32. ተስፋዬ ህይወታችንን›› አጣን  

 ደግ ናቸው፡፡ ለብዙዎች ተስፋ ሰጥተዋል፡፡  ለራሴ ሳይሉ ለሰው ብዙ አድርገዋል፡፡ በመላ ዋሽንግተን ዲሲ ብዙ ሰው ያውቃቸዋል፡፡ በተለይ ሰውን ለስኬት በማብቃት ተወዳዳሪ አልነበራቸውም፡፡ ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ከዛሬ 31አመት በፊት ስለ እኒህ ታላቅ ሰው ጽፎላቸዋል፡፡ እርሳቸው ግን ዋሽንግተን ፖስት ላይ ተጻፈልኝ ብለው ዝም ብለው አልተቀመጡም፡፡ ይልቁን መትጋቱ ላይ በረቱበት፡፡ ስኬትንም አገኙ፡፡ እኒህን ሰው ዛሬ በአካል ብናጣቸውም   ታሪካቸውን ግን ለትውልድ ይቆያል፡፡ ይህን የዊኪዲያ ታሪክ የሚሰንደው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን  በስራ ፈጠራ ዘርፍ የብዙዎችን ታሪክ እየሰነደ ያስቀምጣል፡፡ ታሪካቸው አስተማሪ የሆኑትን በዚህ መልኩ እየዘከረ የሀገርን በጎ ገጽታ ለመገንባት ይጥራል፡፡ የሰው ልጅ ሰርቶ ሰርቶ ያልፋል፡፡ ታሪኩ ግን ይሻገራል፡፡ የአቶ ተስፋዬም ህይወት ለአዲሱ ትውልድ የሚጠቅም አንዳች ነገር አለው፡፡ በመሆኑም አቶ ተስፋዬን ለመዘከር ይህን ታሪካዊ ጽሁፍ አውጥተናል፡፡ ከዚህ ቀደም የታላላቅ ኢትዮጵያውያንን ታሪክ በዚህ መልክ ያወጣን ሲሆን እነሆ አሁን የአቶ ተስፋዬን  እነሆ፡፡ ይህ ጽሁፍ በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት የሚወጣ ሲሆን ጽሁፉም በጋዜጠኛ እዝራ እጅጉ እና ባልደረቦቹ  የተዘጋጀ ነው፡፡

         መልካምነትን ሀገርን ፍቅርን ከአባት መውረስ 

ስራ ፈጣሪው ተስፋዬ ፣ ኢትዮጵያን መውደድንና ለሀገር መስራትን የተማረው ከአባቱ ከቀኛዝማች ህይወት ህዳሩ ነው፡፡ አርበኛ ህይወት ህዳሩ በ1928ቱ የኢጣሊያ ጦርነት ጊዜ ሀገራቸውን ከጠላት የታደጉ ባለውለታ ሲሆኑ በተለይ ሱዳን ተሰደው በነበረበት ጊዜ የሀገራቸውን ነጻነት ለማስመለስ ከሌሎች የውስጥ አርበኞች ጋር ታላቅ ተጋድሎ ያደረጉ ባለውለታ ናቸው፡፡ እኒህ የሀገር ባለውለታ ጠላት ሽንፈቱን ከቀመሰ በኋላና ተጠራርጎ ከወጣ በኋላ ወደ ሀገራቸው በመመለስ በተለያዩ ሙያዎች ሀገራቸውን ማገልገል ችለዋል፡፡ አርበኛው በተለይ  በጥብቅና ስራ ፤ እንዲሁም በትልልቅ የእርሻ ስራዎች ላይ በመሰማራት እናት ሀገራቸውን ያገለገሉ ነበሩ፡፡ ያሳለፉትን ህይወት በተመለከተም ያቺ ቀን ተረሳች በሚል ርእስ መጽሀፍ ያሳተሙ ናቸው፡፡ 5ኛ ልጃቸው አቶ ተስፋዬ ህይወት ታዲያ ይህንን ሁሉ መልካምነት የወረሱት ከአባታቸው እንደሆነ ይነገራል፡፡ ሀገር ፍቅርን ለሀገር ማገልገልን ከአባታቸው መውረሳቸው ለመልካምነታቸው ትልቅ ሚና ነበረው፡፡

 አቶ ተስፋዬ ህይወት አባታቸው ቀኝ አዝማች ህይወት ህዳሩ ሲባሉ ወላጅ እናታቸው ደግሞ ወይዘሮ ወሂባ መንግስቱ   ይባላሉ፡፡ አቶ ተስፋዬ ህይወት  በ1940 አመተ ምህረት የተወለዱ ሲሆን ህይወታቸው ሲያልፍም የ73 አመት ሰው ነበሩ፡፡

 አቶ ተስፋዬ  ትምህርታቸውን  በቅዱስ ዮሴፍ ተማሪ ቤትና በአድቬንቲስት ሚሽን ተከታትለው ጨርሰዋል፡፡  ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁም   አባታቸው ወደ አሜሪካን ሀገር በ1960 አካባቢ ላኳቸው፡፡ አቶ ተስፋዬ ገና በ20ዎቹ መጀመሪያ ላይ ሳሉ የአሜሪካንን ምድር እንደረገጡ  ወደ ከፍተኛ ትምህርት መግባት ነበረባቸው ፡፡  በዚህ መሰረትም በኒዮርክ ስቴት ኒው ፖውል ዩኒቨርሲቲ  ከፍተኛ ትምህርታቸውን በቢዝነስ አስተዳደር በመጨረስ አጠናቀዋል፡፡

 የስራ ፈጣሪው አቶ ተስፋዬ፣ አዲስ ነገር የመፍጠር ክህሎትን የታደሉ በመሆናቸው ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ  ወደ ግል ስራቸው ነበር የገቡት፡፡ ብዙዎች እንደሚናገሩላቸው አዲስ እቅድ የማውጣት ችሎታቸው የዳበረ ስለነበር በአጭር ጊዜ ውስጥ  በዋሽንግተን ዲሲ ከተማ ደረጃውን የጠበቀ ሬስቶራንት በመክፈት የቢዝነስ አለሙን ተቀላቀሉ፡፡

አቶ ተስፋዬ ህይወት፣ በ1970 ከወይዘሮ ምግባር አያሌው ጋር ትዳር በመመስረት  ኑሮን ጀምረዋል፡፡  ሁለቱም በጥምረት የንግዱን ስራ በስፋት ለማካሄድ የጣሩ ሲሆን  በአጭር   ጊዜ ውስጥም ከበሬታን እና ዝናን ለማትረፍ ችለዋል፡፡በተለይ በዋሽንግተን ዲሲ የከፈቱት ናይት ክለብ በአሰራሩና በደረጃው በብዙዎች ለመደነቅ የቻለ ነበር፡፡ በተለይ ደግሞ 7ፎቅ በሆነው ናይት ክለብ ሁሉም አይነት የሙዚቃ ዘውጎች ያሉ ሲሆን ጃዝ የፈለገ በሚፈልገው መንገድ ይቀርብለታል፡፡ ብሉዝ ነው ምርጫዬ ለሚልም እንዲሁ ናይት ክለቡ የደንበኞችን ስሜት በማስተናገድ ዝናን ያተረፈ ነበር፡፡

 አቶ ተስፋዬ፣ ታዲያ የክለብን አሰራር ዘመናዊ ለማድረግ በመቻላቸውና ይህም በብዙዎች መመስከሩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስመ-ጥሩ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል፡፡ ሌሎች ክለቦችም የእርሳቸውን አርአያ በመከተል  ክለባቸውን በእነ አቶ ተስፋዬ ክለብ አይነት በማድረግ  ስራቸውን ለማሳደግ ችለዋል፡፡ ይህ ናይት ክለብ  በመላ የዲሲ ነዋሪዎች ዘንድ የሚታወቅና እንደ ማይክ ታይሰን እና ማይክል ጆርዳን የመሰሉ አለም አቀፍ ሰዎች ዘና የሚሉበት ቤት ነው፡፡ አቶ ተስፋዬም ለዲሲ ማህበረሰብ ባቀረቡት የመዝናኛ አማራጭ በከተማዋ ከንቲባ ሳይቀር ለመሞገስ የቻሉ ነበሩ፡ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ከዛሬ 31 አመት ቀደም ብሎ ስለ አቶ ተስፋዬ ሬስቶራንት ባወ ጣው ዘገባ ይህ ሬስቶራንት ደረጃውን ያሟላ ለብዙዎች መዝናናት ምክንያት የሆነ ቤት ነው ሲል ጽፎ ነበር፡፡ በአንድ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ባለቤትነት የተመሰረተው  ናይት ክለብ መላ አሰራሩ ምርጥ ነው ሲል ማርች 16 1990 ላይ ባወጣው እትሙ አስታውቋል፡፡  ይህን በዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላዩ  የወጣን ጽሁፍ የጻፉት ጋዜጠኛ ኢቭ ዚባርት ይባላሉ፡፡ 

  ሰአሊ እስክንድር ቦጎሲያን፣ በአቶ ተስፋዬ ሬስቶራንት ውስጥ ስእል እንዲስል በማድረግና በመላ አሜሪካም ዝነኛ እንዲሆን የአቶ ተስፋዬ እገዛ ትልቅ ነበር፡፡

 ከሰው ጋር በቀላሉ የመግባባት እና ሰውን የመርዳት ልዩ ፍላጎት የነበራቸው አቶ ተስፋዬ ዋና የህይወት መርሀቸው ለሰው ልጅ በጎ ማድረግ ነበር ፡፡  ታዲያ አቶ ተስፋዬ ለሰው በጎ ሲያደርጉ ለእከሌ ይህንን አደረግኩ ብለው ከመናገር ይቆጠባሉ፡፡ ምክንያቱም ለእርሳቸው ርካታ የሚሰጣቸው ያ ሊረዳ የሚገባው ሰው ሲታገዝ ብቻ ነው፡፡ በዚህ የህይወት መርሀቸው ብዙ አድናቆት አትርፈዋል፡፡

ከዛሬ 38 አመት በፊት በዲሲ በከፈቱት ናይት ክለብ ያልተጫወተ ድምጻዊ የለም፡፡ ድምጻዊት አስቴር አወቀ ለመጀመሪያ ጊዜ አሜሪካን እንደገባች የተጫወተችው በአቶ ተስፋዬ ናይት ክለብ ውስጥ ነበር፡፡  በተጨማሪም፣ አለማየሁ እሸቴ ፣ ነዋይ ደበበን የመሰሉ ሰዎች በዚህ ሬስቶራንት በመጫወት ታዳሚዎችን ማስደሰት ችለዋል፡፡ ታዲያ ከእነዚህ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ጀርባ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ነበሩ፡፡ አቶ ተስፋዬ ከአርቲስቶቹ ጋር በነበራቸው ቀረቤታ በጣም የሚወደዱ ብቻ ሳይሆኑ አርቲስቶቹን እንደ ቅርብ ወዳጅ በማየት በሙያው ላይ እንዲበረታቱ ያደረጉ ታላቅ ባለውለታ ነበሩ፡፡

አቶ ተስፋዬ፣ ሰውን ማቀራረብ ዋና መርሀቸው ነው፡፡  የወዳጆቻቸውን ልጆች እንደራሳቸው የሚያዩ በመሆኑ  በተለይ በሚለግሱት ምክር አዘል ቁምነገር ይታወቃሉ፡፡  በተለይ ታዳጊ ልጆች በትምህርታቸው እንዲበረቱ  በመምከር አቶ ተስፋዬ ሀገራዊ አደራቸውን ተወጥተዋል፡፡  በዚህ የደግነት ባህሪያቸው መላ ኢትዮጵያዊ  እንደ አንድ ደግ አባት አድርጎ ይቆጥራቸዋል፡፡

አቶ ተስፋዬ፣ አሜሪካን ሀገር የጀመሩትን ንግድ ለጊዜው ገታ በማድረግ በ1984 ግድም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ሀገሬን በአንድ በኩል ላገልግል የሚል መርህ አንግበው ነበር፡፡  ዋና ግባቸውም  በአሜሪካን ሀገር የቀሰሙትን ልምድ ለኢትዮጵያውያን ማስተዋወቅ ነበር፡፡  በቀዳሚነት ሰአሊዎች የስእል ስራቸው እንዲታይ በማድረግ  ጋለሪ በመክፈት ትልቅ ቁምነገር ለማከናወን ችለዋል፡፡  ይህም በጊዜው የነበሩ ሰአሊዎችን ያበረታታ ነበር፡፡ የአንድን ሰአሊ ስራ በጥሩ  ዋጋ በመግዛት የሰአሊው ህይወት በተወሰነ መልኩም ቢሆን እንዲቀየር ትልቅ ስራ መስራታቸው በስፋት ይነገራል፡፡

የእነዚህ ሰአሊዎች ስራ፣  በአውሮፓ እና በአሜሪካ ኤግዚቢሽን እንዲታይ በማድረጋቸው እንደትልቅ ባለውለታ ይቆጠራሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አቶ ተስፋዬ  በቴሌ ቶን ገንዘብን የማሰባሰብ ስራን በማስጀመራቸው ይመሰገናሉ፡፡ ይህም ስራ ለብዙዎች የስራ እድል የፈጠረ በመሆኑ አቶ ተስፋዬን እንደ ስራ ፈጣሪ እና ሀሳብ አመንጪ ስማቸው ከፍ ብሎ እንዲነሳ የሚያደርገው ነው፡፡

አቶ ተስፋዬ ህይወት ፣ በድንገተኛ አደጋ ህይወታቸው እስካለፈበት ድረስ  ደከመኝን የማያውቁ ታላቅ የኢትዮጵያ ባለውለታ ነበሩ፡፡  ነሀሴ 14 2013 በ73 አመታቸው ህይወታቸው ያለፈው አቶ ተስፋዬ የሁልጊዜም መርሀቸው  ሰውን ሰው ማድረግ የሚል ይሆናል፡፡ አባታቸው ቀኛዝማች ህይወት ህዳሩም በነሀሴ 14  የማረፋቸው አጋጣሚ የሚገርም ሁኔታ ነው፡፡  አቶ ተስፋዬ ከወይዘሮ ለአለም ፍስሀ ጋር በመሆን ህይወታቸው እስካለፈበት ቀን ድረስ በተድላ እና በደስታ ተሳስረው የኖሩ ነበሩ፡፡

         አቶ ይሄይስ ውሂብ

አቶ ይሄይስ ውሂብ ከአቶ ተስፋዬ ጋር ከልጅነት ጀምሮ ይተዋወቃሉ፡፡  በአቶ ይሄይስ አተያይ   አቶ ተስፋዬ ለስራ ፈጣሪነት የተፈጠረ ድንቅ ሰው ነው፡፡ ‹‹ገና የአሜሪካንን ምድር ከረገጠበት ሰአት አንስቶ፣ ልቡ ለአዳዲስ ነገሮች የተነሳሳ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ቶሎ ስኬትን ማግኘት ቻለ ሲሉ አቶ ይሄይስ ሀሳባቸውን ይሰጣሉ፡፡ ‹‹ተስፋዬ ገና ቅዱስ ዮሴፍ ተማሪ ቤት ሲማር ንቃትን የተላበሰ ሰው ነበር፡፡ ይህን ንቃቱን ከብቃት ጋር ይዞ አሜሪካ ሲገባ ነገሮች ሁሉ ተመቻቹለት፡፡ ተስፋዬ በአሜሪካ ብቻ እርሱ በፈጠረው ስራ ምክንያት አሜሪካውያን ሳይቀሩ የስራ እድል ተመቻችቶላቸዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያን የሚያኮራ ታላቅ ነገር ነው ›› ሲሉ ስለ ውድ ጓደኛቸው  ሀሳብ የሰጡት  አቶ ይሄይስ ውሂብ ናቸው፡፡ አቶ ይሄይስ ስለ አቶ ተስፋዬ የሚደንቃቸው ለሰው ልጅ የሚያሳየው ትልቅ ርህራሄ ነው፡፡‹‹ ሰውን መቀየር ደስ ያሰኘዋል፡፡ ሰው ሲደሰት ደስ ይለዋል፡፡ በአንድ ወቅት አንድን ጎዳና ላይ የሚኖርን ልጅ በእንዴት ያለ መልኩ እንደረዳው ሳስብ ግርም ይለኛል፡፡ ደግነት ከውስጡ የሚወጣ ስለሆነ ይሳካለታል፡፡ ደግሞም  ከመኖር ያገኝ የነበረው ርካታ ይህ ይመስለኛል›› ሲሉ አቶ ይሄይስ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡

አሁንም አቶ ይሄይስ ቀጠሉ‹‹…በአንድ ወቅት የአንድን ሰአሊን ህይወት የቀየረበትን አጋጣሚ አልረሳውም፡፡ ሰአሊው ራሱን ጥሎ በነበረበት ጊዜ  ተስፋዬ ቤቱ ወስዶት መክሮት ህይወቱ እንዲለወጥ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ ሰአሊ በጊዜው ከነበረበት የተስፋ መቁረጥ ህይወት ወጥቶ ራሱን በመቻል ስኬታማ ሰው ፤ ቤተሰቡን የሚያስተዳድር ለመሆን ችሏል፡፡ እንዲህ አይነት ታላቅ ፤ ቸር ሰው ነው ኢትዮጵያ ያጣችው ›› ሲሉ አቶ ይሄይስ ለዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጅ ተናግረዋል፡፡

            እጅግአየሁ ደምሴ

እጅግአየሁ ደምሴ ፣ ስለ አቶ ተስፋዬ ሀሳቧን ስትሰጥ ባለ ራእይ መሆኑ ይታወሳታል፡፡ እንዲህ አይነት  ሰዎች አዲስ ነገር ለማመንጨት  የተዘጋጁ ናቸው  ስትል ወይዘሮ እጅግአየሁ የአቶ ተስፋዮን የማሰብ ሀይል ትልቅ መሆኑን ትናገራለች፡፡  አቶ ተስፋዬ ራእዩን በቃል ይናገራል፤ ከዚያም ይተገብረዋል ስትል ወይዘሮ እጅግ አየሁ ሀሳቧን ትሰጣለች፡፡

‹‹….ተስፋዬ አንድን ሀሳብ ካሰበ በደንብ እንደሚሆን አድርጎ ያስበዋል፡፡ ከዚያም እውን ያደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ሬስቶራንቱን ሲከፍተው የጃዝ ሙዚቃው የቱ ጋር መሆን እንዳለበት፤ ብሉዝ ምን ጋር  መሆን እንዳለበት ቀድሞ በአእምሮው ይስለዋል፡፡ ከዚያም ያ ያሰበው ነገር እውን ሲሆን ይታያል፡፡ታዲያ ተስፋዬ ይህን ሁሉ ሲፈጥር ገንዘብ ምንም ጉዳዩ አልነበረም፡፡ ዋናው የእርሱ ህልም ሀሳቡን ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ አስታውሳለሁ መጀመሪያ አሌግዛንደሪያ ላይ  ሬስቶራንት የከፈተ ጊዜ የመጡ እንግዶችን ሁሉ አይከፍሉም እያለ በነጻ ሲያበላ እንደነበር ትዝ ይለኛል፡፡ ይህ ሩህሩህነቱን የሚያሳየን ነው፡፡ እኛም ይህ እኮ ቢዝነስ ነው እያልን ልንመክረው እንሞክራለን፡፡ ››   ብላለች ወይዘሮ እጅግአየሁ ደምሴ፡፡

 ወይዘሮ እጅግአየሁ ስለ አቶ ተስፋዮ ሬስቶራንት ስታስብ እንደ ማይክል ጆርዳን ያሉ ስመጥሩ ሰዎች ለመዝናናት ይመጡ ነበር ስትል ትዝታዋን ታወጋለች፡፡ ታዲያ በዚያ ሬስቶራንት ማይክል ጆርዳን አለ ከተባለ ሰዎች አድናቆታቸውን ለመግለጽ ከሬስቶራንቱ ይታደሙ ነበር፡፡  

               አቶ ቢንያም ወሃበ

 አቶ ቢንያም ወሃበ  የአቶ ተስፋዬ ህይወት የቅርብ ዘመድ ሲሆን የአክስቱን ልጅ ስኬት ሲመዝነው ሀገሩን የሚወድ ታላቅ ስራ ፈጣሪ ይለዋል፡፡  በአቶ ቢንያም ገለጻ ስራ ፈጣሪው ተስፋዬ የተለያዩ የፋሽን ትርኢቶች እንዲደረጉ በማድረግ ለሙያው እድገት ታላቅ ሚና ነበረው፡፡ ‹‹ ከተስፋዬ የሚገርመኝ ነገር አንድን ነገር ልብ ብሎ ያጤናል፡፡ ከዚያም እንዴት መቀየር እንዳለበት ሀሳብ ይሰጣል፡፡ ብዙ ጊዜ  ምርጥ ሀሳቦች እንዴት እንደሚመጡለት ድንቅ ይለኛል፡፡  አዳዲስ ነገሮችን ለመፍጠር የተካነ ሰው መሆኑን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ እንዲህ አይነት ሰዎችን እውነት ለመናገር አልተጠቀምንባቸውም፡፡ ›› ሲል ሀሳቡን አክሎ ነበር፡፡

              ዶክተር ሳሙኤል አሰፋ

አቶ ተስፋዬ ህይወትን በቅርበት ከሚያውቁት መካከል ዶክተር ሳሙኤል አሰፋ አንዱ ናቸው፡፡ ዶክተር ሳሙኤል የአቶ ተስፋዮን ችሎታ ሲገልጹ በአሜሪካ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሚባሉት አፍሮ አሜሪካን አንዱ ናቸው ይሏቸዋል፡፡ ዶክተር እንደሚናገሩት' አቶ ተስፋዬ በምድረ አሜሪካ ኢትዮጵያውያንን ብቻ ሳይሆን መላ ጥቁርን ያስከበረ ታላቅ ሰው ነው ብለውታል፡፡

‹‹ በተስፋዬ የተመሰረተው ናይት ክለብ ከኤፍቢ አይ ቢሮ አጠገብ መሆኑ ራሱ የሚደንቅ ነው፡፡ ይህ ተስፋዬ ለስራው ያለውን ድፍረት ያሳየናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ደግሞ አንድ ሰው ወደ ናይት ክለብ ለመግባት ከፈለገ የአለባበስ  ደንብና  ስርአትን ማክበር አለበት፡፡ አሊያ እዚህ ጋር ተስፋ§ ድርድር የሚሉትን ነገር አያውቅም፡፡ ይህም ለጀመረው ስራ የሚሰጠውን አክብሮት የሚያሳየን ነው፡፡ ተስፋዬ ለገንዘብ ብሎ ሳይሆን ውስጡ ያለውን ህልም ለመኖር ነበር ብዙ ጉዳዮችን ሲያከናውን የነበረው›› ሲሉ ዶክተር ሳሙኤል የዚህ ሰው መታጣት ለኢትዮጵያ ትልቅ ጉዳት ነው ብለዋል፡፡

ዶክተር ሳሙኤል አሰፋ የአቶ ተስፋዬ ጥረት ከእናት ሀገር ፍቅር ጋር የተያያዘ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ ‹‹ ተስፋዬ ምንም እንኳን ለአመታት በምድረ-አሜሪካ ቢኖርም ሀገሩን በአንድ መልኩ የማገልገል ግብ ነበረው፡፡ ይህ በመሆኑም በ1983 የመንግስት ለውጥ በተደረገ ጊዜ ወደ ሀገር ቤት በመግባት  በአሁኑ ሰአት የኤግዚቢሽን ማእከል በመባል የሚታወቀውን ቦታ በመውሰድ ለመጀመሪያ ጊዜ ዘመናዊ ቅርጽ እንዲይዝ ያደረገ ሰው ነው፡፡ ይህ ለቢዝነሱ አለም ትልቅ ነገር ነበር፡፡ እና ተስፋዬ አዲስ ነገርን መጀመር ያውቃል›› በማለት ዶክተር ሀሳብ ሰጥተዋል፡፡

  ፤ለአቶ ተስፋዬ ህይወት ቤተሰብ መጽናናትን ተመኘን ፡፡ የአቶ ተስፋዬ ህይወት የቀብር ስነ-ስርአት ዛሬ ነሀሴ 18 2013 ወዳጅ ዘመዶቻቸው በተገኙበት ተፈጽሟል፡፡

ይህን በአቶ ተስፋዬ ህይወት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጽሁፍ እንድንሰራ ታላቅ የሞራል የሀሳብ ደጋፍ ያደረጉልንን  3 ሰዎች ማመስገን እንፈልጋለን፡፡

 1ኛ ቤተልሄም ገድሉ

  2ኛ ኢየሩሳሌም ገድሉ

   3ኛ እጅግአየሁ ደምሴ

 

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች