126. ገድለሚካኤል አበበ
አላጋው / gedlemichael abebe alagaw
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ
ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤
በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ
የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር
ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ5 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል
ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም
ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው
ገድለሚካኤል አበበ አላጋው ይሆናል፡፡
ትውልድና ልጅነት
ገድለሚካኤል አበበ
አላጋው ፣ በ1975 በአዲስ አበባ በሾላ ክሊኒክ ተወለደ፡፡ የልጅነት ጊዜውን ያሳለፈው ካዛንቺስ ነው፡፡ ልዩ ስፍራውም
መናኸሪያ ሆቴል ይባላል፡፡ ገድለሚካኤል አይነስውር የሆነው ሲወለድ ነው፡፡ ምክንያቱን ሀኪሞችም ቤተሰቦቹም አያውቁትም፡፡
ያጋጥማል በሚል የታለፈ ነበር፡፡ እድሜው ለትምህርት ሲደርስም
ከ5-7 አመቱ ቄስ ተማሪ ቤት ተምሯል፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በምእራብ ሸዋ ባኮ በምትባል ከተማ
ለአይነ-ስውራን ተብሎ በተዘጋጀ አዳሪ ተማሪ መማር
ጀመረ፡፡ ይህ ተማሪ ቤት ባኮ የአይነ-ስውራን ተማሪ ቤት ይባላል፡፡ ባኮ ከአዲስ አበባ 250ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ነው፡፡ ገድለሚካኤል አበበ ከ1ኛ -6ኛ ክፍል በባኮ አጠናቀቀ፡፡
ትምህርት እና የኪነ-ጥበብ ዝንባሌ
ገድለሚካኤል፣ የ7ኛ
ክፍል ትምህርቱን ለመከታተል አዲስ አበባ መጣ፡፡ በአዲስ አበባም በቀድሞው አስፋው ወሰን በአሁኑ ምስራቅ ጎህ ተብሎ በሚጠራው
ትምህርት ቤት መከታተል ጀመረ፡፡ ገድለ ባኮ ይማር በነበረበት ጊዜ የሙዚቃ ልዩ ዝንባሌ ውስጡ አሳድሮ ነበር፡፡ በተጨማሪም
በሚኒሚዲያ ውስጥ ተሳትፎ በማድረግ ይታወቅ ነበር፡፡ ገድለ፣
ምስራቅ ጎህ ሲመጣ ይህን የኪነ-ጥበብ ችሎታውን እንደያዘ ነበር፡፡
በዛን ወቅትም ብቸኛው አይነ-ስውር ተማሪ ነበር፡፡
ገድለሚካኤል አበበ
የሙዚቃ እና የሚድያ ፍቅሩን እየተወጣ በአንድ በኩል ደግሞ ትምህርቱን ይከታተል ነበር፡፡ 7ኛ እና 8ኛ ክፍል ልዩ የሙዚቃ
ክህሎት ስለነበረው በህጻናትና ወጣቶች ቴአትር ቤት መስራት
ጀመረ፡፡ በጊዜውም ሙዚቃ በመጫወትና መድረክ በማስተዋወቅ አቅሙን ለማውጣት ጥረት ያደርግ ነበር፡፡ ጎንለጎንም በሜጋ
ኪነ-ጥበባት እና በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቴአትር ሙዚቃ ይጫወት ነበር፡፡
2ኛ ደረጃ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒሊክ ተማሪ ቤት ቀጠለ፡፡ ገድለ
በጊዜው ውስጡ ያለውን የኪነጥበብ ዝንባሌ ለማውጣት በዚህ ሰአት ራሱን ዝግጁ አድርጎ ነበር፡፡ በጊዜው ዳግማዊ ምኒሊክ በሙዚቃ
ና በሚድያ የታወቀ ነበር፡፡ገድለም በትምህርት ቤቱ የሚኒሚድያ እና የሙዚቃ ክበብ ውስጥ ተሳትፎ ማድረግ ጀመረ፡፡ ገድለ
እንደሚናገረው ለሚድያ ህይወቱ መሰረት ያስቀመጠው ዳግማዊ ምኒሊክ ይማር በነበረበት ጊዜ ነበር፡፡
ገድለሚካኤል ወደ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ በህግ የመጀመሪያ ዲግሪውን አገኘ፡፡
ነገር ግን ፍላጎቱ በህግ ሙያ መስራት አልነበረም፡፡ የሙዚቃ
ዝንባሌው እየቀነሰ የጋዜጠኝነት ፍቅሩ ግን እየጨመረ ሄደ፡፡
ወደ ራስ ስራ መግባት
ገድለ help
person with disability በሚባል ድርጅት ውስጥ በህዝብ ግንኙነት ባለሙያነት መስራት ጀመረ፡፡ ድርጅቱ የሙዚቃና
የድራማ ክበብም ነበረው፡፡ ገድለሚካኤል በጊዜው ስለ አካልጉዳተኝነት ግንዛቤ ማስጨበጥ እንዳለበት ያወቀበት ጊዜ ነበር፡፡ እናም
በዚህ ጉዳይ ለምን አልሰራም የሚል ሀሳብ ይዞ ገድለሚካኤል ሀሳብ ማውጣትና ማውረድ ጀመረ፡፡ እና በአካልጉዳት ላይ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ የሬድዮ ፕሮግራም ለመስራት
በ2000 በፋና 98ነጥብ አንድ፤ አንድ ፕሮፖዛል አስገባ፡፡ ይህ ፕሮፖዛል ተቀባይነት አግኝቶ የመጀመሪያው በአካል ጉዳተኝነት
ላይ ያተኮረ የሬድዮ ፕሮግራምን መስራት ጀመረ፡፡ ይህም የሬድዮ
ፕሮግራም አንድ ድምጽ የሚል ስያሜ ነበረው፡፡ ማክሰኞ ከ7-8 የሚቀርብ ፕሮግራም ነበር፡፡ ገድለ በመሰረተው ድርጅት
አማካይነት አንድ ድምጥ በፋና ለ 7 አመታት ዘለቀ፡፡ ይህ
ፕሮግራም በየሳምንቱ ሲቀርብ የነበረ
የማህበረሰብ ለውጥ
ለማምጣት የጣረ መሆኑም ይታወቃል፡፡ ገድለሚካኤል በመሀል
ከ2005 ጀምሮ ከፋና በተጨማሪ ከደቡብ ሬድዮና ቴቪ
ጋር አንድ ላይ በመሆን ሰናይ የተሰኘ በአካል ጉዳተኝነት ላይ የሚሰራ የ20 ደቂቃ የሬድዮ ፕሮግራም መስራት ጀመረ፡፡
ገድለሚካኤል አበበ
፤ በየካቲት 2007 ከፋና ወጥቶ በመስከረም 2008 በመሰለ መንግስቱ በተመሰረተው ብስራት ሬድዮ ላይ መስራት ጀመረ፡፡ ያንኑ
አንድ ድምጽ የተሰኘ ፕሮግራም ዘወትር ሀሙስ ከ2-3 ማቅረብ
ጀመርን፡፡ ገድለሚካኤል በአካል ጉዳተኝነት ላይ ከብዙ ተቋማት ጋር አብሮ ሰርቷል፡፡ ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ፤ ዲላ
ዩኒቨርሲቲ እና አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እነ ገድለ በሚሰሩት የሬድዮ ፕሮግራም ላይ ጥናት በመስራት የእነ ገድለን
አርአያነት በጥናት ወረቀታቸው አሳይተዋል፡፡ በደቡብ ሬድዮ የእኛ
ጉዳይ የተሰኘ ዘወትር ከ8-9 የሚቀርብ ፕሮግራምም መስራት ጀመረ፡፡
በመቀጠል የገድለሚካኤል ድርጅት ስራውን ማስፋፋት እንዳለበት አመነ፡፡
አካል ጉዳተኞች አማርኛን ብቻ የሚናገሩ ባለመሆናቸው በሌሎች ቋንቋዎችም ስራውን ለመስራት እንደሚቻል
ገድለ ያስብ ነበር፡፡ ይህን ሀሳቡንም ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጥ ውሳኔ አደረገ፡፡
የኮቪድ 19 መጋቢት 5 2012 ወደ ኢትዮጵያ በገባ ጊዜ አካልጉዳተኞች የበለጠ
ግንዛቤ እንዲይዙ መደረግ እንደነበረበት ገድለ ያምን ነበር፡፡ ይህን እምነቱን በመያዝም አንድ ፕሮጀክት ቀረጸ፡፡
ከኢትዮጵያ
የአካልጉዳተኞች ፌዴሬሽን በተገኘ የገንዘብ ድጋፍም በልዩ ልዩ ቋንቋዎች
የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መሰራት ተጀመረ፡፡ በዚህም መሰረት
በሲዳምኛ፤ በአፋን ኦሮሞ፤ በወላይትኛ፤ በትግርኛ፤ እና በሶማሊኛ
ከየጣቢያዎቹ ጋር በመነጋገር መሰራት ተጀመረ፡፡ ሁሉም
ፕሮግራሞች 30 ደቂቃ ነበሩ፡፡ በዚህ መልኩ ገድለ አርአያነት ያለውን ተግባር መከወን ችሏል፡፡
ገድለ ከሚሰራቸው የፕሮሞሽን እና የግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞቹ በተጨማሪ
ለአካል ጉዳተኞች የሚሆኑ መሳሪያዎችን የሚሸጥ ማእከል አቋቋመ፡፡ በተጨማሪም የምልክት ቋንቋ አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅትንም በመመስረት ስራ ወዳድነቱን ያስመሰከረ ሰው ነው
ገድለሚካኤል አበበ፡፡
ከውጭ አገር የሚያስመጣቸው ማቴሪያሎች
አቶ ገድለሚካኤል፡-
ለዓይነ ስውራን የብሬል መጻፊያ መሣሪያዎች፣ የብሬል ወረቀት፣ ዝቅተኛ የማየት ችግር ላለባቸው ወገኖች ደግሞ አጉልቶ ማሳየት
የሚችል መሣሪያ (ማግኒፋየር)፣ ለእግር ጉዳተኞች የሚውሉ የተለያየ መጠንና ደረጃ ያላቸውን ክራንችና ዊልቸር፣ የመስማት
መሣሪያ፣ የምልክት ቋንቋና የብሬል መማሪያ መጻሕፍት፣ በአጠቃላይ ለአካል ጉዳተኞች የሚያገለግሉ ሌሎችም የአካል ድጋፍ
መሣሪያዎችን ሁሉ እያስመጣ አቅምን ባገናዘበና ተመጣጣኝ በሆነ መንገድ ለተጠቃሚዎች ይሸጣል፡፡
ግንዛቤ ማስጨበጫ ፕሮግራሞች
የአቶ
ገድለሚካኤል፡- ድርጅት በአካል ጉዳተኝነትና ጉዳተኞች ላይ ብቻ
የሚያተኩር አይደለም፡፡ ለምሳሌ ያህል ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ጤና ቢሮና ብርሃን ለሕፃናት ከተባለ መንግሥታዊ
ያልሆነ ድርጅት ጋር በመተባበር የተለያዩ ጉዳዮችንና ለችግር የተጋለጡ የማኅበረሰብ ክፍሎች ባሉባቸው ቦታዎች ግንዛቤ ማስጨበጫ
ፕሮግራሞችን ለአረጋውያን፣ ለወጣቶች ይሰራል፡፡ ለዚህም የሚውል አንድ ትልቅ ስቱዲዮ አቋቁሟል፡፡ ለሚዲያ ባለሙያዎችም ሐዋሳና
አዲስ አበባ ውስጥ የአቅም ግንባታ ሥልጠና ተሰጥቷል፣ ወደፊትም ይሰጣል፡፡ ገድለ የኦዲዮና የኦዲቪዡዋል ዶክመንተሪ ፕሮግራሞችንም እየሠራ ለተቋማት
ያቀርባል፡፡ ይህንንም ሥራ የሚከታተል የኦዲቪዡዋል ዲፓርትመንት ተደራጅቷል፡፡
ገድለ በዚህ ብቻ ሳይወሰን የምክር አገልግሎት የሚሰጥ ድርጅት ያቋቋመ
ሲሆን ይህም ከፍተኛ ርካታ ይሰጠዋል፡፡
የገድለ ብስራት
ፕሮሞሽን 13 አመት የዘለቀ ድርጅት ሲሆን ለሌሎች ባለሙያዎችም
የስራ እድል ከመክፈቱ ባሻገር ሌሎች ባለሙያዎችም የራሳቸውን አየር ሰአት ይዘው እንዲሰሩ ያደረገ ድርጅት ነው፡፡
ገድለም ስለዚህ ጉዳይ ቆም ብሎ ሲያስብ ትልቅ የመንፈስ ርካታ
ይሰማዋል፡፡ ገድለ ዛሬ ለብዙዎች የስራ እድል ከፍቶ የራሱንም ህልም እያሳካ ስለሆነ በዚህ ታላቅ ደስታ ይሰማዋል፡፡
ቤተሰባዊ ሁኔታ
ገድለሚካኤል አበበ ባለትዳርና የ2 ልጆች አባት ሲሆን ባለቤቱም በድርጅቱ
ውስጥ በምልክት ቋንቋ የማስተርጎሙን ስራ እየመራች ትገኛለች፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ