125. ብርሃኑ ሰሙ/ birhanu semu

ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከድርሰት እና ስነጽሁፍ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው ብርሀኑ ሰሙ ይሆናል፡፡

           ትውልድና ልጅነት

ሴት አያቱ (የአባቱ እናት) እና ወላጅ እናቱ ‹‹የተወለድከው በፍልሰታ ፆም ሰሞን ነው›› ስላሉት፣ ‹‹ወልደመድኅን›› የሚል ስም አወጡለት፡፡ የአባቱ ጓደኛ ደግሞ ‹‹በወሩ 27ኛ ቀን፣ በመድኃኒዓለም ዋዜማ ስለተወለድክ ነበር ወልደመድኅን ያልኩህ›› የሚሉትን ሁለት መረጃዎች እርስ በእርስ አናብቦ ሐምሌ 26 ቀን በመወለዱ እርግጠኛ ቢሆንም፤ ስለተወለደበት ዓ.ም እስካሁን ትክክለኛ መረጃ የለውም፡፡ ትውልዱ በቀድሞ ሐይቆችና ቡታጅራ አውራጃ፣ በጉራጌ ዞን፣ በክስታኔ ወረዳ፣ በዋጮ ቀበሌ ገበሬ ማኅበር፣ ፉሌ መድኃኒዓለም ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ነው፡፡ በቀበሌ የነዋሪነት መታወቂያው ላይ በ1966 ዓ.ም መወለዱን አስመዝግቧል፡፡

             ትምህርት  በልጅነት

በልጅነቱ የወላጆቹ ትዳር በመፍረሱ ምክንያት ይኖርበት ከነበረው የእናቱ አባት ቤት ወደ አዲስ አበባ ያመጡት የአባቱ ዘመዶች ነበሩ፡፡ አዲስ አበባ በመጣ ማግስት በጨው በረንዳና በቁጭራ ሠፈር ይገኙ በነበሩ የቄስ ትምህርት ቤቶች ተምሯል፡፡ አንደኛ ደረጃን በሜይዴይ፣ በየካቲት 23 እና በአርበኞች ሲከታተል፤ ሁለተኛ ደረጃን በኮልፌ ኮምፕሬንሲቪ እና በመድኃኒዓለም ትምህርት ቤቶች ነው የተከታተለው፡፡ ‹‹የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ለማጠናቀቅ 16 ዓመታት ነው የወሰደብኝ›› ይላል፡፡

            ለአቅመ-አዳም  መድረስ ትምህርትና ስልጠና 

 በተለያዩ ዘርፎች በርካታ ስልጠናዎችን ወስዷል ፡- 

- በ1979 ዓ.ም አቶ ታደሰ የሚሰጡት የክረምት እግር ኳስ ስልጠና፣

- በ1984 ዓ.ም የአዲስ አበባ ባህልና ስፖርት መምሪያ የክረምት ስነ ጽሑፍ ኮርስ፣

- በ1988 ዓ.ም ከዩኒቨርሳል ቋንቋ ትምህርት ቤት በእንግሊዝኛ ቋንቋ፣

- በ1990 ዓ.ም በመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት (ከእንግሊዝ ሀገር በተልዕኮ)፣

- በ1992 ዓ.ም በምልክት ቋንቋ፣

- በ1997 ዓ.ም በሕትመት ጋዜጠኝነት፣

- በ1998 ዓ.ም በሥራ አመራር፤

- በ1998 ዓ.ም በኢንተርፕረነርሽፕ፤

- በ2000 ዓ.ም በመሠረታዊ የኮምፒዩተር ትምህርት፤

- በ2009 ዓ.ም በሙስና መከላከል ስትራቴጂ፤

- በ2010 ዓ.ም በቅርስ እንክብካቤና ጥበቃ ስልጠናዎችን ተከታትሎ በሁሉም በሠርተፍኬት ያጠናቀቀ ሲሆን፤ ‹‹በ2005 ዓ.ም በአሮማያ ዩኒቨርስቲ በርቀት ትምህርት በድግሪ ፕሮግራም የማኔጅመንት ትምህርት ጀምሬ ስላልተመቸኝ አላጠናቀቅኩም›› ይላል፡፡

-             መክሊትን የማግኘት ጉዞ

‹‹መክሊቴን ለማግኘት በብዙ ውጣ ውረድና በተለያዩ ሥራዎች ውስጥ አልፊያለሁ›› የሚለው ብርሃኑ ሰሙ፤ ‹‹ቀስ በቀስ ያዳበርኩት የማንበብ ልማድ፣ መማሪያና መዝናኛ ብቻ ሳይሆን በውስጤ የፀሐፊነት ተሰጥኦ እንዳለኝ አመላከተኝ›› ይላል፡፡ ከ1987 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ጸሑፎችን እያዘጋጀ ለተለያዩ የሕትመት መገናኛ ብዙኃን በመላክ ለመሳተፍ ጥረት ማድረግ ጀመረ፡፡ መክሊቴን ለማረጋገጥ ያስቻለኝን አቅጣጫ በማሳየት ከፍተኛ እገዛና ትብብር አድርጎልኛል በማለት ጋዜጠኛና ደራሲ አብርሃም ረታ ዓለሙን በተለየ ሁኔታ ያመሰግናል፡፡

           ድርሰት ላይ ያዘነበለው ብርሀኑ

በመጀመሪያ ወልደመድኅን ብርሃነመስቀል በሚለው የብዕር ስም ነበር የሚጽፈው፡፡ የፀሐፊነት ተሰጥኦ እንዳለው እርግጠኛነት ከተሰማው በኋላ በስሙ መጻፍ ጀመረ፡፡ ባለፉት 25 ዓመታት በአዲስ ዘመን፣ በሩሕ፣ በኔሽን፣ በአዲስ ዜና፣ በጽጌረዳ፣ በአዲስ አድማስ፣ በአዲስ ማለዳ ጋዜጦች፤ በዜጋ፣ በቁም ነገር፣ በአዲስ ቱሪዝም፣ በወይ አዲስ አበባ መጽሔቶች፣ በተለያዩ ‹‹ልዩ ዕትም›› ጋዜጣና መጽሔቶች የአጭርና የረጅም ጊዜ ተሳትፎ አለው፡፡ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ የነበረው ተሳትፎ ከሁሉም ይልቃል፡፡  

በጋዜጦችና መጽሔቶች ከመሳተፉ በተጨማሪ በተለያዩ መጻሕፍት ዝግጅት ላይ በተለያየ ደረጃ በመሳተፍ፣ በሙሉ ጊዜ ፀሐፊነት እየሠራ ያለው ብርሃኑ ሰሙ፣ በመጻሕፍት ዘርፍም የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡ በ2000 ዓ.ም አራት ለእንድ በሚል ርዕስ (ልቦለድ፣ ግጥምና የመጻሕፍት ዳሰሳ ላይ ያተኮረ) ያሳተመው 104 ገጾች ያሉት መጽሐፍ ቀዳሚው ሥራው ነው፡፡

ከእንጦጦ ሐሙስ ገበያ እስከ መርካቶ (የአዲስ አበባ ንግድ፣ ነጋዴና ገበያ ታሪክ የያዘ)  328 ገጾች ያሉት፤ በ2003 ዓ..ም የታተመ መጽሐፍ ሁለተኛ ሥራው ሲሆን፤ ይህንን ታሪክ በመጽሐፍ ጠርዞ ከማቅረቡ በፊትና በኋላ በፎቶግራፍ በማሰናዳት በሦስት የተለያዩ ጊዜያት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በተዘጋጁ ዓውደ ርዕዮች ላይ ለሕዝብ አቅርቦታል፡፡

ቀዳሚውን በ1999 ዓ.ም በኢትዮጵያውያን ሚሊኒየም በዓል ዋዜማ የተዘጋጀው ‹‹የፋሲካ ንግድ ትርዒት›› ላይ ‹‹መርካቶ ከ1930 እስከ ሚሊኒየም ዋዜማ›› በሚል ርዕስ ነበር ያቀረበው፡፡ በ2005 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታ 125ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል ላይ በተዘጋጀ ኤግዚቢሽን ላይ ደግሞ ‹‹የ125 ዓመት የአዲስ አበባ ነጋዴዎች ታሪክ›› በሚል ርዕስ በፎቶግራፍ ያቀረበበት ሁለተኛው መድረኩ ሲሆን፤ ሌላኛው የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ በ2011 ዓ.ም ለ11ኛ ጊዜ ባዘጋጀው ከተማ አቀፍ ‹‹የኪነ ጥበባት ሳምንት››  ላይ ‹‹መርካቶ ድር እና ዘንድሮ›› በሚል ርዕስ ያቀረበው ዓውደ ርዕይ ሦስተኛው ነበር፡፡

በ2006 ዓ.ም በግል አዘጋጅቶ ያሳተመውና ወታደራዊ የደንብ ልብስ ቁልፎች ላይ ያለው ታሪክ በኢትዮጵያ ምን እንደሚመስል ያስቃኘበት፤ የአዝራር ዲዛይንና ፋሽን በኢትዮጵያ በሚል ርዕስ  ያቀረበው ሦስተኛ መጽሐፉ ነው፡፡  ብርሃኑ ሰሙ የልብስ ቁልፎችን መነሻ ያደረገው ይህንን ታሪክ በመጽሐፍ እንዲያቀርብ ምክንያት ሆኖኛል የሚለው፣ የልብስ ቁልፍ መሰብሰብን የትርፍ ጊዜ ማሳለፊያና መዝናኛ አድርጎ (HOBBY) ለብዙ ዓመታት በሺህ የሚቆጠሩ ቁልፎች ሰብሳቢነቱን ነው፡፡ የልብስ ቁልፍ ስብስቦቹንም በ2001 ዓ.ም እና በ2007 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል፣ በ2008 ዓ.ም በቅዱስ ዮሴፍ ትምህርት ቤት ለዓውደ ርዕይ አቅርቦታል፡፡

የአዝራር ዲዛይንና ፋሽን በኢትዮጵያ መጽሐፍ በጋዜጠኛ መልካሙ ተክሌ ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉሞ አሳታሚ እያፈላለገ መሆኑን ብርሃኑ ሰሙ ይገልጻል፡፡

ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈጣሪዎች ያቋቋሙት ‹‹ኢምፐርቴክ ኢትዮጵያ ቢዝነስ ሶሳይቲ›› በሚል ስያሜ ይታወቅ የነበረው የኢንተርፕረነሮች ማኅበር፤ ከ1999 እስከ 2005 ዓ.ም ባሉት 6 ዓመታት የብልጽግና ቁልፍ በሚል ርዕስ በተከታታይ ባሳተማቸው 6 ጥራዞች በጽሑፍ ቅንብር ሥራ ላይ፤ ከመምህር አትርሳው ጣሰው እና ከዶ/ር ወሮታው በዛብህ ጋር በመሳተፍ፤ በ6ቱም ጥራዞች ላይ የራሱን አሻራ አኑሯል፡፡

ብርሃኑ ሰሙ በተለያዩ መጻሕፍት ሥራ ላይ የተለያዩ ፀሐፍትን በማማከር፣ በእርማትና በአርትኦት ከተሳተፈባቸው ጥራዞች መሐል ፡-

- ያልተነገረለት የሀገር ባለውለታ  በሚል ርዕስ በወ/ሮ ይድነቃቸው አሰፋ ተዘጋጅቶ በ2004 ዓ.ም፤

- ዓይኔን ተመልከተኝ በሚል ርዕስ በደ/ር ዮናስ ባሕረጥበብ ተዘጋጅቶ በ2010 ዓ.ም፤

- የካንሰር ስጋትና ተስፋ በሚል ርዕስ በዶ/ እንድርያስ ለማ ተዘጋጅቶ በ2012 ዓ.ም፤

- ስደተኛው ሼፍ በሚል ርዕስ በአንተነህ ድፋባቸው በ2013 ዓ.ም በታተሙት መጻሕፍት ላይ በተለያዩ ደረጃዎች ተሳትፎ አድርጓል፡፡

የመርካቶ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን (ቁጥር ሁለት) እና ‹‹ጀማሪዎቹ›› በሚል ርዕስ ለሕትመት ያዘጋጀኋቸው የተለያዩ ጥራዞች አሉኝ የሚለው ብርሃኑ ሰሙ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ነው፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች