129. ዳኜ አበበ

 ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በፊልም ፤ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ  1000 ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፣ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ5 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከቴአትር ዘርፍ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለትም ዳኜ አበበ ነው፡፡

 ውልደትና አስተዳደግ

ውልደቱ እና ዕድገቱ እጅግ በባህል ክምችት በዳበረው ጎጃም፣ የታላቁ ዓባይ መፍለቂያ ግሽ ዓባይ ዙሪያ በምትገኝ የገጠር መንደር ውስጥ ነው፡፡ ለቤተሰብ የመጀመሪያ ልጅ በመሆኑ ብዙ የኃላፊነት ጫናዎችን ለመሸከም በመገደዱ እና ጫናዎቹን አሸንፎ ወደፊት መራመድ የግድ ነበር፡፡ ከአርሶ አደር ቤተሰብ እንደመገኘቱ፣ የግብርናውን ዘርፍ እንዲያግዝ እና አብዛኛውን ጊዜውን ሥራ ላይ እንዲያሳልፍ በቤተሰብ በኩል የነበረው ግፊት ቀላል አልነበረም፡፡  ከትምህርት ገበታ ጎን ለጎን ለቤተሰቡ ያደርግ የነበረው እገዛ እጅግ ከፍተኛ ነበር፡፡ ብዙውን ሰዓት ከሚሸፍነው የቤተሰብ እገዛ ለጥናት የሚያውላት ጊዜ ኢምንት ነበረች፡፡ በመሆኑም በትምህርቱ ላይ የነበረው አሉታዊ ተፅዕኖም በጉልህ የሚታይ ነበር፡፡

     የትምህርት ጉዞ

ዕድሜው ለትምህርት እንደደረሰ ከቤተሰብ እገዛው ጎን ለጎን ዕውቀትን ለመቅሰም ወደ ትምህርት ገበታ አመራ፡፡ ከአንድ ሰዓት በላይ የእግር ጉዞ በሚጠይቀው አጉት አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን (1-8) ተከታትሏል፡፡ በወቅቱ በማህበረሰቡ ዘንድ ቀደም ብሎ በትምህርቱ ዘርፍ በምሳሌነት የሚጠቀስ፣ እንደ ሞዴል የሚታይና የሚያበረታታ ባልነበረበት ለትምህርት የነበረው ፍላጎት እጅግ ከፍተኛና ቁርጠኛ ነበር፡፡ ሆኖም፣ በጥረቱና በትጋቱ የሚመሰገነው ዳኜ ህልሙን ለማሳካት ከ8ኛ ክፍል የሚያረካና ከፍተኛ ውጤት በመያዝ ከቤተሰብ ራቅ ወዳለ ከተማ ለመከታተል ወደ ቲሊሊ አጠቃላይ ሁለተኛና መሰናዶ ትምህርት ቤት በማመራት ከ9-12ኛ ድረስ ተከታትሏል፡፡ በእነዚህ የትምህርት ጊዜያት ከፊት ተሰላፊና ቀዳሚ ተወዳዳሪ ስለነበር ከፍተኛ ውጤት በማምጣት በ2002 ዓ.ም ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በቴአትር ጥበባት ትምህርት ዘርፍ (BA in Theatre Arts) ትምህርቱን ተከታትሏል፡፡ በተመደበበት ትምህርት ክፍል እንዲሁም ከኮሌጅ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ በእጅግ ከፍተኛ ማዕረግ እና የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ በመሆን በ2004 ዓ.ም የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ከዚያም በዚሁ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት በረዳት ምሩቅነት በመመደብ በ2007 ዓ.ም በቴአትር እና ልማት (Theatre and Development) የማስተርስ ዲግሪውን ተከታትሎ በከፍተኛ ውጤት አጠናቋል፡፡

የወሰዳቸው ዋና ዋና የትምህርት ዘርፎች

በመጀመሪያ እና ሁለተኛ ዲግሪ ከተከታተላቸው ዋነኛ የትምህርት ዓይነቶች መካከል፡- ትወና፣ ዝግጅት፣ ፅህፈተ-ተውኔት፣ ሂስ፣ ማስሜዲያ፣ ህዝብ ግንኙነት፣ የምርምር ዘዴ፣ ቴአትር ለልማት፣ ስለ ዓለም ቴአትር፣ ሌሎችም  እና የቴአትር እና ልማት ኮርሶችን ያጠቃልላል፡፡

     የሥራ ልምድ

ከ2005 ዓ.ም ጀምሮ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ቤት ውስጥ በመምህርነት እያገለገለ የሚገኝ ሲሆን፣ በዋናነት ስለ ዓለም እና የኢትዮጵያ ቴአትር ታሪክ፣ ፅህፈተ-ተውኔት/የተውኔት ድርሰት አፃፃፍ ዘዴ (ድራማቲክ ቴክኒክስ)፣ የሬዲዮ ተውኔት፣ ትውፊታዊ ድራማ፣ ቴአትር ለልማት እና ሌሎችንም የትምህርት ዓይነቶች በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡

በአስተዳደሩ ዘርፍ፣ በትምህርት ክፍሉ ውስጥ የፅህፈተ-ተውኔት ክፍል ኃላፊ (Play writing Unit Head)፣ የማስተርስ ፕሮግራም ትምህርት አስተባባሪ (Graduate program co-ordinator)፣ የተማሪዎች ጉዳይ ኮሚቴ እና ሌሎችም ኃላፊነቶች ላይ ሰርቷል፤ አሁንም እየሰራ ይገኛል፡፡

    ተጨማሪ ኪነ-ጥበባዊ እንቅስቃሴዎች

ከማስተማሩ ጎን ለጎን በተለይም የተለያዩ የመድረክ እና የሬዲዮ ድራማዎች ላይ በመሪ ተዋናይነት ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል፡፡ ከመድረክ ቴአትሮች መካከል፡- አፋጀሽኝ፣ ሀገር ማለት፣ ከል የሚያስጥል፣ የካቲት 12፣ ጎህ ሲቀድ፣ ምኒልክ እና ኦቴሎን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የተለያዩ የተሳተፈባቸው፣ በኤፍ ኤም እና በኢትዮጵያ ሬዲዮ ከተላለፉ የሬዲዮ ድራማዎች መካከል የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክት በሆነውና ከሁለት ዓመት በላይ በዘለቀው ተከታታይ ድራማ (Serial Drama) ዋናውን ገፀ-ባህርይ በመወከል በብቃት ተጫውቷል፡፡ 

ለህትመት ካልበቁ የእጅ አሻራዎቹ (ሥራዎች) መካከል፡- አባ ኮስትር፣ አባይ እና ውርሱ (በጋራ)፣ ውቤ (ሙዚቃዊ ድራማ)፣ የአለቅቶች እድር እና ካስማ ምላሽ (አሀዱአዊ ተውኔቶች)፣ ምርኩዜ (ባለ አንድ ገቢር ተውኔት) እና የፊልም ጽሑፎችም ይገኙበታል፡፡

        ጥ ናትና ምርምር (ሕትመት)/አለማቀፋዊ ኮንፈረንስ

ዳኜ ከመማር ማስተማሩ ውጪ በተለያዩ አለማቀፋዊ ጥናታዊ አቅርቦቶች ጉልህ ተሳትፎን እያደረገ ያለ ተመራማሪ ነው፡፡ በተለይም በየዓመቱ በሚካሄዱ የኮሌጅ ኮንፈረንሶች ላይ የተላያዩ ርዕሠ-ጉዳዮችን የሚዳስሱ የምርምር ሥራዎችን በማቅረብ ትልቅ አስተዋፅዖ እያደረገ ይገኛል፡፡ በተጨማሪም ሥራው ውስጥ እጅግ ጉልህ ቦታ ያላቸውን በጥናትና ምርምር የተሰሩ ለዩኒቨርሲቲ፣ ለኮሌጅ፣ በአጠቃላይ ለኪነ-ጥበብ ተማሪዎች ማስተማሪያነት፣ ለተመራማሪዎች፣ ለተለያዩ አንባቢያን የሚሆኑ ‹‹የኢትዮጵያ ቴአትር እና ሥነ-ፅሁፍ ታሪክ ከልደቱ እስከ ዕድገቱ›› እና ‹‹የኢትዮጵያ ቴአትር፣ ልደት-ዕድገት›› የተሰኙ በመስኩ ትልቅ ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ዳጎስ ያሉ መፅሀፍትን በማሳተም ለንባብ አብቅቷል፡፡ ‹‹ንጉሥ ተክለ ሃይማኖት›› የተሰኘ ታሪካዊ ተውኔትንም በማዘጋጀት በሕትመት ሂደት ላይ ይገኛል፡፡

ዳኜ አበበ በአሁኑ ሰዓት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቴአትር ጥበባት ትምህርት ክፍል ውስጥ በመምህርነት እየሰራ የተለያዩ የምርምር ሥራዎችን እያካሄደ ይገኛል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች