109. ምህረትና የለውጥ ቲያትር

    ምህረት ማስረሻ ዘውዴ / Mihret Massresha Zewde

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ  ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ    መስፈርቱን ያሟላሉ  የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን  ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡  አሁን ከቴአትር ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ባለሙያ   ምህረት ማስረሻ ዘውዴ ነው፡፡  ምህረት ቴአትርን ለለውጥ የተሰኘውን ጽንሰ-ሀሳብ በማስፋፋት እየሰራ ያለ ሰው ነው፡፡

   ሙያ

  የለውጥ ቲያትር

• ሕዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን

 ትውልድ

ባሌ፣ ወርቃ ከተማ፣ መስከረም 27 ቀን 1965 ዓ.ም 

እናት፡- መምህርት አስቴር ሌጀቦ

አባት፡- መምህር ማስረሻ ዘውዴ፤

ቤተሰብ

ባለቤት፡- አይናለም ተስፋዬ ለገሰ

ልጆች፡- ኤልያብ ምህረት፣ ባስልኤል ምህረት፣ ዝማሬህይወት ምህረት፣ ዳን ምህረት

ትምህርት

የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ባሌ ጎባ በሚገኙት በአራዳ ሚጫ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤ በነጋዴ ሰፈር መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤትና በባቱ ተራራ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታተለ፡፡

ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በቲያትር ጥበባት የመጀመሪያ ዲግሪ፤ ከዚያው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የጋዜጠኝነትና ኮሚኒኬሽን ትምህርት ቤት በሕዝብ ግንኙነትና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን የማስተር ኦፍ አርትስ ዲግሪ አግኝቷል፡፡

ኬኒያ ናይሮቢ ከሚገኘው የአፍሪካ ቤተሰብ ጥናት ማዕከል በማሕበረሰብ አቀፍ ፕሮግራሞች፤ ሮተርዳም ዘ ኔዘርላድስ ከሚገኘው ፎርማት ከተሰኘ የቲያትር ኦፍ ዘ ኦፕረስድ ማዕከል በአሳታፊ ቲያትር አቀራረብ ዘዴዎች፤ ስዊድን ከሚገኘው ዩኒቨርስቲ ኦፍ ኢስት ዌስት በኢንተር ካልቸራል አደልት ለርኒንግ፤ በመኩሪያ ቲያትር ስቱዲዮና መዝናኛ/ ክሬሽን ኦፍ ኦልተርኔቲቭ ሜትድስ ፎር አድቮኬሲ በአሻንጉሊት ቲያትር፤ በመረጃ ቲያትር አጻጻፍና አዘገጃጀት፣ በሳይኮ ድራማ . . . የተለያዩ አቅም ማጎልበቻ ሥልጠናዎችንና አውደ-ጥናቶችን ተከታትሏል፡፡ 

ምህረትና የለውጥ ቲያትር

ምህረት ወደ ቲያትር ሙያ የተሳበው ገና የአስራ አንድ ዓመት ታዳጊ ሳለ ነበር፤ ከአዲስ አበባ ወደ ባሌ ጎባ የሄደው ቲያትር ከመኖሪያ ደጁ በሚገኘው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ የሚቀርብበት ዕለት፡፡ ቲያትረኞቹ “ኦልድ ቢልዲንግ” በመባል በሚታወቀው  የእንጨት በእንጨት ቢጫ ሕንጻ መካከል ያለውን ከመሬት ከፍ ያለ በረንዳ እንደ ቲያትር መድረክ ተጠቅመውበታል፡፡  ከበረንዳው ፊት ለፊት ግራና ቀኝ በተሰለፉት የተከረከሙ የጥድ ዛፎች መካከል ባለው አረንጓዴ አፀድ ላይ ወንበሮች ተደርድረው ተመልካቹ ግጥም ብሏል፡፡ የበረንዳው ቅርጽ፣ ሥፋትና ከፍታ ቦታውን ወደ ቲያትር መድረክነት በቀላሉ ለመቀየር አመቺ ሆኖላቸዋል፡፡ የቱንም ያህል ጠራራ ቢሆን ድምቀት እንጂ ቃጠሎን የማትረጨው የጎባ ፀኃይ ለተበጀው ጊዚያዊ መድረክ ውበትን ፈንጥቃበታለች፡፡

ምህረት ከሁለት ጓደኞቹ ጋር በትምህርት ቤቱ አጥር ሾልኮ ቲያትር ለመመልከት በተሰበሰበው ተመልካች እግሮች ሥር ተሽሎክሉኮ፤ ሁሉንም አልፎ በመድረኩና በ“ክብር እንግዶቹ” መካከል በነበረው ገላጣ ሥፍራ፤ መሬት ላይ ተቀመጠ፡፡  ቲያትሩ ተጀመረ፤ በአንድ ጥሩ መኖሪያ ቤት ሳሎን ውስጥ ሰዎች የሚነጋገሩበት ትዕይንት ነበር፡፡ በመካከል አንድ ዘናጭ ተጫዋች በመያዣ አንድ ላይ የተደረጉ ቁልፎችን እያሽከረከረና እያቀጫጨለ ወደ መድረክ ገባ፡፡ በቄንጠኛ አነጋገሩ ላንድ ሮቨር መኪናውን ግቢ ውስጥ አቆሟት እንደመጣ በሳሎኑ ለነበሩት ጥቂት ሰዎች ተናገረ፡፡ ሰውዬው በተናገረው ንግግር ውስጥ የተላለፈው መረጃ ለምህረትና ለጓደኞቹ ያስተላለፈው መልዕክት ከሌላው ተመልካች የተለየ ነበር፡፡ መኪና ማየትም ሆነ መነካካት ብርቃችው የሆነው ምህረትና ጓደኞቹ ወዲያው ተያይተው፣ ተጠቃቅሰው፤ ተግባብተው፤ እየታየ የነበረውን ቲያትር ትተው ሰውዬው “አቁሜ መጣሁ” ያላትን መኪና ፍለጋ ወደ ፊት ለፊት በመጡበት አኳኋን ተመልሰው ከታዳሚው መካከል ወጡ፡፡ ከህንጻው ጀርባ ሄዱ፤ መኪናዋ አልነበረችም፡፡ ሕንጻውን ብቻ ሳይሆን በትምህርት ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያሉትን ሕንጻዎች በሙሉ ዞሯቸው፤ መኪና ሊቆምበት ይችላል ብለው የገመቱበትን ቦታዎች ሁሉ አሰሱ፤ መኪናዋ የለችም፡፡

ቲያትሩ እየታየ፤ ሰው ሁሉ ፀጥ ብሎ ይከታተላል፡፡ አለፍ አለፍ እያለ ከሳቅ ጋር የተቀላቀለ የመገረም፣ የማድነቅ፣ የንቀት ወዘተ. ሁካታዎች ይሰማሉ፡፡ በመድረኩ ላይ እየተነጋገሩ የነበሩት እነዚያ ሰዎች ምህረትንና ጓደኞቹን ከተቀመጡበት አስነስቶ መኪና ፍለጋ የሰደዳቸው፤ የሌለን ነገር እንዳለ አድርገው እንዲቆጥሩ ያደረጋቸውን፤ የዚያን ሁሉ ተመልካች ቀልብ የገዛ አንድ በገሀድ የሚታይ፤ እውነት ያልሆነ፤ ግን እውነት ተደርጎ ሊወሰድ የሚችል ክስተት እንደፈጠሩ በምህረት የልጅነት አዕምሮው ውስጥ በጉልህ ተቀረፀበት፡፡ ይህ ምህታት እንዴት እንደሚፈጠር ለማወቅ ጉጉት አደረበት፡፡

በ1985 ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቲያትር ጥበባት ክፍል ገባ፡፡ ተማሪ እያለ የትወና ክህሎት (ፐርፎርማንስ ስኪልስ) መምህሩ  የነበረችው አየርላንዳዊቷ ፍራንሲስካ ሊንግተን በሳንፎርድ ኢንተርናሽናል ት/ቤት ውስጥ ይንቀሳቀስ በነበረው ኒው ቲያትር ክለብ ውስጥ እንዲሳተፍ ታደርገው ነበር፡፡ በዚያ ክበብ አማካኝነት “ዘ ትሪ ዛት ሆልድስ አፕ ዘ ስካይ” የሚለውን የፖል ኪንግን ተውኔት “ዓምደ ሰማይ” ብሎ ወደ አማርኛ መልሶ ከሳንፎርድ ት/ቤት ተማሪዎች ጋር ለመመድረክ ሞክሯል፡፡

ምህረት የቲያትር ጥበባት ትምህርቱን ጨርሶ ለመመረቅ ጥቂት ወራት ሲቀሩት በአንድ የሕጻናት ማሳደጊያ ውስጥ የሚኖሩ በቁጥር አንድ መቶ የሚደርሱ ህጻናት ከሰው ጋር መግባባት እንዳቃታቸው፤ እነዚህን ልጆች ሰው ቀርቦ በሚያናግራቸው ጊዜ የሚቀርባቸውን ሰው ፊት ለፊት መመልከት አለመቻላቸውን፤ ለሚያናግራቸው ሰው መልስ በመስጠት ፈንታ የልብሳቸውን ኮሌታ ማኘካቸውን፤ አንዳንዶቹም በቁማቸው እንቅልፍ እየወሰዳቸው መቸገራቸውን፤ የእጓለ ማውታው ኃላፊዎች ለዚህ ችግር መፍትሄ እንዳጡ በመምህሩ አማካኝነት ተነገረው፡፡ መፍትሄ ይኖረው እንደሆን ተጠየቀ፡፡

በተመረቀ ማግስት ለውጥ ያስፈልጋቸዋል የተባሉት ህጻናት ወደሚገኙበት መንደር በከፍተኛ ጉጉት ተጓዘ፡፡   ከእነዚህ ልጆች ጋር ከስድስት ወራት ላልበለጠ ጊዜ በነበረው ቆይታ በቡድን በቡድን ተከፋፍለው በየቀኑ ቲያትር ለመስራት ያገኛቸው ነበር፡፡ እራሳቸውን ለመግለጽ እድል የሚሰጧቸውን አቀራረቦች፤ የየራሳቸውን የፈጠራ ጽሑፍ (ክርኤቲቭ ራይቲንግ) እንዴት መጻፍ እንደሚችሉ፤ እራሳቸውን እንዴት ማቅረብ እንደሚችሉ በመልመጃዎች የታገዘ ሥልጠና ሰጣቸው፡፡ ቲያትር እንዴት እንደሚጻፍ፣ እንዴት እንደሚተወንና እንዴት እንደሚዘጋጅ በትንሽ በትንሹ መጥኖ አስረዳቸው፡፡ በእጁ ከነበሩ ተውኔቶች ውስጥ ለእነሱ በሚመጥን መንገድ ቀነጫጭቦ አብረው አጠኑ፤ አብረው ተጫወቱ፡፡ 

በመጨረሻም ልጆቹ የአሳታፊ እንቅስቃሴዎቻቸውን ውጤቶች ለአካባቢው ማህበረሰብ በአደባባይ በግልጽ አቀረቡ፡፡ ከተመልካች ጋር ተወያዩ፣ ተነጋገሩ፡፡ ከዚያም አልፈው በመንደራቸው ውስጥ የሚደርሱባቸውን ችግሮች በሰልፍ ሄደው ለኃላፊዎቻቸው አሳወቁ፡፡ ልጆቹ ከዓይን አፋርነት ወደ “ዓይን አውጣነት” መለወጣቸው በተግባር ታየ፡፡ የነበረባቸው የመግባባት ችግርም ተቀረፈ፤ ምህረትም ከእነሱ ጋር የነበረው ቆይታ በዚያው ተጠናቀቀ፡፡ ቲያትር ምትሀት መፍጠር ብቻ ሳይሆን የሰውን አመለካከትና ባህርይ መለወጥ የሚችል ተግባራዊ መሳሪያ እንደሆነ በተግባር ያረጋገጠበት አጋጣሚ ሆነለት፡፡ አባተ መኩሪያ ሙያዊ አስተዋጽዎውን ለወትሮው ለመዝናኛነት ከሚውለው ቲያትር ባሻገር የሰውን መረዳት፣ አመለካከትና አቋም ሊለውጥ በሚችል የቲያትር ሥልት (የለውጥ ቲያትር) መቃኘት ጀመረ፡፡

ምህረት የቲያትር ታሪክን ሲማር ለኮርስ ማሟያ ጥናት የመረጠው ቲያትር የብሉይ (ክላሲካል) ግሪኩን ትራጀዲ የሶፎክለስን “ንጉስ ኤዲፐስ”ን (ኤዲፐስ ሬክስ) ነበር፡፡ ይህ ተውኔት በዶ/ር ኃይሉ አርአያ በጥሩ ሁኔታ መተርጎሙ ብቻ ሳይሆን በእውቁ መራሄ ተውኔት በአባተ መኩሪያ ዓለም አቀፍ ደረጃውን በጠበቀ ልዩ አዘገጃጀት ተሰናድቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ራስ መኮንን አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኘው አፀድ ውስጥ የተሰራበትም ዓመት ነበር - 1985 ዓ.ም፡፡ ምህረት በቲያትሩ ላይ የአንድ መስፍን አጃቢ ሆኖ ለመሳተፍም ዕድሉን በማግኘቱ ቲያትሩን በቅርቡ ለመመልከት ከመቻሉም በላይ አዘጋጁን አባተ መኩሪያን ቀርቦ ለማወቅና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ሊረዳው ቻለ፡፡ ይህ ትውውቅ ቆይቶ አባተ መኩሪያ ከስዊድናዊቷ የቲያትር አስተባባሪ ከካሪን አስፕሎንድ ጋር በመሆን ባቋቋሙት ካማ/ Creating Alternative Methods for Advocacy (CAMA) ይባል ወደነበረ ተቋም እንዲሳብ ምክንያት ሆነው፡፡

ካማ በ1986 ዓ.ም መኩሪያ ቲያትር ስቱዲዮና መዝናኛ ተብሎ ተቋቋመ፡፡ (M.T.S.E 2005) መኩሪያ ቲያትር በአገሪቷ ውስጥ በተለያየ ሥፍራና አቅም ይንቀሳቀሱ የነበሩ የቲያትር ባለሙያችን ሲያቅፍ ምህረትም የቲያትር ሥልጠና ይሰጥበት ከነበረበት ከሐረር ከተማ ሆኖ በ1988 ዓ.ም መኩሪያን ተቀላቀለ፡፡ በዚህ ተቋም አማካኝነት በዩኒቨርስቲ ካገኘው የቲያትር ሥልጠና ላይ በበርካታ ረዣዥምና አጫጭር ስልጠናዎች፣ በሥራ ላይ ተግባራዊ ልምምዶችና በልምድ ልውውጦች መሳተፍ ቻለ፡፡ በምዕራብ ጎጃም ባህል ቱሪዝምና ማስታወቂያ መምሪያ የቲያትር ጥበባት ኤክስፐርት ሆኖ  ይሰራ በነበረበት በ1990 ዓ.ም በሴቶች ላይ በሚደርስ ትንኮሳ ላይ ተመስርቶ አባተ መኩሪያ የጻፈውን “ድፍረት” የተሰኘውን አሳታፊ የለውጥ ቲያትር በባህር ዳር አዘጋጀ፡፡ ቲያትሩ በባህር ዳር ከተማና በአካባቢው በሚገኙ ከተሞች በተለያዩ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ ተመልካቾች ሃምሳ በሚደርሱ መድረኮች ላይ ታየ፡፡

“ድፍረት” በአንድ ማረሚያ ቤት ውስጥ ለሕግ ታራሚዎች ሲቀርብ የተከሰተው አንድ አስገራሚ ነገር ይህ የቲያትር አቀራረብ በሰዎች ዘንድ በጎ ተጽዕኖ የሚያሳድር፤ ሰዎችም ራሳቸው ተለውጠው ሌላውን ለለውጥ እንዲያዘጋጁ የሚያደርግ፤ ለተግባራዊ እርምጃ አንዲነሳሱ የሚያዘጋጅ ለመሆኑ ማረጋገጫ ነበር፡፡ በቲያትሩ እንደ ተመልካች ከተሳተፉት የህግ ታራሚዎች መካከል አንዱ የፖሊስ መኮንን የነበረ ሰው ነበር፡፡ ጥበቃ እንዲያደርግላት በተሰጠችው ሴት ልጅ ላይ ፈጽመሀል በተባለው፤ እሱ ግን መፈጸሙን ባላመነው፤ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል በምስክር ተፈርዶበት ወህኒ ወርዷል፡፡ ይህ ሰው ቲያትሩ በቀረበበት ወቅት በተደረጉ ውይይቶች ወንጀሉን መፈጸሙን አምኖ፣ ወንጀሉን በመፈጸሙ ብቻ ሳይሆን መፈጸሙን በመካዱ ተጸጽቶ፤ ሌሎች ከእሱ እንዲማሩ በገሀድ መናገሩ ለምህረት የዚህ ቲያትር ሥልት ስኬት ሌላ ማሳያ ሆነለት፡፡

በ1986 ዓ.ም አባተ መኩሪያ በታንዛኒያ ኬኒያና ኡጋንዳ ከሚገኙ የሙያ አጋሮቹና ተመሳሳይ መረዳት ካላቸው ሰዎች ጋር በመሆን መስርተውት በነበረው የምስራቅ አፍሪካ የቲያትር ተቋምን /Eastern Africa  Theatre Institute - EATI/  ሥር ሁለት ፕሮጀክቶች ተወለዱ፡፡  ቲያትርን በወቅቱ ፈጣን እድገትና መስፋፋት እያሳየና በማሕበረሰብ ላይ ተጽእኖ እያንሰራፋ ከነበረው የመረጃ መረብ ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተሳሰር፤ የሁለቱን ዘርፎች ተመጋጋቢነት ለማዳበርና አንዱን ለሌላው ጠቃሚ ለማድረግ የሚያግዘው www.dramatool.org /ድራማ ቱል/ አንዱ ሲሆን ሌላው በኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ታንዛንያ፣ ዩጋንዳና ስዊድን የሚንቀሳቀሱ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች ትብብርን ለማጎልበት እንዲያግዝ ታስቦ የነበረው የስዊድንና የምስራቅ አፍሪካ የክዋኔ ጥበባት ትብብር - ፓክሲያ Performing Arts Cooperation Between Sweden & East Africa – PACSEA ነበር፡፡ ምህረት በ1996 ዓ.ም የፓክሲያ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቻፕተር ተጠሪ ሆነ፡፡ የዚህ ትብብር የኢትዮጵያ ተጠሪ  ሆኖ በሰራባቸው ጊዜያት በአገር ውስጥ፣ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራትና ከስዊድን ቲያትር ለማሕበረሰብ ለውጥ ሊያደርግ የሚችላቸውን እገዛዎች በተመለከተ ሰፋፊ ልምዶችን ቀሰመ፡፡

ምህረት በጥቅምት ወር 1995 ዓ.ም ከምስራቅ አፍሪካ የቲያትር ባለሙያዎች ጋር ስቶክሆልምን ጨምሮ አንድ ደርዘን በሚደርሱ የስዊድን ከተሞችና መንደሮች ውስጥ ቲያትር ለማህበረሰብ ሲባል  ጥቅም ላይ የሚውልባቸውን የተለያዩ አግባቦች ከሦስት ሳምንታት በላይ ተዘዋውሮ መመልከት ቻለ፡፡ በጉብኝታችን በተካተቱት ከተሞች ውስጥ በየትምህርት ቤቶቹ ጥሩ ጥሩ የቲያትር ትምህርት መርሀ-ግብሮች፣ ዝግጅቶችና አቅርቦቶች መኖራቸውን ተመለከተ፡፡ ከቅድመ መደበኛ እስከ ኮሌጆች ድረስ ባሉ ትምህርት ቤቶች የተሳታፊ/ ተመልካቹን ዕድሜ፣ ብስለት፣ ማህበራዊ ሁኔታ ያገናዘቡ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች ላይ ተመርኩዘው የሚዘጋጁ ቲያትሮች ለማህበረሰብ ልማት የነበራቸውን ቁልፍ ጠቀሜታዎች ተረዳ፤ ቲያትሮቹም የለውጥ ቲያትሮች መሆናቸውን አየ፡፡

ምህረት ያን ጊዜ የለውጥ ቲያትር በጥናት ላይ መሰረት ተደርጎ በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዐት ውስጥ መካተት አለበት ብሎ ሞገተ፡፡ የቲያትር ሙያ በተገቢው መንገድ ጥቅም ላይ እየዋለ እንዳልሆነ ተገለጠለት፡፡ ዘርፉ አዲስ ትግበራ እንደሚያስፈልገውም ተረዳ፡፡ የለውጥ ቲያትር ሥልት በአገራችን ኢትዮጵያ ውስጥ ባለቤት እንዲኖረውና በመንግስት ደረጃ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲተገበር ከፍተኛ ፍላጎት አደረበት፡፡

በህዳር ወር 1997 ዓ.ም ቲያትር በተገቢው ደረጃ ጥቅም ላይ አለመዋሉን የሚገልጽ ጥናት አዘጋጅቶ ሞምባሳ ኬኒያ በተካሄደው የምስራቅ አፍሪካ ቲያትር ተቋም 3ኛው ዓለም አቀፍ የቲያትር ፌስቲቫል ላይ አቀረበ፡፡ የለውጥ ቲያትር ሥልት ለኢትዮጵያ ሊያበረክት የሚችለውን መጠነ- ሰፊ ጥቅም በመመልከት ሰኔ 2000 ዓ.ም በተካሄደው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቋንቋዎች ጥናት ተቋም 20ኛ ዓመታዊ ጉባዔ ላይ “ተግባራዊ ሥልጠናን መሰረት ያደረገ የኪነ-ጥበብ ኢንደስትሪ - የአዲሱ ሚሊኒየም ራዕይ” በሚል ጽሑፍ አቀረበ፡፡ በ2004 ዓ.ም በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የባህል ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባል የሆነን አንድ ሰው አግኝቶ ከተለመደው የመዝናኛ ቲያትር እጅጉን የላቀ ልማታዊ ፋይዳ ስላለው ስለዚህ የሙያና የምርምር ዘርፍ አጫወተው፡፡ ለሌሎች የቋሚ ኮሚቴው አባላት ኃሳቡን ሲያጋራቸው ያግዘው እንደሁ ብሎ በማሰብ ባለ አንድ ገጽ ማስታወሻ ላከላቸው - ይህ ሁሉ ውጤት አላስገኘም፡፡

ምህረት የለውጥ ቲያትር ስልትን ተከትሎ በ1998 ዓ.ም “የአክስትዬ ውርስ”፤ በ1999 ዓ.ም “ጎዳና ላይ” በ2000 ዓ.ም “ጫና” እና “ያልተያዘው ሽፍታ” በ2002 ዓ.ም “ለሌላ ይሰጣል”፤ በ2004 ዓ.ም “ሽልማት” የተሰኙ የለውጥ ቲያትሮችን ጽፎ፤ ከሁለቱ በስተቀር አምስቱን አዘጋጅቶ በተለያዩ አካባቢዎች፤ በተለያዩ ዐውዶች ለተመልካች አቅርቧል፡፡

ምህረት ከ2007 - 2010 ዓ.ም በለውጥ ቲያትር ረገድ ያደርግ የነበረው እንቅስቃሴ አንድ ደረጃ ከፍ አለ፡፡ “የማሕበራዊ ተጠያቂነት ቲያትር” የተሰኘ የሥልቱን ሌላ አዲስ ዘዴ ማጥናትና ማጎልበት ቻለ፡፡ “ከመጠየቅ” የተሰኘውን የማሕበራዊ ተጠያቂነት ቲያትር  አጥንቶ፣ ጽፎና አዘጋጅቶ በአዲስ አበባ ከተማ ከ75 በላይ መድረኮች ለተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች አቀረበ፡፡ “ከመጠየቅ” ከአማርኛ ወደ አፋን ኦሮሞ ተተርጉሟል፡፡ በትግሪኛ፣ በከምባትኛና በሶማሊኛ በሬዲዮ ቀርቧል፡፡ የዚህን የለውጥ ቲያትር ዘይቤ ተከትለው በርካታ የወጣት ክበባት የራሳቸውን የማሕበራዊ ተጠያቂነት ቲያትር ሰርተዋል፡፡ በ2012 ዓ.ም  “የለውጥ ቲያትሮች” የሚል መጽፍ ጽፎ የኤሌክትሮኒክስ ቅጂውን ለወጣት ባለሙያዎች፣ ለአሰልጣኞችና ለመገናኛ ብዙኃን አገልግሎት ላይ እንዲውል በነጻ አሰራጭቷል፡፡

ምህረት ከለውጥ ቲያትር ልምምዱ በተጨማሪ የቲያትር አሰልጣኝ፤ የዴሞክራሲያዊ ምርጫ ሂደቶች ዋና አሰልጣኝ፤ የኢትዮጵያ የኮሙኒኬሽንና ሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ማህበር መስራችና የቦርድ አባል፤ የሁነቶች አዘጋጅ፤ ተርጓሚና አዘጋጅም ጭምር ነው፡፡








አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች