33. ሶስና አሸናፊ ረጋሣ Sosina Ashenafi Regassa
የአዲስ ቅኝቷ ሶስና
ሶስና አሸናፊ ረጋሣ
፣ በ1965 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ ተወለደች፡፡አፍሪካ አንድነት ቁ2 የህዝብ ት/ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን የተማረች
ሲሆን፤ በመድሀኒያለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን
ተከታትላለች፡፡ ከዚያም በተፈሪ መኮንን ቴክኒክና ሙያ ትምህርት ቤት በኦፊስ ማኔጅመንትና ሴክሬተሪያል ሳይንስ ዲፕሎማዋን
ተቀብላለች፡፡ ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜ በቢሮ አስተዳደር ከሰራች በኋላ ወደ ስነፅሁፍ እና ጋዜጠኝነት በማዘንበል ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ አሁንም ድረስ
በምትኖርበት ካናዳ ቶሮንቶ በሚዲያና ኪነጥበብ ዘርፍ እያገለገለች ትገኛለች፡፡ ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ከዚህ ቀደም
በመዝናኛው ፤ በጥበቡ ዘርፍ ያሉ ሰዎችን አጭር ግለ-ታሪክ ሲያቀርብ እንደነበር ይታወቃል፡፡አሁን ደግሞ ወደ ሶስና ጎራ
እንላለን፡፡ ሶስና በራሷ መንገድ የህይወትና የስራ ገጹዋን እንደሚከተለው ትተርካለች፡፡
ልጅነቴን እወደዋለሁ
በልጅነቴ ጠይም
ናትን/የጥላሁን ገሰሰን /ዘፈን በሶስና ለውጨ “ሶስና ቀይ መልከ
ቀና በውበት ያጌጠች በፍቅሯ ልቤን እንክት አድርጋ የበላች እሷው
ነች” እያልኩ በየሣምንቱ ቅዳሜ እያንጎራጎርኩ ዘፋኝ የመሆን ምኞቴን ለአጎቶቼ እየነገርኩ አስቃቸው ነበር፡፡ ነፍሷን ይማረውና ደግና የዋኋ አክስቴ ለዛሬው የስነፅሁፍ ፍቅሬ
መነሻ የሆነኝን ልብ-ወለድ መፅሃፎችን ታነብልኝ ነበር፡፡ ያብቄለሽ ኑዛዜ፣ እግረ ፀሃይ
፣ አልወለድም ፣ ጅብ ነች እና ሌሎች በአክስቴ ወፍራም ድምጾች ሲነበቡ የሠማኋቸው ታሪኮች ናቸው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ
ብወለድም በነፃነት እንድሮጥ የፈለኩትን እንዳደርግ የሚፈቀድልኝ ልጅ አልነበርኩም፡፡ ያም ሆኖ ልጅነታቸውን ከሚወዱት
ሠዎች መካከል አንዷ ነኝ፡፡ እናም ከቆፍጣናውና ሥራ ወዳዱ አሸናፊ ረጋሣ እና ለልጆቿ መስዋእትነት ከከፈለችው ደብሪቱ ጎሣዬ በመወለዴ ደስ ይለኛል፡፡
ብእር ከወረቀት ማዋሃዴን ቀጠልኩበት
ለቤቱ ሁለተኛ ልጅ በመሆኔና ፤ ነፍሱን ይማረው አባቴ ዳኛ ከዚያም ጠበቃ
ስለነበር የህግ ትምህርት እንድማር በመፈለጉ ከቤት ውስጥ ባላለፈው የመዝፈንና የመደነስ ልምምዴ እንዲሁም ምኞቴ ደስተኛ
ስላልነበር ቁጣውን ፈርቼ እርግፍ አድርጌ ተውኩት፡፡ አክስቴ የተወችልኝን ልብወለድ መፅሃፎችን የማንበብ ልምድና ትንንሽ
ነገሮችን መሞነጫጨሬን ግን ቀጠልኩበት ፡፡ በትምህርቴ አባቴ እንደሚያስበኝ የህግ ተማሪ ባልሆንም የህግ አገልግሎት ከሚሰጡ ባለሙያዎች ጋር ግን መስራት ችያለሁ፡፡ ከተፈሪ
መኮንን በኦፊስ ማኔጅመንት እና በሴክሬታሪያል ሣይንስ ተመርቄ
የፀሃፊነት ስራዬን ስጀምር ደግሞ ከሰዎች አሣዛኝ ፣ አስደሣች፣ አስገራሚና እንዲሁም ስስትና ገንዘብን አብዝቶ መውደድ የሚያስከትለውን አሣዛኝ
አንዳንዴም አስቂኝ ባህሪን ሳስተውል እንደዚህ ነን ለካ የሚያሰኝ ስሜት ስለሚፈጠርብኝ እነዚያን ትዝብቶች በአጫጭር ታሪኮችና ወጎች እየሞነጫጨርኩ አስቀምጥ ነበር፡፡ ጠቅልዬ ወደ ሥነ
ፅሁፍና ጋዜጠኝነት አለም እስክቀላቀል ድረስ የፃፍኳቸው አጫጭር ታሪኮች ከጓደኞቼ ያለፈ አንባቢ አልነበራቸውም፡፡
ከጥበብ ሰዎች ጋር መተዋወቅ-እና አጭር ልቦለዶቼ
በዚህ መሀል ነበር
ነፍሷን ይማረውና ፊርማዬ አለሙ ጋር የተገናኘነው፡፡ የስነፅሁፍ ስልጠና ጋበዘችኝ፡፡ በሴት ደራሲያን ክበብ በተዘጋጀ የግጥም፣
የቲያትር፣ የስነፅሁፍ ስልጠና ለሶሶት ወር ተከታተልኩ፡፡ይህም ለምፅፈው ፅሁፍ አዲስ አተያይ እና ቴክኒክ እንዳውቅ እድል
ፈጠረልኝ ፡፡ ከዚህ ሌላም በአዲስ አበባ መስተዳድር ባህልና ማስታወቂያ ቢሮ በተዘጋጀ የስነፅሁፍ ስልጠና ላይ መሣተፌ
ተፈጥሮአዊ የሥነ ፅሁፍ ክህሎቴን ወደአደባባይ እንዳወጣ መንገድ ጠረገልኝ፡፡ ሞት ቀጠሮ የለውምና ፊርማዬ አለሙ የተጀመረው ስልጠና ሳይጠናቀቅ ነበር ከዚህ አለም ድካም የተገላገለችው፡፡
ፊርማዬ ፀሀፊ ሴቶችን አጉልታ የምትመለከተው ከሚደርስባቸው ተፅእኖና ካለባቸው ድርብርብ ችግር አንፃር በመሆኑ ጆሮዋንም ልቧንም
ሰጥታ ነበር የምታዳምጠው ፡፡ እና ሁልጊዜም አመሠግናታለሁ፡፡ እኔም የሴት ደራሲያንን ክበብ ከተቀላቀልኩ በኋላ በፀሃፊነት እና ግጥም በማለዳን በማዘጋጀት
ለተወሰኑ ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ ክበቡ ወደ ማኀበር ሲዘዋወር መስርቻለሁ፡፡ በወር አንድ ጊዜ የምናዘጋጀው በሀገርI ፍቅር ትንሽዋ አዳራሽ ይካሄድ በነበረው ግጥም በማለዳ ዝግጅትን
ሳስብ ከሚመጡት ገጣሚያን እና ደራሲያን ጋር ውብ ጊዜ ነበረን፡፡
ገጣሚያንን መጥራት የኔ ሃላፊነት በመሆኑ ነብይ መኮንን ፣ጌትነት እንየው ፣ በእውቀቱ ስዩም ፣ እንዳለ ጌታ ከበደ ፣
እንዳለ ጌንቦ እና የተለያዩ ወጣትና አንጋፋ በስም ያልጠቀስኳቸው
በአክብሮት መጥተው መድረኩን ያደምቁት ነበር፡፡ መቼም የሴት ደራሲያን ማኀበርን ለማጠንከር እኔ ከደረስኩባቸው ከፊርማዬ አለሙ
ጀምሮ መቅደስ ጀንበሩ ፣ ሙሉ ሰለሞን ፣ የምወድሽ በቀለ፣ የሺወርቅ ወልዴ፣ ሜሮን ጌትነት ፣ በቅርበት አብሬያቸው የሰራኋቸው
እና ለማኀበሩ መጠንከር አስተዋፅኦ ያደረጉ ናቸው፡፡ ከዚህ ባሻገር እጣ
የተሰኘ የአጫጭር ታሪኮች መድብል ሲታተም ሁለት
አጫጭር ታሪኮች ፅፌያለሁ፣ ከራስሽሽት የተሰኘውን የወግና
ደብዳቤዎች መድብል በግሌ ማኀበሩ አሳትሞልኛል፣ እኛ በተሰኘው ሁለተኛ የግጥም መድብል ላይ
የተወሰኑ ግጥሞች ታትመውልኛል ፡፡
ለትንሽ ጊዜ ደግሞ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማኀበርን በስራ አስፈፃሚ አባልነት
ተመርጨ ተቀላቅያለሁ፡፡ ብዙም ሣልዘልቅ በፈቃዴ ለቅቄያለሁ፡፡
አብሬያቸው ባልቆይም አበረ አዳሙ፣ ጌታቸው በለጠ ፣ እንዳለ ጌታ ከበደ፣ ጋር ለአጭር ጊዜ ቆይተናል፡፡
ወደ አጭር ልቦለድ ጸሀፊነት
የፓኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር ባዘጋጀው የመጀመሪያ የአጫጭር ልቦለዶች
የስነፅሁፍ ውድድር አንደኛ በመውጣት ከመሸለሜም በላይ በጣም ከምወዳቸውና ከማከብራቸው ታላላቅ ደራሲያን ጋር ሥራዬ የህይወት
ጠብታዎች በተሰኘው የፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር የመጀመሪያ የህትመት ውጤት ውስጥ “ያልተሰበረ ተስፋ “ በተሰኘ ርዕስ በ1995 ለህትመት
በቅቶልኛል፡፡ ከዚያ በኋላ ያልተናበቡ ልቦች፣ ሙሉ ሰው፣ዛሬን
ከተጉበት ፣ ታጋቾቹ እና ክንፋም ህልሞች በተሰኙ ሌሎች የፖኘሌሽን ሚዲያ ተከታታይ ህትመቶች ውስጥ ሥራዎቼ ታትመዋል፡፡ ከፖኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር ብዙ ትእግስትን ተምሬያለሁ፡፡
ከነብዩ ተካልኝና ከጋሽ ዘሪሁን አስፋው እንዲሁም ነገሮችን በጥንቃቄ ከማድረግ ጀምሮ ቢቻል አለመሣሣትን ከዶ/ር ንጉሴ ተፈራ
አግኝቻለሁ፡፡ ከሚዲያ ከስነፅሁፍ ከቲያትር ጋር በተገናኘ የሚደረጉ ወርክሾፓች እንዲሁም ጥናቶችን መሠረት ያደረጉ ፅሁፎች መታተማቸው በተጎጂዎች ላይ የሚደርስን
ጉዳት አጉልቶ ከማውጣቱም በላይ ታሪኩን ያጠነክረዋል፡፡ እኔ በፓኘሌሽን ሚዲያ ሴንተር አማካኝነት
የፌስቱላን እና የግርዛትን አስከፊነት በተመለከተ ከችግሩ ገፈት ቀማሾች ጋር ተገናኝቼ በፃፍኩት “እለፍታ እና
የፍቅር እጆች”የተሰኙ ልብወለድና ኢ ልቦለድ ታሪኮች ውስጥ ከልቤ
የማይወጡ ሴቶችን ህይወት አስታውሣለሁ፡፡ የአራት ዓመቷን የፌስቱላ ተጠቂ ህፃን እንዴት እረሣታለሁ፡፡
የልጆች ስነ-ጽሁፍ-ኩኩ መለኮቴ
የኢትዮጵያ ንግድና ኢንድስትሪና ኢንተርኘራይዝ ኢትዮጵያ ከወርልድ ባንክ
ጋር በመተባበር ባዘጋጁት የንግድ ሀሣብ ውድድር ላይ የልጆች
ጋዜጣን ሃሣብ ከባለቤቴና የስራ አጋሬ ጋዜጠኛ ገዛኸኝ መኮንን ጋር በማቅረብ ባገኘነው ሽልማት ኩኩ መለኮቴ የተሰኘችውን
ባለቀለም የልጆችና የቤተሰብ ጋዜጣን ለሶስት ዓመታት አሣትመናል ፡፡ የልጆች ጋዜጣን አሣትሞ
ለማሠራጨት ከባለቤቴ ገዛኸኝ መኮንን እና ከጓደኛዬ ፅጌረዳ ሀይሉ/
ነፍሷን ይማረውና/ የወጣን የወረድነውን አስቸጋሪ
መንገድ እንዲሁም ህትመቱን ካቆምን በኋላ ከየትምህርት ቤቱ እየተደወለ ለምን
ተቋረጠ? የሚለውን የልጆች ጥያቄ ከዓመታት በኋላ
አሁንም አስበዋለሁ፡፡ እና መንግስታዊም ሆነ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ለልጆች የሚቀርቡ ፕሮግራሞችን መደገፍ እንዳለባቸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ አስባለሁ ፡፡ በወቅቱ
ጋዜጣችንን ስንሰራ አብረውን ይሰሩ የነበሩት ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለቅቀው የነበሩት ታላቁ የልጆች አባት አባባ ተስፋዬ ሳህሉ ፣
ኮሜዲያን ክበበው ገዳ፣ የስነ ልቦና ባለሙያዋና መምህርቷ ሰሚራ አለሀዲን እና ዶ/ር ሚካኤል እሸቱ ነበሩ፡፡
ጥላ- አጭር ልቦለድ
ሌላው የመናገር
ነፃነት ላይ ሲሰራ የነበረው ፔን ኢትዮጵያ የተሰኘው የዓለም አቀፍ የስነ ፅሁፍና የሰብአዊ መብት ድርጅት የኢትዮጵያ ቻፕተር
ሲቋቋም ከመስራ’ቾቹ አንዷ ነበርኩ፡፡ በፔን ኢትየጵያ ማኀበር አማካኝነት ከሀገር ውጭ ደቡብ አፍሪካ ጆሀንስበርግ በስነፅሁፍ
እና በምርመራ ጋዜጠኝነት ለተወሰኑ ሳምንታት ስልጠና ወስጃለሁ፡፡
“የነገ ናፍቆት በተሰኘውና ፔን ኢትዮጵያ ለህትመት ባበቃው የአስራ ሶስት ደራሲያን የአጫጭር ልቦለዶች መድብል
ውስጥ “
ጥላ” የተሰኘ አንድ አጭር ልብወለድ ተካቶልኛል፡፡
ከራስ ሽሽት የተባለው መፅሀፌ ታተመ
የፃፍኳቸው ታሪኮች
በመፅሀፍ ከመታተማቸው በፊት በአዲስ አድማስ ሳምንታዊ ጋዜጣ ላይ በተከታታይ ለገፀ- ንባብ በቅተው ነበር፡፡ በኋላ ላይ
እነዚህን ወጎችና ደብዳቤዎች ከአዳዲስ ስራዎች ጋር በመጨመር ከራስ ሽሽት በተባለው መፅሀፌ ውስጥ ለመታተም በቅተዋል፡፡ በወቅቱ
እሰራ የነበረው በህግ ቢሮ ዉስጥ ስለነበረ ጋዜጣውን በሣምንት አንድ ጊዜ የሚታተመውን ተወዳጅ ጋዜጣ ሣነብ በአብዛኛው
ስነ-ፅሁፋዊ ሥራዎችን ያበረታታ ስለነበር እኔም ለምን አልክም የሚል ሀሣብ ብልጭ አለብኝና በፖስታ ቤት መላክ ጀመርኩኝ፡፡
ከዚያ በኋላ በተለያዩ ጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ ፅሁፎቼ የታተሙ ሲሆን ፤ለአብነትም ኔሽን ፣ አዲስ ውበት እና የአፍሪካ ፀሃይ
ከማስታውሣቸው ውስጥ ይገኙበታል፡፡
ጋሽ መስፍን ሀብተማሪያም ወግን ያስተማረኝ ታላቅ ሰው
በኔሽን ጋዜጣ ላይ ኢህአዲግ አ/በባን ሲቆጣጠር ተረኛ የኢትዮጵያ ሬዲዮ
ተረኛ ቴክኒሻን የነበሩትን ጋሽ ግርማን ቃለመጠይቅ አድርጌላቸው ነበር፡፡ የአፍሪከ ፀሀይ መፅሄት አዘጋጅ የነበረው ነፍሱን ይማረውና
ጋሽ መስፍን ሃብተማርያም ስለነበር ከጓደኛዬ ፣
የስራ ባልደረባዬ ፅጌረዳ ሃይሉ ነፍሷን ይማረውና መፅሄቱ ላይ
ተቀጥረን እንድንሰራ አድርጎ ለተወሰነ ጊዜ በሱ ኤዲተርነት
አብረን ሰርተናል፡፡ ይህም አጋጣሚ የወግ አባት እየተባለ የሚጠራውን ኢትዮጵያዊውን ጋሽ መስፍንን እንዳውቀው እድል ፈጠረልኝ ፡፡ በወቅቱ ከጋሽ መስፍን ጋር የነበረን በሣቅ በቀልድ በእድሜ ዘመን ትውስታ
የህይወት ልምዱን ጨምሮ አብረን ያሣለፍነው ጊዜ በጋዜጠኝነት ካሣለፍኩት ጊዜ እጅግ አስደሳችና የማይረሣ ነው፡፡ ጋሽ መስፍን
ስለወግ ፅሁፍ ይበልጥ እንዳቅና የኔ የወግ አፃፃፍም በወግ የአፃፀፍ ይትበሀል ውስጥ ከየት እንደሚመደብ የነገረኝ እሱ ነው፡፡
የብእር ትሩፋት ትዝታ
የሬዲዮ ጋዜጠኛነቴን
ስጀምር መንደርደሪያ የሆነኝ በኤፍ ኤም 97.1 ላይ ይቀርብ የነበረው የብዕር ቱሩፋት ነው፡፡ ሰሎሜ ደስታ አብራኝ በነበረች
ጊዜ ጋዜጠኛ መሆን ትችያለሽ ከማለት ጀምሮ እያንዳንዷ ንግግሯ ብርታት ይሰጠኝ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ሬዲዮ ቴክኒሻኖች ሰላማዊት ግርማ፣ ትርሲት ወንድሙ ፣
በለጥሻቸው፣የአይኔአበባ ስቱዲዮ ካሉ ደስታችን ነበር፡፡ በዚያን
ወቅት አብሬያቸው የመስራት እድል ካገኘኋቸው ጋዜጠኞች መካከል ቅጣው ንጉሴ ፣ ይፍቱ ስራ ቱጂ ፣ ዳግማዊ ታሪኩ ትዝ ይሉኛል፡፡
ደወል
ከዚያ እዚሁ 97.1 ላይ እና በብሔራዊ ጣቢያው ላይ በሳምንት ለሁለት
ቀን ይቀርብ የነበረው “ደወል” የተሰኘ በማኀበራዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር በፍሬድሪክ ኤበርት ስቲፍቱንግ እና በማኀበረራዊ ጥናት
መድረክ ትብብር እንዲሁም በዋግ ኮሚኒኬሽንስ ይቀርብ የነበረው የሬዲዮ ኘሮግራም ላይ አዘጋጅና አቅራቢ ሆኜ ለብዙ ዓመታት ከነ
በፍቃዱ አባይ ፣ አሻግሬ ሃይሉ ፣ ሰለሞን ዮሐንስ፣ ዮናስ ፣ ገሊላ መኮንን ጋር ስንሰራ የዋጋ ኮሚኒኬሽንስ መስራችና ባለቤት
የነበሩት ጥንዶቹ አቶ ተፈሪ ወሰንና ወ/ሮ ታቦቱዋ ወልደሚካኤል
ከብዙ ዓመት የሚዲያ ልምዳቸው ያጋሩንን እውቀትና ልምድ አስታውሣለሁ፡፡ ከወ/ሮ ታቦቷ ጋር ስለስራ ማውራት
ያስደስታል፡፡ የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ለቀጣዩ ሥራ የሚያዘጋጁ
ነበሩ፡፡ ‹‹ደወል›› ለረጅም ዓመታት በጋዜጠኝነት የሰራሁበት
ኘሮግራም ብቻ ሳይሆን በርካታ የኢትዮጵያን አካባቢዎች ተዘዋውሬ ለማየት የቻልኩበት እንዲሁም የተለያዩ ፅሁፎችን ለመፃፍ ፣
ጥናት ለማድረግ የተለያዩ ባህል ውስጥ ያሉትን አስተሳሰቦች ለመረዳት ለመገንዘብ ያስቻለኝ ሲሆን ፤ ከማኀበራዊ ጥናት መድረክ
ጋር በነበረው የስራ ትብብር ደግሞ በሀገራችን የተለያዩ የእውቀት ተቋማት ውስጥ ይሰሩ ፣ ያስተምሩ የነበሩ ምሁራንን ለማግኘትና
ኢንተርቪው ለማድረግ እኔም እግረመንገዴን ለመማርና የጋዜጠኝነት እውቀቴን ልምዴን ለማዳበር እድልን ፈጥሮልኛል፡፡ በሁለት ወር
አንድ ጊዜ አርብ ምሽት ይዘጋጁ የነበሩት “እውቀትን ለትውልድ
ማስተላለፍ “ የተሰኙት መድረኮች በጣም ብዙ እውቀትን የገበየሁባቸው በጥናትና በምርምር ላይ የተመሠረቱ ወረቀቶችንና ህትመቶችን
ያነበብኩባቸው አይረሴ የህይወቴ ክፍሎች ሲሆኑ በዚያን ወቅት ዶ/ር ባህሩ ዘውዴ ፣ ዶ/ር የራስ ወርቅ አድማሴ ፣ኢዛና
አምደወርቅ ፣ ፕሮፌሰር ሽፈራው በቀለ የመሳሰሉ ታላላቅ የእውቀት
አባቶች ጋር የመገናኘት እድልን ፈጥሮልኛል፡፡
ከህሊና ተፈራ ጋር
ከሬዲዮ ሳልወጣ ሌላ
የማስታውሰው ከታዋቂዋ ጋዜጠኛና የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ ህሊና ተፈራ ድርጅት /ተፈራ ኘሮሞሽን” አማካኝነት በኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ ከጓደኛዬ ፅጌረዳ ሃይሉ ጋር “ የነጋዴ
ሴቶች ድምፅ “ የተሰኘ የሬዲዮ ኘሮግራም አዘጋጅተን እናቀርብ ነበር፡፡ በመቀጠልም ከህሊና ተፈራ ጋር ክብር
ለጥበብ የተሰኘ በራስ ሆቴል ለተወሰነ ጊዜ ይቀርብ የነበረ የኪነጥበብ ዝግጅት ላይ ከሜሮን ጌትነት ጋር መስራት ጀመርን
፡፡ ከህሊና ጋር የሰራሁባቸውን ጊዜያት ሳስታውስ ትእግስትን ፣
ጥንካሬንና ተስፋ አለመቁረጥን እንዲሁም ሌላ መንገድ አለ ማለትን
ተምሬበት አልፌአለሁ፡፡
“የጎጆአችን ወግ” እና ‹‹አርኪ ካሜራ››
ወደ ሬዲዮ ጋዜጠኝነቱ ስመለስ ወደካናዳ ከመምጣቴ ጥቂት ቀደም ብሎ “የጎጆአችን ወግ” የተሰኘ በሸገር 1ዐ2.1 ላይ ከዳንኤል ብርሃኑና
ከመሣይ ምትኩ ጋር አዘጋጅና አቅራቢ ሆኜ ሰርቻለሁ፡፡
ሌላው “አርኪ ካሜራ
“ በተሰኘውና በሀገራችን በአርክቴክቸርና የከተማ ፕላን ዙሪያ የሚያተኩር የመጀመሪያው የቴሌቪዥን ኘሮግራም ላይ ከባለቤቴ እና
ከዋና አዘጋጁ ገዛኸኝ መኮንን እና ከሚካኤል ሽፈራሁ ጋር በፕሮግራም አስተዋዋቂነት የተወሰነ ጊዜ ሰርቻለሁ፡፡
የኢትዮጵያ መገናኛ
ባለሙያ ሴቶች ማኀበር በኤፍኤም 93.6 ለይ የቤት ውስጥ ጥቃትን በሚመለከት ያቀርብ በነበረው የሬዲዮ ኘሮግራም ላይ
ከቅድስት ክፍለዮሀንስ ጋር አዘጋጅና አቅራቢ ሆኜ
ሠርቻለሁ ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሴት ጋዜጠኞች ማኀበር አባል
በመሆኔ የተለያዩ ስልጠናዎችን ከቢቢሲ በመጡና ከሀገር ውስጥ
ጋዜጠኞች ስልጠናዎችን ወስጃለሁ፡፡
ስልጠና በኢንተርኒውስ
ስልጠናን በተመለከተ
ሳስታውስ ስለኢንተርኒውስ ኢትዮጵያ መጥቀስ ይኖርብኛል፡፡ ኢንተርኒውስ ኢትዮጵያ ለሬዲዮና ለህትመት ጋዜጠኞች በየጊዜው ይሰጣቸው የነበሩ በጣም ጠቃሚ
የነበሩና የዘመኑን ቴክኖሎጂና ያሰራር ክህሎት የሚያስተምሩ ስልጠናዎችን ከታላላቅ የምዕራብ ሀገራት ጋዜጠኞች እየጋበዘ ሲሰጥ
እኔም በተደጋጋሚ የስልጠናው ተካፋይ ከመሆኔም በላይ በወቅቱ በጣም ውድ የነበረውንና በቀላሉ ገበያ ላይ የማይገኘውን ዙም
የተሰኘ መቅረፀ ድምፅ ሰባት ቤት ጉራጌ ቸሀ ወረዳ ሄጄ በሰራሁት “ድርብ ጋብቻ” ላይ ያተኮረ የሬዲዮ ዶክመንተሪ አማካኝነት
ተሸልሜያለሁ፡፡ ኢንተርኒውስ ኢትዮጵያ እና ሜሮን ስዩም በደንበል ህንፃ ላይ በአዲስ አበባ ለነበሩ ብቻ ሳይሆን ከመላው ሀገሪቱ
ይመጡ ለነበሩ ጋዜጠኞች ያደርጉት የነበረው አቀባበልና ይሰጡት
የነበረው አገልግሎት ፈፅሞ አይዘነጋም፡፡
ከሀገር ከመውጣቴ በፊት ለመጨረሻ የሰራሁት “አዲስ ገፅ ” የሬዲዮ
ኘሮግራም ላይ ሲሆን ፤ መስፍን አሰፋ ፣ ዳንኤል ብርሃኑ ፣ ይፍቱ ስራ ቱጂ እና አስፋው ደገፉ ፡፡ መቼም የማይረሣ የሬዲዮ
ጋዜጠኝነቴን የበለጠ እንድወደውና እንድፈልገው ያደረገኝ መልካም አጋጣሚ ነበር ፡፡
ሶስና በካናዳ
ካናዳ ቶሮንቶ መኖር
ከጀመርኩ ሶስት ዓመት አሳለፍኩ ፡፡ ከአየሩ ፀባይ ጋር ባህሉን
የአነጋገር ዘይቤውን እና የአኗኗር ሲስተሙን መልመድ እጅግ ከባድ ነው፡፡ በዚህ ውጥረት ውስጥ Shoe Project /ስደተኛ
ሴቶች በጫማቸው ውስጥ የአጋጠማቸውን ታሪክ የሚተርኩበት
የፀሃፊያን ኘሮጀክት ውስጥ ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የመሣተፍ እድል አገኘሁ፡፡ በዚህም ፅሁፎቼ ስለኢትዮጵያና
አፍሪካ ሴቶች በፃፍኳቸው My Congo shoe/ እና / My Dad”s Black shoe የተሰኙ ታሪኮች በኮንጎ ጫማ
የኢትዮጵያውያን ሴቶችን እንግልትና ህይወት ስተርክ የአባቴ ጫማ በተሰኘው ደግሞ አባቴ ካለጥፋት በታሰረ ጊዜ የደረሰብንን መንገላታታ እና አሁን ደግሞ
ስደተኞች የሚከፍሉትን መስዋትነት የሚያሳይ ታሪክ በእንግሊዝኛ ፅፌ አሳትሜያለሁ፡፡ የአባቴ ጫማ የተሰኘውን ታሪክም በአጭር
ፊልም ሰርቼው ተወዳጅነትን አግኝቷል፡፡ እዚህ ኘሮጀክት ላይ
በመሣተፌ ብዙ ነገር አትርፌያለሁ ፡፡ የስደት ኑሮ አድካሚና
መባከን የተሞላበት አንዳንድ ጊዜ ሰውነትን የመጎተት ያህል ስሜት የሚሰማ ሀገር የሚናፈቅበት የሀገር ልጅ ሲታይ ሆድ የሚብስበት
ቢሆንም በዚህ ሁሉ መሀል ደግሞ “ሀገራችሁ የት ነው የሚሉ
ዝርዝር ጥያቄዎችን ለሚያነሱ ካናዳውያንና የሌሎች ሀገር ሰዎች
መልስ ይሆን ዘንድ ከባለቤቴ ገዛኸኝ መኮንን ጋር አዲስ
ቅኝት የሚዲያ አገልግሎትን መሥርተን እየሰራን ነው፡፡ የሚዲያ
ስራ አድካሚና ብዙ ትግልና ጥረት እንዲሁም ተስፋ አለመቁረጥ
የታከለበት ቢሆንም የኑሮ ውጣ ውረዱን በአንድ ትከሻችን ተሸክመን
በሌላው የሚዲያ ስራችንን በሰው ሀገር ስለሀገራችን እየሰራን ልጃችንን ደግሞ በኢትዮጵያዊ ባህል እያሳደግን እንገኛለን፡፡
ልጃችን ሄሶጵ ገዛኸኝ ይባላል፡፡ 10 አመቱ ነው፡፡
ገዛኸኝ መኮንን ስለ ባለቤቱ
ሲጀመር ሶስና የልጄ
እናት ባለቤቴ ናት፡፡ ጓደኛዬ ናት፡፡በምሰራው ስራ ውስጥ ደግሞ ሀያሲዬ ናት፡፡ አዲስ ቅኝት ውስጥ ደግሞ ባልደረባዬ ናት፡፡ ሶስና ጎበዝ የአጭር ልቦለድ
ጸሀፊ ናት፡፡ ስትጽፍ በፍጹም አይደክማትም፡፡ ልባም ደራሲ ናት፡፡ ከ10 አመት በፊት ልጃችንን እርጉዝ ሆና በተለይ ልትወልድ በተቃረበችበት ሰአት ብእር ከወረቀት አቆራኝታ ስትጽፍ
ነበር፡፡ ያኔ ለፖፕሌሽን ሚድያ የሚገባ አጭር ልቦለድ ነበርና ታሳየው የነበረው ትጋት አሁን ሳስበው ድንቅ ይለኛል፡፡ ሶስና
ሰው ልብ ብሎ የማያጤናቸውን ነገሮች ትኩረት ሰጥታ ታያለች፡፡ ከዚያም ያንን ያየችውን ነገር ትርጉም ሰጥታ አጭር ልቦለድ ታደርገዋለች፡፡
ይህ ክህሎቷ ወደ ካናዳ ከመጣችም በኋላ የቀጠለ ነበር፡፡ ስራዎችን በትጋት እና በብዛት በመስራት ሶሲ ትታወቃለች፡፡ የተሰጣትን
ስራ በፍቅርና በመሰጠት ስለምትሰራ ይሳካላታል፡፡ አንድን ስራ
በዚህ ሰአት አስረክቢ ከተባለች በተባለችው ሰአት በማስረከብ ሃላፊነቷን የምትወጣ ነች፡፡ እንደ እናት ደግሞ መልካም እናት
ነች፡፡ ልጅን መቆጣት ባላባት ጊዜ ትቆጣለች፡፡ ልጅን በጥሩ ስነ-ምግባር ማሳደጉንም በሚገባ ታውቅበታለች፡፡ ለቤተሰቦቿም አይን
ነች፡፡ ሰውን በጣም የምትወድ ስትሆን ከአዲስ ቅኝ ስኬት ጎን ያለች ጠንካራ ባለሙያ ነች፡፡
መዝጊያ ፤ ሶስና
አሸናፊ በሚድያ እና በስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ደከመኝ ሳትል ያገለገለች ጠንካራ እናት ነች፡፡ ከ 3 አመት በፊት ኢትዮጵያ በነበረች
ጊዜ የጥበብ ጉዳዮች ላይ የፈለገ አያጣትም፡፡ በፈጣራ ስራዎቿ ደግሞ የራሷ ቀለም የፈጠረች መሆኑን በቅርበት የሚያውቋት
ይመሰክራሉ፡፡ ሶስና ትጉህ ናት፡፡ ትጽፋለች-ታነባለች-መድረኮች ላይ ታስተባብራለች ሌላም……፡፡ ይህ ርካታን ስለሚሰጣት ትጋቷን
አታቆምም፡፡ ገና በልጅነት የንባብ ፍቅር ተዘርቶባት ስለነበር እንዲህ በቀላሉ ከጽሁፍ ጋር የምትለያይ አልነበረችም፡፡ እናም
አጭር ልቦለዶችን ከሚጽፉ በጣት ከሚቆጠሩ ሴቶች አንዷ ለመሆን ችላለች፡፡በሚድያው ዘርፍም ቢሆን ብዙም ትኩረት በማይሰጠው እና
ትርፍ በማይገኝበት የልጆች የስነ-ጽሁፍ ስራ ላይ ተሰማርታ / ከባለቤቷ ጋር/ ለ 3 አመታት ሳይደክማት አንድ ቁምነገር
አዋጥታለች፡፡ ብቻ ለጥበብ ነው የተፈጠርኩት ብላ ስለምታምን ከጥበብ ስራዎች ሌላ ስራን መከወን ደስታን አይሰጣትም፡፡ ባለቤቷ
ገዛኸኝ መኮንን የራሱ ድንቅ ታሪክ ያለውና በቀጣይ የእርሱም ታሪክ በዚህ ዊኪፒዲያ የሚወጣ ሆኖ ሳለ በሶስና የጥበብ ስራ ውስጥ
አንድ አስተዋጽኦ ማበርከቱን እናውቃለን፡፡ ገዛኸኝ ካናዳ ቀደም ብሎ የገባ በመሆኑ ነገሮችን አመቻችቶ ሶስናን ጠበቃት፡፡ ዛሬ
ጥንዶቹ ‹‹አዲስ ቅኝት›› የተሰኘውን ሚድያ ከፍተው በካናዳ የሚኖረውን ማህበረሰብ እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ የእነርሱ ሚና በቀላሉ
አይታይም፡፡ ምናልባትም ካናዳ ውስጥ ኖረው የራሳቸውን ሚድያ ከከፈቱ በጣት ከሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን መካከል እነ ሶስና
ይመደባሉ፡፡ በብዙ ነገር ይለያሉ፡፡ 4ኛ አመታቸውን ሲያከብሩ ጉዞው ቀላል አይሆንም፡፡ በዩቲየብ ገጻቸው በርካታ
ኢትዮጵያውያንን በማነጋገር ጥሩ መድረክ ከፍተዋል፡፡ ሶስናም በእነዚህ ፕሮግራሞች ላይ በንቃት ትሳተፋለች፡፡ሀገር ቤት የጀመረው
የትጋት ተምሳሌትነት ካናዳ ቀጥሏል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት ኢትዮጵያውያን በባህር ማዶ በመክሊታቸው ቢሰማሩ መልካም
ነው ይላል፡፡ እንደ እነ ሶስና አይነቶች በአንድ በኩል እድለኛ ናቸው በሌላ በኩል ደግሞ የካናዳን ሲስተም ተረድቶ ሚድያን መምራትና 4ኛ አመትን ማክበር ጎበዝ
መሆንን ይጠይቃል፡፡ ሶስናም በዚህ መልኩ ጥረቷ ታክሎበት 4ኛአመት የአዲስ ቅኝትን በአል ስታከብር ለባለቤቷ ለገዛኸኝ መኮንን
ምስጋና ማቅረብ ትወዳለች፡፡ እርሱ ቀደም ብሎ መጥቶ ነገሮችን በማመቻቸቱ ለሶስና ሁኔታዎች ቀላል ሆነውላታል፡፡ባልና ሚስት
እንዲህ እየተረዳዱ ኑሮን በካናዳ ምርጥ ለማድረግ ይተጋሉ፡፡ በአንድ በኩል ልጃቸውን ሄሶጵን ያሳድጋሉ በሌላ ደግሞ አዲስ
ቅኝትን እየተንከባከቡ ለወግ ማእረግ ለማድረስ ላይ ታች ይላሉ፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት እንደ ሶስና አይነት ሰዎች
መዝገብ ላይ ታሪካቸው ቢሰፍር የሚያስተምሩት ነገር አለ፡፡ በመሆኑም፣ እንደ ሶስና አይነት የተሰጡ ሰዎችን በዚህ ዊኪፒዲያ ላይ
ታሪካቸውን ስላወጣን ደስታቸውን እጥፍ ድርብ ነው፡፡ መልካሙን ሁሉ እንመኛለን፡፡ / ይህ ጽሁፍ የሶስና አሸናፊን ጽሁፍ መሰረት
አድርጎ የተጻፈ ነው፡፡ የአርትኦት እና የመዝጊያ ሀሳቡ እንዲሁም ባለታሪኳን ወደ ዊኪፒዲያ የማምጣቱን ስራ ያከናወነው ጋዜጠኛ
እዝራ እጅጉ ነው፡፡ ይህ አጭር ግለ-ታሪካ ዛሬ እሁድ ነሀሴ 16 2013 በተወዳጅ ሚድያ የፌስ ቡክ ገጽ እና በዊኪፒዲያ ላይ
ወጣ./
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ