118.ስንዱ አበበ  መሐመድ   senedu abebe mohammed

 ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ እስካሁን መስፈርቱን የሚያሟሉ ባለታሪኮች ግለ-ታሪካቸውን እየጻፉ እየላኩልን ነው፡፡

 እርስዎም tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ  ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከድርሰትና ስነ-ጽሁፍ ዘርፍ ታሪኳ የሚቀርብላት ሰው  ስንዱ አበበ  መሐመድ  ናት፡፡









                         ትውልድና  ልጅነት 

  ከአቶ አበበ መሐመድና ከወ/ሮ ዙፋን አህመድ ካፈሯቸው  ከ5 እህትና ወንድሞቿ መሃልም 3ኛ ልጅ ነች። በ1961 ዓ.ም  አዲስ አበባ ተወልዳ ትምህርቷን ወ/ሮ ቀለመወርቅ አርበኞችና መድሃኒያለም ተምራለች።

                     እንደ ጋዜጠኛ

ስንዱ መፅሐፍ ማንበብ የጀመረችው በልጅነቷ ነው። አባቷ አንባቢ ስለነበሩ መፅሃፍ በቅርቡ የማግኘት እድሉን  አግኝታለች። በዚህ አጋጣሚ ነበር ጋሼ ስብሃትን አንብባ አድናቆቷ ሲበዛ ፈልጋ ያገኘችው! እንኳንም አገኘችው!ምናልባት ስንዱ ጋሼ ስብሃትን ባታገኛቸው ምናልባትም ዛሬ ሌቱም አይነጋልኝምን ፣ትኩሳትን ና ሰባተኛው መልዐክ ስራዎችን ማንበብ ባልቻልን ነበር። ምክንያቱም ለአመታት በሳጥኗ አስቀምጣ ያኖረችው እርሷ ናትና። የባለቅኔው ምህላንም ከወደቀበት አንስታ ለህትመት ያበቃችውም ይህችው እንስት ነች! ይህ ብቻ አይደለም 10 አመታትን  በጋዜጠኝነት ያገለገለችው ስንዱ አበበ እንደ ጋዜጠኛ ባለሙያነቷ የደራሲዎችም ሆነ የተራው ህዝብ ጉዳይ ይመለከታት ብቻ ሳይሆን ግዴታዋንም ታውቅ ነበርና " መንግስትዎ ሁሉንም እንደ ፖለቲከኛ ያያል ተብሎ ይወቀሳል፤ እንደነከበደ ሚካኤል ያለ ደራሲ እርግጠኛ ነኝ እርስዎም በሳቸው መፅሃፎች ተምረዋል! እንደነ ስብሃት ያሉ ደራሲም ፤ በቅርቡም የግንደ ቆርቁር በሽታ መድሃኒት ያገኘ ወጣት አይበረታቱም ለምን?" ስትል ሙያዊ መብቷን ተጠቅማ ጥያቄ ለቀድሞው ጠ/ሚኒስትር  መለስ ዜናዊ በማቅረቧ ከስራዋ ልትታገድ ችላለች። ምንም ከስራዋ ብትታገድም ጥያቄዎቿ ግን በከፊል መልስ አግኝተውላት ለደራሲ ከበደ ሚካኤል መኖሪያ ቤት ሲሰጥና የክብር ዶክትሬትም ሲያገኙ የጋሼ ስብሃት ስራዎችም ለህትመት ሊበቁ ችለዋል! "በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ" ትለናለች ።









         የስነ-ጽሁፍ ዝንባሌና  አሳታሚነት 

ስንዱ 10  መፅሀፎችን አሳትማለች፡፡ ከዛ ውስጥ 2ቱ የራሷ ድርሰቶች ናቸው። "ከርቸሌ በውስጥ አይን" እና "ራምቦ" ይሰኛሉ። ራምቦ ከመፅሃፍነትም ባሻገር ሙዚቃም ተሰርቶበታል። ሌላም ""አብረን እንጓዝ" የሚል የጉዞ ማስታወሻዎች ስብስብ በመቅደላና በአካባቢው ዙሪያ የተፃፈ የህዝቡንም ምስክርነት የያዘ ፅሁፍ ሬድዮ ፋና ስራ አስኪያጅ ጋር ቀልጦ ቀርቶብኛል፤ የፕሮግራሙ ክፍል ሃላፊ አንብበውት "ስራ አስኪያጁ መፍቀድ አለበት"ብሎኝ ራሴ እንድሰጣቸው ገፋፍተውኝ ሰጥቻቸው ፀጥ አሉኝ አማላጅ ብልክባቸውም ከለከሉኝ፤ በቁሜ የቀበሩኝ ያህል ይሰማኛል፤ ግን አንድ ቀን ህዝብ ይፈርደኛል!" ትላለች።

  ካሳተመቻቸው መፅሃፎች ውስጥ አንዱ የሆነው "ማሃልዬ ማሃልዬ ዘ ካዛንችስ" የተሰኘው መፅሃፍ ያሳተመችው ሜጋ ሲሆን የሜጋ ስራ አስኪያጅዋ የቀድሞዋ እመቤት ወ/ሮ አዜብ ሜጋ ሱቆች እንዳይገባ ስላገዱባት ለኪሳራ ተዳርጋለች።  ይህ መፅሐፍ በፈረንሳይኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ታትሟል ። ይህ ብቻም ሳይሆን ሲራኖ የተሰኘውም መፅሃፍ እዛው ሜጋ ተበላሽቶባት "ለምን?"ብላ ብትጠይቅ ከመልስ ይልቅ ዛቻ ደርሷት እንባዋን ረጭታለች። 3ሺ ኮፒዎችን አቃጥላም ሌላ ቦታ አሳትማው ለህዝብ ትክክለኛውን አቅርባለች።በዚህ ፈተና አልፋ ያቀረበችልንን ስራ  ምን ያህሎቻችን አውቀነው አንብበነዋል? መልሱን ለራሳችን።

          በፖለቲካው ዘርፍ 

ከዚህ በተጨማሪም በፖለቲካው ዘርፍም በ 1997 እጩ ተወዳዳሪም ነበረች ፤ምልክቷም ብዕር ነበር።

 አንድ እሷ ለብቻዋ ሰላማዊ ሰልፍ የወጣች በራስ መተማመኗ ጥግ የደረሰ ተደናቂ ሴት ነች።

   ስንዱ በአሁን ሰአት የምትኖረው አሜሪካ ኒው ጄርሲ  ውስጥ ነው ።   ለሀገሯ ብዙ ስራ ማበርከት የምትችል ሴት በደረሰባት ግፍ ሀገሯን ጥላ ለመሰደድ ተገዳለች ።

 በሃገሯ ጋዜጠኛነት እና ደራሲነት ወደ ሰው ሀገር የጉልበት ሰራተኝነት ልትሸጋገር ተገዳለች። እርግጥ "ሀገሬ ለኔ ህሊናዬ ነው" ብላ የምታምን ሴት ነች። ግን ምንስ ቢሆን ተወልደው ቦርቀው እንዳደጉበት ሰላም ማግኛ አለን?  እንደዛም ሆኖ "አላማርርም!  ጥበብን ጥበብን ሲሉ በህይወታቸው ከፈረዱ ጓደኞቼ ተምሬአለሁ፤ ዛሬን አሁንን መኖር መልካም ነው " ትለናለች ።

ስንዱ አበበ ተዋናይ ፣ ጋዜጠኛ ና አሳታሚ ሆና አገሯን አገልግላለች፡፡







አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች