175. መሰለ መንግስቱ-
ህልሙን ያሳካ ታላቅ ሰው
ለሁለት አመታት ‹‹ስካይ ስፖርት›› የምትል ጋዜጣን ሲያሳትም የቆየ አንድ ጉጉ ወጣት፣ ወደ ሸገር ኤፍ ኤም ተሻግሮ በ102.1 አየር ሞገድ ድምፁን ሲያንቆረቁር፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ቃለ መጠይቅ አድርጎት በፊት ገፁ ምስሉን ይዞ ወጣ። በቃለ- መጠይቁ መሃል "የወደፊት ህልምህ ምንድን ነው?" የሚል ጥያቄ ተነሳለት፤ መለሰ፦"24 ሰዓት የሚሰራ የስፖርት ሬዲዮ ጣቢያ መክፈት"ከአመታት በኋላ አፍላው አንጋፋ ሁኖ ህልሙ ሰመረና በነሃሴ 2007 ዓ.ም በብስራት ኤፍ ኤም
101.1 በኩል "ኦያያያ... አስደናቂ ነበር" ሲል ተደመጠ። መሰለ መንግስቱ።
መሰለ መንግስቱ
እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ
ይህች በሁለት መስመር ግጥም ልክ ተሰፍታ የተቆረጠች ስንኝ ለዓመታት አየር ሞገድ አቆራርጦ በሬዲዮ ለሚደርሰን ቀጥታ የእግር ኳስ ስርጭት ስም ሁና አገልግላለች። እግር ኳስን ቀጥታ ሲያስተላልፍልን የምናውቀው መሰለ ጥሩ እግር ኳስ ተጫዋች እንደነበር ራሱም ይናገራል። ታምረኛ እግሩ ጎል ብቻ ሳይሆን ሚስትም እንዲያገባም አግዞታል።
በመጋቢት 5 ፣ 1958 ዓ.ም አዲስ አበባ "በቅሎ ቤት" በተባለ ሰፈር በኩል ነው ወደ እዚች ምድርብቅ ያለው። በአቶ መንግስቱ ገ/ስላሴ እና በወ/ሮ አቻምየለሽ መኩሪያ ቤት የነበረና ራሱ "ጣፋጭ" ሲል የሚገልፀውን ልጅነቱንም በዚያው በበቅሎ ቤት ነው ያሳለፈው። ንፋስ ስልክ ትምህርት ቤት እስከ 12ኛ ክፍል ያለ ትምህርቱን ተከታትሏል። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም ዘልቋል።
ወጣቱ መሰለ፣ እግር ኳስን በሬዲዮ ከማስመልከቱ ቀድሞ የቀበሌው የእግር ኳስ ቡድን አምበል ሁኖ ኳስ አንከባሏል። የኳስን ዳና ተከትሎ ሲሮጥ ከሚስቱ ደጅ ደርሷል። ባንድ ወቅት በቀጣይ ቀናት ላለበት ግጥሚያ ከቡድን አጋሮቹ ጋር ልምምድ ሲያደርግ ኳስ አርዝሞ የሰው ግቢ ያስገባል። 'የትም የላካትን ኳስ አምጣ' ተብሎ ተፈርዶበት ያንኳኳው በር ሲከፈት....
ከያኔዋ የልጅነት ፍቅረኛው ከአሁኗ የትዳር አጋሩ ጋር ተጋጠመ። ያኔ ያየውን ለ4 አስርታት ከተጠጉ አመታት በኋላም ሲገልፅ "ልክ የቀን 6 ሰዓት ፀሐይ ጨረር አይንን እንደሚወጋ የአይኗ ጨረር ወጋኝ" ብሎ ነው። ከዚያን ቀን ጀምሮ ኳሱ ገባም አልገባም በውሃ አጠጡን ሰበብ በር ማንኳኳቱ የዘወትር ስራው ሆነ። ሌላ ሰው ከከፈተለት ውሃውን ፀጉሩ ላይ አፍሶ ይሄዳል፤ እሷ የከፈተች ቀን ደገፍ ብሎ ይጨዋወታሉ።
11ኛ ክፍል ሲደርስ በረዘመችበት ኳስ ያውቃት ፍቅሩ ጋር ረዥሙን ትዳር አሃዱ ብሎ 5 ልጆችንና 10
የልጅ ልጆችን አፍርተዋል። ባለቤቱ ሁለተኛ ልጃቸውን ልትወለድ ተቃርባ በነበረ ሰዓት፣ ወደ ጣልያን ለማቅናት ዝግጅቱን አጠናቆ፣ በበቅሎ ቤት ወዳጆቹ ተሸኝቶ፣ ባለቤቱንም 'እኔ አልመለስም ልጆቹን ይዘሽ ሮም እንገናኝ' ካላት በኋላ በጊዜው በነበረ የገዥው መንግስት ርዕዮተ ዓለም ጉዞው ይስተጓጎልና ሳይሄድ ይቀራል። ይሄን 'የሮም እንገናኝ' ውጣ ውረድ በሁለተኛ ልጁ ስም የሮም መንግስቱ ብሎ ቀርፆ አስቀመጠው።
የወጣትነቱን ጀምበር በወጉ ሳይሞቃት በህይወቱ ለመጡ ልጆቹ ሲል ያልሰራው ስራ የለም። የቆዳና የአልሙንየም ፋብሪካዎች ውስጥ ላቡን ጠብ አርጓል፤ ካዛንችሽ እምብርቱ ላይ ሆቴል አቁሟል። ሆቴሉ በረንዳ ላይ ቁጭ ብሎ ራሱ እንደሚል 'የባሉካ ዱለት' እየበላ ከእግር ኳስ እኩል ወደሚወደው ጋዜጠኝነት በህትመት ሚዲያው በኩል ተገለጠ። ሮብ ጠዋት የምትታተም ‹‹ስካይ ስፖርት›› ጋዜጣን በባለቤትነትና በኤዲተርነት እያሳተመ 2 ዓመት ቆዬ። በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ ግለት ስለስቴዲየም ከሚያወሩ ጋዜጦች ይልቅ ስለአራት ኪሎ የሚዳስሱትን ተመራጭ አደረጋቸው። መሰለ ይህን ሁነት ለማስረዳት በተመሳሳይ ቀን የምትታተመውን ኢትኦጵ ጋዜጣ ከራሱ ስካይ ስፖርት ጋር ሲያነፃፅር
"ዝናብ ከመጣ ኢትኦጵ እንዳይመታ በስካይ ስፖርት ነበር የሚሸፍኑት" ይላል። ከዚህ በኋላ ነው ሸገር ኤፍ ኤም ሲመሰረት አመልክቶ ወደ ኤሌክትሮኒክስ ሚዲያ የተሻገረው። ሸገር በቆየባቸው 18 ቀናት ጥሩ ተቀባይነትን እንዳገኘ ያስታውሳል።
ከአንድ አመት ተኩል የሸገር ቆይታው በኋላ ወደ ሬዲዮ ፋና አቀና። በፋና 6 ዓመታትን ሲቆይ ተደማጭነቱንም ተወዳጅነቱንም ጨምሯል። ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ፋና ባሉት የክልል ኤፍ ኤሞች እየዞረ መላው ኢትዮጵያን እግር ኳስን በሬዲዮ እዩልኝ አለ፤ ህዝቡም ከፍ ባለ መውደድ ተቀበለው። ጎንደር ሲደርስ ሞተረኛን ጨምሮ በደመቀ አጀብ ሲቀበሉት "መሰለ ነው መለስ?"
አስባለ፤ ጅማ ሲዘልቅ የኦሮምያ ቴሌቭዥን አቀባበሉን በቀጥታ ስርጭት አስተላልፏል፤ ደሴ ሲሻገር ከፎንተኒና ጀምሮ በፍራፍሬ ምንጣፍ ተቀብሉት፤ ወደ መቀሌ ከፍ ሲል የባጃጅ አሽከርካሪዎች ማህበር በባጃጅ መቀሌን አስጎብኝተውታል።
የፋና ኤፍኤሞች የስርጭት አድማስ ሳይገድበው ከዱባይ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ ባሉበት፤ ከአሜሪካ የሰሜን አሜሪካ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ውድድር ላይ ተገኝቶ እግር ኳስን በሬዲዮ አስመልክቷል።
የመሰለ የበሰለ የቀጥታ እግር ኳስ ዘገባ የአድማጭ/ተመልካቾችን ብቻ ሳይሆን የትልልቅ ተቋማት አመራሮችንም ቀልብ መግዛት ችሏል። የአዋሽ ባንኩ ዋና ሰው አቶ ፀሃይ ሺፈራው፣ ራጉኤል አካባቢ ያለ የባንካቸው ቅርንጫፍ ከመከፈቱ ቀድሞ ዞር ዞር እያሉ ሲጎበኙ ከየኤሌክትሮኒክስ ቤቶች የሚውጣውን ድምፅ ልብ ይላሉ። እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ ኢትዮጵያውያን በያሉበት ሁሉ ሲደርስ መርካቶ ላይ ጎላ ብሎ ይሰማል።
"ኦያያያ" ሲል ደጋግመው የሰሙት መሰለን አስጠርተው፣ የአብረን እንስራ ጥያቄ አቅርበውለት ከ12 ዓመታት በላይ አብረው ዘልቀዋል።
በሸገርና በፋና ቤት ከደመቀ በኋላ አዲስ አድማስ ላይ የተናገረ ህልሙን ማማተር ሲጀምር የመገናኛ ብዙሃን ባለስልጣን ውድድር ያወጣል፤ ዓለምን ያካለለበት የእግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ ዝግጅትን እማኝ አድርጎ ተወዳድሮ አንደኛ ወጣ። አንደኛ ወጣና ህልሙን ብስራት ብሎ እውን አደረገ።
ይንበርበሩ ምትኬ፣ ጎርፍነህ ይመርና የገዛ እህቱን ባለቤት ደምሴ ዳምጤን እየሰማ በስራቸው እየተማረከ ያደገው ብላቴና፣ ስፖርትን ፍለጋ የነአዲስ ዘመንን የጀርባ ገፆች እያማተረ የከረመው ታዳጊ፣ የስፖርት ሬዲዮ ጣቢያ እከፍታለሁ ያለው አፍላው ህልመኛ... ህልሙ እውን ሁኖ ተወዳጁ ብስራት ኤፍ ኤም
101.1 ከኢትዮጵያውያን የኤፍ ኤም ጣቢያዎች እንደ አንዱ ተቆጠረ። ኤፍ ኤሙን በሁለት እግሩ እንዲቆም በማድረግ ልፋት ውስጥ እንቅልፍ የሚነሱ እንቅፋቶች ቢገጥሙትም በጽናት እንዳለፈው ይናገራል። ተደማጭ ፕሮግራሞችን ወደ ጣቢያው በማምጣትም የአየር ሰዓት ድልድሉን በመስራትም መሰለ እጁ አለበት። አይነ ስውራን "የጎደለውን የዓይናችንን ክፍል የሞላው መሰለ ነው" ካስባለው እግር ኳስን በሬዲዮ ተመልከቱ ዝግጅቱ አጠገብ "መሴ ሪዞርት"
በሚል የመዝናኛ ዝግጅቱም ሲገለጥ ግሩም እንደሆነ ሰምተናል።
አሁን ላይ ከ70 በላይ ሰራተኞችን ቀጥሮ፣ ለደመወዝ በወር ከ1 ሚሊየን ብር በላይ የሚያወጣ ተወዳጅ ጣቢያ ሁኗል። ከኤፍ ኤሙ በተጨማሪ ብስራት ቴሌቭዥንን ለሁለት አመታት ካየነው በኋላ ቢቋረጥም በቅርቡ መምጣታችን አይቀርም ለማለት ሲሞክር "ምጣዱን ማሟሸት ሳይሆን ማስማት ብቻ ነው የሚጠበቅብን" ይላል።
ጋዜጠኝነት እንዲከበር የበኩሉን ማድረጉን ይናገራል። የእግር ኳስ አዘጋገብም ሁለት ሶስት እርምጃዎችን ወደፊት እንዲራመድ አድርጓል። የተጫዋቾቹን መለያ ቁጥር እየጠሩ መዘገብን ፉርሽ አድርጎ በስማቸው እየጠራ፣ ታሪካቸውን እያጋራ አለፍም ሲል እየገጠመላቸው የአውሮፓ ጨዋታዎችን አስኮምኩሞናል። በርካቶች የእርሱን ፈለገ ሲከተሉ ሰምተናል፡፡
መዝጊያ ፤ ይህ መዝጊያ የተወዳጅ ሚድያ እና ኮሚኒኬሽን የመዝገበ-አእምሮ / ኢንሳይክሎ ፒዲያ ቦርድ አባላት አቋም
የሚንጸባረቅበት ነው፡፡
መሰለ መንግስቱ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የራሱን ትልቅ አሻራ ያስቀመጠ ነው፡፡
በተለይ በስፖርቱ መስክ ከ25 አመት በፊት የጀመረው ጥረት ፍሬ አፍርቶ ማየት ችሏል፡፡እግርኳስ በሬድዮ ማስመልከት የሚለው
ጽንሰ -ሀሳብ መልክ ይዞ እንዲጓዝ በማደረጉ መሰለ ለኢትዮጵያ የእግር ኳስ አፍቃርያን አንድ ትልቅ ውለታ ውሏል፡፡ መሰለ
መንግስቱ ከስፖርት ውጭ በተለያዩ ስራዎች ውስጥ በማለፉት ብዙ
አይነት ልምድ ለመቅሰም የቻለ ነው፡፡ መሰለ መንግስቱ እግር ኳስን በሬድዮን መጀመሩ ብቻ ሳይሆን ከ6 አመት በፊት
ብስራት ሬድዮን መመስረቱ ያስመሰግነዋል፡፡ ብስራት ሬድዮ ከስፖርት በዘለለ ለብዙዎች አቅም መውጣት ምክንያት የሆነ ጣቢያ
ነው፡፡ መሰለ ዛሬ በከፈተው ጣቢያ ለብዙዎቸ የስራ እድል
ተከፍቷል፡፡ ይህም ቀላል የሚባል ለውጥ አይደለም፡፡ ዛሬ
የአውሮፓ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን በሬድዮ በማስመልከት የራሱን ታላቅ
ጥረት እያደረገ ያለው መሰለ መንሱር አብዱልቀኒን ለመሰሉ ድንቅ የእግር ኳስ ተንታኞች እድል በመስጠት ለሙያው እድገት እየታገለ
ያለ ሰው ነው፡፡ መሰለ መንግስቱ ያለፈበት መንገድ እንደ ስራ ፈጣሪ በተለይ ደግሞ እንደ ሚድያ መስራች አስተዋጽኦው ትልቅ ነው፡፡
እንደ መሰለ አይነት ሰዎች ግለ-ታሪካቸው ተጽፎ ቢነበብ የሚያስተምሩት ብዙ ነገር አለ፡፡ መዝገበ-አእምሮ ለእንዲህ አይነት ሰዎች
ስፍራ አላት፡፡ አዲሱ ትውልድ ሊማር የሚችለው አቅሙን አውጥቶ ካሳየ ሰው ጋር ነውና የመሰለን ግለ-ታሪክ እነሆ ለአንባቢ አቅርበናል፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ