119.በፍቃዱ አባይ
ተክሉ/ Befekadu Abay teklu
ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ
ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤
በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እስካሁን መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለታሪኮች
ግለ-ታሪካቸውን እየጻፉ እየላኩልን ነው፡፡ እርስዎም tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14
2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት
አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ
እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡
በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው
የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት በፍቃዱ አባይ ተክሉ
ይሆናል፡:
ውልደት ልጅነት እና ትምህርት
ጋዜጠኛው፣መድረክ አጋፋሪው፣ዝግጅት አስተባባሪው
እና ሁለገቡ በፍቃዱ አባይ ተክሉ በ1969 ዓ.ም በአዲስ አበባ
ከተማ አራት ኪሎ ተወለደ።ከእናቱ ከወ/ሮ ስንቄ ረዳ እና ከአባቱ ከአቶ አባይ ተክሉ የተገኘው በፍቃዱ አባይ በየኔታ እጅ
የፊደል ልየታ እና አቡጊዳን ተማረ። በዳግማዊ ምኒልክ 1ኛ ደረጃ እና በዳግማዊ ምኒልክ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤቶች ከ1ኛ -12ኛ
ክፍል ተማረ። በዚህ የትምህርት ቤት ቆይታውም በሚኒ
ሚዲያ፣የሙዚቃ እና ድራማ ክበባት ንቁ ተሳታፊ ነበር።
የስራ አለም ና የዩኒቨርሲቲ ትምህርት
ከሁለተኛ ደረጃ
ት/ቤት መልስ ከ1990-1997 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽን ስር ለሰባት አመታት በተለያዩ ክፍሎች
በማገልገል የዜግነት ግዴታውን ተወጥቷል። በዚህ በወረዳ 13 የወንጀል መከላከል ጸሀፊነት፣በኮልፌ ፖሊስ ማሰልጠኛ
በአሰልጣኝነት እንዲሁም በኮሚሽኑ ዋና መስሪያ ቤት የማዕከል
ጨረታ ኮሚቴ ጸሀፊነት ጭምር አገልግሏል። በፖሊስ ሰራዊት ውስጥ የሳጂን ማእረግን ያገኘው በፍቃዱ ለሰባት አመታት ካገለገለበት
መስሪያ ቤት በ1997 ዓ. ም የተካሄደውን ምርጫ ተከትሎ መንግስት የሚወስዳቸው እርምጃዎችን በመቃወም ከሰራዊቱ በግል ፍላጎቱ
ተሰናብቷል።
በአዲስ አበባ ፖሊስ
ሰራዊት ውስጥም ሆነ ከሰራዊቱ ከለቀቀ በኋላ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የማታ ትምህርት ክፍል በመማር በ2000 ዓ.ም በቴአትር
ጥበባት በBA ዲግሪ ተመርቋል፡፡ ለትምህርት ያለውን ፍላጎት
በመቀጠልም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በጋዜጠኝነት እና ተግባቦት ለተጨማሪ አራት አመታት በመማር በመስል ሁኔታ በ2004 ዓ. ም
በጋዜጠኝነት በBA ዲግሪ ተመርቋል።
ከልጅነቱ ጀምሮ
በከፍተኛ ፍቅር ወደ የሚወደው የጋዜጠኝነት ስራ ሙሉ በሙሉ በመግባትም በዋግ ኮሙዩኒኬሽንስ፣በፍሬዴሪክ ስቲፍቱንግ እና በኤፍ
ኤም አዲስ 97.1 እና ኢትዮጵያ ሬዲዮ የጋራ ትብብር በሳምንት ለሁለት ቀናት ይቀርብ የነበረውን ትኩረቱን በማህበራዊ ህይወት
ዙሪያ ያደረገውን ‹‹ደወል›› የተሰኘውን የሬዲዮ ፕሮግራም በዋና አዘጋጅነት እና አቅራቢነት ለ8 አመታት በመምራት አገልግሏል።
የሚድያ ስራዎች
ከደወል የሬዲዮ
ፕሮግራም ቀደም ሲልም በሀገራችን ቀዳሚ በሆነው የኤፍ ኤም አዲስ 97.1 ላይ በርካታ ባለተሰጥኦዎችን ባፈራው የብዕር ትሩፋት
በተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ለ3 አመታት ጽሁፎችን
በመጻፍና በማቅረብ የጋዜጠኝነት ጅማሮውን አድርጓል።
በደወል የሬዲዮ ፕሮግራም በዋና አዘጋጅነት እና አቅራቢነት እየሰራም
ተቀማጭነቱን ሀገረ- አውስትራሊያ ባደረገው SBS ሬዲዮ የአዲስ አበባ ወኪል በመሆን እና ከፍተኛ ድፍረትና ሀላፊነትን በመውሰድ
የሰራ ሲሆን ይህ ስራም ለአስራ አምስት አመታት አሁን ድረስ ቀጥሏል።
ከዚህ በተጨማሪም
የደወል የሬዲዮ ፕሮግራምን መቋረጥን ተከትሎ ለረጅም አመታት
ሲያብሰለስለው ወደ ቆየውና አሁን ድረስ ከፍተኛ ተቀባይነትን ያገኘበትን እንዲሁም መገናኛ ብዙሀን ለንባብ ተገቢውን ትኩረት
እንዲሰጡ ያስቻለበትን ህልም ወደ ተግባር ለመለወጥ ችሏል። በእናት የማስታወቂያ ስራዎች ድርጅት ስር ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ
ላለፉት አስራ አንድ አመታት የዘለቀው ብራና የሬዲዮ ፕሮግራምን በባለቤትነት እና በዋና አዘጋጅነት በመምራት መጓዝ ችሏል።
በሀገራችን ያለውን ደካማ የማንበብ ባህል ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ
ከፍተኛውን ሚና የተጫወተውና ማንበብ ሙሉ ሰው ያደርጋል በሚል ሀይለ መልእክቱ በሚታወቀው ‹‹ብራና የሬዲዮ ፕሮግራም ››በኤፍ
ኤም አዲስ 97.1 ዘወትር እሁድ ምሽት ከሚቀርበው ተጽዕኖ ፈጣሪው የሬዲዮ ፕሮግራምን አላማ ለማስተዋወቅና የንባብ ባህልን
ለማዳበር በማለም መልእክቶችን ይዞ በ2004 ዓ.ም በተካሄደው ታላቁ ሩጫ ላይ የደህንነት ሰዎች አይን ውስጥ በመግባቱ ተይዞ
ለ11 ቀናት በካዛንቺስ የቀድሞው 6ኛ ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰርም
ምክንያት ሆኖታል።ህገ መንግስቱን ለመናድ እና ህዝባዊ አመጽ ለማስነሳት በሚሉ ከፍተኛ እስርን እና አደጋን በሚጋብዙ ክሶች
ለአመታት ፍርድ ቤት በክርክር የተመላለሰው ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ
በመጨረሻም ክሱን በመርታቱ ፍርድ ቤት በነጻ አሰናብቶታል።
ይህ እስር መልኩን
እየለወጠም በቅንጅት እና በመድረክ አባልነት በማስጠርጠር ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂዎችን በሚኖርበት ቀበሌ 07 አመራሮች ለቤተሰቡና
በግልም ለእርሱ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎችን እንዲደርሰውና የፌስ ቡክም ሆነ የግል ስልክና ሌሎች መገልገያዎች ዘወትር በክትትል
ስር እንዲሆን አድርገውት ቆይተዋል።
በንባብ ላይ ያለው አበርክቶ
ከዚህ በተጨማሪም
በ2004 ዓ. ም በሀገራችን በግል ድርጅት ስር ለመጀመሪያ ጊዜ የተካሄደውን የተነባቢ መጽሀፍት የሽልማት መርሀ ግብር
በመጀመርም ሌሎች በዘርፉ ላይ በንቃት እንዲሳተፉ እና ደፍረው እንዲሰሩ ፈር ቀዳጅ ስራ አከናውኗል። በንባብና ንባብ ተኮር
እንቅስቃሴዎች ያለውን ፈር ቀዳጅነት በማስቀጠልም በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተለያዩ የመጻህፍት ሽያጭ፣አውደ ርዕይና
ውይይት እንዲከናወን በማድረግም አሻራውን አስቀምጧል። አዲስ አበባ፣አዳማ እና ሀዋሳ የተከናወኑት መርሀ ግብሮች በዚህ ረገድ
ተጠቃሾች ሲሆኑ በትብብርም ከኢትዮጵያ ብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻህፍት ኤጀንሲ ጋርም በመላው ኢትዮጵያ የተለያዩ
የመጻህፍት ሽያጭ፣አወደ ርዕይ፣የቤተ መጻህፍት መቋቋምና የመጻህፍት ልገሳዎች እንዲሁም በት/ቤቶች የንባብ ክበባትን በማቋቋም
እና ማረሚያ ቤቶች በትክክልም መታረሚያዎች እንዲሆኑ የተለያዩ መርሀ ግብሮችን በመዘርጋትና አብያተ መጻህፍቶቻቸውን ለማደራጀት
በሚደረገው ጥረት ውስጥ ላለፉት 11 አመታት በመትጋት ላይ
ይገኛል። በዚህም አብዛኛውን የሀገራችንን አካባቢዎች ለማድረስ ተችሏል።
ጋዜጠኛ በፍቃዱ
አባይ በንባብ ላይ ያለውን አበርክቶ በማስፋትም ከሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ እና ከጀርመን የባህል ማእከል ጋር በመተባበር
ለተከታታይ 6 አመታት የዘለቀ ወርሀዊ የመጻህፍት ውይይት መድረኮችን በማዘጋጀትም ለንባብ ባህል ማዳበር የሚያስቀምጣቸውን ጡቦች
ብዛት ከፍ አድርጓል።
ትውልድን በመቅረጽም
ረገድ በሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በነጻ ስልጠና የሚወስዱ ወጣቶች በስነ-ጽሁፍ አሰልጣኝነት በማስተማር ለሶስት አመታት ያህልም
አገልግሏል።
በሀገራችን የስነ
ጽሁፍ ምሽቶች ረገድ ፈር ቀዳጅ እና ተወዳጅ በመሆን አሁን ድረስ የዘለቀውን ጦቢያ ጃዝን በእናት የማስታወቂያ ስራዎች
አማካኝነት በማስተባበርም ድርሻው የተወጣ ሲሆን ብራና የተሰኘውን ኢትዮጵያዊ ብራንድ በማስዋወቅ ላይ ትኩረቱን በማድረግም ብራና
ማስታወቂያ ሃ/የተ/የግ/ማህበርን በማቋቋም ብራና ወርሀዊ የኪነ ጥበብ ምሽትን እና ብራና ወርሀዊ የመጻህፍት ውይይትንም
በማካሄድ ላይ ይገኛል።ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ በኢቲቪ ዘውትር ሀሙስ ምሽት ይቀርብ በነበረውና ትኩረቱን በአርክቴክት ላይ
ባደረገው አርኪ ካሜራ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ላይ አስ ደናቂ የአለማችንን ታላላቅ ግንባታዎችን በመተረክ፣በአዲስ ቲቪም በዜና
አንባቢነት በመስራት አገልግሏል።
በሚወደው የኢትዮጵያ ቡና ስፖርት ክለብ የደጋፊዎች ማህበር ውስጥም በህዝብ
ግንኙነት የስራ መደብ አገልግሏል።
የበጎ ፈቃድ አገልግሎት
ላለፉት 3 አመታት
በጉዞ ሚዲያ ሃ/የተ/የግ/ማህበርን ከሌሎች አጋሮቹ ጋር በመሆን ያንቀሳቀሰው በፍቃዱ አባይ አሁን ደግሞ በብራና ዳግም ሌሎች
እንቅስቃሴዎችን እያደረገ ይገኛል። ከእነዚህ መደበኛ ስራዎቹ ባሻገርም የቀድሞውን የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች ህብረትን
በጋራ በማቋቋም በሀገራችን የተለያዩ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ የበጎ ፈቃድ ተሳትፎዎች እንዲደረጉ ከሌሎች
አጋሮቹ ጋር በመሆን ከፍተኛ ሚናውን ተወጥቷል። በዚህ ረገድ በጣና ሀይቅ ላይ የተበራከተውን የእንቦጭ አረምን ከሀይቁ ላይ
እንዲወገድ በህብረቱ ስም ያደረጉት ንቁ ተሳትፎ እና ከፍተኛ ተጽእኖዎች አረሙን በተመለከተ የፌዴራል መንግስት ጭምር ልዩ
ትኩረት እንዲሰጠው ማድረግ መቻሉና የጣና ሀይቅን ብዝሀ ህይወት ለመጠበቅ እየተሰሩ የለውጥ እና ተስፋ ሰጪ ጅምሮች እንዲደረጉ
የማስተባበርና የመምራት ሀላፊነቱን ተወጥቷል።
ይህንን እንቅስቃሴ
ከፍ በማድረግ የአሁኑን የኢትዮጵያ በጎ ፈቃደኛ ጋዜጠኞች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ለሰብአዊ መብቶች ማህበርን በማቋቋም እና
በሰብሳቢነት በመምራት ጋዜጠኞች እና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች በጋራ ሆነው በበጎ ፈቃድ አገልግሎት ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ
እንዲሁም ሙያተኞቹ ሀገርን እና ህዝብን በመምራት ረገድ የሚጠበቅባቸውን እንዲወጡ ለማድረግ ከሌሎች ባልደረቦቹ ጋር በመሆን
እየሰራ ይገኛል። የደም ልገሳ፣የበጎ አድራጎት፣የኮቪድ 19 ስርጭት የግንዛቤ ማስጨበጫ፣ትኩረትና ፍቅር ለትግራይና ለመተከል
የድጋፍ አስተባባሪ ከብዙ በጥቂቱ የተጠቀሱ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳታፊ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛል።
ከመደበኛ
የጋዜጠኝነት ስራው ባሻገርም የተለያዩ ትልልቅ መድረኮችን
በማጋፈር፣ዝግጅቶችን በማስተባበር ፣የሬዲዮና የቴሌቭዥን ማስታወቂያዎችን በማዘጋጀት እና በማንበብም ሙያዊ እና የዜግነት
ግዴታውን በመወጣት ላይ ይገኛል። ጋዜጠኛ በፍቃዱ አባይ ለእናት ሀገሩ ኢትዮጵያ ትልቅ ፍቅር ያለው ሲሆን ይህን ታላቅ ፍቅሩንም
ሀገሩን ከልብ በማገልገል ይወጣዋል፡፡ ህይወት ብዙ አስተምራኛለች
የሚለው በፍቃዱ ከዚህ በላይ የማደግ የመስራት ህልም እንዳለው ይናገራል፡፡ በተለይ በሀገራችን በዋናነት እያንዳንዱ
ሰው የእውቀት አድማሱ ማስፋት አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ መንገድ ያለፈው በፍቃዱ ሌሎች ማገዝ ስለቻለ እግዚአብሄርን ከልቡ ያመሰግናል፡፡ ጋዜጠኛ በፍቃዱ ጋብቻ መስርቶ የ2
ልጆች አባት ሆኗል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ