100. አይናለም ሀድራ -aynalem hadra
የዚህ ታሪክ አሰባሳቢ፣ ተወዳጅ ሚድያና ኮሚኒኬሽን በስነ-ጽሁፍ፣ በስነ-ስእል፣ በፊልም ፣
በቴአትር፣ በሬድዮ ድራማ ፤ በማስታወቂያ ዘርፍ ፤ በሚድያ ዘርፍ ከ1990ዎቹ ጀምሮ አስተዋጽኦ ያበረከቱና አሁንም በስራ ላይ
ያሉ ባለሙያዎችን ታሪክ በፌስ ቡክ ፤ በዊኪፒዲያ እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊ ሚድያዎች እያስተዋወቀ እንዳለ ይታወቃል፡፡ ውድ
ይህን ሀሳብ የምትደግፉ መስፈርቱን ያሟላሉ የምትሏቸው ሰዎች ጠቁሙን ፤ እርስዎም ታሪኬ መሰነድ አለበት ካሉ ይላኩልን፡፡
ከተቀመጠው መስፈርት አንጻር አይተን ታሪክዎን እናወጣለን፡፡
በtewedajemedia@gmail.com
ግለ-ታሪክዎን ይላኩ፡፡ ጥቅምት 14 2014 የ1000 ሰዎች ታሪክ ሲሞላ ድንቅ ታሪካዊ ምረቃ ይኖራል፡፡ ታሪካቸው አሁን
የሚሰራላቸው፤ ብዙዎቹ በወጣትነት አንዳንዶቹም በጉልምስና እድሜ ላይ የሚገኙ ሲሆኑ የዛሬ ጎልማሳ የነገ የሀገር ባለውለታ ነውና
ታሪካቸውን እየሰነድን ለትውልድ እናስቀምጣለን፡፡ ለወደፊቱም ምርምር ለሚያደርጉ እና ወይም የስራ ፕሮጀክቶቻቸውን ለሚደግፉ
ሰዎች ይጠቅማል ብለን እናምናለን፡፡ በ7 ዘርፎች ትልቅ ስራ ሰርተዋል ብለን ያመንባቸውን ሰዎች ታሪክ እናቀርባለን፡፡ ይህ
የማስተዋወቅ ስራ ውድድር ሳይሆን በሙያው የተለየ ሚና ያበረከተ ማንኛውም ሰው ታሪኩ የሚሰነድበት ነው፡፡ ጋን በጠጠር ይደገፋል
እንዲሉ ሙያቸውን በመደገፍ የራሳቸውን አሻራ ያኖሩ ሰዎች ታሪካቸው ይዘከራል፡፡ በሚድያ ዘርፍ ባለፉት 10 አመታት የራሳቸውን
አሻራ ካኖሩት መካከል አይናለም ሀድራ ማዕሩፍ ትጠቀሳለች፡፡
ውልደትና የትምህርት ሁኔታ
ዓይናለም ሃድራ
ማዕሩፍ ተወልዳ ያደገችው በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን በፍሬህይወት 1ኛ ደረጃ አጠናቅቃ ከሰባተኛ
ክፍል አንስቶ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቷን በኮኮበ ጽባህ 1ኛና ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተከታትላለች፡፡ ኋላም በኮተቤ ሜትሮፖሊታን
ዩኒቨርሲቲ በመግባት በዲፕሎማ የቋንቋ መምህርነት ስልጠና ወስዳለች፡፡ መንግስት በመደባት ትምህርት ቤት በማስተማር ላይ ሳለችም
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውጭ ቋንቋዎችና ስነ-ጽሁፍ ትምህርት ክፍልን ተቀላቅላ በመስኩ የመጀመሪያ ዲግሪዋን አግኝታለች፡፡
በተጨማሪም በጋዜጠኝነትና ኮምዩኒኬሽን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪ አግኝታለች፡፡ አዲስ አበባ የመጽሓፍ ቅዱስ
ኮሌጅ በመግባት አሜሪካ መቀመጫውን ካደረገው ግሎባል ዩኒቨርሲቲ በባይብልና ቲዎሎጂ ተመርቃለች፡፡ ታዲያ በተማረችባቸው በሶስቱም
መስኮች በከፍተኛ ማእረግ ነበር የተመረቀችው፡፡ባሁኑ ወቅት በቲዎሎጂ 2ተኛ ዲግሪዋን በመስራት ላይ ትገኛለች፡፡
አይናለም ዘና ብላ የምትከውነው ነገር ሲሆን እንደ ሆቢም
ታየዋለች፡፡ ለዚህም ነው መማር -መማር ደስ እያለኝ መማር ስትል የምትደመጠው
የሚድያ ዝንባሌ በልጅነት
አይናለም ለሚድያ
ያላት ዝንባሌ አሃዱ ብሎ የጀመረው የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለች ነበር፡፡ ያኔ ኮከበ-ጽባህ ተማሪ ቤት ውስጥ በክበባት ውስጥ
ንቁ ተሳትፎ ታደርግ የነበረችው አይናለም ይህን ማድረጓ ደስታን ይሰጣት ነበር ፡፡ በጸረ-ኤድስ ና በስነ-ጽሁፍ ክበባት ውስጥ
የጎላ እንቅስቃሴ ታደርግ የነበረችው አይናለም ከመምህራን ጋር የቀረበች ስለነበረች ገና በለጋነት እውቀትን መቅሰም ችላለች፡፡
ድራማዎችን ማቅረብ በእንግሊዝኛ የስነ-ጽሁፍ ስራዎችን ማቅረብ የአይናለም የልጅነት ትዝታዎች ነበሩ፡፡ ጭውውቶች እያዘጋጁ
ለተማሪ ቤቱ ማህበረሰብ ማቅረብ የእነ አይናለም የዘወትር ተግባር ነበር፡፡ አይናለም በዚህ ብቻ አትወሰንም፡፡ ለስፖርት ታላቅ
ፍቅር ስለነበራት ስፖርትም ላይ የነቃ ተሳትፎ አሳይታ ነበር፡፡ ከታላላቅ ምሁራን ጋር ሀገር ኣቀፍ መድረክ ላይ ሀሳብን
የመግለጽ ልምድን ያዳበረችው በ2ኛ ደረጃ ተማሪ ቤት በነበራት ቆይታ ነው፡፡ ፡ በእርሷ እምነት ተማሪ ቤቶች የሰዎችን መጻኢ
እድል በማመቻቸት ትልቅ ሚና አላቸው፡፡ የኮከበ ጽባህ ተማሪ ቤትም በእርሷ ላይ ያሳደረውን አዎንታዊ ተጽእኖ ዛሬ ድረስ አትረሳውም፡፡
በዛን ወቅት በትምህርቷ ጎበዝ የነበረችው አይናለም አንዳንዳድ ከበድ ያሉ ጥያቄዎችን መምህራን ሲጠይቁ ቶሎ በመመለስ በተማሪዎች
ዘንድ ትታወቅ ነበር፡፡ ቶሎ መመለሷ ብቻ ሳይሆን በድምጹዋም ተለይታ ትታወቅ ነበር፡፡ ሀሳቧን በግጥም ትገልጽ እንደነበርም
አይናለም ታስታውሳለች፡፡ ያኔ አይናለም ሀሳብን አብራርቶ የማስረዳት ልዩ ክህሎት ስለነበራት የሚድያ ሰው ልትሆን እንደምትችል
ብዙዎች ግምት አሳድረው ነበር፡፡ነገር ግን ያኔ ታዳጊ የነበረችው አይናለም ውስጡዋ የኪነ-ጥበብ እርሾ ቢኖርም ዶክተር ወይም
ፖለቲካል ሳይንስ የማጥናት ግብ ነበራት፡፡በተለይ አፍሪካዊነት የሚለው ሀሳብ ውስጡዋ ይብላላ ስለነበረ ፖለቲካል ሳይንስ አጥንታ
ይህን ህልሟን ለማሳካት ትፈልግ ነበር፡፡ በዚህ አጋጣሚ ጥሩ የሞራል ብርታት ይሰጡዋት ለነበሩት መምህራኖቿ ምስጋናን ማቅረብ
ትወዳለች፡፡
ንባብ በልጅነት እና መምህርነት
አይናለም በልጅነት
በርካታ የእንግሊዝኛ እና የአማርኛ መጽሀፍትን ታነብ ነበር፡፡ ደግሞ ካነበበች በኋላ ለሌሎች ማካፈል የዘወትር ልማዷ ነበር፡፡
ይህም ወደ መምህርነት እንድትገባ ያስቻላት ነበር፡፡
አይናለም ሃድራ
በመጀመሪያ እና በሁለተኛ ደረጃ እንዲሁም በመሰናዶ ትምህርት ቤቶች ከ5 አመታት በላይ አስተምራለች፡፡ በቆይታዋም በተለያዩ
ችግሮች ውስጥ የሚያልፉ ታዳጊ ሴቶችን በቅርብ የማግኘት እና ችግሮቻቸውን የመጋራት እድልንም አግኝታለች፡፡ ባላት እውቀትና
አቅም በመጠቀምም ሴቶች በራስ የመተማመን ብቃታቸው እንዲዳብር እና ከወንዶች እኩል ተወዳዳሪ እንዲሆኑ በማድረግ ስራዎች ላይ
ተሳትፋለች፡፡
ልደታ ክፍለ-ከተማ
ኮሚኒኬሽን ቢሮ
አይናለም ሀድራ
ማእሩፍ ፋና ከመግባቷ በፊት በልደታ ክፍለ ከተማ የሚታተሙ የህትመት ስራዎች ዋና አዘጋጅ በመሆን ሰርታለች፡፡ በጊዜው የህትመት
ውጤቶቹን የሌይ አውት ንድፍ ማውጣት መከታተል የጋዜጣ እና የመጽሄቶቹን ይዘት ለመቀየር በሚደረገው ጥረት ውስጥ የአይናለም
ድርሻ የጎላ ነበር፡፡
ፋና
በፋና ብሮድካስቲንግ
ኮርፖሬት በነበራት ቆይታም በርካታ የሬዲዮ ፕሮግራሞችን በማዘጋጀትና በማቅረብ ተሳትፋለች፡፡ ጥበባት፣ ተጓዥ ነቃሽ፣ ትውስታ፣
ገጠመኝና ማስታወሻ፣ ዶክመንታሪዎችና ዜና ጥንቅሮች ከሰራቻቸው ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በተጨማሪ ጆሮ ገቦቹ የፋና የቀጥታ ስርጭት
የዜና ሾዎች - 90 ደቂቃና 120 ደቂቃ ሲጀመሩ ጀምሮ ስታዘጋጅና ስታቀርብ ቆይታለች፡፡ በተለይ በግንቦት 2003 የፋና 90
ደቂቃ አንድ ተብሎ ሲጀመር አዘጋጅና አቅራቢ ከሆኑት መስራቾች አንዷ ነበረች፡፡ በተለይ የፋና 90 ደቂቃ የጠዋቱ በአድማጭ
ዘንድ ከፍተኛ ከበሬታ እንዲያገኝ የጣረችው አይናለም ዛሬ ድረስ አድማጮች በ90 ደቂቃ መሰናዶዋ ያስታውሷታል፡፡ አይናለም 90
ደቂቃ በተጀመረ ጊዜ ሆስት የማድረግ ሃላፊነት ሲሰጣት በደስታ እና በጽኑ ፍላጎት ነበር የተረከበችው፡፡ እናም ለ90 ደቂቃው
የሚሆኑ መረጃዎችን ቀድማ በማሰባሰብ ታደርገው የነበረውን ቅድመ-ዝግጅት በርካታ የሙያ ባልደረቦቿ የሚያስታውሱት ነው፡፡
አይናለም እንደ ነገ 90 ደቂቃ ትገባ ከሆነ ዛሬ መረጃዎችን በበቂ ሁኔታ ካጠናከረች በኋላ ዳግም ጠዋት ላይ ያሉ ትኩስ
ጉዳዮችን አስሳ ለማግኘት ጥረት ታደርግ ነበር፡፡ ለሬድዮ የሚመጥን ጆሮ ገብ ድምጽ ያላት በመሆኑም የእርሷ 90 ደቂቃ ይበልጥ
ይወደድ ነበር፡፡ የዚህ ትልቁ ሚስጥር ለተመደበችበት ስራ የምትሰጠው ፍቅር እና አክብሮት ነው፡፡ የዚህ ዊኪፒዲያ አሰናጆች
ከ10 አመት በፊት አይናለም በአቅራቢነት የሰራችባቸውን የ90 ደቂቃ የቀድሞ የቀጥታ ስርጭቶች እንዳደመጡት ከሆነ አይናለም
ሆስት ስታደርግ ሀይል ትጨምራለች፡፡ ለምትናገረው ጉዳይ ጥሩ ድምጸት ትቸረዋለች፡፡ የምትጠቀመውን ቃል አስባ ትመርጣለች፡፡
አድማጭም ሆነ የቅርብ የስራ ባልደረቦቿ 90 ደቂቃዋን የሚወዱት ራሷ ለምታቀርበው መሰናዶ ታላቅ ክብር የሰጠች በመሆኗ ነው፡፡
አይናለም በሆስቲንግ ብቻ አትወሰንም ፡፡ ዛሬ ድረስ ከአእምሮ የማይዘነጉ ቅንብሮችን አየር ላይ በማዋል ለሙያው ያላትን የጠለቀ
ክብር አሳይታለች፡፡ በ2003 ከሰራችው የ90ደቂቃ ቅንብሮች አንዱ ቁጥሮች ስለ ግድቡ ይህን ይናገራሉ ብላ ኢንጂነር ጌታሁን
መኩሪያን ቃለ-ምልልስ በማድረግ የሰራችው የማይዘነጋ ነው፡፡ የምድር ባቡር ታሪክ በኢትዮጵያ በሚል ርእስም ዘጋቢ ስራ ሰርታ
አየር ላይ አውላለች፡፡
አይናለም በቀጥታ
ዘገባም ሙያዊ ክህሎት ያላት መሆኑን በተግባር አስመስክራለች፡፡ የህዳሴ ግድብ በግንቦት 2003 የመሰረት ድንጋይ በተቀመጠ ጊዜ
ከባልደረባዋ ከደረጀ አያሌው ጋር በመሆን ቀጥታ ስርጭቱን በብቃት መርታለች፡፡ ይህም በታሪኳ ውስጥ ፍጹም የማትዘነጋው አጋጣሚ
ነበር፡፡ በ2004 ዩኒቨርሳል ፒስ ፌዴሬሽን የተባለ የኮሪያ ድርጅት አይናለምን ለሰራችው ስራ የሰላም አምባሳደር አድርጎ
ሾሞአት ነበር፡፡ ይህም በሙያዋ የበለጠ ገፍታ እንድትሄድ ያደረጋት ነበር፡፡ አይናለም ስለ ፋና ቆም ብላ ስታስብ ጋዜጠኝነትን
ከእነ ሙሉ ክብሩ የተማርኩበት ነው ስትል ትገልጻለች፡፡ ስትቀጠር በከፍተኛ ሪፖርተርነት ነበር ከ 2 አመት በኋላ አዘጋጅ
በመሆኑ ለተወሰኑ ወራትም ኤዲተር ሆና የጋዜጠኞችን ስራ የመከታተል እና ኤዲት የማድረግ ስራዎችን ትሰራ ነበር፡፡
‹የኛ› የራዲዮ ፕሮግራም
በ DFID እና
NIKE Foundation ድጋፍ ሲሰራ በቆየው ‹የኛ› የራዲዮ ፕሮግራም ከ ፕሮግራም ቀረጻው ጀምሮ በከተማና በገጠር ከተሞች
በተደረጉ ጥናቶች በቀጥታ ተሳትፋለች፡፡ ከጥናቱ አንስቶ የፕሮግራም ፎርማት ቀረጻ እና የጉዳዮች መረጣውንም ከባልደረቦቿ ጋር
አከናውናለች፡፡ በሌላ በኩል ለፕሮግራሙ አስፈላጊ ቃለ-መጠይቆችን የማድረግ፣ የኤዲቲንግ እና ፕሮግራሙን የማቅረብ(HOSTING)
ሃላፊነቷን ተወጥታለች፡፡ አይናለም በዚህ ፕሮጀክት ውስጥ የስራን ክቡርነት አይታለች፡፡ ትልቅ የሚባሉ ሰዎች ለስራው ክብር
በመስጠት ወርደው ሲሰሩ አይታለች፡፡ በዚህም ሙያን በጉጉት መስራት እንዲሁም በቡድን እንደ አንድ ሆኖ መስራት የሚያስገኘውን
ውጤት አስተውላለች፡፡ አይናለም ይህ የኛ ሬድዮ የተሰኘው ፕሮግራም ሲሰራ ገጠር ድረስ በመሄድ ብዙ እውነታዎችን አይታለች፡፡
ያለእድሜያቸው የተዳሩ፤ አስገድዶ መድፈር የደረሰባቸው ሴቶችን በማነጋገር ህይወታቸውን መካፈል ችላለች፡፡ እንዴት ነው ሴቶቹ
የሚኖሩት የሚለውን የተኙበት ላይ ተኝታ ፤ የበሉትን በልታ ከጥንካሬያቸው ተምራ አንድ ቁምነገርም ወስዳለች፡፡ አይናለም መደበኛ
ስራዋ አቅራቢ ሆስት ቢሆንም በሁሉም የቅንብር ስራዎች ሂደት ላይ በማለፍ የአቅሟን አበርክታለች፡፡ ሪሰርች መስራት ፤ ጥያቄዎች
ማውጣት የመሳሰሉትን ስራዎች በብቃት መልክ አስይዛ ስራዋ የተሳካ እንዲሆን ለማድረግ ሙከራ አድርጋለች፡፡ አይናለም ስለ የእኛ
ሬድዮ ስታነሳ ሰሎሜ ታደሰን ፤ አይዳ አሸናፊን እና ነቢዩ ተካልኝን ማመስገን ትፈልጋለች፡፡ እነዚህ በሳል ባለሙያዎች
የነበራቸው እውቀት በብዙዎች የተመሰከረ ስለነበረ ይህን ጥልቅ እውቀታቸውን ለማካፈል የማይሳሱ እንደነበሩ ታስታውሳለች፡፡
አይናለም፣ በዚህ አጋጣሚ ‹‹የእኛ ሬድዮ›› እንድትገባ ለየእኛዎች ጥቆማ ያደረገውን ረዳት ፕሮፌሰር መኩሪያ መካሻን ማመስገን
ትፈልጋለች፡፡
ከየኛ በኋላ……..
ሌላ ከስራ ባልደረባዋ ጋዜጠኛ ራህዋ ይፍጠር ጋር በመሆን በሸገር ኤፍኤም
102.1 የሚቀርበውን
‹ይመችሽ› የተሰኘ
የሬዲዮ ፕሮግራም በማዘጋጀትም በማቅረብም ስራ ተሳትፋለች፡፡ በዛው ጣቢያ ማያ የተሰኘ የሬዲዮ ኢንተርቴንመንት ፕሮግራም ፎርማት
በመቅረጽ አዘጋጅታ ታቀርብም (LIVE HOSTING) ነበር፡፡
ኋላም በብስራት ኤፍ
ኤም በማለዳና ምሽት የሚቀርቡ የዜና ሾዎችን አዘጋጅታ ታቀርብ ነበር፡፡ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ኤንቢሲ ኢትዮጲያ(NBC
ETHIOPIA) የተሰኘውን የቴሌቪዥን ጣቢያ ከምስረታው ጀምሮ በመቀላቀል በስራ አስኪያጅነት በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡አይናለም
እንደ NBC አይነት ለኢትዮጵያ የሚሰራ ጣቢያ ስታገኝ አላቅማማችም፡፡ በአዲስ ነገር መምጣት ስለምትፈልግ በአሁኑ ሰአት
የማኔጅመንትም አባል ሆና ጣቢያውን እየመራች ትገኛለች፡፡
የህይወት መርሆዎች
እምነት፣ትህትና፣
ፍቅር፣ ታማኝነት፣ ሃገር ወዳድነት ፣ ሰውን ማክበር፣ እጅግ ውጤታመሆን ከመርሆዎቿ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በጥቅሉ ቅዱሱ መጽሃፍ
ይሁን ያለውን ሁሉ ይሁን ባይ ነች፡፡ እንደ ስራ ሃላፊ ተግታ መስራትን የምትመርጥ፤ እንደ ሚስት በጣም ታማኝ፤ እንደ እናት
ራሷን እስከ መስጠት የምትደርስ አንደኛ እናትና ኩሩ ኢትዮጲያዊት ሴት ናት፤ ዓይናለም ሃድራ፡፡ እንደጋዜጠኛ ከሰው ጋር ያላት
ግንኙነት በመልካም መሰረት ላይ የተገነባ ሲሆን የሰው መውደድ የተቸረች በመሆኗም በቀላሉ ለመቅረብ አትከብድም፡፡ አይናለም
በጋዜጠኝነት ዘርፍ በአንድ ወቅት ልምዷን እንድታካፍል ከሌሎች ባልደረቦቿ በተጠየቀች ጊዜ ሙሉ ፈቃደኝነት በማሳየት እጅግ በጣም
ጥሩ ስልጠና ሰጥታለች፡፡ ሰዎችን እንደ ጓደኛ ቀርቦ የመምከር ፤ መንገድ የማሳየት ክህሎት ያላት አይናለም ተናግራ የማሳመን
መክራ አስተሳሰብን የማስቀየር ጉልበት አላት፡፡ ይህም አንዱ በሙያዋ ላይ ያኖረችው አሻራ ነው፡፡ አይናለም ከምንም በላይ
በእግዚአብሄር ያላት መታመን ለብዙዎች ያስደንቃል፡፡ በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ቀድማ በልጅነት የገባችው አይናለም
እግዚአብሄር ከልጅነት እስከ እውቀት አቅፎና ደግፎ አሳድጎኛል ብላ ታምናለች፡፡ አብረዋት በመንፈሳዊ አገልግሎት ውስጥ ያሉ
በግልጽ እንደሚመሰክሩት አይናለም ስለ እግዚአብሄር ማውራት ስለ ታላቅነቱ በታላቅ መደመም ውስጥ ገብታ መመስከር ዋና የህይወቷ
መርህ ነው፡፡ ለሰዎችም ስለ መንፈሳዊ ጉዳይ ስታካፍል እግዚአብሄርን ከሀይማኖት በዘለለ ማሰብ እንደሚያስፈልግ ትናገራለች፡፡
‹‹በብዙ ውጣ ውረድ ባልፍም ደጉ እግዚአብሄር አሁን ላይ አድርሶኛል.›› ይህ የፈጣሪ ደግነት፤ በጎነት አሁን ድረስ አብሮኝ
አለ ስትል አይናለም በዚህ አጋጣሚ ለእግዚአብሄር ምስጋናዋን አቅርባለች፡፡
ቤተሰባዊ ሁኔታ
አይናለም ሀድራ
ባለትዳርና የ 3 ልጆች እናት ስትሆን ወደፊት ከዚህ በላይ ሰርታ አገሯን የማገልገል ግብ ሰንቃለች፡፡ ኢትዮጲያኒዝም ዛሬም
በአለም ናኝቶ፤ ፓን አፍሪካኒዝም እንደ ቀደሙት አባቶቻችን ህልምና ናፍቆት እውን ሆኖ፤ አፍሪካ በእርግጥ አንድ ሆና፤ የአፍሪካ
ህዳሴን ማየት እንደ ኢትዮጲያዊት የምትናፍቀውና ለዚህም በሙያዋ የሚጠበቅባትን ለማድረግ ዓላማ ያላት የአፍሪካ ልጅ የኢትዮጲያ
ልጅ ናት፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ