108. ዳግማዊ ታሪኩ / dagmawi Tariku

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣  ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ    መስፈርቱን ያሟላሉ  የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን  ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡  አሁን ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ጋዜጠኛ ዳግማዊ ታሪኩ ነው፡፡ ዳግማዊ 97ነጥብ  አንድ ሲጀመር ከነበሩት አንዱ ነው፡፡

             ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት

ዳግማዊ ታሪኩ የተወለደው በአዲስ አበባ ከተማ በ1961 አ.ም ተወለደ፡፡ ትምህርት የጀመረው አዲስ አበባ በሚገኘው 5ኪሎ መካነ-ኢየሱስ ነው፡፡ በመቀጠልም በሻሸመኔ ካቶሊክ ተማሪ ቤት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሻሸመኔ 2ኛ ደረጃ ተማሪ ቤትና  በአድቬንቲስት ተማረ፡፡

                    ዩኒቨርሲቲ

፡ከዚያ በ1981 አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ ታሪክ ማጥናት ጀመረ፡፡ ኢህአዴግ በ1983 አዲስ አበባን በተቆጣጠረበት ጊዜም ዳግማዊ የዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን አቋረጠ፡፡ ቀጥታ ወደ ኬንያ በመቅናት ዴይ ስታር በሚባል ተማሪ ቤት ትምህርቱን ቀጠለ፡፡ በኬንያም የማህበረሰብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ነበር ያጠናው፡፡ ኬንያ ቢያንስ ለ 5 አመታት ያህል ቆይታ አድርጎ ነበር፡፡ በዚያን ጊዜ ነበር በህያው ተስፋ ሬድዮ ላይ መስራት የጀመረው፡፡ ከዚያም ዳግማዊ በ1990 ግድም ወደ ኢትዮጵያ መጣ፡፡ አድቬንቲስት ኮሌጅ በማህበረሰብ ልማት ለመመረቅ በቃ፡፡

                ጉዞ ወደ  97ነጥብ አንድ

  ከዚያም በ1991 በኢትዮጵያ ሬድዮ ላይ ለመስራት ፈልጎ ለፈተና ቀረበ፡፡ ነገር ግን መስፈርቱ መምህር የሆነና የሚድያ ልምድ ያለው የሚል ነበር፡፡ ታዲያ ዳግማዊ የህያው ተስፋ ሬድዮ ልምዱ ይጠቅመኛል ብሎ ቢያቀርብም ነገር ግን አልተያዘለትም፡፡ በጊዜው በጣቢያው የስራ ሃላፊ የነበረችው ሰሎሜ ደስታ ዳግማዊ ጥሩ የጽሁፍ ክህሎት ያለው መሆኑ  መስክራ ነበር፡፡ የመቀጠሩ ነገር ቢዘገይም ሰሎሜ የኤፍኤም አዲስ 97ነጥብ አንድ አንድ ተብሎ ሲጀመር   ሃላፊ ተደርጋ ስለነበር ዳግማዊን ወሰደችው፡፡‹‹ ያን ጊዜ አመልክተህ ፈተናውንም አልፈህ ነበር፡፡ ነገር ግን ልምድ የሚባለውን ነገር ያኔ ተነስቶ ነበር፡፡ አሁን ግን ያለህን ክህሎት አይተን እንድትገባ አድርገናል›› ብላ ሰሎሜ ደስታ ለዳግማዊ የመጀመሪያውን  የጋዜጠኝነት በር ከፈተችለት፡፡

‹‹….ያኔ አዳማ የሚኖር አንድ ዘመዴ ጋር ሄጄ ሬድዮ መግባቴን ስነግረው አንተ ውስጥህ የታመቀ የሚድያ ፍላጎት ስላለህ ስኬታማ ትሆናለህ›› መባሉን ዳግማዊ ዛሬያስታውሳል፡፡ ዳግማዊ መጀመሪያ አካባቢ ስራ እንደጀመረ ገንዘብ አይከፈለውም ነበር፡፡ ከ2 ወር በኋላ ግን በፍሪላንስ መስራት ጀመረ፡፡ ዳግማዊ ኤፍኤም አዲስ እንደተጀመረ መስራት የጀመራቸው ፕሮግራሞች ሳምንቱ በታሪክ ወስጥ ፤ የህትመት እፍታን ነበር፡፡ ዳግማዊ ታሪኩ የህትመት እፍታን ጥሩ አድርጎ ለመስራት ሞከረ፡፡ በተለይ እርሱ በመጀመረ ጊዜ እንደሪፖርተር ያሉ ጋዜጦች በመንግስት ሚድያ ህትመት ዳሰሳ ላይ ፈጽሞ አይቀርቡም ነበር፡፡ ነገር ግን በወቅቱ የስራ መሪ የነበረችው ሰሎሜ ደስታ ባደረገችው ታላቅ ጥረት የግል ጋዜጦች የህትመት እፍታ ላይ መቅረብ ጀመሩ፡፡ ያኔ ከሪፖርተርና ከሌሎች የህትመት ውጤቶች ጽሁፍ መውሰድ እና ምንጭ ጠቅሶ መናገር የህትመት ውጤቶቹን ከማስተዋወቅ የዘለለ ሚና  የለውም በሚል ሀሳብ የሚያራምዱ ወገኖች ነበሩ፡፡ በኋላ ላይ ግን የግል ጋዜጦች የህትመት እፍታ ላይ በዳግማዊ ታሪኩ እየተከሸኑ መቅረብ ጀመሩ፡፡  ዳግማዊ ከሳምንቱ በታሪክ ውስጥ እና ከህትመት እፍታ ባሻገር  በኤች አይቪ በሽታ ላይ ትኩረቱን ያደረገ የውይይት ፕሮግራም መምራት ጀመረ፡፡ ዳግማዊ ታሪኩ በዚህ ፕሮገራም ትልቅ ትምህርት መቅሰሙን ይናገራል፡፡ በተለይ በዚህ ፕሮግራሙ አማካይነት ጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ ይሰጥ የነበረውን አለም አቀፍ ይዘት ያለው ስልጠናን ወሰደ፡፡ስልጠናው በኤች አይቪ ጉዳይ ኮሚኒኬሽን እንዴት መሆን አለበት የሚል ስለነበር ብዙዎች እውቀት መቅሰም እንዲችሉ ያደረጋቸው ነበር፡፡ ዳግማዊ ለረጅም ጊዜ በፍሪላንስ ሲያገለግል ከቆየ በኋላ እንዴት ቋሚ እንደሆነ አይዘነጋውም፡፡ ያን ጊዜ አቶ በረከት ስምኦን የጣቢያው ከፍተኛ የስራ አመራር ቦርድ ሀላፊ ስለነበሩ ዳግማዊ ፍሪላንስ መሆኑን ሲሰሙ   ስራውን እየሰራ ስለሆነ ለምን ቋሚ አታደርጉትም የሚል ሀሳብ ያቀርባሉ፡፡ በወቅቱ ዳግማዊ አቶ በረከትን ሲያገኛቸው ‹‹ እኔ በዚህ መስሪያ ቤት ውስጥ ቋሚ ሰራተኛ አይደለሁም፡፡››   የሚል ሀሳብ ሰጥቶ ነበር፡፡ ከዚያም የዳግማዊ ታሪኩ ፋይል ይፈለግ ተባለ፡፡ ፋይሉ ጠፋ፡፡ ብቻ በዚህ አጋጣሚ ዳግማዊ በአዘጋጅ የስራ መደብ መስራት መጀመሩን ያስታውሳል፡፡ ከፍሪላንስ ቶሎ ወደ አዘጋጅ ያደገው ዳግማዊ በቅድሚያ ደሞዙ 300 ብር ነበር፡፡ አዘጋጅ ሲሆን ግን ደሞዙ በ3 እጥፍ አድጎ 900 ደረሰ፡፡ ያን ጊዜ  900 ብር ብዙ ነበር፡፡ እነ ዳግማዊ ደግሞ አንዳንድ ጊዜ ፊልድ በሚላኩበት ጊዜ ጥሩ አበል ይከፈላቸው ስለነበር ኑሮን በተሻለ መልኩ ለመደጎም ይሞክሩ ነበር፡፡ ዳግማዊም በዚህ መልኩ ነበር ስራውን የቀጠለው፡፡ በተጨማሪም  አየር ሰአት ወስደው ከሚሰሩ እንደ ሰይፉ ፋንታሁን  ካሉ ሰዎች ጋር በመስራት ተጨማሪ ገቢ ያገኝ እንደነበር ዳግማዊ ያስታውሳል፡፡








        ካናዳ

ዳግማዊ ለ6 አመት ነበርኤፍኤም አዲስ 97 ነጥብ አንድ ላይ የሰራው ከ1992-1998 ፡፡ ከዚያ በኋላ ቀጥታ መኖሪያውን ካናዳ ነበር ያደረገው፡፡  ላለፉት 15 አመታት ዳግማዊ በካናዳ ኑሮውን መስርቶ ይገኛል፡፡

በ1998 መጨረሻ ላይ ካናዳ የገባው ዳግማዊ ታሪኩ እዚያም እያለ ብዙም ከሚድያ የራቀ ስራ አልነበረም ያከናውን የነበረው፡፡  ካናዳ ከደረሰ በኋላ ዳግማዊ ያከናወነው ጠቃሚ ተግባር ለወንጌላውያን ክርስቲያኖች የሚሆን ጉዞ ሬድዮ የሚባል ሚድያ ለማቋቋም መቻሉ፡፡ በመቀጠልም ጉዞ መጽሄትን ለህትመት በማብቃት የጋዜጠኝነት ክህሎቱን ማውጣት መጀመሩን ይናገራል፡፡ ዳግማዊም በካናዳ የማህበረሰብ ሬድዮ ላይ የራሱን ተሳትፎ በማድረግ  ስራ መስራቱን ይናገራል፡፡

በመቀጠል ዳግማዊ content development  እና ሚድያ ስነ-ሂስ ላይ መማር ጀመረ፡፡    ዳግማዊ ካናዳ እንደደረሰ ካስተዋላቸው ነገሮች አንዱ አንድ የቲቪ ወይም የሬድዮ መሰናዶ ሲቀርብ ዝግጅቱን በጥሞና ተከታትለው ሂስ የሚሰጡ ባለሙያዎች አሉ፡፡  እነዚህ መገናኛ ብዙሀንን እየተከታተሉ ሂስ የሚሰጡ ባለሙያዎች ስመ-ጥር ብቻ ሳይሆኑ በእውቀት ላይ ተመስርተው የሚሰሩ በመሆናቸው በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ተአማኒነትን አትርፈው ነበር፡፡ ዳግማዊም በእነርሱ ጥረት ሁሌም ይደነቅ ስለነበር በሙያው ተሳበ፡፡ እርሱም የሚድያ ሂስ መስጠቱን የጀመረው ይህን ትምህርት ከቀሰመ በኋላ ነበር፡፡ ኢቲቪ ላይ ወይም ሌሎች ጣቢያዎች ላይ አንድ ስህተት ከተመከተ ዳግማዊ አጠር ያለች ጽሁፍ ጽፎ ስህተቱ እዚህ ጋር ነው፡፡ እንዲህ መባል የለበትም በማለት ሚዛናዊ ሂሱን ለማቅረብ ሙከራ አድርጓል፡፡ ጥንካሬም ሲኖራቸው ያንን እያመለከተ ብዙ ጽሁፎችን በፌስ ቡክ ገጹ ላይ  ሊጽፍ ችሏል፡፡

ዳግማዊ ጠቅላላ ሚድያ አለም በቆየባቸው 25 አመታት ሚድያ ምን ያህል ከባድ ጉልበት እንዳለው ተገንዝቧል፡፡ በተለይ የሰዎችን ጤና እና ብሎም ማህበራዊ ኑሮ በማስተካከሉ ረገድ ሚድያ ትልቅ አቅም እንዳለው ዳግማዊ ይገነዘባል፡፡  ለንባብ የተለየ ፍቅር ያለው ዳግማዊ ለደራሲያን ለብርሀኑ ዘሪሁን እና ለሲሳይ ንጉሱ የተለየ አክብሮት አለው፡፡











አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች