110. ለሙያዋ ታላቅ ፍቅር ያላት መታሰቢያ
መታሰቢያ ካሳዬ አርጋው /Metasebia Kassaye argaw
የዚህ ታሪክ
አሰባሳቢ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣
በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም
በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ
ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን
ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት
አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014
የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም
በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ
እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡
በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው
የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን
አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ከሚድያ ዘርፍ
ታሪኳ የሚቀርብላት ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ አርጋው
ናት- ለሙያዋ ታላቅ ፍቅር ያላት መታሰቢያ ካሳዬ ፡፡
ትውልድ ልጅነትና ትምህርት
መታሰቢያ ካሳዬ አርጋው የተወለደችው አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ነው ። ለቤተሰቦቿ 8ኛ ልጅ ስትሆን 6 ወንድሞችና 1 እህት አላት። በልጅነቷ እጅግ ቀልጣፋ አዳዲስ ነገሮችን
የማወቅና የመመርመር ፍላጎት የነበራት እንደነበረች
በቅርብ የሚያውቋት ይናገራሉ። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በሰዋስው ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ ትምህርት ቤት ፤ የ2ኛ ደረጃ
ትምህርቷን ደግሞ በኮልፌ ኮምፕርሄንሲቭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች።
የዩኒቨርሲቲ ቆይታ እና ስራ አለም
የከፍተኛ ደረጃ
ትምህርቷን በዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ተከታትላ በ( Journalism and communication ) በadvanced
diploma ተመርቃለች ። በመቀጠል ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ
በቋንቋና ስነፅሁፍ የመጀመሪያ ድግሪዋን አግኝታለች። ከአለም
አቀፉ የፓን አፍሪካ ፊልም አካዳሚ ደግሞ በዶክመንተሪ እና የፊልም ዝግጅት በዲፕሎማ ተመርቃለች ። ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ የስራ ጅማሮዋ በኢትዮጵያ ሬድዮ
ሲሆን ከ 1997 እስከ 1999 ድረስ ስትሰራ ቆይታለች።
በመቀጠልም ትኩረቱን በንግድና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ አድርጎ
በሚታተመውና‹‹ ነጋድራስ.›› በተሰኘ ሣምንታዊ ጋዜጣ ላይ እስከ
2000 ዓ.ም ድረስ ስትሰራ ቆይታ ረዥሙን የስራ ጊዜዋን
ያሣለፈችበትንና ስሟ የገነነበትን አዲስ አድማስ ጋዜጣ በ2000 ዓ.ም ማጠናቀቂያ ላይ ተቀላቅላ እስከአሁንም ድረስ
በመስራት ላይ ትገኛለች።
ወደ ሙያው ዘለቅ ብሎ መግባት
ጋዜጠኛ መታሠቢያ
ለአመታት የዳበረውን እውቀትና ልምድ በስፋት ለመጠቀም ያስችለኛል ብላ በመረጠችው መንገድ ወደ ሬዲዮ ዘርፍ በመመለስ አሐዱ
ሬዲዮ ስርጭቱን ሲጀምር አብረው ከጀመሩት ፕሮግራሞች መካከል አንዱና
እጅግ ተወዳጅ የሆነውን ‹‹አውደ ህይወት››
የተሰኘ ፕሮግራም ዋና አዘጋጅ በመሆን ከ2009 ዓ. ም ጀምሮ
እስከአሁን እየሰራች ትገኛለች።
ሙያው የሚፈልገውን መስዋእትነት መክፈል
ጋዜጠኛ መታሰቢያ
ካሳዬ በባህርይዋ በቀላሉ ከሠው የምትግባባ ሙያዋን አጥብቃ የምትወድ ሲሆን ለጋዜጠኝነት ሙያ እጅግ የበዛ ፍቅርና አክብሮት
እንዳላትና ሙያው የሚፈልገውን መስዋእትነት ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ እንደሆነች በተደጋጋሚ ትናገራለች። መታሠቢያ በምታነሣቸው
ማህበራዊ ጉዳዮቻችንን የሚመለከቱ ስራዎቿ በብዙዎች ዘንድ
የምትታወቅ ሲሆን በሰዎች ህይወትና ኑሮ ላይ ተጨባጭ
ለውጦችን ያመጡና ሊዘነጉ የማይችሉ ስራዎችን ሰርታለች።
ከነዚህ ስራዎቿ መካከል የቀድሞ የኢፌድሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳን ህይወት የሚዳስስና
ኑሮአቸውን የሚያስቃኝ ሰፋ ያለ ፕሮግራም ሰርታ
ፕሮግራሙ ውሣኔ ሰጪዎቹ የመንግስት አካል ጆሮ በመድረሱ
የፕሬዚዳንቱን ህይወት የሚለውጥ ነገር መደረጉና ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገቡ አንዱ
ስኬቷ ነው። ተደራራቢ መከራና ችግር የደረሰባትን አንዲት የ18 አመት ወጣት የጨለመ ህይወት የሚያበራና የመንትያ
ልጆቿን ህይወት የሚታደግ ስራ በአሐዱ ሬዲዮ መቅረብ መቻሉም የሚዘነጋ አይደለም።
መታሰቢያ ካሳዬ
በስራ ካጋጠሟት አስቸጋሪ ገጠመኞቾ አንዱ ከጥንቆላና ባዕድ አምልኮ ጋር በተያያዘ በወቅቱ እጅግ አነጋጋሪ የነበረውንና ከፍተኛ
የመንግስት ባለስልጣናት ተሣታፊ የነበሩበትን እውነታ ለመጀመሪያ ጊዜ ይፋ በማድረጓ ሣቢያ ለከፍተኛ ችግር የተጋለጠችበትን ሁኔታ
አትዘነጋውም።
በጋምቤላ ክልል አበቦ ወረዳ ከ7 የሙያ አጋሮቿ ጋር ለስራ በሄዱበት አጋጣሚ በወረዳው አስተዳዳሪ እና የጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ታግተው
ድብደባና እንግልት ደርሶባቸው በነበረበት ወቅት ለሰዓታት በእስር ላይ ቆይተው እንደነበረም ጋዜጠኛ መታሰቢያ የማትዘነጋው
አጋጣሚዋ ነው። ታዲያ በዛን ወቅት ከእስር ሲለቀቁ ከሌሎቹ ተለይቶ ለብቻ ተወስዶ ወደ ሌላ እስር ቤት እንዲገባ የተደረገውን አንድ ጋዜጠኛን ከእስር
ለማስፈታት ከፍተኛ ትግል ማድረጓ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ጥረቷ
ተሳክቶም ጋዜጠኛውን ከእስር አስፈትታ ወደ ጋምቤላ ተመልሳለች። ይህን ጉዳይ በወቅቱ የቪኦኤና የዶቼቬሌን ጣቢያዎች ጨምሮ
በተለያዩ የአገር ውስጥና የውጪ ሚዳያዎች ሰፋ ያለ የዜና ሽፋን ሰጥተውት ነበር ። ከዚህ በተጨማሪ እንደ የኢትዮጵያ ሰብአዊ
መብት ኮሚሽን እና ሲፒጄ ያሉ ተቋማት በወቅቱ ስለጉዳዩ ተከታታይ ሪፖርቶች አውጥተዋል። በእንደዚህ አይነት የስራ ላይ ፈታኝ
ገጠመኞች ያልተበገረችው ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ሙያዊ አበርክቶዋን አጠናክራ በመቀጠል በርካታ ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ ዝርዝር
ዘገባዎችን ጭምር በአዲስ አድማስ ጋዜጣ እንዲሁም በአሀዱ ሬድዮ
በራስዋ የአየር ሰዓት ላይ ሰርታለች። መታሰቢያ በተለይም የማህበረሰብ ቀውስ ሊያስከትሉ የሚችሉ ችግሮችን በመንቀስ ልዩ ትኩረት
እንዲያገኙ የሰራችባቸው ጉዳዮች ጥቂት የሚባሉ አይደሉም።
እንደአብነት በአዲስ
አበባ ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች የሚፈጸሙና ለብዙ ወጣቶች ህይወት መበላሸት ምኮንያት የሆኑ እንደ መቃሚያ ቤት ማሣጅ ቤትና
መሠል ስፍራዎች ላይ ተከታታይ ሪፖርት በመስራት መንግስት በጉዳዩ ላይ ትኩረት በማድረግ እርሞጃ እንዲወስድ ማድረጓ የሚጠቀስ
ነው። ጋዜጠኛ መታሰቢያ ካሳዬ ባለትዳር እና የ2 ልጆች እናት ስትሆን የቤተሰብ ሀላፊነትን ከሙያ ሀላፊነት ጋር በማጣጣም
መምራት የቻለች ጠንካራ ጋዜጠኛ ናት ።
ይህቺ ለአዳዲስ
የፈጠራ ሃሳቦች ሁሌም የማትደክመው ብርቱ ጋዜጠኛ
በግሏ ባቋቋመችው ዮኤድ የማስታወቂያ ድርጅት የተለዩ
የሬዲዮና የቴሌቪዥን ማስታወቂያዎችን ዶክመንተሪ ፊልሞችን በመስራት ላይ ትገኛለች። በቀጣይም
በርካታ ለውጥን ሊያመጡ የሚችሉ ስራዎች ላይ እንደምትሰራ እና ሙያዊ ሀላፊነቷን ለመወጣት እንደምትተጋ ትናገራለች።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ