113 . መዓዛ መላኩ Meaza Melaku
የዚህ ታሪክ
አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ
ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች
እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ
መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት
አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014
የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም
በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ
እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡
በ6 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ
ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ከሚድያ ዘርፍ ታሪኳን የምናቀርብላት ሴት መአዛ መላኩ አሉ ከሚባሉ የምልክት ቋንቋ አስተርጓሚዎች አንዷ ስትሆን
አጭር ታሪኳን እንደሚከተለው እናቀርባለን፡፡
ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት
መአዛ መላኩ ፣
አዲስ አበባ ከተማ መነን በሚባል ሰፈር ነው የተወለደችው፣ በቀኝ እጅ ግራ ጆሮን መያዝ የመግቢያ ፈተና በነበረበት
ወቅት፣ 5 ዓመት ሊሞላት 3 ወራት ሲቀሩ ነው ትምህርት የጀመረችው፡፡ ይህም በትምህርት ቤት ቆይታዋ መምህራኖችዋና ጓደኞቿ
የሚሳሱላት የክፍሉ ትንሹዋ ተማሪ አድርጓታል፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ
ትምህርቷን ፀሐይ ጮራ 1ኛ ደረጃ ት/ቤት፣ 2ኛ ደረጃ ትምህርቷን ደግሞ በቀድሞ ተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተከታትላለች፡፡
ልዩ ፍላጎት ትምህርት ዘርፍ
ሕግ መማር የልጅነት ህልሟ የነበረ ቢሆንም በታሪክ የመጀመሪያ ዲግሪዋን
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተከታትላለች፡፡ በኢትዮጵያ ምልክት ቋንቋና መስማት የተሳናቸው ባህል ከዛው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
ሌላ ዲግሪ የተማረች ሲሆን የፋክሊቲዋ ሰቃይ ሴት ተማሪም ነበረች፡፡ በመቀጠል ለከፍተኛ ትምህርት ወደ ኖርዌይ በማቅናት ከኦስሎ
ዩኒቨርስቲ በልዩ ፍላጎት ትምህርት ዘርፍ ሁለተኛ ዲግሪዋን ሰርታለች፣ International Child Development
Program (ICDP) አለም አቀፍ የህፃናት አስተዳደግ የአሰልጣኝነት ሰርተፍኬት ከኖርዌይ ዩኒቨርሲቲም አግኝታለች፡፡ በርካታ
ስልጠናዎችን ለተለያዩ መምህራንም ሰጥታለች፡፡ በመስጠት ላይም ትገኛለች፣ እዚያው ኖርዌይ በሚገኝ ኦስሎ ሜትሮ ፖሊታን በሚሰኝ
ዩኒቨርሲቲ ኢንተርናሽናል ኤጁኬሽን ኤንድ ዲቨሎፕመንት ትምህርት ክፍል (International education and
development) ሌላ ማስተርስ የመማር እድል አግኝታ ኮርሶቹን አጠናቅቃ ጥናታዊ ፅሑፍ (research) መስራት ሲቀራት
ወደ ሃገሯ ተመልሳለች፡፡
የምልክት ቋንቋ ስልጠናን ወሰደች
ተፈሪ መኮንን
ት/ቤት ተማሪ ሳለች በርካታ ማየት የተሳናው ጓደኞች የነበሯት ሲሆን ለበርካታዎቹ የትምህርት መርጃዎችንና የፅሁፍ መረጃዎችን
በማንበብ ታግዛቸው ነበር። ለምልክት ቋንቋ ያላት ዝንባሌ የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ እያለች ከመማሪያ ክፍሏ ፊትለፊት
የሚማሩ መስማት የተሳናቸው ተማሪዎችን በማየት ነበር። ሆኖም መደበኛ ምልክት ቋንቋን የመማር እድል ያገኘችው ግን የዩኒቨርሲቲ
ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ በምስካየ ህዙናን መድሃኔዓለም ገዳም የተምሮ ማስተማር ሰ/ት/ቤት ለአባላቶቹ ያዘጋጀው የምልክት ቋንቋ
ስልጠናን ወሰደች፣ ለሰንበት ትምህርት ቤቱ መስማት የተሳናቸው አባላት ስብከት እና ቅዳሴ የማስተርጎም አገልግሎት መስጠት
ጀመረች፡፡
በምልክት ቋንቋ አስተርጓሚነት
በአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል ተማሪ ሳለችም ለዳግማዊ ምኒሊክ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት መስማት ለተሳናቸው ተማሪዎች
በአስተርጓሚነት በወር ደሞዝ 630 ብር እየተከፈላት ስራ ጀመረች፡፡ ህይወቷ ከአካል ጉዳተኞች ጋር በእጅጉ የተሳሰረ ነበር፡፡
የመመረቂያ ፅሑፏን
የሰዐሊ አፈወርቅ መንገሻ (መስማት የተሳናቸ ው ሰዐሊ ናቸው፣ በተለይ ጊዮን ሆቴል ሳባ አዳራሽ የንግስት ሳባንና የንጉስ
ሰሎሞንን የጣራ ላይ ስዕላቸው እናውቃቸዋለን) የህይወት ታሪክ እና መስማት በተሳናቸው ብሔራዊ ማህበር አመሰራረትና ታሪክ ላይ
ያጠነጠነ ነበር፡፡
ሁለት ዓመታት
እዚያው በዳግማዊ ሚኒሊክ 2ኛ ደረጃ ት/ቤት ሰርታች፣ በመቀጠልም ጥቁር አንበሳ ት/ቤት በታሪክ መምህርትነት እና በምልክት
ቋንቋ አስተርጓሚነት ለ3 ዓመታት ሰርታለች፣ ከዚህ ጎን ለጎን በበርካታ በጎ ፈቃድ ስራዎች ላይ የተሳተፈች ሲሆን በተለይ
በኢትዮጵያ ሴት አካል ጉዳተኞች ብሔራዊ ማህበር በርካታ ስራዎችን አከናውናለች።
በኢትዮጵያ
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት የምልክት ቋንቋ ክፍል ሳምንታዊ የቴሌቪዥን ዝግጅቶችን በማዘጋጀትና በምልክት ቋንቋ ጭምር በመተርጎም
ለ5 ዓመታት ሙያዊ አደራዋን ተወጥታለች።
አለም ዓቀፋዊና ሃገራዊ ኮንፈረንሶች ላይ በአስተርጓሚነት
የሕዝብ ተወካዮች
ምክር ቤትን ጨምሮ አለም ዓቀፋዊና ሃገራዊ ኮንፈረንሶች ላይ በአስተርጓሚነት ሰርታለች፣
በፍቃደኝነት ላይ
የተመሰረተ የኤች አይ ቪ ኤድስ ምክክርና ምርመራ አገልግሎት መስማት ለተሳናቸው ዜጎች በተጀመረበት ወቅትም ከምክክር ባለሙያዎቹ
አንዷ ነበረች፡፡
በትምህርት ሚኒስቴር
ስር ትምህርት በቴሌቪዥን (ፕላዝማ) የምልክት ቋንቋ ትርጉሙን ጥራት ግምገማና የማፅደቁን ስራ በሙሉ ሃላፊነት ሰርታለች፡፡
ከአዲስ አበባ
ዩኒቨርሲቲ የሊንጉስቲክስና ፊሎሎጂ ትምህርት ክፍል ጋር የምልክት ቋንቋ መዝገበ- ቃላት (ያልታተመ) ሰርታለች፣
የተለያዩ የግንዛቤ
ማስጨበጫ ዶክመንተሪዎች ላይም ተሳትፋለች፣
https://www.facebook.com/Etugela/videos/226199130756321
የኢትዮጵያ የምልክት
ቋንቋ አስተርጓሚዎች ብሔራዊ ማህበርን ከጓደኞቿ ጋር ሁና መስርታ ነበር፡፡ ቢሆንም ለትምህርት ከሃገር በወጣችበት መቀጠል ሳይችል ቀርቷል፣
ለተለያዩ መስማት
የተሳናቸውና ለሚሰሙ ሰዎች በግሏ ምልክት ቋንቋን አስተምራለች፣
የኮሮና ቫይረስ
በሃገራችን በተከሰተበት ወቅት መረጃዎችን መስማት ለተሳናቸው ዜጎች ተደራሽ ለማድረግ በግል ፌስቡክ ገጿ ላይና በፋና
ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ፋና ጤና ዝግጅት ላይ በከፍተኛ የሃላፊነት ስሜት የሰራች ሲሆን በርካታ ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው
አካላት የእርሷን ፈለግ እንዲከተሉ ምክንያት ሁናለች።
በኖርዌይ ቆይታዋ
ለትውልደ, ኢትዮጵያውያን ህፃናት አማርኛ ቋንቋን በማስተማር የድርሻዋን አበርክታለች።
ወደ ሃገሯ ተመልሳ
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት መዝናኛ ፕሮግራሞች ዘርፍ በጋዜጠኝነት እየሰራች ትገኛለች፣ በምትሰራቸው የቴሌቪዥን ዝግጅቶች
በተቻላት መጠን መስማት የተሳናቸው ዜጎችን ተደራሽ ለማድረግ ትጥራለች።
መዓዛ ከረጅም አመት
ጓደኛዋ ጋር ትዳር መስርታ እየኖረች ነው።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ