28. እሸቱ ገለቱ ወልዴ እና የሙያ ህይወቱ
እሸቱ እና ያዳመጠው የነፍስ ጥሪው
“አንተ የነካኸው ነገር
ሁሉ እሳት እየሆነ ተቸግሬያለሁ _ እስኪ ሰሞኑን ቢሮ አርፈህ ቁጭ በል!” ብለውት ነበር አለቃው፡፡ የዚህ ባለታሪክ በሳል ዘገቦች
የአስተዳደሮችን ብልሹ አሰራርና ደካማ የህዝብ አገልግሎት አሰጣጥን እያሰሰ ለማጋለጥ የግንባር ስጋ ለመሆን ወደኋላ አለማለቱን ቢወዱለትም
አለቃው የጥቃት ኢላማ እንዳይሆንም እረፍት ሰጥተውት ‘እስኪ ትንሽ ዞር በል!’ ብለው የተቆረቆሩለትም ጊዜ አለ፡፡ እኚህን አለቃ
ይህ ሙያተኛ እንደሚሞግታቸው ያዩ ባልደረቦቹ ደግሞ በተመሳሳይ መዋቀስ ውስጥ ሲገቡ በንዴት እንዲህ አሏቸው _ “ከእሱ ተከራካሪነቱን
ብቻ ሳይሆን በየትኛውም አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ስራውን የማያጓድል ታታሪነቱንም አብራችሁ ኮፒ ብታደርጉ ይበጃችኋል”፡፡ ይህ ባለሙያ
ቀሪ ህይወቱን ልቡ የወደደውን ለመስራት ወስኖ ለአመታት ከቆየበት አለም አቀፍ ድርጅት ሲለቅ አንድ ወዳጁ እንዲህ አለው “ አፈር
ነህና ወደ አፈር ትመለሳለህ ”፡፡ ይህ አስተያየት ጋዜጠኝነት የሚያደኸይ የሙያ መደብ ተደርጎ ከሚሰነዘር ምሬት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡
ይሁንና ባለሙያው ግን
በህይወት የመኖሩ ትርጉም የሚሰጠው ጋዜጠኝነት ነው፡፡ ይህን እንደ ነፍሱ የሚወደውን የብዙሀን መገናኛ ስራን እንደ አልፊ ስራ ሳይሆን
መንፈሱን የሚያረካበት የሚያዝናናው ጉዳይ አድርጎም ይቆጥረዋል፡፡ ስለዚህም ሙያው ቀንም ሆነ ምሽት ሌሊቱን ሁሉ አውሎ ቢያስነጋው
የእጁን ሳይጨርስ እንቅልፍም ሆነ እረፍት አያሰኘውም፡፡ ምኞት አይከለከልምና ድጋሚ የመወለድ እድልን ቢያገኝም እንኳ ሙያውን ጋዜጠኛ
አድርጎ መመለስን ይሻል፡፡ የኢትዮጵያን የጋዜጠኝነት ስራ ቀይዶ የያዘው በእሸቱ ገለቱ እምነት መሰረት ከብዙ በጥቂቱ የፖለቲካ አስተዳደራዊ
ጣልቃ ገብነት (Political interference) እና የተዛነፈ የንግድ ፍላጎት (Twisted commercial
interest) የተጫነው የሙያ ነፃነት (Independence) ማጣት ፣ ጋዜጠኛው ከራሱም ያልተገቡ ተፅዕኖዎች ያልተላቀቀ የሙያ
ብቃት (Professionalism) ውሱንነት እና ባወቁትና ባዳበሩት ልምድም ልክ ለህብረተሰብ ፍላጎት በፅናት የመቆም
(Conviction) ድክመቶች ናቸው፡፡
እሸቱ እና አስተዳደጉ
ሁለተኛውን የአለም ጦርነት
ተከትሎ በጃፓን ፋሺስት ጦር ያኔ ደች ኢንዲስ ከምትባለው ከዛሬዋ ኢንዶኔዥያ የሆላንዱ ኤች.ቪ.ኤ ኩባንያ ሲባረር ነቅሎ ይዞ የወጣውን
የስኳር ፋብሪካ ማሽንን በተከለበት የአዋሽ ወንዝ ተጠምጥሞባት መቀነት ሰርቶ በሚናኝባት ወንጂ ላይ ይህ ሰው ተወልዶ አድጎባታል፡፡
በዚህች የኢንዱስትሪ ባህል ልምዷ ለሀገርም እንዲተርፍ ሆና በ1946 ዓ.ም የፋብሪካ ላንቃ በተከፈተላት የምስራቅ ሸዋዋ የኢንዱስትሪ
ዝማኔ ፈርጥ በሆነችው ወንጂ ሚያዝያ 9 / 1964 ዓ.ም በወንጂ ሆስፒታል ሰራተኛ ለነበሩት ለአቶ ገለቱ ወልዴ እና በአካባቢው
የቤተሰብ ገቢን በሚደጉሙ አነስተኛ የቢዝነስ ፈጣሪነት ለሚታወቁት ወ/ሮ አሰገደች ጥላሁን ቤት 3ኛ ልጅና የመጀመሪያ ወንድ ልጅ
የሆነው እሸቱ ይህችን አለም ተቀላቀለ፡፡
በትምህርት አቀባበል
ጉብዝናው የደረጃ ተማሪ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ኋላ ላይ ለታናሽ ወንድሙ አደፍርስ ገለቱ እንጀራ ሆነው እንጂ በልጅነቱ ኳስ የያዘ የእምቦቆቅላ
ልጅ ስዕልን ጨምሮ የእሱ ስነ ጥበብ አሻራዎች የጎረቤቶችን ሳሎን ግድግዳዎች አድምቀው አልፈዋል፡፡ ስድስት ልጆች ባሉበት ፍቅር
በሞላበትና ማህበራዊ ቅርርብ በደመቀበት ቤተሰብ ውስጥ በተዋህዶ ኦርቶዶክሳዊ እምነት ማደጉና የእግር ኳስ መውደዱ ከልብ ስለነበር
ሁለቱን ዝንባሌ አዋዶ በአበባ አሸብርቋቸው አማልክቱንም ሆነ እነ አፄ ቴዎድሮስንና ቦብ ማርሌን ጨምሮ ኳስ ሲመቱ ስሎ ለእንቁጣጣሽ
አዲስ አመት ስጦታ ማደሉን በልጅነት የሚያውቁት ጎረቤቶች ዛሬም በአግራሞት የሚያወሱት ነው፡፡
ወንጂ ውስጥ በያኔው
ዘመን አመዳደብ በአብዛኛው ከሀገር ቤት ቡድን ቡና ክለብ እንዲሁም ከውጭዎቹ ደግሞ ብራዚል እና አርጀንቲና ብሎም ከአውሮፓ ክለቦች
ደግሞ አያክስ አምስተርዳም እና አርሴናል ይወደዱ እንደነበር የሚያስታውሰው እሸቱ እምቦቆቅላ ልጅ ሳለ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን
የውጭ ውድድር ሲኖረው ለዝግጅት ወንጂ ስታዲየም ላይ ሲለማመድ ውሎ ለአዳር አዳማ ራስ ስለሚያርፍና የ9ኙ ኢንዱስትሪ ውድድርም በክረምት
ወንጂ ይስተናገድ ስለነበር ቀኑን ሙሉ ምሳ ሳይበሉ ኳስ ሜዳ ሲጫወቱ መዋልና ለስፖርተኞች መታጠቢያ ሻወር ቤት አሳይቶ የገንዘብ
መያዣ ላስቲክ ስጦታ በመቀበል ማሳለፍ እሸቱን ከሚያስቀጡት ምክንያቶች ዋነኛው ነበር፡፡ በዚያን ጊዜዋ ወንጂ ተማሪዎች ደጅ ሲዞሩ በመምህራን መታየት ስጋት ከማስከተሉ ባሻገር ቤተሰብም
ሆነ ቤተዘመድ ጭምር ኳስና ፊልም ላይ ማተኮር ትምህርትን ያሰንፋል የሚል ድምዳሜ ስለነበር ከዕለታት በአንዱ ቀን 7ኛ ክፍል ሳለ
በ2ኛ ሴሚስተር ፈተና ሰሞን የየአካባቢው ቡድኖች ሻምፒዮና የዋንጫ ግጥሚያ በነበረበት ወቅት እሸቱ የአጥቂ መስመር ላይ እየተጫወተ
ግብ ባስቆጠረበት አፍታ ተረግጦ ወድቆ በመጎዳቱ ለአንድ ወር ሆስፒታል ተኝቶ ለመታከም በመገደዱ ፈተናውን የወሰደው ሆስፒታል ውስጥ
ሳለ ነበር፡፡ በፈተናው ጭራሽ የክፍሉ ቀዳሚ ውጤትን ቢያገኝም እሸቱ ግን ከዚህ አጋጣሚ ወዲያ ኳስን እርም ብሎ ሚናውን ከተጫዋችነት
ወደ ተመልካችነት ቀይሮ የሙሉ ጊዜ ትኩረቱን ወደ ትምህርቱ አዞረ፡፡፡
ከዕለታት በአንዱ ቀን
እሸቱ በተለምዶ ‘ጨቡድ’ በሚባለው ት/ቤት የ9ኛ (A) ክፍል ተማሪ ሳለ የእንግሊዝኛ መምህሩ ቲቸር አባይነህ ምን መሆን ትሻላችሁ
(What do you like to be?) ብለው ሲጠይቁ ብዙዎቹ ሀኪም ፣ አውሮፕላን አብራሪና መሀንዲስ በማለት በታዳጊዎች የተለመዱትን
ምኞቶች ሲያነሱ “ I would like to be a reporter ” ወይም ዘጋቢ መሆን እሻለሁ የሚለው የእሸቱ ምላሽ ግን መምህሩን
ጨምሮ አብዛኞቹ የክፍሉ ተማሪዎች ዛሬም አይረሱትም፡፡
እሸቱ ገና ከታዳጊነቱ
አንስቶ ከመደበኛ ትምህርት በተጓዳኝ በአማርኛና እንግሊዝኛ የሚዘጋጁ ዘገቦችን እየተከታተለ የሚያነብ እንዲሁም በስነ ጽሁፋዊ ልብ
ወለዶችና ግጥሞች እጅግ ይመሰጥ ስለነበር እጅግ ብዙ መጽሀፍትን የማንበብ ዝንባሌንም ስላዳበረ ከልጅነት አንስቶ ካነበባቸው መጽሀፍት
አሰባስቦ በማስታወሻ የሰነዳቸው ምርጥ ገለፃዎችና ጥቅሶች ዛሬም ድረስ ለስራው ይገለገልባቸዋል፡፡
እንደ ገጠሩ የምሽት
የእሳት ዳር ጨዋታ አይነት ቤተሰብ ምሽት በሚሰባሰብበት የአብሮነት ጊዜያት በሞቀ ጨዋታ መሀል የሬዲዮው ዜና ደርሶ ሲነበብ “ እሽሽሽ ልጆች አንዴ ዝም በሉ! _ ዜና እኮ አደጋ ተከስቶ በዚያ
ጋ ሽሹ እንኳ የሚል መረጃ ቢጠቁም ካላዳመጥነው ለችግር ልንጋለጥ አይደል!“ በሚል በተደጋጋሚ አባቱ አቶ ገለቱ ወልዴ የዜናን ፋይዳ
አበክረው የሚያሳስቡትን እሸቱ አይዘነጋውም፡፡ አባቱ ከልጅ አስተዳደግ ጋር የሚናገሩትንና ማታ ላይ ልጆች ተገላልጠው በርዷቸው ከሆነም
ቃኘት የማድረጉን ልምድ እሱም ቀጥሎበታል፡፡ ልጅን መምታት በአባቱ ዘንድ የማይታሰብ ከመሆኑም በላይ “ጠዋት ልጆችን መቆጣት ፈሪና
ደንዛዛ ያደርጋል ፤ ምሽት ላይ መቆጣት ደግሞ ቅዠት ይለቃል” የሚል አባባል ስለነበራቸው በቤት ውስጥ ስነ ስርአትን በመቆጣጠርና
በመቅጣት ረገድ እናት ወ/ሮ አሰገደች ጥብቅ ስለነበሩ ልጆች እንዳይመቱ አባት ስለሚያሳስቡ እንደ የተባበሩት መንግስታት ሰላም አስከባሪ
ይቆጠሩ ነበር፡፡ እሸቱ በጮርቃነት እድሜው አጥፍቶ እናት አሰገደች ሊገርፉት ሲሉ “አንቺ እማማዬ አሁንስ ሮናልድ ሬገንን ሆንሽ
” ያላቸውን ከዛሬ ጋዜጠኝነቱ ጋር በማያያዝ እናቱ ያስታውሱታል፡፡
እሸቱና እናቱ ወ/ሮ
አሰገደች ጥላሁን በቀንና በማታ ፈረቃ ልዩነት እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ አብረው ስለተማሩ በጋራ በማጥናት መቀራረብ ከመኖሩ በላይ
ወንጂ ገበያ የሚቆመው ቅዳሜ ዕለት ስለነበር እናትን አጅቦ ዘንቢል ይዞ መከተል ገበያው ሲጠናቀቅ በአዘቦት ቀን ክልክል የሆኑት
ጮርናቄና ሳምቡሳን ጨምሮ ኮካኮላ መጋበዝ ስለሚኖር ለገበያ በአጃቢነት መታጨት ለትልቅ ሀላፊነት የመመረጥ ያህል ስለሚቆጠር ልጆች
በጣም የሚፎካከሩበት ጉዳይ ነበር፡፡
እሸቱ በብላቴ አየር
ወለድ ወታደራዊ ካምፕና በኬንያ
በዚህኛው የእሸቱ ህይወት
ምዕራፍ ብዕር ተሰቅሎ ቀረና በውጋ - ንቀል - ወድር ተተካ፡፡
“አርቀን እንዳልገመትንሽ፣
በዓይነ ህሊና አሻግረን
፣ አዲስ ላይ እንዳልቃዥንሽ፣
ልባችን እንዳልነጠረ
፣ ደማችን እንዳልናረልሽ፣
አየንሽ!
እንደ ሕልማችን ፈታንሽ፣
ብላቴ አቤት ሚስጥርሽ፡፡”
“ላብ ደምን ያድናል”
የምትል ታላቅ አባባልን እሸቱ የሰማው በዚህ ወታደራዊ ካምፕ ነው፡፡ ይህን የሚሉት የአየር ወለድ ወታደራዊ አሰልጣኞቹ ተማሪው ስልጠናውን
በአንክሮ እንዲከታተለው ለማሳሰብ ሲሆን በስልጠና የተፈተነ ከጦር አውዱ ሲገባ ራሱን ተከላክሎ የመዋጋት ክህሎትን ስለሚያዳብር አላግባብ
ለሆነ የህይወት ዋጋ ክፍያ እንደማይጋለጥም አብረው ያስጠነቅቁ ነበር፡፡
ከኢትዮጵያ መላ ክፍሎች
በ1983 ዓ.ም የዩኒቨርስቲ እና ኮሌጆች ተማሪዎች ወደ ብላቴ አየር ወለድ ማሰልጠኛ ካምፕ በተመሙበት ወቅት እሸቱ በአዲስ አበባ
ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ካምፓስ የ3ኛ አመት ተማሪ ነበርና ‘ሆ’ ብሎ ከገቡት ተማሪዎች አንዱ ነበር፡፡ በፎለን ሜዳ ማልዶ ወጥቶ
ወታደራዊ ሰውነትን የማነቃቃት ስፖርት _ በወንዝ ዳርና ዳር በተወጠረ ካቦ ላይ ተንጠላጥሎ ከማለፍና በዱር በገደል አልፎ ራስን ከአውዱ አመሳስሎ በብልሀት ተሰውሮ መረጃን
ከማሳለፍ ልምምድ አንስቶ ኢላማ ተኩስና በፈንጂ የታጠረን የጠላት ምሽግ ወረዳን ጠርምሶ በሳንጃ እስከመሞሻለቅ የሚሻገረው የጨበጣ
ውጊያ ድረስ የመግባት የኢንፊልትሬሽን ወታደራዊ ስልትን ጭምር አጠናቆ መመረቅ በሚጠበቅበት ወቅት በአንደኛው ቀን ግንቦት 13
/ 1983 ዓ.ም እንዲህ ሆነ፡፡
በወቅቱ የሀገሪቱ መሪ
ኮሎኔል መንግስቱ ኃ/ማርያም ብላቴን ይጎበኛሉ ተብሎ ቀይ ምንጣፍ ተነጥፎና የህብረ ሰላምታ ሰጪ ኮማንዶ ወታደሮች በተጠንቀቅ ቆመው
ሳለ አንዲት አውሮፕላን ዝቅ ብላ በርራ ሽምጥ ወደላይ ተወናጭፋ በረረች፡፡ ከአሁን አሁን መጡ ተብሎ ሲጠበቅ ወደማደሪያ ኬዝፓን
የሄዱ ተማሪ ወታደሮች የ6 ሰአት ዜና ሰምተው ‘ኮሎኔሉ ለሀገር ሰላም ሲባል ከሀገር እንዲወጡ ተደርጓል’ የሚለው መረጃ እኩለ ቀን
ላይ በኢትዮጵያ ሬዲዮ መተላለፉን ተከትሎ በብላቴ አየር ወለድ ወታደራዊ ካምፕ በሰራዊቱ ዘንድ የነበረው ሀዘንና ተማሪውም ግራ የተጋባበት
ሁኔታ ዛሬም ድረስ በእሸቱ ህሊና ውስጥ ሀገርና ህዝብ ለእድል የተተወበት አስጊ ገጠመኝ ሆኖ ላያልፍ አልፏል፡፡ እሸቱ በብላቴ ቆይታው
ሀገር ተማሪን ሁሉ ስላሯሯጠው ወረርሽኝ በመስፍን አሸብር ግጥም እንዲህ ያስታውሰዋል፡፡
“ ገብተህ የተገኘህ፣
ከዚህች ከብላቴ
በላ ልበልሃ ፣ ተጠየቅ
ሸርተቴ!
ሸርተቴ ሸበላው፣ ሸርተቴ
ፈጣኑ
ኩሩ ዘለግላጋው፣ ሸርተቴ
ጅንኑ
ኩልል እንደ ውሃ፣ ፍስስ
እንደ ዥረት
ቀጭን ኩታ መሳይ _
አረንጓዴ ቢጫ ፣ ባለቀይ ጥለት። ”
ተማሪውን ከካምፑ ለማውጣት
አንቶኖቭ አውሮፕላንም ሆነ አውቶቡሶች ቢላኩም ተባራሪ ተኩሶች አየሩን ሞልተውና ሜዳ ሙሉ ትርምስ በመፈጠሩ ጉዞ ወዴት እንደሆነ
ባልታወቀበት ሁኔታ አብዛኛው ወደ አዋሳ _ ቀሪዎቹ ደግሞ ወደኬንያ በሚል ሰው እግሩ በመራው ቢተምም ከጉጂ መንደሮች አንስቶ እስከ
ኬንያ ባሉት ርቀቶች ውስጥ በቀስት በመወጋት _ በመኪና አደጋና በወንዝ በመወሰድ ጥቂት የማይባሉ የየኮሌጁ ተማሪዎች በህይወት ማለፋቸው
እሸቱን ዛሬም ድረስ ያስቆዝመዋል፡፡
ከብላቴ ሞርቾ - ዲላ
- ሀገረማርያምን ተሻግሮ - ህብረተሰቡም በየመንገዱ ምግብ ለተማሪው እያቀረበ በአውቶቡሶች በኮንቮይ በተደረገው የ3 ቀናት የጭንቅ
ጉዞ የወገን በክፉ ጊዜ ደራሽነትን አሳይቶታል፡፡ ተማሪው ኬንያ ሞያሌ ደርሶ እሸቱም መዳረሻውን በኬንያ ዋልዳ ስደተኞች ካምፕ አደረገ፡፡
የዚያን ወቅት ፕሬዚደንት ዳንኤል አራፕ ሞይ ተማሪዎችን ተቀብለው “Kenya is your second home - ኬንያ ሁለተኛዋ
ቤታችሁ ናት” ያሉትንና የበቆሎ ገንፎና ውሀ በነዳጅ ቦቴ መጥቶ በሽሚያ በኮዳ የቀዱበትን አስመራሪ ሁኔታ ባለታሪኩ አይዘነጋውም፡፡
የቤተሰብ ናፍቆትና የተቋረጠው ትምህርቱ አሳስቦት በ4ኛ ወሩ ወደ ኢትዮጵያ በተመለሰበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን በብላቴው ግርግር ወቅትም
ጭምር አንድም የሚያውቀው ሰው ስላላየው ከኮሌጆች መጥተዋል በተባሉ ተማሪዎች ቤቶችም ዞረው ጠይቀው ተስፋቸው ተሟጦ በነበሩት ወላጆቹ
ዘንድ ሳይሞት አይቀርም የሚል ግምት አድሮ ስለነበር የራስ ፀጉሩንና ፂሙን ጭምር አጎፍሮና አንጨፋሮ ወደ ትውልድ ቀዬው እሸቱ በሰላም
መመለሱ በቤተሰቦቹ ዘንድ አይንን አለማመንና እያነቡ እስክስታ አይነት የተቀላቀለ ስሜት ፈጥሮ ነበር፡፡
በዩኒቨርስቲ ተማሪ ሳለ
ጭምር ዶሮ ሰርተው በአገልግል ይዘው ልጃቸውን ዘወትር ከወንጂ አዲስ አበባ ስድስት ኪሎ ተመላልሰው በስስት ከሚጎበኙት ከእናቱ ጋር
ጥብቅ ቁርኝት ያለው እሸቱ በአምልኮ እድገቱ ከወንጂ አቡነ ተ/ሀይማኖት ተዋህዶአዊ ኦርቶዶክስ መንፈሳዊ ጥምቀቱ አንስቶ ከቤተዘመዶች
ጋር በመሆን በናዝሬት ቅ/ማርያምና በቅ/ገብርኤል ከሚታደምባቸው የንግስ በአላት ባሻገር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ቆይታው መሬት
ይቅለላቸውና በአቡነ ጎርጎሪዮስ ድጋፍ ጭምር በ6 ኪሎ መስኪያህዙናን መድሀኒያለም የነበረውን የአምልኮ ስርአትን እንዲሁም የስራ
ውድድር ማስታወቂያ ሚኒስቴር አልፎ ምድብ በእጣ ሊሆን ባለበት ዋዜማ
አምስት ኪሎ ቅ/ማርያም ያደረሳት ፀሎትና ልመናውን ፈጣሪ ሰምቶ ኢትዮጵያ ሬዲዮ የተመደበበትን አጋጣሚ በሀሴት ያስታውሰዋል፡፡ በብላቴን
በተለይ በኬንያ ስደተኞች ካምፕ ቆይታው መንፈሳዊ መሰረቱን ለማፅናት ተጨማሪ ድርሻ እንዳለው የሚጠቅሰው እሸቱ በሸራው ድንኳን ውስጥ
ቅ/ሚካኤል ይከብር እንደነበር ሲያስታውስ ይህ ሁነት በራሱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶው ማህበረ ቅዱሳን እንዲመሰረት በጎ አስተዋጽኦ አበርክቷል
ብሎ ያምናል፡፡
ከብላቴ ወታደራዊ ስልጠናና
ከኬንያ የስደት ህይወት ጋር በተያያዘ ውሀ ጥም ፣ ማረፊያ መጠለያ ከማጣት ያለፈ ሀገሬ ብሎ ደረት ነፍቶ መናገር የማይቻልበት የቁልቁለት
ጉዞ ፈተና ሰው እንደሚገጥመውና በትዕግስትና ፅናት ግን ሊታለፍ እንደሚችል ትምህርት የሰጠው ታላቅ አይረሴ አጋጣሚ አድርጎ እሸቱ
ይወስደዋል፡፡ እንደውም እሸቱ የብላቴ ዘመቻ ገጠመኝን በአንድ ወቅት ከነበረው ተማሪዎች 12ኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ የመሰረተ ትምህርትን
ለማስፋፋት በየገጠሩ የሚመደቡበትን እንዲሁም ሌላው ዋነኛው ደግሞ የአንድ ወቅቶቹ የየኮሌጁ ተማሪዎች ወደየገጠሩ ከተመሙበት የእድገት
በህብረት ዘመቻ ጋር በማያያዝ እንዲህ አይነት በወጣቶች ላይ ያተኮረ ህብረተሰባዊ ንቅናቄ ታዳጊዎች ወደህብረተሰቡ ቀዬ ዘልቀው መልከ
ብዙ ሀገራቸውን ከማወቅ ባሻገር የወገናቸውን አኗኗር ፣ ባህል ፣ ቋንቋ ፣ እሴትና ወግ በመገንዘብ ከሰው ጋር ተቀራርቦና ተከባብሮ
ለጋራ ህልም አብሮ የመስራትን የማህበራዊ ህይወት ክህሎት ልምድን የሚያዳብሩበት አጋጣሚን የሚፈጥር ከመሆኑ አኳያ ዛሬም ይህን ልምድ
ማስፋፋት ማህበራዊ ሽንቁራችንን ለመድፈን የራሱ ሚና እንደሚኖረው ይህ ባለታሪክ ያምናል፡፡
የእሸቱ የትምህርት ዝግጅቱና አለም አቀፍ አገልግሎቱ
ይህ ብቻ አይደለም የመጀመሪያ
ዲግሪ ትምህርቱን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በውጭ ቋንቋዎች - ስነ ጽሁፍና በተግባቦት (Foreign Languages -
Literature & Communication) መመረቁን ተከትሎ በአዲስ አበባ ከፍተኛ 2ኛ አጠቃይ ት/ቤት መምህር
(English Teacher) ሆኖ ስራ ከጀመረበት አንስቶ በጋዜጠኝነት (Journalist) - በተግባቦት ከፍተኛ ባለሙያነት
(Communication Specialist) እና በስነ ጽሁፍ አርታኢነት
(Literature & Arts critic) ሰርቷል፡፡ የድህረ ምረቃን በተመለከተ በአውሮፓ ጀርመን ዶቼቬሌ አካዳሚ በከፍተኛ
የጋዜጠኝነት ትምህርት (Advanced Journalism) እና በደቡብ አፍሪካ በተከታታይ የጤና ማበልፀግ (Health
Promotion) እና በእመርታዊ የአመራር መስክ (Transformational Leadership) ትምህርት መውሰዱን ተከትሎ በህብረተሰብ
ጤና ማበልፀግ ከፍተኛ አማካሪነት (Public Health promotion advisor) እያገለገለ ይገኛል፡፡
እንዲሁም በህይወት ክህሎት
አሰልጣኝነት (Life skills Trainer) - በስልጠና እና ምርምር ተኮር የብዙሀን መገናኛና የተግባቦት ዘርፍ ከፍተኛ አማካሪ
(Training & research focused media and communication senior consultant) - የስራ
ፈጠራም ባለሙያ (Business Entrepreneur) እና የበጎ ፍቃድ አገልጋይ ሆኖ እየሰራ ነው፡፡
እሸቱ ገለቱ ለአጫጭር
ጊዜ ካገለገለባቸው የኮንትራት ስራዎች ውጪ በአንፃሩ በስፋት ከሰራባቸው መ/ቤቶች መካከል ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉት ናቸው
• በእንግሊዝኛ ስነ
ጽሁፍና ተግባቦት የዲግሪ ተመራቂ ከሆነበት አመት አንስቶ ለ6 ወራት እስከ 1985 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ የአጠቃላይ
2ኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት (English Teacher)
• ከ1985 ዓ.ም አንስቶ
ለ11 አመት ያህል በዛሬው የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን _ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ከሪፖርተርነት እስከ ዜናና ወቅታዊ ጉዳዮች ማዕከል
ዳይሬክተርነት (from Reporter position up to Director of News and Current Affairs
Center)
• ከሌሎች ስራዎች ጋር
በትይዩ ከ1994 አንስቶ እስከ 2011 ዓ.ም ድረስ የእሸት ሚዲያና አድቨርታይዝመንት ፕሮሞሽን (EMAAP) በሚዲያና ኮምዩኒኬሽንስ
ከፍተኛ አማካሪነትና ተባባሪ ዋና ስራ አስኪያጅነት (Consultant & Associate Manager)
• በበጎ ፈቃደኝነት
ከ1995 አንስቶ ኋላ ላይ የላምባዲና የጤና ኮምዩኒኬሽንስ እና ልማት (Lambadina Institute of Health
Communications & Development) በሚል ቀድሞ EVAMPA የነበረውና መልሶ የተቋቋመው የሚዲያ ባለሙያዎች በመሰረቱት
መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ውስጥ የማህበሩ ሊቀ መንበር እና ከ1997 አንስቶ ለ3 አመታት እስከ 50 ሺህ ቅጂ በእንግሊዝኛና አማርኛ
የሚታተመው ጤና ልማትና ወጣትነትን ማበልፀግ ላይ በሚያተኩረው የላምባዲና ጋዜጣ በም/ዋና አዘጋጅነትና በሚዲያ አማካሪነት
• ከ1997 ጨረሻ ገደማ
አንስቶ ለ4 ወራት በኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት (Ethiopian Postan Service) በህዝብ ግንኙነትና ኮምዩኒኬሽን ስራ
አስኪያጅነት (PR & Communication Manager)
• ከ1998 ዓ.ም መግቢያ
አንስቶ ለ7 አመታት የእንግሊዙ አለም አቀፍ የዜና አውታር (BBC World Service Trust) የምስራቅ አፍሪካው ክንፍ አገልግሎት
በሚዲያ ፕሮግራም ይዘትና ቅንብር አማካሪነትና እና ከፍተኛ ፕሮዲዩሰርነት (Senior Consulting Producer)
• ከ2005 አንስቶ
ደግሞ ለ8 አመታት ዋና መስሪያ ቤቱን በሰሜን አሜሪካ ጆርጂያ አትላንታ አድርጎ በጤና ልማት ላይ የሚሰራው እንዲሁም የአፍሪካ ጽ/ቤቱ
አዲስ አበባ በሆነው የቲ-ኤፍ ግሎባል ሄልዝ (በTF Global Health) የሚዲያ _ ኮምዩኒኬሽንና የአጋርነት ልማት ከፍተኛ
አስተባባሪ (Senior Coordinator of Media, Communication & Partnership
development)
• ከሚያዝያ 2009
ዓ.ም አንስቶ እስካሁንም የኢትዮ ስኳር ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ አክሲዮን ኩባንያ መስራች እና ከፍተኛ የኮርፖሬት ኮምዩኒኬሽን
አማካሪ
• ከ2011 ዓ.ም አንስቶ
በ105 ሙያተኞች የተመሰረተው የዋርካ መልቲ ሚዲያና ኮምዩኒኬሽን አክሲዮን ኩባንያ (Ethio Warka Multimedia and
Communication S.C.) ዋና ሀሳብ አመንጪ መስራች እና የኩባንያው ዋና ስራ አስኪያጅ ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡
የእሸቱ የጋዜጠኝነት
ዝንባሌና የወላጆቹ የህይወት ፍልስፍና
እሸቱ በአዲስ አበባ
_ አዲስ ከተማ በከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት በእንግሊዝኛ መምህርነት ጀምሮት የነበረውን ስራ ቢወደውም እጅግ አብልጦ የሚመኘውን
ጋዜጠኝነት በውድድርና በእጣ ድልድል ኢትዮጵያ ሬዲዮ እንደደረሰው በታወቀ ዕለት ወዳጆቹ በደስታ ወደላይ ተሸክመውት የጨፈሩትን አይረሳውም፡፡
ይሁንና ድርብብ ያለ የፀጥታ ህይወት ምርጫቸው የሆነው አባቱ አቶ ገለቱ ግን የስራው ሁኔታ አደባባይ አውጥቶ “ገና ከጅምሩ የእሸቱ
አባት _ የእሸቱ አባት” እያስባለ በየመንገዱ ጭምር የሰው መነጋገሪያ ያደረጋቸውን ጉዳይ አልወደዱለትም፡፡ ለዘገባ በፓርላማና ቤተ
መንግስት ውሎህ መዘዝ እናትህ ቢቸግራት እንኳ የሚያምናት የለምና ይሄ ብድር ከልክል ስራህን መቀየር ከቻልክ ከጎደፈው ለሀገር ጠላት
ከሆነው የፖለቲካ ቁማር ሰፈርም መራቅ ነውና ብታስብበት እያሉ በተደጋጋሚ ያነሱበት ነበርና እሸቱ በግንቦት 1997 ዓ.ም ዋዜማ
በውጪ አካላት ዛቻና የእስር ሙከራዎች እንዲሁም በሬዲዮ ጣቢያውም የሙያ ነፃነትን ጭራሽ የሚጫኑ ያልተገቡ አሰራሮች መንገሳቸውን
ተከትሎ በገዛ ፍቃዱ ስራ የለቀቀበትን ውሳኔ አባቱ የተቀበሉት በደስታ ነበር፡፡ እሸቱ ከአባቱ አባባሎች መካከል “ሰውን ያከበረና
ልቡን ስራ ላይ ያሳረፈ ሰው የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ስኬታማ ይሆናል” የሚለውን አለመርሳት ብቻ ሳይሆን አቶ ገለቱ ልጆቻቸውን
ሲመርቁ ከማያልፉት ጉዳይ መካከል “ልጆቼ የሰው መውደድ ይስጣችሁ _ ሰው የወደደው አምላክ የወደደው ነውና” የሚለው ይገኝበታል፡፡
ከእናቱ ወ/ሮ አሰገደች
ጥላሁን የማይዘነጋው ምክር ደግሞ “የእኔ እሸት ልጄ አደራህን የዱቤ ምግብና ልብስ እንዳትሞክር!” የምትለዋን ስለነበር በኢትዮጵያ
ሬዲዮ ጅማሮ አመቱ ብዙዎች የሚነከሩበትን ሞዴል 6 የሚባለውን ከቀጣዩ ደመወዝ ስቦ በብድር መኖርን ሳይሞክረው አልፏል፡፡ የዘመነ
ኢህአፓ አፍሮ ፀጉር አበጣጠርን እናቱ በልዩ ሁኔታ ሳያዩት እንደማይቀር የሚገምተው እሸቱ በልጅነቱ ፀጉሩን እንዲያጎፍር መሻታቸው
ብቻ ሳይሆን እያጠቡና እያበጠሩ የሚንከባከቡለት እናቱ በማህበራዊ ተግባቦት እጅግ ሰው ከዳር እዳር የሚያውቃቸው በእድርም እቁብ
ሰንበቴና ፅዋ ማህበርም ጭምር ሰፊ ትስስር ያላቸው ብቻ ሳይሆን በቤት እመቤትነት ሳይወሰኑ ልጆቼ ምንም ሳያጥራቸው ማደግ አለባቸው
በሚል ቁርጠኝነታቸው የባለቤቴን እጅ ብቻ አልጠብቅም ብለው በተለያየ ጊዜ የተለያዩ የንግድ አይነቶችን በመሞከር ለታዳጊው እሸቱ
ማህበራዊ ትስስርን በተግባር ስለማጠናከርና የቢዝነስ ስራን ፈጥሮ ገቢን ስለማሻሻል ክህሎት በተግባር ያሳዩት ልበ ብርሀን የህይወት
መምህሩ እንደሆኑ እሸቱ ይሰማዋል፡፡
እናት አሰገደች የቱንም
ያህል እጅግ በጣም ተግባቢ መሆናቸውን ተከትሎ ማህበራዊ ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ ሲሆን ለፈተናም ሆነ ያልተገባ የመታበይ ተፅጽዕኖ
ሲገጥማቸውም የእጅ አልሰጥም እልሃቸው ታዳጊው እሸቱ ከእናቱ የወረሳት ናትና ዛሬ ድረስ በቁም ነገርና ጨዋታው የሚያውቁት ሰዎች
በስራ ሂደት ያልተገባ የመሰለውን መስመር የሳተ ነገርን በልበ ሙሉነት የመጋፈጥ እና ከሙያዊ ሚዛናዊነት የወጣ ተጽዕኖ ከአመራር
አካላት ሲገጥመው በእልህ መሟገትና እስከመጨረሻው ስለሚፋለም ወዳጆቹ ‘ይህኛውን እሸቱ እባክህ ከሌላ ቦታ አቆየው’ የሚል ሀሳብ
በሰነዘሩ ቁጥር የእናቱ ልጅ መሆኑን ያስታውሱታል፡፡
በታዳጊነቱ እናቱ በእልህ
ሲናገሩ የእሱ አባት አቶ ገለቱ ደግሞ በምላሻቸው ‘በይ አሰገድ ብቻሽን ጦርነት ይወጣልሽ ከሆነ ይኸው ቤቱን ለቅቄ ሄጃለሁ - ቆየት
ብዬ እመለሳለሁ’ የሚሉት ነገር ምን ያህል እሳት ሊሆን የቃጣውን ውዝግብ ውሀ ያደርገው እንደነበር በታዳጊነቱ የተረዳው እሸቱ ዛሬም
ድረስ የአባቱ ብልህነት የተሞላውን ነገር የማብረድ ዘዴን ተጠቅሞ በቤትም ሆነ ሌላ ቦታ ጭቅጭቅ ሲነሳ በተቻለ መጠን ስሜት በነደደበት
ወቅት ከመመላለስና ሰውን ከማስቀየም ይልቅ ለጊዜውም ከስፍራው መራቅን የህይወት ዘይቤው አድርጎት ከእናቱ የወሰደውን በማረቅ አጣጥሞ
በአባቱ መንገድ ይኖራል፡፡
እሸቱ እና የፍቅር ትዳር
ህይወቱ
ሙያውና የቤተሰቡ ፍቅር
አንዳቸው ከሌላቸው የሚልቀውን ጊዜ ለማግኘት ሽሚያ ገጥመውበታል፡፡ ስራው ከአብዛኛው የማህበራዊ መቀራረቢያ አጋጣሚዎች ከማራቅ ባሻገር
በሌሊትና ማለዳ እንዲሁም በየሳምንቱ የመጨረሻ ቀናትና በበአላት ጭምር ቢሮ መገኘትን ግድ የሚል ሆነና የምን ይሻለኛል ጥያቄንም
አጭሮበታል፡፡ እናም በሚዛን አጣጥሞ አንዳቸውንም ቅር ሳያሰኝ ሙሉ ልቡን ሊሰጣቸው ደግሞ ይሻል፡፡
ርቆ ሄዶ ውስጥን የሚረዳና
በማስተዋል በአፍቃሪው ጫማ ውስጥ ሆኖ ነገሮችን የሚያይ ውሀ አጣጭን ማግኘት ታዲያ ሙዝ የመላጥን ያህል ቀላለ አይሆንም፡፡ የፈጣሪ
ረድኤት ሆነና መንፈሰ - ብርቱዋ ራሷ ረድኤት ተገኘች፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪ የዩኒቨርስቲ ቆይታው መጠናቀቂያ ላይ እሸቱ ከዕለታት
በአንዱ ቀን የበረሀዋ ገነት ድሬደዋ ካፈራቻት ለዩኒቨርስቲው አዲስ ገቢ ከሆነች ታዳጊ ወጣት ረድኤት ብርሀን ገ/ማርያም ጋር በአንድ
አጋጣሚ ተያዩ፡፡ በአዲስ ስራ ጀማሪና አዲስ የኮሌጅ ተማሪ መካከል የቀጠሉት መፈላለግና መጎበኛኘት በአንድ ጣራ ስር ወደ ውሀ መጣጣት
ተሸጋግሮ የኤዲተሩ (Editor) እና የኦዲተሯ (Auditor) ትዳር የሆነውን ጎጆ መሰረቱ፡፡
በእሱ ዘንድ ገና ሲያስባት
መንፈሱን የምታረጋጋ - ጎጆዬን ብሎ ወደቤተሰቡ ቀልቡን እንዲያሳርፍ በፍቅርና ትህትና የገዛችውን - ቃላት ከሚገልጻት በላይ ናት
የሚላትን ባለቤቱን የቤቴ ዘውድ ናት በሚል ያወድሳታል፡፡ መከባበርና መደጋገፍ መለያው ከሆነው ትዳርም እሸቱና ባለቤቱ በትምህርት
እና በምግባር ምሳሌ የሆኑ ከ6 አመቱ የመዋዕለ ህፃናት ተማሪ እስከ ዩኒቨርስቲ ትምህርት በሚያደርስ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ
አራት (4) ብሩህ ልጆችን ማፍራት ችለዋል፡፡ ባለሶስት ፊደላት ስያሜ ያላቸው ልጆቹ ቤተል ፣ እዮብ ፣ ናኦሚ እና አሜን ይባላሉ፡፡
የተሻለች ሀገር ለመስራት ጥሩ ቤተሰብ መሰረት መሆኑን የሚያምነው እሸቱ የጋዜጠኝነትና የተግባቦት ስራው በሀገር ውስጥም ሆነ በባህር
ማዶ ለመስክ ስራ ብዙ የሚያስወጣው በመሆኑ ሀገር የሆኑ ልጆች የሚፈጠሩበት ቤተሰባዊ ሙቀቱ የተጠበቀ ተናፋቂ ጎጆ ይኖረው ዘንድ
ከስራ ውጪ ያሉትን ጊዜያት በሙሉ ህሊናና ልቡ ሳይከፈሉ ከቤተሰብ ጋር በጨዋታና ዘመድ በመጠየቅ ያሳልፋል፡፡
ከስራው ጋር በተያያዘ
ለቤተሰብ ጊዜ ያጣበት ከ1997 ዓ.ም ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ዋዜማ ካሉት አመታት አንስቶ በዜና ዳይሬክተርነት በነበረበት ወቅት
የመንግስት እርምጃ ነው በተባለ የተበላሽ አካሄድ “አንሚ” አና “ሱናሚስ” የሚል ቅጽል የተሰጣቸው የትምህርት ዝግጅትና የሙያ ልምድ
የሌላቸውን የፖለቲካ ታማኞች በተደጋጋሚ በየሚዲያው የመሰግሰጉ ተግባር በማየሉ ከባድ ጫና ሙያው ላይ ማረፉ እያስቆጨው ሳለ ለቤተሰቡም
በቂ ጊዜ አለመስጠቱ ድርብ ጉዳት እየተሰማው መጣ፡፡ ወይ ከሙያው እርካታ አላገኝም አሊያም ለቤተሰቡ ጊዜ በማጣቱ ከሁለት ያጣ መሆኑ
እየተሰማው በመምጣቱ በተግባቢ ተጫዋችነቱ በሚያውቁት ቤተሰቡና ወዳጆቹ ጭምር ቁጡ ሆነ መባሉን ተከትሎ በተለይም የስልክ ንግግሩ
የመጠለፉና ሊታሰር የተደረገበትን ሙከራ ተከትሎ ቤተሰቦቹም ተጨናንቀው ስለነበር በገዛ ፈቃዱ ስራ መልቀቁ ዛሬም በእዝነ ትዝታው
ሰፍሮ ያለ ታሪክ ነው፡፡
እሸቱና ባለቤቱ ሀዘንንም
ሆነ ደስታን በጋራ ከጎረቤቶቻቸው ጋር በመጋራት በመልካም የእርስ በርስ የመተሳሰብና የመደጋገፍ ማህበራዊ የጉርብትና እሴት የሚኖሩ
ብሎም ከልጆቻቸው ት/ቤት ጋር ጥብቅ ቁርኝት በማበጀት የሀገር ተስፋ የሆኑ ልጆችን ለማፍራት ልጆች በትምህርትና በምግባር ብሎም
በበጎ ፍቃድ አገልግሎት ረገድ ለህብረተሰብ ራሳቸውን ቆርሰው የሚሰጡ ሀላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች ሆነው እንዲያድጉ የሚቻላቸውን ሁሉ
የሚለፉ በብዙዎችም ዘንድ በዚህ ረገድ በአብነት የሚወሱ ናቸው፡፡
እሸቱ እና ዜና ፋይል
በዜና ፋይል ክፍሉ እያንዳንዱ
ጋዜጠኛ የራሱን የአጻጻፍና የአቀራረብ ቀለምን ይዞ አጠቃላይ ህብራዊ ጣዕሙም የሲንፎኒ ኦርኬስትራ ያህል ሁሉም ከዋናው ቅኝት ጋር
በጋራ የተዋደደ እና የተሰናሰለ እንደነበር ባለታሪኩ ይመሰክራል፡፡ እሸቱ ዜና ፋይልን የተቀላቀለው የታዳጊነት ጉጉቱን በማግኘት
ደስታ እና ይህን ከባድ ሀላፊነት እንዴት እወጣው ይሆን በሚል ተስፋን ከስጋት በቀላቀለ ስሜት ነበር፡፡ በፋርስ ባህረ ሰላጤ ቀዳሚ
ጦርነት ወቅት እሸቱ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋ - ስነ ጽሁፍና ኮምዩኒኬሽን ተማሪ የነበረ ሲሆን ከዩኒቨርስቲ በፊት ባለ
ህይወቱ የትውልድ አካባቢው ሰዎች ጎበዙን ተማሪ እሸቱን የሚያውቁት በዝምተኛነቱ ነበርና በሬዲዮ ዜና የሚያቀርበው ያ ጓደኛቸው የወንጂው
ልጅ ስለመሆኑ ለማመን አዳግቷቸው ቆይቷል፡፡
በብዙ ታዳሚዎች ዘንድ
አይረሴ ሆኖ ስለቀጠለው ዜና ፋይል እሸቱ ሲናገር ከጀማሪዎቹ እስከ ነባርና አንጋፋዎቹ ድረስ ያሉትን በትውልድ ቅብብሎሽ የካበተ
እውቀትና ልምድ ባለቤቶችን አሰባስቦ ከመያዙ ባሻገር በጋዜጠኞቹ መካከል ፉክክርም በጋራ መናበብም ያለበት ሆኖ ስለዝግጅት ጥራትና
የአድማጮች እርካታ መጨነቅ ጎልቶ የሚታይበት የተግባራዊ ጋዜጠኝነት ሙያ መቅሰሚያና ማዳበሪያ አምባ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ጋዜጠኞች
እንደተቀጠሩ የሚወስዱትን ስልጠናዎችን ተከትሎ በአፈጻጸማቸው ውጤት መሰረት እንደ ችሎታቸውና የአቀራረብ ድምጻቸው ታይቶ በየዝንባሌያቸው
ሲመደቡ በእሁድ ጠዋት ፕሮግራም መስራችነቱ የምናውቀው ጋሽ ታደሰ ሙልነህ የተመራው የአሰልጣኞች ቡድን ከነበሩት መካከል እሸቱን
ወደዜና ፋይል እንዲደለደል ምክረ ሀሳብ አቀረቡ፡፡ ከአንጋፋዎቹ እነ አማረ መላኩ ጋር ለስምሪት በተከታታይ አጅቦ ወጥቶ የመረጃ
አሰባሰብን እንዲለማመድ ፣ በስቱዲዮ ደግሞ ድምጹን እንዲሞርድ እና በቢሮም በየሰአቱ በሞኒተሪንግ የሚቀረጹ የውጭ ዜናዎችን በፍጥነት
የመተርጎም ስራን ማከናወን ስለመቻሉ ሲረጋገጥ ከወራት ክትትል ወዲያ የጋዜጦች አምድ ዝግጅትን ብሎም የመስክ ስምሪትን በራሱ ወጥቶ
እንዲሸፍንና የዋና የምሽት 2 ሰአት ዜና ዝርዝርን ለማንበብ ብቁ ነው ተብሎ የተፈቀደለት ዕለት እጅግ መደሰቱን ያስታውሳል፡፡
በብዙ መልኩ እሸቱ በጋዜጠኝነት
ሙያ እንደ አብነቴ ነው ብሎ ከሚያወሳው ነጋሽ መሀመድ ክህሎት መካከል ዜና አጻጻፍና አቀራረብን የረቀቀ ጥበብ ያህል አክብሮት እስከመጨረሻዋ
የስቱዲዮ ቀረፃ ደቂቃ ድረስ ተጨንቆ የቃላት ሀብታምነቱን በሚያሳብቅ መልኩ ቃላት እየቀያየረና ንበቱን እየሞረደ በአርትኦት እያሸ
የሚዘልቅበትን ትዕግስቱን ያደንቅለታል፡፡ የባልደረባው አለምነህ ዋሴ ለስሜት ቅርብ የሆኑ ቃላትን በመጠቀም በአድማጭ ዘንድ የድምጽ
ቀለምን (Audio color) የሚያሳይ ምስል ለመከሰት የሚሄድበት ርቀትና ትልቅ አነጋጋሪ ጉዳይ ሲከሰትና የህዝብ ትኩረት አርፎበታል
ብሎ የሚገምተውን ዜና ወስዶ ቀድሞ አድማጭን በአቀራረብ ለመማረክ ታሳቢ አድርጎ የሚያሳየው እሽቅድምድም የሙያ ጉጉቱን ስለሚያመለክት ባለታሪኩ የሚወድለት ባህሪው ነው፡፡
በአጫጭር አረፍተ ነገሮቿ የዜናውን ጭብጥ ቀለል አድርጋ ልክ አጠገብ ሆና እንደ ወግ እያወራች ያህል እንዲሰማን የምታደርገው ንግስት
ሰልፉ ደግሞ ሌላዋ ልዩ የዜና ፋይል ቀለምነቷን እሸቱ በትዝታ ያወሳዋል፡፡
የክፍሉ ኃላፊ ከነበረው
ጋሽ ዳሪዎስ ሞዲ ደግሞ የውጭ ዜናዎችን ትርጉም በተለይም እጅግ ውስብስብ ለሆኑ የእንግሊዝኛ ቃላት ጭምር በገላጭ የአማርኛ አቻ
ቃላት በፍጥነት የሚተረጉምበትንና አለም በዚህ ሳምንት ሲዘጋጅም ስለቅንብሩ ውበት በመመሰጥ እሸቱ ለሚያቀርበው አቅጣጫ በመስጠት
እንዲዘጋጅ የሚያደርግበት መንገድ ስለቅንብር ምሳሌው አድርጎ ባለታሪኩ ያነሳዋል፡፡ ሌላው ዝምተኛ ጀግና ብሎ የሚያስታውሳቸው የኢትዮጵያ
ሬዲዮ ዜና ማዕከል ኃላፊ ከነበሩት አቶ ጥላሁን በላይ ደግሞ ነገሮችን ከተለያዩ አቅጣጫዎች በጥሞና የማስተዋል ልምድን ከመቅሰም
ባሻገር የመጽሀፍ ንባብ ባህልን ማዳበር እንደሚያስፈልግና በተለይ ፖለቲካዊና አለም አቀፍ ግንኙነት ላያ ያተኮሩ መጽሀፍትን ያውሱት
ስለነበር ለፕሮግራም ዝግጅት ግብአት በማከል አስተዋጿቸው የጎላ እንደነበር ባለታሪኩ ማስታወስ ይሻል፡፡
የትርጉም አቻ ቃላትንና
የቃለ ምልልስ ጥያቄዎችን ለማውጣት እርስ በርስ አየተነጋገሩ በመዋጮ ይዘቱን ለማዳበር የሚደረገው መልካም ተሞክሮ እንዲሁም የስፓኒሽ
፣ የሩሲያ ፣ የአረብኛ ፣ የፈረንሳይኛ ቋንቋዎችን ቢያንስ የሚሞክሩ ስለነበሩ በዜና ዝግጅት ወቅት የስምና ቦታ መጠሪያዎችን በተሻለ
የማቅረቡ እድል ለሬዲዮው ተደማጭነት የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው እሸቱ ያምናል፡፡ ዜና ፋይል ውስጥ በቀን ሁለቴ የሚከወነው የኤዲቶሪያል
ስብሰባ አሰራሩን ሁሉም እንዲረዳው በማድረጉ ሰራተኛው የዜና እወጃውን ሰአት አለቃው አድርጎ ስለሚያስብ አላግባብ መጠባበቅ ሳይኖር
በተዘረጋው ስርአት መሰረት ቀድመው የደረሱ ጋዜጠኞች ዜናውን በሰአቱ ለማድረስ ተረባርበው የሚሰሩበት ባህል በመዳበሩ ችግር ሲያጋጥም
ተተካክቶና በምክክርም ተሸፋፍኖ በጋራ የመስራት ልምዱ ለውጤታማነቱ አንዱ ምክንያት እንደሆነ እሸቱ ይጠቅሳል፡፡
በዜና ፋይል ውስጥ በመደበኛነት
በመስክ ስምሪት የሚሸፈኑ የሀገር ውስጥ ዜና ዘገባን ከማዘጋጀትና የውጭ ዜናዎችን ለሬዲዮ በሚስማማ ከመተርጎምና ያልተገለጡ አነጋጋሪ
የህብረተሰብ ጉዳዮች ላይ የምርመራ አሳሽ የክትትል ዘገቦችንና ዜና ትንታኔዎችን ከማጠናቀር አንስቶ ጋዜጠኛ እሸቱ ሀገራዊ የህዝብ
አገልግሎት መስጫዎችን አሰራር የሚፈትሹና አለም አቀፋዊ ሁነቶች ላይ ያጠነጠኑ የትኩረት ጉዳዮችን የሚያብራሩ የወቅታዊ ሪፖርት ዜና
ፕሮግራሞችን ጭምር በይዘት ፣ በጥልቀት ፣ በንበት እና በአቀራረብ ረገድ አድማጭን በሚገዛ መልኩ በልዩነት ያቀርብ ነበር፡፡
በዜና ዘገባ ረገድ እሸቱ
አላግባብ ለሆነ ቅጣት የተዳረገበትን አጋጣሚ አይረሳውም፡፡ ጊዜው 1988 ዓ.ም - ጉዳዩም በአዲስ አበባ የሚኖረው የሙስሊም ህብረተሰብ
የመንግስት የስራ ሰአት የዓርብ ጁምዓ ዕለት የፀሎት ሰአት ጋር ተናፅሮ እንዲስተካከልና ከመጅሊሱ አመራር ውስጥ የፖለቲካ ቅኝት
ያላቸው ተነስተው ሙስሊሙን በአግባቡ የማይወክሉት ሰዎችም ሀይማኖታዊ ስርአቱን እያወኩት እርምት ይወሰድ በሚል ያቀረብቡት ጥያቄ
በዘገባ ይሸፈን ወይ ይቅር በሚለው ከፍተኛ ንትርክ ነበር የፈጠረው፡፡ በዚህ ጉዳይ ከበስተጀርባ ስለሀይማኖታዊ ስርአቱ የማይገዳቸው
ግን ለሆነ የፖለቲካ ቡድን ኢኮኖሚያዊ ጥቅሞችን የሚያደላድሉ አካላት
ላይ ህብረተሰቡ ከፍተኛ ቅሬታ ነበረው፡፡
ይሁንና እስከ ጠ/ሚኒስትር
ቢሮ ድረስ በሰላማዊ ሰልፍ ህብረተሰቡ የጠየቀውን ጥያቄ ወደጎን በመተው የጠ/ሚኒስትር ቢሮ ጠብቁ ሲል ብቻ የሰጠው ምላሽ ተገልጾ
ይተላለፍ የተባለውን ሙያዊ ያልሆነን ክልከላ አሻፈረኝ በማለት ከቀጥታ ስርጭት ስቱዲዮ ገብቶ በሰልፉ የሆነውንና የጠ/ሚኒስትር ቢሮ
ሰጠ የተባለውን ምላሽ አጣምሮ ባቀረበው ትክክለኛ ዘገባ መዘዝ ለአንድ ወር ከመስክ ስራና ከዜና ንባብ የታገደበትን አላግባብ ቅጣት
ሲያስታውስ ዛሬም ህመሙ ይሰማዋል፡፡
በዘመኑ በህብረተሰብ
ዘንድ በኢትዮጵያ ከፍተኛ ተቀባይነት የነበረውን ዘወትር ዓርብ ከቀኑ 5፡30 አንስቶ ለ20 ደቂቃ ሲተላለፍ የቆየው ሰፊ ዳሰሳዊ
ጥልቅ ዝርዝር የትንተና ሚኒ ዶክመንተሪ የአቀራረብ ቅርፅን (ዘይቤን) የሚከተለውን “የሰሞኑ ታላቅ ዜና” የተሰኘውን ቅንብር ከይዘት
ቀረፃና ከፕሮግራም ቲም መረጣ አንስቶ በ1988 ዓ.ም ወርሀ መጋቢት ላይ በቀድሞዋ ዩጎዝላቪያ “በባልካን ቀውስ” ላይ ያተኮረ የበኩር
ትንተናዊ ጥንቅርን ከማቅረብ አንስቶ በተከታታይም ግንባር ቀደም አዘጋጅ በመሆን የፕሮግራሙን ከፍታ በማስጠበቅ ረገድ እሸቱ ከፍተኛ
ድርሻው አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና
ፋይልን ዛሬም ድረስ የማይዘነጋ ያደረገው በእሸቱ እምነት እያንዳንዱ ጋዜጠኛ ሁሌም በእውቀትና ልምድ ራሱን ማዳበሩ ፣ እርስ በርስ
የሞቀ ፉክክር የመኖሩን ያህል ከአንድ የስራ ቡድንነት ባለፈ እንደ አንድ ቤተሰብ ስራውን ማናበብ መቻሉ ፣ ለሆነ ሰው ታይታ ሳይሆን
አለቃ ኖረ አልኖረ ሁሉም ስራውን ለይቶ አክብሮ መስራቱ ፣ ከአንጋፋው እስከ ጀማሪው ጋዜጠኛ ድረስ አብሮ መስራቱ በትውልድ ቅብብሎሽ
የሙያ ልምዳቸውን ይበልጥ እንዲሻሻል እድል መፈጠሩ ፣ የመፅሀፍ መዋዋስና ርዕሰ ጉዳይን አንስቶ በጋራ በጥልቀት የመወያየት ባህል
የጎለበተበት መሆኑ ፣ የተለያዩ የሀገር ውስጥና የውጭ ቋንቋዎችን የሚያውቁ ብሎም አብዛኛውን ድፍን ኢትዮጵያንና የውጭ ሀገራትን
ዞረው ያዩ ሙያተኞችን በቡድኑ ማካተቱ ፣ አባላትን በተቻለ መጠን ከፖለቲካ አድሎ ይልቅ ለሙያው የማደርና እርስ በርስ የመተራረም
ልምድ መጎልበቱ እና ስለሙያ ጥራት ጠንቅቀው አውቀው ለትርጉምና ለአርትኦት ብቻ በሚል ጭምር ዜና የማያነቡ ግን ዜናን በልዩ የሚያዘጋጁ
መኖራቸው ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳል፡፡
እሸቱ ከምርመራ ጋዜጠኝነት
ጋር
በኢትዮጵያ ሬዲዮ ዜና
ክፍል ጋዜጠኞች በራሳቸው ጥረት በሀገራዊ አጀንዳ ላይ ያጠነጠኑና የመንግስት ዝርዝር የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትንም ጭምር አካተው
ጊዜ ተወስዶ በጥናት ላይ የተመሰረቱ በወር ሁለት ዋና ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ አሳሽ ይዘት ያላቸው የፕሮጀክት ዜና ስራዎችን በየግላቸው
አጠናቀው ማስረከብ የሚጠበቅባቸው ሲሆን ይህ ለሬዲዮ ጣቢያው ጥልቅ በሳል መርማሪ ዘገቦችን በመሸፈን ረገድ በህዝብ ዘንድ የሚታወቅበት
ቀለም ለመሆን ችሏል፡፡ እሸቱ ካከናወናቸው ሲተላለፉ አነጋጋሪ ሆነው ካለፉት መካከል የሚከተሉት ለአብነት ይጠቀሳሉ፡፡
- በፕሮጀክት ጥናታዊ
የእቅድ ዜና ሽፋን ረገድ አንዱ በ1986 እና በ1987 ዓ.ም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል በግልጋሎት አሰጣጥ ጫና መዘዝ ተፈጠሩ በሚባሉ
ምክንያቶች በተመሳሳይ ስምና ተቀራራቢ ሰአት ለመጡ ወላድ እናቶቻቸው በተደጋጋሚ ህፃናትን አለዋውጦ ከመስጠት ጋር በተያያዘ የህዝብ
መነጋገሪያ አጀንዳ የመሆኑ አጋጣሚ ነው፡፡ ይህ አነጋጋሪ ፈታኝ አጋጣሚ የጤና ስርአቱ እንዲፈተሽና ኋላም እሸቱ ራሱ ወደ ጤና ዘርፉ
ዘገባ እንዲሳብ ምክንያት ሆኖታል፡፡ ችግሩ በተፈጠረ ቁጥር ሳይጣራ በብስለት ባልታየ ድምዳሜ የጤና ባለሙያውና ተቋሙ ላይ ብቻ የወቀሳ
ውርጅብኝ ይሰነዘር ነበር፡፡ ስለዚህም የችግሩን ውስብስብነትና ጥልቀት ለመገንዘብ በአዲስ አበባ ያሉ ከጤና ጣቢያ አንስቶ ሁሉን
ሆስፒታሎች ብሎም የጤና ሚኒስቴር አገልግሎት ስርአታዊና መዋቅራዊ ጉዳዮችን ጭምር የዳሰሰ ለአንድ ወር ከ15 ቀናት የፈጀ የሰው
ሀይሉን ፣ የህክምና መርጃ መሳሪያዎች ሁኔታን ፣ የመድሀኒትና የህክምና አገልግሎት መስጫ ቁሳቁሶች አቅርቦትን ፣ የአገልግሎት አሰጣጥ
ስርአቱንና መዋቅራዊ ሰንሰለቱን የተመለከተ በአካል ዞሮ በመታዘብና
የጥናት ሰነዶችንም ያመሳከረ ምርምራዊ የአሰራር ፍተሻ በማድረግ በርካታ ዜና ዘገቦችን በማጠናቀርና ሰፊ የሬዲዮ ሚኒ
ዶክመንተሪ የወቅታዊ ፕሮግራሞችን በማቀናበር ለ3 ሳምንታት በኢትዮጵያ ሬዲዮ በተከታታይ መተላለፋቸውንና የህዝብ መነጋገሪያ መሆናቸውን
ተከትሎ ኋላ ላይ የኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴርም ችግሩን ከስሩ ለመፍታት ዘገቦቹን እንደ ተጨማሪ ግብአት ወስዶ የከስልጣን በላይ ጤና
አገልግሎት አሰጣጥ አላላክ ስርአትን (Health Service Referral System) በ1988 ዓ.ም መዘርጋቱ የሚዲያ በጎ
ተጽዕኖ አንዱ ምሳሌ ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡
- በእሸቱ ገለቱ የሙያ
ህይወት ውስጥ በስራው የረካበትም የተፈተነበትም ጉዳይ በሀረር አንድ የሰራዊት አባል ላይ የተፈፀመው የሰብአዊ መብት ረገጣ ነው፡፡
አንድ በእሳት አብዛኛው ሰውነቱ የተቃጠለ ከሆስፒታል በድብቅ ወጥቶ ጉዴን ተመልከቱት ብሎ ከአቡነ ጴጥሮሱ ኢትዮጵያ ሬዲዮ ደጃፍ
ስለፍትህ ብሎ ብቅ ያለው ፖሊስ ብዙዎችን ቢያነጋግርም ጉዳዩን ለመድፈር እያመነቱ ቢያልፉትም እሸቱ ግን ጉዳዩን ከነፈተናው ለመጋፈጥም
ብሎ እንደ ሀኪም መስሎ ጭምር ከጥቁር አንበሳ እስከ ጀጉላ ሆስፒታል - ከአዲስ አበባ እስከ ሀረር ያሉትን የመረጃ አማራጮችን በመፈተሽ
አንድ ወር የፈጀው የምርመራ ዘገባ ኪናዊ ትረካን በተከተለ መንገድ ለ3 ተከታታይ ሳምንታት በእሁድ ጠዋት የሬዲዮ ፕሮግራም ተላልፎ
አድማጮችን በሰፊው አነጋገረ፡፡
እሸቱ ለጋብቻ ዝግጅት
በሚያደርግበት ወቅት በገባበት የምርመራ ዘገባ መዘዝ የእስር ሙከራ እና ከጅግጅጋ መስክ ሲመለስም ሀረር ላይ ሲያድር ‘ይምጣ እንጂ
እናሸዋለን” በሚል ሲፎክሩበት ከነበሩት አካላትም ለማምለጥ በማስመሰያ ስምና መታወቂያ ማደሩ አይዘነጋውም፡፡ መቼ በዚህ አበቃና
እሸቱ ጉዳዩን በእንግሊዝኛ በሚታተመው ‘ዘ - ዴይሊ ሞኒተር’ ጋዜጣ ላይ አስወጥቶት ስለነበር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤም
የሀገር ቤቱን ሪፖርት ሲያዘጋጅ ይህንኑ ጉዳይ ማካተቱን ተከትሎ አምኔስቲ ኢንተርናሽናልና ሂዩማን ራይትስ ኮሚሽን ደግሞ የተጠቂውን
ሰው ጉዳይ በጉልህ በማካትተ የኢትዮጵያን የተጠቃለለ ሪፖርት ቅጂን ለጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊና ለፕሬዚደንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ
በመላካቸው ከፍተኛ ውጥረት ተፈጥሮ በጠ/ሚኒስትር ጽ/ቤት ከፖሊስ ኮሚሽን ጋር የኢትዮጵያ ሬዲዮ አብሮ ቀርቦ ስለጉዳዩ እንዲያስረዳ
ተደርጓል፡፡ የዚያን ወቅት የሬዲዮ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፈቃደ የምሩ በዘጋቢው የሁነት ማብራሪያና የተቀረጹ ሪል ክሮችን ሙሉ
በማዳመጥ በቂ ዝግጅት አድርገው ነገሩን ከስሩ በማስረዳታቸው ዘጋቢው ባለድርሻዎችን ሁሉ በሚዛናዊነት በማካተቱ ፖሊስ ይልቅ ራሱን
ቢያይ በሚል ምክረ ሀሳብ ውዝግቡ መጠናቀቁን እና “የነካኸው ሁሉ እሳት እየሆነ ነው” የሚሉት አለቆችም ሪፖርተሩ ለጥቂት ጊዜም
ዞር ብሎ ቢያርፍ ይመረጣል ማለታቸውን እሸቱ ያስታውሰዋል፡፡
- ከሀጂና ዑምራ ጉዞ
ጋር በተያያዘ ከቀበሌ አንስቶ ወረዳ ዞንና ክልል ጭምር ለሙስሊምነት ማረጋገጫ መታወቂያ እየተባለ ተከታታይ ክፍያዎች መጠየቁ ሳያንስ
መታወቂያው የላችሁም በሚል ከአውሮፕላን ላይ በደህንነት እንዲወርዱ የሚደረገውና ተጓዦች ገንዘብ ለመቆጠብ በመርካቶና አውቶቡስ ተራ
አመድ ላይ እያደሩ ጭምር የሚጠባበቁት አሳዛኝ ሁኔታ ነበር፡፡ ‘የመንግስታዊ
አሰራር ነው’ በሚል ግለሰብ የፖለቲካው ዘዋሪዎች እጅ አዙር ጥቅም ፍለጋ በሀይማኖት ውስጥ ጣልቃ የሚገቡበት ሁኔታ የእሸቱን ትኩረት
ስቦ ለአንድ ወር ከ15 ቀናት በፈጀ የምርመራ ዘገባ የሳዑዲ ሀጂ ሚኒስቴርን ጨምሮ ከመርካቶ እስከመጅሊሱና ውጭ ጉዳይና ደህንነት
መስሪያ ቤትን ባካተተ ሁኔታ እሸቱ ውትብትቡን ሴራ በዝርዝር ፈትሾ በተከታታይ የሬዲዮ ዶክመንተሪ አጠናቅሮት ለ2 ሳምንታት የተላለፈው
ሰፊ ወቅታዊ ፕሮግራም እጅግ አነጋጋሪ ብቻ ሳይሆን በጉዳዩ ባለድርሻ አካላትን ሁሉ በእጅጉ ያስገመገመ ነበር፡፡
- ሌላው የአዋሳ ዱቄት
ፋብሪካ ተረፈ ምርት ከሆነው መኖ አቅርቦት ጫረታ ጋር በተያያዘ ከበስተጀርባ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያሽከረክረው አንድ የግል ተብዬ
የንግድ ኩባንያ (ወንዶ ኩባንያ) ከውል አግባብ ውጪ ባለመብት ከሆነው ሌላ ተዋዋይ የግል ንግድ የስራ ኮንትራትን በተጽዕኖ ነጥቆ
ለመውሰድ የተደረገውን ስውር የንግድ ሴራን ለማጋለጥ እሸቱ የሰራው የምርመራ ዘገባ በመጨረሻ የጠ/ሚኒስትር ቢሮ ጽ/ቤት ጉዳዩን
አጣርቶ ተከታይ ዘገባ ሳይሰራ ውዝግቡን ለባለመብቱ የስራ ኮንትራቱ ለባለመብቱ እንዲመለስ በመወሰን ውዝግቡ የተፈታበት ውጤታማ ዜና
ሪፖርትም አይዘነጋም፡፡
- የሰራተኞችን መብት
እስከመጋፋት የዘለቀን በመተሀራ ስኳር ፋብሪካ ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን የአሰራር ግድፈት የዳሰሰው ዘገባው ሌሎች በተመሳሳይ ችግር
ውስጥ የነበሩት ድርጅቶች ጭምር በትይዩ ፈጣን የእርምት እርምጃ እንዲወስዱ ያስገደደበት ሁኔታ አንዱ ተጠቃሽ ነው፡፡
የዜና ማዕከል ዳይሬክተሩ
እሸቱ እና የ1997ቱ አወዛጋቢ ምርጫ
በኢትዮጵያ የሚዲያ ታሪክ
1997 ዓ.ም እና ተከታዮቹ አመታት እንጥፍጣፊው ተስፋ ተሟጦ አስጊው የጭለማ ዘመን ሀገሪቱን የወረሰበት ነው ብሎ ባለታሪኩ ያምናል፡፡
ጭራሽ ዜናና ወቅታዊ ሪፖርቶች የመንግስት ውዳሴ ከንቱ ማራገቢያነታቸው ሳያንስ በ1997 ጭራሽ በግፍ በአደባባይ የተገደሉ የፍትህ
ያለህ ያሉ ወጣቶችና አረጋውያን ጭምር በህግ ፊት ሳይፈረድና በባህልም ሙት የማይወቀስ ሆኖ ሳለ ያለምንም ማስረጃ በሚዲያዎች “ባንክ
ሊዘርፉ ሲሉ የተገደሉ” በሚል ካልተላለፈ ብለው በውል ባልታወቁ ምንጮች በእጅ ጽሁፍ ጭምር በብልሹ ካድሬ አመራሮች አማካይነት የሚላከው
የዘቀጠ ዘገባ ተብዬ መዘዝ በወቅቱ በኢትዮጵያ ሬዲዮ የዜና ማዕከል ዳይሬክተር የነበረው እሸቱ ስራውን በገዛ ፈቃዱ ለመልቀቅ መጋቢት
1997 ደብዳቤ አስገባ፡፡
አስከፊ ሀገራዊ ገጽታ
ከዛሬ ነገ ይቀየር ይሆን በሚል ህዝብ በጠቅላላው ምርጫው ዋዜማ ጭላንጭል ተስፋ ማድረጉ ቢታወስም በአመራር ላይ የነበረው አምባገነን
አካል ግን የህዝብን ድምጽ ባለማክበር ግንቦት 7 / 1997 ምሽት ላይ የምርጫ ውጤትን በህግ አግባብ ይፋ ማድረግ ያለበት የምርጫ
ቦርድ ሆኖ ሳለ እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ የኤዲቶሪያል ፖሊሲ የትኛውም የፖለቲካ ፓርቲ መግለጫ ቢልክ ሚዲያው የድርጅት ልሳን ስላልሆነ
ከመግለጫው ዜና ቀንጭቦ ከመስራት ውጪ ሌላ እንደማይገደድ በአሰራር በግልጽ ቢቀመጥም የኢህዲግ አሸናፊነት መግለጫ ሙሉ በሙሉ በአንተ
ካልተነበበ በሚል ሚዲያውን በሚዘውሩት አንድ ሚኒስትር ጭምር ግፊት ቢደረግም ሙያውን ያልተከተለ በመሆኑ እንዲቀር እሸቱ ሲወስን
“ማን ነው እሱን ዜና አንሺና ጣይ ያደረገው” ተብሎ በጠላትነት የተፈረጀበት ነበር፡፡
የተቃዋሚው ቅንጅት ፓርቲ
ከግንቦት 7 / 1997 በፊት ባለው አንድ እሁድ የድጋፍ ሰልፍ በወጣበት ወቅት የገዢው ፓርቲ ባለስልጣናት የኢህአዲግ ሰልፍ በቀዳሚው
ሳምንት ልዩ ትኩረት እንዲሰጠው እንዳልተረባረቡ በዚህ ጊዜ ግን በሰልፉ ወቅት የህግ ተጠያቂነት የሌለው ከ12 አመት ያልበለጠ ታዳጊ
ልጅ ከወገብ በላይ ራቁቱን ሆኖ “ሼህ አላሙዲን ሌባ - አርከበ ሌባ!” በሚል እያሰማ የነበረው መፈክር ካልተላለፈ ሞተን እንገኛለን
በሚል ትልልቅ የገዢው ፓርቲ አመራሮችና ሚኒስትሮች ጭምር በቴሌቪዥን በአቶ ሴኩ ቱሬ መግለጫው ጭምር እንዲነበብ ሆኖ ሳለ ይህ የኢትዮጵያ
ሬዲዮ የማን ነው እያሉ በቅርብም በርቀትም ሲዝቱ እንደነበር በቦታው የነበሩ ስለሙያው ማቆልቆል በእዝነት ያስታውሱታል፡፡ በሰልፉ
ላይ የስድብ መፈክሩን ያሰማውን ታዳጊ ልጅ በህግ ለመጠየቅ እድሜው የማይፈቅድ ከመሆኑም በላይ የተቃዋሚ ፓርቲን ምስል በማስጠላት
ርካሽ የፖለቲካ ትርፍን በማስላት ብቻ የከበረ የሞራል ከፍታና አኩሪ የመከባበር ባህል ላለው ህዝብ ስድብን ለዚያውም በዜና ማስተላለፍ
ሙያዊም _ ባህላዊ አውዱም ሆነ ህጋዊው አግባብ አይፈቅድም በሚል ይህ መፈክር እንዳይተላለፍ መደረጉ ግዙፍ ነን በሚሉት ሹማምንት
ረገድ ዜና ዳይሬክተሩ ጥርስ እንዲነከስበት ያደረገ አጋጣሚ ሆኖ አልፏል፡፡
ጋዜጠኝነትንና የፍትህ
ዘርፉን ጨምሮ ሙያተኝነት አፈር ከድሜ የበላበት _ ለህሊናቸው ያደሩ ወደ ወህኒና ሜዳ እንዲጣሉ የሆኑበት ብሎም ሀገርም ወደ የደም
ምድርነት ያዘቀዘቀችበት መሆኑ ያበገነው እሸቱ ቀደም ሲልም ሀገራዊ ታሪክን ፣ ሰንደቅ አላማን ፣ ኢትዮጵያዊ የአርበኝነት ገድልን
፣ ብሄራዊ መዝሙርን ፣ ባህልን ፣ ቋንቋን ፣ ማህበራዊ ወግና እሴትን ለማጥፋት ከ1983 አንስቶ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያንን ጠል
የሆነ ስርአትና መዋቅርን የዘረጋው የሴራ ፖለቲካ ዘዋሪው የጥቂቶች ቡድን በሚዲያ አሰራሩ ላይ ጣልቃ እየገባ የሚዲያውን ተአማኒነት
ማበላሸቱ ባለታሪኩ ይቆጨዋል፡፡ በሚዲያ ውስጥ የኢትዮጵያን ስም ጠቅሶ ስለሀገራዊ ልምላሜና ጀግንነት ብሎም ፉከራና ቀረርቶን ጨምሮ
ሀገራዊ ታሪኮችንና ገድሎችን የሚያወሱ ዘፈኖችና የጥበባት ስራዎች የቴዲ አፍሮን “ጃ ያስተሰርያል _ በ17 መርፌ” የሚለውን ዘፈን
አይነት ጨምሮ በሚዲያዎች በልዩ ጥያቄ በአለቆች እንዲፈቀዱ የሆነበት ብልሹ አሰራርም እሸቱን ያሳዝነዋል፡፡
እሸቱ የጥናትና ስልጠና
አማካሪነት ሚናው
ከመንፈቅ በላይ ፈጅቶ
በሙያ ጥልቀት በዝርዝር የተሰነደው የሚዲያ ስልጠና መመሪያ ዝግጅት ቴክኒካዊ አማካሪ አካል በመሆን ከየካቲት 2013 እስከ ነሀሴ
2013 ድረስ ባለው ጊዜ ከጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ እና በኢትዮጵያ ከአሜሪካ ኤምባሲ ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ የተለያዩ ከተሞች
ተዘዋዋሪ በሆነ መልኩ በእያንዳንዱ ምዕራፍ ለሳምንት 45 ሰአታት ያህል በሚሸፍን ሁኔታ ከ280 ለሚበልጡ ጋዜጠኞች ምርጫንና የግጭት
አዘጋገብን በተመለከተ የከፍተኛ ደረጃ ጋዜጠኝነት ስልጠናን ሰጥቷል፡፡
- ጋዜጠኛ እሸቱ ገለቱ
ከUNESCO, ከUNDP, ከአለም አቀፉ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን (IFJ), ከአለም የምግብ ፕሮግራም (World Food
Program), ከTF Global Health, ከBBC World Service Trust, ከምስራቅ አፍሪካ የጋዜጠኞች ህብረት
(EAJA), ከጤና ሚኒስቴር, ከኢትዮጵያ ብዙሀን መገናኛ ባለስልጣን, ከአዲስ አበባ መስተዳድር, ከአውሮፓ ህብረት
(European Union), ከIntra-Health International, ከDFID, ከORBIS Ethiopia, ከSight
Savers, ከFred Hollows Foundation, እና ከEBC ጋር በመተባበር በተለያዩ ጊዜያት ከ1993 ዓ.ም አንስቶ እስከ
ቅርብ ጊዜ ድረስ ከመሰረታዊ ጋዜጠኝነት አንስቶ በዜናና ሚዲያ ፕሮግራም ቅንብር ፣ በግጭት ዘገባ አሸፋፈን ፣ በምርመራ ጋዜጠኝነት
፣ በፖለቲካዊ ኮምዩኒኬሽን ፣ በህብረተሰብ ጤና አዘጋገብ ፣ ጥበብን ለሚዲያ አጠቃቀም ፣ በችሎት ዘገባ ፣ በማህበራዊ ሚዲያ አያያዝ
፣ በአድቮኬሲ ኮምዩኒኬሽን ስልት ፣ በብሮድካት ጋዜጠኝነት ፣ በአካባቢ ጥበቃ አዘጋገብ ፣ በዳታ ትንተና ጋዜጠኝነት ፣ በስርአተ
ጾታ ጉዳይ አሸፋፈን ፣ በጂኦፖለቲካልና አለም አቀፍ ግንኙነት ጉዳዮች አዘጋገብ እና ሰብአዊ መብት ተኮር ዘገባን በመሰሉ ርዕሰ
ጉዳዮች ላይ ከተለያዩ ሚዲያዎች ለተውጣጡ ከ1600 ለሚልቁ ጋዜጠኞችና የኮምዩኒኬሽን ባለሙያዎች ተከታታይ ስልጠና መስጠቱ ይታወቃል፡፡
እነኚህን ስልጠናዎች ለመስጠት የተዘጋጁት ማኑዋሎች እሸቱ ለሙሉ መፅሀፍ ካዘጋጃቸው ዝርዝሮች ውስጥ የተጨለፉ በመሆናቸው ራሱ ካለፈባቸው
ተጨባጭ ተሞክሮዎች ጋር ተሰናስለው ሁለት የተለያዩ ሙያዊ መጽሀፍትን ለህትመት ለማብቃት በዝግጅት ላይ ይገኛል፡፡
- እሸቱ በሚዲያና ኮምዩኒኬሽን
አማካሪነትና ከፍተኛ ፕሮግራም አቀናባሪነቱ በቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ትረስትና በቲ. ኤፍ. ግሎባል ሄልዝ ቆይታው የህብረተሰብ ማህበረ
ኢኮኖሚያዊ ፣ የባህልና ስነ ልቦናዊ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሰፊ ጥናት ላይ የተመሰረቱ አለም አቀፍ የሚዲያ ቅንብር ጥራትን ያሟሉ
108 የሬዲዮ ሚኒ ዶክመንተሪዎችንና እንዲሁም የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲንና አለም አቀፍ ጤናን የተመለከቱ 26 የኦዲዮ - ቪዥዋል ዶክመንተሪዎችን
አዘጋጅቶ በሀገር ቤትና በውጭ ሚዲያዎች የተላለፉ ሲሆን በእኚህም ከብዙ ተቋማት እውቅና ከማግኘት ባሻገር በግልና በቡድን አለም
አቀፍ ሽልማቶችንም ያስገኙለት ሆነዋል፡፡
- በዘ ኢትዮጵያን ሄራልድ
(The Ethiopian Herald )፣ በዘ ዴይሊ ሞኒተር (The Daily Monitor) ፣ በላምባዲ (Lambadina) ፣ በዓይኔን
(Aynien) እና በአቡጊዳ (Abugida) በተሰኙ ጋዜጦች እና መጽሄቶች በእንግሊዝኛ ጽፎ ታትመው ከወጡለት ተከታታይ መጣጥፎች
ባሻገር በህብረተሰብ ጤና ልማት ፣ በትምህርት ፣ በማህበረተሰብ አኗኗር ዘይቤ ፣ ውሀን ጨምሮ በመሰረተ ልማት አገልግሎት እና በተፈጥሮ
አካባቢ አጠባበቅ ርዕሶች ላይ ያጠነጠኑ 208 ጥናት ላይ የተመሰረቱ ጽሁፎችን በማቀናበር በተከታታይ በየሳምንቱ በጋዜጦች አምድ
ታትመው የወጡትም ለመጽሀፍ በሚሆን መልክ እያዘጋጃቸው ነው፡፡
- ከዚህ በተጨማሪም
ከሚዲያ ይዘት ቀረፃ ፣ ከሚዲያ ፎርማት ማበልፀግ ፣ ከህብረተሰብ የጤና መረጃን መሻት ፣ ከአድማጭ ተመልካች ክትትል ዳሰሳ ፣ ከሚዲያ
ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ነደፋ ፣ ከወጣቶች የህይወት ክህሎት ፎርማቲቭ ሪሰርችና ከቢዝነስ ፕላን ዳሰሳ ጋር በተያያዘ ከተለያዩ የሀገር
ቤትና አለም አቀፍ ተቋማት ጋር ሆኖ በተለያዩ ጥናቶች ላይ ተሳትፏል፡፡
እሸቱ እና የእውቅና ሽልማቶቹ
- እ.አ.አ በ2011
እሸቱ በግሉ ዩኒሴፍ አፍሪካ ባዘጋጀው የጤና ልማት ሚዲያ ውጤቶች ውድድር ላይ የአመቱ ምርጥ የሚዲያ ፕሮግራም አዘጋጅ
(First prize award winner of the year in Media division with special emphasis
on Health Development matters)
- እ.አ.አ በ2010
እሸቱ ለቢቢሲ ወርልድ ሰርቪስ ትረስት የሚዲያ አማካሪና ከፍተኛ ፕሮዲዩሰር ሆኖ በመሪ ግንባር ቀደምትነት “አቡጊዳ” ተብሎ ከሚታወቀው
ቡድኑ ጋር በሰራው ፕሮዳክሽን የአፍሪኮም_ኔት ያዘጋጀው አለም አቀፍ ውድድር በስትራቲጂካዊ የጤና ኮምዩኒኬሽን ዘርፍ በተለይ በሚዲያ
ፕሮጀክት የአመቱ 1ኛ ውጤታማ የሚዲያ ፕሮግራም (Afri-com Net’s Best First Award Winner of The
Year in the Media Category of Strategic Health Communication Contest)
እሸቱ በበጎ ፍቃድ ያገለገለባቸውና
እየሰራ የሚገኝባቸው
- በት/ቤቶችና በታዳጊ
ወጣቶች ለሚመሩ አማተር ሚዲያ እና ጥበብ ክበባት በሙያ ክህሎት ስልጠና ድጋፍ ማድረግ
- በሰሜን ኢትዮጵያ
የጤናና የገጠር ህብረተሰብ ልማት ላይ ባተኮረው የተስፋ ጺዮን ምግባረ ሰናይ ድርጅት ውስጥ የስራ አመራር ቦርድ አባል-
- ከሙያ ማህበርነት
(Ethiopian Volunteer Media Professionals Against AIDS) ወደ ሀገር ቤት ምግባረ ሰናይ ተቋምነት
ያደገው የላምባዲና ጤና ኮምዩኒኬሽንና ልማት ድርጅት ማህበር ሰብሳቢ
- የኢትዮጵያ ቤተሰብ
መምሪያ በጎ ፈቃደኛ
- የአቡጊዳ እና የላምባዲና
ወጣቶች ክበባት የህይወትና ሙያ ክህሎት አሰልጣኝ እና ወጣቶችን የማብቃት ፕሮጀክት በጎ ፈቃደኛ ደጋፊ
- የኢትዮጵያ ብሄራዊ
የጋዜጠኞች ህብረት (Ethiopian National Journalists Union) ምክትል ሰብሳቢ
- በቅርብ የተቋቋመው
ታዳጊ ወጣቶችን በህይወት ክህሎት የመቅረጽ የሰብዕና ግንባታ ላይ
ያተኮረው የቤተል ኢ.ገለቱ መታሰቢያ (Bethel E. Geletu Foundation – Bethel’s Inspiring
Community of Young Ethiopia) መስራችና አስተባባሪ
እሸቱ እና ገጠመኞቹ
እሸቱ የበኩር ዜናውን
የት ሰማት፦ እሸቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበበውን ዝርዝር ዜና የሰማው አራት ኪሎ ፓርላማው ፊት ለፊት ካሉት የቀበሌ ቤቶች ከበዙበት
ተከራይቷት ከነበረች 5 ሰው ሲገባ ከምትሞላ አነስተኛ ቤቱ አቅራቢያ ካለ የተከፈተ ሬዲዮ መታወቂያዋ ከሆነች ሱቅ ደጃፍ በ3 ብር
አራት እንጀራ ለመግዛት በሄደበት አጋጣሚ ነበር፡፡ ባለሱቁ የእኔን ከወትሮ በተለየ ሁኔታ እንጀራውን ገዝቼ እጣደፍ የነበርኩ ሰውዬ
ከሱቅ ደጃፍ መቆየቴ ቢገርመውም እኔም እከሌ ነኝ ዜናዬን ለመስማት ነው የቆምኩት ለማለት ያልደፈርኩት ምናልባትም ዜናውን ሳነብ
ትንሽዬ አርጩሜ ይዘው የሚያባርሩኝ መምሰሌ ይሆን _ እርግጠኛ ግን አይደለሁም፡፡
እሸቱ በወሊሶ ምን ሆነ፦
ለዘገባ መስክ ወደ ጉራጌ ዞን በወጣበት ወቅት ጉባኤው የሚካሄደው በወልቂጤ ቢሆንም ለዜናው ድምጽ ጥራት ሲባል ዲጂታል ስልክ ያስፈልግ
ስለነበር ወደ ወሊሶ እየተመላለሰ ያጠናቀረውን ዜና በስልክ ይልክ ነበር፡፡ በአንደኛው ቀን ግን ዝናብ ሊዘንብ ደመና ሊገፋ የቆረጠ
የሚመስል ሀይለኛ ንፋስ ትግል በገጠመበት ሁኔታ እሸቱ ዜና ሊልክበት የተመደበለት የስልክ መልዕክት ማስተላለፊያ ክፍል በሩ ተሰብሮ
አይዘጋ ስለነበር ሀይለኛው ንፋስ ይዞት ከመጣው አቧራ ጭምር ቤቱን አተራምሶት ሲሄድ የስልኩን እጀታ በአንድ እጁ በሌላኛው ደግሞ
በምዕራፍ የተለዩ ተከታታይ ዜናዎችን የያዙ በግማሽ ገጽ የተቆራረጡ ወረቀቶችን ይዟል፡፡ አንብቦ ያልጨረሳቸው ሁለት ቁራጭ ዜና የተፃፈባቸውን
ወረቀቶች ንፋሱ ይዞት ጠፋና አውላላ መንገድ ላይ እንደ ወፍ መብረር ከቀጠለው የዜና ወረቀት አንዱ በመከራ ከመንገድ ዳርቻ ቦይ
አጠገብ ሲገኝ ሌላኛው ግን ሰፈር ውስጥ ገብቶ ለመያዝ ስንሞክር ብዙዎች የጠፋ ዶሮን ፍለጋ መስሏቸው የዶሮዋን መልክ ይጠይቁ ነበር፡፡
መጨረሻ በሰፈርተኛው ርብርብ ቀሪዋ የዜና ወረቀት ብትገኝም ከአቡነ ጴጥሮሱ ዜና ክፍል ዜናውን ሲቀበሉ የነበሩት ሰዎች በድንገተኛው
የዜና ማስተላለፍ መቋረጥ የተደናገጡበትንና ከወሊሶ ለተጠናቀረው ዘገባ እሸቱ ገለቱ ነኝ ሲል በስልክ ቤቱ ከነበረው የአጀብ ሳቅ
ተወንጭፎ ሮጦ የወጣበትን አጋጣሚ አይረሳውም፡፡
እሸቱ እና የማለዳ ዜና
ተረኛ አዘጋጅነት፦ የማለዳ ዜና ተረኛ አዘጋጅነት ከማለዳው 12 ሰአት ዜና ንባብ አንስቶ እስከ ጠዋቱ 3 ሰአት ድረስ ዜናን አዘጋጅቶ
ማቅረብ የሚጠይቅ ሲሆን ከየቤቱ ተረኛ ጋዜጠኞችንና ቴክኒሻኖችን መኪና እየዞረ የሚያሰባስበው ከሌሊቱ 10 ሰአት አንስቶ ስለነበር
ባለታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ የተመደበበት አጋጣሚ አስጠንቆት ነበር፡፡ የማንቂያ ደወሉን እሸቱ ሲሞላው ንጋት ሳይዳረስ ሌሊት ላይ ቢሆንም
ተኝቶ በርግጎ እንደተነሳ ሰአት ሲያይ 12፡15 ሲል ወይኔ መኪና ክላክስ አድርጎ ጥሎኝ ሄዷል ብሎ ተደናግጦ ሲወጣ ጉለሌ አካባቢ
ጭር ብሎ ነበርና አንድም ታክሲ አጣ፡፡ በእግሩ ሮጥ አቡነ ጴጥሮስ ከነበረው የሬዲዮ ጣቢያ ሲደርስ የጥበቃ ወታደሮቹ መሳሪያ ደግነው
አስቆሙትና‘እሸቱ ነኝ’ ሲላቸው ገና ከሌሊቱ 6 ሰአት ተኩል እኮ ነው ብለው በሀዘኔታ ወደቤት ሸኝተውት ቀሪውን ሰአታት ያለእንቅልፍ
አንግቶ ስራ የገባበትን አጋጣሚ ከማስታወስ ባሻገር ዛሬም ድረስ የሌሊት ወቅት የመኪና ጥሩምባ ዛሬም ድረስ ይረበሸዋል፡፡
መዝጊያ ፤ እሸቱ ገለቱ
በእውቀት ላይ የተሰመረተ ጋዜጠኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲሰፍን ከሚመኙት ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ያለፈበትን መንገድ ስናጤን እሸቱ
ጋዜጠኝነትን በፕሮፌሽናሊዝም መንገድ ለማስኬድ ታላቅ ተጋድሎ አድርጓል፡፡28 አመት እዚህ ሙያ ላይ ሲቆይ ብዙ ታሪካዊ ሁነቶችን
የመዘገብ እድል ገጥሞታል፡፡ በተለይ ኢትዮጵያ ሬድዮ እውቀት የገበየሁበት ቤቴ ነው ሲል ለኢትዮጵያ ሬድዮ ያለውን የላቀ አክብሮት
ይገልጻል፡፡ እሸቱ ኢትዮጵያ ሬድዮ በዜና ፋይል ውስጥ በሰራባቸው 12 አመታት በርካታ የፕሮጀክት እና ወቅታዊ ዜናዎችን ሰርቷል፡፡
እነዚህን ዜናዎች ሲሰራ ብዙ እውቀት ቀስሟል፡፡ በዚህ ዊኪፒዲያ አዘጋጆች እምነት እሸቱ ጎበዝ ከሚባሉ የዜና ጋዜጠኞች አንዱ ነው፡፡
በአድማጭ ዘንድም በቀላሉ የሚታወስ፤ ስሙ ሲጠራ ኦ እሸቱ ገለቱ የሚያስብል ጠንካራ የሚድያ ሰው ነው፡፡ እሸቱ የሚድያ ስራን ፈልጎት
ስለሚሰራው የነካው ሁሉ ከስኬት ይበቃል፡፡ እሸቱ ሚድያ ውስጥ ከገባበት ከ1985 ጀምሮ እንቅልፍ የለውም፡፡ ለነገሩ እንቅልፍ ምን
ያደርጋል-ብዙ አመት ተኝተናል-መትጋት ነው የሚበጅ የሚለውን መርህ አንግቦ ዛሬም እየተጋ ነው፡፡ እሸቱ ከምንም በላይ ማሰልጠን
ያረካዋል-ያወቀውን ማሳወቅ አንዱ ደስታው ነው፡፡ ይህን ደስታውን ለማምጣት ስልጠናዎችን ላይ በበቂ ሁኔታ ተዘጋጅቶ ይሄዳል፡፡ በጋዜጠኝነት
ረገድ እሸቱ በየጊዜው እያደገ ያለ ብሎም እውቀቱን ያለአንዳች ስስት በማካፈል በብዙዎች ተመስክሮለታል፡፡ እሸቱ ገለቱ የህይወት
ገጹን ስናየው ታሪኩ የሚስብና አንድ ቁምነገር የሚጨበጥበት ነው፡፡ egeletumedia@gmail.com
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ