114. አዜብ ታምሩ ታደሰ / azeb tamiru
tadesse
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም
፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ
በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ
የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት
አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014
የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም
በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ
እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡
በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ
ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኳን የምናቀርብላት ሴት አዜብ ታምሩ ታደሰ ናት፡፡
ትውልድ፣ እድገት እና ትምህርት
የሬዲዮ እና
የቴሌቪዥን ጋዜጠኛዋ አዜብ ታምሩ ተወልዳ ያደገችው ኮልፌ ልኳንዳ ነው፡፡ ፊደልን በቄስ ትምህርት ቤት
ሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስትያን እስከ ውዳሴ ማርያም ተምራለች፡፡ አንደኛ ደረጃ ትምህርቷን በሰላም በር አንደኛ ደረጃ ት/ቤት እንዲሁም
ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮልፌ አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትላለች፡፡ ከቅድስት ማርያም ዩኒቨርሲቲ በመምህርነት
ዲፕሎማ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ በቋንቋና ስነፅሑፍ በመጀመሪያ ዲግሪ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጋዜጠኝነት እና ኮሙኒኬሽን
በማስተርስ ዲግሪ ተመርቃለች፡፡ ሁሌም በመማር ስለምታምን ለሙያዋ አጋዥ የሆኑ ትምህርቶችን ከመማር ወደኋላ ብላ አታውቅም፡፡
አዜብ የጋዜጠኝነትኝነት ህይወት ው ስጥ እንድትገባ መንገድ
የሆነቻት የሁለተኛ ክፍል መምህሯ መምህርት አስረበብ ናት፡፡ ከተማሪዎች መርጣ ምንባብ ታስነብባት ስለነበር ሁሌም
ታመሰግናታለች፡፡ አዜብ ጋዜጠኝነት ሁሉም ቦታ መገኛ እና ችግር
መፍቻ ሙያ ነው ብላ ታምናለች፡፡ ለዚህም ከትምህርት ቤት ሚኒሚዲያ እስከ አማተር የጋዜጠኛ ክበባት አባል በመሆን ሙያዋን
አዳብራለች፡፡ ወደ ትክክለኛው የሚዲያ ስራ እስክትገባ በጋዜጦች ላይ በፅሁፍ፣ በሬዲዮ ጣቢያዎች ላይም በድምፅ ትሳተፍ ነበር፡፡
ስራን ባለመናቅም ከካፌ አስተናጋጅነት ጀምሮ ተማሪዎችን ቤት ለቤት በማስጠናት የህይወትን ውጣ ውረድ ተጋፍጣ አሸንፋለች፡፡
የጋዜጠኝት የስራ ህይወት
የዛሬው አዲስ ሚዲያ
ኔትወርክ በኤፍ.ኤም ራዲዮ እሁድ የአንድ ሰዓት ፕሮግራም ሲጀምር ከቀዳሚዎቹ አንዷ ነበረች፡፡ የኤች.አይ .ቪ ኤድስ ስርጭት
ባየለበት ወቅት በ1994ዓ.ም ‹‹ይበቃል›› የተሰኘውን የሬዲዮ ፕሮግራም በሚያዘጋጀው ፕሮፕራይድ የአዲስ ከተማ ጋዜጣ
ም/ዋ/አዘጋጅ ሆናም ሰርታለች፡፡በፌዴራል ፖሊስ ቴሌቪዥን ከ1997ዓ.ም እስከ 2002ዓ.ም ለ5 አመታት ፕሮግራም እና ዜና አዘጋጅ
እና አቅራቢ ነበረች፤ ከዚያም በመቀጠል ለ አራት ዓመታት በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ከፕሮግራም አዘጋጅነት እስከ ዜና
ፕሮግራሞች መሪነት በታታሪነት ሰርታለች፤ በዋልታ ኢንፎርሜሽን ማዕከል የሚዲያ ማርኬቲንግ ባለሞያ ሆናም ለጥቂት ወራት አገልግላለች፤ ከዚያም አባይ ኤፍ.ኤም 102.9 ላይ
ለሁለት ዓመታት ሰርታለች፤ ኢ.ኤን.ኤን በተባለው የቴሌቪዥን ጣቢያም ከምስረታው ጀምሮ ለአንድ አመት ሰርታለች፤ ከዚያም ወደ
አርትስ ቴሌቪዥን በማቅናት ከማቋቋም ጀምሮ የዜና ክፍል ኃላፊ በመሆን አገልግላለች፡፡ በመቀጠልም በጠ/ሚኒስትር ፅ/ቤት የሚዲያ
ዳይሬክተር በመሆን እየሰራች ትገኛለች፡፡
ችግሮችን በሙያ የመቀነስ ተሳትፎ
አዜብ ሀገሯን በጣም
ትወዳለች፡፡ "ሀገር ማለት ሰው ስለሆነ በተለይም ለሰዎች ቀና ልብ ያለውን ሁሉ እወዳለሁ" ትላለች፡፡ ቅን
ለሀገር የሚጠቅሙ ሀሳቦች ያሉበት ቦታ አትጠፋም፡፡ በአካባቢዋ የምታየውን ሁሉ በዝምታ የማታልፍ ናት፡፡ የሚደነቀውን ታደንቃለች
የሚወቀሰውንም ያለአንዳች ትወቅሳለች፡፡ በኤች.አይ.ቪ /ኤድስ የተጎዱ ወገኖችን ወደሚዲያ ከማውጣት ጀምሮ ለራሳቸው እና
ለልጆቻቸው ድጋፍ እንዲያገኙ ብርቱ ጥረት አድርጋለች፡፡ በዚህም በወቅቱ በቤተ- መንግስት የምስጋና ፕሮግራም ላይ ተሳትፋለች፡፡
በሀገራችን ያለው የተሸከርካሪ አደጋ አሳሳቢ በመሆኑ በፋና ሬዲዮ ርዕሰ- ጉዳዩን በማጉላት በተለያየ መንገድ ከማስተማር ባሻገር
በከፈተችው ብሌን ሚዲያ እና ኮሙኒኬሽን ድርጅት አማካኝነት ለሶስት ዓመታት በየሳምንቱ ለአንድ ሰዓት ተኩል የሬዲዮ ፕሮግራም
በማዘጋጀት ማህበረሰቡን ለማስገንዘብ አስተዋፅኦ አበርክታለች፡፡ ኢካሽ ፕሮሞሽን በሚሰጠው የጋዜጠኝነት ስልጠና ላይም ብቸኛ ሴት
አስተማሪ በመሆን ለብዙ ጋዜጠኞች ልምዷን እና የጋዜጠኝነት ዕውቀትን አካፍላለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም በግሏ ሴት የአእምሮ
ህሙማንን ከጎዳና ላይ በማንሳት መጠለያ እንዲያገኙ ጥረት ታደርጋለች፡፡ ከዚህ ጋር ተያያዥ በሆነው የአካል ጉዳት ጉዳይ ላይ
የሚዘጋጀው ‹‹ልባዌ›› የተሰኘው የሬዲዮ ፕሮግራም በጎ ፍቃደኛ አቅራቢም
ናት፡፡
የህይወት መርህ
ጋዜጠኛ አዜብ "የመልካም ልብ ባለቤቶች ብንሆን የምድራችን ሀብት
በቂ ነው" የሚል አስተሳሰብ አላት፡፡
"የትምህርት ጊዜ ይጠናቀቃል፤ ከስራ ቦታም ስራን ልንቀይር እንችላለን:: በዚህ መሀል ሰዎች ልብ ውስጥ በበጎነት እንድንታወስ ደጎች እንሁን
ትላለች"፡፡ በሰራችባቸው ቦታዎች ሁሉ ብዙ መልካም ተግባራትን አከናውናለች፡፡ "ሁሉንም ነገር ትቼ እየሄድኩ
ነው ፤ ለሰው መዳን እና ደስታ ምክንያት የሆንኩባቸው ቀናት የእኔ ትክክለኛ ቀኖች ናቸው" ትላለች፡፡ ሌሎችም ይህንን
እንዲጋሩ ጥረት ታደርጋለች፡፡ "ሰው በንባብ መገንባት እና መበልፀግ አለበት፤ ካላነበበ ያጎደለው ነገር እንዳለ ማወቅ
ይኖርበታል" ስትልም ታሳስባለች፡፡
እውቅናና ሽልማት
አዜብ ታምሩ ፣ባገለገለችባቸው ቦታዎች ሁሉ
ፈጥና ዕድገት የምታገኝ ታታሪ ሰራተኛ እና በስነ-ምግባር የተሞላች ናት፡፡ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ እና በተሸከርካሪ
አደጋ ቅነሳ ላይ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የተለያዩ ምስክር ወረቀቶችን አግኝታለች፡፡ በ2012 ዓም የሬዲዮ ቀን ሲከበር የምርጥ
ሬዲዮ ፕሮግራም ተወዳዳሪ እና ከአሸናፊዎቹም አንዷ ናት፡፡
ልዩ መገለጫ
አዜብ ታምሩ ፈገግታ
ከፊቷ አይጠፋም፡፡ ለውትድርና ህይወት ትልቅ ክብርም አላት፡፡ እናም የውትድርና ስነ-ምግባር ሁሌም አብሯት አለ፡፡ ይህን
የዊኪፒዲያ ጽሁፍ ባዘጋጁት ሰዎች እይታ ከተጎዱ እና ካዘኑ ሰዎች ጎን የመቆም እና ችግር የመፍቻ መንገድ ለመሆን ፍላጎት አላት፡፡ ይህንን በተግባር በማሳየትም በተለይ ጎዳና ላይ የወደቁ
ሰዎችን በግሏ ከድርጅቶች ጋር በመነጋገር እንደ መቄዶንያ ካሉ የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ድርጅቶች ጋር በመተባበር እንዲያገግሙ
አድርጋለች ፡፡ በዚህም ተግባሯ የተለያዩ ማህበራት እና ስብስቦች ውስጥ በበጎ ፍቃደኝነት በማገልገል ትታወቃለች፡፡
"በዓመት አንድ ሰው ከጎዳና አንስቼ ማስጠለል አለብኝ "በሚል መርህ ይህንን ስራዋን ላለፉት አምስት ዓመታት ገፍታበታለች፡፡ አሁንም ለኢትዮጵያ መስራት አለብን በዚህ ምድር ላይ ስንኖር አንድ አሻራ
ማኖር ይጠበቅብናል የምትለው አዜብ ከአሁን በኋላም ሀገር
የሚጠቅም ስራ ለማከናወን ለራሷ ቃል ገብታለች፡፡ አዜብ የሁለት
ሴት ልጆች እናት ናት፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ