120.ክብረት
መኮንን kibret mekonnen
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤
በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ
እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እስካሁን መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለታሪኮች ግለ-ታሪካቸውን
እየጻፉ እየላኩልን ነው፡፡ እርስዎም tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014
የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም
በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ
እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡
በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው
የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰው ክብረት መኮንን
ይሆናል፡፡
ስለትውልድ ፤
ክብረት መኮንን
ውልደቱ አዲስ አበባ ኳስ ሜዳ አካባቢ ነው። እድሜው ለትምህርት ከመድረሱ በፊት በወላጆቹ የስራ ዝውውር ምክንያት ወደ ኢሉባቡር
ክፍለ ሃገር በመሄድ መቱ ቅዱስ ገብርኤል አንደኛ ደረጃ ት/ቤት
ከ1ኛ እስከ 5ኛ ክፍል ተምሯል። ክብረት 8 ወንድሞችና 1 እህት ሲኖረው እድገቱ በጥሩ እንክብካቤ፣ በጥሩ ስነ፡ምግባርና እና
እሴቶች በታነጸ ቤተሰብ መካከል ነው፡፡ ብዙ ጊዜ “በተስፋ እና በደስታ የተሞላ ሙሉ ቤተሰብ ውስጥ ነበር ያደኩት” የሚለው ክብረት “ኢሊባቡር ጣፋጭና ንጹህ የተፈጥሮ ህይወት የመገበችን
ለአፍታ ከአእምሮዬ የማትጠፋ በጣም የምወዳት የዛሬዬን እኔነት የቀረጸች ክፍለሃገር ናት” ሲል ይደመጣል።
ከ6ኛ እስከ 12ኛ
ክፍል ያለውን ትምህርት ወላጆቹ የስራ ዝውውር ጊዜኣቸውን ጨርሰው ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ በሲብስቴ ነጋሲ አንደኛና
መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተባበሩት መምህራን እና በአብዮት ቅርስ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትሎ
አጠናቋል።
የሁለተኛ ደረጃ
ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ በ18 አመቱ ወደ ወለጋ ክፍለ ሃገር በመሄድ ከነቀምቴ የመምህራን ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩት በመምህርነት
ተመርቆ አዚያው ወለጋ ውስጥ ለአንድ አመት ተኩል አገልግሏል። ለትምህርት ባደረበት ጥልቅ ጉጉት ወደ አዲስ አበባ በመመለስ፤
ቀን ቀን በመምህርነትና በፎቶግራፍ ስራ ላይ ተሰማርቶ በአዲስ አበባ ዮኒቨርሲቲ የማታው የዲፕሎማ መርሃ-ግብር በኢትዮጵያ
ቋንቋዎችና ስነጽሁፍ ተመርቋል። እዚያው አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የማታ የድግሪ መርሃ-ግብር ትምህርቱን በመቀጠል የመጀመሪያ
አመቱን እንዳጠናቀቀ በወቅቱ ከተሰማራበት የጋዜጠኝነት ሙያው ጋር በተያያዘ በመንግስት ባለስልጣናት ይደርስበት የነበረውን ጫና
ለመሸሽ ወደ ሆላንድ ሃገር በመሰደዱ ትምህርቱን ለማቋረጥ ተገዷል።
“ጋዜጠኝነት
የማከብረውና የምወደው ሙያ ነው፤ የተሰደድኩበት የሃገሬ ጉዳይ ሁሌም ያንገበግበኛል፤ ይቆጨኛል፤ ያሳዝነኛል፤ በዚህም ምክንያት
ከጋዜጠኝነት ሙያ እና ከመረጃ ላለመራቅ ፅኑ ፍላጎት አለኝ።” የሚለው ክብረት በሆላንድ የመኖሪያ ፍቃዱን እንዳገኘ፥ የአንድ
አመት የደች ቋንቋንና የሙያ ማሻሻያ ኮርስ ከወሰደ በኋላ፥ ኢትዮጵያ በነበረበት ጊዜ ያዳበረውን የፎቶ ጋዜጠኝነት ልምዱን
ተጠቅሞ፥ ከጋዜጠኝነት መስክ ሳይርቅ ከኡትረክት የፊልምና ቴሌቭዥን አካዳሚ (Utrecht School of the Arts)
የአራት አመት ትምህርት ተከታትሎ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቋል።
ቤተሰባዊ ሁኔታ
ክብረት፣ የሁለት
ልጆች አባት ሲሆን በሙያው ብዙ ልጆችን ያፈራ የእውቀት አባት እንደሆነ ይነገርለታል። ከሰዎች ጋር በቀላሉ መግባባት የሚችልና
ሰብዓዊ ግንኙነትን አክብሮ ማስተናገድ የሚችል ስነ-ልቦና ያለው መሆኑን በቅርብ የሚያውቁት ይገልጹታል።
የስራ ልምድ በኢትዮጵያ
ክብረት ከልጅነት እድሜው ጀምሮ ኳስ ተጫዋች፣ ዘፋኝ፣ መምህር፣ ጋዜጠኛ ወይም
ቲያትረኛ መሆን ምኞቱ ነበር። በ19 አመቱ አስተማሪ ሆኖ ማገልገል ጀመረ። በኋላም በሰማንያዎቹ አጋማሽ ላይ የኢህአዴግ
መንግስት ስልጣን ላይ ሲወጣ የታወጀውን የፕሬስ ነጻነት ተከትሎ ከሦስት የዩኒቨርስቲ ጓደኞቹ ጋር ማህደር የህትመትና
የማስታወቂያ ድርጅትን በማቋቋም ‹‹አእምሮ›› የተሰኘ ጋዜጣና መጽሄትን በአሳታሚነትና በአዘጋጅነት አገልግሏል።
የአእምሮ ጋዜጣና
መጽሄት በወቅቱ በህትመት ላይ ከነበሩት የግል ሚዲያዎች በተሻለ አቅምና የገበያ ስርጭት ላይ የነበረ እና የራሱን የፎቶ
ጆርናሊዝም ክፍል በማደራጀት ጋዜጠኞች የራሳቸውን ፎቶግራፍ በማንሳት ለጽሁፍ ስራዎቻቸው መግለጫ መጠቀም እንዲችሉ ጉልህ
አስተዋጽኦ አድርጓል።
ከጋዜጣና መጽሄት
ህትመት በተጨማሪ በመንግስት የቢሮክራሲ ውጣ ውረድ ሳብያ ከትምህርት ሚኒስትር ህጋዊ የትምህርት-ተቋም ማረጋገጫ ሠርተፊኬት
ባይሰጠውም በሃገራችን ፈር-ቀዳጅ የሚባል “ማህደር የፈጠራና ጥበብ ሙያ ማሰልጠኛ ማእከል” በማቋቋም በምክትል ስራ አስኪያጅነት
አገልግሏል። ማዕከሉ በሙያው በሰለጠኑና ልምድ ባካበቱ ባለሙያዎች ከስድስት ወር እስከ አንድ አመት የሚረዝም የጋዜጠኝነት፣
የፎቶግራፍ ጋዜጠኝነት፣ የስነጽሁፍ፣ የቴአትርና የመሰረታዊ የህግ ትምህርት ስልጠና ይሰጥ ነበር።
የስራ ልምድ በሆላንድ
ክብረት ቀደም ሲል
አፍሮ ቪዝን (Afro- Vision) አሁን ደግሞ ታስክ መልቲ ሚዲያ (www.taskmultimedia.com under
contruction) በሚል ስያሜ የግል ድርጅት በማቋቋም በፊልምና ቴሌቭዥን አገልግሎት፣ በሚድያ ስልጠና, እና በባህል ዝግጅት
አደራጅነት ከ20 አመት በላይ እየሰራ ይገኛል። እንዲሁም አእምሮ ሚድያ ሃውስ የሚባል ተቋም በመመስረት;-
- ለበርካታ ወጣቶች
መሰረታዊ የጋዜጠኝነት እና የእውቀት ማሻሻያ ትምህርት በመስጠት ላይ ይገኛል።
- በበርካታ ህዝባዊ
ጋዜጠኝነት ማእከላትን (Civil Journalism) በማደራጀት፣ በማሰልጠንና በመምራት ሰፊ ልምድ አካብቷል።
- በአለም ብቸኛ
እና የመጀመሪያ የሚባል ጎረቤታዊ ፊልም ፌስቲቫል (Neighborhood film festival www.abff.nl)
በአመስተርዳም መስርቶ በመምራት ላይ ይገኛል።
- በአውሮፓ
የመጀመሪያው የአፍሪካ የህዝብ ቤተ-መፃህፍት እና የቋንቋ ማዕከል (Afro-Bieb, www.afrobieb.nl) አቋቁሞ
በመምራት ላይ ይገኛል።
በሆላንድ በኖረባቸው
አመታት የኢትዮጵያን ባህላዊና ማህበራዊ እሴቶች በማስተዋወቅ ረገድ በሆላንድ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ስለ ሃገራቸው ወቅታዊ ሁኔታ
በቅርበት መከታተልና መሳተፍ እንዲችሉ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርጓል። ለአብነት ለመጥቀስ ያህል;-
- እንደ
አውሮፕያዊያኑ ዘመን አቆጣጠር ከ 1998 እስከ 2013 ዓ.ም ኢትዮ ቲቪ የተሰኘ ሳምንታዊ የቴሌቭዥን ስርጭት በማቋቋም በድምሩ
ለ13 አመታት በዳይሬክተርነት ፣ በፕሮዲሰርነት ፣ በካሜራና አርተኦት ስራ አገልግልሏል።
- ለ17 ዓመታት
የኢትዮጵያን አዲስ አመት በዐል በማዘጋጀትና በማስተባበር ግንባር ቀደም ሚና ተጫውቷል።
- ለበርካታ ዓመታት
ኢትዮጵያውያን እንዲሰባሰቡ ልምድና እውቀታቸውን አንዲካፈሉ “ቅዳሜ ምሽት” የተሰኘ ወርሃዊ የስነጽሁፍና የግጥም መድረክ
በማዘጋጀት መሪ ሚና ተጫውቷል።
- ለበርካታ አመታት
በሆላንድ የተወለዱ፣ በማደጎ ያደጉና ከኢትዮጵያውያን ጋር በስራም ሆነ በሌላ ግንኙነት የተዛመዱ የሆላንድ ዜጎችን አማርኛ ቋንቋ
እና የኢትዮጵያን ባህልና ማህበራዊ እሴቶችን በማስተማር ላይ ይገኛል።
ክብረት በብዙ
የስራና የህይወት መንገድ ያለፈ በመሆኑ ይህን በመጽሀፍ የማቅረብ እቅድ አለው፡፡ በዚህ ወደፊት ሊያሳትም ባሳበው የግለ-ታሪክ
መጽሀፉ ላይ በርካታ አስተማሪ ጉዳዮችን አንድ ላይ አድርጎ እንደሚያስብ ይናገራል፡፡ ክብረት ገና በወጣትነቱ ከቅርብ ሰዎቹ ጋር
የጀመራት አእምሮ መጽሄት 13 እትም ስትዘልቅ ብዙ አስገራሚ ፤ አስተማሪ ትዝታዎችን አስተናግዷል፡፡ ለ4 አመታት ወደ አንባቢ ስትደርስ የነበረችው አእምሮ የብዙዎችን የንባብ ጥም ብሎም መረጃ የማግኘት ፍላጎት ታረካ ነበር፡፡
ክብረት እና ጓደኞቹ ታዲያ ይህን የአንባቢን ፍላጎት ለማሳካት ሌት ተቀን ይደክሙ ነበር፡፡
ክብረት ሆላንድ
ሀገር ከመጣ በኋላ አእምሮን ለ5 እትም ያህል በማሳተም ቆየ፡፡
ጋዜጠኛ ክብረት በሚድያ አለም ከ28 አመት በላይ የቆየ በመሆኑና ሆላንድም ከገባ በኋላም ተጨማሪ ትምህርት የቀሰመ
በመሆኑ ይህን እውቀት ለሀገሬ ልጆች መቼ ነው የማካፍለው የሚል ህልም ነበረው፡፡ ይህን ህልሙንም ከ 3 አመት በፊት
አሳክቷል፡፡ በ2010 ኢትዮጵያ የመጣ ጊዜ ለአማራ መገናኛ ብዙሀን እና ለምርት ገበያ ባለስልጣን ባለሙያዎች ስልጠና ሰጥቷል፡፡
ክብረት ወደፊት ስለ ሲቪል ጋዜጠኝነት ለማህበረሰብ መሪዎችና ለአክቲቪስቶች የማስተማር ግብ እንደሰነቀም ይናገራል፡፡
ክብረት መኮንን
ለእናት ሀገሩ ትልቅ ፍቅር ያለው ሲሆን ኢትዮጵያውያን አንድ
ሆነው ለስራ እንዲነሱ ምክሩን ይለግሳል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ