💜























         133. ቡልቻ ደመቅሳ ሰንበቶ-bulcha demeksa senbeto

 ❤❤

ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን ለሀገር የሰሩ ሰዎችን ግለ-ታሪክ በዚህ ድረ-ገጽ ላይ እየሰነደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ እነዚህ ግለ-ታሪካቸውን የምንጽፍላቸው ሰዎች ኢትዮጵያን ጠንክረው ያገለገሉ ሲሆኑ ለብዙዎችም አርአያ የሆኑ ናቸው፡፡ ከእነዚህ አንዱ ደግሞ ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ እኒህ ታላቅ ኢትዮጵያዊ በምጣኔ ሀብት ባለሙያነታቸው ከንጉሱ ዘመን ጀምሮ ያገለገሉ ታላቅ ሰው ናቸው፡፡ ስለ አቶ ቡልቻ በእንግሊዝኛ ቋንቋ አንድ የግለ-ታሪክ መጽሀፍ ታትሞ ለንባብ የበቃ ሲሆን በበርካታ መገናኛ ብዙሀንም አበርክቷቸው በጉልህ ተጽፏል፡፡ የዚህ ግለ-ታሪክ አሰናጅ ዮአኪን ዳንኤል የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ቤተሰብን፤ የቅርብ ሰዎችን በማነጋገር ይህን ግለ-ታሪካቸውን እንድታነቡ ጋብዛለች፡፡  

         ትውልድ እና እድገታቸው

በምእራብ ወለጋ ዞን በቦጂ ብርመጂ ወረዳ   በ ጊንቢ ዞን   አባታቸው አቶ ደመቅሳ ሰንበቶ እና ከእናታቸው ነሲሴ ሰርዳ 1923 . ተወለዱ፡፡

አቶ ቡሌቻ ደመቅሳ የቤተሰቡ 4 ልጅ እና ብቸኛ ወንድ ልጅ ናቸው፡፡ ክቡር አቶ ቡልቻ   አባታቸውን በልጅነት በሞት ቢያጡም አጎታቸው ጎቡ ሰንበቶ እንደ አባት ሆነው የወንድማቸውን አደራ ተቀብለው    ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ አድርገውላቸዋል ፡፡

      የትምህርት ህይወታቸው

የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጊንቢ  አድቬንቲስት  እንዲሁም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በኩየራ አድቬንቲስት ተምረዋል፡፡ በወቅቱ ምንም እንኳን ከፍተኛ ውጤት በማምጣት  ትምህርታቸውን ቢያጠናቅቁም ከመንግስት ትምህርት ቤት  ተከታትለው ካጠናቀቁ ተማሪዎች ውጭ  ወደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመግባት እድል አይገኝም ነበር፡፡ 

ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ  ግን  የቀድሞ የዩንቨርሲቲ አስተዳዳሪዎችን ዶክሜንታቸውን በማሳየት እና በማናገር ተቀባይነትን አግኝተው ወደ አራት ኪሎ ዩንቨርሲቲ በመግባት የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በመከታተል በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ከፍተኛ ውጤት በማምጣትም ተመርቀዋል፡፡

ዩንቨርስቲው ከፍተኛ ውጤት በማምጣት ለተመረቁ 10 ተማሪዎች  መካከል አንዱ በመሆን ወደ አሜሪካ  በመሄድ  በ ሲራኪዩዝ  ዩንቨርሲቲ ውስጥ ተመድበው ትምህርታቸውን ተከታትለው ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል፡፡

ትዳር እና ህይወት

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ  ከቀድሞ ባለቤታቸው ገና የ 18 አመት ወጣት  እያሉ ነበር  ከ ትዳር አጋራቸውን አዲስ አበባ ውስጥ የነርሲንግ ተማሪ የሆነችውን መንበረ ዱጉማ ጋር የተጋቡት፡፡ አቶ ቡልቻ እና መንበረ በ 26 አመታቸው የ አምስት ልጆች ወላጆች ነበሩ ፡፡ ከሁለተኛ ባለቤታቸው ከሆነችው  ወ/ሮ ሄለን ገ/እግዚያብሄር ጋር  ለስራ ምክንያት ወደ ግብጽ ሀገር በሚመላለሱበት ወቅት ነበር የተገናኙት ፡፡ አቶ ቡልቻ እና ወ/ሮ ሄለን አብረው በቆዩበት 50 የትዳር ዓመት አንድ ልጅን በመውለድ በአጠቃላይ የስድስት ልጆች አባት እንዲሁም  አስራ አንድ የልጅ ልጅ አያት  ሆነዋል፡፡ 

 

 

           የስራ ዘመን ታሪክ

ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ በመምህርነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ በገንዘብ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ውስጥ በበጀት ዳሬክተር እንዲሁም ምክትል የገንዘብ ሚኒስተር በመሆን  አገልግለዋል፡፡ በወቅቱም በ ዳግማዊ ቀዳማዊ ንጉሰ ነገስት ሀይለስላሴ እጅግ የሚወደዱ እና ቅቡልነት ያላቸው ሰው ናቸው፡፡ የደርግ መንግስት ስልጣን ላይ ሊወጣ አከባቢ የፋይናንስ ሚንስቴር መስሪያ ቤቱን ለቀው ወደ ሀገረ አሜሪካ ሄደው ነበር ፡፡ ደርግ የስልጣን መንበሩን  እንደ ተቆጣጠረ ወደ 60 የሚጠጉ ባለስልጣናትን እና ሙሁራንን ሲገድል የሳቸው ባልደረቦችን በማጣታቸው በእጅጉን ያዝናሉ፡፡ በዩኤን ዲፒ እንዲሁም  በአለም ባንክ 20 አፍሪካ ሀገራትን ወክለው ሰርተዋል፡፡

 

           የምጣኔ ሀብት አበርክቶ

ከደርግ ውድቀት በኋላ ወደ ሀገራቸው  ከ17 አመት የውጭ ሀገር ቆይታ በኋላ ወደ ሀገራቸው ተመልሰው  ቀጥለዋል፡፡  

ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከምጣኔ ሀብት አበርክቷቸው  አዋሽ ባንክ እንዲቋቋም እና እውን ያለበት ደረጃ ላይ እንዲደርስ የባንኩ መስራችና ፕሬዚዳንት በመሆን ረዘም ላለ ጊዜ ካለ ክፍያ ሰርተዋል፡፡ በተጨማሪም የባንኩ ቦርድ አባል በመሆን አገልግለዋል፡፡  የራሳቸውን አስተዋጽኦ

     የፖለቲካ ታሪክ

በሀገራችን  ዲሞክራሲ እንዲስፋፋ በፖለቲካው ዓለም ተሰማርተው የራሳቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡  እንዲሁም የኦሮሞ ኮንግረስ ፓርቲ ውስጥ በመሳተፍ እና ምርጫ በመወዳደር  አሸንፈው ፓርላማ በመግባት የወቅቱ ጠቅላይ ሚንስተር የነበሩትን አቶ መለስ ዜናዊን በመተቸት ና ሀሳባቸውን በነጻነት በመሰንዘር ይታወሳሉ፡፡

ሀገርን መውደድ ፣ ማንነትን ማክበር  ፡ ሀቀኝነት ሰው ወዳድነት፡ ሩህሩህነት የእርሳቸው መገለጫ ጭምር ነው፡፡

 

 

 

የቅርብ ሰዎች አስተያየት

ወ/ሮ ሄለን ገ/እግዚአብሄር

ባለቤት

እኔ ግብጽ ሀገር ሆኜ ኢትዮጵያን ኤምባሲ ውስጥ እሰራ ነበር፡፡እርሱ ደግሞ ካይሮ ለኮንፈረንስ  ከመጡ ልኡኳን መካከል አንዱ ነበር፡፡ ከእህትሽ መልእክት መጥቶልሻል  ከኢትዮጵያ አለኝ፡፡   በወቅቱ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ምክንያቱም አለም አቀፍ የስልክ ልውውጥ ስላልነበረ እጅግ በጣም ደስ አለኝ፡፡ የመጣልኝ መልእክት ለመቀበል ቸኮልኩኝ፡፡ እሱ ከስብሰባ እንደጨረሱ ‹‹…ቡና እንጠጣ›› አለኝ፡፡ እሺ ብዬ ቡና እየጠጣን ‹‹…ስለ አንቺ ብዙ የሰማሁት ጥሩ ነገር አለ›› አለኝ››  ፡፡ ቀጥሎ ስለ እራሴ ልንገርሽ አለኝ እኔ ደግሞ በልቤ እዩ ሁሉ ምንያስፈልጋል እያልኩ አዳመጥኩት ፡፡ ስለ ራሱ ከነገረኝ በኋላ መልእክት አልመጣልሽም አለኝ ትውውቃችንን እንዲህ ጀምረን አብረን በብዙ ውጣውረድ ውስጥ አልፈን 50 የትዳር አመታትን አብረን ኖረናል፡፡  የፓርላማ አባል ሆኖ ላመነበት ሀሳብ ሲሟገት  ነበር፡፡ እኔም እንደ ባለቤት በምችለው ሁሉ ከአጠገቡ ሳልለይ እረዳው ነበር፡፡

ሰው በመርዳት ያምናል ፡፡ የተቸገረ ሰው ካለ አቅሙ የፈቀደውን ሁሉ ያደርጋል፡፡

ልጅ

ብስራት ብልቻ

አባቴ እራሱንም ለመደገፍም ይሁን ቤተሰብን ለመደገፍ እያስተማረ መማር ነበረበት፡፡ እንግሊዘኛ ቋንቋ ቶሎ ስለለመደ ከሚሲዬኖች ጋር በማስተርጎም ስራ እየሰራ ትንሽ ደሞዝ እያገኘ እራሱን እየደገፈ ያስተምርም ነበር፡፡አባቴ ሀቅ የሚናገር ቅጥፈትን የሚቃወም እውነት ተናጋሪ ነው፡፡

አባቴ ውጭ ሀገር ሆኖ የረር ተራራን ማየት ሁሌም ይናፍቀው ነበር፡፡

 

አቶ ለይኩን ብርሃኑ

የቀድሞ የብሄራዊ ባንክ ገዥ እና የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት የነበሩ

በአካባቢያችን እንደ አርአያ ከሚታዩና እና ከተማሩ  ሰዎች መካከል አቶ ይልማ ዴሬሳ እና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡  እኛ ልጅ ሆነን እነርሱን እንደ አርአያ እያየን ነው ያደግነው፡፡  ታንዛኒያ ሀገር ለአንድ ስብሰባ ሄጄ  ስብሰባችንን እንደ ጨረስን  ቡና እየጠጣን አንድ ኢትዮጵያዊ እኮ አለ አለን፡፡ አዎ ብዙ ኢትዮጵያዊያን እኮ እዚህ ሊኖሩ ይችላሉ አልኩት፡፡ ቀበል አለኝ እና አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የሚባል ሰው ታውቃለህ አለኝ ፡፡ በመገረም እርሳቸውን ከልጅነት ጀምሮ በዝና ነው የማውቀው አልኩት፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ አቶ ቡልቻን በአካል ያወኩት ያኔ ነው፡፡ ያኔ የጀመረው ግንኙነታችን እስካሁን ድረስ የተለያዩ ስራዎችን አብረን በመስራት በተጨማሪም ቤተሰብ ሆነን ቀጥለናል፡፡  ያገራችን ኢኮኖሚ እንዲያድግ የራሱን አስተዋጽኦ  አበርክቷል፡፡ በተለይ በግሉ ዘርፍ ባንኮች ብዙም ባልነበሩበት ወቅት እርሳቸው ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን አዋሽ ባንክ እንዲከፈት እና እንዲስፋፋ የራሱን አስተዋፆ አበርክቷል፡፡

 

ሶፍያ ይልማ

ቤተሰብ

 በወቅቱ አባቴ የገንዘብ ሚኒስቴርን ዘመናዊ እንዲሆን የተማሩ ሰዎችን ከያሉበት እያሰባሰበ  ነበር ፡፡ ከነዚህ ሰዎች መካከል አቶ ቡልቻ ደመቅሳ አንዱ ነበር ፡፡ የገንዘብ  ሚኒስቴር ዘመናዊ እንዲሆን መስሪያ ቤቱን ባገለገሉበት ወቅት የራሳቸውን አስተዋጽኦ አሳርፈዋል፡፡

ወ/ሮ እሌኒ ከበደ

የቀድሞ ፀሃፊ

አቶ ቡልቻ እና እኔ ትውውቃችን  ገንዘብ ሚኒስቴር ውስጥ ፀሃፊ በነበርኩበት ወቅት ነበር፡፡ ያኔ እንደ እርሳቸው እንደ አለቃም እንደ ቤተሰብም ሆነን አብረን ሰርተን ነበር፡፡ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በወቅቱ በነበሩት ንጉስ እጅግ ተቀባይነት ያላቸው እና ገንዘብ ካለ አግባብ እንዲወጣ የማይፈቅዱ ስራቸውን በአግባቡ የሚሰሩ እና ሰው አክባሪ ሰው ናቸው፡፡ የዛን ጊዜ የጀመርነው  ቤተሰባዊነት እስከ አሁን ድረስ አብረን ዘልቀናል፡፡ ጥሩ ቤተሰቦቼ ናቸው፤ በሰርግም በለቅሶም ቢሆን ከነ ሙሉ ቤተሰባቸው እንጠያየቃለን፡፡

ሉሲ  ገ/እግዚሃቤር

ቤተሰብ

 ጋሼ ሀገሩን የሚወድ ሰው አክባሪ ባህሉን የመጣበትን ማህበረሰብ የሚያከብር እና የሚያስከብር ሀሳብ ያለው ሰው ነው፡፡ እኔም ልጅ እያለው ትምህርታችን ላይ እንድንበረታ ጠንክረን እንድናጠና የራሱን አስተዋፆ  አበርክቷል፡፡ እኔም አውን አስተማሪ ነኝ፡፡ እሱ አንብቡ አጥኑ ስለሚል ያኔ የጀመርኩት ጥናት አስተማሪነትን እንድወደው እና እንድሰራበት የጋሼ አስተዋፆ ቀላል አይደለም፡፡

 

 

ኢ/ር ተረፈ ራስ ወርቅ

ጓደኛ

 አቶ ቡልቻ ክርክር የሚወድ ያለውን ሀሳብ በስርኣት የሚያስረዳ ሰው ነው፡፡የገዳ ስርኣትን እንድማር እና እናዳውቅ ለመጀመርያ ጊዜ ያስተማረኝ አቶ ቡልቻ ነበር፡፡

ኢ/ር እሸቱ አበበ

ጓደኛ

አቶ ቡልቻ ወለጋ ጊንቢ ተወልዶ ይደግ እንጂ የወለጋ ልጅ ብቻ አይደለም የመላው ኢትዮጵያዊ ልጅ ነው፡፡ሁሌ ሳስበው ኢትዮጵያ በሚለው ሀሳብ ነው ፡፡ ሁሉን ነገር ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊያን የሚል ሀሳብ ነው ያለው፡፡

አቶ ሙላቱ ገመቹ

የኦሮሞ ፌደራሊስት  ኮንግረስ ፓርቲ ም/ሰብሳቢ

የኦሮሞ ፓርቲዎች ባልተስፋፉበት ወቅት አቶ ቡልቻ ፓርቲ አቋቁመው ለኦሮሞ ህዝብ ድምፅ ለመሆን ጥረዋል ፡፡ ፓርላማ ውስጥም በመግባት ሃሳባቸውን በነጻነት ሲናገሩ ልክ ያልሆነን ሀሳብ ሲተቹ ነው የማውቃቸው፡፡ አቶ ቡልቻ እስከአሁን ድረስ አቅማቸው የፈቀደውን ሁሉ ፓርቲያችንን እየደገፉ እና እየረዱ ይገኛሉ፡፡ እኔ ሰው ወዳድና እውነት ተናጋሪ ከምላቸው ሰዎች መካካል አንዱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ናቸው፡፡ የአዋሽ ባንክ ሲቋቋም እርሳቸው ካለ ክፍያ ረዘም ላለ ጊዜ በነጻ በማገልገል ባንኩ አሁን ያለበትን አቋም እንዲይዝ የራሳቸውን አበርክቶ አበርክተዋል፡፡ ይህ ከፖለቲካው ባሻግር ለሀገራችን ምጣኔ ሀብት የራሳቸውን አስተዋጽኦ  አድርገዋል፡፡

 

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ላበረከቱት አስተዋጽኦ  ስጦታ ተበረክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ እና አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር በጋራ ባዘጋጁት ሥነ ስርዓት ላይ ለአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ለገጣፎ በሚገኘው በመኖሪያ ቤታቸው ተገኝተው ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡

91 ዓመቱ አዛውንት ስጦታው የተበረከተላቸው ለሀገራቸው በምጣኔ ሃብት ዘርፍ ላበረከቱላት የረዥም ዘመን አገልግሎት ነው፡፡  ሰኔ 25 2014 ነበር እውቅና ያገኙት፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በቅርስነት የሚያዝ የልዩ ታሪካዊ ሁነቶች ማስታወሻ የወርቅ ሳንቲም በመሸለም የወርቅ ካባም አልብሷቸዋል፡፡

አዋሽ ኢንተርናሽናል ባንክ  ደግሞ የምስጋና የምስክር ወረቀት እና የወርቅ ሜዳሊያ አበርክቶላቸዋል፡፡

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ የአዋሽ ባንክ ፕሬዚዳንት አቶ ፀሐይ ሽፈራው የአቶ ቡልቻ ደመቅሳ ባለቤት ወይዘሮ ሔለን ገብረእግዚአብሔርና ሌሎችም ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ጊምቢ በሚገኘው ደጃዝማች ገብረእግዚአብሄር ተማሪ ቤት  የተከታተሉ ሲሆን 2 ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሻሸመኔ የሚሽን ተማሪ ቤት ተከታትለዋል፡፡  አቶ ቡልቻ  ከአሜሪካን ሀገር 1953 የማስተርስ ዲግሪያቸውን በኢኮኖሚክስ ካገኙ በኋላ  በገንዘብ ሚኒስቴር ረዳት ሚኒስትር በመሆን  አቅምና እውቃታቸውን ከሀገራቸው አውለዋል፡፡ 1955 በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የህግ ፋክሊቲን በመቀላቀልም  1959 በዲግሪ ለመመረቅ ችለዋል፡፡ ክቡር አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከህግ ትምህርት ቤት ሲመረቁ  በጊዜው የታተመውን ሚዛንና ሰይፍ የተሰኘውን የተማሪዎች የምረቃ መጽሄት እንዳየነው ከሆነ  ከአቶ ቡልቻ ጋር እንደ አቶ አበበ ወርቄ ክቡር አቶ አበራ ጀንበሬ እና  በደርግ ዘመን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት ብርሀኑ ባይህ  የመሳሰሉ ሰዎች አብረዋቸው የተማሩ ነበሩ፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ኢትዮጵያን ወክለው በዓለም ባንክ ውስጥ የቦርድ አባል ሆነውም ሰርተዋል፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ 90 ዓመቱ ፖለቲከኛ የሃገሬ ጉዳይ ያሳስበኛል ይላሉ

Comment(0)  672 Views

– ‹‹ዐቢይን የደገፍኩት መዝኜ አስተውዬ ነው››

ምርጫውን ለማካሄድ መጀመሪያ አንድ መሆን ይፈልጋል

ሕዝቡን ከፋፋይ ንግግር ከልሂቃኑ አይጠበቅም

 

ከፖለቲካ ራሳቸውን አግለው በጡረታ ላይ የሚገኙት የቀድሞ የተቃዋሚ ፓርቲ መሪና የአዋሽ ባንክ መስራች አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ሰሞኑን ድንገት በጠ/ሚኒስትሩ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ተገኝተዋል፡፡ እንዴት? ለምን? ከጋዜጠኛ ሠላም ገረመው ጋር ተነጋግረዋል፡፡ እነሆ፡-

 

በለገጣፎ የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት እንዴት ነው?

እኔ በምኖርበት አካባቢ ማንም ስለ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ክፉ የሚያወራ የለም፡፡ ሁሉም ይወዷቸዋል፤ ያከብሯቸዋል፡፡ ይሄ ሁሌም ነው የሚገርመኝ፡፡

/ ዐብይ ሀገር መምራት ከጀመሩ አንስቶ አይተናቸዋል፡፡ ብቃት አላቸው፤ እንዲመረጡም እንፈልጋለን፡፡ ለዚህ ነው የወጣነው፡፡ ሰልፉን ለማድረግ መጀመሪያ ላይ ትንሽ እንሆናለን ብዬ አስቤ ነበር፤ ነገር ግን ከመጠን ያለፈ ነው የሆነው፡፡

ይሄ ሠልፍ እንደውም ከዚህ በፊት መደረግ ነበረበት ባይ ነኝ፡፡ ዐቢይ እውነተኛ ሰው ነው፤ ይሄንን ስለማውቅ ነው ለመደገፍ የወጣሁት፡፡ እኔ በርካታ የፖለቲካ አመራሮችን አይቻለሁ፤ ለማንም የድጋፍ ሠልፍ ወጥቼ አላውቅም፤ መዝኜ አስተውዬ ነው የደገፍኩት፤ በጣም ቅን ሠው ነው፡፡

 

 

/ሚኒስትሩን አግኝተዋቸዋ ያውቃሉ?

ከዚህ ቀደም ተገናኝተን አውርተን ነበር፡፡ አንዳንድ ነገሮች ላይ ተወያይተን ምክር እፈልጋለሁ ከእርስዎ ብለውኛል:: አንዳንድ ጊዜ የሚፈሉጓቸው ነገሮች ሲኖሩ ይጠይቁኛል፤ መመለስ ያለብኝን እመልስላቸዋለሁ፡፡ በቅርብ ጊዜ ባይሆንም ተገናኝተን እናውቃለን፡፡

 

የአገሪቱን የፖለቲካ አካሄድ እንዴት ያዩታል?

በጣም አሳሳቢ ነው፡፡ እንደሚሰበር ዕቃ በጥንቃቄ መያዝ አለበት፡፡ ዋናው ያለመተዋወቅ ነው፡፡ አፄ ኃይለስላሴ ከልጅነታቸው ጀምሮ ይታወቃሉ፡፡ በእሳቸው ጊዜ ማን ማንን እንደሚክድ፣ ማን ማንን እንደሚያምን ይታወቃል፡፡ ከልጅ እያሱ ጋር ተናንቀው ግልፅ በሆነ የፖለቲካ ታክቲክ አሸንፈዋል፡፡ አፄ ኃይለስላሴ በብልጠት በዕውቀት ነገርን በመረዳት መውጫውን ቀድሞ በማወቅ ነበር ስልጣንን የያዙት፡፡ አሁን ያለው አካሄድ በጣም አደገኛ ነው፡፡ ወጣቱ በሚያውቀው ፖለቲካ ውስጥ እስካሁን ጠቢብ የሆነ፣ ሁሉንም የሚፈታ መሪ አልነበረም፡፡ ‹‹ይሄንን አደረኩ፤ አግባብቼ አስታረቅኩ፤ ይቅርታ አደረግሁ፤ ይሄንን ለአገር አበረከትኩ›› የሚል እንደ አፄ ኃለስላሴ አልነበረም፤ ስለዚህ ሁሉም ይናናቃል፤መከባበር የለውም፤ ሌላው ቀርቶ መንግስቱ እንኳን ይላሉ ሰዎች መንግስቱ እንኳን ቆራጥ ሆኖ አገሩን አረጋጋ፤ በብዙዎች ተፈራ…” እያሉ ያወራሉ፡፡ ይሄ ማለት መግደል ጀግና ያስብላል፤ መግደል አገርን መምራት ቀላል ያደርጋል ማለት ነው፡፡ በርግጥ መንግስቱ አይፈሩም፤ ቆራጥ ነበሩ፡፡ በዚህ ምክንያት ግን መንግስቱን ፈርተው ብዙ ምሁራን ሸሽተው አገር ለቀው ተሰደዱ፤ ይሄ አገሪቱ የተማረ ሰው እንድታጣ አድርጓታል፡፡

 

ኢህአዴግ ደግሞ እውቀት የጎደለው አረማመድ ነበር የሚሄደው፡፡ የአፈና ፖለቲካ ውስጥ ገባ፡፡ ህዝቡም ምንም ተስፋ የሚሆን ነገር አጣ፡፡ ምኞት መመኘት ብቻ ሆነ፡፡ ዋጋ የተከፈለበት ነገር ሁሉ ሲጠፉ ህዝቡ ተስፋ እየቆረጠ መጣ፡፡ ለውጥ መጣልን ብለው በደርግ ጊዜ እንደተሰደዱት ሁሉ በኢህአዴግም ጊዜ መሰደድ ጀመሩ፡፡ ኢህአዴግም በገባው ቃል መሰረት መፈፀም ሲያቅተው ህዝቡን በመጫን በሃይል ማሳመን ፈለገ፡፡ ጫናው እየበዛ ሲመጣ ህዝቡም ተቃውሞውን መግለፅ ጀመረ፡፡ ይሄ ህዝብ ያየው በጭቆና መገዛትን ነው፤ በተለይ ወጣቱ፡፡ ስለዚህ አሁን የመጡት /ሚኒስትር አልገልም፤ በመነጋገር ችግር እንፍታ በማለት ከመግደል ይልቅ ይቅርታን፣ ከማሰር ይልቅ መፍታትን ሲያሳዩ ሃሳቡ በጣም ጥሩ ነበር፤ ግን አንዳንድ አመፅን የሚፈልጉ አካላት የሚያስነሱትን ብጥብጥ በፍቅር ሲያልፉና በይቅርታ ሲያሳልፉት ህዝቡ ያለመደው ነገር ስለሆነ ሊቃወም ይችላል፡፡ / ዐቢይ የውጪ ሃገር አመራርን ነው እያሳዩ ያሉት፡፡ ትክክለኛ ዲሞክራሲ የምንለው ማለት ነው፡፡ በርግጥ ለምን እንደማይገድሉ አውቃለሁ፤ ቢሆንም ዲሞክራሲን ሲናፍቅ የነበረ ህዝብ በአንድ ጊዜ ሲያየው ግራ ሊገባው ይችላል፡፡

 

ከውጪ ሃገራት ገንዘብ ለምኖ ሃገርን የሚታደግ መሪ እኛ ሃገር አልነበረም፡፡ ይሄንን ሁሉ አሁን እያየን ነው፡፡ ስለዚህ / ዐቢይ ሰው እንደሚወዳቸው ያወቁ አይመስለኝም፤ ሊያውቁ ይገባል፡፡ ይሄንን ማወቃቸው ምናአልባት ትንሽም ቢሆን ቆንጠጥ ያለ እርምጃ እንዲወስዱ ያደርጋቸዋል፡፡ እሳቸው የኃይል እርምጃ መውሰድ እንደማይፈልጉ አውቃለሁ ግን ማድረግ አለባቸው፡፡

ሌሎች አገራት ያሉት ወጣት አመራሮች ዴሞክራሲያዊ ፖለቲካ የሚያራምዱት ህዝቡ የለመደው ስለሆነ ነው፤ እሳቸው ያንን ለማምጣት መጀመሪያ ማስተማር ይጠበቅባቸዋል፡፡

 

የጠ/ሚኒስትሩ ድክመቶች የሚሉት ነገር አለ?

እሱማ ለሚቃወማቸው አሳልፎ መስጠት ማለት ነው:: መምከር ካለብኝም በግሌ እመክራቸዋለሁ፡፡

 

የአገሪቱን አለመረጋጋት እንዴት ያዩታል?

በጣም ያሳስበኛል፡፡ በተለይ እኔ ባደኩበት ወለጋ በጣም ከባድ ነገር ነው ያለው፡፡ እኔ ያልገባኝ ‹‹በእንደዚህ አይነት አካሄድ የት ይደረሳል? ብለው ነው አኩርፈው ቤታቸውን ዘግተው የተቀመጡት?›› ብዬ ወለጋዎቹን እጠይቃለሁ፡፡ መተባበር ከሌለ፣ ህዝብ ካልተባበረ ምንም ነገር አይረጋጋም፡፡

እኔን ብዙ ሰዎች ‹‹ያለመጠን በዲሞክራሲ ታምናለህ፤ ትደግፋለህ›› የሚሉኝ አሉ:: /ሚኒስትሩ እያሳዩ ያሉት ዲሞክራሲ ግን በእኔ ሃሳብ የበዛ ይመስለኛል፡፡ አፄ ቴዎድሮስ አንድ ልብ ነበራቸው፤ ወደ ኋላ የማይመለሱ ነበሩ፤ አፄ ኃይስላሴም በጣም ተወደው ነበር፤ ሁሉም ለጥ ብለው ነበር የተገዙላቸው፡፡ ቀስ ብለው ግን ኃይለኛ እየሆኑ መጡ፡፡ ከዛ ቀጥሎ የመጡትም መንግስቱ ይለውጣል ተብሎ ሲጠበቅ ሃይለኛ ሆኑ፡፡ ኢህአዴግም አትተንፍሱ እያለ ሃይሉን ያሳይ ነበር፡፡ እነዚህን ሁሉ አይተን አሁን በነፃነት ስንለቀቅ ይከብዳል፤ እሱን ማሰብ ያስፈልጋል፡፡

 

እኔ ግን በዋናነት የሚያሳስበኝ የአንድነት ጉዳይ ነው፡፡ የአማራና የኦሮሞ የቆየ ታሪክን ሊያበላሹ የሚፈልጉት ወገኖችን መስማት የለባቸውም፡፡ ከኦሮሞም ከአማራም የተማሩና ልምድ ያላቸው ሰዎች አሉ፤ እነሱን አነጋግሮ መፍትሄ ማበጀት በጣም ቀላል ነው፡፡ የእኛ ሃገር ጥል ብዙ ውስጥ የዘለቀ አይደለም፡፡ ምክንያቱም አማራ ላይ አንድ ችግር ቢከሰት ኦሮሞው ዝም ብሎ አይተኛም ይተባበራል፡፡ አማራውም እንደዛው፡፡ መቅደም ያለበት ሰላም ነው፤ ኩርፊያቸው ቀላል በመሆኑ በሚደመጡ ሰዎች ማስመከርና መመለስ ይቻላል፡፡

 

ሌላው የትግራይ ጉዳይ ነው፡፡ ትግራይ ስንል ህዝቡን ነው እኔ የምለው፡፡ በስልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ የነበራቸውን ሃይለኝነት ማውራት አይጠቅምም፤ እራስን ለይቶ ማየት የትም አያደርስም፡፡ ስለዚህ ማንም ማንንም ጥሎ ዝቅ አድርጎ አይቶ መኖር አይቻልም፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ አንዱን እራሱን ለይቶ መጓዝ አይቻልም:: እኔ ቀድሜ ስለ ፖለቲካ አውቃለሁና ብሎ መሄዱ አያዋጣውም፡፡ ምክንያቱም ሌሎቹም ዝም ብለው እንጂ የተሻሉ ብዙዎች አሉ፡፡ ለምሳሌ አማራ ውስጥ በጣም ቆራጦች አቅም ያላቸው ሰዎችን እያየን ነው:: እነዚህ ሰዎች ቀድመው ለምን አልወጡም? ለምን ለሃገራቸው አልተቆረቆሩም? ልንል አንችልም፤ ምክንያቱም ቀደም ሲል በነበረው ስርዓት ታፍነው ነበር፡፡ አሁን አንዱ አንዱን እያስተማረ፣ አብረው ነው መጓዝ ያለባቸው::

 

በአገሪቱ እየታየ የመጣው ዘረኝነት መነሻው ምንድነው ይላሉ?

ማንም ህፃን የለም፡፡ ሁሉም አዋቂ ነው:: ለምሳሌ ኦሮሞዎች ወደ ስልጣን ሲመጡ ለምን እንደ ህወሃቶች ይሆናሉ? ዘረኛ በመሆን ህወሃት ምን ተጠቀመ? ለብቻ መሆን ለማን ጠቀመ? ማንን አሳደገ? ይሄ በአገራችን ብዙ ውድቀቶች ሲያመጣ አይተናል፡፡ ዘረኝነት ከፍ አያደርግም፤ መነሻውን ሁሉም ያውቀዋል፡፡

 

ስለ ቀጣዩ ምርጫ ምን ያስባሉ?

ምርጫው ምንም ትርፍ አያመጣም፤ መጀመሪያ መደረግ ያለበት የትግራይ ህዝብና አሁን ያለውን አመራር ማቀራረብ ነው፡፡ ሰዎች ናቸው፤ መልዐክ አይደሉም ያጠፋሉ፤ ይህንን ሊያምኑ ይገባል፡፡ አንድ የትግራይ አመራር አጠፋ ማለት ሁሉም የትግራይ ተወላጅ ጥፋተኛ ነው ማለት አይደለም፡፡ እራሳቸውን አሳምነው ለህዝቡ ሲሉ ወደ አንድ መምጣት መቻል አለባቸው፡፡ የሚጎዳው ህዝቡ ነው፤ ለህዝቡ ሊታዘንለት ይገባል፡፡ እኔ ሳስበው የትግራይ ማህበረሰብ አንድ መሆን ይፈልጋል፤ ገፍቶ የጠየቀው ስለሌለ እንጂ፡፡ ስለዚህ ይህንን ምርጫ ለማካሄድ መጀመሪያ አንድ መሆን ያስፈልጋል፤ የሚረብሹ ነገሮች መጥራት አለባቸው፡፡

የሀገሪቱ የፖለቲካ ልሂቃን ሲዘላለፉ ይታያሉ፡፡ እርስዎ ምን ይመክራሉ?

ሁሉም ቢመከሩ ይሰማሉ፤ አዋቂዎች ናቸው፡፡ ለተፈጠረው ችግር ምክንያቱ ኦሮሞን ከፋፍለው፣ አማራን ከፋፍለው ማየታቸው ነው፡፡

የእኛ እኮ ችግር እንደ ሊቢያ እንደ ሶሪያ አይደለም፤ በጣም ቀላል ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ዋናው ነገር ለህዝቦች የሚነገረው ጥሩ ሊሆን ይገባል፡፡ ለምሳሌ እኔ በጣም ካዘንኩባቸው ንግግሮች አንዱ፣ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ንግግር ነው:: ‹‹አማራ የበላይነቱን ያድሳል›› ሲል ምን ማለት እንደሆነ አይገባኝም፡፡ አማራን እኮ በርካታ ጀግኖች አስተዳድረዋታል፡፡ ግን የማንንም ክብር አልነኩም፡፡

                ምንጭ: አዲስ ማለዳ

  መዝጊያ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን አቋምን የሚያንጸባርቅ ሲሆን የግለ-ታሪኩ አሰናጅም በሀሳቡ ላይ ትስማማለች፡፡

አቶ ቡልቻ ደመቅሳ ከምንም በላይ ኢትዮጵያን ያስቀድማሉ፡፡ ምክንያት አላቸው፡፡ ኢትዮጵያ ታላቅ ሀገር ስለሆነች ነው፡፡ በተደጋጋሚ በሚሰጡዋቸው ቃለ-ምልልሶች ይህችን ታላቅ ደጋግመው በክብር ያነሷታል፡፡ በንጉሱ ዘመን ከፍተኛ የምጣኔ ሀብት ባለሙያ የነበሩት አቶ ቡልቻ ሀገራቸውን በንቃትና በእውቀት ያገለገሉ ናቸው፡፡ ለሙያቸው ባላቸው ጥልቅ ፍቅር ብዙዎች ክብር ያጎናጽፏቸዋል፡፡ ምክንያቱም አቶ ቡልቻ ከሀገራቸው አንዳችም ሳይጠብቁ ለሀገራቸው የሚሰሩ ባለውለታ ስለሆኑ ነው፡፡ ይህ ለሀገር ያላቸው ጥልቅ ፍቅር አሁን ባሉበት የአዛውንት እድሜም ላይ የሚቀንስ አይደለም፡፡ ይልቁንም ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ስለ ኢትዮጵያዊ አንድነት ሲሰብኩ የኖሩ የኢትዮጵያ ልጅ ናቸው፡፡ አቶ ቡልቻ፣ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ዘርፍ ያበረከቱት ሚና እንዲህ በቀላሉ የሚነገር አይደለም፡፡ በተለየ መልኩ ደግሞ የአዋሽ ባንክ እንዲመሰረት ያኖሩት ትልቅ አሻራ በታሪክ ዝንተ-አለም እንዲታወሱ የሚያደርጋቸው ናቸው፡፡ ከእርሳቸው ስር የሰሩ የፋይናንስ ዘርፍ ባለሙዎች ድንቅ እሳቤ ያላቸው ምሁር ሲሉ ይገልጿቸዋል፡፡ እኛ የዚህ ግለ-ታሪክ አሰናጆች  አዲሱ ትውልድ አቶ ቡልቻ አሳምሮና ከፍ አድርጎ እንዲያውቃቸው እንፈልጋለን፡፡ ብዙ ሊነገርላቸው የሚገባ እንዲሁም ለብዙዎች መነሳሳት የሚፈጥሩ  ሰው ናቸው፡፡ በመሆኑም አቶ ቡልቻን ከማክበር አልፎ አንድነቱዋ የተጠበቀች ታላቂቱን ኢትዮጵያን በወጉ ስላቆዩልን ምስጋናችንን ማቅረብ እንወዳለን፡፡ለእርሳቸውም  ዘመኑ የጤና እንዲሆንላቸው እንመኛለን፡፡

 





አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች