
በላይ እለፋቸው ተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን በሚድያው ዘርፍ ላይ ከጋዜጠኛው ባልተናነሰ መልኩ ልዩ አሻራ ያኖሩ ባለሙያዎችን እያስተዋወቀ ፣ የህይወት ታሪካቸውንም እየሰነደ ይገኛል፡፡ በተለይ ስለ ሚድያ ስናነሳ የካሜራ ሰዎች ፣ የኤዲቲንግ ባለሙያዎች ለስራው ከግብ መድረስ የማይተካ ሚና አላቸው፡፡ አንድ ዘጋቢ ፊልም ሲሰራ ስራው በቡድን የሚሰራ ስለሆነ ከቡድን አባላቱ ውስጥ በካሜራ እና በኤዲቲንግ የጎላ ሚና ያላቸው ባለሙያዎች ሞቅ ባለ ሁኔታ ሊመሰገኑ ይገባል፡፡ አሁን በዚህ ጽሁፍ አማካይነት የህይወት ታሪካቸውን ከምንሰንድላቸው መካከል በላይ እለፋቸው ይጠቀሳል፡፡ በላይ ገና ወጣት ቢሆንም ባለፉት 10 አመታት በዘርፉ ላይ ታላቅ ትጋት ያሳየ በመሆኑ ለሌሎቸም አርአያ በመሆኑ የህይወት ታሪኩን እንደሚከተለው አሰናድተነዋል፡፡ ባንቺአየሁ አሰፋ እና እዝራ እጅጉ እንዲህ ያቀርቡታል፡፡ ትውልድ ልጅነት እና ትምህርት በላይ እናቱ ወ / ሮ ወርቅአለም ጸጋዬ ይባላሉ፡፡ አባቱ እለፋቸው ተፈራ ናቸው፡፡ መጋቢት 16 ቀን 1984 ዓ . ም በአዲስ አበባ ከተማ 24 ቀበሌ ነበር ተወልዶ ያደገዉ፡፡ አባቱ እለፋቸዉ ተፈራ ከጃንሆይ ጀምሮ በቤተመንግሥት ውስጥ ያገለገሉ ሰው ሲሆኑ እናቱ ወ / ሮ ወርቅአለም ጸጋዬ ደግሞ በጤና ተቋም ውስጥ የ ሂሳብ ባለሙያ ሆነው ከ 30 ዓመታት በላይ አገልግለዋ...