117. ኤቢሳ ባይሳ 46 መጽሀፎችን በአፋን ኦሮሞ ጽፎ ያሳተመ

ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በፊልም ፤ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እናስተዋውቃለን፡፡ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ5 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ በስነ-ጽሁፍ ዘርፍ በተለይ በአፋን ኦሮሞ 46 መጽሀፍትን ጽፎ በማቅረቡ ታሪኩ የሚቀርብለት ታታሪ ሰው ኤቢሳ ባይሳ ነው፡፡  

 ኤቢሳ ባይሳ 46 መጽሀፎችን በአፋን ኦሮሞ ጽፎ ያሳተመ

                      ትውልድና ልጅነት

 ኤቢሳ ባይሳ አቤቱ ከአባቱ መምህር ባይሳ አቤቱ እና እናቱ ወ/ሮ ብርቂ ለሙ  ጥቅምት 17፣ 1979 ዓም በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ሊሙ ወረዳ በሪሶ ደንጌ ቀበሌ ተወለደ፡፡ ዕድሜው ለትምህርት ሲደርስ በሊሙ አንደኛ ደረጃ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን ተከታተለ፡፡ ቀጥሎም በሊሙ ሁለተኛ ደረጃ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በመከታተል በ1996 ዓም የመሰናዶ ትምህርቱን ለመከታተል ወደ ጊዳ አያና ወረዳ አቀና፡፡

                   የዩኒቨርሲቲ ቆይታ

 ከ 2 ዓመት ቆይታ በኋላ በ1998 ዓም ዲላ ዩኒቨርሲቲ በመግባት በባዮሎጂ የመጀመሪያ ዲiግሪውን መማር ጀመረ፡፡ ይሁን እንጂ በጠና በመታመሙ ምክንያት ከአንድ ሴሚ ስተር  ቆይታ በኋላ ትምህርቱን በማቋረጥ ወደ ቤተሰቡ ተመለሰ፡፡ ከአንድ ዓመት የህክምና ክትትል በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው በመመለስ ትምህርቱን አጠናቀቀ፡፡

             የስራ አለም

የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ለስራ አዲስ አበባ ከተማ ተመድቦ ሽሮ ሜዳ የሚገኝ እንጦጦ አምባ ሁለተኛ ደረጃ ትምህር ት ቤት የባዮሎጂ መምህር በመሆን 4 ዓመታት አገለገለ፡፡ ከማስተማር ስራው ጎን ለጎን ሁለተኛ ዲግሪ ትምህርቱን ተከታትሎ በስነ-መማከር (ካውንስሊንግ)  ከተመረቀ በኋላ አንድ የግል ድርጅት በመቀጠር ከመስከረም 2005 እስከ ታህሳስ 2008 ዓም አገለገለ፡፡

          በአንድ ፕሮግራም  10  መጻህፍትን ማስመረቅ

ከልጅነቱ ጀምሮ ስኬታማ ደራሲ የመሆን ህልም የነበረው ኤቢሳ የመጀመሪያ መጽሐፉን በነሐሴ 2004 አሳተመ፡፡ የመጽሐፉ ርዕስ ‹‹ሚልቶ›› የሚል የአፋን ኦሮሞ ቃል  ሲሆን ትርጉሙ አብሮ ተጓዥ ጓደኛ ማለት ነው፡፡ የስነ-ጽሑፉን ስራ በትጋት ቀጥሎበት በ2009 ዓ.ም በሀገሪቱ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በአንድ ፕሮግራም 10 መጻህፍትን ማስመረቅ ችሏል፡፡ የራሱን መጽሐፍት ከመጽሀፍ ባሻገርም የሌሎች ደራሲያን መጻሕፍትን ከእንግሊዝኛ ቋንቋ ወደ አፋን ኦሮሞ በመተርጎም ለቋንቋው እድገት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡










                ራስ አገዝ መጻሕፍት

ራስ አገዝ መጻሕፍት ላይ ትኩረት ቢያደርግም ሌሎች መልዕክቶችንም የያዙ መጽሃፍትን በማዘጋጀት ህዝቡን አስነብቧል፡፡ ልቦለድ፣ ግጥም፣ የህይወት ታሪኮች፣ ጠቅላላ  ዕውቀት፣ መንፈሳዊ መጻሕፍት፣ መዝገበ- ቃላት ወዘተ አዘጋጅቶ አሳትሟል፡፡ በአጠቃላይ  ይህ ጽሑፍ እስከተዘጋጀበት ጊዜ ከ46 መጽሐፍት በላይ ጽፎና ተርጉሞ ህዝብ ማስነበብ ችሏል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ከስነ-ጽሑፍ ስራው ጎን ለጎን የ3ኛ ዲግሪ ትምህርቱን በመከታተልና በተለያዩ ቦታዎች የሳይኮሎጂና መንፈሳዊ ስልጠናዎችን በመስጠት ላይ ይገኛል፡፡

ኤቢሳ ባይሳ እስካሁን ለሰራው ስራ የኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ  ኔትወርክ በ2012 ዓ.ም ለኦሮሞ ህዝብ ትልቅ ውለታ የዋሉ ብሎ የሸለማቸው 7 ሰዎች  መሃል አንዱ ነው፡፡ የ 2 ሴት ልጆች አባት የሆነው ኤቢሳ ከባለቤቱ ከደሴ ገመቹ እና ከልጆቹ ከሲፈን እና ሲነን ጋር በአዲስ አበባ ከተማ ይኖራል፡፡ ወደፊትም ባለው እውቀትና ችሎታ ህዝቡን ለማገልገል ትልቅ ራእይ አለው፡፡








አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች