ሰዎች ህልማቸውን ሲያሳኩ ዋናው ተመስጋኝ እግዚአብሄር ነው ከእዝራ እጅጉ ክፍል 2 …….
ከሰሞኑ ‹‹ህልምን መኖርና ሀገር ያለባትን ክፍተት መሙላት›› በሚል ርእስ በፌስ ቡክ ገጼ
ላይ አንድ ማስታወሻ አኑሬ ነበር፡፡ ብዙዎች እንደወደዳችሁት ነግራችሁኛል፡፡
ዋናው ግቤ የማልፍባቸውን መንገዶች ሰዎች እንዲማሩበትና እኔም ውስጤ ያለውን ሳወጣ ቅልል እንዲለኝ በማሳብ ነው መጣጥፉን
የጻፍኩት፡፡ አንዳንዴ ከትህትና ይሁን ሰው ምን ይለኛል በሚል ምክንያት ሰርተን እንዳልሰራን አሰተዋጽኦዋችን ትልቅ ሆኖ ምንም ያላደረግን
ያህል የሚሰማን ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ሰአት ስለ ራሳችን መጻፍ እና መናገር የሀፍረት ካባ ያስለብሰናል፡፡ ይህ ብዙ ጊዜ ሰዎችን ራሴንም
ሲጎዳ አይቼዋለሁ፡፡ ያለፍንበትን የሰራነውን ቁልጭ አድርጎ ማስቀመጥ ጉራ ሳይሆን የማነቃቂያ አንዱ መንገድ ነው፡፡ እና እኔም የህይወት ታሪኬን በመጻፍ ላይ ስለሆንኩ ከታሪኬ በምጥኑ
ላቀብል ፈልጌና የብዙዎችም ጥያቄ ስለሆነ ህልሜን እውን ለማድረግ የሄድኩባቸውን መንገዶች ለመጠቃቀስ ሞከርኩ፡፡ መልካም፡፡ ታዲያ
ከዚህ ሁሉ የህልም እውነት ውስጥ ማን አለ? መቼም መኪና ካለ ቤንዚን ይኖራል፡፡ ቤንዚን ሰጪ ወይም ቤንዚን ሰሪ አለ፡፡ እና ለህልሜ
መሳካት ዋናው ባለቤት እግዚአብሄር ነው፡፡ ይህንን ያልኩት ማለት ስላለብኝና ፈጣሪን ማመስገን ልምድ ስለሆነ የደንቡን ለማደራረስ
ሳይሆን በትክክል የሆነውን በጥናት መልክ ወይም በግኝት መልክ ስለደረስኩበት ነው፡፡ ይህ ደግሞ በቀጥታ የእኔን ህይወት ብቻ ስለሚመለከት እኔ ብቻ የምረዳውን ለናንተ በሚሆን መልኩ ላቀርብላችሁ ሞክራለሁ፡፡
አንዳንድ ሰዎች ጸሎቴ ተሰማ ሲሉ ያመሰግናሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ፈጣሪ ሳልጸልይ የሚያስፈልገኝ
ራሱ አውቆ ድንገት አስደነቀኝ ሲሉ ያመሰግናሉ፡፡ ቀሪዎች ደግሞ ፈጣሪ
ጸሎቴን አሁን አልሰማም ቢሰማም ነገሩ አልሆነልኝም፡፡ ብለው ወይ ተስፋ ሰንቀው ይቆያሉ አሊያ ተስፋን ቆርጠው ነገሬ አልተሳካም
ይላሉ፡፡ እንግዲህ ከዚህ አንጻር የራሴን ህይወት ልገምግም ብዬ ከ3 ጉዳዮች አንጻር የራሴን ህይወት መፈተሸ ጀምርኩ ፡፡
1ኛ እግዚአብሄር ጋር እንዲሆንልኝ ፈልጌ ፤ ጸልዬ ያደረገልኝን ነገሮችን በቁጥር ዘርዘሬ ጻፍኩ
2ኛ እግዚአብሄር ሳልጸልይ እንዲሁ ያስፈልገዋል ብሎ ያመቻቸልኝን ወይም ሳላውቀው ድንገት ያስደነቀኝን
ነገሮች እያስታወስኩ አሁንም ማስታወሻ ደብተሬ ላይ ማስፈር ጀምርኩ
3ኛ በመጨረሻ ደግሞ ለእግዚአብሄር ጸልዬ ያልሆኑ ነገሮች በተለምዶ ያልተመለሱ ጸሎቶች የሚባሉት ፤ በጊዜ ሂደት የሚፈቱ
አሁን ያላገኘናቸው ማለት ነው፡፡ እነዚያን ሁሉ አሰፈረኩ፡፡
ከዚያም መደመር መቀነስ ጀመርኩ፡፡ ጌታ በዚህ
አመት ከህመም አስመልጦኝ ፤ ወረቀት ላይ የጸሎት ርእስ ጽፌ ይሄን ጉዳይ በዚህ ጊዜ አደረገልኝ ያንን ደግሞ ቆይቶ እያልኩ ብዙ
ሀሳብ ሳወጣ ሳወርድ የመጨረሻው ውጤት ላይ ደረስኩ፡፡ በነገራችን ላይ የማወራው በስጋ ስለሚደረጉልን በረከቶችም ጭምር ነው የማወራው፡፡ እናም በመጨረሻ
እኔ እስከማስታውሰው ድረስ ብዙዎቹን የህይወቴን ሂደት የመመዝገብ የመሰነድ ብሎም በጽሁፍ የማስቀመጥ ግምቶችን በትክክል የማስታወስ
ችሎታ ስላለኝ በህይወቴ የተመለሱ ጸሎቶቼን በትክክል አውቃቸዋለሁ፡፡ እና ም የተመለሱት ጸሎቶቼ በቁጥር ወደ 113 ሲጠጉ ጌታ ሳይጸልይ
በራሱ መንገድ ያሳካቸው እና እኔንም የገረሙኝ ብዙ ሊሆኑቢችሉም ወደ 78 ነገሮችን ዘረዘርኩ፡፡ ከዚያም ያልተመለሱ ጸሎቶች ደግሞ
4 ብቻ ሆኑ፡፡ ገረመኝ፡፡ የእውነት ደነቀኝ፡፡ የሰው ልጅ ለካ በምድር ላይ ሲኖር ሁሌም ይሰጠዋል፡፡ ሁሌም ሳይጸልይ የሚያስብለት
ለካ አለ እንድል አድርጎኛል፡፡ እግዚአብሄር የንድፈሀሳብ አምላክ አይደለም፡፡ በተግባር ነገርን አሳይቶ የሚባርክ ነው፡፡ ከእርሱ
በሆነው በረከት ስንደሰት ይደሰታል፡፡ ዋናው አላማው ጌታ ሰዎችን ወደ ራሱ ማምጣት ነው፡፡ እናም ያ ሁሉ ነገር ተደርጎልኝ፤ እኔ
ጠንካራው ሰው ብዬ ልኮፈስ አልችልም፡፡ በእያንዳንዱ ህይወቴ ላይ የእግዚአብሄር እጅ አለበት፡፡ የእኔ አቅም ይህንን ሁሉ ለመስራት
የሚችል አይደለም፡፡ እርግጥ ነው ሰነፍ አይደለሁም፡፡ ግን ደግሞ በዚህ 5 አመት ውስጥ በኑሮዬ እና በስራዬ ላይ ለመጣው ትልቅ
ለውጥ የእኔ ሚና በጣም ኢምንት ነው፡፡ ስለዚህ ከእያንዳንዱ ነገሬ ጀርባ ሳይሆን ጎን ጌታ አለ፡፡ በተለይ ጌታን ካገኘሁበት ከግንቦት
20 2001 ጀምሮ ነገሮች ተአምራዊ መሆን ችለዋል፡፡ በ12 አመት ከወር የጌታ ቤት ቆይታዬ ብዙ ተደረገልኝ እንጂ ከማመስገን በቀር
ለጌታ አንድም ቀን ውለታውን መልሼለት አላውቅም፡፡ እርሱ ያደረገልኝን ያህል ስጸልይ እንደሰማኝ ሁሉ ሲፈልገኝ አቤት ብያለሁ ወይ?
ጌታ ያውቃል- ግን አይመስለኝም፡፡ለጌታ ይህ ያስፈልገዋል ብዮ ልክ እርሱ ይህ ነገር ያስገልገዋል ብሎ እንዳሟላልኝ ሁሉ ጌታን ዋና
ከፍዬ አገልግየዋለሁ ወይ? ጌታ ያውቃል -ግን አይመስለኝም፡፡ለጌታ ምንም ሳላደርግለት ሁሉን አደረገልኝ፡፡ የህልሜ ዋና የሆነውም ራእይ ያስታጠቀኝም እርሱ ነው፡፡
‹‹…..ስለዚህ ጌታ ሆይ ለምህረትህ አመሰግናለሁ፡፡ ስለ ሰጠኸኝ ራእይ አመሰግንሀለሁ፡፡
ስላሳካህልኝ አንተ ክብሩን ውሰድ ፡፡ እኔ የለሁበትም፡፡›› በማለት ዛሬ ከጌታ ጋር ላወራ ጀምሬአለሁ፡፡ እናላችሁ እኔን የምታደንቁ
፤ ወይም በእኔ የምትደነቁ ሁሉ ሀይል የሰጠኝን ባስተዋውቃችሁ ደስ ይለኛል፡፡ በክርስትናዬ ደስ የሚለኝ እንዲህ አይነት ጌታን የማመስገን
እድል ስላገኘሁ ነው፡፡ ይህን እድል ሁሌም ስለምጠቀም ጌታ ከበረከቱ አጉድሎኝ አያውቅም፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ