115 .ተጓዡ
ጋዜጠኛ ------ ሄኖክ ስዩም ደምሴ
ትውልድ እና እድገት
‹‹ተጓዡ ጋዜጠኛ›› በሚል ቅጽል ስሙ የሚታወቀው ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም የቤተክህነት አገልጋይ ከሆኑት ከአለቃ ስዩም ደምሴና ከወይዘሮ ስንቅነሽ ዳኜ በአዲስ አበባ ከተማ ዘነበወርቅ በሚባለው ሰፈር ጥቅምት 5 ቀን 1975 ዓ.ም. ተወለደ፡፡
ተወልዶ በአደገበት
ዘነበ ወርቅ አባ ታምሩ ከሚባሉት በአካባቢው የታወቁ የቄስ ትምህርት ቤት መምህር ፊደልን ቆጠረ፡፡ በልጅነቱ በደብረ ከዋክብት
አቡነ አረጋዊ እና ቅዱስ ገብረ ክርስቶስ ቤተ- ክርስቲያን ያደገ ሲሆን ከወንጌል እስከ ውዳሴ ማርያም ደግሞ ሊቀ -ጠበብት
እሸቴ ጎሹ ከተባሉት መምህር ዘንድ ተምሯል፡፡
አንደኛ ደረጃ ትምህርቱን በቀድሞው ልዕልት ዘነበ ወርቅ በአሁኑ ብሩህ ተስፋ ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን የተከታተለው በአየር ጤና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው፡፡
የስነ-ጽሁፍ ዝንባሌ
ለሥነ-ጽሑፍ
ከልጅነቱ ጀምሮ በነበረው ፍቅር ሬድባርና ኢትዮጵያ በተባለ ግብረ ሰናይ ተቋም ውስጥ በህጻናት ኪነት ውስጥ ሰርቷል፡፡ አንደኛ
ደረጃ ተማሪ ሆኖም በሬዲዮ ፋና ‹‹የከርሞ ሰው›› የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ ስራዎቹን ያቀርብ ነበር፡፡ ውበት አማተር የጋዜጠኞች
ክበብን የተቀላቀለው የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሆኖ ነው፡፡
የሁለተኛ ደረጃ
ትምህርት ቤት ተማሪ ሆኖ በወርሃዊው የፑሽኪን የሥነ-ጽሑፍ ምሽት ንቁ ተሳታፊ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ ወቅት ‹‹ወራዙት››
የሚባል መደበኛ ወጣቶችና ኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ የሚያተኩር በአቤኔዘር ፕሮሞሽን እየተዘጋጀ በሚታተም ጋዜጣ ላይ በአዘጋጅነት
ሰርቷል፡፡ የተለያዩ ግጥሞችን በመጻፍ የሚታወቅ ሲሆን ያልታተሙ የግጥም ሥራዎችም አሉት፡፡ሄኖክ ስዩም ባንኪንግና ኢንሹራንስ፣
ጋዜጠኝነትና የእጽዋት ሳይንስ ስልጠናዎችን ተከታትሏል፡፡
የጋዜጠኝት ህይወት
በከርሞ ሰው የሬዲዮ
ፕሮግራም ስራዎቹን በማቅረብ የጋዜጠኝነት ህይወትን የተቀላቀለው ሄኖክ ስዩም በሬዲዮ ፋና ለ2 አመታት በነበረው ቆይታ ባህልና
ኢትኖግራፊ ላይ ያተኮረውን "ህብር" የተባለ መሰናዶ እና "ሬዲዮ ቱር" የተባሉ ፕሮግራሞችን
በመስራት የሀገራችንን ባህልና አኗኗር አስተዋውቋል፡፡ በሬዲዮ ፋና ቆይታው ከጉዞና ጉብኝት ፕሮግራሞቹ ባሻገር "አውደ
ልማት" "መልካም አስተዳደር" እና "ግብርና" የተባሉ ፕሮግራሞች ቋሚ አዘጋጅ ሆኖ
ሰርቷል፡፡
ሀገሬ ሚዲያ
ኮሙኒኬሽን የተባለ ቱሪዝም ላይ ያተኮረ ድርጅት በመመስረትም የተቋሙን የሚዲያ ሥራዎች በመምራትና በሥራ አስኪያጅነት ይሰራ
ላለፉት 11 አመታት እየሰራ ይገኛል፡፡ በዚሁ ድርጅት የሚታተመውንና በመደበኛነት በአማርኛ ቋንቋ እየተዘጋጀ የሚሰራጭ
ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቀውን ‹‹ቱባ›› መጽሔትን በማኔጅንግ ኤዲተርን እየመራ አዘጋጅቶ ያሳትማል፡፡
ኢትዮጵያን
የሚያስተዋውቀውን ‹‹ጉዞ ኢትዮጵያ›› የተባለ ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ፕሮግራም በመጀመርም በጄቲቪ እና በኢኤንኤን የቴሌቪዥን
ጣቢያዎች ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ጉዞ ኢትዮጵያን በየሳምንቱ በፋና ቴሌቪዥን እያዘጋጀ አየር ላይ ያውላል፡፡
በተለያዩ የዲጂታል
ሚዲያዎች ላይ በጉዞና ጉብኝት ዘገባዎች በፍሊራንስ ጸሐፊነት እየሰራ ሲሆን በተለይም የድሬ ቲዮብ ቋሚ የጉዞና ጉብኝት ዘጋቢ
ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል፡፡
በብዙ የህትመት
ውጤቶች ላይም በአምደኝነት ሥራዎቹን ለህትመት ያበቃል፡፡ በፍትሕ እና በወይ አዲስ አበባ መጽሔቶች በሳል መጣጥፎችን በመጻፍም
ይታወቃል፡፡
የቱሪዝም
ማስተዋወቂያ ሕትመቶች
ሄኖክ ስዩም፤
የኢትዮጵያን ቱሪዝም ለማስተዋወቅ የተለያዩ የህትመት ውጤቶችን አዘጋጅቶ ለማሳተም በቅቷል፡፡ በዚህም፡-
- የጎንደር ከተማን
የቱሪዝም ማውጫ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች፣
- የደቡብ ጎንደር
ዞን የቱሪዝም ማውጫን በአማርኛ ቋንቋ፣
- የሰሜን ሸዋ ዞን
የቱሪዝም ማውጫን በአማርኛ ቋንቋ
- የኢትዮጵያ
ተፈጥሮና ፓርኮች ማውጫን በአማርኛ ቋንቋ፣
- የኢትዮጵያ
ሙዚየም ማውጫን በአማርኛ ቋንቋ፣
- የኢትዮጵያ
ፌስቲቫል ማውጫን በአማርኛ ቋንቋ፣
- ጎንደርን
ለህጻናት የቱሪዝም መጻሕፍ
- ኮንሶን ለህጻናት
የቱሪዝም መጻሕፍ ለህትመት አብቅቷል፡፡
ኩነት ዝግጅት
- የኢትዮጵያ
ከተሞች ቀን በኩነት አስተባባሪ ዝግጅት ባልደረባነት፣
- የጎንደር
ፌስቲቫል 2003 ዓ.ም.፣2004 ዓ.ም.፣2005 ዓ.ም.፣2006 ዓ.ም.፣ 2007 ዓ.ም.
- የኮንሶ ዩኔስኮ
ፌስቲቫል 2004 ዓ.ም.፣ 2005 ዓ.ም.፣ 2006 ዓ.ም.
- ጎፋ ጋዜ ማስቃላ
በደምባ ጎፋ ሳውላ
- ጎፋ ጋዜ ማስቃላ
በጋልማ ዛላ ጎፋ
ድርሰትና ሥነ-ጽሑፍ
ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም
"ደቦ" እና "አቦል" በተባሉ ሁለት የጋራ ስብስብ መጻሕፍት ሥራዎቹን ከሌሎች ጋር በኅብረት
አሳትሟል፡፡ "የመንገድ በረከት" "ጎንደርን ፍለጋ" እና "ሀገሬን" የሚባሉ
ሦስት የጉዞ መጽሐፍትን በመጻፍ አንባቢያንን ደርሷል፡፡ "ጎንደርን ፍለጋ" እና "ሀገሬን"
ተደጋግመው ለመታተም በቅተዋል፡፡
አባልነትና ኃላፊነት
የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች
ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የቱሪዝምና ሥርጸት ማኅበር አባል ሲሆን የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የጣና
አዋርድ የቦርድ ሰብሳቢ፣ የኢትዮጵያ የፍትሕ ሥርዓት ማዕከል የቦርድ አባል፣ የባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ሚኒስቴር አማካሪ ምክር
ቤት አባል ነው፡፡
እውቅናና ሽልማት
በሚሰራቸው ሥራዎቹ
በርካታ ሽልማቶችን ተቀናጅቷል፡፡ የማይስ ቱሪዝም ሆቴል ሾው አፍሪቃ የምርጥ ቱሪዝም ጋዜጠኝነት፣ የብሔራዊ አረንጓዴ ሽልማት
የህትመት ዘርፍ ጋዜጠኝነት፣ የአርአያ ሰው ሽልማት በቅርስ ማስተዋወቅ ሽልማቶችን ተቀብሏል፡፡
ልዩ መገለጫ
ሄኖክ ስዩም ይህን
የዊኪፒዲያ ጽሁፍ ባዘጋጁት ሰዎች እይታ ለሀገሩ ጥልቅ ፍቅር
አለው፡፡ ይህን ፍቅሩንም በተግባር ለማሳየት ችሏል፡፡ ሄኖክ
የሀገሩን ባህል እንዲሁም እሴት ለማወቅና
ለማሳወቅ በብዙ ኪሎ ሜትሮች አቋርጦ ተጉዞአል፡፡ ብዙዎች ለመሄድ በማይደፍሩት ስፍራ ሄኖክ ይጓዛል፡፡ ይህም
የሚወደውና ከፍተኛ ርካታ የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ ስራ ምንም
ዋጋ ቢያስከፍለው ደስ ብሎትና ወዶት ስለሚሰራው ይዋጣለታል፡፡
ሄኖክ ነገሮችን አዋዝቶ መግለጹን ይችለበታል፡፡ ብዙዎች አብረውት የሰሩት እንደሚመሰክሩት ሄኖክ ባለበት ቦታ ሁሉ ሳቅ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ሙያውን ከልብ ከመውደድ
የሚመነጭ ነው፡፡ አንዳንድ የሚድያ ሰዎች ወደ ክፍለ-ሀገር ፊልድ በሚሄዱበት ጊዜ ሄኖክ አብሮ የሚጓዝ ከሆነ የጋዜጠኞቹን
ምቾት ለመጠበቅ ይሞክራል፡፡ ከሰው ሁሉ ጋር የሚግባባ
በመሆኑም በማስተባበር የሚደርስበት የለም፡፡ ከሄኖክ ጋር አብረው የሰሩ ሰዎች አንዱ የሚመሰክሩት ጉዳይ
በሬድዮ የሚተላለፉ ለ 4 ሳምንት የሚተላለፉ ዝግጅቶችን ቀድሞ ሰርቶ በማጠናቀቁ ነው፡፡ ይህ በተለምዶ ባክሎግ / የተጠራቀመ ዝግጅት/ ተብሎ የሚጠራውን አሠራር በወጉ
ተግባራዊ ያደረገ ሄኖክ ስለመሆኑ ብዙዎች አፋቸውን ሞልተው
ይናገራሉ፡፡ በአጫጭር አረፍተ-ነገሮቹ የሚታወቀው ሄኖክ በቱሪዝም ዘርፍ ከዚህ በላይ የመስራት ግብ አለው፡፡ ከበርካታ መገናኛ
ብዙሀን ጋር ባደረገው ቃለ-ምልልስ እንዳለው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ላይ ገና አልተሰራም፡፡ እናም ያለውን ክፍተት
ለመሙላት ሄኖክ ባለው አቅም እየሰራ መሆኑን ያምናል፡፡ ለኢትዮጵያዊነት ለአንድነት ለእኩልነት ልዩ አመላካከት ያለው ሄኖክ ሀገራችን ታላቅ ቦታ ደርሳ ማየትን ይመኛል፡፡ ያ
ምኞቱ እስከሚሳካ ድረስም ሄኖክ መጓዙን ይቀጥላል፡፡
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣
በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ
በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ
የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት
አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014
የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም
በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ
እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡
በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው
የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ከላይ ታሪኩን ያቀረብንለት ሰው ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም መልካም እድል
እንዲገጥመው እንመኛለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ