101. ሰአዳ መሐመድ ኢብራሂም - seada mohammed
Ibrahim
ሴት ድራማ
ጸሀፊ
የዚህ ታሪክ
አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣ በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ
፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ
እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ
የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡ ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን
እናወጣለን፡፡ በ tewedajemedia@gmail.com ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ
ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ
የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር
ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል
ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም
ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው
ይዘከራል፡፡ በስነ-ጽሁፍና በሬድዮ ድራማ ዘርፍ ያለችው ደራሲ ሰአዳ መሀመድ ማናት?
ትውልድ እና ልጅነት
ሰአዳ መሐመድ
ኢብራሂም፡፡ ሀምሌ 5 1968 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ኮልፌ አካባቢ ተወለደች፡፡ ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ሰፈረ- ሰላም
የሕዝብ ትምህርት ቤት ፣ ከ5ኛ ክፍልእስከ 12ኛ ክፍል በአወሊያ አንደኛና መለስተኛ ትምህርት ቤት ተከታትላላች፡፡
በ1989 ዓ.ም
ለአንድ አመት በንግድ ስራ ኮሌጅ ስትከታተለው የነበረውን የአካውንቲንግ ትምህርቷን አቋርጣ “ማህደር የፈጠራ ጥበብና የሙያ
ት/ቤት” ገባች፡፡ በዚያም ለስድስት ወራት የጋዜጠኝነት ሙያ ስልጠናን ተከታተለች፡፡
ወደ ኪነት አለም
ወደ አረብ ሀገር
በመሄድ ለስድስት ወራት ያህል ከቆየች በኋላ ወደ ሀገር ቤት በመመለስ በምትወደው የስነ-ፅሑፍና ጋዜጠኝነት ሙያ ለመሰማራት
መንገዷን ጀመረች፡፡ ለተለያዩ የግል ጋዜጦች ፅሁፎችንና ግጥሞችን
በማቅረብ መሳተፍ ጀመረች፡፡ ኢትዮጵያ ሬድዮ ቅዳሜ ወጣቶች ላይ አጫጭር ጭውውቶችን ፅፋ ስታቀርብ ከቆየች በኋላ በኢትዮጵያ
ሬድዮ ለቅዳሜ ከሰአት የመዝናኛ ፕሮግራም ድራማዎችን ወደ መፃፍ ተሸጋገረች፡፡
የሬድዮ ድራማ ደራሲዋ ሰአዳ
በ1990/91
በኢትዮጵያ ሬድዮ የቅዳሜ ከሰአት እያንዳንዳቸው አራት አራት ክፍሎች ያሏቸው
“ ጥልፍልፎሽ ፣ መክሊት፣ ያበቃ ሕልም፣ ያልተደፈነ ጉድጓድ እና ሦሥቱ መስኮቶች” ድራማዎችን አቅርባለች፡፡ በጊዜው
ገና የ22 አመት ወጣት የነበረችው ሰአዳ በድራማዎቹ ጥሩ
ግብረ-መልስ አግኝታ ስለነበር ተበረታታች፡፡
ልቦለድ ደራሲዋ ሰአዳ
በ1992 ዓ.ም
በአረብ ሀገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ህይወት ላይ የሚያጠነጥን “እሾሀማ ወርቅ” የተሰኘውን ረጅም ልብ- ወለድ ድርሰት ለንባብ
አበቃች፡፡ ይህ ረጅም ልብ-ወለድ ስራዋ በኢትዮጵያ ሬድዮ ከመፅሐፍት አለም ፕሮግራም ከአንድ አመት በላይ ተተርኮላታል፡፡
ፋና ዴሞክራሲ ያሳትመው በነበረው ’እፎይታ ጋዜጣ’ በፍሪላንሰርነት
እየሰራች “እፍታ” በተሰኘውና ፋና ዴሞክራሲ በየአመቱ ያሳትመው
በነበረው የተለያዩ ደራሲያን ስራ ሰብስብ መፅሐፍ በቅፅ 3፣ ቅጽ 4 እና በቅፅ 5 ላይ “የባልቴቶቹ ልጆች እና ደባሎቼ”
የተሰኙ አጫጭር ልቦለዶችንና ግጥሞቿን ለንባብ አብቅታለች፡፡
ጋዜጠኛ ሰአዳ
1993 በየእለቱ
ይታተም በነበረው “ዕለታው አዲስ” ጋዜጣው ተጀምሮ እስከተዘጋበት
ጊዜ ድረስ በሪፖርተርነት ሰርታለች፡፡ ከ”ዕለታዊ አዲስ” ጋዜጣ መዘጋት በኋላ በ”ሩሕ” ጋዜጣ ፣ በ”አልነጃሺ” ጋዜጣ ፣
በ“አልዋህዳ” ጋዜጦች ላይ በተለያየ ጊዜ በአዘጋጅነት ሰርታለች፡፡
ድራማ ላይ አጠናክሮ መቀጠል
ሰአዳ መሐመድ
ከጋዜጠኝነቱ ጎን ለጎን የፅሁፍ ስራዋን በመቀጠል የሬድዮ ድራማዎችን መጻፏን ቀጠለች፡፡ ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ያሳትማቸው
በነበሩ የተለያዩ ደራሲያን የአጫጭር ልብ- ወለድ ስራዎች መድብል “የውድቅት ዕንባ እና ‹‹የስዕሉ ነፍሶች” የተሰኙ አጫጭር
ልቦለድ ስራዎቿ ለህትመት በቅተውላታል፡፡
“Blood Line”
በሚል ርዕስ ፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር በእንግሊዝኛ እንዲተረጎምና እንዲታተም ባደረገው የተለያዩ ደራሲያን በተሳተፉበት የአጫጭር
ልብ- ወለዶች መድብል ውስጥም አንድ ስራዋ ታትሞላታል፡፡
በሬድዮ ፋና ሰባት
ክፍሎች ያሉት “ የወንዝ ድንጋይ” የተሰኘ ተከታታይ ድራማ አቅርባለች፡፡ በኢትዮጵያ ሬድዮ የእሁድ ጠዋት መዝናኛ ፕሮግራም
ለአንድ አመት ያህል የተላለፈ 52 ክፍሎች ያሉት “የባቡ እግሮች” የተሰኘ ድራማን አቅርባለች፡፡
2001 ዓ.ም ጀምሮ
በፖፕሌሽን ሚድያ ሴንተር ይሰሩ በነበሩ ተከታታይ ሬድዮ ድራማ ድርሰቶች ከሌሎች ደራሲያን ጋር በመሆን መስራት ጀመረች፡፡
“ስብራት” 256 ክፍሎች ያሉት፣ “ምዕራፍ” 180 ክፍሎች ያሉት፣ “የረገቡ ፈትሎች” 140 ክፍሎች ያሉት እና “ብርሃን
አፅናፋት” 140 ክፍሎች ያሉት ድራማዎችን ከሌሎች ሁለት ደራሲያን ጋር በጋራ ሰርታለች፡፡
ከፖፕሌሽ ሚድያ
ሴንተር የድራማ ስራዎቿ ጎን ለጎን ከሁለት ደራሲያን ጋር “ የሕልም ጉዞ የተሰኘና 52 ክፍሎች ያሉት ደራማ ጽፋለች፡፡
“ቀጫጭን እግሮች” የተሰኘውና ለብቻዋ የፃፈችው ድራማ 12 ክፍሎች አሉት፡፡
“ዘመን” በተሰኘው
የቴሌቪዥን ድራማ እስከ 52ኛው ክፍል ድረስ የስደት ታሪኩን ከሁለት ደራሲያን ጋር ሰርታለች፡፡
በአፍሪካ ቲቪ
“መስጊዶች” የተሰኘ በመስጊዶች ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን ሳምንታዊ ፕሮግራም አዘጋጅታ ታቀርብ ነበር፡፡
ከ2005 – 2008
ድረስ “የኛ” የተሰኘውን የሬድዮ ድራማ ከሌሎች ሁለት ደራሲያን ጋር በመሆን ጽፋለች፡፡ የኛን በምትሰራበት ወቅትም ከአንድ ሌላ
ደራሲ ጋር በመሆን “የቤት ሥራ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማም ፅፋለች፡፡
“ደባሎቼ” በተሰኘ
ርዕስም አስር አጫጭር ልብ ወለድ ስራዎቿ የተካተቱበትን መፅሐፍ አሳትማለች፡፡
2009 ዓ.ም
ሁለቱም ኩላሊቶቿ ስራ በማቆማቸው ለከፍተኛ የጤና ችግር ተዳረገች፡፡ በህመም ላይ ሳለች ቤተሰቦቿ ጓደኞቿና የስራዋ አድናቂዎች
ባደረጉላት ከፍተኛ ርብርብ ከስምንት ወር የሕመም ስቃይ በኋላ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ለማድረግ ወደ ቱርክ አመራች፡፡ ከህክምና
ከተመለሰች በኋላ 2010 መጨረሻ ላይ “ንባብ ለህይወት - ኢትዮጵያ”
በየአመቱ በሚያዘጋጀው ሽልማት በሥነ-ፅሑፍ ዘርፍ ላበረከተችው አስተዋፅኦ የሕይወት ዘመን የወርቅ ብዕር ተሸላሚ
ሆነች፡፡
ሰአዳ መሀመድ
በአሁኑ ሰአት በፖፕሌሽን ሚዲያ ሴንተር ከሌሎች ደራሲያን ጋር በመሆን 156 ክፍሎች ያሉትን “ንቃቃት” የተሰኘ ተከታታይ
የሬድዮ ድራማ በመፃፍ ላይ ትገኛለች፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ