳ ወጡ።ተማሪዎቹን አንድ ሁለት ዙር ሜዳዉን አስሮጡና
ትንሽ ጅምናስቲክ ብጤ አሰሯቸዉ።
«ቲቸር ዲኖ
ይባላሉ።የሒሳብና የሌላም (ረሳሁት) አስተማሪያችን ነበሩ።ጂምናስቲኩን እንደጨረስን ኳስ ተጨወቱ ብለዉ እሳቸዉ ሔዱ።» እኔና
አንድ ጓደኛዬም ጨዋታዉን ትተን ዛፍ ጥላ ስር ሔደን ቁጭ አልን።
የዛፉ ግንድ ከብቶች
እንዳይግጡት፣እንዳይታከኩት ይሁን ሰው እንዳይደገፈው ባይታወቅም እስከወገቡ ድረስ በ4 ማዕዘን ሳጠራ የተጋረደ በመሆኑ በሌላ
አቅጣጫ የሚደረግ እንቅስቃሴን ቶሎ ማየት አይቻልም።ሁለቱ ተማሪዎች ከተቀመጡበት በተቃራኒዉ አቅጣጫ ባለዉ የዛፉ ስር ሰዉ
መኖሩን ያወቁት አንድ ሌላ አስተማሪ «እዚህ ነሕ እንዴ» ብሎ
ወደ ዛፉ ሲጠጋ ነዉ።
«ቲቸር ዲኖ ጋዜጣ
እያነበቡ ነበር።ያናገራቸዉ አስተማሪ አጠገባቸዉ እንደደረሰ ቲቸር ዲኖ «ይኸ ሰዉዬ የፃፍኩትን ሁሉ ጎማምዶ ያተማትን ታያለሕ»
ብለዉ የጋዜጣዉን ገፅ ሲያሳዩት ተንጠራርቼ አየሁት። ጋዜጣዉ ምን
እንደሆነ አላወቅሁትም።ከገፁ ጥግ ግን አፍንጫዉ ረጅም፣ ጥቁር፣ ጉርድ ፎቶ የሚመስል ስዕል ተለጥፎበት አየሁ።»
ነጋሽና ጓደኛዉ ቦታ
ቀየሩ።እስኪደወል ድረስ ከአስማሪዎቻቸዉ ካዩትና ከሰሙት ሌላ ርዕስ አልነበራቸዉም።የቲቸር ዲኖን የጋዜጣ ላይ ፅሑፍ ለማንበብ
ሲሉ አምስት አምስት ሳንቲም አዋጥተዉ ጋዜጣዉን ገዙት።አስተማሪዎቻቸዉ የተነጋገሩበት፣አንድ ጥያቄ አለኝ የተሰኘዉ የጳዉሎስ ኞኞ አምድ ነበር።
የወደፊቱ ጋዜጠኛ፣
ለመጀመሪያ ጊዜ ጋዜጣ አነበበ።ከጥቂት ወራት በኋላ ያ ጥቁር፣ አፍንጫ ረጅም፣አይን፤ ፀጉርና ጢም አልባ ፎቶዉን እዚያ ጋዜጣ ላይ ያዩት ሰዉዬ ወደ ድሬዳዋ ሲያልፍ አዋሽ (ሰብለ
ወንጌል) ትምሕርት ቤትን ለመጎብኘት መጣ።ይሁንና «የአዳራሽ ጥበት» በሚል ምክንያት የሰዉዬዉን ገለፃ ለመስማት የተፈቀደላቸዉ
አስተማሪዎች፣ የዕድገት በሕብረት ዘማቾች፣ የ5ተኛና የስድስተኛ ክፍል ተማሪዎች (ትምሕርት ቤቱ እስከ 6 ብቻ ነበር) ብቻ
ነበሩ።
እንግዳዉን ለመቀበል
በሚል ሰበብ ሌሎቹ ተማሪዎች እንዲጫወቱ ወይም ወደየቤታቸዉ እንዲሄዱ ቢፈቀድላቸዉም ነጋሽ እና ጥቂት ጓደኞቹ ስብሰባዉ
እስኪያልቅ ድረስ እዚያዉ ግቢ፣ ከመሰብሰቢያዉ ክፍል ፈቅ ብለዉ
ሰዉዬዉን ጠበቁ።
አዲስ አበባ እና
ድሬዳዋን የሚያዉቁ ልጆች ውጪ ስለቆመችዉ ሲትሮ ስለተባለችዉ የሰዉዬዉ መኪና ዘመናይነት፣ ሙሉ በሙሉ ስፒሪግ በመሆንዋ
እንደማትገለበጥ፣ ብትገለበጥም አደጋ እንደማታደርስ የሚሰጡትን ገለፃ ነጋሽና ብጤዎቹ ሲያዳምጡ ስብሰባዉ አበቃ።
ከስብሰባው ቀድመዉ
ከወጡት ተማሪዎች አንድ ሁለቱ «እስከ አራተኛ ክፍል ድረስ ነዉ የተማርኩት አለ----?» እያሉ ሲያወሩ ከነጋሽ ጆሮ ጥልቅ
አለ።ጋዜጠኛ መሆን ባይፈልግም ከ4ኛ ክፍል ሥራ መያዝ መቻሉን ሳያሰላስል አልቀረም።ወዲያዉ አንድ ረጅም፣ፈረንጅ የመሰለ፣
አፍንጫ ትልቅ ሰዉዬ ባስተማሪዎች ታጅቦ ብቅ አለ።ጳዉሎስ ኞኞ።
የመጀመሪያዉን ጋዜጣ
ባነበበት ዓመት፣ የመጀመሪያዉን ጋዜጠኛ አየ። የመጀመሪያዉን ድምፃዊዉም በዚያዉ ዓመት አየ።አያሌዉ መስፍንን።ራዲዮ ከልጅነቱ
ጀምሮ ያዳምጣል።ሙዚቃም ይወዳል።ጋዜጠኛም፣ ድምፃዊም የመሆን ጉጉት ግን አልነበረዉም።
ቦርደዴ እያለ
የሐረርጌ ክፍለ ሐገር ቋሚ የደርግ አባል በጠሩት ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ አንድ ጋዜጠኛና አንድ ፎቶ ግራፍ አንሺ አይቷል።ቀጭን፣
መጣጣ፣ አፍሮዉ (ጎፈሪያሙ) ጋዜጠኛ ስብሰባዉ ተጀምሮ እስኪያልቅ ድረስ ሲፅፍ ነበር።በ2ኛዉ ቀን በራዲዮ የተላለፈችዉ
ዜና ግን ሁለት ደቂቃም አትሞላ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ
በሁለት የተለያዩ ቀናት እትሞቹ ስለ ኩባ ሕዝብ ብዛት ያተሙት ቁጥር ግራ ቢያጋባዉ «ትክክለኛዉ የቱ ነዉ?» የምትል አጭር
ጥያቄ በሬኮማንዴ ልኳል።ጥያቄዉ መታተም-አለመታተሙን ግን አያዉቅም።
በ1974 አፄ
ገላዉዲዎስ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምርት ቤት ለመግባት ሲያመለክት የአብዮታዊ ኢትዮጵያ ወጣቶች ማሕበር (አኢወማ) አባል
መሆኑን የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ማቅረብ ግድ ነበረበት።የሚኖርበት ቀበሌ የአኢወማ አባል ለመሆን ሊመዘገብ ወደ ማሕበሩ ፅሕፈት ቤት
የሔደዉ ስንታየሁ ተካ ከተባለ ጓደኛዉ ጋር ነበር።
ከቦርደዴ ጀምሮ
ጓደኛሞች ናቸዉ።ሁለቱም የዘጠነኛ ክፍል ተማሪዎች ናቸዉ።በትምሕርት መስክ ግን ስንታየሁ ቴክኒክ፣ ነጋሽ ኮሜርስ ለመማር ነዉ
የተመዘገቡት።የአኢወማ አባል የሚያደርገዉ ቅፅ እጩዉ አባል ወደፊት መሆን የሚፈልገዉን በሚሞላበት ሥፍራ ላይ ስንታየሁ
ተሽቀዳድሞ መሐንዲስ (ኢንጂነር) ብሎ ሞላ።ነጋሽ የሚለዉ ጠፋበት።ትንሽ አሰብ አደረገ።እና «ጋዜጠኛ» ብሎ ሞላ።
«ከየት እንደመጣልኝ
አላዉቅም፣ ከሚያስሞላዉ የአኢወማ ሹም ጋር መፋጠጡ ሲረዝምብኝ ያልኩትን አልኩ።» አለ ነጋሽ ባንድ ወቅት።
ከዘጠኛ ክፍል ጀምሮ
ክፍል ዉስጥ ለአማርኛና ለእንግሊዝኛ ፅሁፎች አምባቢነት በተደጋጋሚ ይመረጥ ነበር።ጣምራ ጦር የተባለዉን መፅሐፍ ለእሱና
ለጓደኞቹ ባንድ ሌሊት ተርኳል።ነጋሽና በነጋሽ ግፊት የቅርብ ጓደኞቹ መሐመድ ዑስማንና ምኞቴ ነዋይ፣ አድማስ የተባለዉ የአዲስ
ዘመን ሳምንታዊ (ዕሁድ) አምድ ቋሚ ተከታታዮች ነበሩ።የላይብረሪ ጥናቱ ሲቸከዉ፣ የኢትዮጵያ ሔራልድ የአረፈ ዓይኔ ሐጎስና
የኤፍሬም እንዳለ ፅሁፎችን እንደ እንግሊዝኛ መማሪያ፣ እንደ መዝናኛና መረጃ
መገብያዎችም ያነባቸዉ ነበር።
አዲስ አበባ
ዩኒቨርስቲ እያለ ያኔ የታገደዉ የበአሉ ግርማ ኦሮማይ መፅሐፍ በታይፕ ተገልብጦ የተባዛውን ጥራዝ ጌታቸው መንግስቴ የተባለ
ጓደኛው ተውሶ አመጣ።አዋሹ ለአንድ ሌሊት ብቻ ነዉ የፈቀደላቸዉ።
ነጋሽንና
ጌታቸዉን ጭምሮ 7 ጓደኛሞች አንድ ዶርም ተሰበሰቡ። ነጋሽና
ጌታቸዉ እየተቀባበሉ ለተቀሩት ሲተርኩ አድረዉ ጧት ሁለት ሰዓት ላይ ጨረሱት።
ዉልደቱና የሕፃንነት
እድገቱ አማርኛ፣ አርጎብኛ የገበያ ቀንም ቢሆን አፋርኛ በሚነገርበት አካባቢ ነዉ።ዕድገቱ ኦሮምኛ፣ አማርኛ፣ ሶማሊኛ፣ አፋርኛ፣
አርጎቢኛ፣ አደሪኛ፣ አረቢኛ፣ ትግሪኛ የሚነገርበት የብዙ ጎሳ አባላት ተቀይጠዉ የሚኖሩበት አካባቢ ነዉ።
ከአማርኛ ሌላ
ኦሮሚኛን እየሰባበረም ቢሆን ይናገራል።አርጎብኛ፣ ሶማሊኛ፣ ትግሪኛ፣ አፋርኛ እና አረብኛ (በመጠኑ) ይሰማል።ከውጪ ቋንቋዎች
እንግሊዝኛና ጀርመንኛ ጠንቅቆ ያውቃል።
ሥራ
ዩኒቨርስቲ ለመማር
የመረጠዉ ሌላ ነበር።ነገር ግን የመጀመሪያ ዓመት ውጤቱ ምርጫዉን የሚያስጠብቅ ስላልነበረ የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነ-ፅሑፍ
የሚባለዉ ትምሕርት ክፍል ተመደበ። የመረጠዉን ላለማግኘቱ፣ ዩኒቨርስቲ ከመግባቱ በፊት ስለ ዩኒቨርሲቲ ባሕል በተለይ ስለ
አጠናን ሥልቱ በቂ መረጃ «ባለማግኘቴ» ነዉ የሚል ምክንያት ነበረው።
ይህ ምክንያቱ
ወትሮም አስተማሪነትን ከመውደዱ ጋር ተዳምሮ እንደተመረቀ ለጥቂት ጊዜ አስተምሮ በትምሕርቱ የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎት ነበረዉ።ግን የፈለገውን አላገኘም።
ትምሕርቱን ካጠናቀቀ
በኋላ በሌለበት እጣ ሲወጣለት ማስታወቂያ ሚንስቴር ደረሰው።አስተማሪነት ከደረሰዉ ከአንድ የትምሕርት ቤት ጓደኛዉ ጋር ለመቀያየር
ሞክሮ ነበር።ይሕም አልተሳካም።ማስታወቂያ ሚንስቴር ከገባ በኋላም የፕረስ ጋዜጠኛ መሆን ተመኝቶ ነበር።ከተለያዩ ዩኒቨርስቲዎችና
ከዉጪ (ሩሲያ) ከመጡና አብረዉት ማስታወቂያ ሚንስቴር ከተመደቡት 17 ልጆች ጋር መጀመሪያ ኢትዮጵያ ራዲዮ ተፈተኑ።ነጋሽ
እዚያው ትቀራለህ ተባለ።
የፈለገዉን
አያገኝም፣ አላገኘም።ግን ያገኘዉንና የሚያገኘዉን አልጠላም።
ከሱ ጋራ ራዲዮ
ከቀሩ ሌሎች 6 ባልደረቦቹ ጋር የመጀመሪያዉን መደበኛ ያልሆነ ስልጠና ወይም ልምምድ ጌታቸው ኃይለ ማርያም ሰጣቸው።ሥልጠናው
እንዳበቃ ሌሎቹ የተለያዩ ክፍሎች ሲመደቡ ነጋሽ በጌታቸዉ ኃይለማርያም ጥያቄ እዚያዉ ዜና እና መዋዕለ ዜና ዋና ክፍል
ቀረ።ሶስተኛ ዓመት ባነበበዉ ኦሮማይ መፅሐፍ ያወቀዉን ጌታቸዉን አለቃዉ ሆኖ በቅርብ አወቀው።
ጓድ ሊቀመንበር
መንግስቱ ኃይለማርያም የአየር ኃይል አብራሪዎችን ሊመርቁ በሔዱበት «ተነሳ ተራመድ» የተሰኘዉ መዝሙር ሲዘመር ስቅስቅ ብለዉ
ሲያለቅሱ ተለማማጁ ወጣት ጋዜጠኛ በቅርብ ርቀት አይቷቸዋል።
ሊያለማምደዉ
አስከትሎት የሄደዉ አንጋፋ ጋዜጠኛ ለመዘገብ ግራ ገብቶት ሲጨነቅ ተለማማጁ ዘገባዉን ፃፈለት።ዘገባዉ የአለማማጁ ተብሎ አለማማጁ
አነበበዉ።
ዜና በተለይ ካደረ
አይደገምም።የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ብላቴን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ጣቢያ ሲገቡ አብሯቸዉ የሔደዉ ነጋሽ መሐመድ በጉዞዉ መሐል
ከዘገባቸዉ አንዱ በአድማጮች ጥያቄ (አለቆቹ እንዳሉት) በማግስቱ ተደግመ።ጓድ ሊቀመንበር የመጨረሻዉን የሸንጎ ጉባኤ ሲመሩ
እዚያ ከነበሩት ሁሉ አዲሱ ጋዜጠኛ ነጋሽ ነበር።
አብነት
የከፍተኛ ትምሕርት
ተቋማት ተማሪዎች ለወታደራዊ ስልጠና ብላቴን ሲከትቱ ከጉዟቸዉ
እስከ ማሰልጠኛ ጣቢያቸዉ የነበራቸዉን እንቅስቃሴ ዘግቧል።
የኢሕአዴግ
ባለስልጣናት የመላዉን ኢትዮጵያን የመሪነት ሥልጣን ከያዙ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሰጧቸዉን መግለጫዎች በኢትዮጵያ ራዲዮ
ለመጀመሪያ ጊዜ የዘገበዉ ነጋሽ ነዉ።
የኢጋድ የመሪዎች
ጉባኤ፣ የምሥራቅ አፍሪቃ የንግድ ቀጠና (PTA) የመሪዎች ጉባኤ፣የደቡብ አፍሪቃ የሽግግር ጉዳይ የመሪዎች ጉባኤ፤ የአፍሪቃ
አንድነት ድርጅት ጉባኤ፣ የሱዳን ተፋላሚ ኃይላት ድርድር፣ የሶማሊያ ፖለቲከኞች ድርድር፣ የመሪዎች ጉብኝትን ወዘተ ለመዘገብ
ከግማሽ የሚበልጡ የአፍሪቃ ሐገራት ርዕሰ-ከተሞችና
አብያተ-መንግስታትን ተመላልሶባቸዋል።እስከ አምስቴ የሔደባቸዉ ሐገራት አሉ።
የአፍሪቃና የአዉሮጳ
መሪዎች ጉባኤ፣ የአፍሪቃና የፈረንሳይ መሪ ጉባኤ፣ የእስያና የአፍሪቃ ሐገራት (የደቡብ-ደቡብ ትብብር) ጉባኤ፣ የኢትዮጵያ መሪ
ጉብኝት ወዘተ፣ የቡድን 7/8 ጉባኤ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤን ለመዘገብ ከአቴና እስከ ሶል፣ ከኩዉላሉፑር
እስከ ኮሎኝ፣ ከበርሊን እስከ ቶኪዮ፣ ከፓሪስ እስከ ዋሽንግተን፤
ከኒዮርክ እስከ ለንደን ያሉ ከተሞችን አዳርሷል።
የኢትዮጵያ
(ኢህአዴግ መራሹ) የሽግግር መንግሥት ምሥረታ፣ ሕገ- መንግስት ማፅደቂያ፣ ምርጫ፣ የኢትዮጵያ ቋሚ መንግሥት ምሥረታ፣ የኔልሰን
ማንዴላ በዓለ ሲመት፣ የኤርትራ ሕዝበ ዉሳኔ፣የሩዋንዳ ጭፍጨፋን
በየሥፍራዉ ተገኝቶ ታዝቧል።ሁሉም የየራሱ ሙሉ ታሪክ፣ ልዩ ገፅታ፤ ትዝታና አጋጢሚ አለዉ።ጥቂቱን እንጠቀስ።
«አላሕ አወጣኝ»
«ሰዎች አጀብ ብለዉ
ሳይ ስለቃጠሎዉ ለማነጋገር ከመኪና ወረድኩ።ወዳሉበት ስራመድ አንድ መኪና አጀቡን ሰንጥቃ አለፈች----መኪናዋ መሐመድ አሚንን*
ይዛ ወደ ሆስፒታል መሆዷ ኖራል?» ብሎ ነበር ነጋሽ፣-ግንቦት 1983 በቅሎ ቤት አዲስ አበባ የደረሰዉን ፍንዳታና ቃጠሎ
ሲዘግብ ያጋጠመዉን ሲናገር።
የዚያን ቀን የማለዳ
ተረኛ አዘጋጅ ነበር። ያማርኛዉ ስርጭት እንዳበቃ ወደ ቤቱ ለመሔድ ሲዘጋጅ፣ በረከት ስምኦን የሚባለዉ የኢሕአዲጎች አለቃ
ከነአጃቢዎቹ ነጋሽ ቢሮ (ዜና ፋይል) ገባና ያልተፃፈ «መግለጫ» እንዲያነብ ጠየቀዉ።
ነጋሽ፣ መግለጫ
የሚያዉቀዉ በቅጡ የተተየበ፣ ይሰራጭ በሚል ሸኚ ደብዳቤ (ትዕዛዝ) የታጀበ፣ በፖስታ የታሸገ፣ እያንዳዱ ገፅ መግለጫዉ
እንዲሰራጭ ባዘዘዉ ክፍል ማሕተም የተዥጎረጎረ ነዉ።የዚያን ቀን ግን መግለጫዉ የለም።የአማርኛ የስርጭት ጊዜም አብቅቶ ኦሮሚኛ
ተጀምሯል።
ነጋሽ ሁለቱን
ምክንያቶች ጠቅሶ እንቢኝ አለ።የኢህአዲጉ አለቃ ተራዉን ጋዜጠኛ ለማግባባት በቅሎቤት አደጋ መድረሱን፣ ሰዎች ወደ አካባቢዉ
እንዳይሔዱ፣ እሳት አደጋዎች ቶሎ እንዲደርሱ ማስጠንቀቅ እንደሚገባ እየዘረዘረ ያስረዳ ገባ።
«ማስጠንቀቂያ ነዋ
መግለጫ አይደለም።»
«አዎ እንደሱ
ነዉ።» መለሰ ኃላፊዉ። «ኃላፊነቱን እኔ እወስዳለሁ።»
«ይፈርሙልኛል»
«ችግር የለም።ቶሎ
በል ብቻ»
ከሰዉዬዉ ጋር
ከመጡት ገሚሱ ያጉረጠርጣል፣ ሌላዉ ይስቃል፣ ብዙው ሁለቱ ላይ አፍጥጧል።ሰዉዬዉ ግን ትዕዛዝ አክባሪ ነዉ፤ ቢያንስ የዚያን
ቀን።እዚያዉ ዜና (ፋይል) ባለች አንዲት ቀጭን፣ ደረቅ፣ አረንጓዴ፣ አንድ እግረ ሰባራ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ፣ ወረቀቱን ጭኑ ላይ
አስደግፎ፣ አንዴም ሳያቋርጥ ፅፎ ጨረሰ።
የሰዉዬዉን የመጻፍ
ችሎታ፣ የሐሳብ ፍሰት፣ ፍጥነት አለማድነቅ አይቻልም።ከዓረፍተ ነገሮች መርዘም፣ «ሕዝቦች፣ ሰላምና መረጋጋት፣ ፀረ -ሠላም
ኃይሎች---ደርግ-ኢሠፓ----» በሚሉ የዘመኑ ካድሬ ቃላት መታጨቅ ባለፍ ፅሁፉ አንድም ሰረዝ የለዉም፣ ቁልጭ ብሎ ይነበባል፣
ወረቀቱ ልሙጥ ቢሆንም የፅሁፍ መስመሮቹ አልተንሻፈፉም።
ፃፈ፣ ፈረመም።
ወረቀቱን ነጋሽ ይዞ
ከሰዎቹ ጋር ተያይዘዉ ስቱዲዮ።የኦሮሚኛ አዘጋጆች ከጥቂት
ክርክርና ግርታ በኋላ የአማርኛ ማስታወቂያ እንዳለ ተናግረዉ፣ ዝግጅታቸዉን አቋረጡ።አዲሱ ጋዜጠኛ፣ አዲሱ ባለስልጣን
የፃፉትን አነበበ።
እና አደጋዉን
ለማየት በመኪና ወደ በቅሎ ቤት ሄደ።ትንሽ ቀደም ብሎ ቢሆን ኖሮ
እንደብዙ የአካባቢዉ ነዋሪዎች ሕይወቱን ወይም እንደ መሐመድ አሚን አካሉን ባጣ ነበር።«አላሕ ነዉ ያወጣኝ» አለ
ነጋሽ አንዴ በሰጠዉ ቃለ መጥይቅ።
«አቶ» አላቸው ።አቶ
ሆኑ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ
አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ጦር አዲስ አበባን ከተቆጣጠረ በኋላ፣ የግንባሩ ባለስልጣናት ለመጀመሪያ ጊዜ ለዉጪ
ዲፕሎማቶችና ለጋዜጠኞች የሚሰጡትን መግለጫና ማብራሪያ እንዲዘግቡ የዚያን ቀን ተረኛ የነበሩት ነባሮቹ የዜና ክፍል ጋዜጠኞች
ቢጠየቁ ፈቃደኛ ጠፋ።አዲሱ ጋዜጠኛ ተመደበ።
የእርዳታ እሕል
ከአሰብ እንዲገባ አሰብን ከሚቆጣጠረዉ ሻዕቢያ ጋር ስምምነት መደረጉን፣ ዋስትና መሰጠቱን፣ መንገዱ ሰላም መሆኑን፣ ለዲፕሎማቶቹ
ካብራሩት ከያኔዎቹ ባለስልጣናት መካከል ታምራት ላይኔ፣ አባይ ፀኃይዬ እና አርከበ ዕቁባይ ይገኙበት ነበር።
መግለጫዉ የተሰጠዉ
አዲስ አበባ ሒልተን ሆቴል ነዉ።መግለጫዉ 5 ሰዓት ግድም እንዳበቃ የዜና አገልግሎት፣ የራዲዮና የቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ባንድ
መኪና (በቴሌቪዥኖች መኪና) ወደ ቢሯቸዉ ሲመለሱ ነጋሽ ባልደረቦቹን ጠየቀ።
«ለመሆኑ እነዚሕን
ሰዎች እንዴት ብለን ነዉ የምንጠራዉ?»
«የኢሕአዴግ
ባለስልጣኖች ነዋ» አንዱ መለሰ።
«ማዕረጋቸዉስ?»
ጠየቀ ነጋሽ እንደገና።
መልስ የለም።ተረበኛ
ብጤዉ የቴሌቪዥን ጋዜጠኛ ---«እነሱ ጓድ ነዉ የሚባባሉት---»
«እኛ ጓድ ልንል
አንችልም።» አለ የዜና አገልግሎቱ
የቴሌቪዥኑ ቀበል
አድርጎ
«እኔ ማታ ስለሆነ
የምለቀዉ፣ ራዲዮ ቀን የሚያሰራጨዉን ሰምቼ እከተላለሁ።»
«እኔም ከምሳ በኋላ
ነዉ የምፅፈዉ» አለ የዜና አገልግሎቱ።በቴሌቪዥኑ ዘጋቢ አባባል መንከትከቱን አቁሞ።
«ተስፋ ያደረግሁት
ጋሽ ጌታቸዉን ወይም ዳርዮስን አማክሬ ማዕረጋቸዉን እወስናለሁ ብዬ ነበር።» አለ ነጋሽ ባንድ ወቅት።«ቢሮ ስገባ ማንም
የለም።አንባቢዉም ስቱዲዮ ነበር።ቢኖርም አይረዳኝም።አቶ አልኳቸዉ---ዘገባዬ ተሠራጨ።የተቃወመ የለም---በዚያዉ ቀጠለ።» አከለ
ነጋሽ።
መለስና ስዩም
ከደርግ ዉድቀት
እስከ ሽግግር መንግስት ምሥረታ አንድ ወር ግድም የቆየዉ የጊዜያዊ መንግሥት ፕሬዝደንትና የኢሕዴግ ሊቀመንበር መለስ
ዜናዊ የዚያን ማታ፣ ለመጀመሪያ ጊዜ መግለጫ እንደሚሰጡ
ተጠቆመ።ግንቦት ማብቂያ ወይም ሰኔ መጀመሪያ ነዉ።1983።
ኢሕአዴግ ሥልጣን
ከያዘ ወዲሕ አቶ ጌታቸዉ የወትሮዉ አይደለም።በራስ የመተማመን መንፈሱ፣ኩራት፣ግርማ ሞገሱ የሉም።በፊት ለዘገባ የሚላከዉን ሰዉ
(ሪፖርተር) ራሱ መድቦ፣ እንዴትና መቼ መዘገብ እንዳለበት አስርድቶ (briefing በጋዜጠኞቹ ቋንቋ) አበልም፣ቴፕ ሪኮርደር፣
ሰርቪስ (መኪናም) ካስፈለገ አዝዞ የሚያሰናብተዉ ራሱ ነበር።
የዚያን ቀን ግን
ወደ ዜና (ፋይል) ክፍል መጥቶ ከዕለቱ ተረኞች መካከል መግለጫዉን የሚከታተል ካለ ጠየቀ።እንዲያ ሲያደርግ ሁለተኛ ጊዜዉ መሆኑ
ነዉ።(አቶ ጌታቸዉ ፈቃደኛዉን መድቦ እንደ ወጣ፣« ዴሞክራሲ፣ ዴሞክራሲ የሚሉት ወያኔዎች ስልጣን ከያዙ ወዲሕ እኛም ዴሞክራሲ
ተንበሻበሽን።» ከአማረ መላኩ ዉጪ እንዲሕ አይነት ፌዝና ተረብ ማን ይናገራል) ልክ እንደመጀመሪያ ጊዜዉ ሁሉ ተረኞቹ ሲኒየር
ጋዜጠኞች
ተራ በተራ ቢጠየቁ
መሔድ አልፈለጉም።ነጋሽ ቀረ።«እሔዳለሁ» አለ።
ነጋሽ ፈቃደኛነቱን
እንዳረጋገጠ፣ ዳንኤል ወልደ ሚካኤል (ቅን፣ በሳል፣ተባባሪ) የቡድን መሪ ነዉ።ግን በድምፅ ስለማይሰራ የከፋ ችግር ካልተፈጠረ
በስተቀር ለዘገባ አይወጣም ነበር። ከነጋሽ ጋር አብሮ ሔደ።
መግለጫዉ የሚሰጠዉ
ግዮን ሆቴል ነበር።ሰዓት እላፊዉ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ላይ ስለሚጀመር ሁለቱ ጋዜጠኞች፣ ቴክኒሻን ወልዱን ይዘዉ ልዩ ፍቃድና
አስፈላጊ መሳሪያዎችን በጥድፊያ አዘጋጅተዉ ከሆቴሉ ደረሱ።
አንዲት ጠባብ ክፍል
እንደነገሩ በተዘጋጀዉ መድረክ ላይ ሙሉ ሱፍ ከነከራባቱ የለበሰ ጠይም፣ ወፍራም፣ወዛም፣ ጭንቅላተ መላጣና ሾጣጣ ሰዉዬ
ተቀምጧል።«መለስ ዜናዊ ማለት ይኼ ነዉ» አሰበ ነጋሽ-ከመድረኩ ፊት ለፊት ወለሉ ላይ ከተደረደሩት ወንበሮች መሐል ለመድረኩ
ቀረብ ያለዉን ባይኑ እያማተረ።
ከወንበሮቹ ጀርባ
እንደነገሩ የለበሱ፣ ፀጉራቸው የተንጨበረረ፣ ቦምብ ያገለደሙ፣ ጠመንጃ የተሸከሙ ወያኔዎች አጀብ ብለዉ ቆመዉ ጮክ እያሉ
ያወራሉ።ብዙዎቹ የሚያወሩት፣የሚያዩት ላንዱና ወደ አንዱ፣ የሚያዳምጡት ያንዱን ነዉ።እሱም ለየት ይላል።አልታጠቀም።ሙሉ ሱፍ ነዉ
የለበሰዉ።አጠር፣ደልደል፣ ከግንባሩ ገባ ያለ ብስል ቀይ ነዉ።«የወያኔዎቹ አዛዥ መሆን አለበት» አሰበ ጋዜጠኛዉ።
ጋዜጠኞች ማይክራፎኖቻቸዉን መድረኩ ላይ ከተቀመጠው ሰዉዬ (በነጋሽ ግምት መለስ
ዜናዊ) ፊትለፊት ደርድረዉ ጨረሱ።የፊልምና ፎቶ አንሺዎች ካሜሮቻቸዉን ሰዉዬዉ ላይ ደግነዋል።እሱ ግን አይናገርም።ከጋዜጠቹ
ጀርባ ወደተሰበሰቡት «ተጋዳላዮች» ይቁለጨለጫል።
ከደቂቃዎች በኋላ ያ
ቀይ አጭር፣ ደልዳላ ሰዉዬ እየተጣደፈ መድረኩ ላይ ከነበረዉ ሰዉዬ በስተቀኝ ተቀመጠ።ጠይሙ ሰዉዬ ሰላላ ድምፁን ስሎ« ጓድ
መለስ ዜናዊ የኢሕአዴግ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝደንት መግለጫ ይሰጣል።» አለ።
ጋዜጠኞች
ማይክሮፎኖቻቸዉን ሥፍራ ለመቀየር፣የፊልምና የፎቶ ግራፍ አንሺዎች ያነጣጠሩትን አቅጣጫ ለመለወጥ ይራከቱ ገቡ።ጋዜጠኞቹ መለስ
ዜናዊ መስሏቸዉ የነበሩት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ስዩም መስፍን፣ የታጋዮቹ አዛዥ መስሏቸዉ የነበሩት ደግሞ አቶ መለስ ዜናዊ
ናቸዉ።
ከዚያች ምሽት ጀምሮ
ነጋሽ ከኢትዮጵያ ጠቅልሎ እስከወጣበት እስከ መጋቢት 1992 ድረስ አቶ መለስ ዜናዊ እንደ ጊዜያዊ መንግስት፣ እንደ ሽግግር
መንግሥት ፕሬዚዳንት፣ እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ከሰጧቸዉ ጋዜጣዊ መግለጫዎች ከሶስቱ በስተቀር (አንዴ በግል ችግር፣ ሁለቴ
ለትምህርት ዉጪ ስለነበር) ያልተካፈለበት አልነበረም።
አቶ መለስ
የተሳተፉባቸውን አብዛኞቹን ጉባኤዎች፣ ግብዣዎች፣ ያደረጓቸውን ጉብኝቶች፣ሽምግልናዎች አብሮ እየተጓዘ ዘግቧል።
አንዳንዶች ጌታቸው
ኃይለ ማርያም የሊቀመንበር መንግስቱ ኃይለ ማርያም ልዩ ዘጋቢ (በበዓሉ ግርማ አገላለፅ እንደ እጅ ሻንጣቸው--- ይዘውት
ይዞራሉ) እንደነበረ ሁሉ፣ ነጋሽ መሐመድም የመለስ ሆነ እስከማለት ደርሰዋል።ሌሎች (የስራ ባልደረቦቹ) ጭምር «ወያኔ» እያሉ
የማማታቸዉ ሰበብም ለዚህ ነዉ።
ይሁንና ነጋሽ
መሐመድ በየጊዜዉ የተፈራረቁ አለቆቹ እንደማንኛዉም የጋዜጠኝነት ሥራ እየመደቡት ከመጓዝና መዘገቡ በስተቀር ማስታወቂያ
ሚንስቴር፣ ለማንኛዉም ጋዜጠኛ ከሚከፍለዉ አበል ዉጪ ያገኘዉ ገንዘብ፣ ሥልጣን፣ የትምህርት ዕድል ወይም ሌላ ጥቅም የለም።
«ስቷፉራላሕ»
የሶማሊያ ተቀናቃኝ
አንጃዎች ዉጊያ ባየለበት በ1980ዎቹ አጋማሽ የኢትዮጵያዉ መሪ አቶ መለስ ዜናዊ መጀመሪያ ኢጋድን ኋላ ደግሞ የአፍሪቃ
አንድነት ድርጅትን ወክለው ዋናኛዎቹን አንጃዎች ያደራድሩ ነበር።
በ1984 መጀመሪያ
አዲስ አበባና ናይሮቢ በተከታታይ ከሚደረጉ የሽምግልና ስብሰባዎች አንዱ ናይሮቢ ውስጥ ተሰየመ።የኢጋድ አባል ሐገራት መሪዎች
አንድ አዳራሽ ተቀምጠዉ የዋንኞቹን የተፋላሚ አንጃ መሪዎች፣ ጄኔራል መሐመድ ፋራሕ ሐሰን አይዲድንና ጠንካራ ተቀናቃኛቸዉን ዓሊ
መሕዲ መሐመድን በየተራ እያስጠሩ ያነጋግራሉ።
ዓሊ መሕዲ መሐመድ
መሪዎቹ ካሉበት አዳራሽ ወጥተው ወደ ክፍላቸዉ ለመሔድ ሊፍት ሲጠብቁ፣ ነጋሽና ባልደረባዉም አጠገባቸዉ ነበሩ።እነሱም ሊፍት
ጠበቃ። ሊፍቱ መጥቶ በሩ ሲከፈት ጄኔራል አይዲድ ከሊፍቱ ሲወጡ ወደ ሊፍቱ ለመግባት ካጃቢዎቻቸዉ ቀድመዉ በሩ ጋ የነበሩት ዓሊ
መሕዲ፣ ሰይጣን ያዩ ያክል «ስቷፉራላሕ፣ ስቷፍራላሕ» እያሉ
ፊታቸዉን አዙረዉ ሸሹ።
ዜናዬን ካላየ ካሁን በኋላ አልዘግብም አለ
የኤርትራ ሕዝበ-
ውሳኔን ለመዘገብ ከኢትዮጵያ የተጓዙት ጋዜጠኞች ከ30 ይበልጣሉ። ጋዜጠኞቹ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው በየከተማውና አካባቢዉ
ለአንድ ወር ያህል ሲሰሩ ቆይተዋል።
ነጋሽ የተመደበዉ
ከሁሉም ቡድናት ብዙ ጋዜጠኞች፣ ደራሲዎችና ፊልም ቀራጮች የነበሩበት ቡድን ነዉ።ተልዕኮዉ፣ የአስመራ፣የምፅዋና በየአካባቢያቸዉ
ያሉ ከተሞችን የሕዝበ- ዉሳኔ ሒደት እየቃኘ መዘገብ ነዉ።
ጋዜጠኞቹ ድምፅ
ከመሰጠቱ በፊት ባንደኛዉ ቀን አስመራ ከተማ ውስጥ ተዘዋውረዉ የሕዝብ አስተያየት (voxpop) ሰብስበዉ ዘገቡ።ሐሳቡን
ያፈለቀዉ ነጋሽ ራሱ ነዉ።
አስተያየት
ከተጠየቁት የከተማዋ ነዋሪዎች «ከኢትዮጵያ ጋር አብሮ መኖር ማለት ጤፍ 60ና 70 ብር መግዛት፣ በከሰልና እንጨት እጦት
መሰቃየት ነዉ---»የሚሉ ነበሩበት።ነጋሽ ከራሱ ፍጥነትና ቅልጥፍና በተጨማሪ ለራዲዮ ስለሚሰራ ሁልጊዜ ከተቀሩት ከሁሉም መገናኛ ዘዴዎች ቀድሞ ይዘግባል።
የዚያን ቀንም
አስተያየቱን መራርጦ፤ ያጠናቀረዉን ዘገባ ለቀትር ስርጭት ወደ አዲስ አበባ ላከዉ።6፣30 ተሰራጨ።ተቀራራቢ ይዘት ያለዉ ሌላ
ዘገባ ለማታዉ ስርጭት ላከ።አልተሰራጨም።
አዲስ አበባ ያሉ
አለቆች በማግስቱ ደዉለዉ «እንዲሕ ዓይነት ዘገባ የኤርትራ ሕዝብ ከኢትጵያ መለየት የሚፈልገዉ ለሆዱ ሲል ነዉ የሚያሰኝ ትርጉም
ስለሚያመጣ አልተሰራጨም።ለወደፊቱም ተጠንቀቅ» ዓይነት ምክር ተሰጠዉ።ነጋሽ አመፀ-እንዳቂሚቲ ።ተጠያቂዎች ያሉት መታፈን የለበትም
አለ።ቡድኑን የሚያስተባብረዉ (የኢህአዴግ ባለስልጣን) ዜናዬን ካላየ ካሁን በኋላ አልዘግብም አለ።
በቀን በትንሹ ሁለት
ዘገባ (ለቀንና ለማታ ስርጭት) ይልክ የነበረዉ ነጋሽ ሁለት ቀን ሳይዘግብ ቀረ።ዘገባዉ በመቋረጡ ጉዳዩ የመንግሥት ባለስልጣናት
ጆሮ ደርሶ ነጋሽም ይቅርታ ተጠይቆ ሥራዉ ቀጠለ።ህይወትም።
ነጋሽን ጨምሮ
የተወሰኑትን ጋዜጠኞች የሚያመላልሰዉ ሾፌር (ምናልባት ሰላይም) ኤፍሬም ይባላል።«ወጣት ነዉ ግን 13 ዓመት ተዋግቻለሁ።»
ይላል በኩራት። ለጠረጠረዉ የወገብና የጭኑ ላይ ትላልቅ ጠባሳን ልብሱን እያወለቀ ለማሳየት አያመነታም።
አንድ ቀን መንደፈራ
በሔዱበት ሾፈራቸዉ አክስቱ ቤት ይዟቸዉ ገባ።አክስት፣ ያላቸዉን አቀራርበዉ እንግዶቻቸዉ እንዳይደብራቸዉ ያወራሉ።ከእንግዶቹ
ብዙዎቹ ይጠይቃሉ-የጋዜጠኛ ነገር፤ ጥቂቶቹ አስተያየት ይሰጣሉ ።ሁሉም ይስቃሉ።ነጋሽም እንደብዙዎቹ ያዳምጣል፣ ፣ አስተያየት
ግን አይሰጥም።አይጠይቅምም። ትግሪኛ አይችልማ።ሴትዮዋ መቆጠቡን ዓይተዉ ይሁን በሌላ ምክንያት በቀጥታ ለነጋሽ ያወሩለት
ገቡ።ይፈልጋል ግን አይመልስም።የሴትዮዋን ግራ መጋባት፣ የነጋሽን ጭንቀት የተረዳዉ ኤፍሬም ጣልቃ ገብቶ «ትግሪኛ አይችልም»
ሲላቸዉ ሴትዮዋ ጮኹ።«ዋይ---አንተ ኤፍሬም------እኔ ግንባሩን አይቼ ትግራዊ መስሎኝ-----እያሉ ቀጠሉ።
የትልቁ ሰዉ አጭር መልስ
በ1985 ማብቂያ
የደቡብ አፍሪቃ የግንባር መስመር (Frontline Stats) የሚባሉትና ኢትዮጵያን ጨምሮ በአፍሪቃ አንድነት ድርጅት የተመረጡ ሐገራት መሪዎች በተደጋጋሚ ካደረጓቸዉ ጉባኤዎች አንዱ
የተደረገዉ ሉሳካ-ዛምቢያ ዉስጥ ነበር።የያኔዉ የደቡብ አፍሪቃ የአፍሪቃ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) መሪ ኔልሰን ማንዴላ ጉባኤዉ
ከሚደረግበት ሆቴል የደረሱት ከሌሎቹ ዘግየት ብለዉ ነዉ።
ዝነኛዉ የጥቁር
ብሔረተኛ ተጋይ ከሆቴሉ በር ላይ ሲደርሱ ባካባቢዉ የነበረዉ ሰዉ ከበባቸዉ።እዚያው አካባቢ የነበረዉ ነጋሽም እየሮጠ ከትንሹ
የሕዝብ ባሕር ተቀየጠ።ማንዴላ ከከበባቸዉ ሕዝብ ከፊሉን እየጨበጡ፣ለሌላዉ እጃቸዉን እያዉለበለቡ ሲያልፉ ነጋሽ ጮክ ብሎ
«በመጪዉ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ይወዳደራሉ (Are you going to contest for upcoming presidential
election?)» ጠየቃቸዉ።
«እዚያ ገና አልደረስንም» (We are not yet there!”) መለሱ
ትልቁ፣ ተወዳጁ፣ ዝነኛዉ፣ አዛዉንት ፖለቲከኛ-እንደ ወጣቱ ጋዜጠኛ ሁሉ ጮክ ብለዉ።
የክሊንተን ብልጠት
የዩናይትድ ስቴትሱ
ምክትል ፕሬዝደንት አል ጎር ሕዳር 1993 በሚደረገዉ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ያስታወቁት በ1991 ሰኔ ላይ
ነበር።አል ጎር ዕቅዳቸዉን ሲያስታውቁ አለቃቸዉ ቢል ክሊንተን ቡድን 7+1 ይባል በነበረዉ ጉባኤ ላይ ለመካፈል ከለን-ጀርመን
ነበሩ።
አልጎር ዕቅዳቸዉን
ባስታወቁ ማግስት ክሊንተን መግለጫ ለመስጠት ጋዜጠኞችን ጠሩ።ከፕሬዝደንቱ ፊት ለፊት በቅርብ ርቀት ከተኮለኮሉት ጋዜጠኞች አንዱ
አዲሱ የዶቸ ቬለ ባልደረባ ነበር።ነጋሽ መሐመድ።ዕድል ሲያገኝ ጠየቀ።ምክትል ፕሬዝደንት አል ጎር በሚቀጥለዉ ምርጫ
ለፕሬዝደንትነት ለመወዳደር እንደሚፈልጉ አስታዉቀዋል።እርስዎ አፅድቀዉታል? Vice president Al gore announced
his intention to run for presidency in the next election…..Have you endorsed
him?አጠገቡ የነበረ አንድ የብሪታንያ ቅላፄ ያለዉ ሌላ ጋዜጠኛ የነጋሽን ጥያቄ የሚያጠናክር ሰፋ ካለ ማብራሪያ ጋር ጠየቀ።
ምክትላቸዉ
እራሳቸዉን ማጨታቸዉን ልክ እንደማንኛዉም ሰዉ በቴሌቪዥን ማየታቸዉን፣ ምክንያቱንም በሰፊዉ ካብራሩ በኋላ «ይሕ ጥሩ ነዉ»
አሉ።«እሱ እዚያ የመገናኛ ዘዴ ሽፋን ያገኛል---እኔ ደግሞ እዚያ የናንተን ትኩረት አግኝቻለሁ----ኪኪኪኪ»
ሥልጠናዎች
ነጋሽ መሐመድ
ኢትዮጵያ ራዲዮ እንደተቀጠረ ጌታቸዉ ኃይለማርያም ለ3 ወር ግድም
ከሰጠዉ መደበኛ ያልሆነ ስልጠና ዉጪ ሐገር ዉስጥ ስልጠና የወሰደዉ አንዴ ብቻ ነዉ።የአሜሪካ ኤምባሲ ያዘጋጀዉ፣ አንድ
አሜሪካዊና ኢትዮጵያዉያን የሕግ አዋቂዎች የሰጡት War Crime Tribunals reporting የሚል ሥልጠና ወስዷል።
ዶቼ ቬለ ከመቀጠሩ
በፊት በ1986 መጀመሪያ ላይ ከሌሎች የአፍሪቃ ሐገራት ጋዜጠኞች ጋር ጀርመን ሐገር ያደረገዉ የአንድ ወር የጎዞ (የተለያዩ
መገናኛ ዘዴዎችን የመጎብኘት) «ሥልጠና» ብዙ እዉቀት የቀሰመበት እንደሆነ ይናገራል።በዚያ ጊዜ የኤፍ ኤም (ጀርመኖች UKW
ይሉታል) ሥርጭት ጀርመን ሐገር በስፋት የተጀመረበት ስለነበር የተለያዩ ጣቢያዎችን በጎበኘበት ወቅት ያየዉ አሰራር፣
የተደረገለት ገለፃ፣ የሰበሰባቸዉ መረጃዎች፣ ማኑዋሎችና ብሮሸሮች ኋላ የፋናንና የኢትዮጵያ ራዲዮን (የኤፍ ኤም ስርጭትን)
ሐሳብ ለማፍለቅ፣ ለማጥናትና ለመመሥረት መደላድል ሆነዉታል።
በ1988 እና 89
እንደገና ጀርመን ሐገር ዛሬ በሚሰራበት ዶቸ ቬለና በሌሎች ጣቢያዎችና ተቋማት የወሰደዉ ሥልጠናም ጠቃሚዉ ነበር።ዶቼ ቬለ
እንዲሰራ የጣቢያዉ ኃላፊዎች ለኢትዮጵያ ራዲዮና ለራሱ ለነጋሽ ጥያቄ ያቀረቡትም በስልጠናዉ ወቅት ጥረትና ችሎታዉን በማየታቸዉ ነዉ።
ዶቸ ቬለና ሌሎች
ተቋማት የሚሰጡትን ስልጠና ከነጋሽ መሐመድ በፊት ሌሎች የኢትዮጵያ ራዲዮ ጋዜጠኞች ተከታትለዉታል።የኮንትራት ቅጥር ጥያቄ
የቀረበዉ ግን ለነጋሽ ብቻ ነበር። ዶቸ ቬለ ከኢትዮጵያ ጋዜጠኛ ሲቀጥር ከ24 ዓመታት በኋላ ነጋሽ መሐመድ የመጀመሪያው
ነዉ።ዶቸ ቬለ ከገባ ወዲሕ የተለያዩ ሥልጠናዎችን ተከታትሏል።
London
School of Journalism በተባለዉ ኮሌጅም (በተልዕኮና በአካል) መማር ጀምሮ ነበር።ከቋንቋዉ በስተቀር አብዛኞቹ
ኮርሶች እሱ ኢትዮጵያ ራዲዮ እያለ ለጀማሪ ጋዜጠኞች ከሚያስተምራቸዉ የተሻሉ ስላልነበሩ ተወዉ።
ትችት
ነጋሽ መሐመድ ዜና
በተለይም ትንታኔና ሐተታ (Analysis and commentary) የሚፅፍባቸዉ፣ድርጊቶችን፣ አካባቢና ድባቦችን የሚገልፅባቸዉ
አንዳንድ ቃላት ከአዘቦቱ ንግግር ወጣ ያሉ ከባዶች ናቸዉ የሚሉ አሉ።
በባሕሪዉ
አይናፋር፣ግን ቀልደኛ፣ አድማጭ ግን የሚያምንበትን ፊትለፊት ተናጋሪ፣ ከሰዉ ጋር ፈጥኖ መግባባት የሚከብደዉ ከተግባባ ግን
ሚስጥር የለሽ ነዉ።ቁጡ ግን አዛኝ፣ አኩራፊ ግን ሩህሩሕ፣ ግልፅና ደግ ነዉ።
ስራ ላይ ቀልድ
የለም።የጀመረዉን ሥራ እስከሚጨርስ ወይም በተለይ በሚፅፍበት ጊዜ ሐሳብ አልመጣ ካላለዉ በስተቀር ከሲጋራ በስተቀር አጠገቡ
የሚደረግ፣ የሚባል፣ የሚወራና ያለዉን ነገር በሙሉ አያይም።እስኪሪብቶ ያስቀመጠበት ስለሚጠፋበት አንዳንዴ መፃፍ ከመጀመሩ በፊት
አጠገቡ ሁለት ሶስት እስኪሪብቶዎች ይደረድራል።በቀን ቢያንስ አንዴ ጉዞ ላይም ሆኖ ዜና ካልሰማ አንድ የጎደለዉ ነገር እንዳለ
ሁሉ ያቅበጠብጠዋል።
እርግጠኛ ባልሆነበትን ጉዳይ ላይ አይፅፍም።አይዘግብምም።ለስራዉ
ጥራት፣ፍጥነትና ሙሉዕነት ስለሚጨነቅ ባልደረቦቹ ሁሉ እንደሱ እንዲሰሩ ወይም እንዲያስቡ ይመኛል። ኤዲተራቸዉ የነበሩ አንዳንድ
ጋዜጠኞች ከስራዉ በስተቀር የሰዉን አቅም፣ ችግር፣ የማይገነዘብ፣
ለማሕበራዊ ኑራችን ሥፍራ የማይሰጥ በማለት ይተቹታል።
አንድ ሰሞን አንድ ባልደረባዉ «ጄኔራል» ብሎት ነበር።ሌላ ጊዜ ሌላዋ ባልደረባዉ
«ለመንግስት ጣቢያ ምን አንጨረጨረህ» ብላዋለች።
እንደ
አድናቆት፣አክብሮት፣ ሙገሳ፣ ዉዳሴዉ ሁሉ ከዉጪም ካለቆቹም ስድብ፣ ርግማንና ዛቻ ተለይቶት አያዉቅም።አብዛኞቹ ተሳዳቢ፣ተራጋሚ፣
ተቆጪና ቀጪዎቹ የሠራቸዉን ወይም ያጠናቀራቸዉን ዘገቦች ሚዛናዊ፣ገለልተኛ፣ተዓማኒነት ይጎድላቸዋል የሚል መከራከሪያ ነጥብ
ስለማያገኙ ነጋሽን በኃይማኖቱ ወይም በሚጠረጥሩት ግን መሰረት በሌለዉ
ፖለቲካ የሚወነጅሉት ይበዛሉ።
በመጀመሪያዉ
የባሕረ-ሠላጤ ጦርነት ወቅት የኢራቁ ፕሬዝደንት ሳዳም ሁሴይን ለሕዝባቸዉ ስላስተላልፉት መልዕክት አጭር ትንታኔ
አጠናቀረ።የዘገባዉ መሠረት ሮይተርስ ዜና አገልግሎት ነበር።ዜና አገልግሎቱ ሳዳም በንግግራቸዉ መጨረሻ “God is
great“ማለታቸዉን ይጠቅሳል።
ለአንድ
ጋዜጠኛ፣የየትኛዉም ዕምነት ተከታይ ቢሆን አረብኛ የሚናገር አንድ የአረብ መሪ፣ አረቢኛ ለሚናገር ሕዝባቸዉ በአረቢኛ God is
great ወይም በአማርኛ «እግዚአብሔር ትልቅ ነዉ» ብለዉ ይናገራሉ ብሎ ለማሰብ በርግጥ ደደብነትን ይጠይቃል።
አዲሱ ጋዜጠኛም ብዙ
ማሰብ አላስፈለገዉም።ሳዳም ንግግራቸዉን ሲያጠናቅቁi «አላሁ አክበር» አሉ 3 ጊዜ ብሎ ተረጎመዉ።አሰራጨዉ።
«በማግስቱ ጋሽ
ጌታቸዉ ቢሮዉ ጠርቶ ስለዘገባዉ ጠየቀኝ።አዳምጠዉ አልኩት።አዳምጬዋለሁ አለ።» ይላል ነጋሽ።«ከርዕዮተ ዓለም መምሪያ ለሚንስትሩ
ተደዉሎ እንዲሕ ዓይነት ዘገባ ማሰራጨት ኢትዮጵያ ያሉ ሙስሊሞችን የሚያነሳሳ ነዉ----ተብሏል አለኝ።
አልመለስኩለትም።ቀጠለና
አዲስ መሆንህን ለሚንስትሩ አስረድቼ፣ እሳቸዉ ስለገባቸዉ ከቅጣት ድነሀል-----» አለኝ
የአዲስ አበባ ሕዝብ
የሽግግር መንግስቱን ቻርተር በመደገፍ አብዮት (መስቀል አደባባይ) ያደረገዉን ሰልፍ የዘገበዉ ነጋሽ ነበር።አደባባይ የወጣዉ
ሕዝብ ከሚዘፍን፣ ከሚዘምርባቸዉ ቋንቋዎች ከአማርኛ፣ ከኦሮሚኛና ትግሪኛው እየቆነጣጠረ የሰደረበትን ዘገባ አጠናቀረ።ቅዳሜ
ነበር።ዘገባዉ ቀን ከ7 እስከ 10 ሰዓት ሶስቴ፣ ማታ 2 ሰዓት ተሰራጨ።3 ሰዓት ላይ ግን ከዘፈን-መዝሙሮቹ የትግሪኛዉ አንድ
ክፍል ተቆርጦ ተሰራጨ።
ነጋሽ፣ ሰኞ ቢሮ
ሲገባ ያኔ እንደ ራዲዮ ጣቢያዉ ኃላፊ ከሚቃጣዉ (ትክክለኛዉ ኃላፊ ሌላ ነበር) የአማርኛ ክፍል ኃላፊ ቢሮ ተጠራ።
አለቃዉ ቢሮ
እንደገባ አለቅዬዉ፣ «የትግሪኛዉን ዘፈን ከሌሎቹ የበለጠ ያስጮከዉ አዉቀሕ ነዉ» እያለ ይወቅሰዉ ያዘ።«የአማራ ትምክሕተኞች
ትግሬ ነዉ የሚገዛዉ እንዲሉ፣ የትግሬ ጠባቦች ደግሞ እንዲኮፈሱ----አንተ ራስሕ ሾቪኒስት ነሕ---»
ነጋሽ ቃሉን
ለመጀመሪያ ጊዜ መስማቱ ነበር።ግን አልተበገረም።ለተሳዳቢዉ አለቃ ኤድተር ማለት፣ሪፖርተሩን ሲያሰማራ መስራት ያለበትንና
የሌለበትን፣ ማተኮር የሚገባዉ፣ መምረጥ ያለበትን አንግል፣ አስርድቶ የሚልክ።ሪፖርተሩ የፃፈዉን ከመቀረፁ በፊት
የሚያርም፣የሚያስተካክል፣ ይሕ ቢቀር ስርጭቱን ተከታትሎ ፈጥኖ የሚያርም መሆን እንዳለበት ነግሮት (አስተምሬዉ ነዉ የሚለዉ
ነጋሽ)፣ «እኔ ይሕን ጣቢያ ብለቅ መሔጃ አለኝ።I have a place to go---እንዳንተ ተማርኬ ካድሬ
አልሆንኩም---የማሰናበቻ ደብዳቤሕን እጠብቃለሁ» ብሎት ወጣ።የዚያን ቀን አልሰራም።
የሚገርመዉ ያ አለቃ
ከነጋሽ በፊት ከኢትዮጵያ ራዲዮም፣ ሲበዛ ከሚመካበት ኢሕአዴግም አባልነት ታግዶ ሲንከራተት ነጋሽ ኋላ ራዲዮ ፋና የተባለዉ
ጣቢያ ኃላፊዎችን አግባብቶ አስቀጠረዉ።
አንድ ቀን ዜና
ክፍል ዉስጥ ከቴዎድሮስ ነዋይ ጋር ሲላፉ መስኮት ተሰበረባቸዉ።የዋና ክፍሉ ተጠባባዊ ኃላፊ ዳሪዮስ ሞዲ ፣ ነጋሽን «በጋጠ
ወጥነት» ላደረሰዉ ጥፋት ከወር ደሞዙ 50 ብር እንዲቀጣ የሚጠይቅ ደብዳቤ ለበላይ አለቆች ይፅፋል።ከጥቂት ወራት በፊት ነጋሽን
«ሾቪኒስት» ያለዉ አለቃ የገንዘብ ቅጣቱን «እስካሁን ያደረጉትን አስተዋፅኦ ከግምት በማስገባት በማስጠንቀቂያ እንዲታለፉ
ተወስኗል።» በሚል ደብዳቤ ሻረዉ።
ዶቸ ቬለ ከተቀጠረ
በኋላ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ባራክ ኦባማ ካይሮ ዩኒቨርስቲ ባደረጉት ንግግር «አሰላሙ አለይኩም» ማለታቸዉን በመጥቀሱ፣
እሱ ያለዉ የመሰላቸዉ ደንቆሮዎች ከሰዉታል።እስራኤልን፣ «የአይሁዳዊቱ መንግስት እስራኤል» (The jewish State of Israel) ብሎ በመግለፁ፣
ስያሜዉ የራሳቸዉ የእስራኤል ፖለቲከኞች መሆኑን የማያዉቁ
«ማፈሪያዎች» ከኃይማኖቱ ጋር አገናኝተዉ ከሰዉት ጉጉል ገላግሎታል።
መርካቶ ዉስጥ
የተነሳ ቃጠሎን ለማጥፋት የእሳት አደጋ ሰራተኞች ባካባቢዉ ፖሊስ ባለመኖሩ ሥራቸዉ መስተጓጎሉን ጠቅሶ በመዘገቡ ያቄመ የፖሊስ
ጣቢያ አዛዥ ሌላ ምክንያት ፈጥሮ ላንድ ቀን አስሮታል።
አንዴ ከተቃጣበት
አፈና ምናልባትም ግድያ በቀላል አጋጣሚ አምልጧል።ፖለቲካዋ
በጎሳና በዘር የተከፈለ፣ ፖለቲከኞችዋና ደጋፊዎቻቸዉ ቁል ቁል
የሚነዷት ኢትዮጵያ ነጋሽን ለመሰሉ ገለልተኛ ጋዜጠኞች የግድያ ዛቻ፣ የስድብና ስም የማጥፋት ዘመቻ ማዕከልም ሆናለች።
ነጋሽ መሐመድ
በ1983 ክረምት የተመሠረተዉ የአርጎባ ብሔረሰብ አንድነት ድርጅት (አብአድ) ተባባሪ መስራችና ከመጀመሪያዎቹ መሪዎች አንዱ
ነበር።የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማሕበር (ኢጋማ) የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ ኮሚቴ አባል ሆኖ ተመርጦም ነበር።የሞተዉን ማሕበር ወደ
መቃብሩ ከመንዳት በስተቀር ግን የሰራዉ የለም።ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነዉ።
«ጋዜጠኝነት ብዙ
ያወቅሁበት ግን ትንሽ የተጠቀምኩበት፣በብዙዎች የታወቅሁበት ግን በጣም ጥቂቶችን ያወቅሁበት፣ብዙ የለፋሁበት ግን ትንሽ
የረካሁበት፣ብዙ ዓመታት የለፋሁበት ግን ዛሬም እንዳዲስ የሚፈታተነኝ ሙያ ነዉ»
መዝጊያ፣ ይህ
መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋም የሚንጸባረቅበት ነው፡፡ በተጨማሪም የዚህ ዊኪፒዲያ ዝግጅት ክፍል አባላት ከታሪኩ
መጨረሻ ላይ የሚሰጡት አስተያየት ሙሉ በሙሉ የራሳቸው ነው፡፡ በዚህ መሰረት ነጋሽ መሀመድ በእኛ አስተያየት በአጭር ጊዜ
ቆይታው የሀገሩን ሚድያ በፕሮፌሽናል መንገድ ለማስኬድ የጣረ
ታላቅ ሰው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ በቆየባቸው 10 አመታት በህዝብ የማይረሳ ለመሆን ባለፈ ታሪካዊ ክስተቶችን በጥራት
በመዘገብ ለሌሎች አርአያ ለመሆን የቻለ ነው፡፡ አዳዲስ የሬድዮ ጣቢያዎች አንድ ተብለው ሲጀመሩ ነጋሽ የማማከር ሚናውን ገና
በ27 አመት እድሜው ይወጣ ነበር፡፡ ዛሬ ፋና ብሮድካስቲንግ የተባለው ትልቅ ጣቢያ ስሙን ከማግኘቱ ቀደም ብሎ መሰረታዊ
የማደራጀት ስራዎች ሲሰሩ ነጋሽ የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ ነበር፡፡31 አመት በጋዜጠኝነት መቆየት ብዙ ነው፡፡ ነጋሽ ግን ብዙ
ቢለፋም ርካታው ግን ትንሽ ነው፡፡ይህ የነጋሽ ሀሳብ እንደተከበረ ሆኖ ነጋሽ ለብዙዎች ወደ ጋዜጠኝነት መምጣት ምክንያት የሆነ
ሰው ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ያነጋገራቸው በዶቸ ቬሌ የሚሰሩ በኢትዮጵያ ሬድዮም የሚያገልግሉ እና ሲያገለግሉ የኖሩ
ነጋሽን እንደ ትልቅ አርአያ ይቆጥሩታል፡፡ ይህ መከበር በስራ እንጂ በሌላ የሚመጣ አይሆንም፡፡ ኢትዮጵያ ደግሞ ያልሰራውን
ደፋሩን ታበረታታለች እንጂ እንደ ነጋሽ አይነት ሰዎች ፊትፊት
እንዲመጡ አታደርግም፡፡ እድሉን ስለምትነፍግ የሰሩም ደፍረው አይመጡም፡፡ ያልሰሩ ደፋሮች ግን ያለይሉኝታ የታሪክ መንበሩ ላይ
ተቀምጠው አድራጊ ፈጣሪ እነርሱ እንደነበሩ ይተርካሉ፡፡ በእኛ
እምነት በኢትዮጵያ የሬድዮ ጋዜጠኝነት ታሪክ ውስጥ ከ1980ዎቹ ወዲህ ለመጡ ፕሮፌሽናል አካሄዶች የነጋሽ መሀመድ እጅ
አለበት፡፡ ይህን ደግሞ ተመራማሪ፣ አንባቢ ፣ አዲስ ትውልድና ራሱ ጋዜጠኛው እንዲያውቀው እንሻለን፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አላማም የሰሩትን ብቻ - /እንደግመዋለን/ የሰሩትን ብቻ
ታሪካቸውን በሚዛኑ ለክተን የምናወጣበት ነው፡፡ ነጋሽ መሀመድ በዚህ ጥረቱ እንዲቀጥል ፣ ጀርመን ሆኖ ሀገሩን እንዲያሳድግ
መልካሙን ሁሉ እየተመኘን በ4900 ቃላት ወይም በ18 ገጽ ስለ ነጋሽ ያሰናዳነውን መቋጫ እንሰጠዋለን፡፡/ ይህ ጽሁፍ ከጋዜጠኛ
ነጋሽ መሀመድ የተገኘን ጽሁፍ መሰረት አድርጎ የተሰናዳ ሲሆን የታሪኩ ባለቤትን ከመምረጥ ጀምሮ ታሪኩ ከዚህ ዊኪፒዲያ እንዲበቃ
ያደረገው ጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ ነው፡፡ ይህ ጽሁፍ ዛሬ ቅዳሜ ነሀሴ 15 2013 የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የፌስ ቡክ ገጽ
እና ዊኪፒዲያ ላይ የወጣ ሲሆን አስፈላጊው ማሻሻያ እየተደረገበትም በየጊዜው እንዲወጣ ይደረጋል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ