104. መኳንንት በርሄ  -Mekuanint Berhe

የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡ በtewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ አሁን ከሚድያ ዘርፍ ታሪኩ የሚቀርብለት ሰወ  የስፖርት ዞኑ መኳንንት በርሄ ነው፡፡










        ትውልድ- ልጅነት- እና ትምህርት

መኳንንት በርሄ  በ1977 መጋቢት 19 በጎንደር ከተማ ተወለደ። ዕድገቱም ኦቶፖርኮ  ቀበሌ 17 ውስጥ ነበር። ትምህርት የጀመረውም  ደብረ-ሰላም ማርያም በሚባል በጎንደር የታወቀ የካቶሊክ ሚሲዮን ት/ቤት ውስጥ ነው። ከስምንተኛ እስከ አስራሁለተኛ ክፍል ያለውን ትምህርቱን  በፋሲለደስ ት/ቤት ተማረ።

      ዩኒቨርስቲ

ከዚያ በ1995 ዓ.ም በአ.አ ዩኒቨርሲቲ ገብቶ mass communication እና ጋዜጠኝነት እንዲሁም ታሪክን ደርቦ ተማረ። በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በትምህርት  ሳለ ያን ያህል የተለየ የሚባል ችግር ባይገጥመውም በ1997 በሀገሪቱ ውስጥ በነበረው ሀገራዊ ምርጫ ሰበብ እንግልት ከገጠማቸው ተማሪዎች አንዱ ነበር። በዚህ ምክንያትም ራሱን ለጥቂት ጊዜያት ደብቆ ቆይቷል። በዩኒቨርስቲ  ውሰጥ ሲማር የተለየ ጭንቅላት የነበራቸው ጓደኞች ነበሩት።  ከእነርሱ ጋር በመሆን ሃሳብ የመለዋወጥ የተለየ ልምድም ነበረው። ኳስ እጅግ አብዝቶ ይወዳል። ቅፅል ስምም ነበረው፡፡ በወቅቱ የስፔን አማካይ በነበረው ተጫዋች (ፋብሪሃስ) በሚል። ይህንን ስያሜም ዳንኤል የሚባል የዩኒቨርሲቲ ጓደኛው ነበር ያወጣለት።

    የስራ ህይወት (የሬዲዮ  እና የቴሌቪዥን ጋዜጠኝነት)

በ1999 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ የያኔው የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሮካስቲንግ ኮርፖሬሽን በስፖርት ጋዜጠኝነት ተቀጠረ። በወቅቱ የኤፍ ኤም 97.1 ስርጭት የተጀመረበት በመሆኑ በሁሉም በስፖርት ዜና አንባቢነት፣ ተንታኝነት፣ እና የጨዋታ የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊነት ለ8 ዓመታት ያህል ሰራ። በኢቢሲ ያሳለፈው  ጊዜም ለጋዜጠኝነት ህይወቱ ትልቁን ልምድ ያገኘበት  መሆኑን ይናገራል።

የስፖርት ዞን መጀመር

ከ2008 ነሐሴ 10 አንስቶ ትኩረቱን በሀገራዊ ስፖርታዊ ጉዳዮች ላይ ብቻ የስፖርት ዞን ኘሮግራምን ከባልደረባው ሰዒድ ኪያር ጋር በመሆን በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ዘወትር ከሰኞ እስከ ዓርብ ማለዳ የራሱ ስፖርታዊ ኘሮግራምን በዋና አዘጋጅነት ጀመረ። በስፖርት ዞን ዘወትር ረቡዕ በሚቀርበው መሰናዶ ከ300 በላይ እንግዶችን በቀጥታ ስርጭት በማናገር ለኢትዮጵያ እግርኳስ ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ የመፍትሄ ሃሳብ የሚያመጡ ውይይቶችን አድርጓል። በስፖርት ዞን በቅዳሜ እና እሁድ ፕሮግራሞች እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በሚኖረው ጊዜ ወደ ተለያዩ ሀገራት አብሮ ጉዞን በማድረግ የጨዋታ የቀጥታ ስርጭት አስተላላፊ በመሆን ለረጅም ጊዜ ሰርቷል።

    የሱፐር ስፖርት ቆይታ

እ.ኤ.አ ከ2019 ዲሴምበር አንስቶ ሱፐር ስፖርት መቀመጫውን ደቡብ አፍሪካ በማድረግ የእንግሊዝ ኘሪምየር ሊግ፣ የስፔን ላሊጋ ፣ የጣሊያን ሴ ሪአ ጨዋታዎችን በአማርኛ ቋንቋ ለማስተላለፍ ከተመረጡ ጥቂት ጋዜጠኞች ውስጥ አንዱ ሲሆን በአንድ ወር ወደ 35 ያህል ጨዋታዎችን በቀጥታ ስርጭት አስተላልፏል። የቤትኪንግ የኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ በሚል ስያሜም የኢትዮጵያ ኘሪምየር ሊግ በቀጥታ የቴሌቪዥን ስርጭት በdstv መተላለፍ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በጨዋታ ተንታኝነት፣ የሜዳ የጨዋታ አቅራቢ በመሆንም እየሰራ ነው። እንዲሁም ከአትሌቲክስ ጋር በተገናኘ የሀገራችንን አትሌቶች የስኬት መንገድ በሚያሳየው Rising champions በተሰኘው የsuper sport documentary ላይ ኘሮዲውሰር በመሆን የራሱን ድርሻ አበርክቷል።

          በእውቀት ላይ ተመስርቶ መስራት 

መኳንንት በርካታ የቴሌቪዥን የበዓል መሰናዶዎችን በመስራትም ይታወቃል። ‹ባይተዋሩ ቦክሰኛ›› የሚል ርዕስን የሰጠውና በቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ቦክሰኛ ስለሺ እሸቴ የህይወት ታሪክን የሚዘግበው ዘጋቢ ፊልሞች ውስጥ በቀዳሚ ደረጃ የሚያስቀምጠው መሆኑን ይናገራል። ጋዜጠኛ ጎርፍነህ ይመር፣ በልሁ ተረፈ፣ እና ጋዜጠኛ ተፈሪ ለገሰን በጣም የሚያደንቃቸው ጋዜጠኞች ናቸው። በጣም አዛኝ ፤በሰዎች ችግር ሁሉ ቀድሞ ደራሽ መሆኑን የሚያውቁት ሁሉ ይመሰክራሉ። መኳንንት ለሀገሩ አንድ ነገር ትቶ ማለፍ የሚፈልግ ሰው ሲሆን የሚሰራቸውንም ስራዎች በእውቀት ላይ ተመስርቶ ይሰራል፡፡ በተጨማሪም ስራውን በጣም  ደስ ብሎት ስለሚሰራው ብዙም መጨናነቅ አያበዛም፡፡ በተለይ በስፖርቱ ዘርፍ ባለፉት 5 አመታት ከቀዳሚዎቹ ተርታ  የሚመደበው ስፖርት ዞን የሬድዮ ፕሮግራም በአድማጮች ዘንድ የሚከበርና የሚወደድ ተአማኒነትን የተላበሰ  መሆኑን ብዙዎች ይመሰክራሉ፡፡ ይህ መሰናዶ ታዲያ ለስኬት እንዲበቃ የመኳንንት   በርሄ  ጥረታ ምንጊዜም የሚጠቀስና  በርካታ ሰዎችም የሚመሰክሩት ጉዳይ ነው፡፡






አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች